Tuesday, October 25, 2011

የለውጥ ያለህ! - - Read PDF

አምላካችን እግዚአብሔር የለውጥ አምላክ ነው፤ ይህ ማለት ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከስሕተት ወደ ትክክለኛነት፣ ከሐሰት ወደ እውነት እንድንሻገር ይፈልጋል ማለት ነው፣ ብረት ሲዝግ ምንም ነገር መቁረጥ እንደማይችል ሁሉ የሰው አእምሮ ሲደፈን፣ ሐስት እውነት ሲመስል፣ ጨለማና ብርሃን ሲቀላቀሉ እግዚአብሔር ዝም አይልም። ግፍ ሲበዛ፣ ፍትሕ ሲጠፋ፣ ባዕድ አምልኮ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባ እግዚአብሔር ይቆጣል። ሰይጣን በእንደዚህ ዓይነቱ ድቅድቅ ጨለማ ተሠውሮ ነገሥታቱን መኳንንቱና ፈራጆችን ለክፋት ሲጠቀምባቸው እግዚአብሔር ዝም አይልም። ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከሰላም ይልቅ ሁከት፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየት፣ ሌብነት፣ ዘረኝነት፣ ጭቆና እና ባርነት ለእግዚአብሔር የሚያጸይፉ ርካሽ ነገሮች ናቸው።
   እኛ የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ትውልዶች በእግዚአብሔር እናምናለን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በተደረገልን ነጻ ስጦታ እግዚአብሔር አስደንቆናል። ፍቅሩን በልባችን አፍሶልናል። ጥንታውያን አባቶቻችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኙትን እንደ እሳት የሚያቃጥል ፍቅር ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል
«በዋእየ ፍቅርከ ከመ ሥርወ አእዋም የብሰ ውሳጤ ሕሊናየ ነደ ወልብየ ጤሰ» በፍቅርህ ሙቀት የልቤ ኃጢአት ደረቀ ሕሊናየ ተቃጠለ ልቤም ጤሰ እያሉ አመስግነውታል [መልካ ኢየሱስ] አባቶቻችንን ያቃጠለው የእግዚአብሔር ፍቅር እኛንም ነካክቶናል። ድሮ ሳናውቀው እንዲሁ በጭፍን ስሙን ስንጠራው ኖረናል ነገር ግን አላከበርነውም ነበር።
   ድሮ ከፊደል ጀምሮ ዳዊት፣ ጾመ ድጓ፣ ድጓ፣ ዜማ፣ አቋቋም፣ ዝማሬ መዋሥእት፣ ቅኔ ስንማር መንፈሳዊ ስሜት ይሰማን ነበር እንጂ በሚገባ አናውቀውም ነበር። ከዚህም ጋር የሰሎሞን ጥበብ ነው ተብሎ ስለሚነገረን ጥንቆላ መማር ግዴታችን ነበር። ይህን ሁሉ ትምህርት ተምረን ያተረፍነው ነገር ቢኖር ግን ትእቢት ብቻ ነበር።  ከመጀመሪያው ወደ ትምህርት ቤት ስንገባ አንዳዶቻችን እግዚአብሔር ቢጠራንም አላማ አልነበረንም፣ አንዳዶቻችን በተማርነው ትምህርት መርጌታ ቄስ ሆነን የገጠር መሬትና ደሞዝ አግኝተን ለመኖር ነበር የተማርነው፣ ሌሎቻችን አማራጭ ትምህርት ስላልነበረን በጊዜው ባካባቢያችን የሚገኘውን ትምህርት ለመማር ነው። በዚያም ይሁን በዚህ ያን ያህል እውቀት ብንሰበስብም እውነተኛ የሕይወት ለውጥ አላገኝንም ነበር።
   እንደተመኘነው በየደብሩ መርጌታ ቄስ ዲያቆን ሆነን፣ በደሞዝ ተቀጥረን መሥራት ጀመረን። ነገር ግን ማታ ማታ ማህሌት ቆመን ስንዘምር፣ የላይ ቤት፣ የታች ቤት፣ አጫብር፣ ቆሜ፣ ፋኖ፣ ቤተ ማርያም፣ ነጠላ፣ ድርብ፣ በሚለው የመለያያ ምክንያት ተኮራርፈን አንነጋገርም። ለመደባደብ ለመሰዳደብ ለመናናቅ የሚያግደን አንዳችም መንፈሳዊ ኃይል አልነበረንም። በየክብረ በዓሉ ሌሊት ስንጮኸው የምናድረውን ነገር ምን እንደሆነ አናውቀውም ነበር።
   ካገልግሎታችን ባኋላ ድሆችን ገፍተን ደጀ ሰላም እንገባለን። የጠላና የጠጁን ዓይነት ጠጥተን ሰክረን ተጣልተን እንለያያለን፣ ሀብታም ስናገኝ የንስሐ  ልጅ እንዲሆነን እንጣላበታለን፣ የሰውየውን ነፍስ ለማዳን ሳይሆን ከርሱ የሚገኘውን ጥቅም አስቀድመን በመገመት እርስ በርሳችን እንካሰስበት ነበር። አዲስ አባባ ሀገረ ስብከት እየሄድን የምንውልበት ጊዜም ነበር፣ ደሞዝ ጨምሩን ሹመት ስጡን ለማለት እንጂ ስለቤተ ክርስቲያን በማሰብ አይደለም፣ ከኛ በላይ የተሾሙ ሰዎች ሙዳዬ ምጽዋት ገልብጠው ገልባጭ መኪና ሲገዙ ስላየን እኛም እንደነሱ ለመገልበጥ እናስብ ነበር።
