Sunday, August 21, 2011

ማኅበረ ቅዱሳን (ማቅ) VS ተሐድሶ = አይሁድ VS ክርስቲያኖች - - - Read PDF


ዘመኑ የቱንም ያህል ቢሠለጥን፣ ሰዎች የፈለጉትን እምነት የመከተልና የማስፋፋት ተፈጥሮኣዊ መብታቸው በሕገመንግሥት ቢረጋገጥ፣ የወንጌል ጠባይ ግን አይለወጥም፡፡ ወንጌል ትናንት በመከራና በስደት ውስጥ ነው የተሰበከው፤ ዛሬም ወንጌል በዚያው በተለመደው የስደት ታሪክ ውስጥ ነው የሚሰበከው፤ ነገም ቢሆን የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ ይህም የሚሆነው ወንጌል ጠብአጫሪ መልእክት ስላለው አይደለም፤ እንዲያውም ለሰዎች ሰላምና ዕረፍት ያለበት የምሥራችን የያዘ መልካም ዜና ነው፡፡ ነገር ግን ምንም መልካም ዜና ይዞ ቢመጣ፣ የዚህ ዓለም አምላክ የተባለ ሰይጣን ልቡናቸውን ያሳወረባቸውና እግዚአብሔርን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ያላወቁት ሰዎች፣ በተለይም ሃይማኖተኛ ነን ባዮች አጥብቀው ይቃወሙታል፡፡


ወንጌል ተቃውሞ እንደሚገጥመው ቀድሞ የሚያውቀው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸው ነበር፡- “ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ ዕወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል። ባርያ ከጌታው አይበልጥም ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስቡ። እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ። ዳሩ ግን የላከኝን አያውቁምና ይህን ሁሉ ስለ ስሜ ያደርጉባችኋል።” (የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ቁጥር 18-21) ብሏል፡፡ በተጨማሪም እንዲህ ብሏል፡- “እንዳትሰናከሉ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። ከምኵራባቸው ያወጡአችኋል፤ ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል። ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው። ነገር ግን ጊዜው ሲደርስ እኔ እንደ ነገርኋችሁ ታስቡ ዘንድ ይህን ተናግሬአችኋለሁ።” (የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 16 ቁጥር 1-3)፡፡


እነዚህ ከዮሐንስ ወንጌል የተወሰዱት ሁለት ጥቅሶች የወንጌልን ዐይነተኛ ጠባይና የሚያስከትለውንም ውጤት በግልጽ ያሳያሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ አስቀድሞ እንደነገራቸው፣ በእርሱና በተከታዮቹ ላይ በወንጌል ምክንያት መከራና ስደት ታውጆባቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በሐዋርያት ላይ ብቻ የሚያበቃ ባለመሆኑ በየጊዜው የሚነሡ የእርሱ ተከታዮች ዕጣ ፈንታ ሆኗል፡፡ የክርስቶስ እውነተኛ አገልጋይ ሁልጊዜ ተከብሮና ተፈርቶ፣ ተደማጭነትንም አትርፎ የሚኖር አይደለም፡፡ ስለጌታው በሚገባ እየመሰከረና እርሱን እየመሰለ ለመኖር በወሰነ ቁጥር ተቃውሞና ስደት ይከተሉታል፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር እንደታዘዘበት መቅሠፍት የሚወሰድ አይደለም (ከመከራ አድራሾቹ ወገን እንደመቅሠፍት የሚወስዱት ባይጠፉም)፤ ነገር ግን በትክክለኛው መንገድ ላይ መቆሙ የሚለካበት የመዳኑ ምልክት ነው እንጂ፡፡ በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤” የሚለው ሕያው ቃልም ይህንኑ ያረጋግጣል (ፊልጵስዩስ 1፥28-29)፡፡

የክርስቶስ እውነተኛ ተከታይ ስለክርስቶስ በመመስከሩና ለክርስቶስ በመኖሩ መከራ ቢገጥመው እንደ ሎተሪ የሚቆጠር ዕድል ነው፡፡ መጽሐፍ እንደሚል የክብር መንፈስ፣ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ ያርፋልና፣ በትክክለኛ ክርስቲያንነቱ መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ማመስገን እንጂ ማፈር አይገባውም (1ጴጥ. 4፥14-16)፡፡ እውነተኛ ክርስቲያን ይህን ስለሚገነዘብ ስደትና መከራ በተነሣ ቁጥር ያልተጠበቀ ነገር የገጠመው ይመስል አይበረግግም፤ እንዲያውም ደስ ይለዋል፡፡ ወንጌል በመከራ ውስጥ የሚሰበክና የሚስፋፋ መሆኑን ስለሚረዳ ተቃውሞ ሲመጣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደሆነና ለሥራ እንደ ተነሣ ያስተውላል፡፡

በዚህ ሐሳብ የተንደረደርሁት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተባብሶ ስለቀጠለው የማኅበረ ቅዱሳንና እርሱ “ተሐድሶ” በሚል (የስም ማጥፋት ዘመቻው ሰለባ የሆኑቱ ተሐድሶን የአየር ላይ ስም ይሉታል) በፈረጃቸው ወገኖች መካከል ስላለው መሠረታዊ ቅራኔና የአሳዳጅ-ተሳዳጅ ድራማ ጥቂት ነገር ለማለት ነው፡፡ የሁለቱ ወገኖች ቅራኔ በመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ተከታዮችና በአይሁድ መካከል ከነበረው ቅራኔ ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ መሆኑንም ለማሳየት ነው፡፡

