Friday, June 3, 2011

የማይሞተው ሞተ - Read PDF

መላከ ገነት ጽጌ የሚባሉ ሊቅ መሐለ እግዚአብሔር ለዳዊት በጽድቅ ወኢይኔስሕ ማለት እግዚአብሔር በእውነት ለዳዊት ማለ አይጸጸትም  የሚለውን ንባብ ሲተረጉሙ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አቋረጧቸውና እግዚአብሔር ከርሱ በላይ ያለ በማን ሊምል ነው ? አሏቸው። መላከ ገነትም ፈጥነው እኔ ልሙት ብሎ ማለለታ ጃንሆይ  ብለው መለሱ።  ጃንሆይም መማር እንደ ጽጌ ነው  አሉ ይባላል።
ሰው ነገሩን ለማጽናት ከእርሱ በሚበልጠው ይምላል፤ ቢያጎድል የዚያን የበላይ ወገን ማንነት እንዳቃለለ ተቆጥሮበት ከመሐላ ተቀባዩና ከማለበት ወገን ጋር ይጣላል። በራሱ ሲምል ደግሞ አለመፈጸሙ እራሱን እንደመካድ ይቆጠርበታል። እግዚአብሔር ለዳዊት ሲምል ከእርሱ በላይ ማንም ስለሌበት በራሱ ማለለት። እኒህ ሊቅ ግን የክርስቶስን ቤዛነት ለመግለጥ አዲሱን ኪዳን ለማወጅ እኔ ልሙት ብሎ ማለለታ አሉ። በሀገራችን እኔ ልሙት ብሎ ነገርን ማጽናት የመጨረሻው መሐላ ነው። እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ልሙት ብሎ ምሎ በመስቀል ላይ ሞተልን በዚህም አዲስ ኪዳን ተመሠረተ።
እኔ ፤ ልሙት ብሎ የሚምል ብዙ ወገን አለ። ምሎ ግን የሞተ ከክርስቶስ በቀር ማንም የለም። ሁላችንም ብንሆን የወዳጅ ማስታወቂያ በየጊዜው እናወጣለን። የምንፈልገው ወዳጅ ቅን የሆነ፣ በፍጹም ነፍሱ የሚወደኝ፤ እራሱን የሚሰጠኝ፤ በምክሩ የሚደግፈኝ፤ በርኅራሄው የሚያጸናኝ፤ ጠባየን የሚችልልኝ፣ በመከራ ቀን አብሮኝ የሚቆም፣እስከ ሞት የሚወደኝ፤... እንላለን። ይህንን ደሞዝ በነጻ የሆነ ማስታወቂያ ስናወጣ ግን ሦስት ነገሮችን ለማሰብ ጊዜ አላገኘንም። የመጀመሪያው ይህንን ማስታወቂያና መስፈርት ያወጣነው ራሳችን ማንነታችንና ኑሯችን የተቋቋመው በዚህ መስፈርት ነው ወይ? ሁለተኛ ይህን መስፈርት ያሟላ ክርስቶስ ብቻ ሲሆን እርሱም የምንፈልገው ሳይሆን የተፈጸመና የምናምነው ፍቅር ነው። ሦስተኛ ከክርስቶስ ብቻ የሚገኘውን ከፍጡር ስንፈልግ በማጣት ለሚገጥመን ተስፋ መቁረጥ ዋስትና እንደሌለን ማሰብ አልቻልንም።
የመሥዋዕት ፍቅር የትም አይገኝም። በዓለም ላይ ሜዳ ሜዳውን የሚዘል ፍቅር ሞልቷል፤ ተራራው ላይ የሚሸከም፣ ሸለቆው ላይ የሚሞላ ፍቅር በዓለም ላይ ውድ ነው። የጎንደር አዝማሪ፥
ቢቆጡሽ አለቀስሁ
ቢመቱሽ ደም ወጣኝ፤
ብትሞችስ አልሞትም
ድሀው ምን በወጣኝ
በማለት ሐቁን ተናግሯል። የዚህ ፍቅር ፍጻሜው በመከራ ቀን መጣጣል ነው። የማይዘልቅ ማህበር በጠጅ ይጀመራል  እንዲሉ ኋላ ቅራሪው ላይገኝ! በክፉ ቀን የሚዋስ ፍቅር ውድ ነው። እናትም የማትቆምበት ቀን አለ። በአስከፊ እልቂቶች ሰዓት ሁሉም ራሱን ለማዳን ብቻ  ይሮጣል። እናቶች እንኳ ልጃቸው ከፊታቸው ወድቆ ጥለውት ያልፋሉ። ለቅሶና ዕንባ አያሰሙም። ከእልቂቱ ቀጠና ወጥተው የወገን ዘመድ እህል ውሃ ሰጥቶ ሲያስጥላቸው ያለቁት ወገኖቻቸው ትዝ ይሏቸዋል። ማልቀስና ወይኔ ማለት ይጀምራሉ። እየዬ ሲደላ ነው ሲደላ ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሞታችንን ወስዶ ሕይወቱን ሰጥቶናል፤ እራስህን አድን  እያሉ ሲዘባበቱበት እራሴን ባድን ዓለም አይድንም  ብሎ የራሱን ሕይወት አደጋ ውስጥ ከቶ እኛን አድኖናል። ለእኔ የማይል ምን ዓይነት ፍቅር ነው! ግዳጅ ሳይኖርበት ስለ ፍቅር መቍሰል ምን ዓይነት ቸርነት ነው!