  ከሁሉ የከፋው መጥፎ ሥራችን ግን ቅዳሴ እየቀደስን፣ ሌሊት ማህሌት ቆመን እያደርን በማግሥቱ ስንጠነቁል የአጋንንትን ስም ስንጠራ ስንቆፍርና ስንቀብር ስናሟርት እንዉል ነበር። ሌሊት የእግዚአብሔርን ስም ቀን የሰይጣንን ስም ስንጠራ ኖረናል። ከየመምህራኑ የሰበሰብናቸው የጥንቆላ መጻሕፍት በርካታ ነበሩ። ይህ ሁሉ ሲኖረን ግን አንድም መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረንም። ወንጌል ሰባኪ ሲባል ከፍተኛ ጥላቻ ነበረን፣ በቤተ ክርስቲያን በአገልጋይ ስም ተመድበን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፈጸምነው ግፍ እጅግ ይዘገንናል። መስተፋቅር ግርማ ሞገስ አቃቤ ርእስ ተብለው የሚታወቁ ጥንቆላዎችን የአጋንንትን ስም እየጠራን ደግመናል። ይህን ሁሉ ስሕተት ስንፈጽም ግን «ይወገዙ» ብሎ ለሲኖዶስ ያቀረበን ግለሰብም ሆነ ማህበር አልነበረም። ማህበረ ቅዱሳንም ሆኑ ጳጳሳቱ ጠንቋይ መሆናችንን እያወቁ አልገሰጹንም ነበር። ዛሬም የታወቁ በርካታ ጠንቋዮች አሉ። ነገር ግን ይወገዙ ተብሎ ለሲኖዶሱ አልቀረቡም።
  አንድ ቀን ከኛ ቀድመው ከሰይጣን እሥራት ነጻ የወጡ ወንድሞቻችን አገኙንና መጽሐፍ ቅዱስን ገልጠን እንድናነብ እረዱን። እነርሱን እየጠላናቸው መጽሐፉን በማስተዋል አነበብነው። በዚህ ጊዜ አስደናቂው የኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃን በራልን። የእግዚአብሔር ፍቅር እንደ እሳት አቃጠለን። ለዘመናት የተማርነው ድጓና ዝማሬ ፊደል መሆኑ ቀርቶ መንፈስ ሆኖ ተገለጠልን፣ ኃጢአታችን እጅግ ከባድ ሆኖ ታየን። የእግዚአብሔር ፍርድም አጠገባችን ደርሶ አየነው። ከልጅነታችን ጀምሮ ስሙን እየጠራን የተማርነው፣ በቅድስት እናቱ ስም እየለመንን በልተን የተማርነው ኢየሱስ፣ ነገር ግን ያላወቅነው ወዳጃችንን አገኘነው። ጉልበት ሁሉ የሚንበረከክለት የናዝሬቱ ኢየሱስ እኛን ጠላቶቹን በፍቅሩ ከእግሩ ጫማ በታች አንበረከከን። የተኮፈስንበት እውቀታችን ወደ ሲኦል እየወሰደን እንደነበር ተገነዘብን፤ ትቢታችን ወደቀልን፣ የነበርንበትን ጨለማና የሚጠብቀንን የዘላለም ቅጣት ስናመዛዝነው እጅግ አለቀስን፣ በፊቱ ሰግደን ጌታ ሆይ እኛን ኃጢአተኞችን ይቅር በለን አልነው። ኃጢአተኞችን ሊያድን የመጣው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ይቅር አለን። ሕሊናችንንም በደሙ አንጽቶ ቀደሰን፣ ከዘላለሙ ፍርድም አዳነን፣ ከሞት ወደ ሕይወት ተሻገርን፣ ከሰይጣን አገዛዝ ነጻ ወጣን።
 ሰይጣን ግን በኛ ላይ ተቆጣ ድሮ ጠንቋዮች ሳለን ደጋፊያችን አድናቂያችን መቋሚያችንን እየተቀበለ በከበረ ሥፍራ ያስተናግደን ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ደርሶልን ከሞት ወደ ሕይወት ስንሻገር ግን «ተሃድሶዎች ናቸውና ይወገዱልኝ» አለ፤ እየከሰሰ እየደበደበ ከቤተ ክርስቲያናችን እንድንወጣ ታገለን፣ ሥራውንና ምሥጢሩን ስለምናውቅበት ደግሞም ስለምናፈርስበት ውጡልኝ ይለናል። እኛ ግን እርሱን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናስወጣዋለን እንጂ አንወጣለትም።
  እግዚአብሔር ነጻ አውጥቶ አልተወንም፣ ራእይ ሰጥቶናል፣ በጥንቆላችን ያጠፋነውን ሕዝብ በወንጌላችን እንድንመልሰው ልኮናል። አሁን ያለው የተዘበራረቀ አምልኮና በሙስና የተበላሸ አስተዳደር ይስተካከላል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ሊመስል ይችላል። እግዚአብሔር ግን ለዘሩባቤል የተናገረውን ለኛም ደግሞታል «ታላቅ ተራራ ሆይ አንተ ምንድን ነህ በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናልህ» ዘካ 47 የሚል ቃል ተነግሮበታል። የኛ ራእይ የእግዚአብሔር ክብር በኢትዮጵያ ሞልቶ ማየት፣ ኢትዮጵያ በሰማያዊና በምድራዊ በረከት ተባርካ ማየት ነው።