በአይሁድና በክርስቲያኖች መካከል የነበረው ቅራኔ የተጀመረው ከክርስቶስ ጊዜ አንሥቶ ነበር፡፡ ዋና ጠባቸውም ክርስቶስ ሕጋችንን አፈረሰ፤ ሥርዐታችንን ጣሰ፤ ሰንበትን ሻረ፤ ከኀጢአተኞች ጋር ይበላል፤ የእርሱ ደቀመዛሙርት ከሕጋችን ውጪ የሆኑ ተግባራትን ያከናውናሉ፤ እርሱ ሰው ሲሆን ራሱን አምላክ አድርጓል፤ ወዘተ. የሚሉ ነበሩ፡፡ በጥቅሉ ሲታይ የክርስቶስ ትምህርትም ሆነ ኑሮ ከልማዳችንና ከወጋችን ውጪ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ሽፋን ቢሆንም ከበስተጀርባ የነበረው ዋና ምክንያት ግን እኛ የሕዝቡ መምህራን ሆነን ሳለን፣ ሰው ሁሉ እኛን ተወት አድርጎ እርሱን ተከተለው፤ ከዚህ በኋላ እኛን የሚሰማንና የሚከተለን የለም የሚል ቅናት ነበረበት፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእነዚህ ሁሉ ክሶች ሊከሰስ አይገባውም ነበር፤ ይሁን እንጂ ባለማስተዋልና በክፋት ለቀረቡበት ለእነዚህ ክሶች ሁሉ አጥጋቢና የማያዳግም ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ከእነዚህ ውጪ የሚከሰስበት አንዳችም ጥፋት አልተገኘበትም፡፡ ፍትሕ ከተዛባበት ከከሳሾች አይሁድ በኩል ግን እውነተኛ ፍትሕ ስለማይጠበቅ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሐሰት ክስና ምስክርነት ጥፋተኛ ተብሎ ይሙት በቃ ተፈርዶበታል፡፡ ይሁን እንጂ የእርሱ ሞት ዓለምን ለማዳን በእግዚአብሔር የታቀደና የተወሰነ መሥዋዕታዊ ሞት በመሆኑ በእርሱ አዳኝነት የሚያምኑ ኀጢአተኞች ዕዳ የሚወራረድበት ሆኗል፡፡

እርሱን እስከሞት በማድረስ የተጀመረው የአይሁድ ፀረክርስትና የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከታዮቹን ሁሉ በማሳደድ ቀጥሏል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች፣ አይሁድ ለሞት አሳልፈው የሰጡት ኢየሱስ እንደተናገረው በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ የሚነሣ ከሆነ፣ በሕይወት ከነበረበት ጊዜ ይልቅ አሁን ሌላ ትልቅ የራስ ምታት እንደሚሆን ዐውቀው መቃብሩን በሕግ ጥበቃ ሥር አውለዉት ነበር፡፡ መቃብሩ “ታሸጓል” በሚል በማኅተም ተዘግቶ ነበር፤ ጠባቂ ወታደሮችም ተመድበዉለት ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በአምላካዊ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ አይሁድ የፈሩት ስለደረሰና ነገሩን ወደኋላ ሊመልሱት ስላልቻሉ፣ ጉዳዩን በፈጠራ ወሬ ሊያለባብሱት ሞከሩ፡፡ ወሬአቸው ግን እውነታውን ለመቀበል ባልፈለጉት በእነርሱ ዘንድ ብቻ ሲቀር፣ የጌታ ትንሣኤ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ወጣ፡፡ የዚህ ነገር ምስክር ሆነው የቆሙት ደግሞ ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን ያረጋገጡት ደቀመዛሙርቱ ስለሆኑ ልዩ ልዩ ስም ሰጥተው የተለያየ ስደት አወጁባቸው፡፡ እንደተጻፈውም ከምኩራብ አወጡአቸው፡፡ ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይም አደረሱባቸው፡፡ ማኅበረ አይሁድ ይህን ሁሉ ያደረጉት ግን ለእግዚአብሔር ቀንተው መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ ቃሉ ግን “ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው።” ይልባቸዋል፡፡

የክርስቶስ ተከታዮች ደግሞ በደረሰባቸው ስደት፣ መከራና ሥቃይ ደስ እያላቸው ወንጌሉን ላልሰሙት ለማዳረስ እስከ ምድር ዳር ድረስ ወጡ፡፡ ብዙ ተከታዮችንም አፈሩ፡፡ ይኸው ወንጌሉ በዚያው በተለመደው የስደትና የመከራ መንገድ እየተሰበከ ከዘመናችን ደርሷል፡፡ ዛሬም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉ ወገኖች መካከል ያለው ውዝግብ፣ በተወሰነ መልኩ ወንጌልን በሚሰብኩና “ተሐድሶ” የሚል ታፔላ በተለጠፋበቸው ወገኖች እና ተረታተረቶችን በሚተርቱ፣ ወንጌል ሲሰበክ ደግሞ ዐይናቸው ደም በሚለብስና ጥርሳቸውን በሚያፋጩ ተረፈ አይሁድ ማኅበረ ቅዱሳን መካከል እየሆነ ያለው እሰጥአገባ ጥቂት መልኩን ለውጦ ከመገለጡ በቀር በአይሁድና በክርስቲያኖች መካከል የነበረውን እሰጥአገባ  ይመስላል፡፡ እነሆ ማስረጃዎቹ፡-

1.      ወግና ልማዳችን ቀረ 
እንደክርስትና ትምህርት ሰውን ወደመንግሥተ ሰማያት የሚመራው የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤ የሰው ወግና ልማድ እዚሁ ምድር ላይ ቀሪ ነው፡፡ ወግና ልማድን ማቀንቀን ምድራዊ አጀንዳ ሲሆን፣ ወንጌልን መስበክና ሰውን ለመንግሥተሰማያት ብቁ ማድረግ ደግሞ ሰማያዊ አጀንዳና የቤተክርስቲያን ታላቅ ተልእኮ ነውና ለዚሁ መሰለፍ ይገባል፡፡

አይሁድ ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ለአባቶች ወግና ሥርዐት ነበር ትኩረት የሚሰጡት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር ግጭት ውስጥ የገባውም ስለወጋችሁ ብላችሁ የእግዚአብሔርን ቃል ለምን ትሽራላችሁ? በሚለው አቋም ነበር፡፡ አይሁድም በበኩላቸው ክርስቶስንና በኋላም ተከታዮቹን ሕጋችንን አፈረሱ፤ ሥርዐታችንን ጣሱ፤ ወግና ልማዳችንን አስቀሩ በሚሉ ምክንያቶች ይወነጅሏቸው ነበር፡፡

