Tuesday, March 29, 2011

ስለ ሰዎች ልጆች ፍቅር የተሰቀለው መርቆሬዎስ ነው - Read PDF

ዚቅን ጽፈውታል የሚባሉት ሰዎች ሲያነቡ የተሳሳቱ አልያም የትምህርት ማነስ ምክንያት ሆኖ መንፈሳዊ ነገር ያልገባቸው ሳይሆኑ ሆን ተብሎ የእግዚአብሔርን ክብር፤ የእግዚአብሔርን ምስጋናና የእግዚአብሔርን ሥራ በመለወጥ እንዲያገለግሉት ሰይጣን የሾማቸውና ራሳቸውም ለሰይጣን ያለጸጸት ለመገዛትና ለማገልገል የወሰኑ በርኩስ መንፈስ የተነዱ ናቸው።

Tuesday, March 22, 2011

አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ ማን ናቸው?

አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ ከመምህር ስብሐት ለአብ ገ/ መስቀልና ከወይዘሮ ካሳየ ገብራይ ሰኔ 30 ቀን 1914 ዓ.ም በአክሱም ከተማ ተወለዱ። አባታቸው ስብሐት ለአብ ገብረ መስቀል የአዲስ ኪዳን ትርጓሜ፤ የቅዳሴ እና የሰዓታት መምህር ስለነበሩ ከ3 አመታቸው ጀምረው ትምህርት መቅሰም ጀመሩ።አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ ዜማ፤ ዝማሬ፤ መዋሥዕት፤ አቋቋም የተማሩባቸው መምህራን
1 መርጌታ ዋሕድ
2 መርጌታ ገሡ
3 መርጌታ ስቡሕ
4 አባ ኪሮስ
5 አለቃ ገ/ክርስቶስ


የቅኔ መምህሮቻቸው


1 አለቃ አወቀ ዘወቄጣ
2 አለቃ አክሊሉ
3 አለቃ መጽሔት
4 ቀኝ አዝማች ተካልኝ
5 አለቃ ውቤ
6 አለቃ ካሳ
7 አለቃ ይትባረክ መርሻ ዘላስታ
8 መምህር ግዛው ገብሬ
9 መምህር አዘነ
10 መምህር ጽጌ


የትርጓሜ መጻሕፍት መምህሮቻቸው


1 መምህር አበበ ሻውል
2 አለቃ ሕሩይ ናቸው።
የጻፏቸው መጻሕፍት
1 ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ
2 ሥረ ብዙ
3 ትውፊታዊ ሐሳበ ሐሳበ ዘመንና ታሪኩ
4 አርዮሳውያን
5 ቃል እግዚአብሔር ነበረ
6 ሥላሴ በተዋህዶ በመባል የሚታወቁ መጻሕፍትን አበርክተዋል።
         
    ራእያቸው
1 ቤተ ክርስቲያንን ከባህል ወረራ መጠበቅ
2 ቤተ ክርስቲያንን ከበለአም ትምህርት [ጥንቆላ]መለየት
3 ቤተ ክርስቲያንን ከኤልዛቤል ርኩሰት ማንጻት
4 ቤተ ክርስቲያን ከእንግዲህ ጉድፍ መጣያ እንዳትሆን፤ በጠላትም እንዳትደፈር ቅጽሯን መገንባት
5 ክህነቷንና አምልኮዋን መቀደስ
6 ለቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን ርእስነት ማወጅ
7 የእግዚአብሔር የማዳን ኃይል የተገለጠበትን ወንጌል በጥራትና በጥበብ መስበክ፤
8 ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያን ነገረ ሃይማኖትና ነገረ መለኮት በፍርስራሽ ከተቀበረበት ቆፍሮ ማውጣት እና በሥራ ላይ ማዋል።
9 በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተውን የቤተ ክርስቲያን ቀኖና መጠበቅና ማስጠበቅ
10 ምእመናን ጸንተው እንዲቆሙ መጠበቅ እና መመገብ
11 የምመናንን ፍልሰት ማቆም
12 የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን በአግባቡ ያለመከልከል እንዲሠሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና መቆጣጠር
13 የመንፈስን አንድነት መጠበቅ
የሚሉት ናቸው።


በመጨረሻም በአደራባቸው ሕመም ምክንያት በተለያዩ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች በህክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 5 ቀን 1990 ዓ.ም አረፉ ይላል ታሪካቸው።


ከአለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶች
የመጀመሪያዋ የጥሪ ደወል!


“መርጌታ ስቡሕ የተባሉ መልካም ድምጽ የነበራቸው እውቅ የአቋቋም መምህር በአክሱም ነበሩ። ከርሳቸው ጋር እማር በነበረበት ጊዜ ለሕይውቴ የለውጥ መሰረትን አስቀምጦ ያለፈ ነገር ተከሠተ” በማለት ጀመሩ አለቃ መሠረት።


ሲቀጥሉም “ባካባቢው ከነበሩት ሊቃውንት መካከል በቃል እና በሕይወት የተለዩ በቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት እንደ አጵሎስ  የበረቱ ሰው በ1935 ዓ.ም ወደ አክሱም መጡ። አለቃ በየነ ዳምጠው ይባሉ ነበር። ቅኔ እና ዜማ አዋቂ ከመሆናቸውም በላይ ወንጌልን በግልጥ ይሰብኩ ነበር፤ ሰዎች ለሚያቀርቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች በወቅቱ ያልተለመዱ መልሶችን በድፍረት ከመናገር ወደ ኋላ አይሉም ነበር። እኔም በንግግራቸው ተሳብኩ እና ወደድኋቸው። አባቴ የሐዲስ ኪዳን መምህር እንደመሆናቸው ትርጓሜውን ሲአስኬዱ ከጉባኤው አልለይም ነበርና፤ አለቃ በየነ ዳምጠው ለሰዎች ጥያቄ ይሰጡት የነበረው መልስ ለብዙዎች አልዋጥ ቢላቸውም፤ አባቴ በጉባኤ ከሚተረጉሟቸው መጻሕፍት ቃል ያልወጣ መሆኑን ተረዳሁ። የማንበብና የመመርመር ፍላጎት ያሳደረብኝ በዚያን ጊዜ እሰማው የነበረው የአለቃ በየነ ንግግር እና ጥቅስ አወጣጥ ነበር። በውነቱ ብዙ ማወቅ እንደሚጠበቅብኝ በአለቃ በየነ ንግግር ተግፋፋሁ” አሉ አለቃ መሠረት።