 ለውጥን በአመጻ ወይም በጠብ መንጃ እናመጣለን ብለን አናስብም፣ እኛን በለወጠን በወንጌል እንጂ፣ በአባቶቻችን ፊት መንፈሳዊ ካባ ለብሰን የአመጽ ጩኸት አንጮህም።
«አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰማ ቃሎሙ ውስተ ኩሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ» «ነገር የለም መናገር የለም ድምጻቸውም አይሰማም ድምጻቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ምድር ዳርቻ ወጣ» ተብሎ እንደተጻፈው መዝ 184 ፉከራ እና ሽለላ ሳናደርግ ነገር ሳንጠመዝዝ ክፉውን ትተን የምስራቹን ወንጌላችንን በትሕትና እንሰብካለን።
ለሚያሳድዱን እንጸልያለን፣ የሚረግሙንን እንመርቃለን፣ ወደኛ የሚመጡትን እውነቱን እንነግራለን፣ ሌላ አላማ ከጀርባችን የተደበቀ ያልተገለጠ ሥውር ነገር የለንም። አላማችን መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት ብቻ ነው። የሃይማኖት ወይም የባሕል ለውጥ ለማምጣት ፍላጎቱም ሆነ ጊዜው የለንም፣ አንፈልገውምም፣ እኛ ያየነውን የክርስቶስ ብርሃን ሕዝባችን እንዲያየው እንፈልጋለን፣ እኛ የእለት ጉርስ ለማግኘት የምንጨነቅ ሰዎች እንጂ በፈረንጅ ዶላር የተንበሸበሽን ሰዎች አይደለንም፣ እንደዚህ የሆኑ ወንድሞች ቢኖሩ እንኳ ደስ ይለናል እንጂ አይከፋንም። እኛ ግን ወደ ድሮው ኮፌዳችን ተመልሰናል። እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ትንሣኤ እስኪያሳየን ድረስ እረፍት አይኖረንም።
  ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ መሠረት ያላት እናታችን ናት። ለሐገራችንም ሆነ ለኛ መልካም ናት። ነገር ግን ጠላት በውስጧ ሸምቆ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመዋጋት ላይ ይገኛል፤ ውጊያችን ከዚህ ጠላት ጋር ነው። ከማህበረ ቅዱሳን ጋር የዓላማ እንጂ የግል ጠላትነት የለንም፣ የሥጋ ወንድሞቻችን፣ አብረን የምንሠራ፣ የምንተዋወቅና በግል አብረን የምንውል ነን፣ ነገር ግን ዓይናቸው እንደኛ ስላልበራ የሰይጣን መሳሪያ ሆነዋልና እንገስጻቸዋለን፣ በነርሱ ላይ ክፉ እንዲደርስ አንመኝም አንፈልግምም፤ እንዲለወጡና ለኢትዮጵያ እንዲጠቅሙ እንጸልያለን እንጂ።
  እጅግ የሚገርመን ግን ድሮ ጠንቋይ ሳለን ሲያደንቁን ኖረው ዛሬ ተለውጠን ወንጌል ስንሰብክ ይወገዙልን ማለታቸው ነው። በቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ጠንቋዮች ሰይጣንን የሚጠሩና የሚያመልኩ መኖራቸውን እያወቁ በአሁኑ ሲኖዶስ ከዘረዘሯቸው ሊቃውንት ስም ዝርዝር ውስጥ አንድም ጠንቋይ ይወገዝልን ብለው አላቀረቡም፣ እስከ አሁን ድረስ በቤተ ክርስቲያናችን በታሪክ በሲኖዶስ ደረጃ ጠንቋዮች ተወግዘው አያውቁም። ለምን ይሆን?
  ስለዚህ ድሮ ክፉ ስንሠራ አድናቂያችን የነበረ ዛሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ሕያው ስንሆን ይወገዙልኝ የሚለው፣ ድሮ ስናገለግለው የነበረው መንፈስ ነው፣ ሊበቀለን ይፈልጋል። መስሎት ነው እንጂ አይችልም ሥራው መፍረሱም አይቀርም። አሁን ለሲኖዶሱ ከሶናል ለምን ድሮ ክፉ በነበርንበት ጊዜ አልከሰሰንም? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ በእርግጥ ሲኖዶሱ በቀረበለት ክስ መሠረት ያወግዘን ይሆን? ወደ ፊት የምናየው ይሆናል።
ለማንኛውም ለውጥ እንፈልጋለን ደግሞም የሚለውጥ ፍቅር በጌታ ይዘናልና ለውጥ እናመጣለን። እግዚአብሔር ከኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?
  ከጌታ ምሕረትን ያገኘሁት መርጌታ እሱባለው ነኝ

