Friday, August 26, 2011

ማኅበረ ቅዱሳን የራሱ ብቻ እንጂ የቤተክርስቲያኒቱ ልሳን ሊሆን አይችልም - - - Read PDF

ጥናቱ የማኅበረ ቅዱሳን ወይስ የቤተ ክርስያኒቱ በሚል ርእስ በነጋድራስ ጋዜጣ ሐምሌ 1/2003 ለወጣው ጽሑፍ፣ ትዝብት ዘቀኖና “የጥናት መጽሔት ልሳን አይደለም!” በሚል ርእስ በዚሁ ጋዜጣ የሐምሌ 8/2003 እትም ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መላሹ በመጀመሪያ በመምህር በቃሉ የተጻፈውን የሕጋዊነት ጥያቄና የቀረቡትን ማስረጃዎች በሚያመዛዝን አእምሮ ከመመለስ ይልቅ፣ በጽሑፉ ፈጽሞ ያልተነሡ ጉዳዮችን መምህር በቃሉ እንዳነሡ አስመስለው በማቅረብ ጉዳዩን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመውሰድ ጥረዋል፡፡ ይህም የተለመደ የማኅበረ ቅዱሳን አካሄድ ስለ ሆነ፣ ችግሩ ከቤቱ (ከማኅበረ ቅዱሳን) ነው ከማለት በቀር ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡ ምላሽ ብለው የሰጡት አስተያየትም ሌሎች ጥያቄዎችን የሚያስከትል በመሆኑ ይህ ምላሽ ትኩረቱን በነዚያ ላይ ያደርጋል፡፡ 

ከጽሑፉ ርእስ ብንነሣ፣ መምህር በቃሉ የጥናት መጽሔት ልሳን ነው ፈጽሞ አላለም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የጥናት መጽሔት ለምን ያዘጋጃል የሚል ሐሳብም ፈጽሞ አላነሣም፡፡ እርሳቸው ስፍራ ባይሰጡትም አንባቢ ግን እንደሚያስታውሰው “እንዲህ ዐይነቱ የጥናት መጽሔት መዘጋጀቱ በራሱ ጥሩ ጅምር በመሆኑ ማኅበረ ቅዱሳን ሊመሰገን ይገባል፡፡” ብሏል፡፡ ሌሎች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ ምሁራንና ተመራማሪዎችም ድልብ ዕውቀትና መረጃ በሚገኝባት በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ከባህል፣ ከታሪክ፣ ከቋንቋና ከመሳሰሉት አንጻር ጥናትና ምርምር ማድረጋቸው እጅግ አስደሳች ነው፡፡ ጥናቱ ጠቃሚ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ የተደረገ የአጥኚው ክፍል እንጂ ጥናቱ የተደረገባት የቤተ ክርስቲያኒቱ ነው ማለት የባለቤትነት ጥያቄ ያስነሣልና አያስኬድም፡፡ በተጨማሪም የጥናቱ መነሻ ሐሳብ የመነጨው ከአጥኚው በመሆኑና የራሱም ግብ ስለሚኖረው፣ ምንም ጥናቱ በመረጃ ላይ የተደገፈ ነው ቢባልም ከቤተ ክርስቲያኒቱ እይታ አንጻር ሌላ መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ጥናት ሲያደርጉ ቤተ ክርስቲያኒቱን ማስፈቀድ አለባቸው የሚል ሰው ግን ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፡፡ ይሁን እንጂ ትዝብት ማጠየቂያ የሚሆን ሐሳብ ቢያጡ ነው መሰል፣ ይህን እጅግ በጣም የወረደ “መከራከሪያ” በጽሑፋቸው ውስጥ ሰንቅረው ራሳቸውን ትዝብት ላይ ጥለዋል፡፡

