Friday, July 8, 2011

የቤተ ክርስቲያናችን መሠረተ እምነት (ዶግማ) - ክፍል 2 - - Read PDF

የስህተት ትምህርትን በስፋት ይዘው ከሚያራግቡት መካከል ፈሊጠኞች የሆኑት ደግሞ በጊዜው በለስ ቀንቶት ተቀባይ ያገኘው አስተምህሮአቸው የእውነትን ካባ ካልደረበ በቀር ወደፊት ዕርቃኑን እንደሚቀር ቀድመው ስለተረዱ ስሕተታቸውን ይዘው ወደ እውነት መጠጋትን እንደ አማራጭ በመውሰድ ከጸሎተ ሃይማኖትም ሆነ ከስድስቱ የቤተ ክርስቲያን ዶግማዎች ላይ ቅርጫፍ አበጅተው ኑፋቄአቸውን በማዳቀል ከእውነት ግንድ የወጣ ቅርንጫፍ ለማስመሰል ቢደክሙም የነርሱ ቅርንጫፍ ተቀጽላ እንጂ የግንዱ ትክክለኛ ቅርንጫፍ አለመሆኑን መንፈሳዊ ዐይኑ የበራለት ሁሉ ይለየዋል።
   መሠረተ እምነት (ዶግማ) በእግዚአብሔር ቃል መሠረት  የቆመ፥ የሚጨመርበትና የሚቀነስለት ወይም እንደ ሁኔታው ታይቶ የሚሻሻል ነገር የሌለበት ዘላለማዊ ነው። ቀኖና ደግሞ አምልኮተ እግዚአብሔርን ለማካሄድ፥ ውንጌልን ለማሠራጨትና የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ተግባራት ለማከናወን ሲባል የሚወጣ ሥርዓት ነው። ቀኖና ሥርዓት በመሆኑ እንደጊዜው ሁኔታ ታይቶ መሻሻል የሚደረግበት ነው። ቢሆንም ሥርዓትን የማሻሻልና ያለማሻሻል መብቱ የሁሉም ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ነው። አንዳንድ ጠባቦች ግን በዶግማና በቀኖና መካከል ያለውን መሠረታዊ ልዩነት ካለመረዳታቸውና ለመረዳትም ጥረት ካለማድረጋቸው የተነሳ ሁለቱንም አደበላልቀው በመመልከት ሥርዓት አይሻሻልም ወደሚል አቅጣጫ እያመሩና ቤተ ክርስቲያናን እያወቁ ይገኛሉ። አነርሱ እንዲህ ቢሉም ሥርዓት በባሕርዩ ቋሚነት የሌለው በመሆኑ ከሕዝቡ የኑሩ ደረጃና የአስተሳሰብ እድገት ከዓለም ስልጣኔም አንጻር እየተሻሻለ፥ እያደገና እየተለወጠ መሄዱ አልቀረም።
   ከመሠረተ እምነትና ከሥርዓት ውጪ የሆኑ ብዙ ልምዶችና ባህሎችም በቤተ ክርስቲያን መኖራቸው ይታወቃል። ነገር ግን ተገቢ የሆነ ስፍራቸውን አልያዙም። እንደውም የዶግማውንና የሥርዓቱን ስፍራ አስለቅቀው መሠረተ እምነት መስለው ተቀምጠዋል። ከዚህ የተነሣ አብዛኛው ሰው ሕገ እግዚአብሔር ቢጣስ ያን ያህል ግድ የለውም፤ ከልማዶቹ ወይም ከሥርዓቱ ጥቂቱ እንኳ ዝንፍ ቢል ዱላ ያነሣል እንጂ በቸልታ አያልፍም። ይህም ከትምህርት ጉድለት የመጣ እንጂ የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ አይ እንዲሆን የሚፈቅድ ስለሆነ አይደለም።
   ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አገራችን ፈልሰው የመጡት አይሁድ አምልኮአቸውን፣ ሥርዓታቸውን፣ ባህላቸውንና ልማዳቸውን ጭምር ይዘው መጥተዋል። እነዚህም ሁኔታዎች በሕዝባችን አኗኗር ውስጥ ሠርጸው ስለገቡና የመሠረተ እምነት ያህል ስፍራ ስለተሰቻቸው ሕዝባችን ወደ ክርስቶስ ዘወር እንዳይል መጋረጃ ሆነዋል። (2ቆሮ 3፥14-16)