21 comments:

 1. አይ መሪጌታ ጌታን ሳታውቅ ስንት አመት ስራ ቦታህ ተመላለስክ? ከተራ ምዕመን አንሰህ:: አንተ ለደሞዝ ስራ ቦታ እኛ ምዕመናን ለፅድቅ ቤተ ክርስቲያን ተመላለስን:: ግና ተከፍሎት እግዚአብሄርን የሚያገለግል የበለጠ ከተከፈለው ሰይጣንን ያገለግላል የተባለው አባባል አንተ ላይ ተግባራዊ ሆነ:: የተሻለ ወደከፈለህ (ምናልባትም ሁለተኛ ደሞዝህን) ዞር አልክ ማለት ነው:: ዠግና

  ReplyDelete
 2. መርጌታ እሱባለው Talking and walking are 2 different things. Try to be at least humble let alone pretending that you are a christian.Your story doesn't show you are changed from ጠንቋይ to christianity.You have never mentioned how our fathers are benefited from ዳዊት፣ ጾመ ድጓ፣ ድጓ፣ ዜማ፣ አቋቋም፣ ዝማሬ መዋሥእት፣ ቅኔ by praising and thanking God. Again per your story you have never been and are not a christian. If you are not a fake መርጌታ you still have a chance to be a christian. Will pray for you so that God show you mercy upon you.

