Tuesday, March 20, 2012

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እውነትና እውነተኞች የሚገፉባት፤ ሐሰትና ሐሰተኞች የሚነግሱባት እስከ መቼ ይሆን? - ክፍል 4 - - - Read PDF

ዘሪሁን ሙላቱ ኦርቶዶክሳዊ ወይስ ሰባልዮሳዊ ?

ኑፋቄ 3
ሐዋርያት ያጠመቁት በኢየሱስ ስም ነው

ባለፈው ጽሑፍ ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ እግዚአብሔር ሶስትም አንድም ነው የሚለውን ትምህርትና አገላለጽ በልዩ ልዩ መንገድ እየተማርን ያደግን በመሆናችን የምንስማማ ቢሆንም፣ ምስጢር ያደላደሉ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አምልተውና አስፍተው ያስተማሩትን በተለይም በምስጢረ ስጋዌ ላይ ያለውን ትምህርት ቃል በተለየ አካሉ ስጋ ሆነ የሚለው የተለመደ ኦርቶዶክሳዊ አገላለጽ ለአንዳንዶች ጆሮ እንግዳ መስሎ መታየቱና ይህን ትምህርት ከማሰላሰልና ከማጤን ይልቅ ዘሪሁን ስላሴን ወልዳለች ያለውን ሃይማኖት አፍራሽ አገላለጽ ብዙም ችግር የለው ብለው መቀበላቸው አስገርሞኛል፡፡

አንዳንዶች በነገረ ክርስቶስ ላይ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ስለሆነው ስለአንዱ ክርስቶስ ሲናገሩ፣ በአውጣኬያዊ[1] ስልት ፍጹም ሰውነቱን ወደአምላክነቱ ያዛውራሉ። በየአውደ ምሕረቱ የሚናገሩት ስለአምላክነቱ ብቻ ነው። ለፍጹም ሰውነቱና በሰውነቱ ስለፈጸመው የቤዛነት ስራ ግን ትኩረት አይሰጡም። ይህን የሚያደርጉት በፍጹም ሰውነቱ የፈጸመውን የማዳን ስራ ዛሬ ላይ ሆኖ መናገር እርሱን ከአምላክነቱ ደረጃ ዝቅ ያደርገዋል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ በሌላም በኩል የእርሱን የመካከለኛነት ስፍራ ለፍጡራን ስለሰጡ እነርሱን የት እናድርጋቸው በሚል ጭንቀትም ነው አምላክነቱን እያጎሉ፣ ሰውነቱን እያጎደሉ እንዲለፍፉ የሚያደርጋቸው፡፡ በዚሁ ስሜት ተወጥረው ሲሮጡም ትምህርተ ስላሴን ወደሚንድና የእግዚአብሔርን ሦስትነት በአንድነቱ ወደሚያስጠቀልል የሰባልዮስ ሰፈር ማረፊያቸውን ያደርጋሉ።


ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው ስንል ሶስቱም አካላት ተጠቅልለው አንድ ሆነው ኢየሱስ ተባሉ ማለት ፈጽሞ፣ ፈጽሞ አይደለም!! ሥጋ የሆነው ቃል እግዚአብሔርነት ካላቸው ከሶስቱ አካላት አንዱ አካል ነው ማለታችን ነው። በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሆኖ ያስታረቀውም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቀውም እርሱ አንድ ጊዜ ለዘላለም በፈጸመው የማዳን ስራ በኩል ነው እንጂ ከእርሱ በኋላ የተመደበ ሌላ መካከለኛ የለም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የክርስቶስን መካከለኛነት በማያሻማ ሁኔታ በግልጽ ቋንቋ አስፍሮታል፡፡ አንድ እግዚአብሔር አለና በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛ ደግሞ አንድ አለ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ (1ጢሞቴዎስ 2፡5-6)፡፡ መካከለኛው አንድ ነው አለ፤ እርሱም ሌላ ፍጡር ሳይሆን ሰው የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው አለ፤ መካከለኛነቱ ያለፈ ድርጊት ሳይሆን አንድ ጊዜ በተፈጸመው የማዳን ስራ አሁንም የሚሠራ በመሆኑ በሃላፊ አንቀጽ ነበረ ሳይሆን በአሁንና ቀጣይነት ባለው አንቀጽ አለሲል ዛሬም ኢየሱስ መካከለኛችን መሆኑን አረጋገጠ።

የዘሪሁንና የመሰሎቹ ትልቁ ችግር ለጻድቃን ለሰማዕታት እያደላደሉ ያለውን የመካከለኛነት ስፍራ ኢየሱስ ስለያዘባቸው እርሱን በሰባልዮሳዊ ስልት ከመካከለኛነቱ ለማንሳት ሲሉ፣ እግዚአብሔርን በተግባር አንድ አካል አንድ ገጽ አድርገውት ያርፋሉ። ዘሪሁን በመጨረሻ ላይ ኑፋቄው እውነተኛ ትምህርት መስሎ መስመር የያዘለት ስለመሰለው ሐዋርያት ያጠመቁት በኢየሱስ ስም ነው ሲል ሰባልዮሳዊ መሆኑን በራሱ አንደበት መሰከረ።  ዛሬ ይህን ነጥብ እንመለከታለን፡፡      

ከተጠያቂው ዘሪሁን ይልቅ ጠያቂው የዕንቁ መጽሔት ጋዜጠኛ የተሻለ የነገረ መለኮት ግንዛቤ እንደነበረው በግልጽ በታየበት በዚህ ቃለ ምልልስ ውስጥ ጋዜጠኛው ላነሳው ቀጣይ ጥያቄ ዘሪሁን የሰጠው ምላሽ፣ ሰባልዮሳዊነቱን በግልጽ አሳይቶበታል፡፡ ጋዜጠኛው እንዲህ ሲል ጠየቀው በዚህ ውስጥ ሥላሴ የሚለው መጠሪያ አልተጠቀሰም?

ዘሪሁን፡- ኢየሱስ ስንል የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተገለጸበት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ ሲባሉ ሐዋርያት በኢየሱስ ስም አጥምቀዋል፡፡ ይሄ ማለት ሐዋርያት ተሳስተዋል አያሰኝም፡፡ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተገለጸበት የእግዚአብሔር ፈቃድ ኢየሱስ ስለሆነ ኢየሱስ ስለሆነ በስሙ አጠመቁ፡፡ ልክ እግዚአብሔር የሚለው ስም በውስጡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንደያዘ ኢየሱስ የሚለውም ስም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ይዟል፡፡

ከዚህ የዘሪሁን መልስ የሚከተሉትን ኑፋቄዎች ማውጣት ይቻላል፡፡
1.      ሐዋርያት ያጠመቁት በኢየሱስ ስም ነው
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሀዋርያት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ነው ያዘዛቸው፡፡ ማቴ. 28፡19-20፡፡ እነርሱም በዚሁ መሰረት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው ያጠመቁት፡፡ ተጠማቂዎቹ ግን የጌታ የኢየሱስን ስም እየጠሩ ነው የተጠመቁት። ምክንያቱም ማንኛውም ሰው ክርስቲያን የሚሆነው በክርስቶስ የአዳኝነት ስራ አምኖ ነው። ስለዚህ ሲጠመቅ በአዳኙ አምኖና የአዳኙን የኢየሱስን ስም እየጠራ መጠመቅ አለበት፡፡ በሀዋርያት ስራ ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ የሚለው ሀረግ የሚያሳየውም ሀዋርያት ኢየሱስ የሰጣቸውን መመሪያ ጥሰው በኢየሱስ ስም አጠመቁ የሚል አንድምታ የለውም። ወይም ዘሪሁን ከሰባልዮሳውያን መንደር ቃርሞ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አውደ ምህረት ላይ የኦንሊ ጂሰስን አስተምህሮ እንዳንጸባረቀው፣ ኢየሱስ በውስጡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ይዟል በሚል በኢየሱስ ስም አጠመቁ የሚል ሐሳብ ፈጽሞ አናገኝም። ሀዋርያት ተጠማቂዎቹን ሰዎች በኢየሱስ ስም እንዲጠመቁ አዘዟቸው እንጂ። ማለትም ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን ካመናችሁ ስሙን እየጠራችሁ ተጠመቁ ማለታቸው ነው። አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ የሚለው ቃልም ይህን ያሳያል (የሀዋርያት ስራ 22፡16)። በዚህ ክፍል ሐናንያ ነው ሳውልን ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ያለው እንጂ አጥማቂው (ሐናንያ?) አይደለም በኢየሱስ ስም ያጠመቀው።
ይህን ጉዳይ ይበልጥ ለመገንዘብ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሲጠመቅ የሆነውን ማየት ይጠቅማል። ፊልጶስ ጃንደረባው ያነበው ከነበረው የኢሳይያስ መጽሐፍ በመጀመር ስለ ኢየሱስ አዳኝነት ወንጌልን ሰበከለት። የመጠመቅን አስፈላጊነትም እንደሰበከለት ጃንደረባው ካቀረበው ጥያቄ እንረዳለን። እንዳልጠመቅ ማን ይከለክለኛል? ነበር ያለው። ፊልጶስም ካመንህ ተፈቅዷል አለው። ጃንደረባውም መልሶ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ። (የሀዋርያት ስራ 8፡37)። ስሙን ጠራ ማለት ነው። ወዲያውም ከሰረገላው ወርደው ፊልጶስ ጃንደረባውን አጠመቀው።

የቀሩትንና ይህን የመሰሉትን ጥቅሶች ከሀዋርያት ስራ ብናነብም፣ ሀዋርያት በኢየሱስ ስም አጠመቁ የሚል መልእክት ፈጽሞ የላቸውም። ሀዋርያትና ሌሎቹም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በጊዜው በኢየሱስ አዳኝነት ያመኑትን ወደጥምቀት ሲጋብዟቸው፣ ተጠማቂዎቹ በኢየሱስ ስም ማለትም የአዳኛቸውን ስም እየጠሩ በስሙ እንዲጠመቁ ማዘዛቸውን ነው የሚያስረዱት።

·        ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ (የሀዋርያት ስራ 2፡38)
·        በጌታ በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቀው ነበር እንጂ ከእነርሱ በአንዱ ላይ ስንኳ ገና አልወረደም ነበርና። (የሀዋርያት ስራ 8፡16)
·        በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው። (የሀዋርያት ስራ 10፡48)
·        ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤  (የሀዋርያት ስራ 19፡5)
ስለዚህ ዘሪሁን ጌታችን ሐዋርያትን ያዘዛቸው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም የእግዚአብሔር ስም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ ሲባሉ ሐዋርያት በኢየሱስ ስም አጥምቀዋል፡፡ ይሄ ማለት ሐዋርያት ተሳስተዋል አያሰኝም። ያለው ሰባልዮሳዊ ኑፋቄ በውስጡ ተሰውሮ የሚገኝና የዘመኑ የኦንሊ ጂሰስ (የሀዋርያት ቤተክርስቲያን) አስተምህሮ ነው። ይህን አምጥቶ ኦርቶዶክሳውያን ላይ ሲያራግፍ ዝም መባሉ ቤተክርስቲያኗ አሁንም እንኳ ለእውነት እንጂ ለኑፋቄ በሯ ዝግ እንዳልሆነ አመልካች ነው። የምታሳድደውም እውነትን የሚመሰክሩ ልጆቿን እንጂ፣ ኑፋቄ የሚዘሩ መናፍቃንን አይደለም።

ሌላው ዘሪሁን የዘራው ኑፋቄ እግዚአብሔር የሚለው ስም በውስጡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንደያዘ ኢየሱስ የሚለውም ስም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ይዟል፡፡ የሚል ነው።

ሰው በሆነ ጊዜ ኢየሱስ የተባለው ወልድ ከሶስቱ አካላት አንዱ አካል በመሆኑ፣ እግዚአብሔር የሚለውን የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ የአንድነት ስም እርሱም ይጠራበታል። ከሥላሴ አካላት አንዱ አካል ነው ለማለት ከተጠቀምንበት ትክክል ነው፡፡ ችግር የሚያመጣውና ኑፋቄ የሚሆነው ግን ኢየሱስ ሰውም አምላክም መሆኑን ለማስተባበልና (በተለይ ሰው መሆኑን) የእግዚአብሔርን ሦስትነት በመጠቅለል አንድ ለማድረግ በሚሞከርበት ጊዜ ነው፡፡
በትምህርተ ስላሴ ውስጥ እንደተገለጸው አንዱ አካል በሌላው አካል ህልው ነው። ይህም ሶስትነትን የሚጠቀልል አይደለም። ጌታ ለፊልጶስ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? (ዮሀ. 14፡10) ያለው አንዱ በሌላው ህልው መሆኑን ያስረዳል። ስለዚህ በአብ ውስጥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው። በወልድ ውስጥ አብና መንፈስ ቅዱስ ህልዋን ናቸው። በመንፈስ ቅዱስ ውስጥም አብና ወልድ ህልዋን ናቸው። የእያንዳንዱ አካል ስም ግን የየራሱ መጠሪያ ነው እንጂ መፋለስ የለበትም። አሊያ በስም ሶስት ናቸው የሚለውን ትምህርት ገደል ይጨምራል። ዘሪሁን እያለ ያለው ግን ኢየሱስ የሚለው ስም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ይዟል የሚል ሰባልዮሳዊ ትምህርት ነው።