ይህ ጌታ በመዋዕለ ስብከቱ፦ ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከማኖር ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም  ዮሐ 15፥13 በማለት  የፍቅር የመጨረሻው መግለጫ ነፍስን ስለ ወዳጅ መስጠት መሆኑን ተናግሯል። እርሱ ግን ከዚህ ድንበር አልፏል። ነፍሱን የሰጠው በኃጢአት ምክንያት ጠላቶቹ ለሆንነው ለእኛ ነውና። በዚህ ፍቅር የተደነቀው ጳውሎስ፦ ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቷልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምን አልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ስላን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል  ብሏል ሮሜ 5፥6-8።
የማንቆጣጠረው ነገር በውስጣችን አለ። ይህ አንድ ነገር አይደለም ብዙ ነው። ለምሳሌ የልባችንን እንቅሥቃሴ እኛ የምንቆጣጠረውና አስበንለት ይህን ያህል ይምታ የምንለው አይደለም። ያጣን ሰው ገሸሽ ማለት፤ ለደካማ ፊትን ማዞር ከማንቆጣጠረው ስሜታችን አንዱ ሆኗል። ሰውዬው ለሥራ ብሎ አሮጌ ልብስ ለብሶ ስናየው ያጣ መስሎን በምናገኘው ሰርጥ ገብተን እናመልጣለን። ያው ሰው አጊጦ ስናየው ደግሞ ሁለት አስፋልት ተሻግረን ካልጋበዝሁህ ብለን ከሥረን እንለያያለን። ይህ የማንቆጣጠረው ውድቀታችን ሆኗል ክርስቶስ ግን የሞተው እኛ ሰላምታ ለነፈግናቸው ደካሞች ነው። የሞተው ለኛ ነው ሮሜ 5፥6። ደካማ፤ ኃጢአተኛ፤ ጠላት ሦስቱም የሚወደዱ ክፍሎች አይደሉም።    
     ጻድቅ ማለት እውነተኛ ማለት ነው። ለእውነተኛ እንደነቃለን እንጂ እራሳችንን ለመስጠት አንግደረደርም። ለምሳሌ ኔልሰን ማንዴላን እንደ እውነተኛ እናየዋለን። ግን ዛሬ የሚሞትለት እባካችሁ ቢባል መከራን ለ27 ዓመታት ያውቀዋልና እርሱ ቢሞት ይሽላል ብለን ዘወር እንላለን እንጂ የሚሞትለት አይገኝም። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና  ያለው ለዚህ ነው ሮሜ 5፥7። ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል  ጳውሎስ እዚህ ጋ ተጠራጠረ። ያ ቸር ሰው በረሀብ ቀን ያበላን፤ ደብቆ የሰጠን፤ ሰው ሲርቀን ሰው የሆነልን፤ በክፉ ቀን በሩን የከፈተልን ነውና ለእርሱስ መግደርደር አይቀርም። አንድ ቄስ ሩቅ አገር ቀብር ሄደው ሲመለሱ የቅርቡን ለቅሶ የማልሄደው ሰው ክፍለ ሀገር ቀብር ልደርስ ሄድኩኝ። ምን ላርገው?  የበላ ሆድ መከረኛ ነው  ብለዋል። ቸር ሰው ያግደረድራል። ክርስቶስ ግን የሞተው ለጻድቅም ለቸርም አይደለም። ገና ኃጢአተኞች ለሆንን ለእኛ ነው። የኃጢአት ቀስት ላላለቀበት መበደል በቃኝ ላላለ ሰው ክርስቶስ ሞተ። ይህ፣ ሰው ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር ሳይሆን እግዚአብሔር ለሰው ያለውን ፍቅር ያሳያል። ይህ ፍቅር በራሱ በእግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ፣ ምክንያቱ ማፍቀር ብቻ የሆነ ፍቅር ነው። እኛ የምናፈቅረው በመስፈርት ነው። ያለ መስፈርት ያፈቀረ ምንኛ ቡሩክ ነው!