  ReplyDelete
 3. ለአንተ የገለጸውን ለሌሎች ወንድሞቻችን ሁሉ በተለይ ለማኅበረ ቅዱሳንም የክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስ እሳት እንዲነካቸው የሁልጊዜ ጸሎታችንና ምኞታችን ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው አይዣችሁ

  በእንተ ማርያም ብለዉ በናቱ ስም ለምነው ከተማሩት አንዱ ነኝ

  ReplyDelete
 4. I am always confused about those who gives insulting comments. Comment means, giving opinion in a positive or negative ways. Not insulting the writer. This is being illiterate and ignorant and shows that you do not have any constructive ideas to suggest. It is very useful to give a negative comments if supported by facts. When ever you can not produce facts, you bark like a dog. I don't think these people are Christians. You do not even know what Christianity means. Don't you know insult is a Sin by itself. God Bless You!!

  ReplyDelete
 5. I am a priest living in united states of america , mergeta esubalew will come our lord Jesus christ , i am praying to come all anti - wongel mergetas and mk . Without wongel life is bitter. We are lost without him (Jesus christ).

  ReplyDelete
 6. ይግረማችሁ እኔም ሌላው መሪጌታ ነኝ። ከመሪጌትነቱ ሙያ ባሻገር በጨለማው አሠራር የተካንኩኝ ነበርኩ! እግዚአብሔር በሚያውቀውና እኛም በኖርንበት እውነተኛ ሕይወት ከ1000 ሺህ መሪጌቶች 1 ሰው ከአስማት አጠራርና ከጠልሰም አሰራር ጋር ግንኙነት የሌለው ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ እግዚአብሔር ምስክሬ ነው። ድጓው፤ ጾመድጓው፤ ነገረ ማርያሙና ድርሳኑ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት እጅግ ብዙ ቃል ይኑረው እንጂ በውስጡም የእግዚአብሔርን ክብር የሚቀንስና ፈጣሪነቱን የሚክድ፤ ትርጉማቸው አንድም ቀን ተነግሮ የማያውቁ አስማት የሞላባቸው በመሆናቸው የምናመሰግነው ሁሉ እውነት ይመስለን ነበር። ለዚህ ዓይነቱ እውነትን ከለላ ባደረገ ጣልቃ ገብ መንፈስ የተነሳ እኛም ይህንኑ መንፈስ አብልጠን በመሻት ላይ በመጠመድ ጠቢብ ነው የተባለውን ሁሉ ደጅ ስንጠና ቆይተናል። መስተአብድ፤ መስተሐምም፤ ዐቃቤ ርእስ፤ መስተባርር፤ መድፍነ ፀር፤ አምጽዖ ብእሲት፤ መቅትል፤ ዘኢያወርድ፤ መግረሬ ፀር፤ መስተፋቅር ወዘተ ዓይነቱን ቁጥር የለሽ የአስማት አሰራር የዜማ ይሁን የአቋቋም ወይም የድጓ ወይ የዝማሬ መዋስእት ተማሪ ሲሆን ሁሉን ካልሆነም የተፈተነውን እንደሚይዝ ምንም ጥርጣሬ የለም። መዝሙረ ዳዊትን መሰረት የማያደርግ የድጓም ሆነ የዝማሬ ትምህርት እንደሌለ ሁሉ ዳዊትን መሰረት የማያደርግ የጥንቆላ አሰራር የለም። «ወስኮሙ ጌጋየ በዲበ ጌጋዮሙ፤ ወኢይባዑ በጽድቅከ፤ ወይደምሰሱ እመጽሐፈ ሕያዋን፤ ወኢይጸሐፉ ምስለ ጻድቃን፤ ወይረድ ላእሌሆሙ ዲበ መዓት» መዝ 68፤22 «በኃጢአት ላይ ኃጢአት ጨምርባቸው፤ ወደጽድቅህ አይግቡ፤ ከሕያዋንም መጽሐፍ ስማቸው ይደምሰስ፤ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ፤ ቁጣህ በላያቸው ላይ ይፍሰስ» እያልን የምንጠላው ሰው ላይ ለራሳችን ፍላጎት ወይም ሰዎች የሚጠሉትን እንድናጠፋላቸው ፈልገው ገንዘብ ሲከፍሉን 1 ሱባዔ፤ 2ሱባዔ ስንረግምላቸው ኖረናል። የሚገርመው ደግሞ እኛ መሪጌቶቹ ይህንኑ ቃል ጳጳስ ይሙት ቄስ፤ ምእመን ወንድ ይሁን ሴት፤ ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ሞቶ ጸሎተ ፍትሃት ለማድረግ ሬሳውን ከበን ይህንኑ እርግማን እናወርድበታለን። «ስሙ ከሕይወት መጽሐፍ ይደምሰስ» ብለን ለምናደርሰው የጸሎተ ፍትሃት ሬሳ ቤተሰቦቹ ገንዘባቸውንና የእህል ውኃ ድግሳቸውን ያቀርቡልናል። የዳዊቱን ቃል እየመረጥን በህይወት እያለን ለመግደያና ለማሳመሚያ በእርግማን፤ ሲሞቱ ደግሞ ነፍሳቸው ከህይወት መጽሐፍ እንዲፋቅ እግዚአብሔርን ስንጠይቅ ኖረናል። ዛሬም ይህ ይሰራበታል። ይህንን የማታደርግ ቤተክርስቲያን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አትገኝም። ያውም እኔ በትንሹ ተናገርኩ እንጂ ጉዱ ብዙ ነው። ደረቅ ተቃዋሚ ውሸትህን ነው የሚለኝ ካለ ይሂድና የንስሐ አባቱን ወይም የፈለገውን መሪጌታ ይጠይቅና ያረጋግጥ። ከላይ እውነቱ በራልን ያለው መሪጌታ ከዚህ ዓይነቱ የእርግማንና የማጥቂያ የጭለማ አሰራር ወጣሁ ነው እያለ ያለው፤ ታዲያ ይሄንን ከመተው የበለጠ መዳን ለሰው ልጅ ይኖር ይሆን? ኅሊና ያለው ይፍረድ!!!!!

