Monday, February 20, 2012

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እውነትና እውነተኞች የሚገፉባት፤ ሐሰትና ሐሰተኞች የሚነግሱባት እስከ መቼ ይሆን? - - - Read PDF

ዘሪሁን ሙላቱ ኦርቶዶክሳዊ ነውን?
ክፍል 3
ባለፈው በቀረበው ጽሑፍ ላይ አስተያየት በሰጡ በብዙዎች ዘንድ ግራ መጋባት እንደተፈጠረ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ጽሑፉ በዚህ መልክ ሲቀርብ ግራ መጋባት ሊፈጥር እንደሚችል ቀድሜ ባውቅም፣ የዘሪሁንን የኑፋቄ መንገድ ግልጽ ለማድረግ ሲባል ጉዳዩን እርሱ ባነሣው ነጥብ ማሳየት ግዴታ ሆኗል፡፡ ግራ የተጋቡ አንባቢዎች ግን አሁንም ጉዳዩን በሚገባ ሊያጤኑት እንደሚገባ አስባለሁ፡፡ “በተለየ አካሉ” ሰው ሆነ በሚለው የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አገላለጽ ጥያቄ ከመነሣቱ በፊት “ማርያም ሥላሴን ወልዳለች” ስለሚለው ኑፋቄ ምን ይላሉ? የሚለውን ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ነገሮችን በልማድ ከማሰብና ሳያላምጡ ከመዋጥ አካሄድ መውጣት፣ በትክክለኛውና እውነተኞቹ አባቶቻችን ባቆዩልን ነገረ መለኮት ላይ መመስረት ያስፈልጋል፡፡
ባለፈው የወጣው ጽሑፍ እውነትና አባቶቻችን ያቁዩልን በመሆኑ ለማስተባበል አልተነሣሁም፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች ግራ የተጋቡበትን ጉዳይ በተቻለ መጠን ግልጽ ለማድረግ፣ ሚዛን ሊያስጠብቅ የሚችለውን ተጨማሪ ነገር ግን አክላለሁ፡፡  
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም በአካል በግብር ሦስት፣ በመለኮት፣ በባሕርይ፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ አንድ መሆናቸው የቀና ሃይማኖታዊ ትምህርት ነው፡፡ ሦስትነታቸውም አንድነታቸውም የአምላክነታቸው መገለጫ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ አምላክ እንጂ ሶስት አማልክት አንልም፡፡ ታዲያ እኔ ሳልሆን ሊቃውንቱ ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋ ሆነ ማለታቸውን መጥቀሴ ምን ስህተት አለው? አገላለጹን ከዚህ ቀደም ካልሰማነውና ካላነበብን ጉዳዩን ለማወቅ መሞከር እንጂ፣ በጭፍን ያልተባለውን ተባለ ማለት፣ የተባለውንም በአግባቡ ለመረዳት አለመሞከር ችግር አለው፡፡
ሥጋ ስለ ሆነው ቃል ስንናገር የተለየ የተባለው አካሉ እኮ ከአምላክነት ውጪ አይደለም፤ የአምላክነቱ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ በሥላሴ ውስጥ አካል ስንልም እያንዳንዱ አካል መለኮታዊ አካል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ የተለየ የተባለ አካሉ አምላክነት የሌለውና ከአምላክነት ውጪ እንደሆነ ማሰብ በራሱ ስህተት ነው፡፡ ሶስቱን አካላት አንድ አምላክ የሚያሰኛቸውም መለኮት መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውም ቃል ሥጋ ሆነ ብሎ ነው (ዮሀ. 1፡14)፡፡ ይህም ከሶስቱ መለኮታውያን አካላት አንዱ አካል የሆነው ቃል በተለየ አካሉ ሰው መሆኑን ነው የሚያመለክተው፡፡ መለኮት ሥጋ ሆነ ማለት ስሕተት የሚሆነው መለኮት ሦስቱን አካላት የሚያዋህድና አንድ አምላክ የሚያሰኛቸው እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ መለኮት ስጋ ሆነ ማለት አብና መንፈስ ቅዱስም ጭምር ሥጋ ሆኑ ወደማለት የሚመራ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቃል በተለየ አካሉ ስጋ ሆነ ሲባል ግን ቃል መለኮታዊነቱ ቀርቷል ማለት አይደለም፡፡ ቃል መለኮታዊ አካል ነው፡፡ እንደውም ጌታችን ኢየሱስ ክርቶስ በሰውነቱ የመለኮት ሙላት መኖሩ ተገልጧል  (ቆላ. 2፡9)፡፡  
ኑፋቄ 2                             
ኢየሱስ እግዚአብሔር፣ ሥላሴ ነው
በምስጢረ ሥላሴ ትምህርት እግዚአብሔር ሦስት ከሆነባቸው መገለጫዎቹ አንዱ ስም ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በስም ሦስት ናቸው፡፡ በስም ሦስት ናቸው ሲባልም፣ እያንዳንዱ የሥላሴ አካል የሚጠራበት የራሱ ስም አለው፤ በዚያ ስም ከእርሱ በቀር ሌላው የሥላሴ አካል አይጠራበትም ማለት ነው፡፡ አብ አብ እንጂ ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይባልም፤ ወልድም ወልድ እንጂ አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ አይባልም፤ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ እንጂ አብ ወይም ወልድ አይባልም፡፡

