Monday, January 16, 2012

ራዕይ ያለው ትውልድ መጽሐፍ አጭር ዳሰሳ
በዲ/ን ክንፈ ገብርኤል

‹‹ራዕይ ያለው ትውልድ››[1] በሚል ርዕስ በዲ/ን አሸናፊ መኮንን የተጻፈውን መጽሐፍ በራሴና በትውልዴ በርካታ ጥያቄዎችና እንቆቅልሽ ውስጥ ሆኜ ነበር ያነበብኩት፣ የዚህን መጽሐፍ እያንዳንዱን ገጽ ስገልጽም ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከራሴ ጋር የተከራከርኩባቸው፣ ልቤን ከእጆቼ ጋር ወደ አርያም ወዳለው የአባቶቼ አምላክ ያነሳሁባቸውን የእኔን እና የትውልዴን በርካታ እንቆቅልሾችን በመጠየቅ ብቻ ሳይወሰን ሰፊና የተብራራ የእግዚአብሔርን ህያው ቃል መሰረት በማድረግ ምላሽ በመስጠት ወደራሴ እንዳይ፣ የራዕይን ሰፊና ጥልቅ የሆነ ትምህርትና ትረጓሜ ዳግም በማስተዋል፣ በእግዚአብሔር ቃል መስታወትነት እንዳይ የረዳኝ መጽሐፍ ሆኖ ስላገኘሁት በመጽሐፉ ዙሪያ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድሁ፡፡


በዚህ ጹሁፌ ስለዚህ መጻህፍ ተከታታይ ዳሰሳዎችን እግዚአብሔር ቢኖርና ቢፈቅድ እናደርጋለን። ለዛሬ ግን በመጽሐፉ ዙሪያ በጥቅሉ አንዳንድ ጠቃሚ ሀሳቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፣ «ራዕይ ያለው ትውልድ» በሚል ርዕስ የተጻፈው ይህ መጽሐፍ በአጠቃላይ ፡-

·        በጥልቀት ወደውሰጣችን እንድናይ የሚያደርግና የትላንትን ማንነታችንን በመፈተሽ ዛሬን በምንና በማን ላይ እንደቆምን በማጠየቅ ነጋችን ብሩህና የተሻለ የተሰፋ ጎህ የሚታይበት ይሆን ዘንድ ራዕይ ያለን የዓላማ ሰዎች እንድንሆን ቅን የሆነ መንገድን የሚያመላክት፣ በየትኛውም የህይወት ጎዳና እያለፈ ያለ ሰው ሁሉ ሊያነበው የሚገባው፣

·        በግል፣ በትውልድና በሀገር ደረጃ የሚነሱ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን በራዕይ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን መፍትሄ ለመሻት የምንችልበትን በተለይም ደግሞ የሀገራችን ስልጣኔና የረጅም ዘመን ታሪክ ታላቅ ባለድርሻ የሆነች ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ስለ ራዕይ በሰፊው በማስተማር ባለራዕይ ትውልድን ከመፍጠር አኳያ መወጣት የሚገባትን አደራና ዛሬ ተብትበው ከያዟት ችግሮቿ መውጫ መፍትሄ የሆነውን ዋና ቁልፍ፣ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ወንጌል ልጆቿ በሚገባ እናውቀው ዘንድ፣ በራዕይ የምንኖርና የምንራመድ እንድንሆን የሚያተጋን፣

·         እንደ ባለረጅም ታሪክና ስልጣኔ ያለን ህዝቦች እንደመሆናችን መጠን በማኅበረሰባችን ውስጥ ለዘመናት የቆዩትን ከመንፈሳዊው የአኗኗር ዘይቤ ውጭ በሆኑት ባህሎቻችን፣ እሴቶቻችን፣ የአኗኗር ዘይቤዎቻችንና የሕይወት ፍልስፍናዎቻችንን የሚሞግትና እነዚሁኑ ዳግም በመንፈሳዊ መነጽር በጥንቃቄ እንድናይ አመላካች የሆኑ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮች፣ ሐሳቦችና ተግሳጾች የሞሉበት፤

