Wednesday, December 28, 2011

ጸሎት ወደ ማን ይጸለያል? - - - Read PDF

ጸሎት ማለት «መነጋገር» ማለት ነው። መነጋገር ማለትም «መናገርና ማዳመጥ» ማለት ነው። መናገር ብቻ ጸሎት አይሆንም። ካላዳመጥን መልሱን ላንሰማ እንችላለን። ከማን ጋር ነው የምንነጋገረው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ አጭር ነው፤ ሰምቶ መልስ መስጠት ከሚችለው ከልዑል እግዚአብሔር ጋር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ይሰማል ይናገራልም። አባቶቻችን ይህን ሁኔታ ሲገልጡ "ጸሎት ብሂል ተናግሮ ምስለ እግዚአብሔር [ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ማለት ነው] ብለዋል።

 ጸሎት «መናገር እና ማዳመጥ» መሆኑን ከሃና እመ ሳሙኤል እንማራለን «እርስዋም በልብዋ ትመረር ነበር በእግዚአብሔርም ፊት ጸለየች፥ ጽኑ ለቅሶም አለቀሰች እርስዋም አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ፤ የባሪያህን መዋረድ ተመክልከተህ ብታስበኝ፤ እኔንም ባትረሳ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም ብላ ስለት ተሳለች» ይላል 1ሳሙ 110-11 ይህ የሃና መናገር ሲሆን መልሱን ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ያዳመጠች መሆኗን ደግሞ፣ ቃሉ እንዲህ በማለት ይመሰክራል «ሴቲቱም መንገዷን ሄደች በላችም ፊትዋም ከንግዲህ ወዲያ አዘንተኛ መስሎ አልታየም» 1ሳሙ 118
 ሃና የራሷን ንግግር ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በመንፈሱ ለመንፈሷ የተናገረውንም ስላዳመጠች፤ ከዚያን ቀን ጀምሮ ልመናዋን እንደተቀበላት አምና በደስታ መኖር ጀመረች። ከጸሎታችን በኋላ የሸክም መቅለል፣ የመንፈስ እረፍትና የልብ ደስታ ካገኘን እግዚአብሔር ተናግሯል ማለት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ «በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል የምንለምነውንም ሁሉ እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደተቀበልን እናውቃለን» ብሏል 1ዮሐ 514-15

 ጸሎት በማን ስም ይጸለያል?

«እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድርጉት» ቈላ 327 በጸሎታችን ጊዜ ምሥጋና፣ ዝማሬ፣ የኃጢአት ኑዛዜና ምልጃ ይኖረናል። ጌታ አባታችን ሆይ ካልን በኋላ «ስምህ ይቀደስ» በማለት ጸሎታችንን በምስጋና እንድንጀምር አስተምሮናል። ከዚህ ቀጥሎ መንግሥቱ ወደኛ እንድትመጣና እንድትገዛን፣ ፈቃዱ ምን እንደሆነ በየቀኑ እንዲገልጥልን፣ የዕለት እንጀራ እንዲሰጠን፣ ወደ ፈተና እንዳንገባና ከክፉ ሁሉ እንዲጠብቀን እራሳችንን አደራ እንሰጠዋለን፤ ከዚያም ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን እንናዘዛለን፤ ሌሎች ወንድሞቻችንንም ሁሉ ለኛ የለመንነውን ለነርሱም እንዲያደርግላቸው እንማልዳለን። ይህን ሁሉ የምናደርገው ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና አብም ስለወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ» ብሎ አስተምሮናል ዮሐ 1413-14 የቤተ ክርስቲያናችን እውነተኛ አባቶችም የጸሎታቸው ማሳረጊያ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም መሆኑን «ባንድ ልጅህ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ያለ ክብር ጽንዕ ላንተ ይገባል ከርሱ ጋራ ከመንፈስ ቅዱስም ጋራ ዛሬም ለዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን» የሚለው ጸሎት ያረጋግጣል። /መጽሐፈ ኪዳን/

  ታዲያ ወደ አረፉ ቅዱሳንና ወደ መላእክት መጸለይ ከየት የተገኘ ነው?

በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ስለሁሉም ነገር በግልጥ ሲናገር፤ ወደ አረፉ ቅዱሳንና ወደ መላእክት መጸለይ እንደሚገባ ግን ምንም ፍንጭ አይሰጥም። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው የተመዘገበ ቅዱሳንና ኃጢአተኞች እንኳ ወደ እግዚአብሔር ብቻ እንደጸለዩ የታወቀ ነገር ነው። ለምሳሌ የፈሪሳዊዉንና የቀራጩን ጸሎት በሉቃስ ወንጌል 18 9-14 ብንመለከት ሁለቱም ወደ እግዚአብሔር እንደጸለዩ ነው። «ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳን አልወደደም ነገር ግን አምላክ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር» ይላል። ቀራጩ ኃጢአተኛ መሆኑ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ቢያስፈራውም፣ ጸሎቱን ግን እንዳይጸልይ የከለከለው የለም። ስለዚህ እኛ ኃጢአተኞች ስለሆንን ወደ ቅዱሳን እንጂ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ የለብንም የሚለው የማህበረ ቅዱሳን ትምህርት፣ የሰዎች የአእምሮ ፍልስፋና እንጂ በጌታ ቃል የተደገፈ እምነት አይደለም።

 እኛ ቅዱሳንን ጸልዩልን ብለን መጸለይ እንደሚገባን ሊያስተምሩን የሚፈልጉ አንዳንዶች የነዌን እና የአብርሃምን ጉዳይ ከሉቃስ ወንጌል በመጥቀስ ነው። ቃሉን አስተውለን ስናነበው ግን ሐሳባቸውን የሚያፈርስ እንጂ የሚደግፍ አይደለም። በሉቃስ ወንጌል 1618-31 ላይ የሚገኘው የአብርሃም የአላዛርና የነዌ ታሪክ ነው። ታሪኩ ባጭሩ ይህን ይመስላል።

ነዌ የሚባል በምቾት የሚኖር እጅግ ባለጠጋ ሰው ነበር፤ በነዌ መውጫና መግቢያ ላይ ደግሞ በቁስል የተወረሰ እጅግ ድሃ ሆኖ የሚኖር አላዛር የሚባል ሰው ተኝቶ የኖር ነበር። ነዌ ከራሱ አልፎ ውሾችን የሚያጠግብ ባለጠጋ ሲሆን አላዛር ግን የውሾችን ፍርፋሪ እንኳ ማግኘት የማይችል ምስኪን ረሃብተኛ ነው። ሁለቱም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፤ በምድር ላይ እያሉ እኗኗራቸው የተለያየ እንደነበረ ሁሉ በሰማይም ተለያዩ፤ ነዌ እንደጭካኔው ወደ ጨካኞች ሀገር ወደ ሲኦል ሲሄድ፣ አላዛር ግን ደጋግ ወደ ነበሩት ወደእነ አብርሃም ሀገር ሄደ። ነዌ የገባበት ቦታ የቃጠሎ ቦታ ነው፤ አንድ ቀን አብርሃምንና አላዛርን ከሩቅ አያቸውና «አብርሃም አባት ሆይ ማረኝ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አላዛርን ስደድልኝ» በማለት ጮኸ።
  ይህ የነዌ ጩኸት ከንቱ ነበር፣ በመጀመሪያ ነዌ ከተቀበለው ፍርድ የተነሣ እየጮኸ እንጂ እየጸለየ አልነብረም፤ ሁለተኛ ጩኸቱን ያቀረበው በአካለ ነፍስ ወዳየው ወደ አብርሃም እንጂ ወደ እግዚአሔር አይደለም፤ ሦስተኛ ነዌ አልዓዛርን ስደድልኝ ማለቱ ትክክል አይደለም ምክንያቱም አልዓዛር ወደ ሲኦል ቢገባ እርሱም ይቃጠላልና ነው። ስለዚህ የማይጠቅም ጩኸት ነው። ጌታ በቃሉ በሲኦል የሚደረገውን ጩኸት ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ብሎ ይጠራዋል እንጂ ጸሎት ብሎ አልጠራውም። «አብርሃምና ይስሐቅን ያዕቆብንም ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ባያችሁ ጊዜ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፣ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል» ይላል ቃሉ ሉቃ 1328  ቅዳሴ ጎርጎርዮስም «ያን ጊዜ ጻድቃን ስለ ኃጥአን ያለቅሳሉ ኃጥአንም  ወዮልን እያሉ ይጮኻሉ ነገር ግን የማይጠቅም ጩኸት ነው» ይላል። የነዌ ጩኸትም ይኸው ነው።