የመምህር በቃሉ ጥያቄ የጥናት መጽሔቱን ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ማኅበረ ቅዱሳን በመሆኑ የጥናቱ ባለቤት እርሱ ራሱ ነው፤ በጊዜው በስምዓ ጽድቅና በሐመር ልሳኖቹ ላይም ማኅበረ ቅዱሳን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጥናት መጽሔት መሆኑን ገልጿል፡፡ ነጋድራስ ጋዜጣ ግን “ቤተ ክርስቲያኗ የጥናት መጽሔቷን ይፋ አደረገች” ለምን ይላል ነው፡፡ ምናልባት ጋዜጣው ቤተ ክርስቲያኒቱ ማለት ማኅበረ ቅዱሳን፣ ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሚል አመለካከት በቅንንትም ይሁን በሌላ ምክንያት ይዞ ሊሆን ይችላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንስ በራሱ ልሳኖች ላይ የእኔ ያለውን የጥናት መጽሔት በነጋድራስ ጋዜጣ ላይ የቤተ ክርስቲያኗ ሲባልለት ለምን ዝም አለ? ነው እንጂ የጥናት መጽሔት ልሳን ነው የሚል ሐሳብ ፈጽሞ አላነሣም፡፡ ከዚህ ይልቅ ሐመርና ስምዓ ጽድቅ የማኅበረ ቅዱሳን እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳናት አለመሆናቸውን፣ አንዳንዶች ግን ባለማወቅ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳኖች አድርገው እንደሚወስዷቸው በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል፡፡ ትዝብት በዚህ ላይ ምንም ትንፍሽ አላሉም፤ ምናልባት ስለ ልሳን እመለስበታለሁ ብለዋልና ያኔ ብቅ ሲሉ እንገናኝ ይሆናል፡፡

ሌላው በጥቅምት 5/2003 ዓ.ም. ለወጣ ዜና ከ10 ወራት በኋላ ምላሽ መሰጠቱ ጽሑፉ ቅንነት የጎደለው መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ ይህ በራሱ ትክክል አይደለም፡፡ ይህ ለእርስዎ የቅንነት ጉድለት ከሆነ እንዲህ ማሰብ መብትዎ ነው፡፡ ሆኖም መምህር በቃሉ ሐሳቡን በነጻ መቼና እንዴት መግለጽ እንዳለበት የሚወስነው እርሱ እንጂ ትዝብት አይደሉም የሚወስኑለት፡፡ ቅንንት የሚለካው ደግሞ በጊዜ ርዝማኔ አይደለምና በቶሎ የተጻፈ ቅን፣ ዘግይቶ የተጻፈ ደግሞ ቅንነት የጎደለው ተብሎ ሊፈረጅ አይገባውም፡፡ መቼም ይጻፍ መች የተጻፈው ነገር በያዘው እውነት ነው ሊለካ የሚገባው፡፡ ይህ ለእርስዎ ካልተስማማዎና ተሸፍኖ ታልፎ የነበረው ነገር ዘግይቶም ቢሆን ስለ ተገለጠብዎ የቅንንት ጉድለት ከሆነ እንዲህ ማሰብ መብትዎ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ መምህር በቃሉ ከዐሥር ወራት በኋላ ለምን ይህን ጽሑፍ እንዴት ሊጽፉ ቻሉ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ነጋድራስ ጋዜጣስ በዚህ በከረመ “ቋንጣ ዜና” ላይ የተጻፈን አስተያየት ለምን አወጣ ብለው ዝግጅት ክፍሉን ቢጠይቁ ይበልጥ ምላሽ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡

“በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ለመንቀሳቀስ ከቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተሰጠው አንድ ብቸኛ ማኅበር ጽፎ ያሳተመውና ያሠራጨው የኅትመት ውጤት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን ተብሎ ለመጠራት ሕጋዊ መሠረቱ ምን እንደ ሆነ አልነገሩንም፡፡” ብለዋል፡፡ በቅድሚያ “በቅዱስ ሲኖዶስ ሥር ለመንቀሳቀስ ከቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተሰጠው አንድ ብቸኛ ማኅበር” የሚለው አገላለጽ ሆን ተብሎ አንባቢን ለማሳሳት የቀረበና ለማኅበሩ የገጽታ ግንባታ ፍጆታ ያዋሉት ሐሰተኛ መረጃ ነው፡፡ ይህ ግለሰቡ እንደ ግለሰብ ያንጸባረቁት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ማኅበሩ አባልነታቸው ወይም ደጋፊነታቸው ማኅበሩ ቀን ከሌት የሚያስበውና የሚያልመው መዋቅራዊ ስፍራ እንደ ሆነ ይታወቃል፡፡ እውነታው ግን የማኅበሩ ደንብ በሲኖዶስ የጸደቀ፣ ማኅበሩ ግን በሲኖዶስ ሥር ሳይሆን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማዳራጃ መመሪያ ሥር የተቋቋመ፣ በመምሪያው ሥር ከሚገኙት ማኅበራት መካከልም አንዱ ማኅበር ነው እንጂ ብቸኛው ማኅበር አለመሆኑ ነው፡፡ እንደ እርሱ ባለ ሰፊ መዋቅር ከእርሱ በፊት ሃይማኖተ አበው በቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ተሰጥቶት ይንቀሳቀስ እንደ ነበርም ከቶ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ ስለዚህ አለአግባብ ከእጅዎ ሊያገቡት ያሰቡት ሪከርድ የሚገኘው በሃይማኖተ አበው እጅ መሆኑን ተረድተው “ብቸኛው” ያሉትን ቅጽል ከማኅበሩ ላይ ያንሡ!!