በማያያዝም “ከአለቃ በየነ ጋር ባደርግኋቸው ውይይቶች በዘመናት ውስጥ መቼ እንደገቡ ያልታወቁ የፈጠራ ታሪኮች የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል ሸፍነውብን እንደኖሩና ይልቁንም ከፊደሉ በስተቀር የቃሉን መንፈስ ያጠፉብን ጊዜ የወለዳቸው አዋልድ መጻሕፍት እንደሆኑ በፍጥነት እየተረዳሁ መጣሁ አለቃ በየነ ግን ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ከቶ አይለዩም ነበር በስብሐተ ነግሕ፤ በመዝሙር፤ በማሕሌት ወቅት፤ በፍጹም ተመስጦ ያገለግሉ ነበር” በሕይወታቸው ወደ አንድ አዲስ አቋም ያሸጋገራቸውን ወሳኝ ክስተት እንዲህ በማለት ተረኩ፦


“አንድ ቀን የስቅለት በዓል እየታሰበ በነበረበት ዕለተ ዓርብ ግብረ ሕማማት ይነበብ በነበረበት ጉባኤ መካከል ቀደም ሲል ዐድማ አድርገው የነበሩ ሊቃነ ካህናት ከጭፍሮቻቸው ጋር ሆነው አለቃ በየነ ዳምጠውን ከቤተ ክርስቲያን ጀምሮ እየጎተቱ እስከ አውደ ምሕረቱ አወጧቸው። ከዚያም ድንጋይ እያነሱ ወገሯቸው። ከአቅመ ደካማዎች በስተቀር፤ መነኮሳት፤ ቀሳውስት፤ ዲያቆናት፤ ተማሪዎች ሁሉ በውግረቱ ተካፈሉ። እኔ ቆሜ ድርጊቱን ሁሉ አንድ በአንድ ተመለከትሁ”


ጥያቄ= በዚያን ሰዓት አለቃ በየነ በምን ሁኔታ ላይ ነበሩ?


መልስ= አለቃ መሠረት “ አለቃ በየነማ ልጅህ እኔን ተክቶ የተቀበለው መከራ በሚታሰብበት ዕለት የልጅህ መከራ ተከፋይ ያደረግኸኝ አምላኬ ምን ያህል ብትወደኝ ነው? እያሉ በመደጋገም ጌታን ያከብሩ ነበር። ውግረቱ ለደቂቃዎች ቀጥሎ በኋላ የአካባቢው ባለሥልጣኖች ደርሰው አለቃ በየነን ታደጓቸው። ባለሥልጣናቱ ሊቃነ ካህናቱን ለማሠር ከሰዎች መካከል እየለዩ በነበረበት ጊዜ አለቃ በየነ ቆመው “እኔ አልፈልግም እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው እኔ በበኩሌ ይቅር ብያቸዋለሁ በማለታቸው ወጋሪዎችና ተመልካቹ ወደ ቤተ ክርስቲያንና ወደ ቤታቸው ተመለሱ”


ጥያቄ= ከዚያስ ምን ተደረገ?


መልስ አለቃ መሠረት= “ከዚያማ አለቃ በየነን የታደጓቸው ባለሥልጣናት ወደቤታቸው ወሰዷቸው በዚያ የቀረነው ሁሉ ግን በተለያዩ ጥያቄዎች ተሞላን ያ ሁሉ የድንጋይ ናዳ ወርዶባቸው ሳለ እንዴት ጉዳት አልደረሰባቸውም? መሞት ነበረባቸው ለምን አልሞቱም? ብሎ አንዱ ሲጠይቅ፤ እግዚአብሔር ቢጠብቅቸው እንጂ ለመግደልማ አንዱ ድንጋይ ይበቃ አልነበረምን? በማለት ሌላው መለሰ። ሌላው ወገን ደግሞ “ክርስቲያን የሚባሉ ወጋሪዎች ናቸው? ወይስ ተወጋሪዎች? የካህናት አለቆችን እና የእስጢፋኖስን ታሪክ በመጥቀስ ሌላው ውገን ለጥያቄው መልስ ይሰጥ ነበር። አለቃ በየነ ዳምጠው አይዋሹ፤ አይሠርቁ፤ አያመነዝሩ፤ አይሠክሩ፤ አይሳደቡ፤ እንዲወገሩ ለምን አስፈለገ? የሚለውን ጥያቄ ወጋሪዎቹ ሳይቀሩ ያነሱ ነበር። እነዚህ ኃጢአቶች የሚያስወግሩ ቢሆኑማ ኖሮ ወጋሪዎቹ በተወገሩ ነበር” የሚል የፌዝ መልስም ያስተጋባ ነበር።


ለእኔ እንደሚመስለኝ አሉ አለቃ መሠረት “በዚህ ትርዒት መነሻ አንዳድ ሰዎች ሃይማኖታቸውን እንዲመረምሩ እግዚአብሔር ያሳሰባቸው ይመስለኛል። እኔም የሃይማኖቴን መሠረት እንዳውቅና አቋም እንድይዝ ያድረገኝ በሥፍራው ተገንቼ በዓይኔ ያየሁት ይህ ገድል ነበር” በማለት ታሪኩን አጠቃለሉ።
ከብዙ ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ አለቃ በየነና አለቃ መሠረት ተገናኝተው ሲጠያየቁ መኖራቸውን የአለቃ በየነ ዳምጠው የትውልድ ቦታ መርሐ ቤቴ እንደሆነና በአዲስ አበባ በንግድ ሥራ ተሠማርተው ሲተዳደሩ ከቆዩ በኋላ ማረፋቸውን ተረድተናል።


አለቃ በየነ ዳምጠው ከቤተ ክርስቲያናቸው ተደጋግሞ በደረሰባቸው ስደት ምክንያት በአዲስ አበባ የአንዲት ወንጌላዊ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆነው እንደኖሩ አረጋግጠናል።


ጥያቄ= በዚህ ጊዜ ነበር በጌታ አዳኝነት መንፈስዎ ያረፈችው?


