Tuesday, January 4, 2011

ማህበረ ቅዱሳንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሻሻል አለባት የሚሉ ተሐድሶዎች።

ክፍል አንድ
ተሐድሶዎች እነማን ናቸው?
ብዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ስሄድ የስብከት ካሴት ሳዳምጥ፤ የተለያዩ ሥነ ጽሑፎችን ሳነብ ፡ተሐድሶዎች ተሐድስዎች፡ የሚል ጩኸት እሰማለሁ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥር የተቋቋመው ማህበረ ቅዱሳን የሚባለው ድርጅት አባላቱም ሆኑ አመራሮቹ ስለተሐድሶዎች  በስብከታቸው እና በጽሑፋቸው ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ሳያነሱ አያልፉም።
እኔም ተሐድሶዎችን ለማወቅ ብዙ ጥረት አድርጌአለሁ ምን ዓይነት አቋም እንዳላቸውና የት ዕንደሚገኙ፤ አላማቸው ምን እንደሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳወቅ ፈለግሁ እነርሱ ግን ተሃድሶ የሚለውን አይቀበሉትም እኔ ተሃድሶዎች ስል አንባቢ በሚገባው ቋንቋ ለመጠቀም እንዳሰብሁ ይረዳልኝ። ማህበረ ቅዱሳን የሚባለው ማህበርም ከተሐድሶዎች ጋር ያለውን ቅራኔ ለማቅረብ እሞክራለሁ አንባቢ የራሱን ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ እንዲሠጥ አንዳችም ሳልቀንስ እና ሳልጨምር ትክክለኛውን መረጃ ለማቅረብ እሞክራለሁ። መነሻየ ግን ከማህበረ ቅዱሳን እና ከተሐድሶዎች ሥነ ጽሑፎች ነው። የሁለቱንም ቡድን እንቅሥቃሴ በተከታታይ አቀርባለሁ መልካም ንባብ።
ተሐድሶ ማለት ይላሉ ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት የሚሉ ወገኖች ማደስ፣ መጠገን፣ ማጽዳት፣ ማለት ነው ይላሉ።ለምሳሌ ቤት ከተሠራ በኋላ ሳይታደስ ብዙ ከቆየ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሊፈርስ ይችላል ስለዚህ ከመፍረሱ በፊት የሚደርግለት እንክብካቤ ቤቱን ያጸናዋል። እንደሸረሪት ድር፤ የጢስ ጠቀርሻ ያሉ ነገሮችም ከቤቱ ላይ ሊጠረጉ ይገባል። ማደስ ማለት ማፍረስ አይደለም በቤቱ ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፤ ማስወገድ እና በፈረሰው በኩል መጠገን ነው በሌላ አነጋገር መሠረቱን ሳይነኩ እና ሳያናውጡ ጥንታዊነቱን እንደያዘ ቤቱን ማሳመር ማለት ነው።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ብዙ ዘመን ከመኖሯ የተነሣ ብዙ ስሕተቶች ይገኙባታልና መጽዳት አላባት ባህሉን ከሃይማኖቱ፤ ውሸቱን ከውነቱ፤ ክፉውን ከደጉ መለየት አለባት  የሚል ራእይ ያላቸውና ለዚህ ሌት ተቀን ያለ እረፍት የሚሠሩ ናቸው።
 የሚገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ጳጳሳት፤ ቀሳውስት፤ ዲያቆናት፤ መምህራን፤ የድጓ፤ የቅኔ የቅዳሴ መምህራን የሰንበት ተማሪዎች፤ እንዲሁም ምእመናን ሁሉ ያሉበት  ነው የታወቀ ማህበር ግን የላቸውም አንዳዶች ማህበር መሥርተዋል። ኑሮአቸው እና ሥራቸው በዚያው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሲሆን በተለያየ ቦታ ጽ/ቤት እና በርካታ ማሰልጠኛዎች አሏቸው። በርካታ መነኮሳት እና ሰባኪዎች በነዚህ ቦታዎች ይሰለጥናሉ። ይህን ሁሉ እንቅሥቃሴ የሚያደርጉት ግን ቤተ ክህነቱ ሳያውቅ ነው። ቀሳውስቱ ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ በየቤተክርስቲያናቸው ሌሎች ቀሳውስት በመመልመል ያሰለጥናሉ አንዳድ ጳጳሳትም ለዚሁ ሥራ የሚውል በግላቸው ከፍተኛ እርዳታ ያደርጋሉ። ተሐድሶዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ቁልፍ ቦታ አላቸው በተለይ በአሁኑ ሰዓት በየአብያተ ክርስቲያናቱ በብዛት ይገኛሉ። በገጠር አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እና በገዳማት ሁሉ አሉ። ደሞዛቸውን የሚያገኙት ከዚያው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ነው። ግን ከሌሎች የእምነት ድርጅቶችም እርዳታ ያገኛሉ ተብለው ይታማሉ። ተሐድሶዎች እራሳቸውን ተሃድሶ ብለው አይጠሩም  ስማቸው በሥራቸው ምክንያት የተሰጣቸው ነው። በቤተ ክርስቲያን ባሕላዊ ትምህርት ጥልቅ የሆነ ዕውቀት ያላቸው ስለሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተና ደካማ ጎንም ሆነ ጠንካራ ጎን ለይተው የሚያውቁ ሊቃውንት ናቸው። የተሃድሶዎች እንቅሥቃሴ ከባድ እንቅሥቃሴ ነው ምክንያቱም እስከሞት ድረስ የቆረጡ ሲሆኑ ታላቅ እራዕይ ያላቸው ናቸው።
የተሃድሶ እንቅሥቃሴ በኢትዮጵያ መቼ ተጀመረ?
የተሃድሶ እንቅሥቃሴ በኢትዮጵያ የቆየ ታሪክ አለው። በጣም ጎልቶ የወጣው ግን በአስራ አምስተኛው መቶ[1430] ክፈለ ዘመን ነው።
በአሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደቂቀ እስጢፋኖስ የሚባሉ ኃይለኛ የሃይማኖት ሰዎች ተነሥተው ነበር እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዘርዓ ያዕቆብ የሚካሄደውን አምልኮ፤ ባዕድ አምልኮ አለበትና ይህን ሁኔታ አንቀበልም ብለው ለማስወገድ የተነሡ ነበሩ።
 አባ እስጢፋኖስ የሚባሉት መነኩሴ በምሥራቅ ትግራይ በአጋሜ አውራጃ ስቡሐ በተባለ አውራጃ የተወለዱ ናቸው። አባታቸው በልጅነታቸው ስለሞቱ አጎታቸው አሳድገዋቸዋል። አባ ስጢፋኖስ በግና ፍየል በሚጠብቅበት ወቅት መንፈሳዊ ስሜት አደረበትና ያደገበትን መንደር ለቆ ቤተ ኢየሱስ በተባለች ሥፋራ መንፈሳዊ ትምህርቱን ጀመረ። ቤተ ሰባቸው ደግሞ ወታደር እንጂ ቄስ እንዲሆንላቸው ስለአልፈለጉ ከሄዱበት አመጧቸው እርሳቸው ግን  እንደገና ተመልሰው ለዲቁና የሚያበቃቸውን ትምህርት አጠናቀው በ18 ዓመታቸው ዲቁና ተቀበሉ። አባ ስጢፋኖስ ቤተ ሰባቸው ያወጣላቸው ስም ሀደገ አንበሳ ሲሆን መምህራቸው ግን ትጋታቸውን እና ትህትናቸውን አይተው እስጢፋኖስ ብለው ሰየሟቸው።
ከዚያም እናታቸው እርሳቸውን ለመዳር ስታወጣ ስታወርድ ባለችበት ሰዓት የሚከተለውን ቃል ተናግረው ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ሄደው ምንኩስናን ተቀበሉ።
አባ ስጢፋኖስ ለእናታቸው የተናገሩት“ አባቴ በልጅነቴ ስለሞተ እግዚአብሔር አባት እና እናት ሆኖ አሳደገኝ ስለዚህ ሰው ሁሉ ወልዶ ላሳደገው ይገዛል እኔም ከልጅነቴ ጀምሮ ወልዶ ላሳደገኝ ለእግዚአብሔር እራሴን ማስገዛት ስለምፈልግ ከዛሬ ጀምሮ እኔን ማየት አትችይም እራስሽን ለእግዚአብሔር አስገዢ በሰላም ኑሪ” የሚል ነበር።[ ከገድለ እስጢፋኖስ]