  ReplyDelete
 7. ውይይታችሁ መልካም ነው ነገረ ግን ''ከጌታ ምሕረትን ያገኘሁት መርጌታ እሱባለው ነኝ'' ማን እንደሆነ የት እንዳለ ማወቅ ፈልጌ ነው
  እግዚሀብሄር ሰላሙን ይስጠን

  ReplyDelete
 8. Anonymous said...
  አይ መሪጌታ ጌታን ሳታውቅ ስንት አመት ስራ ቦታህ ተመላለስክ? ከተራ ምዕመን አንሰህ:: አንተ ለደሞዝ ስራ ቦታ እኛ ምዕመናን ለፅድቅ ቤተ ክርስቲያን ተመላለስን:: ግና ተከፍሎት እግዚአብሄርን የሚያገለግል የበለጠ ከተከፈለው ሰይጣንን ያገለግላል የተባለው አባባል አንተ ላይ ተግባራዊ ሆነ:: የተሻለ ወደከፈለህ (ምናልባትም ሁለተኛ ደሞዝህን) ዞር አልክ ማለት ነው:: ዠግና

  ReplyDelete
 9. ቂቂቂቂቂ!!! ሬሳ ይሁን ሬሰ አስተያየት ሰጪ- ምን ብለህ ነው መሪጌታ እሱባለውን የፈለግኸው? ባታውቀው ለማቅ ክስህን ልታቀርብ ነው ወይስ መሪጌታ እሱባለው የሚባል ስለምታውቅ እሱ ነው አይደለም የሚል ጥርጣሬህን ልታረጋግጥ? ቅን ሰው ከሆንክ እሱን ከመፈለግ ይልቅ እሱ ያስተላለፈልህን ቃል ለመለወጥ ተጠቀምበት!!!