ይቀጥላል
ከጸጋ ታደለ[1] አውጣኬ በተዋህዶ ጊዜ መለኮት ስጋን ዋጠው አጠፋው በማለት ያስተማረና በአበው የተወገዘ መናፍቅ ነው

32 comments:

 1. ሠይፈ ገብርኤልMarch 20, 2012 at 7:48 PM

  ትኩረት ቢሰጥበት፡-
  1 ጢሞ 2፡5-6 አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥

  አሁንም በተጠቀሰው ጥቅስ ግድፈት ተፈጽሞ አያለሁ ፡፡ ኃይለ ቃሉ የሚያበቃው በነጠላ ሠረዝ ሳይሆን በአራት ነጥብ አረፍተ ነገር ነበር ፡፡ በስህተት ወይም የግል ስሜትን ለማንጸባረቂያ እንዲመች ታስቦ እንደሆን ጸሐፊው እራሱን ይመርምር ፡፡ ኃይለ ቃሉ የሚያበቃበት ወይም የሚደመድምበት “ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ፡፡” በማለት ያለፈ መሆኑን የሚያስገነዝበን ቃል ነበረው ፡፡ ይኸነ የመሰለ አገላለጽም በሚከተለው ኃይለ ቃልም ይደግመዋል ፡፡

  “ነገር ግን የሆነው ሁሉ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከእርሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና ፣ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር ፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖር ፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልዕክተኞች ነን ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን፡፡ …” 2 ቆሮ 5፡18-21

  ከእነዚህ በሁለቱ ኃይለ ቃሎች የምንገነዘበው የመካከለኛነትና የማስታረቁን ወይም የማማለዱን ሥራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈጽሞት ለዘለዓለም አድርጐ እንደደመደመው ነው ፡፡

  አሁን ቤተ ክርስቲያን ኃጢአትን እንድታስተሠርይ ጌታ በሰጣት ሥልጣን መሠረት ፣ ልዩ ልዩ ምሥጢራትን በመፈጸም ከኃጢአት እሥራት በመፍታት ፣ ሰውን ከእግዚአብሔር ታስታርቃለች ፤ ሰውና ሰውንም በፍቅር ታስተባብራለች /ዮሐ 2ዐ፡21-23 ፤ ሉቃ 24፡47/

  ሰላም ሁኑልኝ

  ReplyDelete
  Replies
  1. ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ! ጢሞቴዎስ ያለውን በአራት ነጥብና በነጠላ ሰረዝ ካባ ሸፋፍነኸው ከማለፍ፣ እንዴትና ለምን? እንዳለ ልታብራራ ይገባህ ነበር። ጥቅሱን በዚህ ኢ-አመክንዮዊ ሰበብ ከማለፍህ በላይ የዚህን ጥቅስ መደምሰሻና መሻሪያ ያገኘህ ይመስል ቆሮንቶስ ላይ ሮጥክ።
   «አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው»
   ግርዛትን በመገረዝ እና አለመገረዝን ደግሞ በእምነት ሁለቱን አንድ አድርጎ የተገረዙት አይሁዳውያንንና ያልተገረዙ አሕዛብን ከእግዚአብሔር ያስታረቀ መካከለኛው ማነው? ያለምንም አራትነጥብና ነጠላ ሰረዝ መልሱ «ኢየሱስ ነው»
   «እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ» ኤፌ 2፣14 ጳጳስ አይደለም፣ ቄስም አይደለም!!

   «ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ ደግሞ አምላክ አይደለምን? አዎን፥ የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያጸድቅ አምላክ አንድ ስለ ሆነ የአሕዛብ ደግሞ አምላክ ነው» ሮሜ 3፣29
   በዚህ መሃከል ጣልቃ የሚገባ ሌላ እሱ ማነው?
   እኛ ግን እንዲህ እንላለን።
   «ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን» 1ኛ ቆሮ 8፣6
   ማስታረቅ፣
   ክርስቶስ በሞቱ ሞታችንን ደምስሶ ከአባቱ ጋር አስታረቀን።
   «እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ»
   ሰው ይህንን ያገኘውን የእርቅ ነጻነት በኃጢአት እንዳያጠፋ፣ በተሰጠው የሕይወት ወንጌል ጸንቶ እንዲኖር፣ ለዘለዓለም አንዴ የተሰበከውን አገልግሎት እለት እለት የሚሰብኩ፣ የሚጸልዩ፣ ወድቀን ከሆነ ታረቁ ብለው የሚመክሩ ቅዱሳን አሉ። አዎ አሉ!!
   « አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ፣ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ» ተሰ 1፣21-25
   ጳውሎስ ያገለገለው ስለቤተክርስቲያን ፈጽሞ ይሰብክ ዘንድ ይሄንን ተናገረ እንጂ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ ሆኖ ስለሰው ልጆች ኃጢአት የእርቅ መንገድ እኔ ነኝ ማለት አይደለም። ከክርስቶስ በቀር መካከለኛ የለም የተባለው ክርስቶስ ለሞት ድረስ የታመነ ልጅ ስለሆነ ነው። ልጁ ደግሞ የቤቱ ወራሽ ነው። ሌላ ሁሉ ሎሌ ነው። ያለቤቱ ወራሽ ከአባቱ ቤት ማስገባት የሚችል ሎሌ የለም።
   «ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ ነበረ፥ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው፣እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን» ዕብ 3፣5-6
   «ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ» ገላ 4፣7 በቤቱ ላይ በታመነውና ወራሽ መሆኔ በተነገረበትን በክርስቶስ የአብ ልጅነቴ ወርጄ ሌላ አውራሽ ከየት እፈልጋለሁ?
   ስለዚህ «አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው» ሲል «አለ» ማለት ነበረ ወይም ይኖራል ሳይሆን እስከ የሌለው ፍጻሜ መሆኑን ስለሚያሳይ ይህንኑ አምናለሁ፣ እቀበላለሁ።

   ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው ገላ 5፣11

   Delete
  2. ሠይፈ ገብርኤልMarch 22, 2012 at 8:13 AM

   መካከለኛ - የቃሉ ትርጉም በሁለት ወገኖች መካከል ለማስታረቅ የሚቆም ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ለበደለኞች የሚያማልድና ከእግዚአብሔር ምሕረትን የሚያስገኝ ማለት ነው ፡፡ /ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ትርጓሜ የተወሰደ/

   እኔ ስለምን አስተያየቴን ልጽፍ ተገፋፋሁ ? የተጠቀሰው ምዕራፍ ቁጥርና የቀረበው ቃል ስላልተመጣጠነልኝ ብቻ ነው ፡፡ የቀረበልን ይህን ይላል “አንድ እግዚአብሔር አለና በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው መካከለኛ ደግሞ አንድ አለ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ” (1ጢሞቴዎስ 2፡5-6)፡፡

   የምንጠቀመው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ አይነት ከሆነ ደግሞ የተጠቀሰው ቁጥር ሙሉ ኃይለ ቃል በእኔ እንዲህ ይነበባል ፡፡ 1 ጢሞ 2፡5-6 “አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ፤” ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ የሚለው ቃል ከላይ በንባቡ ውስጥ ጐድሏል ፡፡ ይኸ የጐደለ ቃል ደግሞ እናንተ ከምትሉት በተለየ አድርጐ ትርጉሙን ይቀይረዋል ፤ ማለትም ኃላፊ ፣ የተፈጸመ ተግባር መሆኑን ግልጽ አድርጎ ያስረዳል ለማለት ነው፡፡ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበር የሚለው ቃል ባይጨመር ኖሮ እናንተ የምትሉትን ትክክል ተብሎ ሊቀበሉት የሚገባ ነበር ፡፡ ይህ ኃላፊ የሆነውን ነገር የሚያመለክተው የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው እንዳንልም በኪንግ ጀምስ ስም በተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስም ላይም "to be testified in due time" በማለት ተጠቅሶ ይገኛል ፡፡
   1 Timothy 5-6 “For there is one God and one Mediator between God and men, the Man Christ Jesus, who gave Himself a ransom for all, to be testified in due time,”

   ለምን ከቆሮንቶስ ሰዎች መልዕክት ተጠቀሰ ? ለጢሞቴዎስ የተጻፈው የኢየሱስ ክርስቶስን የቤዛነትን ሥራ ስለሚመሰክርና ሁለቱም አንድ ቃል ስለሚናገሩ ብቻ ነው ፡፡ ቤዛነቱን ተንተርሰን የመካከለኛ ሥራውን ማለትም አስታራቂነቱን ፣ አማላጅነቱን እንመሠክራለን ፡፡ የዚህም ቃል አተረጓጐምና ግንዛቤ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ከኘሮቴስታንት እምነት የሚለየን አንዱ ምክንያት ስለሆነ ፣ ሁሉም ሊያስተውለው ይገባል ፡፡

   ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዕለተ ዓርብ ድረስ በዚህ ዓለም በአካለ ሥጋ ተመላልሶ በመጨረሻ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በፈጸመልን ካሳ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስና ከራሱ ጋር ሲያስታረቀን የመካከለኛነት ሥራውን ፈጽሞ ደመደመው እንላለን ፡፡ ካሳው ተከፍሎ ከተፈጸመ በኋላ ፣ በደሉ ስለማይታሰብ መካከለኛ ፣ አስታራቂ አማላጅ የሚባል ጉዳይ አይኖርም ፡፡

   ብርሃኑ ጐበና በሆኀተ ብርሃን መጽሐፉ ከጻፈው የተወሰደው እንዲህ ይነበባል ፡-
   “1 ጢሞ 2፡5 እግዚአብሔር አንድ ነው ሲል በባሕርይ በመለኮት ሥላሴ አንድ መሆኑን ሲያስገነዝብ ሲሆን ፣ ሰው ሆኖ ሰውና እግዚአብሔርን ያስታረቀ ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ ነው አለ ፡፡ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ መዋሐዱን ሲያስረዳ ነው ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሁሉ ቤዛ አድርጐ ራሱን አሳልፎ ለሕማም ለሞት መስጠቱን ገልጾ እርሱ ታርቆን በተለየ አካሉ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ መስዋት ሆኖ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ፣ ከባሕርይ ህይወቱ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር እንዳስታረቀን ገለጸ ፡፡ እግዚአብሔርነት የሦስቱም ገንዘብ ነውና እግዚአብሔር የሚለው ስም የሥላሴ የአንድነት ስም ነው ፡፡”

   “ምናልባት አንድ ሰው በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው የሚለውን በአማላጅነት ወስዶት ዛሬም ከእግዚአብሔር አብ ጋር የምንገናኝበት አማላጃችን መሆኑን የሚያስረዳ ነው ሊል ይችል ይሆናል ፡፡ ይህ ግን ስሕተታዊ አመለካከት ከመሆኑ አልፎ የሥላሴን የባህርይ አንድነትና በመለኮታዊ ሥልጣን አንድ መሆናቸውን የሚጻረር ነው ፡፡ በእርግጥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ስለ አዳም ካሣ ሆኖ መቅረቡ የማይካድ ቢሆንም የማስታረቅ አገልግሎቱ ግን የተፈጸመው በመስቀል ላይ ነው ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ሲያስታርቀን የሚኖረው በእለተ አርብ የፈጸመው የማስታረቅ አገልግሎቱ ነው ፡፡ ይኸውም ተልዕኮ ለዘለዓለሙ ህያው እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን 7፡25 ላይ ገልጾታል “ዘወትር በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ለዘለዓለም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል”

   “በዕለተ ዓርብ ባደረገው ተልዕኮ እስከ ምጽአት ድረስ ሲያድንበት የሚኖር ስለሆነ ያስታርቃቸዋል ሊል ቻለ እንጂ ዛሬም ክርስቶስ አብን ይለምናል ማለቱ አይደለም ፡፡ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት ሆኖ ምልጃን ይቀበላል ፤ ይማለዳል እንጂ አያማልድም ፡፡ በባህርይ በመለኮታዊ ሥልጣን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ ነውና ፡፡ አብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ አይበልጥም ከተባለ ታዲያ ክርስቶስ ለአብ የሚያማልደው ለምንድን ነው ? ነገር ግን በዕለተ ዓርብ የፈጸመው የማስታረቅ አገልግሎት ዛሬም እኛን ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ ባጭሩ ከእግዚአብሔር ጋር ሲያስታርቀን ይኖራል እንጂ ዛሬ ኃጢአት ስንሠራ ከኃጢአታችን ለመንጻት የክርስቶስን ዳግመኛ መስቀል የምንጠባበቅ አይደለንም ፡፡ ይህንን ሁኔታ ግልጽ ሲያደርግ ጳውሎስ ለዘለዓለም ሕያው ነውና ያስታርቃቸዋል ብሎ ሕያው ዘለዓለማዊ አምላክ የፈጸመው የማስታረቅ ተልዕኮ ዘለዓለማዊ መሆኑን አስረገጠን እንጂ ክርስቶስ ዛሬም ያማልዳል አላለም ፡፡” በማለት ይደመድማል ፡፡