   ሁሉም የዓለማችን ማኅበረሰብ ለራሱ የሚወደድ መልካም የሆነ ባህል፣ ሥርዓት፣ ልማድ አለው። ከእግዚአብሔር ውጪ መኩራት ተገቢ አይደለም እንጂ የእኛም የኢትዮጵያውያን ባህል ለራሳችን የሚያኮራን መልካም ባህል ነው። ወደ እምነት ጉዳይ ሲመጣ ግን ሃይማኖትና ባህል ተነጣጥለውና የየራሳቸው ስፍራ ተሰጥቷቸው እንደየደረጃቸው ሊታዩ ይገባል። መቼም ቢሆን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርብ ባህል ስለሌለ ባህልና ልማድን በእምነት ስፍራ ማስቀመጡ ትልቅ ስሕተት ነው። ዛሬ ሕዝባችን ባለማወቅ ዶግማ ውይም ቀኖና አድርጎ የሚወስዳቸው ልማዶች ከቀጥተኛው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አንጻር ሲታዩ ከዶግማ ወይም ከቀኖና ቁጥር የማይገቡ እንዲሁ ልማዶች ብቻ መሆናቸውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ይህንም ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ገልጸውታል፦ “ የብሉይ ኪዳን ልማዶችና ባህሎች ባሁኑ ጊዜ በክርስትና ሃይማኖታችን ውስጥ እንደ ዶግማ ወይም እንደ ቀኖና ሳይሆን እንደ ልማድ ሆነው የሚጠበቁ ናቸው” ካሉ በሁዋላ በምሳሌነት የብሉይ ዲዳን መጻህፍት እንዳይበሉ የሚከለክላቸውን እንስሳትና አዕዋፍ አለመመገብን፥ ግዝረትን፥ በአጠቃላይ በህዝቡ የኑሮ ሥርዓትና ሃይማኖታዊ ስሜት፥ በኅዘን በደስታ ጊዜ ያለው ሁኔታ፥ የበዓላት አከባበር፥ የሴቶችና የሕፃናት ጌጣጌጥ ሁሉ ከአይሁድ የተወረሰ ልማድ መሆኑን ገልጸው ሲያበቁ “በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ የማሕሌት ሥርዓት፥ የካህናቱ ልብሰ ተክህኖ፥ ካባው፥ ድርቡ፥ ጸናጽሉ፥ ከበሮው፥ ኩፋሩ፥ መጠምጠሚያው የታቦቱ ክብርና ሌላውም ሁሉ ከብሉይ ኪዳን ሥርዓት ጋር ይመሳሰላል።” ሲሉ ጽፈዋል። (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ገጽ 16-17)
   በስተመጨረሻው ላይ ያሰፈሩትና አሁን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩት ኦሪታዊ ሥርዓቶችና ልማዶች ከብሉይ ኪዳን ሥርዓት ጋር ይመሳሰላክ ያሉት ግን ነገሮችን አቻችሎ ለማቅረብ ታስቦ ይመስላል እንጂ ብዙ እውነትነት የለውም። እንዲያውም “ይመስላል” ከማለት ይልቅ “ ከብሉይ ኪዳን ሥርዓት የተወረሰ ነው” ቢባል ለተናጋሪውም ለሰሚውም ይመቻል።
   በቤተ ክርስቲያናችን ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ የሆኑትንና አሁንም እየተሠራባቸው ያሉትን ትምህርቶች ሥርዓቶች ምንነት ያለፉትም ሆኑ አሁን ያሉት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አሳምረው የሚያውቁት ቢሆንም ለማስተካከልና ቤተ ክርስቲያንን ወደ ጥንቱ እውነተኛ መሠረቷ ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት እጅግ አናሳ ነው። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይኖሯቸዋል። ከነዚህም ውስጥ ለማስተካከል እንነሣ ብንል ስሕተቶች ዘመናትን ያስቆጠሩና ሥር የሰደዱ፥ በሕዝቡም ልብ ውስጥ የእውነትን ያህል የሚታዩ በመሆናቸው ሰሚ አናገኝም፥ እውነትን በሚቃወሙ ክፍሎች “መናፍቅ” የሚል ስም ተሰጥቶን እንደተሰደዱት ወንድሞቻችንና ልጆቻችን መሰደድ፥ ከእንጀራችን መፈናቀል ሌላም ሌላም መከራ ይገጥመና፨e የሚሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
   በጽሑፍ አሳባቸውን ለመግለጽ ቢፈልጉ እንኳን የእግዚአብሔር ቃል ምስጢር ከመጽሐፍ ቅዱስ ተቀድቶ ያለቀ ይመስል አንባቢው ወገናችን እስኪሰለች ድረስ መልሰው መላክሰው የሚጽፉት ያንኑ ተቃዋሚዎች ሁሉ የሚያብጠለጥሉትን አንድ ዓይነት ነገር ነው። ከሺህ አንድ እውነት ለመናገር ደፍረው እንኳ በመካከል አንድን እውነት ጣል ቢያደርጉበት ተቃዋሚዎች በጀሌዎቻቸው ታጅበው ለውግዘት ይነሱባቸዋል። እውነትን የሚያወግዙ መናፍቃን የመብዛታቸውን ያህል ውሸትን በብዕራቸው ጫፍ እንኳ ለመንካት የሚደፍሩ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መታጣታቸው ያሳዝናል። ቤተ ክርስቲያናችን ያሉባትን መንፈሳዊ ችግሮች ሊቃውንቱ የሚያውቁትን ባያህልም ምእመናንም በበኩላቸው የሚያውቁት ብዙ ጉዳይ እንዳለ ግልጽ ነው። ሌላው ሁሉ ይቅርና በአብዛኛው ምእመን ልብ እንኳ ቢያንስ ቢያንስ “ ይህስ ትክክል አይደለሁም” የሚባል አንዳንድ ነገር መኖር ሳይጠቀስ አይታለፍም።
   እንግዲህ የቀደሙት ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ ያስቀመጧቸው አስተምህሮዎች፥ ስርዓቶችና ልማዶች ከቤተ ክርስቲያናችን ትክክለኛ ትምህርት ጋር በመደበላለቃቸው ምክንያት አብዛኛው ሕዝባችን የእግዚአብሔርን ቃል ከሌሎች ነገሮች ጋር ሳይቀላቅል ከሚሰብከው ይልቅ የሰው ወግና ሥርዓትን የሚሰብከው ቁጥር በርካታ በመሆኑም ከአምላካውው ሕግና ስርዓት ይልቅ የሰውን ሥርዓት አስበልጦ ይመለከታል። ይህ ሁሉ ከንቱ አምልኮ ነው። (ማቴ 15፥9) ከዚህ ሁሉ ጥፋት ለመዳን የሰው የሆኑትን ነገሮች ከትክክለኛው የቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት ውሳኔና ዶግማ አንጻር መመርመርና መልካሙን ሁሉ ይዞ በሃይማኖት ጸንቶ መኖር የያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ወገን ኃላፊነት ይሆናል። (ኤፌ 5፥10፤ 1ተሰ 5፥21፤ 1ዮሐ 4፥1)

ከተቀበረ መክሊት መጽሐፍ የተወሰደ

1 comment:

  1. ወንድሜ ስለንስሐ ታውቃለህ ንስሐ ግባ ብትባል ምን ታደርጋለህ? አምኖ መቀበልና ታምር ማድረግ የተለያዩ ናቸው ለምን ቢባል ታምር የሚሰሩ ከሚያምኑት መካከል እንደባቄላ ቅርጣን ስለሚወጡ ወይም በየዘመኑ ስለሚገኙ ነው የሚያምኑ ሁሉ ታምር ሰሪዎች ስላይደሉ ታምር ማድረግን በስጦታ እንደ ነቢዩ ኤልሣዕ ላሉት አብዝቶ ተሰጥቷል የእምነት ምስክር አንዱ ታምር ማድረግ ነው ምስክር ደግሞ ደቀ መዝሙር ነው

    ReplyDelete