Wednesday, February 8, 2012

‹‹ራእይ ያለው ትውልድ›› መጽሐፍ ዳሰሳ ክፍል ሁለት፡፡

  በዲ/ን ክንፈ ገብርኤል፡፡
በባለፈው የጀመርነው ‹‹ራዕይ ያለው ትውልድ›› በሚለው በዲያቆን አሸናፊ መኮንን መጽሐፍ ላይ የጀመርነውን ደሰሳ አሁንም እንቀጥላለን፡፡ ባለፈው ዳሰሳዬ በመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘትና አቢይ መልእክት ላይ አንዳንድ ሐሳቦችን ለማንሳት ሞክሬያለሁ፡፡ ለዛሬ በመጽሐፉ ሽፋንና የደራሲው ቀዳሚ ቃል መልእክትን አስመልክቶ አንዳንድ ቁምነገሮችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡
በመጽሐፍ ዙሪያ የሚባል አንድ የእንግሊዝኛ አባባል አለ፤ ይኽውም፡- ‹‹Don‘t judge a book by its cover›› የሚል፤ ይሁን እንጂ ምንም እንኳን መጽሐፍን በሽፋኑ ገጽ መፈረጅ ደግ ባይሆንም፣ ይህ ‹‹ራእይ ያለው ትውልድ›› በሚል ርዕስ ለተፃፈው መጽሐፍ የተመረጠው የመጽሐፉ የሽፋን ምስል በራሱ አንዳች የሚስተላልፈው ትልቅ ቁም ነገር ስላለው በመጽሐፉ ሽፋን ምስል ላይ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድኩ፡፡
በድንግዝግዝ ላለው፣ የራሱ፣ የትውልዱ ብሎም የሀገሩ የኢኮኖሚው፣ የማኅበራዊው፣ የፖለቲካው፣ ብሎም የቤተክርስቲያናችን የነገ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ግራ ለተጋባው፣ በዚህም ሆነ በዚያ የሚታየውና የሚሰማው ነገር ሁሉ አስደንጋጭ ለሆነበት፣ የጨለማው ግርማና አስፈሪነት ከጊዜ ወደጊዜ እየባሰ ለሄደበት፣ የተስፋ ጭላንጭል ያለ በሚል ብርቱ ምጥ ትውልድ በሚናጥበት በዚህ አስጨናቂ ዘመን፤ እግዚአብሔር ለትውልዱ ያየለትን መልካምና በጎ ነገር አጥብቀን እንድንይዝ የሚያተጋንና የእግዚአብሔር በጎ ሐሳብ የተንጸባረቀበት ይህ መጽሐፍ በሽፋኑ ምስል የሚነግረን እውነታ ቢኖር፡-
 ድቅድቅ ከሚመስለው ጨለማ በሻገር የእግዚአብሔር የሕይወት ብርሃን፣ ለእኛ ያለው ተስፋና ፍፃሜ ያላት ፍቅርንና በጎነትን የተሞላው የዘላለም እቅዱ ዛሬም ከእሱ ሐሳብና ፈቃድ ጋር ለተስማሙ ሁሉ፣ ጨለማን አሸንፎ የሚወጣ እንደ ንጋት ኮከብ በሩቅ የሚታይና የራእይን ፍፁም ብርሃን የሚገልጥ፣ ያለ ፊደል፣ በዝምታ በብዙ ተናጋሪ የሆነ ለመጽሐፉ መልእክት በእጅጉ የሚስማማ ምስል ነው፡፡
በዚህም መጽሐፉ ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት ገና ወደ ውስጥ ገጹ ከመግባታችን በፊት የራእይን ሁለተናዊ ባህርይና በጨለማ ውስጥ እንኳን እንደ ማለዳ ጀምበር የሚፈካውን የራእይን መንገድ በብሩህ ተሰፋ ሊያሳየን ይተጋል፡፡ በዚህም የተነሳለትንና ሊስተላልፍ የፈለገውን የመጽሐፉን አቢይ ቁም ነገር በአንባብያን ልብ ውስጥ በማድረስ የፈለገውን ግቡን አሳክቷል ለማለት ያስችላል፡፡
በሃያ ስድስት የተለያዩ ምዕራፎች የተከፋፈለው በዲያቆን አሸናፊ መኮንን የተፃፈው ‹‹ራእይ ያለው ትውልድ›› የሚለው መጽሐፍ መልእክቱን ማስተላለፍ የሚጀምረው እንደ ሐዋርያዊቷና ጥንታዊቷ ቤተክርስቲያናችን እምነትና ትውፊት፡- ‹‹በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!›› በማለት የጅማሬና የፍፃሜ ባለቤት የሆነውን ስመ ሥላሴን በማስቀደምና በማመስገን ነው፡፡ ጸሐፊው በመጸሐፉ ቀዳሚ ቃል ላይ ይህንን መጽሐፍ ሊጽፍ ያነሳሳው ዋናውና አቢይ ቁምነገር፡- ‹‹ራእይን በተመለከተ በብዙዎች ዘንድ ያለው ድንግዝግዝ ያለ፣ ያልጠራና የተዘበራረቀ መረዳትና አመለካከት እንደሆነ ይገልፃል፡፡››