መልስ አለቃ መሠረት “አይደለም አይደለም ይህ የተባለው ሁኔታ በሕይወቴ ውስጥ የተከናወነው በጣም ዘግይቶ ነበር። የአለቃ በየነ የመጨረሻ ገድልና ከዚያ በፊት ለአንዳድ ጥያቄ ይስጡ የነበረው መልስ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የቤተ ክርስቲያኔን ታሪክ እንድመረምርና ምርቱን ከግርዱ እንድለይ በውስጤ የሚዛን መሠረትን ስላስቀመጠ መጻሕፍትን ማንበብንና ማጥናትን ቀጠልኩ፤ መማርንና ቤተ ክርስቲያን ማገልገልን ሳላቋርጥ በግሌ ማንበብንና ማጥናትን አዘውትር ነበር።


አክሱምን በመልቀቅ እና ወደ ደብረ መንኮል በመሄድ ከታላቁ የቅኔ መምህር ከየኔታ አወቀ ዘወቄጣ ዘንድ ገባሁና የቅኔ ትምህርት ጀመርኩ። የኔታ አወቀን በኋላ ጊዜ ካስተማሩኝ ከሌሎች የቅኔ መምህራን የተለየ የሚያደርጓቸው እውቀት፤ችሎታና ጠባይ ነበሯቸው። ከ300 በላይ ይቅኔ ጎዳናዎችን ያውቃሉ ይባል ነበር።
ቅኔዎቻቸው በምሥጢር የበለጸጉ በተመረጡ ቃላት የተዋቡ በመጻሕፍተ ብሉይና ሐዲስ እንዲሁም በሊቃውንት መጻሕፍት ላይ ብቻ የተመሠረቱ ነበሩ። ተማሪዎቹ ከገድል፤ ከድርሳንና ከታምር ታሪኮችንና ንባቦችን ሲጠቅሱ በአያሌው ይቆጡ ነበር። እንዲህ ያለውን ተማሪ ለብዙ ቀን አንተ ገድል ጠቃሽ መበለት እያሉ እርሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተማሪዎችን ጭምር ተመሳሳይ ስሕተት እንዳይሠሩ ያስተምሩበት ነበር” በማለት አለቃ መሠረት አሰብ በማድረግ ጥቂት ቆዩ።
እናም አሉና ቀጠሉ “እናም የኔታ አወቀ ከላይ ከተገለጸው በተጨማሪ ከዚያ በፊት በሌላ ሰው ሲነገር ያልሰማሁትን አስደናቂ ምሥጢርን ሲገልጹ ሰምቻቸው ነበር። አንድ ቀን በመንገድ ላይ እያለን አንድ ተማሪ ለሌላው ጥያቄ ሲመልስ አዳምጠው ኖሯል። ተማሪዎቹ ይወያዩ የነበረው “ኵሉ ዘቦአ ውስተ አፉሁ ለሰብእ ኢያረኩሶ ለስብእ አላ ዘይወጽእ እምአፉሁ” በሚለው ቃለ ወንጌል ላይ የተመሠረተ ነበር። አንደኛው ተማሪ ወደ ሰው አፍ የሚገባ የተባለው ክፉ ነገር ነው እንጂ የሚበላ ነገር አይደለም አለና ተከራከረ። ንግግሩ ተወርውሮ ወደ ጀሮአቸው ገብቶ ኖሮአል፤ በዚህ ጊዜ የኔታ አወቀ ወደ ተማሪው ዞር አሉና አስተውል እንጂ አንተ ነገር በአፍ ይገባል እንዴ? በጆሮ ነው እንጂ በአፍስ ከገባ በኋላስ ወደ ሆድ ይገባልን? ከሆድስ ወደ እዳሪ ይወጣልን? አስተውሎ መናገር ይገባል  የክፉ ነገር ማህደር ልብ ነው በጆሮ የገባውን ይቀበላል። ክፉ ነገር መውጫው ከልብ በአፍ በኩል ነው እባካችሁ ልጆች እያስተዋላችሁ ተናገሩ። ደግሞም ከፍ ብላችሁ ይህን ንግግር ያስከተለው መነሻው ምን እንደሆነ ብታስተውሉ እጅን ሳይታጠቡ መብላት ሰውን ያረከሰው እንደሆነ ለቀረበው ጥያቄና ለተደረገው ክርክር የተሰጠ መልስ ነው። ባልታጠበ እጅ የሚበላው ብቻ ሳይሆን ማናቸውም በአፍ የሚገባ ወደ ልብ ሳይሄድ በሆድ በኩል ዐልፎ ወደ እዳሪ የሚወድቅ መሆኑን ጌታችን አስረዳ። ንባብን ከላይና ከታች ካለው  ዐውደ ንባብ ገንጥላችሁ አትውሰዱ ብለው በቁጣ ጭምር ተናገሩ።


በሌላም ጊዜ ተማሪዎቹ “ኢትትአመኑ በመላእክት ወኢበእጓለ እመሕያው “ በግእዙ ጥሬ ቃል በመላእክትና በሰው ልጆች አትታመኑ ብሏል። ሆኖም መላእክት ያላቸው ገዥዎችን ስለሆነ በቅዱሳን መላእክት መታመንን አይከለክልም በማለት ሲከራከሩ የኔታ አወቀ ሰምተው ከራእየ ዮሐንስ ም 19 ቁ 10 እና ም 22 ቁ 9 ጠቅሰው መላኩ “እስመ አነሂ ገብር ዘካማከ እኔም እንዳተው የኢየሱስ ባሪያ ነኝ ያለውን ምን ልታደርጉት ነው? መላእክት እንደሰው ፍጡራን አይደሉም ልትሉ ነውን? ብለው ተቆጡ።