አባ ስጢፋኖስ ብሉያትን እና ሐዲሳትን ከተማሩ በኋላ ነገሮችን ሁሉ ማስተዋል ጀመሩ መምህሩንም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት “ ሃይማኖት መጻሕፍት እንደሚናገሩት ነው? ወይስ እደ ሰው ልማድ” የሚል ነበር። መምህሩም ሃይማኖትማ መጻሕፍት እንደሚሉት ነው ብለው ሲመሉስላቸው ታዲያ ይህ ሃይማኖት የሚመስል የሰው ልማድ ከሄት መጣ ብለው ሲጠይቁ ይህማ ከራሱ ከሰው የመጣ ነው ብለው መለሱላቸው። ከዚህ በኋላ አባ ስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ቃል ከሰው ልማድ እየለዩ ውሸቱን ከእውነቱ እያበጠሩ በማስተማር የራሳቸውን ደቀመዛሙርት ለብቻ ማደራጀት ጀመሩ ያስተማሯቸው ደቀ መዛሙርት በራሳቸው ወዝ ሠርተው እንዲበሉ እንጂ ከሰው እንዳይቀበሉ ሥራ እያስተማሯቸው አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት ከራሳቸው አልፈው ለሌላው ህዝብ መትረፍ ጀምረው ነበር።
በዚህ ጊዜ የራሳቸው ጓደኞች መነኮሳት ትምህርታቸው ከእኛ የተለየ ነው፤ ልማዳቸውም የኛን የሚቃወም ነው በማለት ይከሷቸው ጀመር።ይህንም ክስ በዘመናቸው ንጉሥ ለነበረው ለዘርዓ ያዕቆብ አቅርበውት ነበር።
ዘርዓ ያዕቆብ ከአጼ ዳዊት ቀጥሎ የነገሠ ሲሆን በልጅነቱ ግሸን ላይ ታሥሮ እንደኖረ ይነገርለታል ከዚያም ወደ ገዳም ገብቶ ከመነኮሰ በኋላ ምንኩስናውን ትቶ አግብቶ የነገሠ ሰው ነው።
ንጉሡ የተማረ ሰው ስለነበር ድርሰት መድረስ ዋና ሥራው ነበር። ከደረሳቸው ድርሰቶች ውስጥ
ታምረ ማርያም እና መጽሐፈ ብርሃን፤ የታወቁት ናቸው ማህሌተ ጽጌ እና መጽሐፈ ሰዓታት በርሱ ዘመን የተደረሱ ድርሰቶች ናቸው። በኢትዮጵያ በ30ው ቀናት ውስጥ  በርካታ በዓላት እንዲከበሩ አዋጅ ያወጀው አፄ ዘራዓ ያዕቆብ ነው የእመቤታችን 33 በዓላት እንደ እሑድ ሰንበት እንዲከበሩ፤ የመስቀል በዓል ብሔራዊ በአል ሆኖ እንዲከበር እና ስለ መስቀል ክብር የሚናገሩ ድርሰቶች እንዲደረሱ ያደረገው ዘርዓ ያዕቆብ ነው።
ለማርያም ስእል እና ለመስቀል[ለመስቀለኛ እንጨት] ስግደት እንዲደረግ አዋጅ ያወጣው ዘራዓ ያዕቆብ ነው።
አንድ ቀን ዘራዓ ያዕቆብ ታምረ ማርያምን ጽፎ ከአባ እስጢፋኖስ ገዳም በየሳምንቱ እሑድ እሑድ እንዲነበብ ከሚል ጥብቅ ትእዛዝ ጋር ይልከዋል። አባ እስጢፋኖስም መጽሐፉን በጥንቃቄ ካነበቡት በኋላ ይህ መጽሐፍ ከገዳማችን አይገባም መጸሐፉ ደቀ መዣሙረቴን የሚያሰንፍ ነው። ድንግል ማርያምንም አያከብርም በማርያም ስም የተነገረ ባዕድ ትምህርት ነውና አልቀበለውም ብለው መልሰው ላኩለት።
በዚህ ጊዜ ዘርዓ ያዕቆብ በመጀመሪያ ይሰማው ከነበረው ክስ ጋር የሚመሳሰል ነገር አገኘና እጅግ ተቆጥቶ እስጢፋኖስን አስጠራቸው። ደብረ ብርሃን ላይ ትልቅ ጉባኤ ተደረገ ሊቃውንት ምእመናን እና መነኮሳት ከየገዳሙ ተሰበሰቡ። አባስጢፋኖስ እና ደቀ መዛሙርቱ በአንድ በኩል ተቃዋሚዎች እና አፄ ዘራአ ያዕቆብ በሌላ በኩል ቆመው ክርክር ተደረገ።
አፄ ዘራዓ ያዕቆብ እና ተከታዮቹ የሚሉት፦
ለማርያም እና ለሥእሏ ስገዱ
ለመስቀል[ለመስቀለኛ እንጨት] ስገዱ
ለእኔም ለንጉሡ ስገዱ
ታምረ ማርያምን ተቀበሉ ነው
አባ እስጢፋኖስ እና ደቀመዛሙርቱ የሚሉት፦
“ኢንሰግድ ለባዕድ ዘእንበለ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” ትርጉም ለአብ ለወልድ እና ለምንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ለአራተኛ አካል አንሰግድም።
