Wednesday, February 22, 2012

ተጠንቀቁ - ክፍል አራት - - - Read PDF

ሪሳውያን ሰዎች ስለሚሰጡት አስተያየት ይጨነቃሉ

"የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል  እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ። ለኢየሱስም መልሰው አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።" (ማቴ 21:25-27)

ፈረሳውያን በአንድ ነገር ላይ አቋም ለመውሰድ ሲያስቡ ብናደርገው ሰዎች ስለኛ ምን ያስባሉ በማለት ይሰጋሉ። የሚተማመኑበት እና የሚያሳስባቸው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ባካባቢያቸው ባሉት ሰዎች ምን ይሉናል በሚል የተመሰረተ ነው።  እኛም ሰው ምን ይለኛል እያልን ትክክለኛውን ነገር ህሊናችን የሚነግረንን ነገር የማናደርግ ከሆነ እንደ ፈሪሳውያን ነን ማለት ነው። ብዙ ሰባኪዎች ሰው መስማት የሚፈልገውን ብቻ እና ሰውን ለማስደሰት ሲሉ ነው የሚናገሩት። እንደዚሁም ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው ስርአት ይዘው እንዲያድጉላቸው ይፈልጋሉ ይሄን የሚያድርጉት ግን ለእግዚአብሔር ክብር ብለው ሳይሆን እራሳቸው እንዲመሰገኑ ነው። ብዙ ሕጎችንም አውጥተው ልጆቻቸውን እንደወታደር እንዲታዘዙ ያደርጓቸዋል። ሰዎች ምን ይሉኛል ብለን በማሰብ ልጆቻችንን የምንቀጣ ከሆነ ለዚህ ዓለም አጋልጠን እንሰጣቸዋለን። የፈሪሳውያንን መንገድ በመከተል ልጆቻችሁን አታበላሹዋቸው። ጳውሎስ እንዳለው "ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" (ገላ 6:14)

ፈሪሳውያን ገንዘብ ይወዳሉ

"ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር።" (ሉቃ 16:14)

ፈሪሳውያንን ስናስብ ገንዘብ ስለመውደዳቸው አናስብም ነገር ግን ይህ አንዱ የፈሪሳውያን ምልክት ነው። እኛም እንደፈሪሳዊ ለመሆን ይህ አንዱ ባሕሪ ያለምንም ጭማሬ በቂ ምልክት ነው። ጌታ እንዳለው "ለሁለት ጌቶች
መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም" (ሉቃ 16:13) ማንም አማኝ የፈለገውን ያህል ገንዘብና ሀብት ሊኖረው እና ሊገለገልበት ይችላል። ነገር ግን ገንዘብን መውደድ ስንጀምር እንደ ፈሪሳውያን መሆን እንጀምራለን። እግዚአብሔር ገንዘብን እና ሀብትን እንድንጠቀምበት እና ሰዎችን ደግሞ እንድንወድ ሰጠን። ሰይጣን ግን በሰው ልጆች መካከል ይሄንን እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታ ገልብጦ ገንዘብን እንድንወድ እና ሰውን እንድንጠላ እና እንድንጠቀም (ጥቅም እንድንወስድ) አንደረገ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ይሄንን የሰይጣንን ሴራ ገለባብጦ ሰዎችን እንድንወድ እና በሀብት በገንዘብ እንድንጠቀም እና ሰዎችን ለመባረክ ወደዚህ ዓለም መጣ። ብዙ ሰባኪዎች ባሁኑ ጊዜ ለራሳቸው የበለጠ ገንዘብ ለመስራት ሲሉ በቤተክርስቲያን
ውስጥ ያለባቸውን ኃላፊነት ይዘነጋሉ ምክንያቱም ፈሪሳዊ ስለሆኑ አስተሳሰባቸውም ሁልጊዜ ገንዘብ ላይ ያተኮረ ነው። እኛ ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችን መውደድ አለብን።

ፈሪሳውያን እራሳቸውን ከሌላ ሰው የተሻሉ አድርገው ያስባሉ

 "ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥እንዲህ ሲል። ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ" (ሉቃ 18:9-11)

  እዚህ ምሳሌ ላይ ፈሪሳዊው ወደእግዚአብሔር እየጸለየ አልነበረም። ከሌሎች ሰዎች የተሻለ በመሆኑ በልቡ እግዚአብሔርን አመሰገነ። እኛም ይሄን የመሰለ ነገር ካደረግን "መንፈሳዊ ኩራት" ላይ እንወድቃለን። ኩራት እና ራስ ወዳድነት ጌታ እስኪመጣ ድረስ እና እሱን እስክንመስል ድረስ በቀላሉ ልንላቀቃቸው የማንችላቸው ሁለት ኃጢአቶች ናቸው። እስከዛው ድረስ ግን በተቻለን መጠን እራሳችንን ማንጻት መቻል አለብን።

ፈሪሳውያን በራሳቸው ጻድቅነት ያምናሉ

"ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ " (ሉቃ 18:9)