ይህ የየኔታ አወቀ አባባል “ ሲሉ ቀጠሉ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ “ከአለቃ በየነ የሰማሁትንና እየተገነባሁበት የመጣውን ምርምሬን የሚያጎለበት ሆነልኝ። በእውነቱ የኔታ አወቀ በቅኔው የሚደነቁበትን እውቀት ያህል ቅዱሳት መጻሕፍትን የመመርመርና የመረዳት ችሎታቸው ፍጹም ሳይሆን እንዳልቀረ አወቅሁና ታዝቤ ዐለፍኩ።


በዚህም ጊዜ ሆነ በቀጣይ ዓመታት አሉ አለቃ መሠረት አያይዘው “እውነትን እና ሐሰትን በመለየት ምርቱን ከግርዱ ለይቶ በማወቅ ብቻ ተወስኜ ቆየሁ። የድኅነትን ጉዳይ ግን አላሰብኩበትም፤ ሰውም አልነገረኝም፤ እኔም አልተረዳሁትም ነበር። ይህና ይህ ግን እውነት ነው ይህ ውሸት ነው እያልኩ በየኼድሁበት እንደ አለቃ በየነ በአደባባይም ባይሆን ለሚቀርቡኝ ተማሪዎች እናገር ነበር።


አንድ ቀን ልዩ ነገርን እግዚአብሔር አደረገልኝ አሉና የእግዚአብሔር መንፈስ ልባቸው ያረፈበትን የመዳን መንገድ እንዴት እንዳሳያቸው ተረኩልን። “የቅኔን ትምህርት በማስፋፋት ላይ በነበርኩበት ጊዜ ይጠይቁኝ ለነበሩ ተማሪዎች ብዙ እውነትን ገላልጬ ነገርኳቸው። ተማሪዎችም የተደገፉበትን የሐሳብ ምርኩዝ ሁሉ አስጣልኳቸው ተማሕጽኖተ ሙታንን፤ ተስፍዎ መናፍስትን[መናፍስትን ተስፋ ማድረግ]፤ የዳነ ሕይወት ውጤት ያልሆነ ምግባርን እና የሕገ ኦሪትን ጽድቅ ሁሉ በቃለ እግዚአብሔር ናድኩባቸው። ችግራቸው እንኪያ ማን ያድነናል? በምንስ መንገድ እንድናለን? እያሉ በመጨነቅ ጠየቁኝ። ወደ ገላትያ ከተጻፈው የጳውሎስ መልእክት ም 2 ቁ 1-21 ድረስ ያለውን አነበብኩላቸው። ቁ 21 ላይ ጽድቅስ በኦሪት ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ! ከሚለው ላይ ስደርስ ለተማሪዎች በማስረዳት ላይ መሆኔን ረሳሁት። እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ? እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ? ብዙ ጊዜ ደጋግሜ እራሴን እየጠየቅሁ ለራሴ አነበብኩት። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ነው ከኃጢአት ያዳነኝ፤ ጌታ ኢየሱስ ያላዳነኝ ቢሆን ኖሮ ሞቱ ከንቱ ነው በተባለ ነበር። ደጋግሜ አስቤ በአፌም እናገር ነበር። የሞቱን ጥቅም ለራሴ ሳላውቅ ለሰዎችም ሳልናገር ያሳላፈኩት ጊዜ ሞቱን ከንቱ ያደረግሁበት ጊዜ ነው አልሁ ይህን ሁሉ እናገር በነበረበት ጊዜ ሁሉ ሳይታወቀኝ እንባ ይፈሰኝ ነበር።
በውስጤ የሚፈስ ቀዝቃዛ ነገር ይሰማኝ ነበር። አዲስ ደስታ፤ ሰላም፤ እረፍት እርካታንም ይሞላብኝ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በጌታዬ ሞትና ትንሣኤ የተገኘውን መዳን፤ጽድቅ፤ የእግዚአብሔር ልጅነት፤ የዘለዓለም ሕይወት፤ ባለመብትነት የሚያረጋግጡት ቀደም ሲል በውስጤ የነበሩት ጥቅሶች ተከታትለው መጡ። እግዚአብሔር በቃሉና በመንፈሱ ሕይወቴን የቀመመበት ለራሴም ለሰውም ጣዕምና ቃና ያለውን ኑሮ እንድጀምር ያደረገበት ልዩ ወቅት ይህ ነበር” ሲሉ በፍጹም ተመስጦ መሰከሩልን። ይቀጥላል----- 


ከጮራ መጽሔት የተወሰደ

Tuesday, March 8, 2011

ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ማስቀደም አስፈላጊ መስሎ አይታያችሁምን?

ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ። በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፥ ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች። ጥላዋ ተራሮችን ከደነ፥ ጫፎችዋም እንደ እግዚአብሔር ዝግባ ሆኑ። ቅርንጫፎችዋንም እስከ ባሕር፥ ቡቃያዋንም እስከ ወንዙ ዘረጋች። አጥርዋን ለምን አፈረስህ? መንገድ አላፊም ሁሉ ይቀጥፋታል መዝ 80፥8-12
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረ ሰቦች ሐገር ናት ይህ አባባል የብዙ ሰዎችን ልብ ያደከመ ይመስላል ሆኖም እውነቱ ግልጽ ነው በሃይማኖትም ደረጃ ቢሆን ብዙ የተለያዩ ሃይማኖቶች አሉ ሁሉም ሃይማኖት ለራሱ እንደክብሩ ነውና። በዚህ ጽሑፍ ግን ሃይማኖት ማለት “እምነት” ማለት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።

