Friday, January 7, 2011

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥር ተመሥርተው እያገለግሉ ያሉ እና የነበሩ ጥንታዊ ማህበራት

በቤተ ክርስቲያን ማህበር ማቋቋም አሁን የመጣ ዕንግዳ ነገር አይደለም የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በማህበር ነበር የተመሠረተችው። አሁንም ማህበር ወይም ጉባኤ ናት  ማህበር ማለት የወንድሞች ኅብረት ማለት ነው። <<ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን>> እንዲል [ጸሎተ ሃይማኖት]
በአሁኗ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በፍቅር እና በሰላም የሚያገለግሉ የወጣቶች መንፈሳዊ ማህብራት ነበሩ እነዚህ ማህበራት የእርስ በርስ መነካከስ እንደዛሬዎቹ ማህብራት አልነበራቸውም። አንዳዶች በአሁኑ ጊዜ የሉም አንዳዶች እስከአሁን በሕይወት አሉ። እስኪ ጥቂቶችን ላስታውሳችሁ
1ኛ ሃይማኖተ አበው
ሃይማኖተ አበው እ.ኢ.አ.በ1950 ዓ.ም ግንቦት 24 “የኢትትትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር” ተብሎ በመሰየም በኮሌጅ ተማሬዎች ተመሠረተ። የበላይ ጠባቂው ግርማዊ ቀዳማዊ ኃ. ሥ. ሲሆኑ በወቅቱ እስከ ሁለት ሺህ[2000] የሚድርሱ ወጣቶች በአባልነት ተመዝግበው ነበር።
 የማህብሩ አላማ
የማህበሩ አላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እምነት ለወጣቱ ለማስተማር እና ቤተ ክርስቲያኒቱን በሚያስፈልጋት ሁሉ ለመደገፍ ነው።
የአደረጃጀቱ ሁኔታ
1ኛ ማህብሩ እራሱን የቻለ ጽፈት ቤት ነበረው።
2ኛ ወጣቱን ሥርአተ ቅዳሴ ለማስተማር በተስማሚ ሁኔታ አዘጋጅቷል
3ኛ በወር በወር የሚወጡ የአማርኛ እና የእንግሊዘኛ ጋዜጦች ነበሩት
4ኛ ሠራቶኞችን በሙሉ የሚያገናኝ በዓመት አንድ ጊዜ የሚደረግ ጠቅላላ ጉባኤ ያደርግ ነበር።
5ኛ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እሑድ እሑድ በየሳምንቱ ጉባኤ ያደርግ ነበር ይህ ጉባዔ በኋላ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ተዛውሮ ነበር።
ከሌሎች ጋር ያለው ግንኙነት
ማህበሩ በመላ ኢትዮጵያ ቅርንጫፎች የነበሩት ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም እውቅና ነበረው።
ለምሳሌ 1ኛ የዓለም ክርስቲያን ተማሪዎች ፌደሬሽን ተብሎ ከሚታወቀው ማህበር ጋር ከ1956 እ.ኢ.አ. ጀምሮ አባል ሆኖ ነበር።
2ኛ ከዓለም አባያተ ክርስቲያናት ድርጅትም ጋር ግንኙነት ነበረው በዚህም ብዙ ጊዜ የጉባኤው ተካፋይ ነበር።
3ኛ በአፍሪካ የክርስቲያን ተማሪዎች ፌዴሬሽን አባል ስለነበር በምስራቅ አፍሪካ ዝነኛው ማህበር ለመሆን በቅቷል።
4ኛ በአሜሪካ የፕሬስ ቤተ ክርስቲያን የዩንበርስቲ ተማሪዎች ጋር ግንኙነት ነበረው።
ሃይማኖተ አበው ከዓለም አብያተ ክርስቲያን ተማሪዎች ፌደሬሽን 4000 የአሜሪካን ዶላር ከኢትዮጵያ ኦ.ቤተ ክርስቲያን በሳምንት 20 ብር ያገኝ ነበር። ከሜሪካ ክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት የተሰጠችው አንድ ቦልስዋገን ነበረችው።ይህን ትልቅ እርምጃ የተራመደ ማህበር ዛሬ የት ገባ? አዎ ማህበሩ በሕይወት አለ ነገር ግን በማህበረ ቅዱሳን ከባድ እንቅሥቃሴ ምክንያት በቤተ ክህነቱ ተጽዕኖ ስለተደረገበት በዝምታ ተውጦ ይገኛል።
  2ኛ የተምሮ ማስተማር ማህበር