ኢየሱስ ወደሚለው ስም ስንመጣ፣ ይህ ስም የቃል ወይም የሥጋ ብቻ መጠሪያ ሳይሆን “ቃልና ሥጋ ተውሕደው አንድ የሆኑበት የአንድ አካል የሥግው ቃል ስም” እንጂ አብና መንፈስ ቅዱስንም የሚያጠቃልል ስም አይደለም (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት)፡፡ ዘሪሁን ግን በምንጭ አልባውና በለከት የለሹ ማብራሪያው ኢየሱስ የሥላሴ ስም ነው በማለት ከመናገሩም በላይ ሰባልዮሳዊ ኑፋቄውን በስርዋጽ ለማስገባት ሞክሯል፡፡ የተቃወመው ግን የለም፡፡ ለዚህ ነው በቤተ ክርስቲያናችን ውግዘት የሚተላለፍባቸው እውነትና እውነተኞች እንጂ ሐሰትና ሐሰተኞች አይደሉም የምለው፡፡ እስኪ ቀጥሎ ዕንቁና ዘሪሁን የተመላለሱትን እንመልከት፡፡       
ዕንቁ፡- ሥላሴ አትበሉ ሲባልና ኢየሱስና እግዚአብሄር አንድ አይደሉም ሲባል ምን ማለት ነው?
ዘሪሁን ሙላቱ፡- አንድ አይደሉም ማለት አይገባም፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርም ደግሞ ኢየሱስ ነው፡፡ ኢየሱስ የሚለው ስም በቋንቋ ደረጃ ኢ ማለት እግዚአብሔር ሲሆን፣ የሱስ ማለት ደግሞ ያድናል ይሆናል፡፡ በጥምር የቃላት ትርጉም ኢየሱስ ማለት እግዚአብሔር ያድናል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ኢየሱስ የሚለው ስም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን በግልጽ የተጠራበት ስምና የእግዚአብሔር ስም ነው፡፡
ይህ የዘሪሁን ማብራሪያ ምንም መሠረት የሌለውና ምስጢረ ሥላሴን በሰባልዮስ መንገድ የሚያስተምር ኑፋቄ ነው፡፡ በቅድሚያ እግዚአብሔር አንድም ሦስትም ነው ስንል፣ አንድነትም ሶስትነትም አለው ማለታችን ነው፡፡ አንድነቱ ሶስትነቱን አይጠቀልለውም፡፡ ሶስትነቱም አንድነቱን አይከፋፍለውም፡፡ ከዚህ አንጻር ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ስንል ሶስትነትን በጠበቀ መንገድና ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ለማመልከት ከሆነ አገላለጹ ስሕተት አይሆንም፡፡ ነገር ግን ሶስትነቱን በመጠቅለል ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ማለት ሰባልዮስን መሆን ነው፡፡ ጠያቂ ጠፋ እንጂ፣ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስም የሆነውን እግዚአብሔርን ጠቅልሎ ኢየሱስ ነው ከማለት የከፋ ኑፋቄ የለም፡፡

ዘሪሁን በቋንቋ ደረጃ ኢ ማለት እግዚአብሔር ነው ያለው ግን ከየትኛው መዝገበ ቃላት አምጥቶ እንደሆነ ቢነግረን የተሻለ ነው፡፡ ምናልባት በቅርብ የሚያውቁት እንደሚመሰክሩት እርሱ “ኤቲስት” ስለሆነ ሃይማኖት ለእንጀራ መብያው እንጂ የህይወት ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ አሉታ የሆነችውን “ኢ”ን “እግዚአብሔር” ብሎ የተረጎመው እግዚአብሔር የለም ከሚለው እምነቱ በመነጨ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር አይከፋም፡፡ ታላቁ ሊቁ አለቃ ኪዳነ ወልድ ዕብራይስጡንም ግሪኩንም ጠንቅቀው ስለሚያውቁ የሱስ ይበቃ እንደነበር፤ ኢየሱስ የሚለው ስም ላይ ኢ የተጨመረው በከንቱ እንደሆነና ምንም ምስጢር እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ ኢ እግዚአብሔር የሚል ፍቺ ፈጽሞ የለውም፡፡ ባጠቃላይ ኢየሱስ እግዚአብሔር የተጠራበት ስም ሳይሆን ከሶስቱ አካላት አንዱ አካል ሥግው ቃል ተጠራበት ስም ነው፡፡ ትርጉሙም መድሀኒት ማለት ነው (ማቴ 1፡21)፡፡      

ዕንቁ፡-  ከቤተክርስቲያን መጻሕፍት ለዚህ ማስረጃ ይኖራል? 
ዘሪሁን ሙላቱ፡- አዎ ግብረ ሕመማት የተባለ መጽሐፍ ‹‹ሰማይና ምድር እንኳ ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም አልተፈጠሩም›› ይላል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የሚለው ስም የፈጣሪ የእግዚአብሔር ስም፣ ወልድ የሚለው ደግሞ ሰው በሆነበት ዘመን የተጠራበት ሲሆን እግዚአብሔር ሊመለክበት ሊጠራበት ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ያዘጋጀው ስሙ ነው፡፡

