Thursday, October 6, 2011

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና ጥረታቸው

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌና ጥረታቸው
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተወለዱትና ካደጉት ታላላቅ ሊቃውንት መካከል አንዱና ትልቁ ናቸው። እኒህ ሰው በቤተ መንግሥትና በቤተ ክህነት ስፍራ ተሰጥቷቸው ታላቅ ሥራ ሰርተዋል። ለሀገራችንም ሆነ ለቤተ ክርስቲያናችን በሠሩት ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን አግኝተዋል።
እኒህ ሰው ከሁሉም የተሻለና የላቀ ሥራ ለሕዝባችን ካበረከቱት ዋና ሥራ እውቀታቸው ተሰውሮ እንዳይቀር ተተኪ ትውልድ እንዲያውቀውና እንዲጠቀምበት ለማድረግ በጽሑፍ ያሰፈሩት እውቀታቸው ነው። ያኔ አንድ እርሳቸው ብቻ ያዘጋጁትን እጅግ ግዙፍ መዝገበ ቃላት በዛሬ ያሉት ብዙ ሊቃውንት ተብየዎች ተሰባስበው ሊያዘጋጁት ብቃቱም ችሎታውም ያንሳቸዋል። ብለን ደፍረን ልንናገረው የምንችለው ሐቅ ነው።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በአማርኛ፤ በግእዝ፤ በእንግሊዘኛ፤ በእብራይስጥ፤ በግሪከኛ፤ በዓረብኛ፤ በጀርመነኛ፤ አቀላፍተው የማንበብ ብቃታቸው ከሁሉም የተሻሉ በመሆናቸው፤ መንግሥት እንኳ እርሳቸውን ከጉያው እንዲያጣቸው አይፈልግም ነበር። ብርቱ የነበሩት አለቃ የሀገሪቱ ዕዳ በእርሳቸው ትከሻ ላይ መውደቁን አውቀው የክፉዎችን ወሬ ለክፉዎች በመተው ሕዝባቸውን ከትልቅ ድንቁርና ለማውጣት ከላይ ታች እያሉ ነው ዘመናቸውን የጨረሱት?። ለእርሳቸው ጭንቅ የነበረው ዋናውና ትልቁ ነገር ቤተ ክርስቲያን የተጣበቀባትን ባዕድ ትምህርት ብታስወግድ ለምድሪቱ ሁለንተና በረከት ትሆናለች ብሎ ማሰብና መተግበር ነበር። በወቅቱ በዚህ እውቅት አለቃ ብቻ መገኘታቸው ለመላ ኢትዮጵያ አንዲት ሻማ እንደመለኮስና እንደማብራት ያህል ነው። ሆኖም ወቅቱ ቢጠብባቸውም እኛን ይጠቅሙ ዘንድ የተጠቀሙበትን ያን መልካም ጥበብ በጽሑፍ አቆዩን። አደራ የሚጠብቅ እግዚአብሔር ብድራታቸውን ይከለክል ዘንድ አመጸኛ አይደለም። ያለቃን ጽሑፍ ስንቃኘው በክርስቶስ ደም የተዋጀች ቤተ ክርስቲያን በባዕድ ነገርና ትምህርት ልትያዝ አይገባትም በሐሰተኛ ትምህርት አትጠመድም፤ ይልቁንም ክፉ ሥራን ሁሉ ወደ ብርሃን ታወጣዋለች እንጂ የሚል ነው።
አለቃን ካስቆጣቸውና ካበሳጫቸው ትልቅ ነገር የገድላትና የድርሳናት የእርስ በእርስ አለመግባባትና እውነተኞች ሆነው አለመገኘታቸው ነው። ገድላትና ድርሳናት ሁሉ የራሳቸውን እውነት ይዘው ስለማይገኙ ጥገኛና ሌባ ሆነው የነሱ ያልሆነውንና የጓደኛውቸውን ታሪክ በመሥረቅ ባለሆኑትና ባላደረጉት ነገር እንደ ባለቤት ሆነው መገኘታቸው ነው። አለቃ ይህን ሁሉ መልክ መልክ ለማስያዝ ብዙ ጥረዋል። ብዙም ደክመዋል። ተሰፍሮ ተቆጥሮ የማያልቀው የሰነፎችና የክፎዎች ታሪክ ግን በርሳቸው ብቻ ተጠርጎ የማያልቅ በመሆኑ በነበረው ላይ እየተጨመረበትና እየበዛ ከዘመናችን ደርሷል። ሊቁ ኪዳነ ወልድ እንደ ጥናት