ማኅበረ ቅዱሳንም ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጠው ለእግዚአብሔር ቃል ሳይሆን ለባህልና ለሥርዐት፣ ለወግና ለልማድ ነው፡፡ ባህልን፣ ሥርዐትንና ልማድን መሠረት አድርጎ ለተቋቋመ ማኅበር ወይም በዚህ መስክ ለተሰማራ የጥናትና ምርምር ክፍል ይህ መልካም ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች በሃይማኖት ውስጥ ቢኖሩም፣ ከሃይማኖት ጋር ሳይጣሉና ሃይማኖትን ሳይተኩ የማኅበረሰቡ እሴቶች ሆነው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ሃይማኖትን ተክተውና እንደ ሃይማኖት ተቆጥረው በሥራ ላይ ይዋሉ ከተባለ ግን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን (ማቅ) ባህልና ልማድ ሃይማኖትን ይተካ የሚል አቋም እያራመደ ነው ማለት ያስደፍራል፡፡ ልማድና ሃይማኖትን በመቀላቀል ሃይማኖትን በወግና በልማድ የመተካት አካሄድን ነው የሚከተለው፡፡

ማቅ “ተሐድሶ” ሲል የሠየማቸውን ወገኖች፣ አባቶች ያቆዩልንን ትምህርትና ሥርዐት ለማፍረስ የተነሡ ናቸው እያለ በሕግ አፍራሽነት ይከሳቸዋል፡፡ ከአይሁድ ክስ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የአባቶቼ የሚላቸው ብዙዎቹ ትምህርቶችና ሥርዐቶች በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽር ሲታዩ ግን ኢመጽሐፍ ቅዱሳውያን ወጎችና ልማዶች ሆነው ይገኛሉ፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ከቃሉ ጋር የሚቃረኑ ናቸው፡፡ ከቃሉ ጋር የማይጋጭ ከሆነ ግን ባህላችንና ሥርዐታችን ሊጠበቅና ለቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከተመሠረተች በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ከቃሉ ውጪ በስውር ሠርገው የገቡና በኀይልም እንዲገቡ የተደረጉ ልዩ ልዩ ኢመጽሐፍ ቅዱሳውያን ትምህርቶችና የአምልኮ ባዕድ ልምምዶች አሉ፡፡ በተለይም ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ወዲህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርትና ሥርዐት በስሕተት ትምህርት እንደተበረዘና ከመሥመር እንደወጣ ይታወቃል፡፡ ማቅ አይነካ፣ እንከን የለሽ ነው የሚለው ይህን ቤተክርስቲያኒቱን ትልቅ መንፈሳዊ በሽታ ላይ የጣላትን የዐፄውን ትምህርትና ሥርዐት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ቤተክርስቲያናችን የምትገኝበትን ይህን ይዞታዋን በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ፈትሾ እንድትታረም ለማድረግ መንቀሳቀስ ለማቅ መናፍቅነት ነው፡፡ ተሐድሶ ለሚላቸው ወገኖች ደግሞ የክርስቶስን አርኣያ ተከትሎ የተበላሸውን ትምህርትና ሥርዐት በቅዱስ ቃሉ መሠረት ማስተካከል ነው፡፡ ክርስቶስ በአይሁድ ከመሥመር የወጣ ሥርዐትና ትምህርት ላይ ተሐድሶን እንዳካሄደ ማለት ነው፡፡

ማቅ እንደጸሐፍት ፈሪሳውያን ግመልን ውጦ ትንኝን የሚያጠራ ስብስብ ነው፡፡ ተሐድሶ በሚላቸው ወገኖች ላይ የሚያቀርበው ክስ ዋና ከሚባለው ሃይማኖታዊ ጉዳይ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውና ተራ ወግና ልማድ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በምእመናን ዘንድ ተደማጭነት ያገኙ መዘምራንን ዜማቸው ዘፈን ይመስላል፤ የመዝሙር ለዛ የለውም ይላል፡፡ በእውነቱ ይህ ትልቅ ግብዝነት ነው፡፡ ያሬዳዊ ዜማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ሁሉ አንጡራ ሀብት ነው፡፡ ዜማው በዜማነቱ እንዲጠበቅ ማድረግ ከቅርስ ጥበቃ አንጻር የሚታይ እንጂ ሃይማኖታዊ ጉዳይ አይደለም፡፡

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜማ (ዘፈኑንም ጨምሮ) ከእርሱ የተቀዳ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ፡፡ ስለዚህ በአንድ ወገን ከዚያው ካልወጣና አሁን ላለው ትውልድ የሚስማማና ተቀባይነትን ያገኘ እስከሆነ ድረስ፣ በደረስንበት የዜማ ስልት ብንጠቀም ምኑ ላይ ነው ስሕተቱ? ደግሞም አሁን በሊቃውንቱ ዘንድ አገልግሎት ላይ የዋለው ያሬዳዊ ዜማ “ኦርጅናሉ” ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ብዙ መሻሻሎች እንደተደረጉበት ምንም አያጠራጥርም፡፡ የሊቃውንቱ ዜማ ብዙ መማርን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ምእመናን ሁሉ ፀዋትወ ዜማ ይማሩ አይባልም፤ ይህ ለምእመናን አስቸጋሪ ከመሆኑ አንጻር እነርሱ በሚችሉትና አሁን በተያዘው የዝማሬ መንገድ መዝሙሮች ቢቀርቡ ምንድን ነው ችግሩ? በእውነቱ ሁለቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ ይቻላል፤ በሊቃውንቱ ዘንድ ያለውን ሊቃውንቱ ይዘዉት ቢቀጥሉና ምእመናን አክብረው ቢያዩት፣ በምእመናን ዘንድ ያለውም ባለበት ቢቀጥልና ሊቃውንቱ ባይንቁት ለቤተ ክርስቲያን ውበት እንጂ ጥፋት አይደለም፡፡ ይህ ከዜማ ጋር የተያያዘው እሰጥአገባ ሃይማኖትን እንደመጣስ የሚቆጠር ምንፍቅና ተደርጎ ሊወሰድ ግን በፍጹም አይገባም ነበር፡፡ ለማቅ ግን ይህም መናፍቅነት ሆኗል፡፡ ስለዚህ መናፍቅ የሚለው ቃል ማኅበሩ እያነሣ በሆነው ባልሆነው የሚለጥፈው ተራ ስድቡ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