ዘሪሁን የእግዚአብሔርን ሶስትነት ጠቅልሎ አንድ ላደረገበት ሰባልዮሳዊ ትምህርቱ ማስረጃ ብሎ የጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጽ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ ለድንግል ማርያም ስሙን ኢየሱስ ትይዋለሽ ብሎ የተናገረው መልአኩ ገብርኤል ነው፡፡ ከዚህ በፊት እግዚአብሔር ወልድ በዚህ ስም አልተጠራም፡፡ ኢየሱስ የሚለውን ስም ወደ እምቅድመ ዓለም መውሰድ፣ ቃል ሥጋ የሆነው በደኃራይ ዘመን ሳይሆን እመቅድመ ዓለም ነው ያሰኛል፡፡ ሰማይና ምድር ብቻ ሳይሆኑ ሁሉ የተፈጠረው በእርሱ በወልድ ነው፡፡ ከፍጥረት ጋር በተገናኘ የተጠራው ግን በአብዛኛው የእግዚአብሔር ቃል ተብሎ ነው (መዝ. 33፡6፤ ዮሐ. 1፡1-3፤ ዕብ. 11፡3)፡፡ ስለዚህ ከሥጋዌ በኋላ ሥጋ የሆነው ቃል የተጠራበትን ኢየሱስ የሚለውን ስም ከሥጋዌ በፊት የነበረ ቀዳማይ ስም ማድረግ ከስህተት በቀር ምንም ትርፍ የለውም፡፡

ከሁሉም በላይ ዘሪሁን የነገረ መለኮት እውቀት እንደሌለው ያስመሰከረው “ወልድ” ስለሚለው ስም በሰጠው ማብራሪያ ነው፡፡ ወልድ የሚለው ስም የሚነሳው ከምስጢረ ስላሴ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ወልድ የሁለተኛው የሥላሴ አካል የግብር ስም ነው፡፡ ወልድ የተባለውም መወለድ ግብሩ ስለሆነ ነው፡፡ “ወአስማቲሆሙኒ ለአካላት አኮ ግብር ከንቱ፥ ሶበ ንሰምዮ ለአብ አበ በእንተ ዘኮነ ወላዴ፤ ወለወልድኒ ወልደ በእንተ ዘተወልደ እምአብ፤ ወለመንፈስ ቅዱስኒ መንፈስ ቅዱስ በእንተ ዘወፅአ አም አብ”  እንዲል ሃይማኖተ አበው፡፡

ይህም ማለት “የአካላት ስሞች ከንቱ ግብር አይደለም፤ አብን አብ ብለን የምንጠራው ወላዲ ስለሆነ ነው፤ ወልድም ወልድ የተባለው ከአብ የተወለደ ስለሆነ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ የተባለው ከአብ ስለሠረጸ ነው” የሚል ነው፡፡  ዘሪሁን ግን “… ወልድ የሚለው ደግሞ ሰው በሆነበት ዘመን የተጠራበት ሲሆን እግዚአብሔር ሊመለክበት ሊጠራበት ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ያዘጋጀው ስሙ ነው” ብሏል፤ በነገረ መለኮት ገለጻ ውስጥ ከዚህ ቀደም ያልተሰማ፣ የአበውን የትምህርት ፈለግ ያልተከተለና ያልተስማማ ነገር ባለአዋቂነትና በድፍረት ይናገራል፡፡ መቼም እንዲህ የሚናገር አላዋቂና ደፋር እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ “እርሱ (ኢየሱስ) በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊልጵ. 2፡6-11) ይላል፡፡

ከላይ ምላሽ የተሰጠበትን የዘሪሁንን ማብራሪያ ተከትሎ ጋዜጠኛው እንዲህ ሲል ጥያቄውን አስከተለ፡፡
“ይሄ ታዲያ እግዚአብሔር በሚለውና ኢየሱስ በሚለው ስም መካከል ልዩነት አያመጣም?”
ዘሪሁን፡- በፍጹም አያመጣም አልዓዛርን ከሙታን ያስነሣው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ስንል እግዚአብሔርን ሥላሴ ማለታችን ነው፡፡

ይህም ከላይ እንደ ተባለው እግዚአብሔርን አንድ አካል አንድ ገጽ የሚል ሰባልዮሳዊ ትምህርት ነው፡፡ በግልጽ እንደ ተጻፈው አልዓዛርን ከሞት ያነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ዮሐ. 11፡43)፡፡ መጋቤ ሐዲስ በጋሻውም ማሳየት የፈለገው ይህንን ነው፡፡ ሶስቱም አካላት እርስ በርስ ህልዋን (አንዱ በአንዱ የሚኖር) ናቸው፤ በወልድ አብና መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው፤ ወይም አንዱ ከአንዱ ጋር በመገናዘብ ይኖራል፡፡ በዚህ መንገድ ህልዋን ናቸው ማለትና ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር፣ ሥላሴም ነው ማለት ፍጹም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ትልቅ ኑፋቄም ነው፡፡

ከጸጋ ታደለ
ይቀጥላል


15 comments:

 1. ጸጋ ያልከው ሁሉ ልክ ነው
  ላንተ ድጋፍ የሚሆን የአቡነ ጎርጎርዮስንም መጽሐፍ (በዓለም መድረክ) ማንበብ ይረዳል
  ዘሪሁን በጊዜ ተው ሊባል የሚገባው ሰው ነው
  ነገር ግን ቤተክርስቲያኒቱ ሰው አላት ወይ
  ሰብዕ አልብየ ይሉሃል ይህ ነው
  ማህበረ ቅዱሳንም ከዘሪሁን የሚያገኙት ጥቅም(በጋሻውን ስለሚሰድብላቸው)ስለሚበልጥባቸው ወይንም ይህ ስለማይገባቸው አይናገሩም
  ያሳዝናል

  ReplyDelete
 2. እናታችን ቅድስት ፣ ብፅእት ፣ ድንግል ማርያም በድንግልና በማህጸኗ የተሸከመችው መወለድ ባህርዩ የሆነውን አምላኳንና ፈጣሪዋን /እግዚአብሔርን/ ነው ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም በታዘዘው መሠረት ሲያበሥራት ፣ የዚህን መወለድ ባህርዩ የሆነውን አምላክ /በድንግልና ያለአባት ተጸንሶ ፣ በድንግልና የሚወለደውን ህፃን/ ስም ኢየሱስ ትይዋለሽ በማለት መጠሪያው እንደሚሆን ስለተናገራት የተወለደልን /ሰው የሆነው አምላካችን/ ኢየሱስ ነው እንላለን ፡፡ እስከዚህ ያለችግር በሰላም የሄድኩ መሰለኝ ፡፡

  የአምላክ ስሙ እንደ የዓላማው የተለያየ ቢሆንም የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ክብሩን ለመግለጽ የተቀራረበ ትርጉም ስለሚኖረው እግዚአብሔር በሚለው ትጠቀማለች ፤ ፈረንጆቹ ጎድ (God) ፣ ዲዮስ (Dios) ፣ … እንደሚሉት ማለት ነው ፡፡ ይህም የሚያከራክረን አይመስለኝም ፡፡

  እግዚአብሔር የአንድነትና የሶስትነት ፣ የሶስትነትና የአንድነት ባህርይ ስላለው ለመጠሪያው ከመጽሐፍ ቅዱስ ባገኘነው መሠረት አብ ፣ ወልድ ፣ መንፈስ ቅዱስ እንላለን ፡፡ ሥላሴ የሚለውን ቃልም ይህን የስም ሶስትነት /አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን/ ለመተካት እንጠቀምበታለን ፡፡ ይህም የሚያከራክረን አይመስለኝም ፡፡

  ለቀመረኞች
  - እግዚአብሔር = ሥላሴ
  - እግዚአብሔር = አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ
  - እግዚአብሔር = አብ
  - እግዚአብሔር = ወልድ
  - እግዚአብሔር = መንፈስ ቅዱስ
  - አብ = ወልድ = መንፈስ ቅዱስ

  እስከዚህ ድረስ የተጓዝኩበትን ሁላችንም የምንስማማበት ከሆነ ፣ ከዚህ ወዲያ የምንለያየው በሰዎች ወግና ባህል ፣ ማለትም በተለየ በተለየ በአገራችን ላይ በዘመናችን የተዘራውን የጐጥ ፣ የቡድንና የቀበሌ ሥሪት ስሜት ወደ ፈጣሪ ግዛትም ለማስፋፋት በማለም የምንታገል ይመስለኛል እንጅ የአምላክን ባህርያት ጠንቅቆ የሚረዳ ፣ የቤተ ክህነት ሊቅ ምስጢሩ ተሰውሮበት ምንም የማናውቀውን አማንያን የሚያደናብረን አይመስለኝም ፡፡ እንዲያው በየዋህነቴ ሳጤነው ይኸ ሙግት የእግዚአብሔርን አንድነቱን ገድፈህ ፣ አንዱን ትተህ ለአንዱ ሾመህ ፣ በቡድን በቡድን ከፋፍለህ ፣ አንዱን ከአንዱ ነጥለህና አበላልጠህ ልትሰራው ላቀድከውና ለፈለግከው ዓላማ ለማዋል በህቡዕ የምትታገል ይመስለኛል ፡፡

  የእግዚአብሔር ባህርያቱ ወይም ጠባይዓት የሚባሉት አፍቃሪነቱ ፣ ጥበበኛነቱ ፣ ዓዋቂነቱ ፣ ምሉዕነቱ ፣ ከሃሊነቱ ፣ ቅዱስነቱን ፣ ዘለዓለማዊነቱንና ፍትሃዊነቱን ሁሉ የሚያካትት ነው፡፡ እነዚህን ባህርያት ጠንቅቀን ከተረዳናቸው የጣት መቀሳሰራችን ሥራ ያቆም ይመስለኛልና ለጊዜው ያስኬድ ስለመሰለኝ ፣ እንድናየው አንዱን ባህርይ ብቻ አነሳለሁ ፡፡ ዘሪሁን የሚባለው ያስተላለፈውን ትምህርት ስላልተመለከትኩ በማለት ነው ከተጻፈው ብቻ በመነሳት የምሞክረው ፡፡

  በምሉዕነት ባህርዩ እግዚአብሔር የሌለበት ሥፍራና ቦታ ፣ ዘመንና ጊዜ የለም /መዝ 139፡8/ ፡፡ በሰማይ ቢወጡም አለ ፣ ወደ ምድር ዝቅ ቢሉም አለ ፤ ወደ ጥልቁ ባህር ቢገቡም ከዛም አለ ፤ ከቶውንም የማይኖርበት ሥፍራ የለም ፡፡ መጠንና ዓይነቱን ስለፈቀደ ብቻ ተረዳነው እንጅ የሰዎች አእምሮና ጥበብ ፣ ፍልስፍናና ምርምር ሁሉ እሱን ለማወቅና ለመረዳት የማይጠቅሙ ከንቱ ስሌቶች ናቸው ፡፡ እኛን እንዲገባን በትንሹ ተመጠነልን ፣ እንዲያድነንም ሲል በጥቂት ተወሰነልን እንጅ ፣ የቀረበን በባህርዩ ቢሆን ኖሮ አንዳችንም አንረዳውም ነበር ፡፡

