Monday, January 10, 2011

የተደፈነ የውሃ ጉድጓድ (ዘፍ 26፥15-22)

ቤተ ክርስቲያን ወደ ቀደመ ክብሯ መመለስ ይኖርባታል የሚሉ ወገኖች (ተሃድሶዎች) ራዕይ በቀላል ቋንቋ ሲገለጽ፦

ሕይወት ላለው የፍጥረት ወገን እጅግ በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች መካከል ውሃ ግንባር ቀደሙ ነው። ሕይወት ያላቸው ፍጥረቶች ያለ ውሃ ህልውና አይኖራቸውም። በመሆኑም በአርአያ ሥላሴ የተፈጠሩ የሰው ልጆች ኑሮአቸውን ሁሉ የሚመሠርቱት ከውሃ ማግኘት ጋር በተያያዘ መንገድ ነው።


በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታላቁ የእምነት አባት አብርሃም ጌራራ በተባለው ስፍራ በስደት ሲኖር ለእርሱና ለቤተሰቡ እንዲሁም ለእንስሶቹ ፍጆታ የሚውል ውሃን ለማግኘት ሲል በዘመኑ ጥበብ (ዘዴ) ተጠቅሞ በጌራራ ሸለቆ ባስቆፈራቸው ጉድጓዶች ውስጥ በሚገኘው ንጹሕ ውሃ በዘመኑ አብርሃምና መላው ቤተሰቡ እንስሳቱም ጭምር ተጠቅመው ነበር። ታሪክ ተደገመና ከአብርሃም ሞት በሁዋላ ልጁ ይስሐቅም በራብ ምክንያት ተሰድዶ ወደ ጌራራ መጣ። በዚያ ሲኖር ግን ውሃን ለማግኘት ሌላ ዐዲስ የውሃ ጉድጓድ መቆፈር አላስፈለገውም። አባቱ አስቆፍሮ በተጠቀመባቸውና እርሱ ከሞት በሁዋላ ፍልስጥኤማውያኑ በደፈኑአቸው የውሃ ጉድጓዶች ለመጠቀም ወደደ። ምንም እንኳ በተለያዩ ቆሻሻ ነገሮች የተደፈኑትን የአባቱን የውሃ ጉድጓዶች እንደገና መቆፈር አሰልቺና እልህ አስጨራሽ ቢሆንም አባቱና ቤተሰቡ ከጠጡት ንጹሕ ውሃ ለመጠጣት ጽኑ ፍላጎት ያደረበት ይስሐቅ ይህን አድካሚ ሥራ ለመሥራት ታጥቆ ተነሣ። በተለያዩ ቆሻሻ ነገሮች ተደፍነው የኖሩትን ጉድጓዶችም እንደገና አስቆፈረና አብርሃም ይጠራቸው በነበረው ስም መልሶ ጠራቸው።

ከዚህ ሁሉ ድካም በሁዋላ ግን ይስሐቅን የገጠመው ችግር አሳዛኝ ነበር። ለብዙ ዘመናት በተለያዩ ቆሻሻዎች ተደፍነው የቆዩት የአብርሃም የውሃ ጉድጓዶች ዳግመኛ ተቆፍረው የአብርሃም ወገን የሆነ ሁሉ እንዲጠቀምባቸው የማይሹት ፍልስጥኤማውያን ሥራውን በመቃወም በጉድጓዶቹ ላይ የይገባናል ጥያቄ አቀረቡ። ይስሐቅም የአባቱን የውሃ ጉድጓዶች ቢፈልጋቸው እንኳ ከጠቡ ለመራቅ ሲል መተውና ሌላ መቆፈር ግድ ሆነበት።