·        እንዲሁም ከበርካታ የኋላ ዘመን መውደቅ መነሳታችንን ከዳጎሰው ታሪካችን እያጣቀሰ ሁሉን ዳሰስ በሆኑ የታላላቅ ባለዕራዮችንና የእግዚአብሔር ሰዎችን የሕይወት ምስክርነቶችን፣ ውስጥን በሚኮረኩሩ አይረሴ በሆኑ ምሳሌዎችና የሕይወት ገጠመኞችን እያነሳ፣ እንዲሁም ጸሐፊው ስለራእይ፣ በራዕይ በመኖርና ራዕይን ተግባራዊ ለማድረግ የተጓዘባቸውን ጥልፍልፍና ፈታኝ ሁኔታዎች ከሕይወት ልምዱና ከአገልግሎቱ ውጣ ውረድ በመጥቀስ ለራሳችን፣ ለትውልዳችንና ለሀገራችን ያለንን ወይም ሊኖረን የሚገባንን ራዕይ እንድናውቅ ብቻ ሳይሆን ራዕያችንን፡-

·        እንድንኖርለት፣ አንድናሳድገው፣ ደግሞም እንድንከባከበው፣ ቢያስፈልግም ለራዕያችን እስከ ሞት ድርስ እንኳ ዋጋ ለመክፈል ወደኋላ ማለት እንደማይገባን፣ እግዚአብሔር ለእኛና ለትውልዱ ያየውን መልካምና ፍጻሜ ያለውን የእሱን ሐሳብና ፈቃድ አጥርተን እንድናይ የሚጋብዝ የጊዜው መጽሐፍ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ይሄ ደግሞ መጽሐፉ ከሚያነሳው መሰረታዊ የትውልድ ጥያቄ ባሻገር በተጨማሪ እንዲሁም ከመንፈሳዊው ሕይወትና ከመልካም አኗኗር ያፈነግጥንባቸውንና ከእግዚአብሔር ሐሳብና ፈቃድ ውጪ በመሆን ያለራዕይ በመባዘን የከሰርናቸውን፣ ትርጉም የለሽ ዘመኖቻችን በንስኃ አድሰን ዳግም በአዲስ ተስፋና ራዕይ መንገዳችንን እንድጅምር የሚያበረታቱ፣ እቅዶቻችንን፣ በሕይወታችን ዓላማ ብለን የያዝነውን ነገር ዳግም በእግዚአብሔር ቃል ቆም ብለን እንድንፈትሽ የሚጋብዙን፣ በዚህ ምድር ላይ ምን ሰርተንና ምን ሆነን ማለፍ እንዳለብን ዘላለማዊና ሕያው ከሆነው የእግዚአብሔር ቃል አንጻር ምላሽ የሚሰጥ ቅዱስና ሕያው ቃሉ የማዕዘን ራስ የሆነለት የቅዱሱ የእግዚአብሔር ፈቃድና ሐሳብ የተንጸባረቀበት መጽሐፍ ነው፡፡ ይህን መጽሐፍ እያነበብኩ እያለሁም፣ በእግዚአብሔር የጥበብ፣ የምክርና የመጽናናት ቃል ነፍሴ ሐሴት በማድረጓ እንዲህ በማለት ወደ ሰማዩ አምላክ ጸሎቴን አደረስኩ፡-

የአባቶቻችን የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የእሥራኤል አምላክ፣ ለእኛም ደግሞ አምላክ ተብለህ ልትጠራብን ያለፈርክብን በዘመናት ሁሉ ህዝብህን ከፍቅር በሆነ ምክርና ተግሳጽ ወደ ጽድቅ ሕይወትና ወደ እውነት መንገድ እየመራህ፤ አንተ ቅዱሱና ህያው ጌታ ወዳየህልንና ወዳቀድክልን ፍፃሜ እንደርስ ዘንድ፣ የአንተን ሐሳብና ምክር የሚያካፍሉንና የጊዜውን ቃል የሚያቀርቡልንን፣ ስለ ልጅህ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ወንጌል በነፍሳቸው የተወራረዱ እንዲህ ዓይነት እውነተኛ እና ባለራዕይ አገልጋይ ወንድሞችን ለቅድስት ቤተክርስቲያንና ለትውልዱ የሰጠኸን የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ስሙ ይክበር ይመስገን! አልኩ በለሆሳስ፡፡ ከንባቤ ለአፍታ ያህል ዕረፍት አድርጌ።