     ሰዎች የሰጡንን ፖስት ካርድ ከቴሌቪዥናችን በላይ ከብፌውም አናት ላይ አስቀምጠነው ባየነው ቍጥር የወዳጃችንን ፍቅር እናዘክራለን። በሚያስበን ወዳጃችን ፍቅር መነካትና እንደ ገና መታደስ እንጀምራለን። ሰዎች የሰጡንን ወርቅ ሁልጊዜ ከአንገታችን አንለየውም፡፤ ለማንም አልሰጥም ማስታወሻዬ ነው እያልን የምንናገርበት ነው። ይህ ውለታም እንቅልፍ ይነሣናል። ነፍሱን የሰጠንን ጌታ ግን ፍቅሩን ረስተነዋል። ይህ አሳዛኝ ምርጫ ነው!
    ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተው መዳናችን በሌላ ሊፈጸም ስላልቻለ ነው። በብሉይ ኪዳን ቤዛ የሚሆኑት ንጹሐን በጎች ነበሩ። በደለኛውን የምትወክለው ያች በግ ንጹሕ ነበረች። ቤዛ ንጹሕ መሆን አለበትና። ስለ በደለኛው በደል የሌለበት ሲወከል ይህ ቤዛነት ይባላል። ከሰው ወገን ንጹሕ አልተገኘም። ጻድቅ የለም እንድስ እንኳ  እንደተባለ ሮሜ 3፥11። ስለዚህ ሰውን ሰው ቤዛ ሊሆነው ባልቻለ ጊዜ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ዳግመኛም ንጹሕ ሆኖ በመሞት ቤዛችን ሆነልን። ለዚህ ነው ቤዛ ለመሆን አምላክነት ያሻዋል የሚባለው።
    ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው። ሰው ብቻ ቢሆን ሊያድነን ባልቻለ ነበር። ምክንያቱም በፍጡር ሞት ዓለም አይድንምና። አምላክ ብቻ ቢሆንም ሞቶ ዕዳችንን መክፈል ባልቻለ ነበር ምክንያቱም መለኮት በባሕርዩ አይሞትምና። ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በሆነው በክርስቶስ ግን መዳናችን ተፈጸመ ለዚህ ነው በሃይማኖተ አበው እንዲህ የተባለው፦ የሕይወታችን መገኛ የሚሆን የክርስቶስ ሞት የእኛን ሞት ወደ ትንሣኤ እንደለወጠ እናምናለን ክርስቶስም ሞትን አጥፍቶ የማታልፍ ትንሣኤን ገለጠ፤ ከሰውም ወገን ማንም ማን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፤ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፤ ዳዊት በሕያውነት የሚኖር፤ ሞትንም የማያያት ሰው ማን ነው? ነፍሱን  ከሲኦል ሥጋውንም ከመቃብር የሚያድን ማን ነው? ብሎ እንደተናገረ መዝ 88፥48። ራሱን ማዳን ያልተቻለው ሌላውን ማዳን እንዴት ይችላል? አንድ ራሱን ሊያድን ያልቻለስ ዓለምን ሁሉ ሊያድን እንደምን ይችላል? ኃጢአት በሰው አድሮ ይኖር ነበርና ሞትም ይከተለው ነበርና... ከአዳም አንስቶ እስከ ሙሴ ሰዎችን በአዳም በደል አምሳል ያልበደሉ ሌሎችንም ሞት እንደ ገዛቸው ተናገረ፤ መጀመሪያ የበደለ አዳም ነው፤ አዳምንም በበደለ ጊዜ  የሚመስሉትን ያን ጊዜ ወለደ  [ዘአቡሊዲስ ም 42፥6-9 ገጽ 145]
  ታዲያ የሚከብደው የቱ ነው? ክርስቶስ ስለኛ በደለኛ መባሉ ነው? ወይስ እኛ ስለ ክርስቶስ ጻድቃን መባላችን ነው? ክርስቶስ የማይገባውን ሞት የሞተው የማይገባንን ሕይወት እንድናገኝ ፍርድ እንዲስተካከል ነው። ጻድቁ እጅግ ከተኮነነ ሚዛኑ ልክ የሚሆነው ደካሞቹ እጅግ ስንጸድቅ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው  [2ቆሮ 5፥21] ብሏል።