በሀገራችን ክርስትና ተጀመረ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ለክርስትና መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረገችው ጥንታዊትና ወንጌላዊት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በየዝመናቱ ያለፈችበት ታሪክ ቀላል አይደለም። ይህ የወንጌል ዘር በአፍሪካ በወንጌላዊዊ ፊልጶስ ከዚያም በአባ ሰላማ ወደ ዚህች አገር ከገባ ቆይቷል። ከዚያው ጊዜ ጀምሮ የገጠማት ፈተና ከባድ ነበር። ለምድሪቱ ዘር የተሸከመችው ይህችው ቤተ ክርስቲያን በትክክል የተዘራው ዘር በትክክል እንዳይበቅል ጠላት በሚገባ ተፈታትኖታል ብንል ታሪክ በምሥክርነት ይቆምልናል።
ዓላማዋን እንዳታሳካ መሣሪያውን እየቀያየረ ደብድቧታል። ክርስትና ከመካከለኛው ምሥራቅ ቀጥሎ የገባው ወደ ኢትዮጵያ ነው፤ ለመቶ አመታት ከአረማዊና ኦሪታዊ አምልኮ ጋር ሲታገል የነበረው ክርስትና ከመቶ አመታት በኋላ ግን እራሱን በጥረት ማቆም አቅቶት ከባህልና ከልማድ ጋር እንዲሁም ከሐሰት ትምሕርቶች ጋር እየተቀላቀለ ነገሮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ጋር ማገናዘብ አቅቶት እየተጨነቀ መጓዝ ከጀመረ ሰንብቷል።
ዛሬ አንዳድ የሃይማኖት ድርጅቶች ኦርቶዶክስ ማን ናት? ማለት ከጀመሩ ቆይተዋል። ውለታን ቆጥሮ ማመስገን እና መብትን መጠየቅ ሌላ ነገር ሆኖ ሳለ ማን ነው? ማን ናት? እንዲያውም ነጻነቴን ነፍጋኛለች፤ ማለትና ማወጅ “ባጎረስኩኝ ተነከስኩኝ” የሚለውን የአበው ብሂል እንድናስታውስ ያደርገናል።
ወጣም ወረደ ሕዝባችን ሃይማኖቱ ተጽእኖ እንዳደረገበት ካለው የስነ ምግባር አራያነትና ካለው ፈሪሃ እግዚአብሔር መረዳት ይችላል። ሆድ ብሶት ገፍቶ ካልወጣ በስተቀር እግዚአብሔርን በመለመን የሚያምን፤ የርስበርስ እልቂትን የሚጠላ፤ በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ ተጋብቶና ተዛምዶ በሰላም የሚኖር መሆኑ ያስደንቃል። የውጭ አገር ዜጎች ወርቅ ፒያሳ ላይ በየመስኮቱ ተንጠልጥሎ ሲሸጥ ሲያዩ “እዚህ አገር ሌባ የለም ወይ” ሲሉ ይጠይቃሉ። ምክንያቱን ብናጠናው ግን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፈሪሃ እግዚአብሔርን በማስተማሯ ነው። ሕዝቡም ሃይማኖታዊ ስራት ማለት የማዘዝ እና የመታዘዝ ሥራት እንዲኖረው አድርጋለች። በነበሩት ውስብስብ ሁኔታዎች ቤ/ክ/ ለተለያዩ ነገሥታት መጠቀሚያ የሆነችው የሕዝቡ የመገዛት ጠባይ መሠረት ተደርጎ ነው። እንግዲህ ይህ ሁሉ  ያሳደረባትን ተጽእኖ ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ ቤተ ክርስቲያኒቱን መውቀሱ አመጽ ነው እንላለን።
በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሚሲዮናውያን የኦርቶዶክስን ቤተ ክርስቲያን ተተግነው ከገቡ በኋላ ምእመኖቹ እነሱ የሚሉትን እንዲሉ በማድረግና ካሉበት ቦታ በማስኮብለል የጀመሩት ሥራ ቤተ ክርስቲያንን አስከፍቷል። ጠባሳውም እስከ ዛሬ በመኖሩ በሀገሪቱ ያለው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ያህል እያደረገ እንዳልተራመደ ብዙ ምሁራን ይናገራሉ። የሥነ መለኮት ተማሪዎችም አፍሪካን በሚመለከት በሃይማኖት ስም የተደረገውን ቅርመታ በስፋት ዘግበውታል።
አባቶቻችን መሬታችንን አናስነካም እያሉና በሃይማኖት አንድ በማድረግ አንድነታችንን እና ሀገራችንን በሚችሉት ሁሉ በማስተባበር ያደረጉትን ተጋድሎ መርሳት ከኛ ከልጆቻቸው አይጠበቅም።
ከዚህም ሁሉ ጋር ቤተ ክርስቲያን አንድነታችንን እና የሀገራችንን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት፤ የክርስቶስን በሥጋ መወለድ የአምስቱን ምሥጢራት ትምህርት ከሕጻንነታችን ጀምረን እንድናውቀው በማድረግ ዛሬ ለደረስንበት ሁኔታ አስታዋጽዖ አድርጋልናለች ብለን የምናምን ጥቂቶች አይደለንም።
ዛሬ አገሪቱ ካለችበት የሃይማኖት እንቃሥቃሴ አንጻር ከግራና ከቀኝ የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን መሸራረፍ የዘሩትን ማጨድ እንዳለ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መርሳት ነው። ለዚህ እንዲያመች ተብሎ ቤተ ክርስቲያኒቱን “ቤተ ክርስቲያን አይደለችም” ማለት ሌላ ጥፋት ነው።
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በ1600 ዓመታት ውስጥ ያለፈችበት ጎዳና ዛሬ በምድራችን ያሉና የክርስትናን ስም ይዘው ከወራት እስከ እስከ 100 አመት የሆናቸው ቤተ እምነታት አሁን የደረሰባቸውን ቀውስ በመመልከት ነገ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ አስቀድሞ ማየት አስፈላጊ ነው።
በቅርብ የወጣ አንድ መንፈሳዊ መጽሔት ባለፉት ዓመታት ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት “አስቸግረውናል” በማለት በተለያየ ነገር ሲከሷቸው የነበሩና እንግሊዝ ሐገር ኑረው በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ የመጡ አንድ ሰው በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ ተገኝተው መናገራቸውን ዘግቦ ነበር። እኒህ ሰው እንዲህ ብለው ነበር “ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን ከዓለም እንጂ ከቤተ ክርስቲያን አናወጣም ወደ ጤናማነት እንመለሳለን እንጂ ወደ እብደት አንሄድም። ብልጽግና ብልጽግና አትበል ብልጽግናህ እግዚአብሔር ነው እንደ ጭልፊትና ንሥር ባለጠጋን መናጠቅህን አቁም ከሌላው የተነጠቁ ምእመናን ሁሌም የናንተ አይደሉም የዚህ ሰው ፈውስ ያለው በቤተ ክርስቲያኑ ነው። ስለዚህ ሙሉ ወንጌል የሆነውን ወደ ሙሉ ወንጌል መልሱ መሠረተ ክርስቶስ የሆነውን ወደ መሠረተ ክርስቶስ መልሱ ኦርቶዶክስ የሆነውን ወደ ኦርቶዶክስ መልሱ ካቶሊክ የሆነውን ወደ ካቶሊክ መልሱ አዎን የክርስቶስን ሥራ በዚያው በሥፋራቸው ሆነው ያቀጣጥሉ... ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሥር እየሄድህ ሰው አትሥረቅ ወደ አደባባይ ውጣ ከአደባባይ አምጣ ብለዋል...” ይህን ካሉ በኋላ ሪፖርት አቅራቢው የራሳቸውን ሐሳብ ለማንጸባረቅ እንዲህ በለዋል “ ወንጌል እሰብካለሁ እያላችሁ በየቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ እየሄዳችሁ ሰው አትስረቁ” ማለታቸው ብቻ ሳይሆን ይባስ ብለው ይላል ዘጋቢው “ከአብያተ ክርስቲያናት የሠረቃችኋቸውን ምእመናን  ወደየቤታቸው መልሱ” ማለታቸው ለኔ ያስረዳኝ ነገር ቢኖር በርሳቸው የመጣው ኃይል እጅግ ብርቱ ስለመሆኑ ዘጋቢው አበክረው ገልጠዋል።