  አብርሃምም ለነዌ ጩኸት የሰጠው መልስ «ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ። ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ» የሚል ነበር 25-26

 ገደሉ፦ በእውነትና በሐሰት፣ በክፋትና በደግነት፣ በቅድስና እና በርኩሰት፣ በጽድቅና በኩነኔ መካከል ያለ ልዩነት ነው። በእግዚአብሔር መንግሥት በዘመድ በወዳጅ በጓደኝነት ወይም በማጭበርበር መሥራት የለም። ይህን እንዳይሆን የእግዚብሔር እውነተኛ ፍርድ እንደ ጽኑ ግንብ ሆኖ ቆሟል። ይህን ገደል ለመዝለል መሞከር ስብራትን ያመጣል። አብርሃም ለነዌ ቢራራለትም ገደሉን ማለፍ እንደማይችል አስታወቀው። ነዌም ከገነት ወደ ሲኦል በሚላኩ ጻድቃን ትንሽ እረፍት እንደማይገኝ አወቀ። ከዚህ በኋላ ለወንድሞቹ  እንዲህ ሲል ማለደላቸው።

 «እርሱም። እንኪያስ፥ አባት ሆይ፥ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤ እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ» 27-28 ነዌ በዚህ ጥያቄው በምድር ላይ ቃሉ ተሰብኮላቸው ክርስቶስን ተቀበልው ንስሐ ያልገቡ ሰዎች፤ በሰዎች የማይጠቅም ጩኸት ቀጥታ ወደ ገነት እንደማይገቡ ተረድቷል። እንዲያውም ንስሐ ያልገቡ ሰዎች ሥፍራቸው እርሱ ያለበት እንደሆነ አውቋል። ስለዚህ አንድ የሞተ ሰው ከገነት ወደ ምድር ሄዶ ይስበክላቸው የሚል ጥያቄ አቀረበ። ይህም ትክክል አይደለም መቼም በምድር እያለን እንጂ ሲኦል ከገባን በኋላ ትክክል እንሆናለን ወይም ባማላጅ እንወጣለን ብለን ማመናችን ስሕተት ነው «የመዳን ቀን አሁን ነው» ተብሎ ተጽፏልና።
 ነዌ ትክክል አይደለም ያልሁበትን ምክንያት ላብራራ፦ በመጀመሪያ ነፍሳትን ከገነት ወደ ምድር ሊሰድ የሚችል አብርሃም አይደለም፤ ሙታንን የሚያስነሣ እግዚአብሔር ብቻ ነውና። ሁለተኛ አልዓዛር ጎረቤቱ በነበረበት ጊዜ የውሻ ፍርፋሪ እንኳ ሊያካፍለው ያልወደደ ሰው ሆኖ እያለ፣ ዛሬ ወደ ምድር ልኮ ውለታን መፈለግ ያልዘሩትን ማጨድ ነው። እኔ የነዌ ተቃዋሚ አይደከሁም ነገር ግን ሰዎች የነዌን ስሕተት ምሳሌ አድርገው እያስተማሩ ወገኖቼን እንደ ነዌ እያሳሳቱ ስለሆነ፤ እንኳን እናተ ነዌም ትክክል አልነበረም በማለት ለማስረዳት ስለምፈልግ ነው።

 አብርሃም ለዚህ የነዌ ሦስተኛ ጥያቄ ሲመልስ «አብርሃም ግን። ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው።» አለ። የነዌ ወንድሞች እዚህ ምድር ላይ በነዌ ኃብት ተጣልጠው እየተካሰሱ ነው። የነዌ ሃብት ነዌን የት እንደከተተው አያውቁም። ቤተ ክርስቲያን አይሄዱም፣ ወንጌልን አይማሩም፣ ንስሐ ነክቷቸው አያውቅም፣ ስጋና ደሙን አይቀበሉም፣ በሥስት ሀብት ለማካባት ብቻ የሚጣደፉ ነገር ባመት አንድ ጊዜ የገብርኤል በአል ሲሆን ጧፍና ሻማ የሚያመጡና ገብርኤል ያማልደናል እያሉ የተዘናጉ ናቸው። ነዌ በምድር እያለ ይህ የነርሱ ከንቱ ኑሮ ትዝ እያለው ከራሱ ጩኸት አልፎ ስለሌሎችም ተጨነቀ።