የማቅ አባላትና ተከታዮች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የአጿጿም ሥርዐት ያልጠበቀውን እጅከፍንጅ ካገኙት በመናፍቅነት ወይም በተሐድሶነት ይፈርጁታል፡፡ ይህም አይሁድ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ባልታጠበ እጅ በመብላት የአባቶችን ወግ ስለምን ይተላለፋሉ፤ እንዲሁም በሰንበት እሸት ቀጥፈው ለምን ይበላሉ ካሉት ጋር ሊገናዘብ የሚችል ነው፡፡ በመሠረቱ ሥርዐትና ደንቡ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ተቃራኒ እስካልሆነ ድረስ፣ አንድ ሰው አባል ለሆነባት ቤተክርስቲያን ሥርዐትና ደንብ መገዛት አለበት፡፡ ይሁን እንጂ መብልን በተመለከተ አንዱ ሌላውን መናፍቅ ወይም ተሐድሶ ሊል የሚችልበት ክርስቲያናዊ ትእዛዝ የለም፡፡ ቃሉ የበላ ለእግዚአብሔር በላ፤ ያልበላም ለእግዚአብሔር አልበላም ስለሚል በሁለቱም አቅጣጫ ሁሉም ለእግዚአብሔር ክብር ከተደረገ ኀጢአት አይደለም፡፡ ኀጢአት የሚሆነውስ የራስን ጾም መጾም ትቶ ሌላውን መከታተል፤ ወይም እንደወንጀለኛ ቆጥሮ ያልጾመውን ወንድም ወይም የበላውን ወንድም መክሰስ ነው፡፡

2.   ሰላይነት፣ ከሳሽነትና አሳዳጅነት
አይሁድ ብዙ ጊዜያቸውን ያጠፉት ክርስቶስንና ተከታዮቹን በመሰለል፣ በመክሰስና በማሳደድ ነው፡፡ ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ በሚገባ ከማስተማር ይልቅ በክርስቶስና በተከታዮቹ ላይ ስሕተት ሲፈልጉ፣ በወጥመዳቸው ለመያዝ የሚያስችል ፈታኝ ጥያቄ በመጠየቅ ሲገዳደሩ፣ ስሕተት ያልሆነውንና ከወጋቸው ጋር የሚጋጨውን ትምህርተ ወንጌልና ሥርዐተ ወንጌል እያጋነኑ ሲያወሩና ሤራ ሲሸርቡ ነበር ጊዜያቸውን ያጠፉት፡፡ በተመሳሳይ ማቅም ወንጌልን በመስበክ ሰውን ወደዘላለም ሕይወት ሲያመጣ አልታየም፡፡ ለነገሩ እርሱ ያላገኘውን ለሌላው እንዴት ማካፈል ይችላል፡፡ በእርሱ እጅ ያለው ሕይወት የማይገኝበት ወግና ሥርዐት ብቻ በመሆኑ ያን እየጠረቀ፣ ወንጌል የሚሰብኩትን እየተቃወመናተሐድሶ-መናፍቃን” የሚል ታፔላ እየለጠፈባቸው ሲሰልላቸው፣ ሲወነጅላቸው፣ ሲከስሳቸው፣ ሲያወግዛቸውና ሲያሳድዳቸው ነው የኖረው፡፡

ክርስትና ከክርስቶስ ጀምሮ እየተስፋፋ የመጣው ወንጌልን በመስበክና ሰዎችን በማሳመን ነው፡፡ አይሁድ ግን የስለላ መረብ ዘርግተው ክርስቶስን ይሰልሉ፣ የተናገረውንም ከአፉ እየለቀሙ ለክስ ለማመቻት ስውር እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፡፡ ተከታዮቹንም ቢሆን በዚህ መንገድ ሊያጠምዷቸው ይሰልሏቸው ነበር፡፡ ማቅም ከሚያከናውናቸው ስውር ሥራዎች አንዱ፣ ለእርሱ ትምህርትና ሥርዐት ተቃራኒ መስለው የታዩትን የቤተክርስቲያን ልጆች በመሰለል ለክስ ማመቻቸትና ከቤተክርስቲያን የሚባረሩበትን መንገድ መጥረግ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት መቅረፀድምፅ ሰጥቶ የሚልካቸው ሰላዮቹ ስንቶቹን ከቤተክርስቲያን እንዳስወጧቸው የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡

በቅርቡ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መመሪያው ድረገጽ ይፋ ያደረገው የማኅበሩ የውስጥ ለውስጥ ደብዳቤም የማኅበሩን የተለመደ የስለላ ሥራ ያጋለጠ ነው፡፡ የመቐለ ንኡስ ማእከል ለማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት ክፍል በጻፈው ደብዳቤ፣ የቅዱስ ፍሬምናጦስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ተሐድሶዎች ናቸው በሚል ዲኑንና ምክትል ዲኑን ጨምሮ የ14 ሰዎችን ስም ጠቅሶ በአንዳንዶቹ ላይ የሠራውን ስለላዊ ሥራ የተመለከተ ሪፖርት አድርጓል፡፡ በቀጣይም መረጃዎችን እያደራጀ እንደሚልክና አዲስ አበባ ያለው አመራር በተዘረዘሩት አገልጋዮች ላይ እርምጃ ይወሰድ ዘንድ በርትቶ እንዲሠራም ያሳስባል፡፡ ማቅ እንዲህ ባለ የስለላ ሥራ መጠመዱ፣ ማኅበሩ ከሃይማኖታዊነት ይልቅ ፖለቲካዊነት አለው የሚለውን የብዙዎችን ግምት እውነት የሚያደርግ መሆኑን ድረገጹ አክሎ ገልጿል፡፡

