Thursday, August 17, 2017

ኢትዮጵያ፥ እግዚአብሔር በደህና ጊዜ የሸጣት አገር“የሃይማኖት አገር!” የሚለው አባባል ኢትዮጵያ ውስጥ ጊዜው ያለፈበትና የተበላ ተረት ሆኖዋል። አጥር ተሳልሞ የሚመለስ፣ ዕሮብና ዓርብ ራሱን ጥሉላት ከሆኑ የምግብ ዓይነቶች ከልክሎ ሲያበቃ ምላሱ የሰው አጥንት ስታደቅ ጸሐይ የምትጠልቅበት፣ ዛሬ ቅድስት አርሴማ ናት ነገ አቡነ ሐራ ነው እያለ ሲኖዶስ የማያውቃቸውን ስሞች እየጠራና ቀናት እየቆጠረ አብያተ ክርስቲያናትን የሚያሳድድ፤ መቼ ይሄ ብቻ - እሁድ በመጣ ቁጥር በክራባት ታንቆ ሲዘምርና “ሲያመልክ” እንደ ቦይንግ 767 ክንፉን ዘርግቶ የሚዘል፣ በቀን አምስት ጊዜ እየታጠበ ሶላት ለማድረስ ወደ መስጅድ የሚመላለስ፣ ቁጥር በክትባት መልክ በቀበሌ የተሰጠ ይመስል ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ቤተ እምነቶች የሚመላለስ ሃይማኖተኛ ዜጋ ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሯል።  
ኢትዮጵያ ውስጥ “ሃይማኖት አልባ” በተለምዶ “ከሃዲ” የሚባለውና በባህላችንም መሰረት በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የሌላው፣ በጋራ ተሰባስበው የሚወያዩበት “ማዕከል” ቀርቶ “ሃይማኖት አልባ/ከሃዲ” ግለሰብን (ሃይማኖት አልባ ግለሰብ የሞራል ኮምፓስ የለውም እያልኩ አይደለም። የ“ሃይማኖት አልባ” ዜጎች ቁጥር ማነስ  ቆጭቶኝም አይደለም) ወይም ሰውን በኩራዝም ቢሆን ፈልጎ ማግኘት ቀላል አይደለም። ቀለል ባለ አማርኛ - ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ሺህ ሰው እጅ ለመጨበጥ አጋጣሚውን ያገኙ እንደሆነ ከጨበጡት እጅ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኙ ከራሱ በላይ በሆነ “ፈጣሪ አለ” ብሎ በመለኮታዊ ሃይል “የሚያምን” ህዝብ ነው። በአንጻሩ ምድሪቱ ከሙስና የተነሳ እየተናጠች ሳይ ደግሞ - “ኢትዮጵያ፥ እግዚአብሔር በደህና ጊዜ የሸጣት አገር” አስብሎኛል።

Friday, July 7, 2017

የተሳሳተው ማን ነው? ብፁዕ አቡነ በርናባስ ወይስ የማህበረ ቅዱሳን ጆቢራዎች?በቅርቡ ታላቁ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ በአሜሪካ በታላቁ ካቴድራል በድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ በዕለተ ሰንበት የወንጌል ትምህርት በሚያስተምሩበት ሰዓት ብዙ ሊቃውንትና ካህናት እንዲሁም ምእመናን በተገኙበት እጅግ ደስ በሚልና ልብን በሚማርክ አቀራረብ ነገረ ድኅነትን /soteriology/ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገውና ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮውን ጠንቅቀው ለሕዝበ ክርስቲያን በሚገባ መልኩ ያስተማሩ ሲሆን ከትምህርቱም በኋላ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና ካህናት እንዲሁም በወቅቱ ትምህርቱን እስከ መጨረሻው በደንብ ሲከታተሉ የነበሩ ምእመናን ለብፁዕነታቸው ያላቸውን አክብሮትና በሰጡትም ትምህርት የተሰማቸውን ደስታ በሚገባ ሲገልጹ ነበር።


እኛም በዕለቱ በቦታው ላይ ስለነበርን ትምህርቱን በሚገባ  ስለ ተከታተልን እንዲህ ዓይነት ለወንጌል የጨከኑ እውነትን ሳይሸቃቅጡ ገልጸው የሚያስተምሩ አባት እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያናችን ስለ ሰጠን ከልባችን አመስግነናል ።

