Sunday, May 8, 2011

የቤተ ክርስቲያናችን መሠረተ እምነት (ዶግማ) - Read PDF

ክርስትና በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የተመሠረተና የተደመደመ ሃይማኖት ነው። ይህም ሲባል መሠረተ እምነቱና (ዶግማውና) ሥርዓቱ (ቀኖናው) ሁሉ በአንድም በሌላም መንገድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ማለት ነው።

ከሕዝብም ከአሕዛብም ወገን የሆኑትንና በክርስቶስ አዳኝነት ያመኑትን ወገኖች በማሰባሰብ መንፈሳዊት ጉባኤ የሆነችው አንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ጌታ ለሐዋርያቱ ያስተላለፈውን እርሱ ካረገ በሁዋላም መንፈስ ቅዱስ መጥቶ የገለጠውን ትምህርት (ዮሐ 16፥12-13) ከሐዋርያቱ ተቀብላ ስትመራበት ቆይታለች። ይህም ከጥንት ጀምሮ “የሐዋርያት ትምህርት” ተብሎ ይጠራ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ፍንጭ ይሰጣል። (የሐዋ ሥራ 2፥42) የሐዋርያት ትምህርት መሠረት እምነት በመሆኑም የሃይማኖት መግለጫዎችን ወይም ውሳኔዎችን እንደያዘ የሚጠቁመንን ሌላ ክፍልም እናገኛለን። (ዕብ 6፥2) በዚህ ትምህርት መሠረት ቤተ ክርስቲያን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ እስከ 4ኛው መቶ ክ/ዘ ድረስ ስትመራ መቆየቱዋን ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ መረዳት አያዳግትም።
      በዘመነ ሐዋርያትና ዘመነ አርድእት አልፎ ቤተ ክርስቲያንም በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ ብቻ መወሰኑዋ ቀርቶ አየተስፋፋችና አብዛኛውን የዓለም ክፍል እየሸፈነች ስትመጣ ያላትን የመንፈስ አንድነት ለመጠበቅና የቀደሙት ሐዋርያት እንዳደረጉ (የሐዋ ሥራ 15፥24-29) የትምህርትን ዐረሞች ለማረምና ነቅሎም ለመጣል እንዲረዳት የስብከተ ወንጌል ክልሎችን በአራት አህጉረ ስብከት አመራር ሥር ከፈለች። እነዚህም የአህጉረ ስብከት መናብርት የሚገኙባቸው ከተሞች ሮም፥ እስክንድርያ፥ኤፌሶንና (በሁዋላ ቁስጥንጥንያና) አንጾኪያ ሲሆኑ የተቀሩት አገሮች ግን እንደ ቅርበታቸውና ጆኦግራፊዋዊ አቀማመጣቸው በአራቱ በአንደኛው ውስጥ እንዲታቀፉ ተደርጓል። አራቱም መናብርት ባሉባቸው ከተሞች በሊቀ ጵጵስና ማዕረግ የሚሾሙ አባቶች ተሠይመው በየአቅራቢያቸው ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት እንዲያስተዳድሩ፥ የወንጌልን ሥርጭት እንዲከታተሉና እንዲያፋጥኑ የስሕተት ትምህርቶችንም እንዲቆጣጠሩ ስምምነት ተደርጓል። (ፍትሐ ነገሥት መንፈሳዊ 1ኛ ክፍል አንቀጽ 4)
      እንዲቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ መዋቅር ዘርግታ ወንጌልን ለማዳረስ በምትፋጠንበት በዚያ ዘመን ከሐዋርያት ተቀብላ ስትመራበት የቆየችውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የሚያደፈርሱ የኑፋቄ ትምህርቶች ብቅ ብቅ በለው የአንዲት ቤተ ክርስቲያናን መንፈሳዊ አንድ,ት ለመከፋፈልና ህልውናዋንም ለማናጋት በመሞከራቸው ቤተ ክርስቲያን የወከለችው ጉባኤ በየጊዜው ተሰብስቦ የመናፍቃንን ትምህርተ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ቃል እየመረመረ እውነቱን በመግለጽና ስሕተታችውን ዐርመው እንዲኖሩ ዕድል መስጠት ፍትሐዊ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። ነገር ግን መናፍቃኑ ኑፋቄአቸውን ጥለው በቀናው መንገድ ለመጓዝ እንቢተኞች በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን እነርሱንም ትምህርታቸውንም ከአንድነቷ አውግዛ ስተለያቸው ለራሷ ደግሞ በኑፋቄያቸው አንጻር መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የሃይማኖት መግለጫ አውጥታ የእምነቷ ደንብ አድርጋ እየተጠቀመችበት ትገኛለች። በኒቅያ በ 325 ዓ/ም የአርዮስን፥ በቁስጥንጥንያ በ 381 ዓ/ም የመቅዶንዮስን ትምህርተ ሃይማኖት ለመመርመር የተሰበሰቡት የቤተ ክርስቲያን አባቶች በሁለቱ ጉባኤዎች መጨረሻ ላይ ያስተላለፉት ውሳኔ ዛሬ ጸሎተ ሃይማኖት በመባል የሚታወቀው ነው።
      ጸሎተ ሃይማኖት የተሰኘው የሃይማኖት መግለጫ 12 አንቀጾች ያሉት ሲሆን ሰባቱ በኒቅያ ጉባኤ፥ አምስቱ ደግሞ በቁስጥንጥንያ ጉባኤ የተረቀቁ ናቸው። ሁሉም ልብ ይላቸው ዘንድ አሥራ ሁለቱም አንቀጾች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል።