ጸሐፊው ራእይን በተመለከተ ያስተማረው፣ የደከመለት መምህር ባይኖርም የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር የራእይን ጎዳና እንዲይዝ እንደረዳው በአፅንዖት ይገልፃል፡፡ በራእዩም፡- የትውልድን መፈወስ፣ የፍቅር መቀጣጠል፣ የይቅርታ ቅብብል፣ የኅብረት ዝማሬ፣ ቀና ብሎ የመሄድን ነፃነት ለራሱ፣ ላለውና ሊመጣ ላለው ትውልድ፣ ይህም መልካምና በጎ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሆንለትና እግዚአብሔር ለሰጠው ለዚህ ራእይም እንደሚተጋ፣ እንዲሁም ዕድሜውንና ዘመኑንም ለዚሁ ራእይና አገልግሎት በመወሰን እንደሰጠ በዚሁ ክፍል ላይ ይገልፃል፡፡
መቼም ከራስ አልፎ ቤተክርስቲያንን፣ ትውልድንና ሀገርን ጭምር ማእከል አድርጎ የእግዚአብሔር መልካም ሐሳብና በጎ ፈቃዱ ይፈጸም ዘንድ ከእሱ ጋር ተስማምቶ እሱ የቅዱሳን አምላክ እግዚአብሔር በሚሰራበት ዘመን ገንዘቡ ለመሆን መቻል፣ ለዚህም ቅዱስ ዓላማ ሕይወትን ለእግዚአብሔር አገልግሎት መወሰን ትልቅ እድል፣ መልካም ምርጫም ነው!!!
በዚህ ዘመን ራእይንና ባለራእዮችን ስናስብ የብዙዎቻችን ልብ ይደክማል፣ ነፍሳችን ትዝላለች፣ ሐዘንና ምሬት ይሰማናል… ቁጭት እንደ እግር እሳት ያንገበግበናል… መሪና ተምሳሌት የምናደርገው እባክህ አንድ የራእይ ሰው ስጠን በሚል ጸሎትና ምልጃ ነጋ ጠባ በምንቃትትበት፤ የቤተክርስቲያናችን፣ የትውልዳችንና የሀገራችን ሰቆቃ ያበቃ ዘንድ በፈረሰው ቅጥር በኩል የሚቆምልን በነፍሱ የተወራረደ፣ ለዓላማው እስከ ሞት ድረስ እንኳን የጨከነ መሪ፡- ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ተሃድሶ ሊያመጣልን የሚችል ባለራእይን ስንመኝ ብዙ ዘመናት አልፈውብናል፡፡
ዛሬም ካለራእይ ለመገልበጥ አፋፍ ላይ የደረስን ህዝቦች ወደመሆን እየተንደረደርን ነው፤ ቤተክርስቲያን በግብዞችና በአስመሳዮች ምክንያት እግዚአብሔር ከሰጣት ራእይ ወደኋላ ያፈገፈገችበት፣ ለልጆቿ ፍቅርንና ተሰፋን መስጠት ተስኗት መላንና መፍትኄን ከደጅ እየፈለገች ያለንበት የእንቆቅልሽ ዘመን ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ ይህ ትውልድ ራሱንም ለመታደግ ከመጪውም ትውልድ የታሪክ ወቀሳና ፍርድ ለማምለጥ ይቻለው ዘንድ ያለው አማራጭ ከእግዚአብሔር ጋር መስማማትና እግዚአብሔር ለሰጠው ራእይ ታማኝ የመሆንን መንፈሳዊ ቆራጥነት እንዲኖረው መትጋትና መቁረጥ ነው፡፡
‹‹ራእይ ያለው ትውልድ›› በዚሁ በቀዳሚ ቃል መልእክቱ በተጨማሪም በአቢይ ቁምነገርነት ሊያስጨብጠን የፈለገው እውነታ፡- ራእይ እውነትን ይዞ የሚጓዝ፣ የተስፋ ባለቤት፣ የሚፈተን ግና እንደ ወርቅ ነጥሮ የሚወጣ፣ የሞትን ድንበር እንኳን አልፎ የሚሻገር፣ ከጨለማው ማዶ ፍንትው ያለ ብርሃን፣ ከተራራውም ባሻገር ደልዳላ ሜዳ እንዳለ የሚያይ መሆኑን ብቻ ነግሮን አያቆምም፤ ነገር ግን ብዙ አታላይና እውነት መሳይ ራእይና ባለራእዮች ሊኖሩ ስለሚችሉ በዚህ ዘመን ራእያችንንና ባለራእዮችን እውነት በሆነው በእግዚአብሔር ቃል እንፈትሽ ዘንድ ምክርንም ጭምር የሚለግሰን ነው፡፡ ጸሐፊው በአጭር ቃል እንዲህ ይለናል፡-
‹‹ምንም እንኳን ስለራእይ ብዙ ግንዛቤ ቢኖረንም ይህ መጽሐፍ የራእይ ቱንቢ ሆኖ ከመሰረቱ የወጣውን ግንባታ ይመረምራል… ›› ጸሐፊው በቀዳሚ ቃል የመጽሐፉ መጨረሻ መስመር ላይ ሁሉን ያዘጋጀ እግዚአብሔር እንደሆነ፣ ለእሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ምስጋና እንዲሆንለት በመጸለይና ለአንባቢያንም መልካም ንባብ እንዲሆንላቸው በመመኘት ነው ወደ መጽሐፉ ውስጥ ክፍል እንድንገባ የሚጋብዘን፡፡ እኔም ይሄንኑ የጸሐፊውን ግብዣ ለክቡራን አንባቢዎቼ በመድገም ብንኖርና እግዚአብሔር ቢፈቅድ በቀጣዩ በመጽሐፉ ዋና ዋና ምዕራፎች ላይ የጀመርኩትን ዳሰሳ እቀጥላለሁ፤ መልካም ንባብ!