እንደዚህ ዓለም መንግሥት የስለላ መረብ በመዘርጋት ሰዎችን እየሰለሉ ከቤተክርስቲያን የሚባረሩበትን ሥራ መሥራት በምንም መስፈርት ክርስቲያናዊም ሆነ መንፈሳዊ ሊሆን በፍጹም አይችልም፡፡ ከክርስትና ትምህርት ውጪ ለሆነ ትምህርትና ሥርዐት አንገዛም፤ በክርስቶስ ያገኘነውን ነጻነት ወደባርነት አንለውጥም ያሉትን ወገኖች መሰለል፣ መወንጀልና ማሳደድ ተረፈ አይሁድነት እንጂ ክርስቲያንነት አይደለም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ “… ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር የገቡ ቢጽ ሐሳውያን (ሐሰተኞች ወንድሞች) ነበሩ” ይላል (ገላትያ 2፥4)፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች እንዲህ በሌሎች ይሰለላሉ እንጂ ማንንም አልሰለሉም፤ አይሰልሉምም፡፡

ማቅ ተሐድሶ በማለት በሚጠራቸው ወገኖች ላይ የሚያቀርባቸው ብዙዎቹ ክሶች፣ አይሁድ በክርስቶስና በተከታዮቹ ላይ ከሰነዘሯቸው ክሶች ብዙም የተለዩ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ፡- አይሁድ ኢየሱስን ሰው ሲሆን አምላክ ነኝ ይላል በማለት ከሰዉት ነበር፡፡ የማቅ አባላትም ለአፋቸው ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ተቀብለናል ቢሉም፣ በሰውነቱ ያከናወነውን የመካከለኛነት ግብሩን በሌላ ተክተዋልና፣ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚናፍቁ (የሚጠራጠሩ፣ መናፍቃን) ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስን መካከለኛነት የሚናገረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የሚያስተምሩትን ሁሉ ይቃወሟቸዋል፤ ተሐድሶ-መናፍቃን ይሏቸዋል፡፡

አይሁድ ሐዋርያው ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ቃል በተቃራኒ የሆነ ወጋቸውንና ልማዳቸውን ስለተቃወመና የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ስለሰበከ፣ የመናፍቃን መሪ ነው የሚል ስም አውጥተዉለት ነበር፡፡ ማቅ እንደአይሁድ ተረቱን አልቀበል ያለውንና የክርስቶስ የማዳኑ ብሥራት የሆነውን ወንጌልን ብቻ የሚሰብከውን ሰው መናፍቅ፣ ተሐድሶ የሚል ስም ያወጣለታል፡፡ እንዲህ እንደሚሆን ደግሞ ክርስቶስ አስቀድሞ ተናግሯልና የደረሰው የተጻፈው ነው፡፡ ሁሉም እንደተጻፈለት እየኖረ ነው ማለት ነው፡፡

አይሁድ ከክርስቶስና ከተከታዮቹ ጋር ማንም እንዳይተባበር አድማ መትተው ነበር፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙዎች በእርሱ ቢያምኑም ከአይሁድ የተነሣ ስለ እርሱ ሊመሰክሩለት አልደፈሩም፡፡ ዛሬም ማቅ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ መሽጎ ከክርስቶስ፣ ከትምህርቱና ከተከታዮቹ ጋር ማንም እንዳይተባበር ለማድረግ የተቻለውን ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ብዙዎች የክርስቶስ ወንጌልና የማቅ ተረት ልዩነቱ ቢገባቸውም፣ ከምኩራብ እንዳይሰደዱ ብለው በማቅ ምክንያት ለገባቸው እውነት መኖር አልቻሉም፡፡ እንደኒቆዲሞስ በኅቡእ መከተሉንም እንደአማራጭ ይዘዉታል፡፡

አይሁድ በኢየሱስ ላይ ለሞት የሚያደርስ አንድም ጥፋት አላገኙበትም፤ ነገር ግን በከንቱ ስለጠሉት ምስክርነታቸው እውነተኛ ሆኖ ባይገኝም በንጹሑ ላይ የሐሰት ምስክር ገዝተው ከማስመስከርና እንዲሞት ከማድረግ ወደኋላ አላሉም ነበር፡፡ ማቅም ዛሬ ወንጌልን ከማስተማርና ቤተክርስቲያንን ከማነጽ ይልቅ ልዩ ልዩ ወንጀል እየፈበረከና ለሰዎች ያለስማቸው ስም እየሰጠ እውነተኞችን ከቤተክርስቲያን በሕገወጥ መንገድ እንዲባረሩ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሕጋዊ ከለላ የሰጠውን የማደራጃ መምሪያውን ኀላፊ እንኳ ያለሥራቸው እስከመክሰስ የደረሰና ፍርድ ቤት ለማቆም ያላፈረ “የወንድሞች ከሳሽ” ነው፡፡

አይሁድ ለእግዚአብሔር እንደሚቀኑ ሐዋርያው ጳውሎስ መስክሯል፤ ቅናታቸው ግን ያለዕውቀት ነው፡፡ ባዶ ቅናታቸውም ከእግዚአብሔር በተቃራኒ እንዲሰለፉ አድርጓቸዋል፡፡ የተከተሉት ሃይማኖታቸውን የመጠበቅ ስልት ተቃራኒ ያሉትን ሰው ማሳደድ፣ ማንገላታትና መግደል ነው፡፡ ክርስቶስ ግን የእግዚአብሔርን መንገድ የሰበከው በፍቅር ነው፡፡

ማቅ ሃይማኖትን መጠበቂያ ብሎ የነደፈው ስልት ማሳደድና እስከ መደብደብ ወይም ወሮበሎችን ቀጥሮ እስከማስደብደብ የደረሰ እርምጃ ነው፡፡ በቅርቡ በደብረ አሚን ተክለሃይማኖት ለተሠራው ድራማ ደራሲው ማቅ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በደጀሰላም ድረገጹ ጉዳዩን አስመልክቶ ያስነበበው ዜናም ምስክር ነው ይላሉ፡፡ በድረገጹ “የተክለሃይማኖት ድል በዮሴፍ ይደገማል” በሚል መሪ ቃል የጀመረው የቤተክርስቲያን ልጆችን የማሳደድ ዘመቻ፣ በዮሴፍ ቤተክርስቲያን በየሳምንቱ ማክሰኞ ይሰጥ የነበረውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ለማደናቀፍና ምእመናንን ለመከፋፈል ሙከራዎችን አድርጓል፤ አንዳንድ የደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ከማሳደም የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ደብዳቤ እንዲጽፍ እስከማስደረግ የደረሰ የማደናቀፍ ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አንዳንድ የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችን ፊርማ በማሰባሰብ ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ትልቅ አደጋ እንደተጋረጠና የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሁሉ ለተቃውሞ እንደተነሡ አድርጎ ያቀነባበረውም ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አስታውቋል (ፍትሕ ጋዜጣ ዓርብ ሐምሌ 15 ቀን 2003 ዓ.ም. ገጽ 13)፡፡