እስኪ እርስዎም ይጠየቁና፣ አንድ ማኅበር በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ፈቃድ ተሰጠው ማለት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን ሆነ ማለት ነው የሚለው ንድፈ ሐሳብዎ ምን ሕጋዊ መሠረት አለው ይላሉ? አንድ ማኅበር በአንድ ሕጋዊ አካል ሥር እንዲንቀሳቀስና ዐላማውን እንዲያሳካ ጥያቄ አቅርቦ ተቋቋመ ማለት ለራሱ ህልውና ሕጋዊ ከለላ አገኘ ማለት ነው እንጂ፣ ሕጋዊ ከለላ ለሰጠው አካል ልሳን ሆኖ ያገለግላል ማለት አይደለም፡፡ ልሳን ይሆን ዘንድ እርሱ ጠይቆ ሳይሆን ሕጋዊ ከለላ የሰጠው አካል ያስፈልገኛል፣ ልሳን ይሆነኛል ብሎ ያቋቋመው ክፍል መሆን አለበት፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ያስፈልገኛል ብላ ያቋቋመችው ማኅበር አይደለም፤ በአገራችን የነበረውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎና በቤተ ክርስቲያኒቱ የነበረውን ክፍተት ተጠቅሞ፣ ታሪካዊ ተገዳዳሪውን ሃይማኖተ አበውን ገፍቶ በራሱ ጊዜ የተቋቋመና ቤተ ክርስቲያኒቱን ጠይቆ ሕጋዊ ከለላ ያገኘ ማኅበር ነው፡፡ ስለዚህ ለእርስዎ ባይዋጥልዎም ማኅበሩ በተሰጠው ሕጋዊ ከለላ ስር ሆኖ የሚያስተላልፈው የራሱን መልእክት እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊሆን የሚችልበት ምንም ሕጋዊም አመክንዮኣዊም መሠረት የለም፡፡ ካለ ግን ሊነግሩን ይችላሉ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን የመሆን ብቃት የሌለው ማኅበር ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዐት ውጪ የተሳሳቱና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚጥሱ ጽሑፎችን በማውጣቱ የተለያዩ ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የተሰጡትን ማሳሰቢያዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፡- በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና የሌለና ካሁን ቀደም ያልተሰማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጽዋማት 8 ናቸው ብሎ በነሐሴ 1987 ሐመረ ተዋሕዶ ላይ ለጻፈው ዘገባ፣ “ጾመ ጽጌ የፈቃድ እንጂ ከሰባቱ አጽዋማት የሚቈጠር ስላይደለ … አስቸኳይ እርማት እንዲደረግበት” አዝዞ፣ በቀጣይ የማኅበሩ ኅትመቶች ሁሉ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አማካይነት እየታረሙ እንዲወጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ በቊጥር 6738/8513/87 በ2/13/87 ዓ.ም. ለማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡ በተጨማሪ ደጋግሞ የሰዎችን ስም በማጥፋት ሥራ በመጠመዱ ጋዜጣውንና መጽሔቱን በሊቃውንት ጉባኤ እያስመረመረ እንዲያወጣ በተደጋጋሚ ታዟል፤ - ማኅበሩ አሻፈረኝ ቢልም፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለው በሕጸጽ የተሞላና ራሱን አለቦታው የሰቀለ አልታዘዝ ባይ ማኅበር እንኳን ለቤተ ክርስቲያቱ ልሳን ሊሆን ቀርቶ በቤተ ክርስቲያቱ ሥር ሆኖ ለሚያወጣቸው ጽሑፎችም ሃይማኖት እንዳያፈርስና ሥርዐት እንዳይጥስ ጠባቂና ተቆጣጣሪ የሚያሻው ወገበ ነጭ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ሌላው የትዝብት ሥጋት፣ ጥናቱ የማኅበረ ቅዱሳን እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ አይደለም መባሉ፣ ማኅበሩን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ለመነጠል ታስቦ የተደረገ ነገር ነው የሚል ነው፡፡ በመሠረቱ ለማለት የተፈለገው ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን አባልነቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ይነጠል አይደለም፤ ነገር ግን እርሱ ማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ማለት ደግሞ እርሱ ተደርጎ እንዲወሰድለት የሚያደርገው ጥረት ተነጥሎ ይታይ ነው፡፡ አሁንም በዚሁ አቅጣጫ ማኅበሩና ቤተ ክርስቲያኒቱ ተነጣጥለው መታየት አለባቸው፡፡ እርስዎና ማኅበርዎ ግን ይህን በፍጹም አትፈልጉትም፡፡

