Monday, May 14, 2012

ቤተክርስቲያናችን ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በቅድሚያ ቅዱስ ሲኖዶስ በ1991 ዓ.ም ያወጣውን ህግ ማሻሻል እንዳለበት ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ዘገበ

ከጥቂት አመታት ወዲህ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ በርካታ ችግሮች እየተከሰቱ መሆናቸውን በየጊዜው ከሚዳያዎች እያስተዋልን ነው። የአንዲት ቤተክርስቲያን አባቶችና ልጆች ጎራ ለይተው እየተወዛገቡና አንዱ ሌላውን እየወነጀለ ይገኛል። በዚህ መካከል እየተጎዳ ያለው ምእመኑና አገልጋዩ ነው። በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል በስብሰባ ላይ እየተፈጠረ ያለው አለመግባባትና ክፍፍል ምንጩ ምንድን ነው? የሚለው ብዙ እያነጋገረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደጵጵስና የመጡ አባቶች ማንነት፣ እንዲህ እንዲሆኑ ነጻነት የሰጣቸው ህግና ከማህበረ ቅዱሳን ጋር በተሳሳተ መንገድ የፈጠሩት «የእከክልኝ ልከክልህ» ግንኙነት ራሳቸውን ትልቅ ትዝብት ውስጥ የጣላቸው ሲሆን፣ ማኅበሩ አፍኜ እይዘዋለሁ ያለውና በሌላ በኩል እየተነፈሰው ውስጥ ለውስጥ ይፋ ያደረገው ብዙ ገበናቸው ቤተክርስቲያኒቱን ስም እያጎደፈና ለብዙዎች መሳለቂያ እያደረጋት መሆኑን የዜና ቤተክርስቲያን ዘገባ ያመለክታል።«ቤተክርስቲያንንና መንጋዎቿን ከወቅታዊ አደጋ ለመታደግ ከግንቦቱ ሲኖዶስ የሚጠበቅ የህልውና ውሳኔ» በሚል ርእስ ጋዜጣው ባሰፈረው ወቅታዊ ጽሑፍ ቤተክርስቲያኒቷ ህልውናዋ በብዙ መንገድ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል። የችግሩ ዋና ምንጮችም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መሆናቸውን ያተተው ጽሁፉ፣ ከመነሻው በአሿሿማቸው ውስጥ የምእመናን ተሳትፎ አለመኖሩ፣ በሁሉም አቅጣጫ ለጵጵስና ብቃት ያላቸውና በሰው ፊትም የተመሰከረላቸው እንዲሆኑ የሚያደርግ አንቀጽ አለመካተቱ የችግሩ መንስኤ ነው። በርእሰ አንቀጹ ላይም ጋዜጣው «… በጳጳሳት ምርጫ ጊዜ የካህናትና የምእመናን ተሳትፎ የለም፤ እንደ ስምኦን ቀሬናዊ ቆሞሳቱን ከመንገድ እየጎተቱ ለጵጵስና የሚመርጧቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ናቸው።» ብሏል። ይህ ትክክለኛ ምስክርነት ነው። አንዳንዶቹ ጵጵስና የተሾሙት ለቦታው ስለሚመጥኑ፣ ጥሩ የሕይወት ምስክርነት ስላላቸው፣ በትምህርት በኩልም ለሹመቱ የሚያበቃ ትምህርት የተማሩ ስለሆኑ አይደለም። አንዳንዶቹን እንደብፁዕ አቡነ መርሐጽድቅ ያሉት አባቶች «ይህንንስ ጳጳስ ከምናደርገው ብንድረው አይሻልም ወይ?» ሲሉ እንደቀልድ የተወሰደ ግን በኋላ ላይ እውነተኛ ሆኖ የተገኘ አስተያየት ሰጥተው ነበር። ግን ማን ሰምቶ? ይኸው አሁን እንደእነዚህ ያሉት ቤተክርስቲያንን የሚያውኩ ሆነዋል። እንደእነዚህ ያሉትን ሰዎች በጵጵስና መሾም ተመልሶ ራስ ምታት የሆነው ለቤተክርስቲያኒቱ ነው። በዘመናቸው ብዙ ክፍተቶች ያሉትንና የቀደሙትን ሕጎች የተኩትን እነዚህን ህጎች እንዲወጡ የፈቀዱትን ፓትርያርክ ጳውሎስንም ብዙ ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሆነ ይታያል።
