Wednesday, January 19, 2011

የታቦት መባዛት ምስጢር

እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደፊተኞቹ አድርገህ ጥረብ። በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። (ዘጸ 34፥1)

ሙሴ አሥሩ ትእዛዛት የተጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ከተራራው ሲወርድ ሕዝበ እስራኤል የሙሴን መዘግየት ምክንያት አድርገው የእግዚአብሄርን ድንቅ ተአምራት ፈጥነው በመርሳት የጥጃ ምስል አቁመው ሲያመልኩት በተመለከተ ጊዜ በእጁ የነበሩትን ጽላቶች መስበሩ ይታወቃል። (ዘጸ 32፥19)

እንደገና ግን በሰበራቸው ምትክ ሁለት ጽላቶችን ጠርቦ እንዲያመጣና እግዚአብሔር ራሱ ሕጎቹን እንዲጽፍባቸው ነገረው። (ዘጸ 34፥1)

አሁን ቤተ ክርስቲያናችን አራብታ የምትገለገልባቸው የተለያዩ ጽላቶች (ታቦታት) አመጣጣቸው ከዚህ እንደሚጀምር የሚያስተምሩ አሉ። በመሆኑም ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን እንደፊተኞቹ አድርገህ ጥረብ የሚለው ትእዛዝ ጽላትን ሰው እንዲሰራና አሁን በቤተ ክርስቲያናችን እንደሚታየው በብዛት እንዲራባ አመላካች ነው ይላሉ።

ነገር ግን ይህ ትርጉም ተግባራዊ የሆነው የዘጸ 34፥1 ቃል ታቦትን ስለማራባት እንደሚገልጽ በሚታመንበት በኛ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በሌላ የእስራኤል ታሪክ ውስጥ ግን ተግባራዊ አልሆነም። እስራኤላውያን ከሙሴ ዘመን ጀምሮ እስከ ባቢሎን ምርኮ ድረስ የነበራቸው አንድ ቤተ መቅደስና ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን የያዘ አንድ ታቦት ብቻ ነው። ታቦትን ማራባት የታዘዘ ወይም የተፈቀደ ቢሆን በእስራኤል አውራጃዎች ሁሉ ቤተ መቅደሶችን እያነጹ ጽላቶችን እየቀረጹ ይጠቀሙ ነበር። ሌላው ቀርቶ ክብረ ነገስት በተሰኘው መጽሐፍ ወደ ኢትዮጵያ በሕጋዊ መንገድም ሆነ በስርቆት እንደመጣ የሚተረክለት ታቦታቸው ምትክ ሌላ ታቦት ሊሰሩ ይገባቸው ነበር። ሁሉም ግን አልሆነም። ለነገሩማ በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ በክብረ ነገሥት መጽሐፍ የተተረከለት ታቦት ከሰሎሞን ዘመነ መንግሥት በሁዋላ ብዙ ዓመታት ቆይቶ በ 16ኛው የይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ዘመን እዚያው ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ መታየቱ የክብረ ነገሥት ትረካ ተአማኒነትን እንዲያጣ ያደርገዋል። (2ዜና 35፥3)

ስለታቦቱ ከተነሣ ሳይዳሰስ የማይታለፍ ጉዳይ አለ። ታቦት የተሰጠው ለሕዝበ እስራኤል ብቻ ነው። የተሰጠበት ዓላማም እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ተገልጾ የእስራኤልን ልጆች በመሪዎቻጸው አማካኝነት ለማነጋገርና ረድኤትን ለመስጠት ነው። (ዘጸ 25፥22) እነዚህም ተግባሮች በታቦቱ አማካኝነት የታቦት አገልግሎት እስካበቃበት ጊዜ ድረስ ተከናውነዋል። (ዘኁ 7፥89፤ ኢያ 3፥8-17፤ 6፥6-21፤ መሳ 20፥27-28፤ 1ሳሙ 5፥1)

ታቦቱ በውስጡ በድንጋይ ጽላት ላይ የተቀረጹትን በእግዚአብሔርና በእስራኤል ልጆች መካከል ምስክር የሆኑትን ቃል ኪዳኖች ስለያዘ የቃል ኪዳኑ ታቦት እየተባለ ተጠርቷል። (ዘዳ 10፥8)

የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳኑን በማፍረሳቸው እግዚአብሔር ሌላ ዐዲስ ኪዳን እንደሚገባና ዐዲሱ ቃል ኪዳን ከብሉይ ቃል ኪዳን በተለየ መንገድ እንደሚሰጥ ተናገረ። (ኤር 31፥31-34)