የሰው እጅ ለሠራው ለስእልም ሆነ ለመስቀለኛ እንጨት ባዕድ አምልኮ ስለሆነ አንሰግድም አሉ። በዚህ ጊዜ አባ እስጢፋኖስ ከባድ ግርፋት ከደረሰባቸው በኋላ ታስረው በነበረበት ቤት አረፉ።ደቀ መዛሙርቱም ለብቻ እምነታቸውን ቢጠየቁ አባታችን ካስተማረን ንቅንቅ አንልም አሉ። እጅግ ከተገረፉ በኋላ እስከ አንገታቸው የሚደርስ ጉድጓድ ተቆፍሮ  በዚያ ገብተው ፈረስ እና ከብት በጭንቅላታቸው ላይ ተነዳባቸው። ይህን ታሪክ  በታምረ ማርያም ም 12 ላይ እና በገድለ እስጢፋኖስ ማግኘት ይቻላል። በተለይም ፕሮፌሰር ጌታቸው በሕግ አምላክ በሚል ርእስ የደቂቀ ስጢፋኖስን ገድል ስለ ተረጎሙት እርሱን በማንበብ በቂ መረጃ ማግኘት ይቻላል።
ሌሎች ተደብቀው የቀሩት የአባ እስጢፋኖስ ደቀ መዛሙርት ከያሉበት እየተፈለጉ እጅ እና እግራቸውን ተቆረጡ፤ አፍንጫቸውን ተፎነኑ፤ ሴቶች ማህጸናቸውን በእሳት ተጠበሱ። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በፕሮፌሰር ጌታቸው መጽሐፍ ላይ በሰጡት አስተያየት በደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ሂትለር በአይሁድ ላይ ከፈጸመው ግፍ ጋር አመሳስለውታል።
ደቂቀ እስጢፋኖስ ደቅ እና ቆራጣ የሚባል በጣና ደሴት አካባቢ መታሰቢያ አላቸው በትግራይ ደግሞ ጉንዳጉዴ የሚባል ገዳም አላቸው ይህ ገዳም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚተዳደር ሲሆን ታምረ ማርያም ግን እስከ አሁን ድረስ አይነበብበትም።
ደቂቀ እስጢፋኖስ በቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ አሁን ድረስ እንደ መናፍቅ የሚወገዙ ሲሆን ምሥጢሩን የሚያውቁ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሰዎች ግን እንደ ሰማእታት እና እንደ ቅዱሳን ይቆጥሩአቸዋል።
ይህ የነ አባ እስጢፋኖስ እንቅሥቃሴ በጊዜው በነበረው የፖለቲካ የበላይነት ተዳፍኖ ቢቆይም ውስጥ ውስጡን ግን ሲሄድ እና ቀስ ብሎ ሲጓዝ የኖረ እንቅሥቃሴ ነው። ይህን ውስጣዊ እንቅሥቃሴ በርካታ ሊቃውንት በሥዉር ሲሳተፉበት ኖረዋል። ለምሳሌ ከነዚህ ሊቃውንት ውስጥ ጥቂቶች ከመጻሕፍቶቻቸው መረዳት እንደሚቻለው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤  አለቃ ታዬ፤ አለቃ ብላቴን ጌታ ሕሩይ፤ ፤ አለቃ ገብሩ ደስታ፤ ዘመንፈስ፤ የሚባሉ ሊቃውንት ሲሆኑ በደንብ ወደ አደባባይ ካወጡት እና ከቤተ ክርስቲያን ከተገለሉት የቅርብ ሊቃውንት ውስጥ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ እና ጓደኞቻቸው ይገኙባቸዋል። የአለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ ጓደኞች አሁንም በሕይወት ስለአሉ ስማቸውን መጽሐፍ አልፈለግሁም እነርሱም ስማቸው እንዲወጣ አይፈልጉም ዛሬም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በተለያዩ ሥራዎች ተመድበው ይገኛሉ። ከላይ ስማቸውን የጠቅስኋቸው ሰዎች የአባ እስጢፋኖስ ሐሳብ ነበራቸው።  ይህን ለማለት ያስቻለኝ አሁን ያሉት ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት የሚሉት ወገኖች ከሚያራምዱት አላማ ጋር መጻሕፍቶቻቸውን በማስታያየት እና የሕይወት ታሪካቸውን በማገናዘብ ነው።
የታሐድሶዎች ዓላማ ምንድን ነው?
ተሐድሶዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሻሻል አለባት ይላሉ። ራእያቸውም ቤተ ክርስቲያኒቱ በሐዋርያት እምነት ላይ የተመሠረተች በመሆኗ፤ የሐዋርያትን ትምህርት መከተል አለባት። አሁን የሚታዩት የሕዝብ ልማዶች እንደ ሃይማኖት ሆነው የሚታዩት ከዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ጀምረው በኃይል እና በፖለቲካ የበላይነት የተጫኑብን እንጂ እውነተኛው እና ጥንታዊው የኦርቶዶክስ እምነት አይደለም ባይ ናቸው። እውነተኛውን ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትንም ሆነ እምነትን የሸፈነ ልማድ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አለ። ይህን ቀስ በቀስ ሕዝብን በማስተማር መሰረቱን ሳያፈርሱ ውሸት የሆነውን ሁሉ እናስወግዳለን የሚል ራእይ አላቸው።
ተሐድሶ እንዲደረግ የሚፈልጉትም፦
1ኛ በአምልኮው ላይ 2ኛ በመጻሕፍቱ ላይ 3ኛ በአስተዳደሩ ላይ ተሐድሶ እንዲደረግ ይፈልጋሉ ለዚህም መጻሕፍቶቻቸውን ማንበብ ይቻላል በርካታ መጻሕፍት አሏቸው። በገድላት፣ በድርሳነ ሚካኤል እና በድርሳነ ገብርኤል በድርሳነ ኡራኤልም ላይ በጠቅላላ በድርሳንቱ እና በግድላቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ትችታቸውን ጽፈዋል ወደ ፊት እናቀርበዋለን።
በአስተዳደር ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ከማህብረ ቅዱሳን ጋር ተመሳሳይ ነው። አስተዳደሩ መንፈሳዊ ካልሆኑ ሰዎች ተላቆ በተማሩ እና ፈሪሃ እግዚአብሔር ባላቸው ሰዎች ይመራ ባይ ናቸው በአስተዳደሩ የሚፈጸሙ የዘረኝነት እና የሙስና አሠራርን አጥብቀው የሚቃወሙ ሲሆን በየቤተ ክርስቲያኑ በበዓል ቀን መንፈሳዊ ያልሆነ አሠራር እየተስፋፋ ነው ይህም የንግድ ሥራ እንጂ የእምነት ሥራ አይደለም በማለት አጥብቀው ይቃወማሉ። ጠንቋዮች በቤተ ክርስቲያኒቱ መታቀፍ የለባቸውም ጠንቋይ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ባዕድ አምልኮን በማስፋፋት ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ስለሚገኙ ይወገዱልን ባይ ናቸው በዚህ እረገድ ማህበረ ቅዱሳንም ጠንካራ አቋም አለው። ስለ ማህበረ ቅዱሳንና የቀረውን የተሐድሶ እንቅስቃሴ ታሪክ በሚቀጥለው አቀርባለሁ። ከኔ የቀረውን አንባቢ ቢያስተካክለው ደስ ይለኛል።

4 comments:

 1. Very interesting! look forward to the next part

  ReplyDelete
 2. wow it is very interesting

  ReplyDelete
 3. እውነት ባይሆንም ከሌሎች የተሻለ በመሆኑ እናመሰግናለን

  ReplyDelete
 4. @ fikr if it is not true why don't u write the truth?

  ReplyDelete