አድርገው ካቀረቡት መካከል በአንድ ስም ተጣብቀው ታሪካቸው ተደባልቆ ማን ምን እንደሆነ መለየት ተሥኖን ያለውን ነገር የሦስቱን ተክለ ሃይማኖቶች ነው። ምንም እንኳ ታሪካቸው ለሊቃውንቱ ብዙ የተሰወረ ባይሆንም አላዋቂው ግን ብዙ ስለተሳሳተበት ስለዚህ ጉዳይ በአለቃ ዘንድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ትኩረቱ እውነት ነውና እኛም ይህንኑ ጥናት ለማየት ሞክረናል። እኒህ ታላቅ አባት "ሃይማኖተ አበው ቀደምት‚ የቀደምት አባቶች ሃይማኖት ርእስ ይሰጡና መነሻቸውን እስክንድርያ አድርገው የኢትዮጵያን ሁኔታ ይቃኛሉ ኢትዮጵያ ከእስክንድርያ ጋር የተሳሰረችበት ነገር አለና ከዚያው መነሣቱ አግባብ ነው።
ወንጌልን ለመስበክ የጠሩ ብዙዎች ሆነው የተመረጡና አገልግሎታችውን በመልካም የፈጸሙ ጥቂቶች አለቃ ተናግረዋል። ከነዚህ መካከል ሦስቱ አባቶች ናቸው በማለት መረዳታቸውን አሳይተውናል።
እነርሱም፦
 
ሐዋርያዊ አትናቴዎስ
. ሰላማ ከሳቴ ብርሃን
. ጻድቁ ተክለሃይማኖት ቀዳማዊ ዘብሔረ ሳይንት[ዳውንት]በጌምድር በሕየ ምድር የተወከዱ ናቸው። እነዚህ አበው ለቤተ ክርስቲያንና ለምድራችን እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው አበው እንደሆኑ እውነተኛ ታሪካቸው ምሥክር ነው። እነዚህ አበው ለምን እንደተጠቀሱ እንድንቀበለው የሚያስችለንን እውቀት ከታሪካቸው ጠቀሜታ ስላለው ሦስቱን ጥቂት እንመልከታቸው።
1ኛ አታናቴዎስ ሐዋርያዊ
ይህ አባት ከመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ብዙ ያልራቀ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ታላቅ ሰው ነው። በዘመኑ የስሕተት አስተማሪዎች ቢበዙበትም መከራውንና ስደቱ ታግሶ ወንጌልን እየሰበከ ትግስቱን አሳይቷል።
ምንም እንኳ አንገቱ በሰይፍ ባይቆረጥ እና ደሙን ያፈሰሰ ሰማዕት ባይባልም ቅሉ ሊቁ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ "ሰማዕት ዘዕንበለ ደም‚ ሲሉ አሞግሰውታል። በእርግጥም ስለክርስቶስ ወንጌል የሚሰደዱ ሁሉ የወንጌል ምሥክሮች ናቸውና ይህ ሰው አትናቴዎስ ይህን ስም ማግኘቱ አግባብነት ያለው ነው። አትናቴዎስ በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ በመሆን በተራ ቁጥር ለተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ አራተኛ ለእለስክንድሮስ ሁለተኛ ሆኖ ሲያገለግል አርዮስ የተባለ መናፍቅ ወልድ በባሕርየ መለኮቱ ፍጡር ነው ስላለ በኒቅያ ጉባኤ በጸሐፊነት በመገኘት "ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ‚ በመለኮቱ ከአብ ጋር እኩል ነው የሚለውን አቋም በጽሑፍ አስፍሯል። ይህም እስከ ዛሬ ድረስ ለሁሉም ማለት ለኦርቶዶክሳውያን፤ ለካቶሊካውያን፤ ለወንጌላውያን[ፕሮቴስንታንት] የሃይማኖት መግለጫ ሆኖ ያገለግላል።