ራሱ ከሳሽ፣ ራሱ ወይም የእርሱ ግብርአበሮች ዳኛ ሆነው ከቤተ ክርስቲያን ያስወጡትን ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ከጥቂቶች በቀር በሲኖዶስ ወይም በተገቢው የቤተ ክርስቲያን ወሳኝ አካል ፊት ቀርበው ውሳኔ የተሰጣቸው በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ አብዛኛው የቤተክርስቲያን ልጅ የተሰደደው ስለሃይማኖት ምንም በማያውቁና የማኅበረ ቅዱሳን አመለካከት ሰለባ በሆኑ ተራ ምእመናን አድማ ነው፡፡ ዛሬም ይህ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አሠራር በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡ ብዙዎችም የፍትሕ ያለህ እያሉ ነው፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቀኖና እና ሥርዐት ውጪ “እገሌ መናፍቅ ነው” “እገሌ ተሐድሶ ነው” የሚለው እንቅስቃሴ ከሐምሌ 25 ቀን ጀምሮ ሕገወጥ ነው ማለታቸው፣ ደስ የሚያሰኝና የሚደገፍ ነው፡፡ አሁን በተነሣው ውዝግብ ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ሕገቤተክርስቲያንን ባልጠበቀ ሁኔታ በማኅበረ ቅዱሳን ውንጀላ ያለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከእናት ቤተክርስቲያናቸው የተሰደዱትን ልጆቿን ሁሉ ወደቤታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ልታመቻችላቸው ይገባል፡፡ “ወልዶ አሳድጎ ለባዳ” … እስከ መቼ!  

3.   በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለው አቋም
ማቅ ተሐድሶ መናፍቃን በሚላቸው የቤተክርስቲያን ልጆች ላይ የሚያቀርበው ሌላው ክስ፣ ስለኢየሱስ ብቻ ነው የሚሰብኩት፤ ስለቅዱሳን አይሰብኩም የሚል ነው፡፡ ይህም ጥቂት መሻሻል የተደረገበት ይምሰል እንጂ ከአይሁድ የክስ ጭብጥ ብዙም የተለየ አይደለም፡፡ አይሁድ በዚህ ሰው (በኢየሱስ) ስም ስለምን ታስተምራላችሁ? ይሉ ነበር፡፡ ማቅ ደግሞ ስለኢየሱስ ብቻ ለምን ትሰብካላችሁ? ነው የሚለው፡፡ ሊሰበክ የሚገባው ስለኀጢአታችን የሞተው መድኀኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እግዚአብሔር አብም የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት ነው ያለው፡፡ ከእርሱ በቀር መዳን በሌላ በማንም ስለሌለ እርሱን ተክቶ ወይም የእርሱ ተለዋጭ ሆኖ የሚሰበክ ሌላ አዳኝ ፈጽሞ የለም፡፡ ቅዱሳን ስለእርሱ ያሳዩት ፍቅርና የከፈሉት ዋጋ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን በስብከት ውስጥ ሊወሳ ይችላል፤ ማቅን ደስ ለማሰኘት ወይም ተሐድሶ ላለመባል ሳይሆን እውነት ስለሆነና አርኣያቸውን ለመከተል ጠቃሚነት ስላለው ነው፡፡ ነገር ግን ያም ቢሆን ኢየሱስን ተክተውና አማራጭ መድኀኒት ተደርገው ይሰበኩ ማለት ግን እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሊሰበክ የሚገባው ብቸኛው መድኀኒት የዓለም ቤዛ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ከእርሱ በቀር የምንሰብከው ሌላ አዳኝ ማንም የለም፡፡ ይሁን እንጂ ይህም ለማቅ መናፍቅነት ነው፡፡ የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በተሰኘው ሰሞነኛ መጽሐፉ ውስጥ እንኳ የቤተክርስቲያንን ዋና መሠረት በማፍረስ ማንነቱን ግልጽ አድርጓል፤ ክርስቶስን አስኳል አድርጎ መስበክ የተሐድሶዎች ስልት እንጂ የእርሱ አቋም አለመሆኑን ጽፏል (ገጽ 55)፡፡ ይህም ማቅ ፀረ ወንጌልና ፀረ ክርስቶስ ስብስብ መሆኑን ያሳያል፡፡

ማቅ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንሰብካለን ቢልም ብቸኛ አዳኝ አድርጎ አይሰብከውም፡፡ ኢየሱስን ከታሪክ አንጻር በተለያዩ ትርጓሜዎች አጠይሞናደብዝዞ ነው የሚገልጸው፡፡ አይሁድም ቢሆኑ አዳኝነቱን አይቀበሉ እንጂ ኢየሱስ በታሪክ የነበረ፣ እነርሱ አሳልፈው የሰጡትና የሰቀሉት “ዕሩቅ ብእሲ” (ተራ ሰው) መሆኑን አይክዱም፡፡ ማቅ ተሰቅሎ ስለሞተው ስለአዳኙ ከመስበክ ይልቅ አሳልፎ ስለሰጠው ስለይሁዳ ክፋት ቢዘረዝርና ቢያመሰጥር ደስ ይለዋል፡፡ ከምንም በላይ የኢየሱስ አዳኝነት ብቻ ሲነገር መከፋቱ በክርስቲያንነቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሣና ተረፈ አይሁድ ነው የሚያሰኘው ተግባር ነው፡፡ ከይሁዳ ታሪክ ትምህርት ቢገኝም እንኳ ወደመዳን አያመጣንም፡፡ የሚያድነው ኢየሱስ ካልተሰበከ ስብከት ሁሉ ስብከት ተብሎ ሊጠራ እንደማይችል የስብከት ዘዴያችን እንኳ ይመሰክራል፡፡