የእርሳቸውን ሁኔታ ንግግር የተረዱ ሌላው እዚያው ያሉ አገልጋይ “በምድር ያሉት የቤተ ክርስቲያን አባሎች ሁሉ የእግዚአብሔር ቤተ ሰቦች ናቸው። ስለዚህ በወንድሜ ቦታ ለመቀመጥ መፈለግ ትልቅ አመጽ ነው። እኛ ግን ሁሌም ስናየው የማንወደውን ልንለውጠው እንፈልጋለን ሰይጣንም ያደረገው እንዲህ ነው ለምን እግዚአብሔር ዙፋን ላይ አልቀመጥም ያለው እንዲሁ ነው። ለምን ? እግዚአብሔር ትንሽ ስጦታ ሲሰጠን ሊገለገልብን ሲጀምር ሁሉም ነገር እኛ ላይ ያረፈ ይመስለናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል
“እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን ሮሜ 12፥3-5።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልልቅ ጥፋት የፈጸሙ ሰዎች በጣም ጥበበኛ እና ኃይለኛ ሰዎች ናቸው ሰይጣን ከተሰጣችሁ ወሰን በላይ እንድትሄዱ በትቢት እንድታስቡ ያደርጋችኋልና ወሰናችሁን እወቁ በኛ ውስጥ መኖር ያለበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው እንኳን ኩራታችሁን መከፋታችሁን እንኳ ገደብ የሌለው አታድርጉት” በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል።
ሆኖም የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት በዚህ መወነጃጀል ከጀመሩ አንድ ምዕት አመት አልፏቸዋል። በዚህም የመጀመሪያዋ ተጠቂ ጥንታዊቷ እና ወንጌልን በመጀመሪያ የተቀበለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ናት። ቤተ ክርስቲያኒቱ መታደስ እንጂ መፍረስ የለባትም ምእመናኗም ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን መፍለስ የለባቸውም የሚሉ በጎ ሕሊና ያላቸው ሰዎች ቢኖሩም አንዳድ አፍራሽ ግለሰቦች የሚናገሩት ግን ወንጌልን መሠረት ያላደርገ ነው።
የአባቶችን የቀድሞውን ድንበር ምልክት እያፈረሱ ሌላ የድንበር ምልክት ለመሥራት ምሞከር በጣም አደገኛ ነው  ለምሳሌ አሁን ያሉት ሌሎች የክርስቲያን ድርጅቶች ከጎናቸው በመኮብለል ሌላ ድንበር በመግፋት ወይም እናሰፋለን እያሉ ከየቦታው እየቦጫጨቁ በወሰዷቸው ሰዎች ነገሮችን ሲደጋግሙ ማየት የተለመደ ነው። በየድርጅቱ በመንከራተት በወሬ ብቻ ሕይወቱ የተመሰቃቀለበት መንፈሳዊ እርካታ ሲያጣ ሁሉንም ትቶ እቤቱ የተቀመጠውን ሕዝብ ማየት በቂ ነው “የዘሩትን ማጨድ እንዲህ ነው”
ሃይማኖት ከባድ ነገር ሲሆን እምነት ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሙሉ ለሙሉ ካልተማሠረተና በየጊዜው እየታደሰ እያደገ ካልመጣ አደጋው ሰፊ ነው ሰዎች እምነታቸውን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ካላደረጉ በፍጹም ሰውነቱ እና አምላክነቱ ላይ ካልቆሙ ምንም ስለማይረኩ አደጋው እየሰፋ ይሄዳል። ከዚያም ጨካኞች፤ ሰብና የሌላቸው በመሆን የሚያራምዱት እምነት ከእግዚአብሔር ሐሳብ ውጭ ይሆናል።  በተጨማሪም ከዚህ እምነት ውጭ መሄድ ሲጀመር አምባጓሮው እየቀነሰ ከመምጣት ይልቅ እየጨመረ ይሄዳል የዚያን ጊዜ ቆም ብሎ ነገሮችን መፈተሽ አስፈላጊ ነው። እግዚአብሔር በፍትሕ ጻድቅ በመሆኑ እየሆኑ ያሉትን ነገሮች በማስተዋል ወደ ቦታቸው ለመመለስ መታገል አስፈላጊ ነው።
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ከርሷ የሚጠበቅ አለ፤ መቼም አንዳዱን ነገር መመለስ ከባድ ሊሆን ይችላል ነገር ግን እራሷን ከጥፋት ያድናታል ብዬ ያሰብሁትን ለመጠቆም እፈልጋለሁ።
ኮበለሉ የተባሉትን ልጆች በአዋጅ ጠርቶ ማናገር ቅሬታቸውን መጠየቅ እና ለዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚስማማ መልስ መስጠት ተገቢ ነው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ የስሕተት ትምህርቶች በግልጥ ይታያሉ እነዚህን የስሕተት ትምህርቶች የኔ አይደሉም ብሎ አቋም መያዝ ይሻላል እነዚህን የስሕተት ትምህርቶች የተቃወመውን ሁሉ ማስወጣት ግን አለማስተዋል ነው ቤተ ክርስቲያኒቱ ባዶዋን እንድትቀር የሚያድረግ እርምጃ ነው። ቤተ ክርስቲያኒቱ በምድሪቱ ላይ የጀመረችውን አገልግሎት እንደ እግዚአብሔር ቃል በየጊዜው እራሷን እየፈተሸች መንጋዋን ሳትበትን ዳግም ለሚመጣው ለኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ማስረከብ አለባት። አሁን ተሃድሶዎች የጀመሩትን አገልግሎት ቤተ ክርስቲያኒቱ ብትመራው አካሄዱን ለማስተካከልም ሆነ መንጋዋን ለመጠበቅ ይጠቅማታል። ቤተ ክርስቲያኒቱ ተሃድሶዉን ከመጠን በላይ እየገፋችው ከውስጧ እያራቀችው ከሄደች ግን ከዚህ በፊት ከደረሰባት አደጋ የከፋ አደጋ ይደርስባታል። ወደድንም ጠላንም ተሃድሶዎችን ለመቆጣጠር እና ለመምራት የምንችለው በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር ካደርግናቸው ብቻ ነው ከገፋናቸውና ካባርርናቸው ግን የያዙትን ይዘው በዚያው ይጠፋሉ ይህ ደግሞ ለሃገሪቱ አንድነትም ሆነ ለቤተ ክርስቲአይኒቱ እድገት አይጠቅምም። ተሃድሶው አቅጣጫውን እንዳይስት በቤተ ክርስቲያኒቱ መመራት አለበት።
ማህበረ ቅዱሳን ማስተዋል አለበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ቅናት ያላችሁ መሆናችሁን አውቃለሁ ነገር ግን ቅናታችሁን ቆም ብላችሁ ብትመረምሩት እያፈረሰ እንጂ እየሠራ እይደለም ፕሮቴስታንቱን ለመከላከል “ማባረር” ነው የሚለውን አቋማችሁን እንደገና ፈትሹት እኛ ባባረርን ቁጥር ሌላው ይደራጅበታል እንጂ ምንም ጥቅም የለውም ከተሃድሶዎች ጋር መወያየት እና የሚታረመውን በጋራ ማረም በምትስማሙበት ላይ በጋራ ለመሥራት የጋራ የሆነ የሊቃውንት መድረክ መኖር አለበት። ተሃድሶዎች እነማን ናቸው ከኛ ጋር የሚቀመጡት ? የሚል ግትር አቋም ካላችሁ ግን ትእቢት ነው አደገኛ አካሄድ መሆኑንም ልነግራችሁ እወዳለሁ። በዚህ ወቅት ጋዳፊ በያዘው ግትር አቋም ብዙ የደከመባትን ሀገር ባጭር ጊዜ ውስጥ እያፈረሳት ነው የማህበረ ቅዱሳን አለመሻሻልም የቤተ ክርስቲያኒቱን እድገት ከማበላሸት ያለፈ ፋይዳ የለውም።
እኔን የሚያሳስበኝ የተሃድሶ እንቅስቃሴ በየጓዳው መሆኑ ነው እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ መታደስ አይደለም እንዲህ ያደረገው ደግሞ የማህበረ ቅዱሳን አለማስተዋል ነው ይህ ወደ ፊት በኢትዮጵያ አንድነትን የሚያጠፋ ነው እባካችሁ አስቡበት። ተሃድሶውን ቤተ ክርስቲያኒቱ በትክክል እና ብጥንቃቄ ብትመራው በጣም ጠቃሚ ነው ባይ ነኝ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር  አሜን
ተስፋ ነኝ