  የሙሴና የነቢያት መጻሕፍት ስለጽድቅና ኩነኔ ስለዘላለማዊው ፍርድ መልካም ስለሆነውና ክፉ ስለሆነው በግልጥ ይናገራሉ። ወንጌልም ከሁሉም በላይ ሁሉንም ግልጥ አድርጎታል፤ ጌታም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሐዋርያትን፣ ነቢያትን፣ አስተማሪዎችን፣ ካህናትን ወደ ሰው ልጆች ሁሉ ልኳል። እነሱን መስማት ሲገባ ገና በሰማይ ሌላ አማላጅ መጠበቁ የማያዋጣ መሆኑንን በዚህ ትምህርት እንገነዘባለን።

«ለእኔም። ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው። ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ» ራእይ 2210-13

  ይህ ቃል የተጻፈው በከንቱ አይደለም ማንም የሥራውን ያገኛል፣ ቅዱሳን በሕይወታቸው እያሉ፣ ለሰዎች የሚማልዱት ይህን የጌታ ውሳኔ ሰዎች እንዲያውቁና ለንሥሃ እንዲበቁ እንጂ ከፍርድ በኋላ ፍርድ ለማስቀልበስ አይደለም። ያረፉ ቅዱሳን የሚያማልዱ ይሁን አይሁን በግልጥ አልተጻፈም፤ ቢያማልዱም እንኳ እኛ ወደነርሱ ስለጸለይን ሳይሆን በምድር እያሉ የሚያስታውሱትን ሁሉ እነርሱ ወዳሉበት እንዲመጣላቸው እርሱም ክርስቶስን እንድናምን ሊማልዱ ይችላሉ። ይህም ቢሆን አልተጻፈም የራሴ አመለካከት ነው። ያለ ክርስቶስ በቀጥታ ወደ ገነት ለማስገባት ይማልዳሉ የሚለው ግን መቸም እውነት አይሆንም።

 በአርሃምና በነዌ መካከል የተደረገው ጥያቄና መልስ በነፍሳት ዓለም ወይም በዓካለ ነስፍ ያሉ ፍጥረታት ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንጂ በሥጋ በሚኖር ሰውና በዓካለ ነፍስ በሚኖር ሰው መካከል የተደረገ አይደለም። ስለዚህ እኛ በአካለ ሥጋ የምንኖር ሰዎች የሙሴንና የነቢያትን መጻሕፍት መስማት፣ ዛሬ ወንጌልን እየሰበኩ የንሥሐ ጥሪ የሚያደርጉልንን ሰባኪዎች ማዳመጥና ከሲኦል ማምለጥ እንጂ ወደ ነፍሳት መጸለይና እነርሱን ተስፋ ማድረግ አይገባንም። እነርሱ ይማልዱ አያማልዱ አናውቅም። ቢማልዱልን እሰየው፣ እኛ እንድንፈጽመው የታዘዝነው ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነን ንስሐ እንድንገባና ከክፉ መንገዳችን እንድንመለስ ነው።
  ስለዚህ በዓለመ ነፍሳት የተደረገው ውጤት እንደሌለው ካወቅን የጌታን ትምህርት ከማጣመምና ሰውን ከማጥመም እንድንቆጠብ ስል በትሕትና እጠይቃለሁ። መዳናችንም ሆነ መጥፋታችን በምድር ላይ እያለን የሚወሰን እንጂ በሰማይ ሌላ የክርክር ፋይል እንደማይከፈትልን የምናስተውልበት ትምህርት ነው።

«በልጁ የሚያምን አይፈረድበትም በልጁ የማያምን ግን በአንዱ እግዚአብሔር ልጅ ስላለመነ አሁን ተፈርዶበታል»ዮሐ 318

መርጌታ እሱባለው ነኝ

20 comments:

 1. እውነት እውነት እላችኋለሁ፤በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገዉን ደግሞ ያደርጋል ከዚህም የሚበልጥ፤የሚለው የክርስቶስ ቃል አንተ የጻፍከዉን አብዛኛዉን ከንቱ አድርጎብሀል።ዮሐ14:12
  ነብዩ ኤልያስ ደቀ መዝሙሩን ኤልሳን "ወደ እኔ ለምን(ጸልይ)" ያለውም እንዲሁ።ከዚያም መንፈሱን እጥፍ ድርብ አድርጎ ሰጠው።2ነገሥት2:9
  ቅ ጰጥሮስና ቅ ዮሐንስ አንድ ልምሾ የሆነ ሰው"ወደ እኛ ተመልከት" አሉት ከዚያም ፈወሱት።የሐዋ ሥራ4:4
  ቅ ጎርጎሪዮስን ጠቅሰህ ቅ አትናተዎስን ረሳህ፤እንዲህ ይላል"ብሩሃን ከዋከብትን የምትመስሉ ሁላችሁ ምእመናን ሆይ ለእናንተ ክብር ይገባል፤ክርስቶስ አንድነትን ወደ ሚያደርግበት ወደዚያች ሰርግ በምትገቡበት ጊዚ ጌታችሁን ታጥቆ ከእናንተ ጋራ እየተመላለሰ የርሱን ሀብት ሲሰጣችሁ ባያችሁት ጊዚ ለእናንተ ክብር ይገባል።ያን ጊዚ ለኛ ለምኑልን።ሰለእኛ አማልዱ።ይምረን ይቅር ይለን ዘንድ።በሥራችን አይደለም በሥራችሁ ነው እንጂ።"ቁ99ና 100
  መጽሐፈ ሀኖክ"ሙታን ለህያዋን፡ህያዋን ለሙታን ይጸልያሉ" ያለውን አትርሳብኝ ወንድም

  ReplyDelete
 2. "በእነዚያም ወራቶች በሰማያት የሚኖሩ ቅዱሳን አንድ ይሆናሉ፤በአንድ ቃልም ይማልዳሉ፤ይጸልያሉ፤ያመሰግናሉም።ሃኖክ 12፤34
  "በዚያም ሌላ ራእይ አየሁ፡የጻድቃን ማደሪያቸውንና የቅዱሳንም ማረፊያቸውን አየሁ።በዚያም ዐይኖቺ ከመላእክት ጋራ ማደሪያቸውን ከቅዱሳንም ጋር ማረፊያቸውን አዩ።ስለ ሰው ልጆች ይለምናሉ፤ይማልዳሉ፤ይጸልያሉ።"ሃኖክ9:21-23

  ReplyDelete
 3. ዓይን ያለው እንዲህ ሲመሰክር ዐይነ ልቦና የሌላቸው ግን እነሱ አያዩ፤ያዩትንም እነሃኖክን ያስተባብላሉ፤ይክዳሉ።እግዚኦ ይቅር ይበለን።

  ReplyDelete
 4. መችም ማኅበረ ቅዱሳንን የማይሰድብ ጽሁፍ ላለማዉጣት ምላችኋል አይደል?

  ReplyDelete
 5. አቶ እሱባለው
  እስኪ መሪጌትነቱ ይቆይና እንደ ምእመን እናውራ

  ለመሆኑ ከዚህ በታች ያሉትን “ሰው ከሞተ በኋላ ቃል ኪዳኑ እንደሚሠራ/እንደሚያድን የሚገልጹትን አንብበሃቸው ይሆነ? እስኪ አብረን እንያቸው ።

  1.አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ፤ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። ዘጸ ፡ 20 5-7

  2.ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ።

  3.ነገር ግን ከልጅህ እጅ እቀድደዋለሁ እንጂ ስለ አባትህ ስለ ዳዊት ይህን በዘመንህ አላደርግም። 1ኛ ነገ 10 12 ።

  ሌላም ብዙ መጨመር ይቻላል ፡

  ለታመነባቸውና ለተማጸነባቸው ሁሉ ፡ የቅዱሳኑ ቃል ኪዳናችወ ከሞቱ በኋላም እንደሚሠራ ተረዳ ።

  ReplyDelete
 6. yemogn zefenu hulgzie ....endemibalew mkn kalanesah ayihonlhm. Ay mergeta lemehonu keneman new yetemarkew? Mk behlmih yimetabhal aydel?

  ReplyDelete
 7. I belive in this. Mk belive in this. Pente- tehadeiso-menafeqe didn't. So I'm MK. I'm orthodox. I'm MK.

  ReplyDelete
 8. This article is an advant of the antichrist.Saint Elias is here. The fight has began. Pray Ethiopians Pray.

  ReplyDelete
 9. What is mk ? Is it branch of religion such like catholic, orthodox and kalehiwot?