  ከዚሁ የምሉዕነት ስሌት በመነሳት ፣ እግዚአብሔር ከፈቀደው ፣ የተቀደሰና የተባረከ ማኀፀን ውስጥ ተገኘ ቢባል ብዙ ወንጀል ያለው አልመሰለኝምና ፣ ግድፈት አለው የምትሉን ሰዎች ብዙ ምስጢር ስለምታውቁ ስለሆነ ፣ ከቻላችሁ የምታውቁትን በሥርዓቱ ተርትራችሁ ፣ ዘርዝራችሁ ጻፉና አስነብቡን ፡፡ ይህን የምለው የሌለበት ሥፍራ የለም ብለን ስለምንደመድም ማለቴ ነው ፡፡

  ይቀጥላል

  ReplyDelete
 3. ere Zrihun ahunm sint nifaqe eytnagere new btley adisu mikael k mr. mihrtab gar gtimaw chigir eyfatru new.

  ReplyDelete
 4. ክፍል ሁለት ስላልወጣ ምናልባት አልደረሳችሁ እንደሁ በማለት ከትንሽ ለውጥ ጋር

  እኔ የ… ጸጋ ታደለ ጽሁፍን አካሄድ መደምደሚያ እንደገመትኩት ኢየሱስ ተወለደልን ፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሞቶ አዳነን እንጅ ሌሎቹ በማዳን ሥራ ውስጥ አያገባቸውም ፣ አብና መንፈስ ቅዱስ ስለ ድኀነታችን አይመለከታቸውም ለማለት ቀስ በቀስ የሚንሻፈፍ መሰለኝ ፡፡ ይኸ የተበላሸ ትምህርት ከየት ወገን እንደሆነ መገመት እንችላለንና በቤተ ክርስቲያን ላይ ልዩ አስተምህሮ እንዳለ አድርገን በየዋህነት የሚያመልከውን ህዝብ አናምታታው ፡፡ እኔ እንደ አንድ ምእመን የተረዳሁትን ያህል ተጓዝኩበት እንጅ ይኸ ረቂቅና ጥልቅ እውቀት የሚመረመርና የሚሸነሸነው እንደ እኔ ዓይነት ምንም ምልከታ በሌለው ሰው አይደለም ፤ እግዚአብሔርን የመረዳት ነገር ፣ እጅግ ትልቅ ጥበብ በመሆኑ ፣ ተገፋን ማለቱንና ኩርፊያችሁን ትታችሁ በምሁራኑ አካባቢ ብታቀርቡትና የተለያየ ትርጓሜ ብትሰጣጡበት መልካም ነው የሚል አስተያየቴን ባትቀበሉትም ዛሬም እደግመዋለሁ ፡፡ ከዚህ ቀደም ያስተላለፍክልን በልዩ አካሉ በሚል የተገለጸው መለኮት የጋራ ንብረታቸው ስለሆነ ፣ ሥጋን የተዋሃደው መለኮት የሌለው ልዩ አካል ብቻ ነው የሚል እንደምታ እንደነበረውና የንስጥሮስ ዓይነት ስህተት እንዳንፈጥር ሰጋሁኝ ማለቴን አስታውሳለሁ ፡፡ ዛሬ ደግሞ ልዩ አካል ሲባል አምለክነት /መለኮት/ የተዋሃደው ልዩ አካል ነው ስትለን የራስክን ያለፈ ሃሳብ በራስህ ተቃረንክብኝና ይበልጡኑ ግራ ገባኝ ፤ ለማለት የፈለግኩት እንዲህ ነበር የምትለን ከሆነ ሥርዓት ነው ፤ ሁላችንም እየተማርን እንድንሄድ ለማለት ፈልጌ ነው ፡፡ በተንኰል ሳይሆን ፣ ይህን ዕውቀት በአግባቡ ከተረዳኸው ደግሞ ፣ ነባር ትምህርቶችንና መጽሐፎችን ቃኝተህና ፈትሸህ ፣ ሁላችንም ትምህረት እንድናገኝበት ፣ በወግ አድርገህ ብታቀርብልን በግሌ በጣም ደስታውን አልችለውምና ለወደፊቱ እሰብበት ፡፡

  ከዚህ በተረፈ እንደምረዳው የኢኦተቤ በድንግል ማህጸን ያደረው ወልድ እንደሆነ ታምናለች ፣ በመስቀል ላይም ደሙን ያፈሰሰው ፣ መሞት ሳይገባው ስለፍቅሩ ሞቶ ያዳነንም ኢየሱስ እንደሆነ ታውቃለች ፤ ይህንኑም ታስተምረናለች ፡፡ ነገር ግን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ተነጥሎና ተሰውሮ ይህን የማዳን ሥራ ለብቻው ፈጽሞታል የምትል አይመስለኝም ፤ ሰውን የማዳን ዕቅዱ የሶስቱም የአብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በመሆኑ ወልድ ስለ ባህርዩ ፈጸመው እንጅ ፣ ያለ ሌሎቹ ፍቃድ አላደረገውም ፡፡ አሁንም መልስ ካለህ እጠይቅሃለሁ ፣ የኛ መከፋፈል ሳያንሰን የእነሱን ደግሞ መከፋፈል ለምን ጉዳይ ሲባል ፈለግነው ፡፡ በተናጠል አይሰገድላቸው ፣ በተናጠል አይቀደስላቸው ፣ ምን አስበህ? ምንስ አልመህ? ይህን ርዕስ አድርገህ ተቆረቆርክለት? ይኸን የፈጠረው የናንተ የጥበበኞቹ ችግር ይመስለኛልና ተወቃቅሳችሁ ታረቁ ፤ ይቅር ለእግዚአብሔር ተባባሉ ፤ በአባቶችም ለመዳኘት ፈቃዱ ይኑራችሁ ፤ ሰላምን ፍጠሩ ፡፡ አንድነታችን ይጠቅመናል እንጅ አይጐዳንም ፤ ከጀርባ እየተጐሰመብን ያለውን ነጋሪት በዩ ቲዩብ ብትከታተሉ ፣ ሰላማዊ መንፈስ ካላችሁ አሁኑኑ ሱባዔ ታውጃላችሁ ፡፡