አትናቴዎስ ከአርዮስ በሚደርስበት መከራና ስደት ሁሉ ታግሶ መመናንን በማስተማርና ወንድሞቹን በማጽናት እጅግ ብርቱ ሰው ነበር። በችሎታና በእውቀት እጅግ ብርቱ ሰው የነበረው አትናቴዎስ አርዮሳውያን ከመንግሥት በሚያገኙት ድጋፍ ሥቃዩን አብዝተውበት ነበር። ዛሬም በአለም አቀፍ ኅብረተ ሰብእ ዘንድ [በኦርቶዶክስ፤በካቶሊክ፤ በፕሮቴስንታት] እውቅናና ተቀባይነት ያለው አትናቴዎስ ብትምህርቱና በእምነቱ ነቀፌታ ያልነበረበት አባት ነበር። በተለይም እርሱ የነበረበት ወቅት እጅግ አደገኛ ዘመን ስለነበር ዶክትሪናል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርግ ነበር።
በዚያን ዘመን አትናቴዎስ ባይኖር ኖሮ አርዮስን ተከራክሮ የሚረታ፤ በእውቀት የበሰለ፤ በሥነ ምግባር የታነጸ አባት አይገኝም ነበር ይባላል። "እግዚአብሔር ወልድ በመለኮቱ ፍጡር ነው‚ የሚለው ክፉ ትምህርት በእስክንድርያ ብሔራዊ ሃይማኖት እስኪዎን ድረስ በባለ ሥልጣን የተደገፈው የአርዮስ እንግዳ ትምህርት በመላ ሀገሪቱ እንዳይዳረስ አንድ ብቻውን በትጋት የተንቀሳቀሰው አትናቴዎስ የአርዮስ ትምህርት ሥር እንዳይሰድ በጊዜው እንዲመክን አድርጎታል።
ከዚህም የተነሳ የመጀመሪዋ ቤተ ክርስቲያን ይህን ታላቅ አባት "ቅዱስ‚በሚል ማዕረግ ትጠራዋለች። አሁንም በዚሁ ማዕረግ ቅዱስ አትናቴዎስ ተብሎ ይጠራል። በእርግጥ እርሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ አንደሆነ አምነው በቅድስናው ሥር የተጠለሉት ቅዱሳን ሁሉ የቅድስናው ተካፋዮች ናቸው። እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ብሏልና እስከዚህ ዘመን ድረስም ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሳትሆን የምመናን ስብስብ እንደሆነች የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል።
በዚህ ሰው ዘመንም ምንኩስና የተባለው ሥራት ለጽድቅ ሥጋን መጨቆን፤ ትዳርን መፍታት፤ ራስን ማግለል፤ በብቸኝነት ከሰው ተነጥሎ መቀመጥ የሚለውን ክፉ ትምህርት ይዞ በነአባ ጳኩሚስ፤ በነአባ ጳውሊ፤ ይሰበክ ጀመር። "የገብያ ግርግር ለሌባ ያመቻል‚ እንደሚባለው የተጨነቀም ሁሉ፤ ብድርም ያለበት ሁሉ፤ በንግድ የከሰረው የተከፋም ሁሉ ወደዚህ ክፉ ትምህርት አዘነበለ ሁሉም የክፉ ቀን መውጫ አደረገው፤ አትናቴዎስ ግን መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ አሳልፎ ይሰጣልል እንደተባለው፤ ተጋድሎውን በጽናት ፈጸመ እንጂ እንዲህ አላደረገም።
2ኛ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን [ፍሬምናጦስ]
ይህ ሰው ደግሞ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ወደ ሀገራችን ወደ ኢትዮጵያ ብንግድ ምክንያት ከአባቱ ጋር ከገባ በኋላ አባቱ በኢትዮጵያ ወደብ ድንበር ሲሞት እርሱና ወንድሙ ግን በሕይወት ተግኝተው በቤተ መንግሥት በእንክብካቤ አደጉ ይኸው ፍሬምናጦስ በዚሁ አድጎ ሃይማኖታዊ ትምህርትና ሥራት ይዞ እንዲመለስ ወደ እስክንድርያ ተልኮ ከአትናቴዎስ ጋር ጊዜ ወስዶ በመጨዋወት ሐሳብ ከተለዋወጡ በኋላ ራሱን ሰላማን ሹሞ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ አድርጎታል።