   ሐዋርያው ጳውሎስ ዘዳ 6፡4 ለመግለጽ አንድ እግዚአብሔር አለ ፡፡
   ገላ 3፡19 – 20 እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ። መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
   ገላ 4፡4 ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤
   ማር 1ዐ፡45 ፤ ማቴ 2ዐ፡28 እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።
   ቲቶ 2፡14 መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን፥ መልካሙንም ለማድረግ የሚቀናውን ገንዘቡም የሚሆነውን ሕዝብ ለራሱ እንዲያነጻ፥ ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል።

   ዕብ 9፡12 የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። በኦሪቱ ሕግ ሰው በኃጢአት በወደቀ ቁጥር መስዋዕት የማቅረብ ደንብ ፣ እንደ መካከለኛም ሆኖ የሚሠራ ካህን ነበራቸው ፡፡ ኢየስስ ግን ተደጋጋሚ መስዋዕት መሆን አያስፈልገውም ፤ አንድ ጊዜ የፈጸመው ለሁላችን የሚበቃ ፣ ለዘለዓለም የሚሆን ነውና ፤ ስለዚህም ተደጋጋሚ አስታራቂነትና መካከለኛነት አይኖርም እላለሁ ፡፡
   አመሰግናለሁ

   Delete
  3. ብዙ ዝብዝብ አባዛህ!
   የኦሪቱ ሊቀካህን አገልግሎት፣ የእግዚአብሔርን ወደ ሕዝቡ፣ የሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር በማድረስ መካከለኛ መሆን ነው። አይደል?
   ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ስጋ የለበሰበት ዋናው ነገር ሰዎች ከፈጣሪያቸው ጋር የነበራቸውን ጥል በሞቱ አፍርሶ ለማስታረቅ በመሃላ የተሾመ ሊቀካህናት ስለሆነ ነው። እርቁን እንደኦሪቱ ካህን በጥጃ ደም ሳይሆን በራሱ ደም አንዴ ፈጽሞ ለዘላለም በሆነ ማዳን በሥጋው ያረገ እንዲህ ያለ ሊቀካህናት በአብ ቀኝ ተቀምጧል።
   «ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን»ዕብ 8፣1

   እዚህ ጋ ጥያቄ ላንሳልህ? ዘለማማዊው ሊካህናት ክርስቶስ በሥጋው ያረገው ወይም ማረግ ያስፈለገው ለምንድነው?

   በለበሰው ሥጋ ያረገውና በአብ ቀኝ የተቀመጠው አምላክ ስላልሆነ አይደለም።
   ካረገም በኋላ በምድር ላይ የነበረውን ሰውነት ትቶ ያረገ በማስመሰል አሁንም ሊቀካህናት አይደለም እንዴት ይባላል?
   ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ ዕብ 9፣24

   በሥጋው ያረገው «ስለእኛ ይታይ ዘንድ» መሆኑን ልብ ይሏል? ለመለኰትማ መውጣትና መውረድ የለበትም።
   ስለእኛ የሚታይልን ሊቀካህን በሰማይ አለን።
   «ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም» ዮሐ14፣6

   ስለዚህም ይለናል ጳውሎስ፣ «ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል» ዕብ7፣25
   መካከለኛነቱ በእርሱ ለታመኑ ሁሉ አንዴ ፈጽሞ ባጸናት አገልግሎቱ ሆኗል።

   Delete
  4. ሠይፈ ገብርኤልMarch 23, 2012 at 9:06 AM

   እንድንማማር በበሰለ አእምሮ ሃሳብን መለዋወጥ ይልመድብህ ፣ባህልህም አድርገው !!! ለሁላችንም ይጠቅመናል ፡፡
   ወደ ኤፌሶን ሰዎች ምዕራፍ 2 ፡
   4-5 ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥

   8 ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤

   13-17 አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል። እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤

   ካሳው ተከፍሎልን ድናችኋል ፣ ቀርባችኋል ፣ የጥል ግድግዳ ፈርሷል ፣ ጥልንም በመስቀሉ ገድሏል ስለተባለ የአስታራቂነት ሥራው ተፈጽሟል ይባላል እንጅ ዛሬም ያማልዳል አይባልም ፡፡ አንድ ጊዜ የተፈጸመው መስዋዕትነት የአዳም ዘር ለሆንነው በሙሉ ህያው ሆኖ ስለሚያገለግለን ዕብ 7፡25 ማለት ተቻለ ፡፡

   አመሰግናለሁ

   Delete
  5. ሠይፈ ገብርኤልMarch 26, 2012 at 8:23 AM

   ተጨማሪም አስተያየት
   የሰው ልጅ አፈጣጠሩ እንደ ንጉሥ ቧለሟል ሆኖ ሁሉን እየተቆጣጠርና እያስተዳደረ ፣ ከአንዲት የዛፍ ፍሬ በቀር በሁሉም እንዲገለገልበት ተፈቅዶለት ነበር ፡፡ የፈጣሪን ዝግጅትና አደረጃጀት /አየሩ ፣ ውሃው ፣ ምግቡ ፣ ብርሃኑ ፣ ሙቀቱ ፣ ቅዝቃዜው ፣ ጸጋ ክፋኑ…./ ስናስብ እግዚአብጤር አዳምን /እኛን ይጨምራል/ ምን ያህል እንደወደደው ፣ ምን ያህል እንዳፈቀረው እንረዳለን ፡፡ ከሌሎች ፍጥረታቱ ለይቶ አዳምን በአርአያውና አምሳሉ ፈጥሮ ፣ የማትሞት ነፍስን መስጠቱም ሌላው የፍቅሩ መገለጫ ነው ፡፡ ይኸም ማለት ይወድና ያፈቅር የነበረው ገና ሳይፈጥረው ፣ ወደ እዚህ ምድር ሳያመጣው አስቀድሞ ነበር ያሰኛል ፡፡ እንደ አሁኑ ዘመነኛ ወላጆች ፣ ያልተወለደ ህጻን ልጃቸውን ለመቀበል በናፍቆት እንደሚዘጋጁት አልጋ ማዘጋጀት ፣ ልብስ መግዛት ፣ ጡጦ ፣ ሳሙና ማሰናዳትና መጨነቅ ዓይነት ማለት ፡፡

   እግዚአብሔር አዳምን ኃጢአት ከመሥራቱ በፊት ወዶት ነበር ብለንም አናበቃም ፡፡ ይልቁንም ይኸ ፍቅሩ አዳም አምላኩን ከበደለ በኋላም አልተለወጠም ፤ አልጠፋም ፤ እንዲያውም ይበልጥ ጠነከረ ፤ ይበልጥም ተገለጠ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ሰው አይደለምና ባህርዩን አይቀያይርም ፤ ቃሉንም አያጥፍም ፤ ዕቅዱንም አይሰርዝም ፡፡ እግዚአብሔር አንድ ጊዜ ያለው ለዘለዓለም ቋሚ ነው ፡፡ ብርሃን ይሁን አለ ይኸው እስከ ዛሬ ብርሃን አለ ፤ ፀሃይና ጨረቃም በብርሃን እነዲሠለጥኑ ታዘዘ ፣ ይኸው በቀንና በለሊት ሥርዓትን ሳያዛንፉ ይገኛሉ ፤ ምድርንም ታብቅል አለ ይኸው እያበቀለች እንደሆነ እናያለን ፡፡ ስለዚህም ሰውን የወደደበት ፍቅሩም ዘለዓለማዊ ነውና ፣ ለማዳንና እራሱን ፣ በራሱ በኩል ሊያስታርቅ በመፍቀዱ የፈጠረውን ሥጋ በአንድያ ልጁ በወልድ በኩል እስከመዋሃድ ደረሰ ፡፡

   ወልድም መንበሩን ትቶ በኃጢአት ወደ ረከሰው ሰው ሲመጣ አልተጠየፈም ፤ ይልቁንም መዋረዱን ተቀብሎ ርግማናችንን ርግማኑ ፣ ሞታችንንም በሞቱ አድርጐ ነጻ አወጣን ፡፡ ከዛም የተዋሃደውን ሥጋ ሳይተው ወደ ጥንት መንበሩ አረገ ፤ የኃጢአተኛው የአዳም /የማርያም/ ሥጋም ፣ በወደደን በኢየሱስ በኩል ከበረ ፡፡ ለንጉሥ ባለሟልነት የተፈጠረው አዳም በወልድ በኩል ሆኖ ይበልጥ ማዕረግ ወይም ክብርን አገኘ እንላለን እንጅ ሥጋችንን ተዋህዶ ሰለሄደ ያማልዳል አንልም ፡፡ ይህ ስጋችንን ተዋህዶ አርጓልና ያማልዳል ማለት የጽርፈት አባባል ነው ፡፡ ስለምን ቢሉ ፣ አምላክነቱን ሽሮ ወደ ሰውነቱ መልሶ አሁን ተኝቷል ፣ አሁን ደክሞታል ፣ ውሃ ይጠማዋል ፣ ምሳ አምጥተንልሃል ለማለት ስለሚያስደፍር ፤ አምላክነቱን ክዶ ፍጹም በሰውነቱ ባህርይ ማኖር ስለሚሆን ፡፡ ስለዚህም ስጋችንን በመዋሃዱ አከበረን ማለትን እንልመድ ፡፡ እርቅና አማላጅነቱ እስከ መስቀለ ሞቱ ድረስ ተጉዞ ፈጸመ ፤ ከፈጠረው ሥጋ ያልተፈጠረው አምላክ መዋሃድ ያስፈለገውም ፣ መስዋዕት በመሆን ካሳችንን ከፍሎ ፣ ፍርድን ፈጽሞ ሊያስታርቀን ነው እንጅ ፣ ዛሬም እንደ ቀደመው በሥጋው ሊወጣበትና ሊወርድበት ፣ ሊገለገልበት እና ሊያማልድበት አይደለም ፡፡ አንድ ጊዜ የተከፈለው መስዋዕት ፣ እንደ ፍየልና በግ ስላልሆነ ለዘለዓለም ያገለግላል ፡፡ ስለዚህም ዘለዓለማዊው ካህን ፣ ህያው መስዋዕታችን አቀረበልን እንላለን ፡፡

   ክርስቶስ ከተሰቀለና ልጅነት ከተመለሰ ወዲያ እንደ ቀድሞው የነፍሳት ወደ ሲዖል መጋዝ ቀርቷል ሮሜ 5፡11 መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን ይለዋልና ። ክርስቶስ ወዶና ፈቅዶ ራሱን በማዋረዱ ፣ ተዋርደንና ተጥለን የነበርን እኛ ከንቱዎቹ ከብረናልና ፡፡
   ስለዳንንበት ፣ ስለታረቅንበት ኢየሱስን አምነን ማመስገን እንልመድ ፤ በኢየሱስ ማዳን እንመካ ፤ አብ ወልድ መንነፈስ ቅዱስንም ስለ ማዳን አሠራራቸው እናወድስ፡፡

   አመሰግናለሁ

   Delete
  6. TO :-ሠይፈ ገብርኤልMar 22, 2012 08:13 AM
   ካሳው ተከፍሎ ከተፈጸመ በኋላ ፣ በደሉ ስለማይታሰብ መካከለኛ ፣ አስታራቂ አማላጅ የሚባል ጉዳይ አይኖርም ፡፡U SAYS THIS,BASED ON THIS(UR)IDEA EVERY ONE IS SAVED WHETHER HE/SHE BELIEVED OR NOT.BUT FOR THOSE WHO BELIEVE,HE IS MEDIATOR FOR THEIR SIN.FOR THOSE WHO R NOT BELIEVE HE IS THE MEDIATOR FOR EVERLASTING LIFE TO COME TO THE FATHER THROUGH JESUS.BASED ON JOHN 14:6

   Delete
  7. ሠይፈ ገብርኤልMarch 29, 2012 at 1:41 PM

   ለመዳንና የተገኘውን እርቅ ተጠቃሚ ለመሆን ፣ አምኖ መጠመቅ ያስፈልጋል ፤ በጅምላ መዳን ፣ በጅምላም መታረቅ የሚባል ነገር የለም ፡፡ አምላካችን ሰው ሆኖ ስለእኛ ሞተልን ፣ እንደገናም በራሱ ሥልጣን ተነሣ ፣ አረገ በአባቱም ቀኝም ተቀመጠ ፣ ወደፊትም ለመፍረድ ዳግም ይመጣል ብለህ አምነህ ከተጠመቅህ በኋላ ግን አዲስ ልጅነትን ስለምትቀዳጅ ፣ አስቀድሞ የነበረብህ ኃጢአት /በግብር ወይም በውርስ/ በሙሉ ይሻራል ወይም ይደመሰሳል ፡፡ ስለዚህም የአስታራቂነቱን ሥራ አምነን በመጠመቃችን ድልን አገኘን እንላለን ፡፡ ከታረቅንና ዳናችሁ ብሎ የምስራቹን ከአበሠረን በኋላ ሌላ አዲስ እርቅ እንደገና አንጠብቅም ፣ ሌላ ምልጃም ዳግም አይፈጸምም ፡፡ ከተጠመቅን በኋላ በድክመት የምንፈጽመውን በደል በሙሉ ንስሐ በመግባትና የቤተ ክርስቲያን ቀኖና የሚያዘውን የጾም ፣ የስግደት ወይም ሌላ ማስተማርያ እርምጃ በመፈጸም ይቅርታ እናገኛለን ፡፡

   አመሰግናለሁ

   Delete
 2. Yehe menafeke sewene menafeke sil ayaferem. Zerihun Yemenafekan aleka new.

  ReplyDelete
 3. ወገኖች ይህ የስላሴ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያን የታሪክ ሂደት ውስጥ ለበርካታ ወገኖች ችግር የፈጠረና ለመደናገር ምክናያት የሆነ ርዕስ ስለሆነ ኦንሊ ጅሰስ የሚጠቅሷቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ወስዳችሁ ትክክለኛ ትርጉማቸውን በማስረጃ ለማቅረብ ብትሞክሩ መልካም ይመስለኛልና ትኩረት ሰጥታችሁ ብታስቡበት??? ለሚሉትና በሚያስተላልፉት ትምህርት ላይ የበለጠ መረጃ ለማግኘት እንድትችሉ የሚጠቀሙባቸውንና በአንድ በተለወጠ የሱማሌ ተወላጅ ሙስሊም (PAUL THOMAS) የተጻፉትን:

  1) WHO ARE YOU LORD?
  2) THE RIGHT HAND OF GOD
  3) THE SECOND MAN THE LORD FROM HEAVEN

  አግኝታችሁ ብታነቡ የምትሉትን የበለጠ ማወቅና ማግኘት ትችላላችሁ::

  ሁላችንንም እግዚአብሔር ይርዳን አሜን::

  በለጠ ተሰማ

  ReplyDelete
 4. Zerihun knmehretabe gare wana mafiya new.haymanot yelelw kehadi selhone kebet kerstiyan lejoch mhale ayekoterm.

  ReplyDelete
 5. ወገኖች!!!

  እውነትን ከመንፈስ ቅዱስ ተምሮ የተረዱትን ላልተረዱት ለማስረዳት መሞከር እውነተኛ ክርስቲያናዊ ተልዕኮ ነው:: ስለዚህ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ትክክለኛ ማንነት የሕይዎት መመሪያ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ከሚለው ውጪ ለማለት መሞከሩ ተሳስቶ ከማሳሳትና እራሱ ጌታ የተነገረው 'ወንድምን ከማሰናከል የወፍጮ መጅ በአንገቱ አስሮ...' የሚለው የፍርድ ቃል በራሳችን ላይ እንዲሠራ መጋበዝ ነውና ከቃሉ ባንወጣ እጅግ እጅግ ይመረጣል:: ይሻላልም:: ስለዚህ:-

  'ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር'(1ጴጥ 4:11) ስለሚል የምንለውን ከቃሉ መረጃ በማቅረብ ለማስረዳት ብንሞክር አንባቢንና የቤተ ክርስትያናችንን በርካታ ሕዝብ ከመደናገር እናድነዋለን::

  በዚህ መሰረት የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅነት በቃሉ:-

  1)'... እርሱ ግን የብዙ ስዎችን ኃጢአት ተሸከመ ስለ ዓመፀኞችም ማለደ::' (ኢሳ53:12)

  2)'የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሣው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው ደግሞም ስለ እኛ የሚማልደው
  ክርስቶስ ኢየሱስ ነው::' (ሮሜ 8:34)

  3)'እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው.....ናቸው: እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ
  የማይለወጥ ክህነት አለው: ስለእነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና(ዕብ7:23-25)

  4)'ልጆቼ ሆይ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ:: ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው::' (1ዮሐ 2:1)

  ወ ዘ ተ የመሳሰሉትን በመንፈስ ሆነን ለመረዳት ብንሞክር የክርስቶስ የምልጃ ሥራ እስከምን ደረጃ ድረስ እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን ብየ አምናለሁ::

  ለምሳሌ ከዚህ በላይ ያስቀመጥኳቸውኝ ጥቅሶች ብቻ እንኳ ለማየት ብንሞክር:-

  ሀ)በተራ ቁጥር 2 ላይ ጌታ በአብ ቀኝ ያለው ማለቱ ከእርገቱ በኋላ ያለውን
  ለ)በተራ ቁጥር 3 ላይ ደግሞ ለዘላለም የሚኖርና የማይለወጥ ክህነት አለው የሚለው ዘላለማዊነቱን
  ሐ)በተራ ቁጥር 4 ላይ ያለውም በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን የሚለው በተጨማሪ መቼ ብለን ብንጠይቅ
  ኃጢአት በሠራችሁ ጊዜ(ዛሬም ነገም) በአብ ዘንድ ወደአለው ጠበቃችን መጮህ የሚል መልስ
  የምናገኝ ይሆናል::

  ታዲያ ጌታ ከከበረ ወይም ካረገ በኋላ ያለውን ማንነቱንና በዚህ ምድር የነበረበትን ማንነቱን ክፋፍለን በማየት ያማልድ ነበር:: አሁን ግን ይማለዳል እንጂ አይማልድም በማለት እንድናየው የሚደረገው ምን ዓይነት የቃሉ መረጃ አግኝተን ነው? ነው ወይስ ቃሉን እንዳመቸን አንድም እንዲህ አንድም እንደዚያ እያልን በመተርጎም ወደምንፈልገው አቅጣጫ እንደፈለግን በማስኬድ የስጋ ስሜታችንን እንዲያገለግል ማድረጉ ከየት የመጣ ነው??? እባካችሁ እዳ በላያችን ላይ ባናበዛ ይሻላልና ዝም ብለን ከመንፈስ ቅዱስ ብንማር???????????????

  የጌታ ማስተዋል ለሁላችን ይብዛልን!!!

  ሰማያዊና የማይጠፋ መዝገብ መሰብሰብ እንጂ የፍርድ እዳ ባናካብት መልካም ነው::

  ሰላም ሁኑልኝ

  በጌታ ፍቅር እወዳችኋለሁ::

  ሰላም ነኝ

  ReplyDelete
  Replies
  1. ሠይፈ ገብርኤልMarch 22, 2012 at 12:58 PM

   ስለ አማላጅ የተጠቀሱ ሌሎቹንም ምዕራፎች አብረን መተርጐምና ማስማማት ከቻልን ደግ ስለሚሆን እስቲ በጥሞና እንመልከታቸው ፡፡
   ሮሜ ምዕራፍ 8፡ 26 – 27 እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና። /ግንዛቤ መንፈስ ቅዱስ ይማልድልናል/

   ሮሜ 8፡34 የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። /ግንዛቤ ኢየሱስ ይማልዳል/

   ኤር 7 ፡23-25ነገር ግን። ቃሌን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው። ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር። /ግንዛቤ እግዚአብሔርም ይማልዳል/

   እነዚህን ሦስቱንም ኃይለ ቃሎች አስማምተንና አስታርቀን ለመጠቀም እንድንችል በጸሎታችን ማለት የሚገባን አብ ፣ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አማልዱን ማለት ሊያስፈልግ ይመስላልና የገባችሁን አስረዱኝ ፡፡ ሦስቱም ለሰው ልጆች አማላጅ ከሆኑ ተማላጅ ማን ሊሆን ይችላል ? ማንስ ሊሆን ይገባል ?
   አመሰግናለሁ

   Delete
  2. ኤር. 7፡25 ‹‹አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስካዛሬ ድረስ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር›› ተብሎ የተጻፈው ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እያከታተለ በላካቸው ነቢያት አማካኝነት ወደ እርሱ እንዲመጡ በየጊዜው የጠራቸው መሆኑን ይገልጻል፡፡ ዛሬም በዐዲስ ኪዳን በሐዋርያትና በሌሎቹም አገልጋዮች እየማለደ ድኀነት የሚገባቸውን ሁሉ እንደሚጠራ ማለት ነው፡፡ (2ቆሮ 5፡ 20)
   በጥሪው የተገኘው ውጤት ‹‹ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፡፡ አባቶቻቸውም ካደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ›› (ኤር 7፡26) የሚል ሲሆን ‹‹በየዕለቱ እየማለድሁ›› ለሚለው ቃል ሙሉ ትርጉም ይሰጣል፡፡ እግዚአብሔር በነቢያቱ ኑ ብሎ የለመናቸውና እንቢተኛ የሆኑት እነርሱ ናቸው ማለት ነው እንጂ አብ ወደ ሌላ አምላክ ማለደ አያሰኝም፡፡

   ስለ መንፈስ ቅዱስ በሮሜ 8፡ 26-27 እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፡፡ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለቅዱሳን ይማልዳልና የተባለው በጸሎታቸው ጊዜ ክርስቶስን በማመን ቅዱሳን የሆኑትን ሁሉ መንፈስ ቅዱስ እንደሚረዳቸውና በድካማቸው እንደሚያግዛቸው ያመለክታል፡፡ ቅዱሳን በመንፈስ ሆነው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ሆኖ መንፈሳዊ ነገርን ማለትም ምስጋናን፣ ስለሌሎች ምልጃን፣ ልመናን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ ኃጢአታቸውንም እያሳሰበ እንዲናዘዙበትና ከዲያብሎስ ክስ ነጻ እስከማድረግ ድረስ የሚያደርግላቸው እገዛ ነው እንደ ምልጃ የተቆጠረው፡፡

   Delete
  3. ሠይፈ ገብርኤልMarch 23, 2012 at 6:19 PM

   ቃሉን እንዳመቸን አንድም እንዲህ አንድም እንደዚያ እያልን በመተርጎም ወደምንፈልገው አቅጣጫ እንደፈለግን በማስኬድ የስጋ ስሜታችንን እንዲያገለግል ማድረጉ ከየት የመጣ ነው?