የዚህ ትውልድ ዕጣ ፈንታም ከዚህ ያልተለየ ነው። ትውልዱ አባቶቹ የጠጡትንና መንፈሳቸው የረካበትን ንጹሕ ውሃ በእጅጉ ይፈልጋል። ከዘመናት ብዛትና ወራሽ ከመታጣቱ የተነሣ የአባቶች የንጹሕ ውሃ መገኛ ያ ጉድጓድ በተለያዩ ቆሻሻ ነገሮች ተደፈነ። የተደፈኑትን ጉድጓዶች እንደገና መቆፈር ለትውልዱ አሰልቺና እልህ አስጨራሽ ስለሚሆንበት፣ እንደገናም ቆሻሻውን ቆፍሮ ለማንሣት ደፋ ቀና ማለት ሲጀምር ጉድጓዱን ለደፈኑት ሰዎች ወገን የሚሆኑ ክፍሎች ስለሚከለክሉት የአባቶቹን ጉድጓድ ትቶ ሌላ ለመቆፈር ይገደዳል።

እግዚአብሔር ለቀደሙት የብሉይ ኪዳን አበው በነቢያቱ አፍ የተናገረውና ተስፋ የተገባለት ዘላለማዊ ዕቅዱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ማርያም ተወልዶ ስለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት ቤዛ ሆኖ በመሞቱና በመነሣቱ እውን ሆኗል። በዘመኑ ፍጻሜ ለድኅነታችን የተገለጸውን ይህን እውነት ጌታ ለቀደምት ደቀመዛሙርቱ፥ ደቀመዛሙርቱም በእነርሱ ፍለጋ ለተተኩት የቤተክርስቲያን አበው በትውፊት እያስተላለፉት ከዘመናችን ደርሷል። (2ጢሞ 2፥2) ሆኖም ተቀብሯል።

በዚህም ምክንያት በተለያዩ የፈጠራ ድርሰቶች ያልደፈረሰውን ንጹሕ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት አሁን ካለችው ቤተ ክርስቲያናችን ለማግኘት የማይቻል ሆኗል። ለዚህም ይመስላል ትውልዱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በተከታዮቹ ሐዋርያት የተሰበከውን ወንጌል በእጅጉ የሚሻው። በስም ጥንታዊቷ በተግባር ግን ዐዲሲቷ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስንና የሐዋርያቱን ትምህርት ቀብራ በዐዲስ ልብ ወለድ ትምህርቶች መሞላቷና የእግዚአብሔርን ክብር ለፍጡራን መስጠቷ ፍንትው ብሎ ስለሚታየው የልቡ ደርሶለት መሻቱን ሊፈጽም ባለመቻሉ ትውልዱ እናት ቤተ ክርስቲያኑን እየተወ ወደ ሌላው ለመሄድ ተገድዷል።

ለአንዳንዶች ዐዲስ ትምህርትሲባል አሁን በቅርብ የተገኘ ብቻ ይመስላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው እውነት ውጪ የሆነው ሁሉ ዐዲስ ትምህርት ነው። የትክክለኛው ትምህርት መለኪያ የዕድሜ መርዘም ወይም ማጠር ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ብቻ ነው። ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያልተመሰረቱ በመሆናቸው ዐዲስየሚሰኙ ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያናችን ሞልተዋል። ቢሆንም በወንጌል ከተሰበከው ውጪ የሆኑት ልዩ ልዩ ትምህርቶች በሐዋርያት ሥልጣንና ቃል የተወገዙ ናቸው። “….ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ። ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።“ (ገላ 1፥8-9)

ትውልዱ ግን ሊያስተውል የሚገባው ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ጉድጓዱ ውስጥ የተሞላውን ቆሻሻ ነገር ብቻ መሆን የለበትም። ቆሻሻው ቢነሣ ሊገኝ የሚችለውን ያንን ቀደምት አባቶቹ የጠጡትን ንፁሕ ውሃም ጭምር ነው እንጂ።


የተቀበረ መክሊት በሚል ርዕስ ዲ/ን አግዛቸው ተፈራ ከጻፈው መጽሐፍ የተወሰደ።

1 comment:

  1. WOW! great awesome insight. Kale hiwot yasemalin. Egziabher betekiristianachinin yitebklin. Amen

    ReplyDelete