 እግዚአብሔር የሰጠን የጽድቅ እምነት አለ ሌላው ደግሞ ራሳችን የምንፈጥረው ጻድቅነት አለ። የትኛው እንዳለን ወይም ከነዚህ ከሁለቱ የትኛውን እንደያዝን ለማወቅ ከፈለግን በጽድቃችን እንደምንኮራ ራሳችንን መጠየቅ ነው። የምንኮራ ከሆነ ጽድቃችንን ራሳችን የፈጠርነው ነው ማለት ነው። ጸጋችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ነጻ ስጦታ ከሆነ ግን እግዚአብሔርን እናመሰግናለን እንጂ አንኮራበትም። ፈሪሳውያን ግን ያላቸው ጽድቅ የሚኮሩበት ነው። ሰው በጻፈው መጽሐፍ ሊኮራ ይችላል ነገር ግን ሌላ ሰው በጻፈው መጽሐፍ መኩራት አንችልም። ስለዚህ ባለን ጥሩ ባሕሪ ወይም በምናደርጋቸው ነገሮች የምንኮራ ከሆነ ለምሳሌ በለጋስነታችን በትሕትናችን በጸሎታችን የምንኮራ ከሆነ ከአምላክ የተሰጡን ሳይሆን ራሳችን ያፈራናቸው ናቸው ማለት ነው። ምክንያቱም ከእግዚአብሔር በነጻ የተሰጡን ቢሆን ኖሮ እንዴት እንኮራበት ነበር? እንግዳ ተቀባይ መሆን በጣም ጥሩ ነገር ነው ነገር ግን የምንኮራበት ከሆነ እንግዳ ተቀባይነታችን በእግዚአብሔር ፊት የሚያስከፋ ይሆናል። የምንኮራበት ነገር ሁሉ ለምሳሌ እኛ ትልቅ ነገር ኖሮን ሌላው ትንሽ ነገር ሲኖረው ይህ የራሳችን ጥረት ውጤት ነው እንጂ ክእግዚአብሔር ያገኘነው ነገር አይደለም። የእግዚአብሔር ሥራ ከሆነ አንኮራበትም። ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔር አገልግሎት በሚያደርጉት አገልግሎት በኩራት ይናገራሉ። ይህ የሚያሳየው ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ስለኛ የከፈለውን መከራ አለመመልከታቸውን ነው። ልክ ኮከብን በጸሐይ ማየት እንደማንችል ሁሉ የክርስቶስም ብርሃን በአእምሮአችን ውስጥ ሲበራ እኛ አሳለፍን ብለን የምንኮራበት መከራ ልክ እንደኮከቡ የማይታይ ይሆናል። ያሳለፍነውን መከራ ሁሉ የምናስታውሰው ከሆነ (በኩራት መልክ) አሁንም ጨለማ ውስጥ እንዳለን መገንዘብ አለብን።

ፈሪሳውያን ሌሎችን ቁልቁል ይመለከታሉ

"ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ " (ሉቃ 18:9)

ሰዎች ለምን ሌሎችን እንደሚንቁ ብዙ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ከቤተሰቦቻቸው የተማሩት ሰውን በትምህርቱ በሀብቱ ወይም በዘሩ ቁልቁል ማየትን ይሆናል። ወይንም ደግሞ በትምህርት ቤት ውስጥ ጎበዝ ሆነን ሌሎችን በንቀት የምናይ ሆነን በዛውም ላይ ደግሞ ወላጆቻችን ጉብዝናችንን ደጋግመው የሚነግሩን እና የበለጠ እንድናውቀው የሚያደርጉን ከሆነ ነገሮች እየተበላሹ ነው የሚሄዱት። እንደዚህ ያሉ ብዙ ነገሮች አሉ ሌሎችን በንቀት የምንመለከትበት። እዮብ 36:5 ላይ እንዲህ ይላል "እነሆ፥ እግዚአብሔር ኃያል ነው፥ ማንንም አይንቅም" እግዚአብሔርን እየመሰልን በመጣን ቁጥር ስዎችን መናቅ ትተን ዋጋ መስጠት እንጀምራለን። ስለዚህ እራሳችንን እናንጻና ሰዎችን እግዚአብሔር እንደሚመለከታቸው ለማየት መማር አለብን። "አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?" (1 ቆሮ 4:7)

ፈሪሳውያን ራሳቸውን ከሌላው የበለጠ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ

"እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።" (ሉቃ 18:14) 
 ፈሪሳውያን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ አያገኙም ምክንያቱም እራሳቸውን ከፍ አድርገው ስለሚመለከቱ ነው። እራሳችንን ከሌሎች የበለጠ ከፍ አድርገን የምናይበት እና የምንናገርበት ብዙ ብልጠት የተሞላበት አነጋገር
አለ። ለምሳሌ ያገቡ ሰዎች ስለትዳራቸው ጥሩነት ያላገቡ ሴቶች ፊት ሲያወሩ በጣም አዳንቀው እና ከፍ አድርገው ይናገራሉ። ይህ አነጋገራቸው የነዚህን ያላግቡ ሴቶች ስሜት የሚነካ እንኳም ቢሆን ንግግራቸውን ለመቆጠብ አይሞክሩም። በእደዚህ ዓይነት ምስክርነት ሌሎችን መጉዳት የለብንም። ፈሪሳውያን ስለ ሌሎች ሰዎች ስሜት ምንም ግድ የሚላቸው አይደሉም። ስለዚህም ነው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ወይም ትክክለኛ ተብለው የማይታዩት ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚያጸድቀው ትሁትን ብቻ ነው። ሌሎች ብዙ መንገዶች አሉ እራሳችንን ከሌሎች አስበልጠን የምንናገርበት ይህ እንዳይሆን አስተሳሰባችንን እንዲያርም መንፈስ ቅዱስን መጠየቅ አለብን።