1)     በአንድ አምላክ እናምናለን ሁሉን የያዘ አባት ሁሉን የፈጠረ የሚታየውንም የማይታየውንም
2)     በእግዚአብሔር ልጅ በአንድ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን፥ ብቻውን ከአብ የተወለደ ይኸውም ከአባቱ ባሕርይ ከአምላክ የተወለደ አምላክ፥ ከብርሃን የተወለደ ብርሃን፥ ከእውነተኛ አምላክ የተወለደ እውነተኛ አምላክ የተወለደ እንጂ ያልተፈጠረ፥ በመለኮት ከኣባቱ ጋር አንድ የሚሆን ሁሉ በእርሱ የሆነ በሰማይም በምድርም።
3)     ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለ መዳናችንም የወረደ፥ ሥጋ የሆነ፥ ሰውም የሆነ
4)     የታመመ (መከራን የተቀበለ) የሞተ የተቀበረ
5)     በ3ኛው ቀን ዳግመኛ የተነሣ
6)     ወደ ሰማያት የወጣ
7)     ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ ዳግመኛ የሚመጣ፤ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን።

የቁስጥንጥንያ አንቀጸ ሃይማኖት

8)     በጌታ፥ በአዳኝ፥ ከአብ በሠረጸ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ እንስገድለት እናመስግነው
9)     በሁሉ ባለች በሐዋርያት ጉባኤ ባንዲት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን
10)  ለኃጢአት ማስተስረያ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን
11)  የሙታን ትንሣኤን ተስፋ እናደርጋለን
12)  የሚመጣውን ሕይወት እንጠባበቃለን ለዘለዓለሙ አሜን!