ማኅበሩ እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገጽታ እየገነባ እንደ ሆነ ተናግረዋል፡፡ የማንን ገጽታ እየገነባ ነው የሚለው ግን ለተመልካች ቢተው መልካም ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በሚሠራው ሥራ የራሱን እንጂ የቤተ ክርስቲያቱን ገጽታ ገንብቷል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሁሉም ሰው ማኅበሩ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ለማኅበሩ እንጂ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቦታ ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡ እንዲያውም ማኅበረ ቅዱሳን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ፣ እርሱ ከሌለ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደማትኖር ያህል እንዲታይ እያደረገ የራሱን ገጽታ ከመጠን በላይ እየገነባና ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ ልዩ መምሪያዎችና ክፍሎች የሌሉ ያህል እንዲቆጠሩ እያደረገ ነው ቢባል ምንም ስሕተት የለበትም፡፡ በዚህ ምክንያት ከአንዳንድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችና ክፍሎች ጋር ግጭት ውስጥ የገባበትን ሁኔታ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፡- ማኅበሩ የልሳኖቹን የስምዐ ጽድቅንና የሐመር 10ኛ ዓመት አስመልክቶ የካቲት 20/1996 ዓ.ም. አዘጋጅቶት በነበረው ዐውደ ጥናት ላይ፣ የራሱን ልሳኖች ከፍ ከፍ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን የሆነውን ዜና ቤተ ክርስቲያንን ደግሞ ዝቅ ዝቅ እያደረገ ማቅረቡን ተከትሎ፣ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በ1996 ዓ.ም. የመጋቢትና ሚያዝያ ዕትሙ “የ60 ዓመቱ ሽማግሌ በ10 ዓመቱ ሕፃን ተዘለፈ” በሚል ርእስ የማኅበሩን ውስጠ ማንነትና በሃይማኖት ካባ የተሸፈነውን ድብቅ ዓላማውን የሚያጋልጥ የሰላ ሂስ ሰንዝሮበታል፡፡

ሌላው ነጥብ፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ በካቶሊክና በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከአንዳንድ የየራሳቸው አስተምህሮዎችና ሥርዐቶች በቀር፣ በመሠረታዊ የክርስትና ትምህርት ልዩነት የለም የተባለውን ሐሳብ መቃወምዎ ነው፡፡ ይህም የክርስትና መሠረታዊ ትምህርት ፈጽሞ ያልገባዎና ማኅበረ ቅዱሳን ምርቱን ከግርዱ ሳይለይ “የክርስትና ትምህርት” ብሎ የሰጠዎን ሁሉ ተቀብለው እርሱኑ መልሰው የሚያስተጋቡ የአንድ ማኅበር ተከታይ ብቻ መሆንዎን ያሳያል፡፡ መሠረታዊው የክርስትና ትምህርት የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነው፡፡ ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠረት እንደማይችል (1ኛቆሮንቶስ ምዕራፍ 3 ቁጥር 11) እና እንደማይገባ (ዕብራውያን ምዕራፍ 6 ከቁጥር 1-2) ተጽፏል፡፡ ከሐዋርያት በኋላ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተማሩት ትምህርትም ከሐዋርያት የተላለፈውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርትና በእርሱ ላይ የተመሠረተውን ትምህርት ነው እንጂ አዲስ ትምህርት አይደለም፡፡ እምነታቸውንም ጸሎተ ሃይማኖት በተሰኘው የሃይማኖት ውሳኔ ገልጠዋል፡፡