   ዓለም ሳይፈጠር፣ ዘመን ሳይቆጠር፣ ታሪክ ሳይመረመር፣ የነበረው እግዚአብሔር ወልድ የፈጠረውን ሥጋ ተዋሕዶ ዘመን ተቆጠረለት፤ ከእርሱ አስቀድሞ ማንም አልነበረም። ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አልፋ[መጀመሪያ] የተባለው በሥጋ ልደቱ ዮሐንስ መጥምቅ በለጠው ተባለ። የማይሞተው መለኮት በለበሰው ሥጋ ሞተ ተባለለት። የቃል ክብሩን ለሥጋ፣ የሥጋን ትሕትና [ውርደት] ለቃል የሰጠ፤ እኛን ወንድሞቼ ብሎ ሲጠራን ያላፈረብን እንዴት ድንቅ ነው!
     በኪሩቤል ጀርባ የነገሠው በከብቶች መብል[ሣር] ላይ መተኛቱ ከላይ ሳይታጣ ከታች መወለዱ፤ ሁሉን ይዞ ሳለ በናቱ ክንድ መታቀፉ፣ እንዴት የማይመረመር ምሥጢር ነው! ኤልያስን በእሳት ሰረገላ የወሰደ ከጴጥሮስ ጀልባ መለመኑ፤ በአእላፋት መላእክት የተከበበው እንደ ብቸኛ መታየቱ፤ አሮንን ለክህነት የጠራው በሐናና በቀያፋ ፊት መቆሙ፣ እኛን ውሉደ እግዚአብሔር [የግዚአብሔር ልጆች] ያሰኘን የእግዚአብሔር ልጅ አይደለህም ተብሎ መከሰሱ ለሙሴ አንደበት የሆነው በችሎት ፊት ዝም ማለቱ፤ ለመበለቲቱ የሚፈርደው በጲላጦስ ፊት ፍርድ ማጣቱ፣ የተራቆተውን ስንት ጀርባ ያለበሰ ልብሱን መገፈፉ፣ ዓለምን የያዜው መስቀል መሸከሙ፣ የወደቁትንያነሣ ደፋ ቀና ማለቱ በመገበው በሰው እጅ በጥፊ መመታቱ፣ ባከበረው ሰው መዋረዱ፣ በፈወሰው በሰው እጅ መቁሰሉ፣ እንዴት ረቂቅ ነው!
    ሙታንን ቀስቅሶ ለወላጆቻቸው የሰጠ ለሞት መነዳቱ፣ ሰውን በፍቅር የቀረበ በገመድ መታሠሩ፣ በሰንፔር ድንጋይ ላይ የተቀመጠው በመስቀል ላይ መዘርጋቱ፣ የፍጥርት እራስ የእሾህ አክሊል መሸከሙ፣ የቤተ ክርስቲያን ሙሽራ  በደም ማጌጡ፣ ረሐብተኞችን በበረከት የመገበ እጅ በችንካር መያዙ፣ ከገነት ጫካ እስከ ቀራንዮ ሰውን የፈለጉ እግሮች በምስማር መጠረቃቸው፣ አቤት እንዴት ግሩም ነው!
   ስለኔ መዳን ራስህን በአደጋ ውስጥ ያሳለፍህ፣ ከመንግሥትህ የራቅሁትን ልትመልስ የሞትን ግዛት ያቋረጥህ፣ እኔን የወደደ ልብህ በረጅም ጦር የተወጋ፤ ለእኔ ተስፋ ልትሰጥ ቀትሩ የጨለመብህ፤ እኔን ከጻድቃን ጋር ልትደምር ከወንበዴዎች ጋር የተቆጠርህ፣ ለእኔ ወዳጅ ልትሆን የገንዛ ደቀ መዛሙርትህ የካዱህ፣ ለእኔ ውቅያኖስና ሐይቅን ወንዝና ምንጭን ፈጥረህ ለጥማትህ ሆምጣጤ የቀረበልህ፣ ከስቃይህና ከሞትህ በላይ የገዳዮችህ ነፍስ አሳስቦህ ይቅርታን የለመንህ፣ እኔ ተስፋ እንዳገኝ ወንበዴን ያጸደቅህ፣ የሞትኩትን ልታጸድቀኝ የሞትክ፣ የሚገባኝን ሞት አሳልፈኽልኝ፣ የማይገባህን ሞት የሞትኽልኝ፣ ኑሮህም ሞትህም ቤዛ የሆነኝ፣ ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ አመሰግንሃለሁ። የማትሞተው ለእኔ ሞተሃል፣ እንዲህ ያለ ፍቅር በዘመኔ አላየሁም፣ እንኳን እስከ ሞት የሚወደኝ ፍቅሬንም የሚረዳልኝ አጥቻለሁ። እንኳን የሚሰዋልኝ የሚኖርልኝ አላገኘሁም፣ እንኳን የሚኖርልኝ የሚሰነብትልኝም የለም፣ አንተ ግን ለኔ ሞተሃል።ትርጉሙ የራስህ ፍቅር ብቻ ነው። ባንተ መስዋዕትነት የባሕርይ አባትህን እና የባሕርይ ሕይወትህን የመንፈስ ቅዱስን ፍቅር አያለሁ። አሜን!

አባሰላማ

2 comments:

  1. ሲጠቃለል ዛሬስ ኢየሱሰ ያማልደናል ወይስ አያማልደንም

    ReplyDelete
  2. ቃለ ህይወት ያሰማልን! The work of the Lord is amazing and this paper puts it beautifully

    ReplyDelete