Wednesday, March 2, 2011

በትርጉም የተቀበሩ እውነቶችና ቦታ ያገኙ ውሸቶች

በመጽሐፍ ለተገለጹት እውነቶች የተሳሳተ ትርጉም ከተሰጣቸው ምክንያቶች መካከል ዋናው ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ ሰርገው ለገቡት የስሕተት ትምህርቶች ሕጋዊነት ለመስጠት ሲባል መሆኑ ምስክር አያሻውም። ብዙ የስሕተት ትምህርቶች በማስመሰል መንገድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ እንዲኖራቸው የሚደረገው መጽሐፍ ቅዱስን ሁሉም የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን ስለ ሚስማማበት ነገሩ ተቀባይነት እንዲኖረው ነው። መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንዲሉ አበው።


የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል ተብሎ የተጻፈውን ቃል በማስተዋልና ሁሉን ፈትኑ መልካሙን ያዙ በሚለው ቃል መሠረት ማንኛውም ምእመን የሃይማኖቱን ትምህርት በእግዚአብሔር ቃለ መሠረት ሊመረምርና መልካሙን ከመጥፎው ለይቶ ሊይዝ ተገቢ ነው። (ምሳ 14፥15፤ 1ተሰ 5፥20)

የቤርያ አይሁድ አመለካከት ከተቀበልነው ውጪ ሌላ መስማት አንፈልግም በሚል ጠባብነት ያልተሞላና ከላይ ባየነው የእግዚአብሔር ቃል ላይ የተደገፈ በመሆኑ እውነትን ከሐሰት፥ ትክክለኛን ነገር ከተሳሳተው ለይቶ ለመረዳት ቀና መንገድ ሆኖላቸዋል። (የሐዋ ሥራ 17፥11)