  ReplyDelete
 10. 1 - Give us bible verse .. Metsehafe HENOK is not part of the bible

  2- በሥራችን አይደለም በሥራችሁ ነው እንጂ - I don't care who said that, not even sure. That is Menafikenet we are saved be kirstos sira not by kidusan ..

  3 - “ሰው ከሞተ በኋላ ቃል ኪዳኑ እንደሚሠራ/እንደሚያድን የሚገልጹትን አንብበሃቸው ይሆነ ? we are not saved by kidusan kalkidan not even kidane miheret. Only Jesus is ye addis kidan mehakelegna.... Give us any biblical verse that tell us to pray to them.

  ReplyDelete
 11. ሠይፈ ገብርኤልDecember 29, 2011 at 6:57 PM

  ሥራችሁን ብታስተካክሉት በማለት የምሰጠው አስተያየት
  እንደ ደረስኩ የሰደድኩላችሁን ደካማ አስተያየቴን በድኀረ ገጻችሁ ምንም ሳታጐድሉ እንዳለ ስላስተናገዳችሁልኝ ከሁሉ አስቀድሜ ታላቅ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ፣ ይህን በማየቴም ከሌሎች ለየት ያለ ለውጥ በእናነተ ዘንድ እየተጀመረ መሆኑን ተገነዘብኩ ፤ ይህንን በጐ ጅምርም በማየቴ ከዚህ ወጣ ባለ መልኩ የተሰማኝን የግል ስሜት ለመግለጽ ተገፋፋሁ ፡፡ በአጋጣሚ ባለኝ የእረፍት ሰዓት ስለ ተዋህዶ እምነታችን የሚጻፈውን ለማንበብ ፣ የሚባለውንም ለመከታተል በማለት በኢንተርኔት ስፈልግ አሐቲ ተዋሕዶ የሚል አድራሻ አገኘሁ ፡፡ በዚሁ ድኀረ ገጽ ላይ የቀረበውን ሳነብ ስለ አባ ሰላማ ድኀረ ገጽ በተሰጠው አስተያየት ምክንያት የእናንተን ብሎግ ለማወቅ ቻልኩ ፡፡ የአባ ሰላማ ብሎግን ደግሞ ለማንበብ ስጀምር ማኀበረ ቅዱሳን የሚባል ቡድን እንዳለ አወቅሁኝ ፡፡ ክፋት ባይኖረውም አንድን ቡድን በደግም ይሁን በክፉ ባነሳነው ቁጥር እኛም የራሳችንን የማስተዋወቅ አስተዋጽኦ እያደረግንለት እንደምንሄድ መረዳት ከምጠቃቅሰው የተረዳችሁ ይመስለኛልና ሁላችንም እናርመው ፡፡

  ለምሳሌ አንድ ባለጌ ጠጋ ብሎ በጆሮዬ አንተ ሌባ ብሎ ቢሰድበኝና ዝም ብዬ ሳላናግረው እንዳልሰማ ብሄድ ፣ ምናልባት ውስጥ ውስጤን በሂደት ይከነክነኝና ይረብሸኝ እንደሁ እንጅ ፣ ሌሎች ተደምረው ሌባ እንዲሉኝ ዕድሉንና መንገዱን ስላልከፈትኩ ተጨማሪው ስድብ አይደርስብኝም ፡፡ ነገር ግን በአደባባዩ ሌባ እኮ ብሎ ሰደበኝ ፣ እንዴት ሌባ ይለኛል ብዬ በህዝብ መሃል ባንገራግር ይበልጡኑ ብዙ ህዝብ ስለ ባህርዬ እንዲረዳ ስለሚያደርግ ነገ ተነገ ወዲያ ሌሎችም ይህንኑ ስም ሳልፍ ሳገድም ሊደጋግሙኝ ይችላሉ ፡፡ እናንተን በየት በኩል እንዳገኘሁዋችሁና ማኀበረ ቅዱሳንንም እንዴት እንዳወቅሁት ልብ በሉልኝ ፡፡

  የአባ ሰላማ ብሎግ ስለምን እንደተቋቋመ ከማንበቤ በፊት በቀጥታ ያወጣውን ጉዳይ ማንበብ በመጀመሬና በቀረበው ጽሁፍ በመሳቤ እኔም በበኩሌ የሚሰማኝንና በንባብ ያወቅሁትን በማካፈል ክርስትናውን ይበልጥ እንድንማረው ወደፊት መጽሐፍ ቅዱስንም እያነበብን እንድናጠናው ይረዳ ይሆናል በማለት የተሳተፎ መክፈቻዬን አንድ ብዬ ጀመርኩ ፡፡