4.     ፖለቲካዊ አጀንዳ
አይሁድ ክርስቶስንና ተከታዮቹን የጠሉበት አንዱ ምክንያት፣ ሰዎች ሁሉ የእርሱ ተከታዮች ከሆኑ ሮማውያን መጥተው አገራችንን ይወስዳሉ የሚል ፖለቲካዊ ሰበብ ነው፡፡ በጊዜው ክርስቶስ ወደዓለም የሚመጣው ዓለምን ለማዳን መሆኑ በመጽሐፋቸው ተጽፎ የነበረ ቢሆንም፣ ከሮማውያን ቅኝ ግዛት ለመላቀቅ ከነበራቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ፣ ክርስቶስን የዚህ እንቅስቃሴያቸው መሪ አድርገው እስከመቁጠር ደርሰው ነበር፡፡ እርሱ የሚመጣው መንግሥትን ከሮማውያን እጅ ወስዶ ለእስራኤል ልጆች ለመመለስ ነው ብለው ደምድመዋል፡፡ ክርስቶስ ግን በጠበቁት በዚህ መንገድ ስላልተንቀሳቀሰ አልተቀበሉትም፡፡ እንዲያውም አገራቸውን በሮማውያን ሊያስወስድ እንደሆነ ገምተው ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ማቅም ራሱን የቤተ ክርስቲያን ብቸኛ ዘብ አድርጎ ሲሠይም፣ ዐላማው በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ሆኖ በወረቀት ላይ በሰፈረው መተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የድርሻውን መወጣት ሳይሆን፣ ከዚያ ጀርባ ያለውን ድብቅ ዐላማ መፈጸም እንደሆነ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ በቅርቡ በደጀሰላም ድረገጹ ላይ ለጥቂት ጊዜ ሰቅሎ ያወረደው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ቅሬታዊ አቤቱታ የሚጠቁመን አንዳች ነገር አለ፡፡ ዲያቆን ዳንኤል የቀድሞው የማኅበሩ አጀንዳ ቤተክርስቲያኒቱ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እግዚአብሔር ወዳየላት ግብ እንድትጓዝ ሳይሆን፣ ማኅበረ ቅዱሳን ወደቀየሰላትና እርሱ ወደሚፈልገው ግብ ማድረስ ነበር፡፡ ተሐድሶ-መናፍቃን ያላቸው ወገኖች ለድብቅ ዐላማው እንቅፋት እንደሆኑበት ስለተረዳ ግን፣ እንደአይሁድ ዐላማቸው ቤተክርስቲያናችንን በፕሮቴስታንቶች ማስወረስ ነው የሚል ፖለቲካውን መንዛት ይዟል፡፡ ይህን የሚልበት ምክንያት ግን ለቤተክርስቲያን ተቆርቁሮ ሳይሆን፣ ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ሊያራምደው የሚፈልገው የተዳፈነ የፖለቲካ አጀንዳ ስላለው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እስከጊዜው ግን ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ መንቀሳቀስ አማራጭ የሌለው ስልት ነው፡፡ ሃይማኖትን ከፖለቲካ እያጣቀሰ የሚያደርገው ጉዞ፣ ብዙዎችን ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ዕዳ ሆኖባታል ወደሚል ድምዳሜ  እያመጣ ነው፡፡

5.   የጥቅም ግጭት
ማቅ ተሐድሶ ያላቸውን ወገኖች የሚጠላበት ሌላው ምክንያት ከጥቅም ግጭት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አይሁድ ኢየሱስን ሰው ሁሉ መከተሉ ስላበሳጫቸው የተከተለውን ሕዝብ ከእርሱ ለመለየት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሰውን በማስተማርና በማሳመን ከእርሱ መለየት ግን ስላልቻሉ፣ የነበራቸው ብቸኛ አማራጭ የእርሱን ስም ማጉደፍና ከእርሱ ጋር የተባበረ ሰው ከምኩራብ እንዲወጣ አድማ መምታት ነበር፡፡ ይህ ለጊዜው ብዙዎችን በፍርሃት ወጥሮ ኢየሱስ ብቻውን እንዲቀር ለማድረግ አስችሎ ነበር፡፡ ቆይቶ ግን የሚሠራ ስልት አልሆነም፡፡ ዛሬ ከአይሁድ ተከታይ ይልቅ የኢየሱስ ተከታይ ይበዛል፡፡ ማቅ ተሐድሶ ብሎ ከፈረጃቸው ወገኖች ጋር ጊዜ እየጠበቀ ግጭት ውስጥ የሚገባው ተሰሚነቱ እየቀነሰ የመጣ ሲመስለውና ሰው ሁሉ ወደ ወንጌል ዘወር ማለት ሲጀምር መሆኑ ካለፉት ዓመታት እንቅስቃሴዎቹ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለዚህም ሽፋኑ ሃይማኖት ተባለ እንጂ ድብቁ ምክንያት ቅናት ነው፡፡    

ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሰውን በእግር በፈረስ ፈልገው የራሳቸው ተከታይ እንዲሆን ካሳመኑ በኋላ ይበልጥ የገሃነም ልጅ እንደሚያደርጉት ተጽፏል (ማቴዎስ 23፥15)፡፡ ማቅም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመለመላቸውን ሰዎች በራሱ ዶክትሪን አጥምቆ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሳይሆን የራሱ ተከታዮች ነው የሚያደርጋቸው፡፡ አባላቱ ቅድሚያ ለማቅ የሚሰጡና ራሳቸውን ማኅበረ ቅዱሳን ነኝ የሚሉ ሲሆን፣ ቤተክርስቲያኒቱን በሁለተኛ ደረጃ ነው የሚመለከቷት፡፡ የማኅበሩ በተረታተረት የተሞላ አስተምህሮ ሰውን ለዘላለም ሕይወት የሚያበቃ ሳይሆን የባሰ የገሃነም ልጅ የሚያደርግ ነው፡፡ ምክንያቱም መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንጂ በሌላ በማንም በምንም ስለሌለ (የሐዋርያት ሥራ 4፥12)፣ ማኅበሩ ደግሞ ይህን እውነት ከልሶና በርዞ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ላይ ሌሎች “አዳኞችን” አክሎ ስለሚያስተምር፣ ይህ ትምህርት  ወደገሃነመእሳት የሚጨምር እንጂ ወደመንግሥተሰማያት የሚያስገባ አይደለም፡፡