ይህ ማህበር በ1939 ዓ.ም እ.ኢ.አ. በተፈሪ መኮነን ተማሪዎች ተመሠረተ። በኋላ በ1949 ዓ.ም. የግርማዊት እትዬ መነን ተማሪዎችም ማህበሩን በመቀላቀል አባ ሃና ጅማ የሚባሉትን አባት አድርጎ <<ተምሮ ማስተማር>> የሚል ስም አውጥቶ  በምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ስብሰባ እያደረገ ሥራውን ጀመረ።
የማህበሩ አላማ
1ኛ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሚሆኑ ተተኪዎችን ማሰልጠን።
2ኛ  መሠረታዊ የሆነውን የኦርቶዶክስ ትምህርት ለወጣቱ ማስተማር።
3ኛ ድሆችን መርዳት እና መንከባከብ።
4ኛ የተጣሉትን ማስታረቅ ሰላምን ማወጅ የሚሉት ናቸው።
ማህብሩ ከኢትዮጵያ ሐዋርያዊ ድርጅት ጋር ጥብቅ ግንኙነት ነበረው።አሁንም ጥሩ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ቢሆንም በማህበረ ቅዱሳን እየተዋጠ መምጣቱ ይነገራል።
    3ኛ የወንጌል መልክተኞች እና የሰንበት ት/ቤት ማህበር
ይህ ማህበር በቅድስት  ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በ1942 ዓ.ም ተቋቋመ ይህን ማህብር የመሠረቱት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሰዎች ነበሩ። በኋላ ግን ተማሪዎችም ይመሩት ነበር።
የማህበሩ አላማ
ሕጻናትን ከልጅነታቸው ጀምሮ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖራቸው ፈሪሃ እግዚአብሔርን ለማስተማር የተቋቋመ ነበር።
ማህበሩ በተለያዩ ቦታዎች ለሚገኙ ማህበራት እና አባያተ ክርስቲያናት የሥእል እና የመጻሕፍት ሥጦታ በየጊዜው ያቀርብ ነበር። ይህ ማህበር በአሁኑ ሰዓት ሰንበት ትምህርት ቤት በመባል የሚታወቅ ሲሆን በማንኛውም አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ይገኛል።
    4ኛ ማህብረ ሐዋርያት ፍሬ ሃይማኖት
ይህ ማህበር በኤርትራ ዋና ከተማ በአስመራ  በ1942 ዓ.ም. ተመሰረተ።
የማህብሩ አላማ
1ኛ ካህናትን እያሰለጠነ ወንጌል ወደ አልደረሰበት ቦታ መላክ እና መጽሐፍ ቅዱስን ማሰራጨት የሚል ሲሆን
  የበሽተኞች መታከሚያ
  የሕጻናት ማሳደጊያ
  የሽማግሌዎች መጦሪያ የሚሆኑ ድርጅቶች ነበሩት።
ይህ ማህብር መጻሕፍትን በማሳተም ከሁሉም ማህበራት ከፍተኛውን ሥፍራ የያዘ ነበር ልዩ ልዩ የግእዝ መጻሕፍትን ወደ አማራኛ በመተርጎም ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል። ጋዜጦችንም በስፋት ያዘጋጅ ነበር። ይህ ማህበር የተመላላሽ እና የአዳሪ ትምህርት ቤቶች አቋቁሞ ነበር። ከነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል።
 1ኛ መርሃ ሕጻናት እስከ ስደስተኛ ክፍል የሚደርስ
 2ኛ ማህደረ ብርሃን ት/ቤት
3ኛ ደብረ ደናግል ት/ቤት
4ኛ ቀራንዮ ትምህርት ቤት ወዘተ...
በጠቅላላው በመላዋ ኤርትራ 24 ትምህርት ቤቶችን ለማቋቋም የቻለ ጠንካራ ማህበር ነበር። አሁን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም።
ሌሎች ትናንሽ ማህበራት
አንቀጸ ብርሃን በቀዳማዊ ኃ. ሥ. 2ኛ ደርጃ ትምህርት ቤት።
መርሐ ጽድቅ በጅማ
ብርሃነ ሕይወት በሲዳሞ
ብርሃነ ወንጌል በአሩሲ
ከሣቴ ብርሃን በሐረር
ኆኅተ ሃይማኖት በናዝሬት
እነዚህ ሁሉ ማህብራት በአሁኑ ሰዓት እውቅና ስሌላቸው ስማቸው በየቦታው ተወስዶ ሌላ ማህበር ተመሥርቶባቸዋል።
ወደ ፊት በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ምን ያህል ማህበራት እንዳሉ እና አላማቸውስ ምን እንደሆነ የነጋዴዎችን ማህበር እና እውነተኛ ሥራ የሚሠሩ ማህበራትን እንጠቁማለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

1 comment: