Wednesday, February 16, 2011

የቃል ኪዳኑ ታቦት እና ሰሎሞናዊው ሥርወ መንግሥት

ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል እየተባለ የሚነገርለት የቃል ኪዳኑ ታቦት ብዙ ጥያቄዎችን እየፈጠረ ያለ ነገር ነው። በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ሰዓት ታቦት ተብሎ የሚጠራው እግዚአብሔር ለሙሴ ከሰጠው ታቦት ጋር በይዘትም ሆነ በአሠራር ተመሳሳይ ባለመሆኑ የሁለቱንም ልዩነት ይዘት እና አሠራር በማቅረብ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ጉባኤ ወይም እኔ አውቃለሁ የሚል መምህር ሁሉ መልስ እንዲሰጥበት ትክክለኛውን መልስ የማይሰጥ ከሆነ ሕዝብን ከማደናገር እንድንቆጠብ ይህን ለመጻፍ ወደድን።

Saturday, February 12, 2011

ተክለ ሃይማኖት የነፍሳችን መዳኛ

ከዚህ ቀደም እንደጠቆምነው የገድል ጽሑፍ ውርርስ በመኖሩ አንደኛው ከአንደኛው ለመበላለጥ እግዚአብሔርን ክርስቶስንና መንፈስ ቅዱስን አልፎ አልፎ በመጥቀስ እንዲሁም ተክለ ሃይማኖት የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው በማለት የሚናገሩ ቃላቶች አሉበት። ይህም መጽሐፉ ተቀባይነት እንዲያገኝ ሲባል በዘዴኞች የተደረገ ጥበብ ነው።

Wednesday, February 9, 2011

ገለባ ውስጥ የተደበቁትን ሁሉ ትንሽ እሳት ያስፈራቸዋል

ከፍርሐት፣ ከሥጋትና ከጭንቀት ነጻ ሆነው የሰላም እንቅልፍ ተኝተው ማደር የሚችሉት እውነትን የያዙና የሰው ደም የሌለባቸው ንጹሐን ብቻ ናቸው። ቃኤል ወንድሙን አቤልን ያለምንም ምክንያት ከገደለ ጀምሮ ፈሪና ተቅበዝባዥ ሆኖ ትንሽ ኮሽታ ሲያስደነግጠው የኖረ ሰው ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የአቤል ደም ወደ እግዚአብሔር በመጮኹ ነበር። ዘፍ 3፡10። የጻድቅ ደም እንቅልፍ አያስተኛም።

Saturday, February 5, 2011

የተክለ ሃይማኖት ተቅማጥ - የደፋሩና የከሐዲው ጸሐፊ ጉድ

ብዙ ሰዎች የገድላ ገድል ጸሐፊዎችን በጅምላ ሲፈርጁ መጻሕፍትን መረዳት የተሳናቸው አላዋቂዎች ናቸው በማለት ይናገራሉ። በእርግጥ ጥቂቶች እንዲህ ቢሆኑም አብዛኞች ግን ስሕተተኞች ብቻ ሳይሆኑ ደፋሮች ከሃዲዎችና የሰይጣን አጋፋሪዎች ናቸው ለማለት እንደፍራለን።ሰዎቹ ሆን ብለው በእግዚአብሔር የዘላለም እቅድ ላይ አይቻላቸውም እንጂ ቢሆንላቸው ማጥፋት ካልሆነም ሕዝብን በማሳሳት የሰይጣንን ድርሻ ማበራከት ተሰጥተው የተነሱበት ዓላማቸው ነው። ስለሆነም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በክርስቶስ የመስቀል መከራ ላይ በጠላትነት መነሳት፤ ክቡር ደሙን ማክፋፋት፤ ቅዱስ ሥጋውን ማራከስ፤ ስመ ክርስቶስን ማስካድ፤ ከሕዝቡ ኅሊና ማስረሳት በፈጠራና በአጋንንታዊ ትምህርቶች የሕዝቡን ኅሊና መያዝ ዋና ዋና መንገዳቸው ነው።