ሰላማ በትውልዱ ግሪካዊ ሲሆን እድገቱ ግን በግሪክ በኢትዮጵያ፤በእስክንድርያ እንደሆነ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ይስማማሉ። በተለይም ሰፊውን ጊዜ በኢትዮጵያ ያሳለፈ በመሆኑ ኢትዮጵያዊነት ስለሚሰማው ወደ ሀገሩ እንደሄደ ለመቅረት ዝንባሌ አላደረበትም። ይልቁንም ለኢትዮጵያ የሚበጅ የሚጠቅም ሐዋርያ እንዲላክ አትናቴዎስ አጥብቆ ያሳሰበ እውነተኛ አባት ነበር። ሆኖም ከርሱ ሌላ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም አባት ባለመገኘቱ እርሱ ራሱ ተሹሞ እንዲመለስ በመምከር፤ ለሦስት አመታት ያህል ፍጹም ወንጌል በማስተማር ሾሞ ሰደደው። እርሱም ባዕድነቱ፤ የቀለም ልዩነቱ፤ የአመጋገብ ስራቱ ሳያስጨንቀው ያሳደገችውን ኢትዮጵያን ለማገልገል ተመልሶ መጣ። ፍሬምናጦስ ከጤናማ ሰው የተማረውን ጤናማ ትምህርት በጨለማ ስንኖር ለነበርነው ለኛ ብርሃን ስለሆነና ከሞት ወደ ሕይወት የሚያሻግረውን ወንጌለ ብርሃን ይዞ ስለመጣ "ሰላማ ከሳቴ ብርሃን‚ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል። ሰላማ ከወንጌል ጋር ወደ ሀገራችን ሲገባ በፊት የነበረው አምልኮ ባዕድና ሥራተ ኦሪት ተሸቃቅጦና ተደባልቆ ሕዝቡ ለሁለት አምላክ ተገዢ ሆኖ ይኖር ነበር። ሆኖም ቀደም ሲል ክርስትናን በመጠኑም ቢሆን የተለማመደው ሕዝባችን በቀላሉ ወደ ክርስትና እምነት ሊለወጥ ችሏል። በሌላም በኩል ንጉሥ የተቀበለው ሃይማኖት እንደትልቅ ነገር ስለሚቆጠር ሕዝቡ ቢገባውም ባይገባውም የንጉሥ ሃይማኖት ነው በማለት ያለማንገራገር ሊቀበለው ችሏል።
ይሁን እንጂ ክርስትና ገባ ማለት ሌሎች እምነቶች ጠፉ ማለት አይደለም ዛሬም እንኳ በአክሱም ሐውልት ላይ የመስቀል ምልክትና የፀሐይ ምስል በስእል ተቀምጦ የሚታየው በዚያን ጊዜ የነበረውን ማንነታችንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።
ሰላማ በብርቱ ትግል ሁሉም ባዕድ ነገር ቦታውን ለወንጌል እንዲለቅ በማድረግ አስደናቂ ሥራውን አሳይቷል፤ ምንም እንኳ ክርስትናን ቤተ መንግሥት እን ሳይቀር ቢቀበለውም አምልኮ ባዕድ ፈጽሞ ባለመጥፋቱ ለተተኪ አገልጋዮች አስቸጋሪ ነበር ተብሎ ይታመናል። ሰላማም ቢሆን የራሱ እሩጫ ሮጠ እንጂ ቀጣይ ሥራውን የሠሩ ዘንድ ተተኪ ደቀመዛሙርትን አላፈራም፤ ይህም አሰራር ቤተ ክርስቲያን እስከ ዛሬ ድረስ ለወደቀችበት ውድቀት እንደምክንያት የሚጠቀስ ነው። ሰላማ ከሚወደድበት አንዱ ሥራው ደግሞ ቅዱሳት መጻሕፍትን ወደ ብሔራችን ቋንቋ ለመተርጎም ባቀደ ጊዜ ሥራው ሁሉ እንዲሳካለት ሴሜቲክ [ሴማዊ] የነበረውን እና በአልፋ ቤት ብቻ የተቀመጠውን የግእዝ ፊደላት እያንዳዱ ፊደል በተለያዩ ቅርጾች በተለይ ጭረትና የዜሮ ምልክት በቅንፍ ውስጥ ባሉት ምልክቶች በመጠቀም ከሀ እስከ ሆ የሚደርሱ ሆሄያት ከሀገራችን ሊቃውንት ጋር ሆኖ አዘጋጅቷል። ዘአክሰመ የሚለው ቃል ሲስተካከል ዘአክሱም የሚል ሆኗል።