ዜና ቤተክርስቲያን ከጠቃቀሳቸው የህጉ ክፍተቶች መካከል የእድሜና የትምህርት ጉዳይ ይገኝበታል። ፍትሕ መንፈሳዊ ለጵጵስና የሚሾመው ሰው እድሜ 50 መሆን እንዳለበት ቢደነግግም፣ የ1991ዱ ህግ ግን ከ45-60 በሚል ደንግጓል። እንደዜና ቤተክርስቲያን ትዝብት ይህ የእድሜ መስፈርት «… የተወሰኑ ሰዎችን ለማስመረጥ ተብሎ የተከናወነ አካሄድ…» እንደሆነ ያመለክታል ይላል። በልካቸው የተሰፋ አንቀጽ መሆኑ ነው። በቀደመው ዘመን ተለምነውና እንቢ ብለው በስንት ትግል ለቦታው የሚመጥኑ አባቶች የሚገቡበትን ጵጵስና፣ እንኳን ለጵጵስና ለሌላም ለማይታሰቡ አንዳንድ «ከወጣትነት ሰፈር በቅርቡ ለወጡት» ማእረጉን ማሸከሙ ቤተክርስቲያንን በእጅጉ ጎድቷታል። ያ ይታፈርና ይከበር የነበረው የጵጵስና ሞገስ በወጣቶቹ «ጳጳሳት» ላይ ፈስሶ አይታይም። እንዲያውም በአንዳንድ ክብረ በኣላትና አጋጣሚዎች ላይ የአንዳንዶቹ ጳጳሳት ያልተሰበረ እይታና አይነውሃቸው እስኪያሳብቅ ድረስ በአንዳንድ ሴቶች ላይ አይናቸው ሲንከባለል ማየት እንዴት ኣሳፈሪ ነው! አንዳንዶቹ ደግሞ ይህን ለመደበቅ ጳጳስ መሆናቸውን ረስተው ሌላ ተልእኮ እንዳለውና ራሱን መሰወር እንደፈለገ ሰው ጥቁር መነጽር አድርገው ይታያሉ።
እነዚህ ጳጳሳት ከትምህርት አንጻርም ብቁ አለመሆናቸውን ጋዜጣው የሚከተለውን አስፍሯል «ብሉያትን ሐዲሳትን ያልተማረ ይልቁንም ዐራቱን ወንጌል ያልተረጎመ አይሾም (ፍ.መ. 5፡11) የሚለው ቀርቶ ‘በነገረ መለኮት በቂ ችሎታ ያለው’ በሚል ሾላ በድፍን አይነት ህግ መቀየሩለነገዪቱ ቤተክርስቲያን የሚበጅ አይደለም» በአንድ በኩል የአብነት ትምህርት ቤት እየተዳከመ ነው ምን ይበጃል? እየተባለ በተለያየ አጋጣሚ ሲነገር እንሰማለን። በሌላ በኩል ቤተክርስቲያን ወደሹመት የምታመጣቸው ብዙዎቹ ትምህርት ጠል የሆኑ መነኮሳት ናቸው። የእነርሱም ሩጫ እንደአንዳንዶቹ ከወጣትነት በቅርቡ የወጡ ጳጳሳት፣ ጳጳስ ሆኖ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ያለመጠየቅና ያለመከሰስ መብትን ለማረጋገጥ ነው። ታዲያ ነገሩ እንዲህ ከሆነና ምንኩስና ብሎም ጵጵስና በብቃትና በተገቢነት የሚገኝ ሳይሆን በአቋራጭ የሚደረስበት ማእረግ ከሆነ መማር ለምን ያስፈልጋል? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው። ስለዚህ ቤተክርስቲያን ወደጵጵስና በምታመጣቸው አባቶች ላይ መስፈርቶቿን ጠበቅ ማድረግ አለባት። ለታይታ በሚደረግ አንዳንድ እንቅስቃሴ ብቻ ብቁ ያልሆነውን መነኩሴ እንደ ቀሬናዊው ስምኦን ከመንገድ እየጠለፉ ማጰጰስ አሁን የተፈጠረውን ችግር እንደወለደ በመገንዘብ የአሁኑንም የወደፊቱንም ማስተካከል ይገባል።