የቀደመው ቃል ኪዳን ከሕዝቡ ሕይወት ውጪ በሆነ የድንጋይ ጽላት ተቀርጾ ነበር። በብዙ መንገድ ከውስጣዊ ሕይወታቸው የራቀ መሆኑ ደግሞ እነርሱ እንዳይፈጽሙት የሚያደርገው ተጽዕኖ ቀላል አልነበረም። ዐዲስ ኪዳን ግን ሕጉ ወደ ውስጣቸው የሚገባበት፥ የድንጋይ ጽላት በልብ ጽላት የሚተካበትና አገልግሎቱ በፊደል መሆኑ ቀርቶ በመንፈስ የሚከናወንበት በመሆኑ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ተምሮ እግዚአብሔርን የሚያውቅበት ኪዳን ነው። በዚህም ኪዳን እግዚአብሔር በደልንና ኃጢአትን ደግሜ አላስብም ሲል ቃል ኪዳን ገብቷል። (ዕብ 8፥6-13፤ 2ቆሮ 3፥3)

በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ ይላል እግዚአብሔር በዚያን ዘመን የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፤ ልብ አያደርጉትም፤ አያስቡትምም፤ አይሹትምም፤ ከእንግዲህ ወዲህም አዲደረግም። ተብሎ በኤርምያስ እንደተነገረው የእስራኤል ልጆች ከምርኮ ተመልሰው በአገራቸው መኖር ሲጀምሩ ዘሩባቤል ባነጻው ቤተ መቅደስ ውስጥ ታቦት ማኖር አላስፈለጋቸውም። እግዚአብሔር እንደተናገረው የአገልግሎቱ ዘመን አብቅቷልና። (ኤር 3፥16፤ ዕዝ 1፥9-11)

እግዚአብሔር እየደጋገመ በአጽንዖት የተናገረውን የኤር 3፥16ን ቃል ለውጠው ትንቢቱ የተነገረው ታቦቱ ወደ ኢትዮጵያ ስለመጣ ነው ለማለት የሚዳዳቸው ደፋሮችም አልታጡም።

አሁን በምንገኝበት ዘመን በዐዲስ ኪዳን የታቦቱ አገልግሎት በኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት ስለተተካ እግዚአብሔርን ለማነጋገርም ሆነ እርዳታውን ለመፈለግ ወደ ታቦት አንሄድም። ያኔ በታቦት ላይ ተገልጾ ሕዝቡን ያነጋግር የነበረው እግዚአብሔር አሁን ራሱን በአንድያ ልጁ በኩል ገልጾ አነጋግሮናል። (ዮሐ 1፥18፤ 14፥8-9፤ ቄላ 1፥15፤ ዕብ 1፥1-3) በልጁም ሁሉን ነገር እንዲያው ሰጥቶናል። (ሮሜ 8፥32፤ 6፦23፦ 5፥17)

ከዚህ እውነታ ተነስተው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የዐዲስ ኪዳን አማናዊ ታቦት ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑንና የታቦት ምሳሌነት በክርስቶስ መምጣት መፈጸሙን መስክረዋል። ኤፍሬም ሶርያዊው በውዳሴ ማርያም፦ ታቦት በወርቅ ልቡጥ እምኩለሄ ዘግቡር እምዕፅ ዘኢይነቅዝ ይትሜሰል ለነ ዘእግዚአብሔር ቃል ዘኮነ ሰብአ ዘእንበለ ፍልጠት ወኢውላጤ

ትርጓሜ፦ በውስጥና በውጭ በወርቅ የተለበጠ ታቦት ያለመለወጥና ያለመለየት ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይመስልልናል ሲል ቄርሎስም በበኩሉ ወእምድኅረዝ ኮነ ሰብአ ተሰምየ ብእሴ፥ ወመሲሐ፥ ወኢየሱስሃ፥ ወታቦተ፥ ወዐራቄ፥ ወበኩረ ለዘሰከቡ፥ ወበኩረ ለዘይትነሣእ እሙታን፥ ወርእሰ ሥጋሃ ለቤተ ክርስቲያን

ትርጓሜ፦ ሰው ከሆነ በሁዋላም በእሲ፥ የተቀባ፥ ኢየሱስ፥ ታቦት፥ አስታራቂ፥ ለሙታን በኩር፥ ከሙታን ወገን ለሚነሣም በኩር የቤተ ክርስቲያን ራስ ተባለ። (ሃይ አበ ም 81 ክፍል 51 ቁ 8)

በሙሉነህ ታዬ

2 comments:

  1. የታቦት መባዛት ምስጢር የተሰኘው ጽሑፍ የተወሰደው ከተቀበረ መክሊት ገጽ 106 ላይ ሆኖ ሳለ ምንጭ አለመጠቀሱ ጽሑፉን የአቶ ሙሉነህ ታዬ ያስመስለዋልና ምንጭ መጠቀስ አለበት፡፡

    ReplyDelete
  2. ይህን ብሎግ አይታችሁታል www.betepawlos.com አንብቤው ደስ ብሎኛል፡፡ እባካችሁ እስተዋውቁት፡፡

    ReplyDelete