ፈሪሳውያን በሚያከናውኑት ስራ ጉራ መንዛት ይወዳሉ

"ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ። እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ" (ሉቃ 18:11-12)

 እግዚአብሔር በኛ ውስጥ ሆኖ ያደረገውን እኛ እንዳደረግነው አድርገን ስንቆጥረው እራሳችንን አደጋ ላይ እየጣልን ነው። ከፈሪሳውያንነት ነጻ መሆን ከፈለግን ለእግዚአብሔር ብለን በምንሠራው ሥራ ምንም ዓይነት ጉራም ሆነ ኩራት ሊይዘን አይገባም። የምንሠራውን ሥራ ለእግዚአብሔር ለብቻው እንዲያየው መደበቅ አለብን። ከሠራነው ሥራ ትንሽ እንኳ ጉራ ካለብን ከእግዚአብሔር ጸጋን አናገኝም። እግዚአብሔር ጸጋን የሚሰጠው ለትሑቶች ነውና።

 በፍቅርተ ኢየሱስ
ውድ አንባቢዎቼ ተጠንቀቁ በሚል ርእስ ሳካፍላችሁ የቆየሁትን የእግዚአብሔር ሐሳብ ከዚህ ላይ ጨርሻለሁ በሚቀጥለው «ድነሃልን ?» በሚል ርእስ ጽሑፍ አቀርብላችኋለሁና ጠብቁኝ። አባ ሰላማን አመሰግናለሁ።

2 comments:

 1. እነዚህ ሁሉ የፈሪሳውያን ባህሪ የሚንፀባረቀው በመናፍቃን ላይ ነው።ከኛ በላይ አማኝ የለም፡በኢየሱስ ድነናል፡ከኛ በላይ ክርስትያን የለም፡ባይኖራቸውም እንዳላቸው ለማስመሰል ይሞክራሉ፡ጉራ ያጠቃቸዋል፡ፃድቃን ነን ይላሉ፡ገንዘብ ይወዳሉ።

  ReplyDelete
 2. መናፍቅ ማለት እንደ ቃሉ ሲተረጎም በጌታ ትምህርት ላይ የማያምንና ጌታን እራሱን ቃሉን እየጠቀሰ (የማያምንበትን) እንደ ፈተነው የጽድቅ ጠላት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ከበርካታ ባእድ ነገሮች ጋር በመቀላቀል ክርስቲያን የሚለውን የማይኖርበት ስም ይዞ በመሳት የሚያስት አሰማሳይ ሲሆን ዋናው ዓላማውም ቃሉ የሌለውን ሕዝብ በደካማ ጎኑ ሁኔታዎችን እየተጠቀመ የሚያስት የነቁበትን የመንፈስ ቅዱስ ተማሪዎች ደግሞ መናፍቅ ሃይማኖች ከላሾች አገር ሻጮች መጤዎች ወዘተ በማለት ባልነቃው ሕዝብ ማስጠላትን ዋና ሥራው አድርጎ በመንቀሳቀስ የዚህን ምድራዊ ኑሮውን ማደላደል ነው:: ልክ ጌታ በሽተኞችን እየፈወሰና አጋንንቶችን እያስወጣ በነበረበት ወቅት አጋንንት አለበት እንዳሉትና ከዚያም እንደሰቀሉት ዓይነት ማለት ነው::

  ስለዚህ ወገኖች ማን ምን እንደሆነ በጌታ ቃል እየፈተሽን እናስተውል እንጂ ውሸት ልማዳቸው የሆኑትን ሰዎች ቃል ሰምተን እንደወረደ አንቀበል:: ሁሉንም በሕይዎት ፍሬያቸው እንፈትንና የሚጠቅመንን እንያዝ::

  ከዚህ በላይም ኮሚንት የሰጡ ሰው ላሉት የስድብ ቃል መረጃ ካለዎት ያቅርቡና ያሉትን እንመንዎት ደግሞስ ሰው በክርስቶስ ከሆነ ጻድቅ እንጂ ሌላ ምን ሊባል ነው? ልዩ ወንጌል ካለዎት ደግሞ እርግማን ስለሚሆንብን መቀብል ያቅተናልና አይልፉ::

  የጌታ ማስተዋል ይባዛልዎት! በምህረቱም ይጎብኝዎት!!

  ሰላም ይሁኑልን

  አክባሪ እህትዎ

  ሰላም ነኝ

  ReplyDelete