የሚያድነው እምነት በትምህርተ ሥላሴ (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ብሎ) እና በትምህርተ ሥጋዌ (አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፤ አዳኝ ነው ብሎ) ማመን ነው፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም የተከራከሩት በዋናነት በእነዚህ የሃይማኖት ትምህርቶች ላይ ነው፡፡ የክርስትና መሠረቱም ይኸው ነው፡፡ ሌላውም ሁሉ ከእያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ባህልና ሥርዐት አንጻር የሚከናወን ከመሆኑ በቀር፣ የክርስትና መሠረታዊ ነገሮች በሁሉም ዘንድ አሉ፡፡ በተጨማሪም አንዲቱ ከሌላዋ የምትለይባቸው የራሷ ትምህርቶችና ሥርዐቶች አሏት፡፡ በአንዲቱ ዘንድ ኖረው በሌላዋ ዘንድ ግን የሌሉ ትምህርቶችና ሥርዐቶችም ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ግን ዋና የክርስትና ትምህርቶች ተደርገው ሊወሰዱ አይችሉም፡፡ በዋናው መሠረታዊ እምነት አንድ የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትም ልዩነት ሊፈጥሩባቸው አይገባም ነበር፡፡

የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ማንነት ያልገባቸው ወገኖች ግን ከጥንት ጀምሮ አንድ የሚያደርጋቸውን የክርስትና ትምህርት ሳይመለከቱ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚል ለሥልጣን፣ እንደ ራሳቸው ትምህርትና ሥርዐት ብቻ ሊወሰድ የሚችለውን ግላዊ ትምህርትና ሥርዐት ለልዩነት ምክንያት አድርገው በመውሰድና በሌሎችም ምክንያቶች አንዲቱን ቤተ ክርስቲያን ከብዙ ክፍል ከፋፍለዋታል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት አንድ ስለሆኑባቸው ነገሮች ከመናገር ይልቅ፣ አንድ የሚያደርጋቸው አንድም ነገር እንደሌለ አድርጎ በማቅረብ ልዩነትን ሲያራግብ ነው የኖረው፡፡ እርስዎም የዚህ የልዩነት መንገድ ተጓዥ እንደ ሆኑ ግልጽ አድርገዋል፡፡ አመለካከትዎ በመንግሥተ ሰማያት ቦታ ያለው ለእርስዎ ማኅበር አባላት ብቻ እንደ ሆነና ሌሎች ግን ቦታ እንደሌላቸው የሚያጸባርቅ ይመስላል፡፡ ሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናት እንደዚሁ ቢያስቡ ተሳስተዋል፡፡ በምድር እንጂ በሰማይ የእምነት ተቋማት ሁሉ በያዙት ስያሜ ዕውቅና አላቸው ብሎ ማሰብም እግዚአብሔርን እንደ ሰው መቁጠር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ የምትታወቀው አንዲት ቤተ ክርስቲያን ስትሆን እርስዋም በሁሉ ዘንድ ያለች ናት፡፡ ይህ ነው መጽሐፍ ቅዱስም የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ያቆዩልን እውነት፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ግን የምታስበው እርስዎ እንደሚሉት አይደለም፡፡ ልዩነቶች ቢኖሩም አንድ የሚያደርጉን ነገሮች እንዳሉ ስለምታምን፣ ልዩነቱ እንደ ተጠበቀ ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር መቀራረብ ስለሚፈጠርበት ሁኔታ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም የጌታ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያን እንድትከፋፈል ሳይሆን “አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ” (የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 10 ቁጥር 16) በተባለው መሠረት አንድ እንድትሆን ነው፡፡ በጸሎተ ሃይማኖት የተገለጠውም የእምነት አቋም “በሁሉ ዘንድ ባለች በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” የሚል ነው እንጂ ከእኛ በቀር ቤተ ክርስቲያን የለም፤ ሌላው ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን የእምነት ተቋም ነው የሚል የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ አይደለም፡፡

የ4 ኪሎው ትዝብት በመጨረሻ ያነሡት ጋዜጠኞች ቤተ ክርስቲያኒቱን በተመለከተ ወደ ማኅበረ ቅዱሳን የመሮጣቸውን ምክንያት ነው፡፡ እንደ እርሳቸው አስተያየት ጋዜጠኞቹ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለመጠየቅ ወደ ማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች የሚሄዱት የማኅበሩ ሰዎች ዕውቀት ያላቸው በመሆናቸውና በጋዜጠኞቹ ተመራጭ ስለሆኑ ነው ብለዋል፡፡ እንዲህ ዐይነት ጥያቄ ማንሣት በራሱም የመጻፍና የመናገር መብትን ከመገደብ እንደሚቆጠርና የቅናት እንደሚያስመስልም ተናግረዋል፡፡ የመምህር በቃሉ ሐሳብ የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች ለምን አስተያየት ሰጡ አይደለም፡፡ “ማኅበረ ቅዱሳን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ማኅበር ዐቋሙን እንዲያንጸባርቅ ዕድል መስጠት አንድ ነገር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክሎና ልሳኗ ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የተለያየ ነገር እንዲናገር ማድረግ ግን ሌላ ነገር ነው፡፡” የሚል ነው፡፡ ይህ መለየት አለበት፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት ውጪ ሰው የሌላት እስኪመስል ድረስ፣ ጋዜጠኞቹ ቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ መስላ እንድትታይ የማኅበሩን ገጽታ የመገንባት ሥራ መሥራታቸው ትክክለኛ አይደለም፡፡