7 comments:

 1. have you read the letter in deje selam which has no any signature, seal and has not any responsible body?

  ReplyDelete
 2. ኃይለ ገብርኤል
  እናመሰግናለን ለግምገማህ

  ReplyDelete
 3. they always have that kind of stuff they say some thing and they dont take resposiblity ..dn ashenafi i read all of yor books they are owsome they are life changing menfese kidus kalgeletelh beker thos kind of writnig manm liset ayichelm .. my number one gift for every body is your books ..keep writing brohter.

  ReplyDelete
 4. ለደጀ ሰላም ከተላከ አስተያየት-
  ጥያቄ አለኝ። አባ ፋኑኤልን ሲኖዶስ ወደአሜሪካ ሲመድባቸው ወደሀገረ ስብከቱ እንዳይመጡብን በማለት የተቃውሞ ደብዳቤ ለሲኖዶስ መጻፉን በዚሁ በደጀሰላም ብሎግ አንብቤአለሁ። አሁን ደግሞ ወደሀገረ ስብከቱ ይምጡልን ብለዋል ማለት ምን ማለት ነው? ማን ነበር የተቃወመው? አሁን ደግሞ ማን ነው የሚጠራቸው?
  አዬ ክርስትና! እናንተስ ደጀሰላሞች ምን ትላላችሁ?

  ReplyDelete
 5. ዲ/ን ክንፈ ገብርዔል በጣም እናመሰግናለን፡፡ መጽሐፉን አንብቤዎለሁ፡፡ ሁሉም ሰው እንዲያነበውም እኔም እጋብዛለሁ፡፡ እውነት ነው ይህ መጽሐፍ ለምን እንደተፈጠርን በማወቅ ለምን እንደምንኖርና ወዴትም እንደምንሄድ እራሳችንን የምናይበት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የዲ/ን አሸናፊ መኮንን ሁሉም መጽሐፎች መነበብ ያለባቸው ናቸው፡፡ ዲ/ን አሸናፊ በጤናና በዕድሜ እግዚአብሔር ይባርክህ፡፡ ፀጋውንም ያብዛልህ፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. አሜን እግዚአብሔር ይባርክህ! እኔም ካንተ ጋር አብሬአለሁ፡፡ ዓለም ግን የከፈለችው ፀረ ወንጌሎች ያሸከሙት ከባድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን አሻግሮት ለዚህ አድርሶታል፡፡ ዲያቆን አሸናፊ ሁሉም ያልፋል፡፡ እግዚአብሔር የተናገረህን እንጂ ሰዎች የሚናገሩህን አትስማው ፡፡ ኢየሱስን የጠሉ አንተን እንዴት ይወዳሉ፡፡ እነዮሐንስ አፈወርቅም የጠቀማቸው አለመኖራቸው እንጂ በማኅበሩ የክስ ዝርዝር ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ አጽም ይቃጠል ብለው የተነሡ ሕያዋኑን ቢወዱ ነው የሚደንቀው፡፡ በርታ !!!!!!
   ዲ/ ወልዱ

   Delete