Tuesday, July 4, 2017

“እስመ አቡየ ወእምየ ገደፉኒ ወእግዚአብሔር ተወክፈኒ” (መዝ. 26፥10)ይህን መሪ ቃል መጥቀስ የተፈለገበት ምክንያት አለው፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት እየተባለ ቢጠራም እየተፈፀመበት ያለው ግፍ ሰሚና ተመልካች በማጣቱ፣ በችግሩ ሰለባዎች አንጻር ለቆመ ሰው ችግሩን ይህ መሪ ጥቅስ ሃይለ ቃል በመጠኑም ቢሆን ይገልፀዋል ተብሎ በመታሰቡ ነው፡፡ ይኸውም ንጉስ ዳዊት እንዳለውና የቤተክርስቲያን ሊቃውንት እንደሚተርኩት አንደምታ ዳዊት 26-27-1ዐ አባትና እናቴም ትተውኛል እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ ይላል፡፡
በአንድ አገር አንድ ንጉሥ ነበር ሕማመ ኮክሽ የሚባል ታመመ ይላል፡፡ በዚህ ንጉሥ ዙሪያ የነበሩ ጠንቋዮች አወቁ፣ መድሃኒት ፈልጉ ቢባሉ ከሰይጣን የሚገኘው መልስ ከድሮም ሰይጣን ነፍሰ ገዳይ ነውና (ዮሐ. 8፥44) ጠንቋዮች የሰጡት ወይም ያቀረቡት ሃሳብ ለእናት አባቱ አንድ የሆነ ልጅ አስመጥተህ እናቱ ይዛው አባቱ አርዶልህ በደሙ በፈርሱ ብትታጠብ ይሻልሃል ይሉታል። ንጉሥ የፈለገውን ማድረግ ይችላልና ንጉሥ ለእናት አባቱ ገንዘብ ከፍሎ በልጁ በምስኪኑ ደም ሊታጠብ አስመጣው። በእናቱ ያዥነት በአባቱ አራጅነት ተስማሙ፡፡ አባቱ ሊያርደው ሲል ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ቀና እያደረገ አስቸገረ፡፡ ምን ታያለህ? አሉት ጥንቱን ለልማዱ ለልጅ የሚያዝኑ አባት እናት ነበሩ እነርሱ ጨክነው ሊያርዱኝ ተስማሙ፡፡ ጩኸት ሰምቶ የሚያድነውና የሚፈርደው ንጉሥ ቢጨክንብኝ ወዴት አቤት ልበል አለ ይላል፡፡

Tuesday, June 27, 2017

«ውግዘቱን እንቃወማለን!!!»«የተወገዘ ሲኖዶስ ማውገዝ አይችልም!!»
ከሃያ ዓመታት በፊት ለሁለት የተከፈለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የመከፈሉ ዋነኛው ምክንያት የቀነኖ ጥሰት እንደ ነበር ሁላችን የምናውቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው። 


በቤተክርስቲያኒቱ ጥብቅ ቀኖና መሰረት አንድ ፓትርያርክ በህይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ መሾም ፍጹም የተወገዘና በእግዚአብሔር ፊት እርም የሆነ ግብር እንደ ሆነ በግልጽ ተቀምጦ ሳለ ኢትዮጵያ ያለው ሲኖዶስ ግን ለእግዚአብሔርና የቀደሙ አባቶቻችን ላስቀመጡልን መንፈሳዊ ቀኖና ከመገዛት ይልቅ ለመንግስት ፖለቲካ በመንበርከክ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ ታምራት ላይኔ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ሲኖዶሱ አራተኛውን የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ከአገር ተሰደው እንዲወጡ በማድረግ በእርሳቸው መንበር ላይ ሌላ ፓርያርክ አምስተኛ አድርጎ ሾሟል ይህ ፍጹም ሕገ ቤተክርስቲያንን እና ቀኖና ቤተክርስቲያንን የጣሰ አካሄድ አግባብ አለመሆኑን በብፁዓን አባቶችና በአገር ሽማግሌዎች ለሲኖዶሱ አባላት ቢገለጽላቸውም እግዚአብሔርን ባለመፍራትና ለሚመሩት መንጋ መከፋፈል ባለመጠንቀቅ በእምቢታቸው ስለ ጸኑ በስደት ላይ የሚገኘው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በማይፈታ ጽኑ ማሰሪያ ኢትዮጵያ የሚገኘውን ሲኖዶስ አውግዞታል በዚህ ከባድ ውግዘት ታስሮ ያለ ሲኖዶስ ከታሰረበት ውግዘት ሳይፈታ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በተለያየ ጊዜ ማህበረ ቅዱሳን ቀምሮ በሚያመጣለት የሐሰት የክስ ዶሴ በመመራት ጠርቶ ሳይጠይቅና ምላሻቸውን ሳይሰማ አውግዣለው እያለ የሚያውጀው ውግዘት ፍጹም የማይሰራና ተራ የሆነ ኢቀኖናዊ ውግዘት በመሆኑ «ወፈ ገዝት» ከመባል የዘለለ ቁም ነገር የሌለው ከንቱ ወሬ ነው። ወፈ- ገዝት በረባው ባልረባው ጉዳይ ላይ አውግዣለው የሚል የሰነፍ ካህን ማስፈራሪያና በስልጣነ ክህነት የዋሕ ክርስቲያኖችን ማስደንገጫ መሳሪያ ነው፤ አንዲት ወፍ ከዛፍ ዛፍ ስትበር መስቀል፡ እያወጣ ባለሽበት ቁሚ ገዝቼሻለው የማለት ያህል ነው።