ማቅ በዚህ ሁሉ ድርጊቱ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝ ይመስለዋል፡፡ ግን ይህ ከክርስትና ፈጽሞ የራቀ ኢክርስቲያናዊ ሃይማኖትን የመጠበቂያ ስልት ነው፡፡ ክርስትና የእግዚአብሔርን ቃል በፍቅርና በእውነት በመስበክ የሚስፋፋ የሕይወት መንገድ ነው፤ የሚሞቱለት እንጂ የሚገድሉበት፣ የሚሰደዱለት እንጂ የሚያሳድዱበት፣ የሚንገላቱለት እንጂ የሚያንገላቱበት ሃይማኖት አይደለም፡፡ ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳንን ከዚህ አንጻር ክርስቲያናዊ ማኅበር ነው ማለት አያስደፍርም፡፡ ታዲያ ማኅበረ ቅዱሳንና አይሁድ፣ ጸሐፍት ፈሪሳውያን አንድ ናቸው ቢባል፣ አሁን ያለው ውዝግብም በአይሁድና በክርስቶስ ተከታዮች መካከል ያለ ውዝግብ ነው ቢባል ምን ስሕተት አለው?

መምህር በቃሉ
ከ5 ኪሎ
ምንጭ ነጋድራስ ጋዜጣ የነሐሴ 7 እና 13 ዕትም፡፡

9 comments:

 1. it is great job i like it

  ReplyDelete
 2. You did not elaborate the article, especially in the issue of Politics and use becauses these are the core problems of MK.

  ReplyDelete
 3. wey Gud, yegeremal ... Jesus is always the winner - no matter what.

  ReplyDelete
 4. Minim bitetsifu yemisakalachihu aymeselegnem mikiniayatum alamachihu min endehon yemayawuke sew yale aymselegnem. You guys always accuse MK but they will be winners of you because GOD with his mother St. Marry as well as angels is with MK and with EOTC. Therefore, don't write always false about MK but if you write the truth you will get the followers unless you will never succeed.

  ReplyDelete
 5. Those of you who want to preach Jesus, please make sure that you teach the complete truth that Jesus has revealed to us in the Bible. Even if I disagree with MK on many points, it is not fair to label them as "Jew Faris." The EOTC fight is against the heresy of protestants and their likes. Because of their fear not to stray to protestant heretic ways of teaching, they (mk) may not be comfortable with preachers that don't teach the complete truth as believed by the EOTC church. Of course, if anyone teaches a half or partial truth in the name of Jesus, that preacher would be called inferior and thrown to hell on the day of judgment. Some innocent or unlearned people think that their constant invokation of the name "Christ Jesus" would amount to being a better christian. That is a mistake! In other words, while it is crucial to teach about the salvation given to us through the Cross, it is also critical that any preacher teaches about the difference between us and the protestant and other churches. That difference needs to be clearly drawn to avoid confusion and heresy. I think that is what MK wants to see when they complain about some preachers. Sometimes, worldly desires and animosity for the wrong reasons come in to play as well.

  Any way, we should all pray for a better environoment at our church.

  ReplyDelete
 6. my bro , let me tell you the secret first read the holy bible, know about the saviour , HE IS THE LION OF JUAD , OUR LORD JESUS . SO WHAT DO TALK ABOUT ? MK OR OTHERS MK IS NOT YOUR SAVOIUR AND YOU ARE TALKED ABOUT SAINT MARY AND ANGELS . OK LET ME TELL YOU THESE ARE GOD'S SERVANT. OFCOURSE SAINT MARY IS MOTHER OF JESUS DO YOU REMBER WHAT SHE SAID LISTEN WHAT JESUS CHRIST SAYS SO WHY YOU DONOT LISTEN HIM ?
  MY BROTHER, GO AND READ ACTS 4; 12 NO ONE CAN BE SAVE EXCEPT THE NAME OF JESUS , THIS IS APOSTLES TEACHING ACCEPT THIS TEACHING , THE REAL ORTHODOX TEACHING . IF YOU READ BIBLE YOU IGNORE MK'S TEACHING IF YOU DONOT READ BIBLE YOU ARE UNDER MK AND THIER SERVANT . BRO, I AM PRAYING TO YOU TO RETURN TO JESUS CHRIST.

  ReplyDelete
 7. mahibere kidusan is bussinss organisation, they have too many bussiness centers, 42 shops in the country and unkown abroad, five resturants, two regular publication [profitble], two departemetns for fundrasing in the name of Monasteries and traditional schools,naw in the name of Tehadiso, so many copied publications, 20,000.00 members contribution every month[like 100 Birr and more every month], MONEY is POWER they have money so they are miss-using their financial power, I am a member and I know how much money is spent for few people, the are bribing people to perform their UN-CHRSTIAN activities

  Like Daniel i will tell you so many secrets of MK to the public

  ReplyDelete
 8. ፈጥነው ይጠፋሉ.  ሐሰተኞች ነቢያት

  በህዝብ ውስጥ አሉ

  ስለ ዝሙታቸው

  ብዙዎች ያታለሉ

  ለራሳቸው መንገድ

  መምህር ይመርጣሉ

  የሚያጠፋ ኑፋቄ

  አሾልከው ያስገባሉ

  “የበቃን ነን” ብለው

  ”ምንአለበት” ሲሉ

  ለሥርዓት ያልቆሙ

  ሕጉን ይሽራሉ

  የጽድቅ መንገድንም

  “ሐሰት ነው” ከሚሉ

  የዋጃቸው ጌታን

  “አማላጅ ነው” ካሉ

  ጊዜ ቢሆን እንጂ

  ፈጥነው ይጠፋሉ፡፡  ከ መኮነን አበረሄ(ዲላ)

  ReplyDelete
 9. betun ymitbeq geta wdyte hedo nwe? God rasu betune yaqna

  ReplyDelete