ደፋሮችና ከሐዲ የሆኑት እነዚህ ጸሐፊዎች በአንዱ በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ወደ ዓለም ገብቶ የነበረውን ኃጢአት ለማስወገድ እግዚአብሔር ይበጃል ያለውን አንድ ልጁ ክርስቶስ በደሙ ፈሳሽነት ያደረገውን ሥርየት ዋጋ ለማሳጣት በገድለ ተክለ ሃይማኖት /ምዕራፍ 54፥23/ ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል።

ወናሁ ትመውት በሕማመ ብድብድ በእኩይ ሞት ወእሬሲ ለክ ኪያሃ ከመ ስቅለትየ ወከመ ደመ ሰማዕት እለ እምቅድሜከ አኮ ለባሕቲትከ አላ ደቂቂ ከኒ እለ ይወውቱ በሕማመ ብድብድ በውስተ ዛቲ ገዳም እኃልቆሙ ምስለ ሰማዕታት ወአወፍዮሙ ለከ በመንግሥተ ሰማያት

ትርጉም፦ እነሆ በክፉ ሞት በተቅማጥ ትሞታለህ፣ እሷንም እንደ ስቅለቴና ከአንተ በፊት እንደነበሩት ሰማዕታት ደም እቆጥርልሃለሁ ነገር ግን ለብቻህ አይደለም በዚች ገዳም በተቅማጥ በሽታ የሚሞቱትን ልጆችህንም ቁጥራቸውን ከሰማዕታት ጋራ አደርጋለሁ በመንግሥተ ሰማያትም ለአንተ እሰጣቸዋለሁ ብለዋል።

ይህን የምታነቡ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላችሁ ወገኖቻችን እንዲህ ያለ የተረገመ ጽሑፍ ያለበትን መጽሐፍ ይህ የዋህ ሕዝብ ለበረከት እንዲሳለመውና ሰውነቱን እንዲያሻሽበት እየተባለ ተሰውሮ ባላወቀው መንገድ ከመርገም ሥር እንዲወድቅ መደረጉን በማሰብ ከእንባ ጋር መጸለይን እንዳትረሱ አደራችን ታላቅ ነው።

ከቅዱስ አምላካችን ለይቶን የነበረውን ኃጢአት የቅዱሳን ሰዎች እንባ ጾምና ጸሎት ባለመቻሉ ሁሉ በእርሱ ዘንድ የሚቻል አምላክ በተወደደ ልጁ ደም ኃጢአታችንን እንዳነጻው ሐዋርያቱ አስረግጠው ጽፈውልናል። ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሲገልጽ ከአባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከከንቱ ኑሮአችሁ በሚያልፍ ነገር በብር ወይም በወርቅ ሳይሆን ነውርና እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክቡር በክርስቶስ ደም እንደተዋጃችሁ ታውቃላችሁ ሲል ቅዱስ ጳውሎስም የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ፣ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፣ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችሁዋል? በማለት ለዚህ ደም ክብር እንድንሰጥ ጽፎልናል።

ይህን ታላቅና የከበረ የክርስቶስ ደም ነው ጸሐፊዎቹ ከአንድ ተራ ሰው ተቅማጥ ጋር እኩል አድርገው ተቅማጥህ እንደ ስቅለቴ ደም ነው ብሎታል በማለት የሚናገሩት። ዐርብ ዕለት ከፈሰሰው ለዓለም ኃጢአት ማስተስረያ ከፈሰሰው የጌታ ደም ጋር አስተካክለው ያስተማሩት። ምዕመናን በክርስቶስ ደም መፍሰስ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ከማስተማር ይልቅ እንደ ተክለ ሃይማኖት በተቅማጥ የሞተ ሁሉ ተክለ ሃይማኖት ገቡበት ወደ ሚሉት እንደሚገቡ በገድሉ ላይ አስቀምጠዋል።

በዚህ ገዳም (በተክለ ሃይማኖት) በተቅማጥ በሽታ (አሜባ) የሚሞቱ ባንተ የታመኑ ልጆችህ ሁሉ ቁጥራቸውን ከጻድቃንና ከሰማዕታት ጋር አደርጋለሁ በመንግስተ ሰማያትም ለአንተ እሰጣቸዋለሁ ብሎ ጌታ ቃል ገብቶለታል በማለት ጽድቅ በተቅማጥ በሽታ ነው ይሉናል።