ይህንም ለማድረግ የሚጠይቀው ድካም ቀላል አይደለም። ይህም ከሆነ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍትን በዚሁ አዲስ ቋንቋ ለመተርጎም የበለጠ ከባድ መሆኑ ጥርጥር የለውም። እንደ ዋና ሆኖ የሚቆጠረው ችግርም ቋንቋው አዲስና ሰፊ ቃላት የሌለው በመሆኑ የቃላት እጥረት በሰፋ ሁኔታ ስለሚያጋጥም ነው። በአተረጓጎምም ቢሆን ስሕተትና የምሥጢር መዛባት ስለሚያመጣ ነው። ይህም ሆኖ ሰላማ ተሳክቶለት አያሌ መጻሕፍትን ወደ ሀገራችን ቋንቋ መልሷል።
3ኛ አባ ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያ ፀሐይ ዘኢትዮጵያ
ይህ ደግሞ ማለትም ተክለ ሃይማኖት ሐዋርያ የተባለው በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሳ ታላቅ አባት ነው። ይህ ሰው በንጉሥ አርማህ ወይም ዳዊት ዘመን የነበረና እውነተኛውን ወንጌል የሰበከ ሐዋርያ ነው። እርሱም እንደነሰላማ በዚህ ዓለም ነገር ራሱን ሳያጠላልፍ ራሱን ለወንጌል የተለየ ጃንደረባ አድርጎ ዘመኑን ሁሉ በአገልግሎት የፈጸመ አርበኛ ነው። ቀዳማዊና በኩር የተባለው ይህ አባት ከርሱ በኋላ በተነሱ ሌሎች ተክለ ሃይማኖቶች ታሪኩ ጠፍቶና ታሪክ አልባ ሆኖ በርሱ ታሪክ፤ ታሪክ አልባዎቹ እየተሞገሱበት ይገኛሉ።
ይህ ሰው ወንጌልን ያለፍርሃት በድፍረት፤ ያለ ስሕተት በእውነት፤ ያለ መወላወል በጭካኔ የሰበከና ሐዋርያዊ ተልዕኮውን በፍቅርና በሐዋርያዊ ፈለግ የፈጸመ ሰው ነው።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ያገኙት የዚህ ሐዋርያ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ እንደሚለው "ዝኬ ሐዋርያ ዓለም ወሰማዕተ ገዳም ገባሬ ታምር ወመንክር ኃይል ወመስተጋድል መነኮስ ተአሳየ እንጦስ‚ ትርጉም "ይህ የዓለም ሐዋርያ የበርሃ ምሥክር ድንቅና ታምር ያደረገ ብርቱ ተጋዳይ የእንጦስ አሥረኛ ነው‚ ማለት ነው።
ምንኩስና በዘመናችን ብዙ የሚያነጋግርና አሕዛብ ለአማልክቶቻቸው ከገንዘባችው አልፈው ሕየወታቸውን ለመሰዋት ብቸኛና ብሳቢስቴ የሌለው ድኃ ሆኖ በመኖር መታዘዛቸውን ይገልጡበት ዘንድ የሚወስኑት ውሳኔ ነው። ራስን ወይም ሥጋን በመጨቆን ጽድቅ የሚያስገኝ የሚመስለው ይህ ክፉ ትምህርት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገደማ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሰተት ብሎ ገብቶባታል። ቢሆንም ታላላቅና ወንጌልን የተረዱ ቅዱሳን አበው ሲገቡበት ግን ለወንጌል አገልግሎት አስፈላጊ ጊዜን ሁሉ ለክርስቶስ እንደመዋጀት ይቆጠራልና እንደበጎ ሊታይ ይችላል። የምንኩስና ክፋቱ ክፉ ሰዎች ሲገቡበት ጽድቅን ከክርስቶስ አውጥቶ በሰው ድካምና ጥረት እንዲፈጸም ማድረጉ ላይ ብቻ ነው።