  እኔ ብዙ ዕውቀት እንዳለህ ከጽሁፍህ ብቻ እገምታለሁ ፡፡ ነገር እውቀትክን ሌሎቻችንን ለማስረዳትና ለማስተማር ብታውለው ብዙ ትጠቅመናለህና አስብበት ፡፡ ሰዎችን ለመክሰስ ብለህ ጉዳይህን ስታቀርበው ስለ ጉዳዩ የማናውቀውን ሰዎች ወደ ጉዳዩ ለማስገባት ትገፋን እንደሆነ እንጅ ሌላ ጥቅም አላይበትም ፡፡ ይህን ትምህርት ለቅድስናና ወገንን ለማስተማር ተግባር ብታውለው ደስ ይለኛል ፡፡

  ከመጽሐፍ ቅዱስ አብና ወልድ አንድነት እንዳላቸው እነደገና እንድታዩትና - ማለቱ እንዲመረመር እጠቅሳለሁ
  - ዮሐ 1ዐ ፡ 30 እኔና አብ አንድ ነን።
  - ዮሐ 1ዐ ፡ 38 አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ
  - ዮሐ 14 ፡11 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤
  በኢኦተቤ ትምህርት ደግሞ መንፈስ ቅዱስ የአብና የወልድ እስትንፋሳቸው ስለሆነ ፣ የሶስቱም በአንድነት የመገኘትን ቋንቋ ብንናገር ስህተቱ አልጐላልህ ይለኛልና ፣ ድክመቴን የተረዳችሁት አግዙኝ ፡፡

  በተረፈ የሱስ = መድኀን የሚለው ከዕብራውያን መጽሐፍ የተተረጐመውን የተከተልን እንደሆነ ነው /በአማርኛም ይኸ ስም በ1878 በተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይገኛል/ ፡፡ በዚያን ወቅተ ኢየሱስ የሚለው ከግሪክ ከተተረጐመው መጽሐፍ ሲቀርብላቸው ፣ ኢ ከገባ በግዕዙ አፍራሽ ቃል ስለሆነ አያድንም ያስብላልና የጌታችንና የመድኃኒታችን ትክክለኛ መጠሪያ የሱስ መሆን አለበት ብለው ተከራክረውበታል የሚል ነገር አለ ፡፡

  ኢየሱስ (Greek - Ἰησοῦς, Iesous; Latin - Iesus) = የግሪክኛውን መጽሐፍ ቃል ትርጉም ከተከተልን
  የሱስ (Hebrew - Yeshua, Yehosua, Joshua; Aramaic - Yesua) = የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቃል ትርጉም ከተከተልን
  የሁለቱም ስሞች ትርጉም ያህዌ ያድናል ፣ መድኀን ነው ለማለት ስለሆነ ብዙ አያከራክረንም ፡፡

  ስህተት የምንፈጽመው ከዕብራይስጡ የኢየሱስ ስም ውስጥ Ye የሚለው ያህዌን ያመለክታል ስለሚሉ ፣ በአማርኛም አስተካክለን እንደነሱው እንተርጉመው በማለት የመጀመሪያው "ኢ" የሚለውን ፊደል እግዚአብሔር ነው ማለት ከፈለግን ነውና ፣ ያለ ቋንቋችን ብልሃት የሰዎችን መከተሉ አያስኬደንም እላለሁ ፡፡

  ሰላምና የእግዚአብሔር በረከት ከሁላችሁ ጋር ይሁን

  ReplyDelete
  Replies
  1. wendeme bemegemeriya yebetekerestiyan astemehero min endehone eweke keza saf. aynehene chefenehe seleberehan demeket lemawerat atemokere. betekerestiyan bela yematawekiwene atebele. edege

   Delete
 5. ዘሪሁን ..ወልድ የሚለው ስም ሥጋን ሲዋህድ የተሰጠው ስም ነው ያለው ነገር ሊገባ›ን አልቻለም ። ከእውቀት ማነስ ነው ወይስ ከክህደት ?

  ReplyDelete
 6. He was wrote yepapasu kelate to attack abune samuel that indicate criminal mind. Leave the curch unless yemtebekeh ewoke beteun lematedat we will take all action shuold be worth.