  ReplyDelete
 10. ደጀ ሰላሞች?
  በሌላ ርእስ ‘ማንያዘዋል’ ያላችሁት እንደዋዛ ወደ ብሎጋችሁ ብቅ እንድታደርጉት ያስገደዳችሁ የናንተ ሰዋዊ መንፈስ ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ ነው። የሐሳዊው መሲሕ ነጠላ ለብሶ በቁጥር አንድ እዛም እዛም እያለ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚያምሳት ያለ ፍጡር እሱ ነው። ይግረማችሁ ወሬን ለቅሞ አባት ካባት፣ ሰንበት ተማሪ ከሰንበት ተማሪ፣ትኦሎጂያን ከማህበረ ቅዱሳን፣ ዘማርያንና ሰባክያን እርስ በርሳቸውና ከማቅ፣የድርጅት ሰራተኞች ከድርጅት ሰራቶች፣ ምእመናን ከምእመናን፣ ግለ ሰው ከራሱ ጋር ለማጋጨት የማይገኝበት ክፍለ ሀገርና ቤት የለም፤ የጠንቋይና ዘማ ቤት ሳይቀር ማለትዬ ነው። “ቆማጣ ቆማጣ ካላሉት መሐል ገብቶ ይፈተፍታል” እንደ ተባለው ይህ ግብረ እከይ የሞላበት ሰውዬም ርእስ ይዛችሁ በብሎጋችሁ የቅሌት ካባን ካላከናነባችሁት አልታወቅሁም በማለት የተየያዘውን ሰይጣናዊ ስራ እስከ ግብዓተ መሬቱ ይቀጥልበታል።
  እባካችሁ አደራ እንደዋዛ አትዩት፤ እንድያውም መንግስት ተከታትሎ እርምጃ እንዲወስድበት የሚቻል መንገድ ካለ ማሳወቁ መልካም ነው።

  ReplyDelete
 11. it is very nice topic i am also a Monk(abba) saved by our Lord Jesus Christ i will pray to God to give good mind to mk.

  ReplyDelete
 12. The most highly God bless you! yes, the accuser are our brother and sister, but knowingly or unknowingly serving devil.

  ReplyDelete
 13. መርጌታ እሱባለው please include your current picture, contact address,profession so that we know this is a real story.

  ReplyDelete
 14. Why should I listen to 'meregeta esubalew' and the likes of him! After all Judas Iscariot was among the disciples of Jesus, the same is with esubalew and the likes of him. Just replicas of Judas Iscariot! I have been with the protestant church for more than 10 years, everything there is false, no life in it and it's a betrayal of the Lord and the Creator of Jesus. Thanks to the Almighty, while 'meregeta' esubalew and his likes are going for death to the protestant churches, I back to the holly and the oldest church again, thanks to the Almighty! Tefiche yeneberehu sihon Ye dingil mariam lij adanagn!

  ReplyDelete
 15. Yegna mergeta mejemeria rasihin mermir ? Sim ayatsedkim ? Endihnegn slalk manem ayaminhm mikinyatum kehawaryat mekakel yhuda wetual , kelikawent abew degmo yante yegbr abat "ARIWOS " Kehiwot menged wetewal antem felegachewn bemeketelh litazenlh ygebal ! Lebonahn ymelislh !!!

  ReplyDelete
 16. it is from devils who make loud without any evidence.it is true you are giving support to devils since you are out of truth.All who want to suffer MK,are working with diabloas.please mind,rehearse to get your original personality.otherwise you are driven by diabloas.
  if you suffer mk,you are suffering God,but you couldn't.our truth is God,not merigata.if merigeta may be fake,he is his fault.he is not our example.God is the only one how to

  ReplyDelete
 17. I wonder on the comment of Zewde about the guy manyazewal. i know him he is always in teklay betekhinet wanderering. even he has no his own house but he is living in different houses. really meaningless person.