በተለይ ምንኩስና እጅግ በከፋ ሁኔታ ምንኩስና መልኩንና ውበቱን እንዲያጣ ካደረጉት ክፉ ሰዎች መካከል እጨጌው ተክለ ሃይማኖትና ከርሱም በኋላ እርሱን አብነት አድርገው የተነሱት ሰዎች ናቸው። ምንኩስና ለወንጌል አገልግሎት እንጂ ለሌላ ለምንም እንደማይጠቅም እየታወቀ ጠማማ ትምህርት በሚያስተምሩ ሰዎች ምክንያት ግን ዓላማውን እንዲለቅና ልዩ ተልእኮ እንዲኖረው የወንጌልንም ቦታ የሚጋፋ የጽድቅንም መንገድ የሚያጣምም ከውነትም መንገድ ፈቀቅ የሚያደርግ እንዲሆን ተደርጓል። በዚህ ዘመን ደግሞ የርኩሰት ሁሉ መገኛ ተቋም ሆኖ ለሰይጣን እያገለገለ ነው።
መራ ተክለ ሃይማኖት
ይህ ሰው በአሥረኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ ሆኖ የአክሱም መንግሥት በዛጐየዎች ከተነጠቀ ከብዙ ዓመታት በኋላ እንደሆነ ይነገራል። ይህ ሰው በንጉሥነት እንደነበረና ወገኑም ከዛጐየዎች ወይም ከነገደ አገው እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ሰው በተክለ ሃይማኖት ስም ቢጠራም የታወቀ ሥራ ታሪክ የለውም።
ዛጒየዎች መንግሥትን በያዙበት ዘመን ግሩም የሆኑ ሕንጻዎችንና ትሪኮችን እንደሠሩ የእጅ አሻራዎች ዛሬም ድረስ ይገኛሉ። ሆኖም ከነዚህ ወገን የሆነው ተክለ ሃይማኖት ግን በታሪክ ሰፊ ቦታ የለውም። እነዚህ ነገደ ዛጒየዎች መንግሥትን ለሦስት መቶ ዓመታት ይዘው በነበረበት ወቅት ከፍተኛ ሥልጣኔ እንዳሳዩ ዛሬም የሥራ ውጤታቸው በግልጥ ያሳያል።
እነ አጼ ላሊበላ፣ እነ አጼ ይትባረክ፣ የመሳሰሉት ሁሉ ከዚሁ ነገድ የነገሡ ናቸው። ሆኖም ለነዚህ ነገሥታት ለታሪካቸው ክትትል ያልተደረገ በመሆኑ ሰፊ ነገራቸውን ለመተረክ ይከብዳል ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን ቤተ ክርስቲያናችን እነዚህን ሰዎች ቅዱሳን በማለት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እየሠራች ታቦት በየስማቸው እየቀረጸች የስግደት አምልኮ እያበረከተችላቸውና ደህንነትም በነርሱ በኩል እንደሚገኝ እየሰበከች ትገኛለች። ከነዚህ ጋርም ምንም እንኳ ከነዚህ ተክለ ሃይማኖቶች ጋር የተቀራረበ ታሪክ ባይኖረውም የጎጃሙ ተክለ ሃይማኖት አሉ።
እጨጌው ተክለ ሃይማኖት
ይህ ሰው በአሥራ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣና የናቱን የእህት ልጅ ይኩኖ አምላክን ቅብቶ ያነገሠ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ያገኙት መረጃ ያረጋግጣል። ይህ ተክለ ሃይማኖት የእጨጌዎች ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነም ተገልጧል። ይህ ሰው ባለትዳር እና ሕጋዊ ቄስ እንደነበርም የራሱ ገድል ይናገርለታል። የዚህ ሰው ገድል ማንም እንዳያነበው እንዳያገኘው ተደርጎ ተደብቆና ተቀብሮ በወይንጌና በበጌምድር ውስጥ በምትገኝ ግራርያ በምትባል አገር ውስጥ ይገኛል። ይህም የተደረገበት አቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መቀለጃ እንዳይሆንና እንዳይዘበትበት እንዲሁም የታሪክ ተወቃሽ ጭምር ነው።