የማኅበሩ አባላት ዘመናዊ ዕውቀት ያላቸው መሆኑ እንደ ሃይማኖት ዕውቀት ይቆጠርላቸዋል ማለት ደግሞ አይደለም፡፡ ሆኖም ሁለቱንም አጣምሮ መያዝ አይቻልም እየተባለ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሁለቱን አጣምሮ መያዝ ለቤተ ክርስቲያኒቱ እጅግ ጠቃሚ መሆኑ አያጠያይቅምና፡፡ ነገር ግን በቅርቡ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደ ጠቀሰው፣ የማኅበሩ አንዳንድ ሰዎች የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሳይማሩና ላይሠሩበት እንደ ክብር ዶክትሬት የተሸከሙትና ለራሳቸው የሰጡት ማዕርግ ብቻውን የሃይማኖት ሊቃውንት እንደማያሰኛቸውና ቤተ ክርስቲያቱን እንደ ቤተ ክርስቲያን የሚወከሉበት መብት እንደማይሰጣቸው ግልጽ ነው፡፡

በተጨማሪ እርስዎ እንዳሉት በየጊዜው የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች በሚያቀርቡት ሐሳብ ላይ የተሳሳተ ሐሳብ ካለ ማስተካከያ መስጠት በተቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን ወንጌልን ከተረት፣ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ከልማድና ከወግ ያልለየና በክርስትና ስም የቀረበ ኢክርስቲያናዊ ትምህርት ምኑ ይታረማል፡፡ የሚታረመው እኮ በሰብል ውስጥ የበቀለ አረም ነው፡፡ ማሳው ያበቀለው ሁሉ አረም ከሆነ ግን ማረም ሳይሆን መፍትሔው ሙሉ በሙሉ ገልብጦ እንደ ገና ሌላ ንጹሕ ዘር መዝራት ነው፡፡

የስንብት ቃልዎ (ቸር ያሰማን) የዛሬን አያድርገውና፣ የማኅበረ ቅዱሳንን ህልውና ለማስጠበቅ ሽብር ነዝቶ ቸር ወሬ ያሰማን ይል የነበረውን “ደጀ ሰላም” ድረ ገጻችሁን ያስታውሳል፡፡

መምህር በቃሉ
ከ5 ኪሎ
ምንጭ፡- ነጋድራስ ጋዜጣ የሐምሌ 15 ዕትም

1 comment:

 1. Wegenoche,

  Please let's focus on value-adding issues instead of attacking our church for being comprehensive and for preserving holy books. Some people were attacking our church for including Metsehafe Henok among the holy books, but it has now been proved that that book is truly a holy one. Also, only Ethiopia (EOTC) has the true complete copy.... We owe lots of gratitude to our fathers.

  It is sad that the current generation admires and believes anything foreign and from the west while despising anything of our own. This is a serious moral crisis... Even if the west is superior to us in science and technology, they are not a match for us in spirituality. We just need to learn the core of our faith and the true teaching as documented in the bible, the andimita, the haimanote abew, and the other good books written by the holy fathers.

  As the saying goes... "A nail becomes stronger as it gets hit on its head..." Our church will become stronger as we get hit from different angles. That is what happened to the apostles, the martyrs and the saints.

  However, the author deserves an answer if he is genuinely attempting to learn. We know some present their opposition and disguise themselves as open minded while carrying their poison at the bottom of their heart. Anyway, please let's not attack for the sake of attacking. My only issue with the EOTC is that it needs to teach the pure bible (in the orthodox way, of course) to all and all the time, instead of telling some useless stories all day long and making the church a place of quarrel. That is somehow coming and we need to support those who are doing this. We only need to fight those who are standing on the way of the bible.

  ReplyDelete