በቁስጥንጥንያው ጉባኤ የመጨረሻዎቹን አምስቱን አንቀጾች ከማርቀቅ ባሻገር በኒቅያ አንቀጸ ሃይማኖት ውስጥ ተጨማሪ (ሥርዋጽ) ቃላትን የመጨመር ሥራ ተከናውኗል። (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ከአባ ጎርጎርዮስ ገጽ 113-114፤ 130-131)
   እነዚህ የሃይማኖት ውሳኔዎች የተላለፉት በሌሎች ስብሰባዎች እንደሚደረገው ሌሎችን ጎድቶ የራስን ጥቅም ከማስከበር አንጻር በድምጽ ብልጫ በዚህ እናምናለን፤ በዚህ ደገሞ አናምንም በሚል ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል በሚለው መሠረት ተጠንተው ነው። ምንም እንኳ ውሳኔው ቃል በቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ የተቀዳ ባይሆንም የያዛቸው መልእክቶች ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው።
   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት ይኸው የእምነት መግለጫ (ጸሎተ ሃይማኖት) ነው። ከዚህ ውጪና ተጨማሪ የሆነ መሠረተ እምነት ቤተ ክርስቲያናችን እስካሁን ድረስ የላትም፤ ለወደፊቱም አይኖራትምe። በአባ መልከጼዴቅ የተጻፈው ትምህርተ ክርስትና 2ኛ መጽሐፍ ገጽ 3 ላይ ይህንኑ ይመሰክራል “ይህ ተአምኖ ሃይማኖት ለትምህeርት ለምስክርነት በቂ ስለሆነ ማንኛውም ሊቅ ስለዶክትሪንe ሰፋ አድርጎ እጽፋለሁ ቢል ከዚህ ውጪ ሊሄድ ከቶ አይችልም፤ እንዲሁም በመጠኑ ቢጽፍም ከዚህ ውስጥ የሚቀንሰው የሚተወው የለም። ምክንያቱም መጀመሪያውኑ በጥሩ መልክ የተዘጋጀ ስለሆነ ያለምንም ለውጥ ለመኖር ይችላልና”
   ይሁን እንጂ ለዘመናት ቤተ ክርስቲያናችንን ከመሪዋ ከመንፈስ ቅዱስ ለይተው ያስኮበለሏትና ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ እንደ ገዛ ፈቃዳቸው እያሽከረከሩ ከመምራት ስተው ያሳቷት ጊዜ የሰጣቸው ጣልቃ ግብ ነገሥታትና አቀንቃኞቻቸው ናቸው። ለራሳቸው ክብርና ዝና እንዲሁም የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘምና ኑሮአቸውን ለማደላደል ሲሉ ከእነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩት የሃይማኖት ውሳኔዎች ውጪ የሆኑትንና ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር የሚቃረኑትን ኑፋቄዎች ሌላ አውጋዥና ከልካይ በሌለበት የሥልጣን ዘመናቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን በዐዋጅ በማስገባት የተከሉብን ክፉ መርዝ ሥር ሰድዶ የአንዲቱን ቤተ ክርስቲያን ልጆች በመከፋፈል የጎሪጥ እንዲተያዩ አድርጓል። በተጨማሪም ራሱን እውነተኛ አድርጎ በማስቀመጡ አማኙንና ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያን ልጅ መናፍቅ፤ በአስተምህሮው መናፍቅ የሆነውን ደግሞ አማኝ ሲያሰኝ፥ ሲያስወጣና ሲያስገባ ቆይቷል።

ይቀጥላል
ከተቀበረ መክሊት መጽሐፍ የተወሰደ

3 comments:

 1. ''ተሰብአ ወተሰገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል''የሚለው አንቀጽ ለምን ተገደፈ ? ተሐድሶዎች በቅድስት ድንግል ማርያም ''ድንግል በሥጋኪ ወድንግል በህሊናኪ''በሚለው ሃይለ ቃል ያምናሉ ? አማልጂነቷንስ?

  ReplyDelete
 2. ewnet enante ortodox nachu?

  ReplyDelete
 3. አባ ሰላማ ብሎ በቅዱሳን ስም መነገድ ወይም መውቀስ አግባብ አይመስለኝመ
  ደግሞ ሰላማ ማለት ሰላም ወይም የሰላም አባት ማለት ነው ነገር ግን በዚህ ስም
  ሰላምን መስበክ ሳይሆን ሀሜት፥ቅናት፥አድመኝነት፥ትችት፥ምንፍቅና እና የመሳስሉትን
  እያቀረባችሁ እንዴት አባ ሰላማ ብላችሁ ለመጥራት ደፈራችሁ
  ደግሞ ኢየሱስ ሁለት ሺህ ኣመት ሙሽራ ነው አላችሁ ሙሽራ ሁልጊዜ ሙሽራ አይሆንም
  የሙሽራነቱ ወቅት ያልፋል የክርስቶስ ሙሽራነት እስከ መስቀል ነበር የሰው ደግሞ ሙሽራነት ወንድ ከሆነ ከሚስቱ
  ሴት ከሆነች ለባል ነገር ጊን ሁልጊዜ ሙሽራ አይደሉም በተጨማሪም ደቀመዛሙርቱ ያልጾሙት ሙሽራው ከነሱ ጋር ስለነበር ነው
  ሙሽራው ሲሄድ ግን መጾም ጀምረዋል ታዲያ ጾምን ቀድሱ ሲል ያስተማረ ቅዱስ ቃለ ማን ተቺ አደረጋችሁ ሰላማዎች እናንተ ሰላማ ሳትሆኑ የዛ የክፉው ጠላም ዲያቢሎስ (አርዮስ)ልጆች ናችሁ

  ReplyDelete