ስንቶቻችን የሃይማኖታችንን ትምህርት በእግዚአብሔር ቃል መርምረናላ? መመራመር መጥፎ ነው የሚለው የሰነፎች ብሂል አስሮ የያዘንስ ስንቶች ነን? በተገለጠው ነገር ላይ መልካሙን ከመጥፎው ለመለየት የሚደረገው ምርምር ምንም መጥፎ ጎን የለውም። እንግዲያውም ወደ እውነት ያደርሳል። ከተገለጠልን ውጪ እግዚአብሔር ራሱ ምስጢር ያደረገውን ነገር ለመግለጥ መፍጨርጨሩ ግን ወደ አልተፈለገ ስሕተት ይመራናል። ብዙዎች ከሃይማኖት ወጥተው በትዕቢት ተነፍተው የወደቁት ከዚህ የተነሣ ነው። ለሁሉም ግን ሁሉን ፈትኑ መልካሙን ያዙ የተባለው በተገለጠው እውነት ላይ ሁሉን በእግዚአብሔር ቃል መሠረት መርምረን እንደ ቤርያ አይሁድ ወደ እውነት እንድንደርስ መሆኑን አንዘንጋ።

አንዳንዱን በትክክል ሳንረዳ እኛ እናውቅላችሁአለን በሚሉን ሰዎች ስንመራ ኖረናል። የእግዚአብሔርን እውነት አግኝተን ግን አላረፍንም። ለነገሩማ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቡ፥ ተማሩ፥ አስተምሩ ብለው ሰጥተውን ነበር። እኛም ገልጠን ማንበብ፥ መማር፥ ማስተማር ጀመርን። በዚህ ጊዜ የተረዳነው እውነት ከእነርሱ አስተምህሮ ጋር ሳይስማማ ቀረ። ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ብልጭ ብሎልን ጥያቄ ስናቀርብ እንኳን ዘመናትን ካስቆጠረው ስሕተት ጋር ጥያቄአችን ስለሚጋጭ ይህ የመናፍቃን ጥያቄ ነው። ተብለን እንነቀፋለን። መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ የሚሆኑ ቢገኙም ለህልውናቸው ሲሉ በማቻቻልና አገም ጠቀም በሆነ መንገድ የማያረካ መልስ ይሰጣሉ። እግዚአብሔር ይመስገን! አሁን ግን የእግዚአብሔርም ልጅ እንደመጣ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደሰጠን ተረድተናል። (1ዮሐ 5፥20)

እውነት እንዲዛባ ያደረገው በአተረጓጎም ላይ የተፈጠረው ስሕተት ነው። ከዚህ ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያናችን የተሳሳተ ትርጓሜ ከተሰጣቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መካከል አንዱን ብቻ እንቃኛለን።

ያዕቆብ በሕልሙ ያየው መሰላል

ያዕቆብ ከቤርሳቤት ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ። ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ። ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ። በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሳ። ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ ሕልምም አለመ። እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር። እነሆም እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር። (ዘፍ 28፥10-13)

ያዕቆብ ከወንድሙ ከኤሳው ፊት ሸሽቶ በጉዞ ላይ ሳለ ካደረበት ቦታ ሌሊት ተኝቶ በሕልሙ ያየው ይህ መሰላል ድንግል ማርያም ናት ብለው ብዙዎች ያምናሉ፥ ያስተምራሉም። በድርሰቶቻቸውም ውስጥ አስረግጠው በስፋት ጽፈዋል። ይህም የክርስቶስን ስፍራ ለእርሷ ለመስጠት ብለው ያደረጉት ነው።

ያዕቆብ በምድር ተተክሎ፥ ራሱን ወደ ሰማይ ደርሶ ያየው መሰላል በምድር የሚኖሩ ሰዎች በሰማይ ካለው አምላክ ጋር የተገናኙበት ሰው የሆነው አምላክ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። ለያዕቆብ በምሳሌነት የታየው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ሲመጣ መላእክት በመሰላል ላይ ሳይሆን የሰው ልጅ በተባለው በክርስቶስ ላይ እንደሚወጡና እንደሚወርዱ ራሱ ጌታችን ተናግሯል፦ እውነት እውነት እላችሁአለሁ። ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ። (ዮሐ 1፥52)

ያዕቆብ ስለመሰላሉ ያየው ራእይ በክርስቶስ መፈጸሙን ሊቃውንተ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በየድርሳኖቻቸው አስቀምጠውልናል።

ወሶበሂ ርእይዎ ዓዲ እንዘ የዓርግ ሰማየ ተፈሥሑ ወተሐሠዩ ጥቀ ወዐርጉ ምስሌሁ ውስተ ሰማይ ወበእንተዝ እምአመ ዕለተ ዐርገ እግዚአነ ኢየሱስ ክርስቶስ ኮነ ራእይ ዘነጸሮ ያዕቆብ እሙነ እንዘ መላእክት የዐርጉ ወይወርዱ ኃበ አብ ወዝ ውእቱ ርእይ ሐዲስ ዘኮኑ ይትሜነዩ ይርአይዎ እምቅድመ ዮም ወናሁ ይእዜ ርእይዎ

ትርጓሜ፦ ዳግመኛ ወደ ሰማይ ሲያርግ ባዩት ጊዜ ፈጽሞ ደስ አላቸው። ወደ ሰማይም ተከትለውት ወጡ ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገበት ቀን ጀምሮ መላእክት ወደ አብ ሲወጡ ሲወርዱ ያዕቆብ ያየው ራእይ ደረሰ ተፈጸመ። ከዛሬ አስቀድሞ ሊያዩት ይመኙት የነበረ እንግዳ ማየት ይህ ነው። እነሆ አሁንም ዛሬ አዩት። (ሃይ። አበ ዘዮሐ አፈ ም 68 ክፍል 25 ቁ 34)

ያዕቆብኒ ይቤ ርኢኩ ሰዋስወ ዘሰማይ፤ ወመላእክተ እግዚአብሔር የዐርጉ ወይወርዱ፤ እንተ ይእቲ ሰዋስወ ኢየሱስ ይነብር በየማነ አቡሁ አእላፍ መላእክት ይትለአክዎ።

ትርጓሜ፦ ያዕቆብም ወደ ሰማይ የደረሰ መሰላልን አየሁ አለ። የእግዚአብሔር መላእክትም የወጡበታል ይወርዱበታል። ይህችም በአባቱ ቀኝ የተቀመጠ አእላፍ መላእክት የሚያገለግሉት የኢየሱስ መሰላልነት ናት። (የዮሐንስ ድጓ ገጽ 88 3ኛ ዓምድ)


አብይ - የተቀበረ መክሊት ከሚለው መጽሐፍ የተወሰደ።