   አመሰግናለሁ

   Delete
 6. ሠይፈ ገብርኤልMarch 22, 2012 at 12:36 PM

  ድንግል ማርያም በእርግጥ ስላሴን ወልዳለች?
  በስማ በለው ተመርቶ ድምዳሜ ላይ መድረስ ፣ አብሮ አጫፋሪ ወይም አጋፋሪ ከመሆን ያለፈ ልዩ ትርጉም አልሰጠውም በማለት ራሴን ከፍትጊያው በማውጣት ነጻ የአእምሮ ስሌቶችን ተጉዠባቸዋለሁ፡፡
  የ….. ጸጋ ታደለ የከሰሰበትን ምክንያት ለማጣራት ፣ የ.. ዘሪሁን የተናገረውን ለማግኘት ብሞክርም ያ ትምህርት የተሰጠበትን ድምጸ ምስል ማግኘት አልቻልኩም ፡፡ ስለዚህም ነገር ያለሰለስኩ መስሎኝ አስታራቂ ሃሳብ ለማግኘት እንዲያው በምናልባት በዚህኛውስ በኩል ተረድቶት እንደሁ ፣ ምናለ ነገሩን ባናከብደው ብዬ በራሴ ክፍተትን ለማግኘት ብዙ ሞከርኩ ፡፡ ይኸም የእውቀት ማነስ ወይም የመወገን ስሜት ፣ ለሆድ ማደርና የጥቅም ተገዥነት ተጭኖኝ ሳይሆን የተጣሉ ወገኖችን ቢያንስ በጾም ወራት ማጫፈሩ ቅዱስ ሥራ ስላልመሰለኝ ነው ፡፡ በጊዜው ያየሁት
  1. ከስላሴ ምሉዕነት ባህርይ በመነሳት በድንግል ማኀፀንም ተገኘ ብሎስ ቢሆን
  2. አብ በእኔ ውስጥ እንዳለ ፣ እኔ ደግሞ በአብ ውስጥ የሚለውን የወንጌል ትምህርት በመመርኮዝና አንድነታቸውን በመመልከት ተናግሮት ከሆነስ
  3. ወልድ ከሥላሴ አንዱ አካል ስለሆነ ፣ በሌላ ቋንቋ ሲገልጽ ምናልባት የምላስ መዳለጥ ሥላሴን በድንግል ማኀጸን አደረ አስብሎስ ከሆነ /ለምሳሌ አንድ ቤተሰብ አንድ መኪና ቢኖራቸውና ከቤተሰቡ ውስጥ አንዱ ልጅ ብቻ እያሽከረከረ የቤተሰቡ መኪና ቢታይ ፣ የእነ አቶ እከሌ መኪና እንደሚባለው ያህል ማለቴ ነው/
  ስለነዚህ ምክንያቶች ነገሩን ችላ ብላችሁ ወደ እርቀ ሰላም ግቡ ፤ ለእኛ የተማራችሁት ሰዎች እጅግ ታስፈልጉናላችሁ ፡፡ በሰበብ አስባቡ ስትበታተኑ ፣ ትጐዱን እንደሁ እንጅ ጥቅም አናገኝበትምና ራሳችሁን አሸንፉት ለማለት የተጠቀምኩበት አገላለጽ ነበረ ፡፡ ተወቃሽ ግለሰብ የታማበትን ጉዳይ ምክንያት ቢያቀርብልን ኑሮ የኔም እዛና እዚህ መዘላበድ ባልመጣም ነበር ፡፡ ነገር ግን በአሉባልታ ብቻ ፍረዱኝ የሚል ማመልከቻ ሲቀርብ ፣ የበዳይን ምክንያት ምን እንደሆነ ከሥሩ አላወቅንምና ፣ ለጊዜው መልካም መንገድ የመሰለኝን በሩቅ ለማሳየት ሞከርኩ ፡፡
  ከዚህ በተጻራሪ የቀረበውን አቤቱታ ለመቃኘት ስሞክር ደግሞ ለኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ቀናዒ አስተሳሰብ በመነሳት ነው ብዬም እገምታለሁ ፡፡ ባለጉዳዩ የኢየሱስን መጸነስ በመግለጽ ይጀመርና ፣ በርሱው መስዋዕትነት ይቀጥላል ፤ ኋላ ላይ ደግሞ አዳኛችን ኢየሱስ ብቻ ነው ለማለት ይገደዳል ፡፡ ይኸም በአንዳንድ የሥላሴ ምሥጢርን በሥርዓቱ ያልተማርነውን ክርስቲያን ወገኖች አብንና መንፈስ ቅዱስን መግደፍን ያስከትላልና አጉል ጅምር ነው ለማለት ሞክሬአለሁ ፤ አካሄዱንም በመፍራቴ ወደ ሌላ አምልኮ እንዳንሄድ በማለት በደፈናው ስጋቴን አሳወቅሁ ፡፡
  አስቀድሞ መለያየት በመሃከላችሁ አይኑር 1 ቆሮ 1 ፡ 1ዐ
  በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ መንፈሳውያን የሆናችሁ በየውሃት መንፈስ አቅኑት ገላ 6 ፡ 1
  በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት በአሳቡም ላይ አትፍረዱ ሮሜ 14 ፡ 1
  ሰሚ ካገኘ ሐዋርያው ክርስቲያን ወንድምህ ቢደክምብህ ብቻውን ምከረው ፣ አልሰማ ቢልህ በሁለትና በሶስት ሰው መሃከል ሞክረው ፤ ቢያስቸግርህ ወደ አባቶች እያለ ደረጃውን ዘርዝሯል

  ከዚህ በላይ በዘረዘርኳቸው ምክንያቶች ግድፈጽግ ፈጽሜአለሁና ትችቱን ስለአስተማሪነቱ እቀበላለሁ ፡፡ በተረፈ የሚከተለውንም አንባቢ እንዲመለከተው አዘጋጅቻለሁ ፡፡

  ክፍል ሁለት ይቀጥላል

  ReplyDelete
 7. ሠይፈ ገብርኤልMarch 22, 2012 at 12:37 PM

  አቋም ፡-
  “የጥበባችን ምንጭ ሁሉ እግዚአብሔር ስለሆነ ፣ እንኳንስ አንብበን የተረዳነውን መልሰን የምናነበንብና የምንጽፍ ሊቃውንት ይቅርና ፣ በምርምር የሮኬት ሳይንስንም ያገኘው ጠቢብ ቢሆን በራሱ ዕውቀት ሊመካ አይገባውም ፡፡”
  ምሳሌ 2፡6 - እግዚብሔር ጥበብን ይሰጣል ፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፡፡
  ምሳሌ 9፡7 - ኀጥእንም የሚዘልፍ ነውርን ያገኛል ብሎ መጽሐፍ ይመክረናልና ዳግም አንሳሳት ፡፡

  ለአንባቢ ማስገንዘቢያ ፡-
  ይሄ ጽሁፍ የአንድ ምእመን የንባብ ግንዛቤ እንጅ ፣ በሃይማኖት ትምህርት የጠለቀ ዕውቀት ያለው ፣ የሠለጠነ የሊቅ ጽሁፍ እንዳልሆነ አንባቢ አስቀድሞ እንዲረዳው አስገነዝባለሁ ፡፡

  የጽሁፉ ዓላማ ፡-
  ከዚህ መነሻ ሃሳብ በመነሳት ሁሎችም የቤተ ክርስቲያን ልዩነቶቻችን ከየት እንደመጡ እነዲመረምርና ፣ የአንድነት መንገድ ከተገኘ እንዲቃኝ ፣ እንዲፈልግ በማለም ነው ፡፡ ሌላውም ደግሞ የምንወቀስበትን የአነጋገርና የአጻጻፍ ግድፈት ለመቀነስም ያግዘን እንደሆን በማሰብ ነው ፡፡

  የቤተ ክርስቲያን መከፋፈልን ያስከተሉ ምክንያቶች፡-
  በሐዋርያት ዘመን የክርስትና እምነትን የሚፈታተኑት ፣ ከውጭ ሃይማኖቱን ያልተቀበሉ ወገኖች ብቻ አልነበሩም ፡፡ ይልቁንም ችግሮች የተፈጠሩት የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትን አምነው በተቀበሉ ክርስቲያን ነን በሚሉ አባቶች ናቸው ፡፡

  በመሃከላቸው ለተፈጠሩት አለመግባባቶች ቀዳሚ ምክንያቶች የነበሩት ፣ በነገረ ክርስቶስ ፣ በመንፈስ ቅዱስና ነገረ ማርያም ዙሪያ የተነሱ የግንዛቤ ልዩነቶች ናቸው ፡፡ በወቅቱ ተነስተው የነበሩ የአመለካከት ልዩነቶችን አጠቃላይ ግንዛቤ ለመንደርደሪያ ያህል እንዲሀን በማለት በአጭሩ እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡

  የሃይማኖት ክፍፍል ተቀዳሚ ምክንያቶች ፡-
  ሀ/ ኢየሱስን በተመለከተ ፡-
  ሀ. ኢየሱስ ከአምላክ ያነሰ ፣ ነገር ግን ከሰው የበለጠ ፣ ለየት ያለ ፍጡር ነው
  ለ. ኢየሱስ ፍጹም አምላክ ነው
  ሐ. ኢየሱስ ሰው ነው ፣ አምላክ አይደለም
  መ. ኢየሱስ በብዛት አምላክ ሲሆን በመጠኑ ደግሞ የሰውነት ባህርይ አለው
  ሠ. ኢየሱስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው ፡-
  1- ሰውና አምላክ ቢሆንም አሠራራቸው በተናጠል ነው ፣ ስለዚህ መለኮት አልሞተም ፣ ሥጋ ሲሰቀልም ፣ መለኮት ትቶት ተለይቷል ፣ ስለዛም ትቶት ሲሄድ ለምን ተውኸኝ ብሎ አቤቱታ አቅርቧል /ካቶሊክ/
  2- ሰውና አምላክ በፍጹም ውህደት አንድ ሆነዋል ፣ በዚህም ሥጋና መለኮት ባህርያቸውን አንዱ የሌላውን ገንዘቡ አድርጓል ፤ መለኮት ፍጹም ሥጋን በመዋሃዱም /የሥጋን ባህርይ ገንዘቡ በማድረጉ/ በመስቀል ላይ ሞቷል ባይባልም ፣ ሥጋ ሲሞት አልተለየውም /ኦርቶዶክስ/

  ለ/ መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ ፡-
  ሀ. መንፈስ ቅዱስ አምላክ አይደለም ፣ አብና ወልድ የሚገለገሉበት ኃይል ነው
  ለ. መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው
  1- መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይወጣል /ይሰርጻል/ ስለዚህም ምክንያት ከሁለቱም የሚያንስ ፍጡር ነው
  2- መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ ይወጣል / ይገኛል ፤ በአምላክነትም ከአብና ከወልድ ትክክል ነው

  ሐ/ ድንግል ማርያምን በተመለከተ ፡-
  ሀ. ድንግል ማርያም የክርስቶስ እናት እንጅ ፣ የአምላክ እናት መባል የለባትም
  ለ. የአምላክ እናት መባል አለባት ፣ ቃል ፣ ወልደ እግዚአብሔር ስጋን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በማህጸኗ ስለተዋሃደ አምላካችንን ወልደዋለችና እመ አምላክ ትባላለች

  ክፍል ሦስት ይቀጥላል

  ReplyDelete
 8. ሠይፈ ገብርኤልMarch 22, 2012 at 12:37 PM

  እነኝህን መሠረታዊ ልዩነቶች ለመፍታት አባቶች እየተሰበሰቡና የተከራካሪዎችን ሃሳብ እያዳመጡ ፣ ከመጽሐፍ ጋር የሚስማማውን በመቀበል ፣ የተሳሳተውን ወገን ደግሞ እንዲታረም እየመከሩ ፣ አልሆንም ሲልም እያወገዙ የቤተ ክርስቲያን አባትነት ግዴታቸውን በጊዜው ተወጥተዋል ፡፡ የተላለፉ ውሳኔዎችን የመቀበልና ያለመቀበሉ ሁኔታ ግን ቤተ ክርስቲያንን እስከዛሬ ድረስ ከፋፍሏት ይገኛል ፡፡ ለምሳሌም ያህል

  - የመጀመሪያ ሁለቱን ጉባዔዎች ውሳኔ ብቻ የተቀበሉ - ንስጥሮሳውያን
  - የመጀመሪያ ሦስቱን ጉባዔዎች ውሳኔ ብቻ የሚቀበሉ - የኦርየንታል ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት /ኢትዮጵያ ፣ ግብጽ…/
  - የመጀመሪያ ሰባቱን ጉባዔዎች ውሳኔ ብቻ የሚቀበሉ - የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት /ግሪክ ፣ ሩስያ …./
  - የሁሉንም ጉባዔዎች ውሳኔ የሚቀበሉ ደግሞ - የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ

  የተደረጉ ጉባኤዎች
  1. የኒቂያ ጉባዔ - የተደረገው በ325 ዓ.ም. የአርዮስን የተሳሳተ ትምህርት /ኢየሱስ አምላካዊ ፍጡር ነው የሚለውን/ በማውገዝ የተጠናቀቀው ነው
  2. የቁስንጥንያ ጉባዔ - የተደረገው በ381 ዓ.ም. ነው ፡፡ በውሳኔአቸውም የኒቂያን ሃይማኖት አጸኑት ፤ መንፈስ ቅዱስ ፍጹም ጌታ ፣ ህይወትን የሚያድል ፣ ከአብ የወጣ ፣ ከአብና ከወልድ ጋር በአንድነት የሚሰገድለት ፣ የሚመለክና የሚመሰገን አምላክ ነው በማለት ተጠናቀቀ
  3. የመጀመሪያው የኤፌሶን ጉባዔ - የተደረገው በ431 ዓ.ም. ነው ፡፡ የንስጥሮስን አመለካከት በማውገዝ ተጠናቀቀ ፡፡ ድንግል ማርያም የወለደችው አምላክ እንደሆነ ተገለጸ ፡፡ የሁለተኛው የኤፌሶን ጉባዔ - የተደረገው በ449 ዓ.ም. ነው ብዙ ተሰብሳቢ ስላልነበረው በአብዛኛው እንደ ጉብዔ አይቆጠርም ፡፡ አውጣኪን በማውገዝ የተጠናቀቀ ነው ፡፡
  4. የኬልቄዶን ጉባዔ - የተደረገው በ451 ዓ.ም. ሲሆን የንስጥሮስ ሃሳብን እንደ አዲስ ለመፈተሽ ስለተፈለገ ነበር ፡፡ ኢየሱስ ከሁለት አካልና ከሁለት ባህርያት የወረሰው አንድ አካልና ሁለት ባህርያት ፣ መለኮትንና ሥጋን ሳይዋሃዱ ፣ ሳይለወጡ ፣ ሳይከፋፈሉ ነው ፡፡ በኢየሱስ ውስጥ የመለኮትና የሥጋ ባህርያት ለየብቻቸው ተነጣጥለው ይገኛሉ ፡፡ ሥጋ የሥጋን ሥራ መለኮትም የመለኮትን በየፊናቸው ይሠራሉ እንጅ አልተጠፋፉም በማለት ስለተወሰነ ፣ ውሳኔውን የማይቀበሉት አባቶች የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በማለት ራሳቸውን ከስብሰባው ውሳኔ ለዩ ፡፡
  5. 5ኛ እና 6ኛው ጉባዔዎች - ሁለተኛው በ553 ዓ.ም. ሦስተኛው በ68ዐ ዓ.ም. የቁስጥንጥንያ ጉባዔዎች ተርገዋል ፡፡ በተለይም በስድስተኛው ጉባዔ የኢየሱስን ባህርይ በተመለከተ ለመጨረሻ ጊዜ ክርስቶስ ሁለት ፈቃድ /የሥጋና የመለኮት/ ሁለት የተለያየ አሠራርና የሥራ ድርሻ እንዳላቸው ተደርጐ ተወሰነ ፡፡ ከሁለት አካልና ሁለት ባህርይ ፣ አንድ አካልና ሁለት ባህርይ ተገኘ ፤ ስለዚህም ሁለቱም የየራሳቸውን ይሠራሉ ፡፡
  6. 7ኛው ጉባዔ - ሁለተኛው የኒቂያ ጉባዔ /787 ዓ.ም./ አስቀድሞ በ754 ተወግዞ የነበረውን በማሻሻል የመንፈሳዊ ስዕላትን ቅዱስነት የሚደነግግ ደንብ ወጣ ፡፡ የዚህን ጉባዔ ውሳኔ ኋላ ላይ የመጡት አንዳንድ የኘሮቴስታንት ቡድኖች አይቀበሉትም
  7. በ1ዐ54 ዓ.ም. በመንፈስ ቅዱስ መገኛ ግንዛቤ ልዩነትን መነሻ ምክንያት በማድረግ ከሮማ ካቶሊክ ኢስተርን ኦርቶዶክስ ነን በማለት ግሪክና ሩስያ ተገነጠሉ
  8. በ1517 ዓ.ም. ደግሞ የሮማ ካቶሊክና ኘሮቴስታንት በቤተ ክርስቲያን የውስጥ አስተዳደር ዋልጌነትን መነሻ ምክንያት በማድረግና የሃይማኖት ግልጋሎቱ ከገንዘብ ጋር መያያዙን በመቃወም ጀርመናዊው የሃይማኖት ሊቅ ማርቲን ሉተር ደጋፊዎቹን ይዞ ተከፈለ
  9. በ1529 ዓ.ም. የሮማ ካቶሊክና የእንግሊዝ /አንገሊካን/ ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ /የሮማውያንን መዳከም ተከትሎ/ በመጠቀም በሃይማኖት ልዩነታቸው ተለያዩ

  የተወገዙት ትምህርቶች አጭር መግለጫ ፡-
  አርዮስ - ኢየሱስ እንደማንኛችንም የእግዚአብሔር ልጅ ሲሆን ፣ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ቃልን ከፈጠረው በኋላ እሱ ደግሞ በተራው ሌሎቹን ፍጥረታት ፈጠረ የሚል ትምህርት በአሌክሳንድርያ ቤተ ክርስቲያን ማስተማር ጀመረ ፡፡ እንደ አርዮስ ግንዛቤ በአብ የተፈጠረ ብቸኛ ፍጡር ወልድ ብቻ ነው ፤ በዚህ ትምህርቱም የኢየሱስ አምላክነትን አጐደለ ፡፡

  ክፍል አራት ይቀጥላል

  ReplyDelete
 9. ሠይፈ ገብርኤልMarch 22, 2012 at 12:38 PM

  የጉባዔ ውሳኔ - ወልድ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ፣ ከእውነተኛ አምላክም የተገኘ እውነተኛ አምላክ ነው ፡፡ ከአብ የተገኘ እንጅ ያልተፈጠረ ፣ እንደ አብ ዘለዓለማዊ የሆነ አምላክ ፣ በባህርዩም ከአብ ጋር የሚተካከል መሆኑን አስረድተው ህግን አወጡ ፡፡

  መቅዶናውያን - - ኢየሱስና አብ ትክክል ፣ እኩል ናቸው ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን በኢየሱስ ስለተፈጠረ /ፍጡር ነው በማለት/ ከአብና ከወልድ ያንሳል /የአብና የወልድ ህላዌን ወይም ባሕርየ መለኮትን/ አይሳተፍም ፡፡ ማለትም በትምህርታቸው መንፈስ ቅዱስ እንደ አብና ወልድ አካል እንዳለውና መለካታዊ ባህርይን እንደሚጋራ አይቀበሉም ፡፡ እንዲያውም ለአብና ለወልድ የበታች አገልጋያቸው እንደሆነ አድርገው ነው የሚረዱት ፡፡

  አፖሊናሪዝም - ኢየሱስ እንደእኛ የሥጋና የነፍስ አንድነት በመሆን ፈንታ በክርስቶስ ሥጋ ላይ የአብ ቃል የነፍስን ሥፍራ ያዘለት ፤ ስለዚህም ኢየሱስ መለኮታዊ ባህርይ ሊኖረው ቻለ ፡፡ ከዚህ በመነሳት ኢየሱስ ሰው ነው ቢባልም በትክክለኛ የሰው መንፈስ የለውም ፣ የሱ መንፈስ የመለኮት ብቻ ነው ፡፡ አፖሊናሪስ ክርስቶስ ሁለት ባህርያት አሉት የሚለውንም አይቀበልም ፣ የክርስቶስ የስጋ ባህርይ ደካማ ስለሆነ ፣ መለኮት ጐልቶ ወጥቷል በማለት የኢየሱስን ፍጹም ሰው መሆን የሚክድ ፣ ኢየሱስን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የሚያደርግ ፣ ለአርዩስና ለመቄዶናውያን እንቅፋት እንዲሆን ብቻ በማሰብ እንደማስተካከያ ያቀረቡት ትምህርት ነበር ፡፡

  የጉባዔው ውሳኔ - መንፈስ ቅዱስንም ደግሞ ህይወት የሚሰጥ ፣ ከአብ የሚወጣና ፣ ከአብና ከወልድ ጋር የሚተካከል ፣ የሚመለክ ፣ የሚቀደስና የሚባረክ አምላክ ነው ፤ ኢየሱስም ቢሆን በተዋህዶ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው በመሆኑ ንጹህና ቅዱስ መስዋዕት ሆኖ ሊቀርብ ቻለ በማለት ተብራርቶ መልስ ተሰጠ ፡፡ በእነዚህ ውሳኔዎች የስላሴ ትምህርትና ትርጉም ግልጽ ስለተደረገና ስለተደገፈ ፣ በአራተኛው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የባዛንታየን ንጉሥ ቴዎዶስዩስ ስላሴን የግዛቱ የእምነት መመሪያ አደረገው

  ንስጥሮስ - የሥጋና የመለኮት ውህደት ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት በድንግል ማህጸን አልተፈጸመም ፡፡ ድንግል ማርያም የወለደችው ከመለኮት ያልተዋሃደውን የኛን የመሰለ ሥጋ ነው በማለት የአምላክ እናት መባሏን አይቀበልም ፡፡ ኢየሱስ ከድንግል ማርያም የተወለደው በሥጋው ብቻ ነው ፣ መለኮት በኋላ መጥቶ ሥጋን ሞላው ስለዚህ ድንግል ማርያም የአምላክ እናት መባል የለባትም ፣ ሥጋ ለቃል ማደሪያ ፣ ተሸካሚ ሆነ ማለት ነው ፡፡ ፍጡርም ፈጣሪውን ሊወልድ አይችልም ፣ ሥጋ መውለድ የሚችለው ሥጋን ነው ፡፡ ንስጥሮሳውያን ኢየሱስ ምንታዌ ባህርይ እንዳለው ቢያውቁም የመለኮትንና የሥጋ ውህደት አያምኑም ፡፡

  የጉባዔ ውሳኔ - ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፣ ፍጹም ሰው ነው ፡፡ ድንግል ማርያም የወለደችው መለኮትና ሥጋ በማህጸን የተዋሃዱትን አምላካችንን ስለሆነ እመ አምላክ መባል ይገባታል ፡፡

  አውጣኪ - የንስጥሮስን መወገዝ ከሰማ በኋላ ያስተካከለ መስሎት ፣ ሥጋና መለኮት ተዋህደዋል ፣ አንድም ሆነዋል ፤ ነገር ግን ከተዋህዶ በኋላ መለኮት ስጋን ስላዳከመው የሥጋ ባህርዩ ጠፍቷል ፤ ስለዚህም ኢየሱስ እንደ እኛ ዓይነት ሰው ነው ሊባል አይገባም ፡፡ ይኸን ገለጻው ኢየሱስ በደልን ላለመፈጸሙም እንደ ምክንያት አድርጐ ያቀርበዋል ፡፡

  የጉባዔው ውሳኔ - ሥጋና መለኮት ተዋህደዋል እንጅ አልተጠፋፉም

  መደምደሚያ፡-
  እኔ ያለዕውቀት ቢሆንም ይህን ያህል ተጉዣለሁ ፤ በድረ ገጽ ለማቅረብ ስልም አብዛኛውን ታሪክ በቻልኩ አሳጥሬዋለሁ፡፡ ጥበቡ ሙያው የሆነላችሁና ችሎታው ያላችሁ ፣ እግዚአብሔርም የገለጠላችሁ ወንድሞችና እህቶች ደግሞ ፣ ምእመን የተሻለውን መረጃ እንዲያገኝ ማቃናት ፣ ማፍታታትና ማስተማር ይጠበቅባችኋል ፡፡ ለአንድ ምእመን በነዚህ በተሰመሩ ደንቦች ውስጥ ያለስህተት መራመድ እስከምንለማመድ ድረስ ግድፈትን መፈጸማችን አሁንም ፣ ወደፊትም ቢሆን አይቀርም ፤ ከማስተማር ያለፈ በመሃላችን የሊቅነት ነገር አይወሳ ፡፡ ከመተቸት ማስተማር ቢቀድምልን እንገነባበታለን ፡፡

  አመሰግናለሁ

  ReplyDelete
  Replies
  1. 10 Q ሠይፈ ገብርኤል!!!!!!!!!!!

   Delete
  2. Thank u ሠይፈ ገብርኤል!!!