  በድኀረ ገጻችሁ ያወጣችሁትን ሌሎች ዝርዝር ርዕሶች ለማንበብ ስሞክር ግን ከማሰተማሪያነታቸው ውጭ በአብዛኛው ማኀበረ ቅዱሳንን ለማውገዝ የወጡ ፣ የዛንም አባሎች ድክመቶች በመጠቋቆም የፖሊስና ርምጃው ሪፖርት የመሰለ ነገር ማቅረባችሁን ተረዳሁ ፡፡ ይህ የእናንተ አካሄድ ለክርስትናው ማደግና መጐልበት ይጥቀም አይጥቀም ፍትሃዊ አስተያየት ለመስጠት ባልችልም ፣ ለእንደኔ አይነት ስለ ወንጌል ትምህረት የተሻለ ዕውቀት እንዲኖረውና ከአሳሳቾች እንዲጠነቀቅ ለመማር በተገኘበት የሚዳክረውን አሉታው እንደሚያመዝንበት መገንዘብ አያዳግተኝም ፡፡

  በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የሚካሄዱት የአምልኮ ሥርዓቶችና ልምዶች በማኀበረ ቅዱሳን የሃይማኖት ሊቆች ወይም አባሎች ጥበብና ፍልስፍና እንዳልተጀመሩና እንዳልተመሠረቱ ከእኔ ይልቅ እናንተ ይበልጥ ታውቃላችሁ ፡፡ ይኸኛው እውነት ከሆነ ታድያ አእምሮአችን ሊያተኩርበት የሚገባውን የወንጌል ትምህርት ማስፋፋት ጉዳይ ችላ ብለን ወደ ሌላ ወደማይረባ የእርስ በርስ ንትርክ ለምን እንሳባለን ? ቤተ ክርስቲያንን እያጋየ የሚያወድም ፣ አማንያንን እንደ ከብት የሚያርድ ተቀናቃኝ በታየባት አገር ላይ ፣ ክርስቲያን ነን የምንለው ወገኖች እርስ በርሳችን ቅራኔን በመሃላችን እየፈጠርን ለምን ልዩነታችንን እናሰፋዋለን ?

  እንደ ክርስቲያን ትዕግሥቱ ካለንና የክርስትና ሃይማኖት ታሪክን መሬት ተቆፍሮ ከወጣው ሳይሆን ከራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ከመረመርን ፣ በእምነት ሥርዓት መለያየትና መከፋፈል የተጀመረው ከመነሻው በጌታ ሐዋርያት /በጳውሎስና በበርናባስ/ መሃከል ነው /ሥራ 15 ፡ 39/ ፤ ኋላ ላይ ደግሞ የቀጠለው ለሐዋርያው ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል እንደተሰጠው ገልጾ እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት /ለአሕዛብ/ የሆነው ወንጌል ተሰጠኝ በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ በማስተማር ተልዕኮው ላይ ልዩነት እንዳላቸው ገልጿል /ገላ 2 ፡ 7/ ፡፡ ይህን በመመልከት የምሰጠው የልጅነት ምክር ፣ ሁሉም በየበኩሉ እውነተኛዋን ወንጌል ያስተምርና ለሁሉም ያዳርስ ፣ በሂደት አንድ ቀን ምናልባት ሁላችንም የምናስተምረው ከአንድ መጽሐፍ ስለሆነ የምንዋሃድበት ፣ የምንናገረው አንድ ቋንቋ ይሆን ይሆናልና በትምህርት ማስፋፋቱና ነፍሳትና በማትረፉ ሥራችን ተስፋ ሳንቆርጥ እንበርታ ፡፡

  “ወዳጆች ሆይ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ ፡፡ አንዳንዶች ተከራካሪዎችን ውቀሱ ፤ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ ፤ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ” /ይሁዳ 2ዐ - 23/፡፡