  ReplyDelete
 7. በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ እየተባለ የተነገረው /ማቴ 28፡20፣ 2ኛ ቆሮ 13፡14/ በቆጠራ ማንም ሰው ሊረዳው የሚችል የሦስት /3/ መለኮታውያን አካላት ስም ነው፡፡

  1. አብ ቃልንና ሕይወትን አወጣ በተባለበት ከዊን መግለጫው ልብ
  2. ወልድ ከልብ እንደሚወለድ (እንደሚወጣ) ከአብ ወጣ በተባለበት የከዊን መግለጫው ቃል
  3. መንፈስ ቅዱስ ከልብ እንደሚወጣ ከአብ ወጣ በተባለበት የከዊን መግለጫው ሕይወት ነው፡፡

  ይህ የመሆን (የኩነት) ሦስትነት አንድነትን የሚያስከትል ስለሆነ በኤሎሂምነት ራሱን የገለጸው እግዚአብሔር አንድ ነው ሊባል ተገባ፡፡
  በሥላሴ መንግስት እያንዳንዱ አካላዊ መንፈስ በባህርይ ምሉዕነትና በህላዌ ፍጹምነት ተገኝቶ ራሱን የገለጸበትን ስራ ሲሰራ ይታያል፡፡ አንዱ አካላዊ መንፈስ የሁለቱ ግልባጭ አይደለም፡፡ ጊዜውን እየጠበቀ በሦስት ስሞችና ኹነታዎች የሚገለጽ አንድ አካልም አይደለም፡፡ ሦስቱ መለኮታውያን አካላት ለአንዲት መንግሰት የሚሰሩት የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ እግዚአብሔር አብ የመለኮታዊ አሳብ መነሻ፣ የዘላለም ዕቅድ ምንጭ ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ የአሳቡ ተናጋሪ ቃል፣ የእቅዱ ፈጻሚ ኃይል ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በወልድ ለተከናወነው ተግባር ሕይወትና ውበት ሰጪ ነው፡፡ እነዚህ ድርሻዎች በዋናነት የተገለጡት በፍጥረተ ዓለምና በድኀነት ዓለም ነው፡፡
  ይህን ዓለም ለመፍጠር እግዚአብሔር አብ አቀደ፣ በወልድ ቃልነት ዓለም ተፈጠረ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት /ቀጣይነት/ አገኘ፡፡ ዓለምን በማዳን ሂደትም እግዚአብሔር አብ ዓለምን አፈቀረ፣ እግዚአብሔር ወልድ ፍቅሩን በሞቱ ገለጠ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ምስክርነቱን ለዓለም አደረሰ፡፡ ሦስት ተግባራት አንድ አላማ፣ ሦስት አካላት አንድ መለኮት፣ ሦስት ገጽ አንድ መንግሥት!
  ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከስጋዋ ስጋ ከነፍሳ ነፍስ ነስቶ የተወለደው በተለየ አካሉ እግዚአብሔር ወልድ እንጂ ሥለሴ ናቸው አንልም፡፡

  ReplyDelete
 8. "ዓለምን በማዳን ሂደትም እግዚአብሔር አብ ዓለምን አፈቀረ፣ እግዚአብሔር ወልድ ፍቅሩን በሞቱ ገለጠ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ምስክርነቱን ለዓለም አደረሰ፡፡ ሦስት ተግባራት አንድ አላማ፣ ሦስት አካላት አንድ መለኮት፣ ሦስት ገጽ አንድ መንግሥት!"
  "ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከስጋዋ ስጋ ከነፍሳ ነፍስ ነስቶ የተወለደው በተለየ አካሉ እግዚአብሔር ወልድ እንጂ ሥለሴ ናቸው አንልም፡፡"

  የዶግማ ነገር ስለሆነ ተሰውረው የነበሩት እነ መምህር አብራራው ብቅ ሊሉልን ነው መሰለኝ ፤ በርቱ መማማር ማለት ይኸ ነውና ግፉበት ፤ የምንፈልገው ስለሆነ የምታውቁትን እየመጠናችሁ ተንፍሱልን ፤ ቆንጆ አገላለጽ ነው ፤ እሰከዚህ ድረስ እኔም ተደናብሬ ደርሻለሁ ፤ ከዚህ በኋላ ቀጣዩን ትምህርት ብታብራራልን ድንቅ ይሆናልና በዚሁ ጨረስኩ ብለህ እንዳትጠፋ ፡፡

  “የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አብን በልብ ፣ ወልድን በቃል መንፈስ ቅዱስን በእስትንፋስ የመሰሉበትን ብልሃት ሦስት ኩነታት ብለው ይጠሩታል ፡፡ ይኸውም ከዊነ ልብ ፣ ከዊነ ቃል ፣ ከዊነ እስትንፋስ ማለት ነው ፡፡ በዚሁም መሠረት ልብ ምንጊዜም ኩነቱን /ለባዊነቱን/ ሳይለቅ በራሱ ከዊን ጸንቶ ማለት ከዊንነቱን ሳይተው ፣ ቃልና እስትንፋስ ያስቡበታል ፤ ቃልም ቃልነቱን ሳይተው ፣ በራሱ ከዊንነት በመጽናት ልብና እስትንፋስ ይናገሩታል ፤ እስትንፋስም በራሱ ከዊንነት በመጽናት የልብና የቃል እስትንፋስ ነው ፡፡ አብ ልባቸው ነው ፤ ወልድ ቃላቸው ነው ፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ እስትንፋሳቸው ነው ፡፡” ይህ የሚያሳየው አንድነታቸውን ፣ ስምምነታቸውን ፣ የስላሴን የተዋህዶ ባህርይ ነው ፡፡ በእኛ አካል ውስጥ እንደሚኖሩት ብልቶቻችንና /ልብ ፣ ጉበት ፣ ኩላሊት.../ እኛ አንድ ሰው እንደምንባለው ማለቴ ነው /እንዲገባን እንጅ እጅግ ደካማ ምሳሌ ነው/፡፡