   Delete
 10. ሥላሴ የግእዝ ቃል ነው፡፡ ሦስትነት፣ ሦስትዮሽ፣ ሦስት መሆን ማለት ሲሆን በተጨማሪም በሦስትነት ጸንተውና ታውቀው ለኖሩት ለሥላሴ (ለአብ፣ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ) የሦስትነት መለያና መታወቂያ የሆነ አኀዛዊ (በአኀዝ ላይ የተመሰረተ) ስም ነው፡፡ የመለኮት አሐድነት ያለው እግዚአብሔር በሦስት አካላዊ አቀሞችና (ህላዌያትና) ሦስት ኩነታት ራሱን የገለጸ ስለ ሆነ የእግዚብሔር አካላዊ አቀሞችና ኩነታቱ ከሦስት ያልበለጡና ያልጎደሉ ፍጹም ሦስት መሆናቸው ስም ሊሆን በሚችል በሚታወቅ አኀዝ ‹‹ሥላሴ›› ተብሎ መነገሩ አግባብነት አለው፡፡ አብ፣ወልድና መንፈስ ቅዱስ በአካላት ሦስት ቢሆኑም በባሕርይ (በመለኮት) አንድ በመሆናቸው ሦስቱም ከዚሁ ከአንዱ ባሕርይ (መለኮት) ናቸውና በጊዜ መቀዳደምና በክብር መበላለጥ በሥላሴ ዘንድ የለም፡፡ መናፍቃን ‹‹ከእኔ አብ ይበልጣል›› የሚለውን ወልድ የተፈጠረውን የሰውን ባሕርይ ገንዘብ ካደረገ በኋላ የተናገረውን ሰው ከመሆኑ በፊት በባሕርየ መለኮት ብቻ በነበረበት ጊዜ እንደተናገረው አስመስለው ይጠቅሱታል፡፡ ሰው ከሆነ በኋላማ ሰውን ለማዳን ሲል ራሱን ባዶ አድርጎ በፈቃዱ በእግዚአብሔርነት መኖርን ትቶ ከመላእክት በሚያሳንሰው ውርደት ህማም ሞት በኩል እንኳ አልፎአልና ይህን ልብ ሊሉት በተገባ ነበር፡፡
  አብ፣ወልድና መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዳቸው እኔ፣አንተ፣እርሱ በሚያሰኝ ሦስት ምልአተ አካላዊ አቌም እያሉ አንድ አምላክ ሲሆኑ የተለያየ መንግሥት ሐሳብ ፈቃድና ሥልጣን ላይኖራቸው የቻለበት ምስጢር ከአንድ ከማይከፋፈለው ባሕርይ (መለኮት) መሆናቸው ነው፡፡ አትናቴዎስ ይህን እንዲህ ያብራራዋል፡፡ መለኮት እንደ አካላት በሦስት የማይከፈል አንድ ብቻ ሲሆን ሥላሴ ግን በአካላት ፍጹምነት ያላቸው ሦስት ናቸው፡፡ እንግዲያውስ ሦስቱ አካላት በክብር በደረጃ በሥልጣን አንድ የሆኑበት አንድ መለኮት ብቻ አለ፡፡ ሥላሴ በመለኮት በባሕርይ አንድ ናቸው ተብሎ ሊነገር ይገባል እንጂ ለአካላት የሚነገረውን መመሳሰልና መተካከል ለባሕርይ በመስጠት በባሕርይ ይተካከላሉ ይመሳሰላሉ አይባልም፡፡
  መለኮት (ባሕርይ) ሦስቱን አካላት በአንድ አምላክ መሆን ያዋሐደ ነውና በነጠላ ቁጥር ‹‹አንድ›› ተብሎ ይገለጻል፡፡ ሥላሴ ባሕርያቸው ለሆነው ለአንዱ መለኮት በተዋህዶ (በአንድነት) እኩል ባለቤቶች ናቸው፡፡ ሊከፈል ሊከፋፈል ከማይቻለው ከባሕርየ መለኮት የሚበልጥም ሆነ የሚያንስ ድርሻ ለማንም የለውም፡፡ ስለሆነም አብም ወልድም መንፈስ ቅዱስም አንድ በሚያደርጋቸው በዚሁ በአንዱ መለኮት በእኩልነት ሲጠሩ ‹‹አብ መለኮት፣ ወልድ መለኮት፣ መንፈስ ቅዱስ መለኮት›› ይባላሉ፡፡ መለኮት መከፋፈል ሳይደርስበት ሦስቱም ይጠሩበታል፣ ይመሰገኑበታል፡፡
  እንግዲያውስ እግዚአብሔር በአካላት ሦስት በመለኮት አንድ ነውና እኛ ኦርቶዶክሳውያን ‹‹ወልድ ሰው የሆነው በተለየ አካሉ ነው›› እንላለን እንጂ ‹‹በባሕርዩ ሰው ሆነ›› አንልም፡፡ ወልድ በባህርዩ ሰው ሆናል ካልን የአብም የወልድም የመንፈስ ቅዱስም መለኮታዊ ባሕርይ ያው አንድ ነውና ወልድ የተለየ አካል እንጂ የተለየ ባህርይ ስለ ሌለው ያንኑ አንዱን ባህርይ መለኮት ከሰው ባህርይ ጋር አዋሐደው ከዚህም የተነሳ አብና መንፈስ ቅዱስም በባህርያቸው ሰው ሆኑ ማለትን ስለሚያስከትል ወይም አብና መንፈስ ቅዱስ ያለ ባህርይ መለኮት በአካል ብቻ ቀሩ ያሰኛል፡፡
  ዩሐንስ አፈ ወርቅም ለዕብራዊያን ከተጻፈው መልእክቱ ምዕራፍ አንድ ቁጥር አራትን ሲተረጉም ‹‹ወልድ ከመላእክት የሚበልጥ ስምን ወረሰ›› መባሉ ከአብ ጋር አንድ የሆነበትን የተለየ አካሉን ብቻ ያመለክታል ባህርየ መለኮቱ ሰው አልሆነምና፡፡ በክበበ ሥላሴ የተለየ አካል ያለው ከአብና ከመንፈስ ቅዱስም ጋር አንድ የሚሆንበት መለኮታዊ ባሕርይ ያለው ወልድ በአንድ ሙሉ ህላዌ (አካላዊ አቌም) ይታወቃል፡፡ የራሱ የሆነ ህላዌ አለው፡፡ በኋላም መንፈስ ነፍስና ሥጋ የሆነውን ፍጹም ሰብእነትን ሲዋሐድ ሁለት ህላዌያት ያሉትን መለኮቱንና ትስብእቱን አገናዝቦ በእንድ ህላዌ አቌም ተገለጠ፡፡ አንድን ማንነት ገንዘብ አደረገ፡፡ ‹‹ህላዌ›› ባሕርይ ማለት አይደለም፡፡ ሰው የሆነው ወልድ ‹‹እኔ ራሴ›› የሚልበትን የራሱን ሙሉ ማንነቱን ለመግለጽ የገባ ቃል ነው፡፡ እኔ ራሴ በሚልበት በራሱ ሙሉ ማንነት ብቻ ኀጢአትን አነጻ ማለት ነው፡፡
  ክርስቶስ ለሕዝቡ በደሙ ያስገኘው ተስፋ የዘለዓለም ሕይወት ሲሆን ምልክቱና ማህተሙ ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡ ሰዎች የዚህ ቃል ኪዳን ተካፋዮች እንዲሆኑ ንስሐ መግባትና ማመን አለባቸው፡፡ ንስሐ የመግባታቸውና የማመናቸው ምልክትና ማኀተምም ጥምቀት ነው፡፡
  በመጽሐፍ ቅዱስም ሰዎች በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲጠመቁ ታዝዛEል፡፡ በሥላሴ ስም የጥምቀት ሥርዓት እንዲፈጸም ከተደነገገ ለምን ሐዋርያት በክርስቶስ ኢየሱስ ስም ሰዎች እንዲጠመቁ አዘዙ; ለዚህ ብዙ መልስ ማግኘት ይቻላል፡፡ የክርስቶስ ትእዛዝ ድንጋጌ ሲሆን የሐዋርያት ሥራ ግን የሐዋርያትን ቃል በሙሉ ሳሆን በዐጭሩ የሚገልጥ መጽሀፍ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ሐዋርያት ስለ ጥምቀት ሲናገሩ የኃጢአት ይቅርታ በደሙ ባስገኘላቸው በክርስቶስ ላይ አተኮሩ ማለት ይቻላል፡፡ በሥጋ የሞተላቸው ወልድ እንጂ አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ አልነበረም፡፡ በሥላሴ ስም እንዲጠመቁና ከሦስቱ አካላት ጋር ኀብረት እንዲኖራቸው ያደረገው የወልድ መሥዋዕት መሆን ነው፡፡ በዚህ መሰረትም ወልድ ወደ አብ ያቀርባልና በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቀናል ዮሐ 14፡6፣ 7፡37-39፣ 16፡7

  ReplyDelete
 11. ለአብዛኛው የኦርቶዶክስ አማኝ የክርስቶስ አዳኝነት ሌላ የክርስቶስ መካከለኛነት ደግሞ ሌላ ይመስላቸዋል፡፡ እንደዚሁም አዳኝነቱና መካከለኛነቱ አንድ ጊዜ ተፈጽሞ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ እየሰራ የሚቀጥል አገልግሎቱ መሆኑን ለመቀበል ይቸገራሉና ያለፈ ድርጊት ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ ለዚህም ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡ የመጀመሪያው ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም መካከለኛ ከተባለ ከአምላክነቱ ደረጃ ዝቅ ይላል የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ክርስቶስ ዛሬም መካከለኛ ነው ከተባለ በልዩ ልዩ መንገድ በእርሱ ስፍራ መካከለኛ አድርገው ያቆማEቸው ‹‹መካከለኞች›› ተግባረ ፈት ይሆናሉና ያንቀላፉ ቅዱሳንንና መላእክትን ምን እናደርጋቸዋለን የሚል ይመስላል፡፡ አነዚህን ክፍተቶች መሙላት ስለሚቸግራቸውም ክርስቶስ ዛሬም አዳኝ ነው መካከለኛም ነው የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ይቃወማሉ፡፡ ስለ ክርሰቶስ አዳኝነት ስንናገር አዳኝነቱ ስለ ተከናወነበት መካከለኛነቱ መናገራችን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን ‹‹የአዲስ ኪዳን መካከለኛ›› ይለዋል፡፡ (ዕብ. 12፡24) አዲስ ኪዳን በክርስቶስ ደም የተመሰረተና እርሱ ዳግመኛ እስኪመጣ ድረስ አንድ ጊዜ በተከናወነው ቤዛነት የሚያምኑ ሁሉ መዳንን የሚቀበሉበት በኀጢአት ቢወድቅ የሚነሱበት ኪዳን ነው፡፡ የዚህ ኪዳን ብቸኛው መካከለኛ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
  ብዙዎች አንድ ጊዜ የተፈጸመውን የክርስቶስን የማዳንና የማስታረቅ ሥራ ያምናሉ፡፡ በተግባር ግን ያ አንድ ጊዜ የተፈጸመው ለዘላለም የሚያድንና የሚያስታርቅ መሆኑን ከፍ ብለው በተገለጹት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ አይቀበሉም፡፡ እንዲያውም ያስተባብላሉ፡፡
  ኢየሱስ አሁን ፈራጅ እንጂ አማላጅ አይደለም - ጊዜውን በትክክል መጥቀስ ባይቻልም ይህ አመለካከት የክርስቶስን የመካከለኛነት ስፍራ ለቅዱሳን መላእክትና ላንቀላፉ ቅዱሳን ሰዎች መስጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ እየተስፋፋ የመጣ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት እንደ ሆነ መገመት አያስቸግርም፡፡ የአመለካከቱ አቀንቃኞች ለኢየሱስ አምላክነት በመቅናት ትስብእቱን (ሰው መሆኑን) በንግግር ያመኑት መስለው በተግባር ግን ይክዱታል፡፡ ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጅ እንጂ መካከለኛ አስታራቂ አማላጅ ጠበቃ … ከተባለ እርሱን ዝቅ ማድረግ ይሆናል ይላሉ፡፡ በርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ራሱን ዝቅ አድርጎል፡፡ ‹‹ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው ይኸውም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ጉልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው፡፡››
  አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ ሳይሆን እጅግ ከፍ ብሎ ነው ያለው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ በፈጸመው የማዳን ሥራ አምነው በእርሱ በኩል የሚመጡትን ሁሉ የሚያስታርቃቸውና የሚያድናቸው እርሱ ብቻ ነው (ዕብ. 7፡25) ምክንያቱም ስለ ኀጢአታችን ያቀረበው መሥዋዕት አንድ፣ ፍጹም የማይደጋገምና ዘላለማዊ ነው (ዕብ 10፡12-18) ይህም ማለት ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው እስከ መስቀል ሞት ድረስ እንደ ነበረው ዓይነት እየወደቀ እየተነሳ ይለምናል ይማልዳል ማለት አይደለም፡፡ በእርሱ አዳኝነት በኩል አምነው ለሚመጡት በቀደመው ልመናውና መሥዎዕቱ ይታይላቸዋል በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል ማለት ነው (ዮሐ. 16፡23-24፣ ዕብ 5፡ 7-10፣ 9፡24-28)፡፡ ለአንድ በሽታ ፈዋሽ መድሀኒት ስለ ተገኘና መድኀኒቱ በየፋርማሲው ስለሚሸጥ በሽታው ጠፍተEል በበሽታው የተያዙ ሰዎችም ድነዋል መላት አይደለም፡፡ ለመዳን በሽተኞቹ መድኀኒቱን መውሰድና በተገቢው መንገድ መጠቀም አለባቸው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ መድኀኔ ዓለም ክርስቶስ ስለ ተሰቀለና በሞቱ የኀጢአትን ዕዳ ስለ ከፈለ ወይም ለኀጢአት ሁሉ የሚበቃ መሥዋዕትን (ራሱን) ስላቀረበ ሰዎች ሁሉ ድነዋል ማለት አይደለም፡፡ ሰዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጸመውን የማዳን ሥራ ለእነርሱ እንደ ተከናወነ በማመን በኢየሱስ መካከለኛነት በኩል መቅረብ በእርሱ ስራም ድኀነትን እንዳገኙ ማመን አለባቸው፡፡ በክርስቶስ ሥራ ሲያምኑ የዘላለምን ሕይወት ያገኙ ክርስቲያኖች ወዲያው ፍጹም አይሆኑምና ኀጢአት መሥራታቸው አይቀርም፡፡ ስለሚሰሩት ኀጢአት ግን ያው አንድ ጊዜ በቀረበው የክርስቶስ መሥዋዕትነት በኩል ስርየትን ያገኛሉ እንጂ ሌላ መሥዎዕት አይቀርብላቸውም (ዕብ 7፡27፣ 9፡25-26፣ 10፡18-26) አንድ ጊዜ ለዘላለም የቀረበው መሥዋዕት (የክርስቶስ ሞት) ፍጹምና ለኀጢአት ሁሉ የሚበቃ በመሆኑ ይህን ኀጢአታቸውንም ይሰርያል (ሮሜ 3፡25፣ 1ዮሐ. 1፡ 7-9፣ 2፡2)
  መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን ፈራጅ ነው የሚሉት ወገኖች ተሳስተዋል የሚባሉት ኢየሱስ ፈራጅ ነው በማለታቸው አይደለም በአዳኝነቱ ዘምን እርሱን ፈራጅ ብለው በመሰየማቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ዓለምን እንዲያድን የላከውን መድሀኒታችንን ኢየሱስን በዓለም ፍጻሜ ደግሞ ፈራጅ አድርጎ ሾሞታል፡፡ ሐዋርያቶች ፈራጅነቱን የጠቀሱት ወደ ፊት በዳግም ምጽአቱ ከሚሆነው ፍርድ ጋር አያይዘው ነው፡፡ ወደ ፊት ሊፈርድ የተዘጋጀው እርሱ ስለ ሆነ ከሚመጣው ፍርድ ለማምለጥ ዛሬ በአዳኝነቱ እመኑ የሚል ነበር መልዕክታቸው፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ሠይፈ ገብርኤልMarch 23, 2012 at 8:47 AM

   ስለተሰጠው ትልቅ ትምህርት አመሰግናለሁ ፡፡

   ወንድሜ ከላይ የገለጽኩትን አቋም ያሳወቅኩት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው በመነሳት እንጅ በበኩሌ ሌላ አማላጅን ለመደንቀር ፈልጌ አይደለም /ከሞት ዕዳ ነጻ ያወጣን እሱ ብቻ ሰለሆነ/፡፡
   ለመንደርደሪያ ይሆን ዘንድ አንድ ሁለት ጥያቄ ለአእምሮአችን እናቅርብ ፡፡
   ኢየሱስ አስታረቀን የምንለው ስለምንድር ነው ? ሰዎች ወደ አምላካቸው በራሳቸው ትግል ወደ ጥንት ጸጋ ክብራቸው ሊመለሱ ያልቻሉበት ምክንያት ምንድር ነው ?