  ክርክርንና አሉባልታን ፣ ጥላቻንና እርግማንን ስለማያሰፍሩ ለማስተማርያነተ አርአያ ሊሆኑን ይችላሉ የምላቸውን ሁለት ባጋጣሚ ያገኘሁዋቸውን ድኀረ ገጾች እንድትመረምሯቸው በማለት አስፍሬአለሁ ፡፡
  http://www.betepawlos.com/ - ቤተ ጳውሎስ
  http://thetruthlife.com/ - እውነተኛ ሕይወት
  ለአርአያነት የመረጥኩባቸው ምክንያቶች ፡-
  - እስከቃኘሁበት ዕለት ድረስ የማንንም እምነት አይደግፉም ወይም አያወግዙም /እንደ ሰው የእኛ ዓይነት ስሜት ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን ዓላማቸውን ላለመሳት ሲሉ የመረጡት አካሄድ ይመስለኛል ፤ ኦርቶዶክስ የሚለውንም የወል ስም እንደሁላችን ይጋራሉ/
  - ወንጌልንና ሥነ ምግባርን ከማስተማር ውጭ ለማንም ትምህርት ወግነው ድጋፍና ተቃውሞ አያሰሙም


  በመጨረሻም የማቀርብላችሁ ጥያቄ ፡-
  ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እንደ ጌታችን የልደት ዕለት የኢትዮጵያውን ክርስቲያኖች ዘመንን ከሁለት የከፈለ ሊቅ እንደሆነ በዚህኛው ትውልድ እየተነገረን ነው ፡፡ የኢትዮጵያ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አጥኝዎች መረጃ አሰባስበው ብቅ ካላሉን በስተቀር ይኸ አሁን የምናየው በጐራ የተከፋፈለ ወገን የሚያሰማንን ታሪካዊ ግኝት ለማመንና ለመቀበል በእጅጉ ያስቸግራል ፡፡ ንጉሡ ይህን ያህል የጣልቃ ገብነት አስተዋጽኦ ከነበራቸው እስከ ዛሬ ስለምን በቤተ ክርስቲያንና ታሪክ ተመራማሪዎች አንዳች አልተባለላቸውም ? ሁሎቹም የቅዱሳን መታሰቢያ ቤተ ክርስቲያናት አስገኚአቸው እኚሁ ሰው ስለሆኑ ስለምን በውዳሴና ቅዳሴአቸው መሃል ስማቸውን አይዘክሩም ? ነፍሳቸውንስ በየቀኑ ይማርልን እንዴት አይሉም ? ከህገ ልቡናና ህገ ኦሪት ጀምሮ ኢትዮጵያ ሃይማኖትን የተቀበለችና በተግባር ላይ ያዋለች ኋላም ክርስትናን ከሁሉ ቀዳሚ በመሆን ለህዝቧ ያስተማረች እየተባለ ረጅም የአማኝነት ታሪኳ ሲነገረን ፣ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ታሪክ በተጓዳኝ ስላደረጉት አስተዋጽኦ ሁሉም እንዲያውቃቸውና ቢያንሰ እንዲያመሰግናቸው እንዴት ሳይጻፍልን ቀረ ?


  አደባባይ ካወጣችሁት መልሳችሁን ለማየት እከታተላለሁ
  ቢገለጽልኝ ብቸኛዋን ሃይማኖት በመረዳት ለመከተል የምዳክር
  ሠይፈ ገብርኤል

  ReplyDelete
 12. beKidusan kiber yekenachu temeselalachu yenesu kiber enante kemitasebut belay naw libonachihun kifetu

  ReplyDelete
 13. Ato Esubalew Yehen hulu ateta kemitetsef bachiru "ene Dingay negn sele kidusan kiber minem alakim" bitel beki neber

  ReplyDelete
 14. beKidusan kiber yekenachu temeselalachu yenesu kiber enante kemitasebut belay naw libonachihun kifetu

  ReplyDelete
 15. እስቲ ለውንድሞቼ ጥያቄ ቅዱሳን በአንድ ጊዜ በሁሉም ቦታ ይገኛሉ

  ReplyDelete
 16. ዘፀአት ምዕራፍ 7።

  1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል።

  ReplyDelete
 17. የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14፤12
  እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል

  ReplyDelete
 18. Enkwan le kedusan aydelem le tekeberut...le sew lij kibir situ,,,kibir lemigebaw kibir situ yelal ena,,,,,,,be beqmezamurte sim 1kezkaza ye birchiku wha ye sete be semay bet mels alew yelal ena enkwan yelemen.....protestant & tehadesu = 666 ZAREM altesakalachum ke egzabher gar atgafu ..

  ReplyDelete