  ReplyDelete
 18. መንፈሳዊ እውርነት ከአካላዊ አይነ ስውርነት ይልቅ የከፋ ነው:: አንዳንዶች በዚህ ቦታ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ከጭፍን እውርነት ብቻ የሚመነጭ ነው:: ጥያቄያችሁ መሪጌታ ሆኖ ጠንቁዋይ የሆነ የለም ከሆነ የምዕራቡን አለም አብያተ መጻህፍት ያጨናነቁትን የአስማት መጻህፍቶቻችንን ከመልክአ ሳጥናኤል ጋር መመልከት ነው:: ጠዋት አሐዱ አብ ቅዱስ ብለው ማታ ከአጋንንት ጋር የሚዋረሱ ምእመናኖቻችንን በደብተራ መንፈስ የያዙ መኑ ስምኪ ( ስምሽ ማነው) አይቴ ብሔርኪ ( ትውልድሽ የት ነው) እያሉ በጥንቆላቸው የመበለቶችን ቤት የሚገፍፉ ብዙዎች ናቸው:: እነዚህ በዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን የሉም የሚሉት የጠንቁዋዩ ልጆች ብቻ ናቸው:: ከዚያ ይልቅ እውነቱን አምኖ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን እንዲያጸዳ በጸሎት የቅዱሳን አምላክ ወደሆነው ወደ እርሱ መቅረብ ነው:: ይህን ማድረግ ፕሮቴስታንትነት አይደለም:: ፕሮቴስታንቱም አለም ቤተ ክርስቲያናችን እየታገለች ያለችበት ችግር በእጥፍ ያለበት አለም ነው::

  ReplyDelete
 19. ውሸት ምን ርግልሃል እራስህን እንደ ውስጥ አዋቂ በመቁጠር ሚስጥር ያውጣህ በሚመስል ሁኔታ ላማጥላላት ያደረከው ሙከራ ከሙከራነት አያልፍም በቃ አንተ ተሸውደኃል ይበቃል ሌላውን በማስመሰል ለማጻለል መሞከር ምንም አይጠቅምም ደሞ እኮ ሚገርመው ቀዳሴውን በሌላ ቦታ ሲመቻችኁ ትተቻላቸሁ እንደገና ደሞ አሁን ቅዳሴ ተደፈረ ብለህ የማስመስል ንግግር ትናገራልሀ ደሞ አንተ ጥንቆላ አልተማርክም አትችልም መቼም ሰው እንደዚህ ሲባል ቶሎ ያምናል ብለህ ነው እንጂ ደሞ ምን ስንል (ማህሌት ሲቆም) እንደምናድር አላውቅም ያልከው እውነት ነው እንዳታውቅ የከለከለህ ኖሮ ሳይሆን ደደብ ስለነበርክ ነው አሁንም ያወክ መስሎህ ከሆነ ተሳስተሃል እኛ ግን ምን ሲባል እንደሚታደር እናውቃለን፡፡ ደሞ ድሀ ግፍተን ጠጅ ጠጣን ትላለህ አታፍርም አንተ ራስህ አሁን የተውከው ጠጅ እንደሌለ ስላወክ ነው ቢኖር አሁንም ተመልስህ ተጋፍተህ እንድምትገባ ይታወቃል ዋናው ቆመው አድረው መሆኑን አለመካድህ ጥሩ ነው ቆሞ ያደረ ምናለ የፍልግውን ቢያደርግ መቼም ለሰራ ዋጋው ገባዋል መቸም ካህን ሲባል አለበት ያልከውን ድካማ ጎን በመጠቀም ማጥላላት ነው የፈለከው ግን አትልፋ ሁሉም ነገር ክርስቲያኑ ህዝብ ያውቀዋል ልፋትህ ከንቱ እንደሆነ እወቅ ማንም በዚህ የሚታለል የለም እሺ
  አረባካቸሁ አትዋሹ!!!!!

  ReplyDelete
 20. Please post again, there was a big mistake in my earlier comment.

  Why should I listen to 'meregeta esubalew' and the likes of him! After all Judas Iscariot was among the disciples of Jesus, the same is with esubalew and the likes of him. Just replicas of Judas Iscariot! I have been with the protestant church for more than 10 years, everything is false there, no life in it and it's a betrayal of Jesus, the Lord and the Creator of the whole world. Thanks to the Almighty, while 'meregeta' esubalew and his likes are going for death to the protestant churches, I am back to the holly and the oldest church again, thanks to the Almighty! Tefiche yeneberehu sihon Ye dingil mariam lij adanagn!

  ReplyDelete
 21. no one can scape from the truth

  ReplyDelete