   ነገር ግን እነዚህ ከላይ በመነሻ የተቀመጡ ጥያቄዎችን ስናስባቸው መልሱ በተሻለ ግልጽ የሚሆን ይመስለኛል ፡፡ እርቅ ያስፈለገበት ምክንያት አዳም በአምላክ የተሰጠውን ትእዛዝ በመተላለፍ ፈጣሪውን በመበደሉና ዘለዓለማዊ ሞት ስለመጣ ብቻ ነው ፡፡ ብዙ ጻድቃን ፣ ብዙ ነቢያት ተነሱ ፤ ምግባራቸውን አስተካከለው ጻድቅ ተባሉበት ፣ ሞገስን ተቀበሉበት እንጅ ያን በደል ደምስሰው እርቅ ሊፈጥሩ ፣ ዘለዓለማዊ ሞትንም ሊያስታግሱ አልቻሉም ፡፡ ሌላውም የሰው መንገድ በሙሉ /ከአምላክ ፈቃድና ፍላጐት ውጭ ልጅ እስከ መሰዋት የደረሱበት/ ምንም መፍትሄ ስላላስገኘ የሚወደን አምላካችን ራሱን ከስጋ አዋህዶ ሞትን በሞት ድል ለማድረግና እኛን ለማዳን ወደ እዚህ ዓለም መጣ ፡፡

   ይህም ማለት ሊያድነን ያስፈለገው የአዳም በደል ካመጣው ዘለዓለማዊ የሞት ፍርድ እንጅ ከሌላው ድክመትና ኃጢአት አይደለም ፡፡ ከሌላው ስንፍናና ድክመት ሰዎች /ሄኖክ ፣ ኤልያስ …/ በጽናት ቆመው በራሳቸው የአምልኮ ትግል ቅድስናን አግኝተውታልና ፡፡ ስለዚህም ምክንያት ራሱን መስዋዕት በማድረግ ማንም ሊሽረው ያልቻለውን ፍርድ በመስቀል ላይ ነፍሱን ሰጥቶ ዕርቅን ፈጸመልን ብለን እንመሰክራለን ፡፡ ያ ዕርቅ ከተፈጸመ ፣ ካሳውም ከተከፈለ በኋላ ፣ የሰው ልጅ ወደ ጥንት ክብሩ የመመለሱ ነገር ተረጋግጧልና ሌላ ሥራ ቀርቶታል ማለት ያስቸግረኛል ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም እርስ በርሱ ይጣላል ወይም ይጋጫል የሚል ቋንቋን ካልተናገርን በስተቀር ሐዋርያው

   2 ቆሮ 5 ፡16-20 ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።
   ሐዋርያው በዚህ ባስተላለፈው ቃል ሁሉም የማዳንና የማስታረቅ ሥራ ተከናውኖ እንዳበቃ የሚያስረዳ ነውና ፣ የተለየ አተረጓጐም ካለህ አስነብበኝ
   አመሰግናለሁ

   Delete
  2. Surprising, from what time protestants started to say "ande yekerebew meswaet lezelalem beki new" I think they copied from Orthodox church. My neighbourhood who is pente didn't believe like this. He believe even today Jesus prays for his sin. Other pentes also say like that.

   I think these persons are originated from Orthodox church & trying to correct the misconception of protestants.

   Ohh seife Gebriel I like u in all of the times. u r really equipped with the Orthodox church teachings.

   Delete
  3. እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልእክተኞች ነን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናል (2ቆሮ. 5፡20)
   ይህ ጥቅስ ስላንቀላፉ ቅዱሳን አማላጅነት ይናገራል ተብሎ በብዙዎች ዘንድ እንደ ማስረጃ የተወሰደው ጥቅሱ ይህን ሀሳብ ስለሚደግፍ አይደለም፡፡ ነገር ግን እንደሚማልድ በሚለው ቃል ውስጥ ‹‹ል›› ከሌሎቹ ፊደላት ደመቅ ብላ ስለ ተጻፈች በመጀመሪያ ‹‹ለ›› የነበረውን ደልዘው ‹‹ል›› አድርገውት ነው በሚል አስተሳሰብ ነው፡፡‹‹ለ›› ቢሆን ኖሮ ጥቅሱ ‹‹…..እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ….››የሚል ፍቺ ይሰጥ ነበር፡፡ ይህም እግዚአብሔር በቅዱሳን እንደሚለመን ያሳያል፡፡ ‹‹ለ›› ወደ ‹‹ል›› ስትለወጥ ግን የቅዱሳንን ማማለድ ያስቀራል የሚል ነው ክርክሩ፡፡

   ….እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ…ቢባል ስሕተቱ ከምን ላይ ነው; ስሕተቱን ለመረዳት በቅድሚያ ዐውዱ ስለ ምን እንደሚናገር መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ከቁጥር 18 ጀምሮ ያለውን ስንመለከት እግዚአብሔር በክርሰቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ እንደ ነበረና በሐዋርያቱ ውስጥም የማስታረቅን ቃል እንዳኖረ ይናገራል፡፡ በዚሁ የማስታረቅ ቃል አማካይነት ሐዋርያት ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ የሚገባቸውን ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለው እንደሚለምኑአቸው በክፍሉ ውስጥ እናነባለን፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ በክርስቶስ አማካይነት ዓለሙን ከራሱ ጋር እንዳስታረቀና በእርሱ የተከናወነውን እርቅ ያልሰሙና ያልተቀበሉ ሰዎችን ደግሞ የማስታረቁን ቃል(ወንጌልን) በውስጣቸው ባስቀመጠው አገልጋዮች በኩል ዛሬም እየጠራቸው እንደ ሆነ ነው የምንረዳው፡፡ ‹‹ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን›› ከሚለው አነጋገርም የምናስተውለው እነርሱ ወደ እግዚአብሔር መለመናቸውን ሳይሆን ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ወደሚፈጽሙት ዕርቅ መጋበዛቸውን ነው፡፡ የ2ሺሁ ዕትም መጽሐፍ ቅዱስም ‹‹ከእግዚአብሔር ጋር ትታረቁ ዘንድ በክርስቶስ እንለምናችኀለን›› ነው የሚለው፡፡ የክፍሉ መልእክት ይህ ሲሆን ‹‹እንደሚማልድ››የሚለው ቃል ‹‹እንደሚማለድ›› በሚለው ቢተካ ግን ትርጉም ያጣል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ክፍል የጌታ አገልጋዮች ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ስለ ማለታቸው እንጂ ጌታን ስለ መማለዳቸው አልተናገረም፡፡

   Delete
  4. ሠይፈ ገብርኤልMarch 24, 2012 at 2:48 PM

   ይህ ጽሁፍ የተወሰደው ከ1611 በኪንግ ጀምስ ስም በእንግሊዝኛ ከተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ በካልአይ ቆሮንቶስ መልዕክቱ ምዕራፍ አምስት ላይ ከሚናገረው ነው ፡፡ ከቁጥር 16 ይጀምራል
   "16 Wherefore henceforth know we no man after the flesh: yea, though we have known Christ after the flesh, yet now henceforth know we him no more.
   17 Therefore if any man be in Christ, he is a new creature: old things are passed away; behold, all things are become new.
   18 And all things are of God, who hath reconciled us to himself by Jesus Christ, and hath given to us the ministry of reconciliation;
   19 To wit, that God was in Christ, reconciling the world unto himself, not imputing their trespasses unto them; and hath committed unto us the word of reconciliation.
   20 Now then we are ambassadors for Christ, as though God did beseech you by us: we pray you in Christ's stead, be ye reconciled to God.
   21 For he hath made him to be sin for us, who knew no sin; that we might be made the righteousness of God in him."

   ተቀራራቢ አጭር ትርጉሜ ፡- ኢየሱስ የሰው ልጆችን ከእግዚአብሔር በስጋውና በደሙ አስታርቆ ወደ መጣበት ተመለሰ ፡፡ አሁን ደግሞ የክርስቶስ አምባሳደሮች /ተወካዮች/ እኛ በመሆናችን ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ እንላለን ይላል ፡፡

   አንድ ሌላ ነገርም ልበለ ፤ አንተ ወገኔ ብዙ የመጽሐፍ እውቀት እንዳለህ እገነዘባለሁ ፡፡ ይጠፋሃል ብዬ ባልገምትም በዚህች በደንቆሮ አንደበቴ ሳልመክር ማለፍ የማልሻው ፣ “ወደዚህ ወደእኛ ዘመን ቀረብ ብለው የሚጻፉትን መጽሐፍት ከቀደምት መጽሐፍት ጋር አለመፋለሳቸውን እያስተያየህ እንድትመለከታቸው ነው” ፡፡ ምክንያቱም አሁን በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝኛውም የሚጻፉትን ቅዱሳት መጻሕፍት ቢሆን ፣ ዘመነኛው ሲያነብ እንዳይቸገር በማለት ብዙ የቃላት ለውጥ ተደርጐባቸዋል ፡፡ ይኸ የተያዘው ለውጥ ደግሞ ትርጉም በማስቀየሩ ምክንያት ሃይማኖትም ተረት ይመስል በድሮ ጊዜ ወይም ድሮ እንዲህ ይባል ነበር ወደመባል የሚያዘግም ይመስላልና ጥንቃቄ አድርግ በማለት ለማስታወስ ነው ፡፡

   በተረፈ ለእኔ ድንቅ መምህር ነህ ፡፡ በብዙ ቦታ ከሌሎች የማልስማማባቸውንና መግለጽ ያላወቅሁባቸውን ጉዳዮች አንተ በዕውቀትህ ውብ አድርገህ በማቅረብህ ፣ የሚያነቡ ወገኖች ሁሉ ትምህርት የሚያገኙበት ይመስለኛል ፡፡

   አክብረህ ጥያቄዎቼንና ሃሳቤን ስላንሸራሸርክልኝ አመሰግናለሁ ፡፡

   Delete
 12. Zemedkun betam kame tetkame yakam telkem yemel now , but its ok majority mk eating chat and smoking crak. We ready and finished all preparation to clean our church from devil mk which now we will take all action yemegemera shermuta papas no way to serv mk devil and eotc no more safe any where if they support terrsist mk. Long live for pauos

  ReplyDelete
  Replies
  1. You writer are you human being or Lucifer himself? I doubt your identity from your comment that you are not a normal human being. Why are you insulting our fathers like this? Why are you become the son of devil? Why don't you think about your soul's home in the future life? Who thought you that by insulting human beings one can get heaven? I am really sorry for your soul. Bible Yeminegiren Awurewuna meselochu bekidusanu lay afachewun endemikefitu new. Are you the son/follower of the "Awure"? Please Nisiha Giba geta Yikir lileh Yanten memeles bicha yitebikal. embi kalikem mirichahin yitebikilihal. Bye!!!!

   Delete
 13. ክርስቲያኖች - ኢየሱስ ክርስቶስን አማላጅም አልነው ፈራጅ ካለርሱ በስተቀር የሚያድነን በፍጹም የለም፡፡ ሁለቱ ቃላት ከሚያጣሉን ኢየሱስ አዳኝ ነው የሚለው ያስማማን ይሆን?

  ReplyDelete
  Replies
  1. ሠይፈ ገብርኤልMarch 24, 2012 at 2:51 PM

   አማላጅ የሚለው ቃል ነው እንጅ አሁን ለሚገኝበት ክብሩ አይገባም የተባለ ማዳኑማ የጋራ ቋንቋ ነው ፡፡

   Delete