  ወልድ መወለድ ግብሩ ስለሆነ በድንግል ማህጸን አደረ ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በመነሳት ይህን ከላይ የተመለከትነውን አንድነታቸውን እንደ ዶሮ ብልት እንዳንበታትንና እነሱንም በሰው ብልሃት እንዳንከፋፍል እሰጋለሁ ፡፡ በዚሁ እየቀጠልን ከሄድን እኮ በመስቀል ላይ መወሰን የቻለውም ሥጋን የተዋሃደው ቃል ብቻ ነው ፤ ሞተና ተነሳም የምንለውም ቃልን ነው ፤ ወደፊት ይመጣልም ብለን የምንጠብቀው እሱኑ ነው ፡፡ ይሄ አካሄድ ታድያ ወዴት ያደርሰን ይመስላችኋል? የዚህን ምላሽ ለመስጠት የምትጣደፉ ካላችሁ በትዕግስት አጢኑት ፤ ምክንያቱም ከዚህ ጥያቄ መልስ በመነሳት ለየት ወዳለ አምልኮ የተጓዙ ወገኖች አሉና ፣ በየዋህነት እኔ እሱ እንዳይሆን እፈራለሁ ፡፡ ይህ እንዳይሆን ደግሞ ድንግል ማርያም ሥላሴን ወለደች እንበል ማለቴ አይደለም ፤ ያም ስህተት ነው ፡፡ ነገር ግን ብዙ መተንተን ውስጥ ስንገባ ወደ አለሆነ አቅጣጫ ሊወስደን ስለሚችል ነው ፤ ያንንም አገላለጽ የተጠቀመው ግለሰብ ምናልባትም ከምርምር ብዛት የደረተው ይመስለኛል ፤ የሚሰጠውን ምክንያት ቢያቀርብልን ለሁላችንም ጥሩ ይሆን ነበር ፡፡ ለማንኛውም ሃይማኖትን በምርምር ጥበብ ደርሰን ለማመን የምንሞክር ካለን ብዙ ያስቸግረናልና ፣ በተቻለ በአንድ ልሳን የምንነጋገራቸውን ትምህርቶች እንፈልግ ፡፡ ልዩነት ያለበቱን ደግሞ በመማማር ፣ በመረዳዳት ብዛት ልናለዝበው እንችላለን የሚል አመለካከት አለኝ ፡፡

  ለመረዳት የሚያስቸግረን በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያልተቀመጠው የዶግማው ትምህርት ብዙ ስለሆነ ወንድሜ አንዱን ጀምረሃልና ፣ ተጨማሪ ካለህ ቀጥልበት ፡፡
  አመሰግናለሁ ፡፡

  ReplyDelete
 9. ‹‹በዚሁ እየቀጠልን ከሄድን እኮ በመስቀል ላይ መወሰን የቻለውም ሥጋን የተዋሃደው ቃል ብቻ ነው ፤ ሞተና ተነሳም የምንለውም ቃልን ነው ፤ ወደፊት ይመጣልም ብለን የምንጠብቀው እሱኑ ነው ፡፡››
  በትክክል በመስቀል ላይ የዋለው የእግዚአብሔር ልጅ የማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ (እግዚአብሔር ወልድ) ነው፡፡ ቤተክርስቲያንም እንደምታስተምረን የሃይማኖት ጸሎት … ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን፡፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል ሁሉ በእርሱ የሆነ ያለ እርሱ ግን ምንም ምን የሆነ የለም በሰማይም ያለ በምድርም ያለ ስለ እኛ ስለ ሰው እኛን ለማዳን ሲል ከሰማይ ወረደ ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ሆነ ሰው ሆኖ በጴንጤናዊ በጲላጦስ ዘምን ስለ እኛ ተሰቀለ ታመመ ሞተ ተቀበረም በሶስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ አረገ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ ዳግመኛም በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ በጌትነት ይመጣል ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፡፡

  ReplyDelete
 10. ለገባችሁ ሰዎች የተጠቀሰው አምልኮ ምንም ችግር የለውም ፤ እኔም ይህንኑ ድንቅ ቃል እደግመዋለሁ ፡፡ ነገር ግን በእምነት ደካማ ለሆንነው ወገኖች ፣ ሁሉም ነገር በአንድ አካል ብቻ የሚፈጸም ስለሚመስለን ፣ ሌላ ሰፈር ምን እናደርጋለን ፣ ለምን ጊዜአችንን በሆነ ባልሆነው እናጠፋለን የሚል ድምዳሜ እንዳያስከትልና በአብና መንፈስ ቅዱስ ላይ ክህደት እንዳያመጣ እፈራለሁ ፡፡ ኢየሱስ ብቻ (Jesus-Only)የሚል ሃይማኖትም ይኸን የመሰለ ትምህርት (አልቦቱ ስላሴ)ስላላቸው ነውና ግምቴ ስህተት ከሆነብህ ይቅርታ ፡፡

  ፍራቻዬንና ጥቆማዬን ከተረዳችሁልኝ በያለንበት ያለችግር እንቀጥላለን
  አመሰግናለሁ

  ReplyDelete
 11. - እግዚአብሔር = ሥላሴ
  - እግዚአብሔር = አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ
  - እግዚአብሔር = አብ
  - እግዚአብሔር = ወልድ
  - እግዚአብሔር = መንፈስ ቅዱስ
  - አብ = ወልድ = መንፈስ ቅዱስ

  ReplyDelete
 12. KKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKKK

  ReplyDelete