ዜና ቤተክርስቲያን ያነሳው ሌላው ነጥብ የዜግነት ጉዳይ ነው። «በ1991 ዓ.ም ተሻሽለው ከቀረቡት አንቀጾች አንዱ ዜግነትን የሚመለከት መስፈርት ዳግም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ከዚያ በፊት አንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ የሚሾም ማሟላት ካለባቸው መስፈርቶች አንዱ ‘በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆነ’ የሚል አስገዳጅ ነጥብ ነበር። የ1991 ኣ.ም ህገ ደንብ ግን ባይሆንም ‘የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታይ ሆኖ ስርአተ ቤተክርስቲያን ጠንቅቆ ያወቀ…’ የሚል አክሎበታል። በዚህ ሕግ መሰረት የፈለገው አገር ዜጋ ይሁን የቤተክርስቲያናችን እምነት ተከታይ እስከ ሆነ ድረስ በኢትዮጵያ ጳጳስ ሆኖ የመሾም፣ ቤተክርስቲያኗን የመምራት መብት አለው ማለት ነው።
«ይህ ደግሞ በአንድ በኩል ቤተክርስቲያኗ የራሿ ዜጎች የሆኑ ብቁ ሰዎች የሏትም የሚል ትርጉም ከመያዙም በላይ ከግብጽ ቤተክርስቲያን ነጻ ወጥታ ራሷን መምራት የጀመረችውን ቤተክርስቲያን ዳግም ‘በአሜሪካውያንና አውሮጳውያን’ ቅኝ አገዛዝ ስር እንድትወድቅ በር የሚከፍት አደገኛ አካሄድ ነው። በተለይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያንንና አውሮጳውያንን ለማለት ተፈልጎ ከሆነም አንቀጹ በማያሻማ መልኩ መቀመጥ አለበት። ያም ቢሆን አንዴ ዜግነታቸውን (ኢትዮጵያዊነታቸውን በፈቃዳቸው የተዉ በመሆናቸው መሾም አንኳ ካለባቸው ባሉበት ውጭ አገር እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆን የለበትም። በአሁኑ ጊዜ ካሉት አባቶች መካከል የውጭ ዜግነት ያላቸው ጥቂት አባቶች እንዳሉ ይታወቃል ስለሆነም በ1991 ዓ.ም ሕግ እነዚህን ጥቂት አባቶች ለማካተት የወጣ መስሎ ስለሚገመት ሊታሰብበት ይገባል።»  
እንደ እውነቱ ከሆነ ቤተክርስቲያን ሕግና ደንብ የምታወጣው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመስርታ ለቤተክርስቲያን ጥቅም በሚሰጥበት መንገድ መሆን አለበት። 1991 ዓ.ም ህግ ግን አንዳንድ ጳጳሳትን ለመጥቀም ተብሎ የተረቀቀና በልካቸው የተሰፋ መሆኑ ግልጽ እየሆነ ነው። በተለይ ከዜግነት ጋር የተያያዘው አንቀጽ አባቶቻችን በስንት ትግል ያመጡትን መንበረ ጵጵስና በርካሽ ዋጋ እንደመሸጥ የሚቆጠር ነው። ጳጳሳትስ ምን አጥተው ነው ዜግነታቸውን የሚለውጡት? ስለዚህ የዜና ቤተክርስቲያን ሀሳብ የሚደገፍ ነውና ይህን አንቀጽ ማሻሻልና ወደቀደመው መመለስ ይገባል።
ይቀጥላል

4 comments:

 1. Aba selam

  Ende, MK yetal zegbachihu wist.... for the first time , you left MK

  ReplyDelete
 2. This the first positive article I read from you!

  ReplyDelete
 3. ድሮ ድሮ አማራና ትግሬ ብቻ ፓፓስ ይሆን ነበር
  አሁን ደግሞ የምን ዜጋ ዜጋ ወሬ ነው?
  ለአባ ሰላማ
  የኔ ልጅ የተወለደው አሜሪካ ነው
  ምንም ቢማር ምንም መንፈሳዊ ቢሆን ክህነት ሊከለከለ ነው?
  እመ ነስአ ማህተመ ሰጋ እንዘ ስመከ ይሰሚ
  አልቦ አይሁድ ወአልቦ አረሚ::

  ReplyDelete
 4. ዜና ቤ/ ክርስቲያን አውጩ መልካም ብሏል፤(ማን ሰምቶ)የሚል ሐረግ አስቀምጧል፤
  ተጨማሪ ሐረግ(ማን አይቶ)በማለት ግራም ቀኙም በመገደድ እስኪ ሰማና እስቲያይ ድረስ እንቀጥል፤

  ReplyDelete