ውስጥ ያለኖሩ ሰው በመሆናቸው ይልቁንም በዚህ ዓለም ላላቸው ዘማዊነትና ምድራዊት ለሆነች ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡና ከነገሥታቱ ጋርም በማለዳ በማዕድ በመቀመጥ የሕዝብንና የካህናትን ጉዳይም በመፍታት ውሳኔም በመስጠት ቀልጣፋ በመሆናችው እንደባለ ሥልጣን የነበሩ ሰው ነች። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ስለዚህ ሰው ሲናገሩ "አኮኬ በአለ ትሩፋት ወፍጹመ ትምህርት አላ ብሩሃ ልብ ወበሊሃ ንባብ ዘርቱዓ ይመትር ነገረ ካህናት ወሕዝብ‚ ትርጉም "ይህ ሰው በጎ ምግባር የለውም በቂ ትምህርት አልነበረውም ነገር ግን አንደበተ ርቱዕና አእምሮው የበራለት ብልህ ሰው ነበር የሕዝብን እና የካህናትን ጉዳይ በአግባቡ በመፍታት ውሳኔም በመስጠት ተወዳጅ ነበር‚ ማለት ነው። ከዚህ ችሎታውና ለመንግሥትም ካደረገው ውለታ የተነሣ ሲሦ መንግስት ተሰጥቶት የመጀመሪያው እጨጌ ተክለ ሃይማኖት ተብሎ ተሹሟል።
በ1042 ዓ.ም በላስቶች ዘመን ተጽፎ ከደብረ ሊባኖስ ወደ አውሮፓ የተወሰደው የሮማውያን ሥንክሳር ስጋዊና ደኃራዊ ነገር ሳይጨምር የመጀመሪያውን ተክለ ሃይማኖት ታሪክ ነገር እንደሚናገር ዲልማንና አንጧን ዲባዲ የተባሉ አውሮፓውያን ግእዝ አውቂ ምሑራን በእንግሊዝ አገር አግኝተውት እንዳዩት ተናግረዋል።
ይሁንና የሐዋርያውን ታሪክና የጨጌውን ታሪክ በአንድ ላይ አደባልቆ አንዱን ባንዱ አጣፍቶ አንድ ተልክለ ሃይማኖት ብቻ አድርጎ የጻፈው ከግራኝ መሐመድ ወረራ በኋላ በአጼ ሚናስ ዘመነ መንግሥት ዮሐንስ ከማ የተባለ ሰው እንደሆነ ሊቁ ገልተዋል። ሊቁ ስለዚህ ሰው የተሰማቸውን ቅሬታ ሲገልጡ የሚጽፍ ሁሉ በጥንቃቄ እንዲጽፍ ሲያስገነዝቡ "ጣፊ ለጣፊ ዋሾ ቀጣፊ ማለት እንደዚህ ያለው ነው‚ብለዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገድልና መጽሐፈ ምሥጢር በሌሎችም ዜና በነቀውስጦስ ገድልም እንደዚህ ያለ ውሸት እንደሚገኝ አስረግጠው ተናግረዋል።
ሰለዚህ ታሪክን የሚጽፍ ሰው ምን ዓይነት ሰው መሆን እንዳለበት ሲመክሩ "ታሪክና ገድልን የሚጽፍ ሰው ምሎ ተገዝቶ እንደሚመሠክር ሰው ወይም የሰውን መልክ እንደሚያነሣና እንደሚስል ሰው እንደዚያ መሆን ሲገባው እውነቱን እውነት ሐስቱን ሐሰት ከማለት ወጥቶ የማይገባውን እንደ አዝማሪና እንደ አሚና ቢያቆላምጥ አለስሙና አለመልኩ ሌላ ስምና መልክ ቢሰጥ ወይም እንደ ባለቅኔ እውነቱን እያሳበለ ሐሰቱን እያስበቀለ ለአዳም ሥጋ ያለተሰጠ ሕዋስ ስድስት ክንፍ አስራ ስድስት ክንፍ እያለ የኩሸት የምጸት ቃል ቢጽፍ ታላቅ እዳ አለበት‚ ብለዋል።
ከግራኝ መሐመድ በኋላ እጨጌው ተክለ ሃይማኖት ከሞተ 254 ዓመት ዘግይቶ ዮሐንስ ከማ የተባለ አላዋቂ ሰው በተለይም እጨጌውን ብቻ የሚያውቅ ሰው በመሆኑ ታሪኩ ምስቅልቅል እንዲል አድርጎታል ምንጊዜም ቢሆን እንደዚህ ያሉ ጸሐፊዎች ብርሃኑን ጨለማ ጨለማውን ብርሃን ስለሚያደርጉ ጣፋጩን መራራ መራራውን ጣፋጭ ስለሚሉ ለሀገርም ለወገንም በሽታዎች ናቸው።
ዮሐንስ ከማ የጻፈውን አሁን በየቤተ ክርስቲያኑ የሚነበበውን ገድለ ተክለ ሃይማኖት ስንመረምረው አለቃ እንዳሉት ለሰው ያለተሰጠ ሕዋስ እግዚአብሔርም ለሰው ያልሰጠው ገጸ ባሕርይ በመስጠት ያስተምራል። ገድሉ ጤናማ አእምሮ ካለው ሰው የወጣ አይመስልም። አይደለምም።