ትውልድን ከመታደግና መልካሙን መንገድ ከማሳየት ይልቅ በትውልዱ ላይ የተጫነውን የተስፋ መቁረጥ ቀንበር በማጥበቅ፣ ትውልዱ ለነገ ተስፋ የሚሆነው አንዳች የብርሃን ጭላንጭል በማያይበት፣ ራዕይና ባለራዕዮች ብርቅ በሆኑበት በዚህ ክፉና ፈታኝ ዘመን፣ እንዲሁም ኢ-ሞራላዊ ወደሆነ የሕይወት ልምምድ ትውልዱን የሚጎትቱ ህትመቶች እና መጻህፍቶች ገበያውን ባጨናነቁበት፣ የተለያዩ ድረ ገጾችና የኤልክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ልቅ የሆኑ ወሲባዊና ርካሽ የሆኑ መረጃዎችን በገፍ በሚያቀርቡበትት በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነቱ መጽሐፍ ትውልዱ ከተጫነበት ከባድ ቀንበር የሚላቀቅበትን የእግዚአብሔርን ምክርና ተግሳጽ የሚገልጡ በመሆናቸው በሰፊው ለአንባብያን ሊዳረሱ ይገባቸዋል።

በዚህ «ራዕይ ያለው ትውልድ» በሚለው መጽሐፍ ራሴን እንድመረምርና እኔ ማን ነኝ፣ ከየትስ መጣሁ፣ በዚህ ምድር ላይ ያለኝስ ድርሻ ምንድን ነው፣ የመኖሬ ዓላማስ ለምንድን ነው፣ ሕይወቴስ ራዕይ አለውን ወይስ… የሚሉትን የብዙዎች ሰዎች የዘመናት፣ መሰረታዊ የሕይወት ጥያቄ ዳግም ለራሴ በማቅረብ ለመሆኑስ አሁንስ ያለሁበት የሕይወት ጉዞዬ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለኝ ነው፣ ወይስ በተቃራኒው፣ በዚህ ምድር መኖርን የሚያስናፍቀኝ ለራሴ፣ ለትውልዴ እና ለሀገሬ እንድፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠኝ ራዕይ ምንድነው… የሚሉትን ጥያቄዎች ራሴን በመጠየቅ «ራዕይ ያለው ትውልድ» በሚለው መጽሐፍ ላይ ይህችን አጠር ያለች ዳሰሳ ለማድረግ ሞከርኩ።

እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር መጽሐፉ በራዕይና በባለራዕዮች ዙሪያ በሚያነሳው ዝርዝር ሐሳቦች ላይ በሌላ ጊዜ ሰፋ ያለ ዳሰሳ በማድረግ እርስ በርሳችን የምንመካከርበትና ለራሳችን፣ ለትውልዳችንና ለቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር የሆነ መፍትሔ የምንቀበልበትን እንዲሁም ብሩህ ነገን፣ ፍጻሜ ያለው ከእሱ ዘንድ የሆነ ራዕይን ለቤተክርስቲያን፣ ለሀገራችን እና ለትውልዱ አምላካችንና አባታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሰጠን በህብረት፣ በአንድነት ሆነን በጸሎት እንትጋ፣ በፍቅርና በቅንነት መንፈስ እንመካከር፣ እንወያይ ለማለት እወዳለሁ።

                                              ወይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ።

                                           

[1] አሸናፊ መኮንን (ዲ/ን)፣ ራዕይ ያለው ትውልድ፣ አዲስ አበባ፣ ባናዊ ማተሚያ ቤት፣ ሰኔ 2003 ዓ.ም።

6 comments:

 1. i read it it is a very nice book

  ReplyDelete
 2. What a wonderful and constructive idea... I should get this book and read such timely and generation redeeming book. Dear Dn. K/Gebriel we really thank you very much that you brought such a wonderful book to light. May the Almighty God bless you!Ethiopia desperately need a generation with a practical 'vision' of course a vision from Above. thanks!
  From Jerusalem!

  ReplyDelete
 3. go a head Egziabher Yebarekachehu ... tera worena alubaleta selechen eko ...ufffffffffff

  ReplyDelete
  Replies
  1. I agree. Le alubalta sihon hulum niqu tesatafi new. Qum neger gin zero.

   Delete
 4. Brothers and sisters, I can see people have little interest on serious education (qum neger), when it is gossip, everyone have something to say, and it becomes hot issue. But when it is about people or MK, Dn. Begashaw everyone has long tongue.

  Egziabher hiqir yibelen

  ReplyDelete
 5. I wishe I can get this book. it seems very intersting and good book. Thank you for the article. May the Lord Jesus bless you.

  ReplyDelete