እንደ ገድለ ተክለ ሃይማኖት ደራሲ አባባል በተገባላቸው ቃል ኪዳን መሠረት በአባ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የነበሩ ሰዎች ሁሉ በተቅማጥ በሽታ ወዲያዉኑ ተያዙ (54፥27) ይህ በሽታ የጽድቅ ቃል ኪዳን ስለሆነ በምዕራፍ 54 ቁጥር 30 ላይ የተቅማጥ በሽታ አምጪ የሆነችውን ተኅዋስ ተክለ ሃይማኖት እንዲህ አሏት፦ ጻድቁን እንጂ ኃጥኡን አትንኪ አላት በማለት በተቅማጥ የተያዙት ሁሉ ጻድቃን ነበሩ በማለት ጽፏል። ይህን የተረገመ የአጋንንት ትምህርት ሰዎች ሁሉ በማወቅና በመንቃት የክርስቶስን ደም ከማክፋፋትና የባሰ ቅጣት ከመቀበል እንድን ዘንድ ጽፈናል። ይቀጥላል ….

ይህንን ጽሑፍ የማቅረባችን ዓላማ፦ 1ኛ) ይህንን ጉድ ህዝብ እንዲያውቀው እና ባለማወቅ የዚህ ወንጀል (ክህደት) ሰለባ እንዳይሆኑ ለመጠቆም 2ኛ) ይህ በአንዳንድ የሰይጣን አጋፋሪዎች የተጻፈና ሳይታወቅ ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሰርጎ የገባ ጉድ መሆኑን አንባቢ ተረድቶ ወደ ትክክለኛው የእግዚአብሔር ቃል እና ትእዛዝ እንዲመጣ ለመርዳት። 3ኛ) እዚህ ላይ ለመጠቆም የሞከርነው ክህደት ወደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ሳይታወቅ ሰርጎ ይግባ እንጂ የአሁኖችም ሆነ ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት አይቀበሉትም። ይህን እና የመሳሰሉ የክህደት ጽሑፎች ከቤተ ክርስቲያናችን ጠርጎ ለማስወጣት ሊቃውንት በጥረት ላይ ናቸው። ሆኖም ግን ማህበረ ቅዱሳን ተብሎ የሚጠራው ማህበር ምንም መነካት የለበትም፤ ሁሉም ነገር ጥርት ያለ ነው በሚል ጭፍን እና አዋቂነት የጎደለው አቋም እንዲህ አይነቱ ክህደት እንዲታረም የሚሞክሩ ወይም አስተያየት የሚሰጡትን የቤተክርስቲያን ልጆች ፕሮቴስታንት ወዘተ በሚል ያለቅጥ በተጋነነ የስም ማጥፊያ ፕሮፓጋንዳ ይዘምትባቸዋል። ለጊዜው ግን ኦርቶዶክሳዊ ወገናችን ይህንን እንዲረዳ ወደድን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ሙሉ ሰው

Friday, February 4, 2011

ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት - በሌላ እይታ

 
አቡነ ተክለኃይማኖት ቡልጋ ደብረ ጽላልሽ ወይም ዞረሬ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የሰበካ ክልል ከአባታቸው ከካህኑ ቅዱስ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ቅድስት እግዚእ ኃረያ መጋቢት መጋቢት 24 ቀን ተፀንሰው፤ በ1196 ዓ.ም ታሕሣሥ 24 ቀን ተወለዱ፡፡ በተወለዱ በሦስት ቀናቸው ከእናታቸው እቅፍ ወርደው «አሐዱ አብ ቅዱስ፣አሐዱ ወልድ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ» ብለው ሥላሴን አመስግነዋል፡፡ ወላጆቻቸውም ፍስሐ ጽዮን አሏቸው፡፡ ትርጓሜውም የጽዮን ተድላዋ ወይም ደስታዋ ማለት ነው፡፡