ይህን ተክለ ሃይማኖትን ለርሱ ተብሎ የተጻፈለትን ገድል ገድል ስንመለከተው ዓለት ከተባለውና ከውነተኛው ቤዛችን የሚለይ ፍጹም ክህደት የሞላበት የክፉዎች ትምህርት ነው። ከመጀመሪያውና ከሁለተኛው ተክለ ሃይማኖት የተለየ ከሰውም ወገን የማይመስል ልዩ ፍጡር እስኪሆን ድረስ ተጽፎለታል። የርሱ ገድል የተባለውን ታሪክ እንደሚከተለው ስናቀርበው ሕዝባችን በክፉ ሰዎች ትምህርት እንዴት ተይዞ እንደቆየ እንዴት ተይዞ እንደቆየ እንዲረዳና አሁን አሁን ደግሞ ክፋቱን ሲያገኘው ወደ ሌላ የእምነት ድርጅቶች እንዳይሄድና ባለቤት ቤተ ክርስቲያን በባለቤትነት በመቆም ሐሰቱን እንዲከላከል ለማድረግ ነው። ምንም ለያንዳዱ እንደየሥራው የሚከፍል ጌታ ቢሆንም
"ፍትሑ ለነዳይ ወለጓለ ማውታ ወአጽድቁ ግፉአ ወምስኪነ‚ ልድሀውና ለድሃ አደጉ ፍረዱ የተገፋውንና ምስኪኑንም አድኑ እንደተባለ የመጀመሪያውን አባትና ሐዋርያ በቤተ ሰቡዕ ፍስሐ ጽዮን በኋላም በመንፈሳዊ አገልግሎቱ ተክለ ሃይማኖት የተባለውን አባት ስም ቀምቶ ባለታሪኩን ቀብሮ ታሪክ አልባውን አጽድቆ ስላገኘነው መንፈሳዊ ግዴታችንን ለመወጣት ብቻ ነው።
ገድሉ በጥንቃቄ ተመርምሮ አበይት ክህደቶች የተባሉት በምራፍና በቁጥር ተለይተው እንደሚከተለው ተዘጋጅተዋል። እግዚአብሔር ይልጁን ብርሃን ያብራልን።
"በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ ይህ ተክለ ሃይማኖት ነው‚ ገድ ተ/ ሃይ/ ም 2፥9።
ይቀጥላ
ባሕታዊ ሰይጣን በደብረ ሊባኖስ ገዳም ከተባለው መጸሐፍ የተወደ
በመርጌታ ጽጌ ስጦታው
አቅራቢ ተስፋ
 

4 comments:

 1. እስካሁን በጨለማ ስንከራተት የት ነበራችሁ?

  ReplyDelete
 2. ewenete endihe tafeto sikerebe des yasegal.

  ReplyDelete
 3. ''አሌ ሎን ለእለ ይነቡ አመፃ ላአለ ፃድቅ'' በፃድቅ ላይ አመፃን ለሚናገሩ ወዮላቸው። እግዚአብሔር ያፀደቀውን ማንም አይኮንነውም ። በቤተክርስትያን ስም የምታታልሉ የበግ ለምድ ለባሽ ተኩላዎች የፃድቁ የተክልዬ አምላክ ልቦና ይስጣችሁ። ፃድቁንስ ከተፃፈላቸውና ከሰማነውም በላይ ዛሬ በፀበላቸው፣በንፍሮውሃው፣በመሬታቸው ሁሉ እየደረጉት ያሉትን ተአምሮች በዓይናችን እያየን ነው። የናንተ መሰረት አልባ ዲስኩር ይልቁንም መርጌታ ተብየው የናት ጡት ነካሽ ስድብ ከፃድቁ ፍቅር ልያናውጠን የሚችል አይደለም። ንስሐ ግቡ ተፀፀቱ ዋሽታችሁ ሆዳችሁን ለመሙላት ብቻ አትራሯጡ ።ነገ ሟች ናችሁና። email ethioabis2000@gmail.com ፃፉልኝ

  ReplyDelete
 4. ለመጀመሪያ ጊዜ ስጽፍ ብታወጡትም ባታወጡትም
  ጽኁፉንም አላነበብኩትም ነገር ግን እርሳቸውም ሆኑ መምህራቸው እልም ያሉ መናፍቅ ናቸውና፤ ለዚህም የእነ አለቃ አስረስ የኔ ሰው መጽሕፍትን በደንብና በማስተዋል አንብባችሁ ብትጽፉ እንጂ እነዲሁ በጥራዝ ነጠቅና በስሚ ስሚ ብቻ ባትጽፉ፤ የእነዚህን ሰዎች ትምህርት አብነት አድረጋችሁ መጻፋችሁ ራሱ እጅግ በጣም ስህትት ነው፡፡
  …..ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ…..

  ReplyDelete