Friday, May 18, 2012

ቤተክርስቲያናችን ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በቅድሚያ ቅዱስ ሲኖዶስ በ1991 ዓ.ም ያወጣውን ህግ ማሻሻል እንዳለበት ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ዘገበ

ይህን የዜና ቤተክርስቲያን ዘገባ ተከትሎ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዴት እንሰደባለን በሚል ቀድሞ ያልተያዘ ሌላ የውዝግብ ሰበር አጀንዳ ፈጥረዋል። በሌላው ሚዲያ ብንሰደብ ምንም አይደል፤ እንዴት በእኛው ጋዜጣ እንዴት እንሰደባለን? በሚል ለዛሬ 7/8/2004 ዓ.ም የጋዜጣው አዘጋጆች ቀርበው እንዲጠየቁ ጳጳሳቱ ሁሉ ተስማምተዋል ተብሏል። ግን በዛሬው የሲኖዶስ ስብሰባ ውሎ «አዘጋጆቹ ተጠርተው ይቅረቡ» ያሉት አባቶች ያደረጉትንና የሚከተላቸውን ስላወቁ ዛሬ ሀሳባቸውን ቀይረው ይግቡ አይግቡ የሚል ውዝግብ ውስጥ ገብተው ውለዋል። ዋና አዘጋጁ መጋቤ ምስጢር ወልደሩፋኤል ፈታሒም «ንስሐ ግቡ ብለን መጠቆማችን ስህተት ከመሰላቸውማ ጉዱን ሁሉ እንዘረዝርላቸዋለን» ማለታቸው ሲዘገብ ትናንት ከጉርምስና ጠባይ ያልተላቀቁትና ሲደነፉ የነበሩት አባ ሳሙኤልና አባ አብርሃም ዛሬ ይግቡና እንጠይቃቸው የሚል ድፍረት አጥተው ሳያነጋግሯቸው የዛሬው ስብሰባ ተጠናቋል።
የማኅበረ ቅዱሳን ድረገጾች ደጀሰላምና አንድ አድርገን፣ ለዚህ የሲኖዶሱን ስብሰባ ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አቅጣጫ ያስለወጠውንና በሌላው ላይ ጣቱን ሲቀስር የነበረው ጳጳስ ሁሉ ራሱን እንዲመረምር ከባድ የቤት ሥራ የሰጠውን፣ ወደሌላ አጀንዳ መሸጋገር አቅቷቸው «ስታክ» እንዳደረጉ ባሉበት ያቆማቸውን ታሪካዊና እውነተኛ የዜና ቤተክርስቲያን ዘገባ ማጣጣላቸውንና ከማንም ጉሮሮ የማይወርድ ወሬ ሲያናፍሱበት ውለዋል። ከሁሉም ያስገረመው ደግሞ ለትንሽ ለትልቁ ከውግዘት በቀር አፋቸው ላይ ሌላ እርምጃ የማይመጣላቸው ድረገጾቹ፣ በተለይም አንድ አድርገን «አብዛኞቹ  የምልዓተ  ጉባኤ አባላት  አዘጋጆቹ  ተወግዘው  ከስራ ይሰናበቱ  በሚለው  አጽንኦት  ሰጥተው  የተናገሩ  ሲሆን  ምንም  እንኳ  በዜና  ቤተክርስቲያን ለሚወጡ ማንኛውም ጽሁፎች  የጋዜጣው  አዘጋጆች  ተጠያቂ  ቢሆኑም  የጽሁፉን  ትክክለኛ አዘጋጆች ለማውቅ ስለሚረዳ  ዛሬ  ጠዋት ቀርበው እንዲያስረዱ  በመውሰን  የቀትር  በኋላ  ውሎ ተጠናቋል፡፡» ሲሉ ዘግበዋል። ለእነዚህ መደዴ ድረገጾች «ውግዘት» የስድብ ያህል የቀለለ ነገር ነው። ከእነርሱ ጋር የዋሉትና ተገዢያቸው የሆኑት እነአባ ሳሙኤልም «ውግዘት» ቢጠይቁባቸው ብዙ አያስገርምም። ያው የተማሩትንና የሚያውቁትን ያህል ነውና የሚፈርዱት። ለመሆኑ ግን ውግዘት ሲጠይቁባቸው ይህን ድፍረት ከየት አመጡት? እንዲህ የሚል ኅሊና መቼም የሞተ እንጂ ህያው አይደለም። እውነተኛ ዳኛ ቢኖር ግን ሊወገዙ የሚገባቸው የቤተክርስቲያንዋን ህግ ለግል ጥቅማቸውና በቅምጥልነት ለመኖር ብለው ያፈረሱት እነርሱ ናቸው። ስንቱን የኖረ ህገ ቤተክርስቲያን ያፈረሱና በልካቸው አላማዊ ህግ የደነገጉ፣ ለመነኮሳት ባልተፈቀደ አኗኗር እየኖሩ ያሉት እነርሱ ናቸው መወገዝ ያለባቸው። እነመጋቤ ምስጢርማ ያሉት አባቶች ራሳቸውን እንደጠፋው ልጅ ቆጥረው ወደልባቸው  ይመለሱና ንስሃ ይግቡ ነው ያሉት። ስለዚህ ወቀሳቸው ወደንስሃ የሚመራ በመሆኑ መመስገን ነው ያለባቸው። ጉዳዩ ከተካረረም አሳ ጎርጓሪ እንድሆን ያሰጋል።
የማቅ ድረገጾች በተጻፈው ላይ ሳይሆን በጸሀፊው ላይ በማተኮር፣ ማነው የጻፈው በሚል መልእክቱን የአንባቢዎቻቸው አይን እንዳይመለከተውና ጉዳዩ ሌላ መልክ እንዲይዝ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን ልብ ላለው ሰው ማንም ይጻፈው ማን መልእክቱ ውሸት ነወይ? በፍጹም!!!!!!!! የተጻፈው እውነት ነው። እንዲያውም እየደረሰ ካለው ጥፋት አንጻር የሚያንስ እንጂ ያለውን እውነታ ሙሉ በሙሉ ያሳየ ነው ማለት አይቻልም። ቤተክርስቲያኒቱ የተዘፈቀችበት ፈርጀብዙ ችግር ቢዳሰስማ «ጆሮን ጭው» የሚያደርግ በሆነ ነበር።
ታዲያ የማቅ ድረገጾች እውነታውን መጋፈጥ ትተው ለቅጥረኛ ጳጳሳቶቻቸው ሙግት በመግጠማቸው «ቆመንላታል» ለሚሏት ቤተክርስቲያን ፈጽሞ የማያስቡና በውድቀቷ የሚደሰቱ መሆናቸውን አስመስክረዋል። የማቅ ደረገጾች ከዚህ በላይ ውድቀት ምን አለ? ለሁሉም ይህን ለታዛቢ ትተን በቀጣዩ ነጥብ ላይ እናተኩር።
«የሀብት የውርስ ጉዳይ»
ዜና ቤተክርስቲያን ትኩረት የሰጠበት  ሌላው ጉዳይ የጳጳሳት ሀብትና ውርስን የተመለከተው ነው። ጋዜጣው ይህን ሀሳብ በቀጥታ ከሙስና ጋር ነው ያያያዘው። ምክንያቱም ጳጳሳት በሙስናዊ መንገድ ካልሆነ በቀር ሀብትና ንብረት እንዲያፈሩ የሚፈቅድ ህግ በቤተክርስቲያን የለም። ስለዚህ ዜና ቤተክርስቲያን ጳጳሳትና መነኮሳት በዚህ ዓለም ለእግዚአብሔር መገዛት እንጂ ለራሳቸው ሀብትና ንብረት በማፍራት ከተጠሩበት የጥሪ መስመር ወጥተው እንዳይገኙ የሚደነግገውን ፍትሕ መንፈሳዊን ጠቅሶ ይሞግታቸዋል። የኖረውን ህግ የ1991ዱ ህግ ሽሮት ጳጳሳት የሀብትና የንብረት ባለቤቶች እንዲሆኑና ሲሞቱም ሀብታቸውን ለሌላው ማውረስ እንደሚችሉ ይደነግጋል። ህጉ በአንቀጽ 45 ቁጥር 1 ላይ «‘አንድ የቅዱስ ሲኖዶስ  አባል ከዚህ ዓለም በሞት በሚለይበት ጊዜ የግል የሆነ ገንዘብ ቢኖረው ይረዳቸው ለነበሩ እጓለ ማውታና ለችግረኞች ይሰጣል’ የሚል እስካሁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ያልነበረ ህግ አውጥቷል። ይህ አንቀጽ መሰረታዊውን የምንኩስና የሚያፋልስ ከመሆኑም በላይ የቤተክርስቲያንዋ ጥንተ መሰረት የሚያናጋ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የነበራቸውን ተአማኒነት የሚሸረሽር፣ ንጽህናቸውንና ቅድስናቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚጨምር ነው።
«ይህ ሕግ  ከወጣ በኋላ እየታዩ ያሉ ችግሮች የዚህ አንቀጽ አላስፈላጊነት በተጨባጭ እያሳዩ ነው፡፡ ብፁዓን አባቶች ከዚህ ዓለም በሞት በሚለዩበት ጊዜ ከሀብት ንብረት ውርስ ጉዳይ በተያያዘ ቤተ ክርስቲያንዋ  የፍርድ ቤቱ ስምዋ ከመነሣት አልፎ የአንዳንድ ብፁዓን አባቶች ስም ባልሆነ መንገድ ሲጐድፍ ይታያል፡፡ የሟች አባቶች ስም ከውርስ ጋር በተያያዘ ከፍርድ ቤት በሚወጡ ማስታወቂያዎች በየመብራትና ስልክ  ዕንጨቶች፣ በየጋዜጦች ተለጥፎ ማየት ለቤተ ክርስቲያንዋ ውርደትና ሐፍረት እንጂ ክብር አለመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚገባ ሊያጤነው ይገባል፡፡ ‹‹ለዕጓለ ማውታ›› የሚለው አባባልም ተቀባይነት የለውም፤ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያንዋ እጓለ ማውታ የምታሳድግባቸው የራሷ ማዕከላት ስላሉዋት አባቶች ወደሚቀርባቸው ማዕከል በመሄድ ማስተናገድ ይችላሉና ነው፡፡»
ይህ የጋዜጣው አስተያየት ትክክለኛ ነው። ከዚህ ቀደም የአንዳንዶቹን ገበና በዚህ ድረገጽ ስናወጣ አንዳንድ ሰዎች ሆነ ብለን ስም ለማጥፋት እንዳደረግነው ቆጥረው ነበር። ነገር ግን የተባለው ሁሉ እውነት መሆኑን፣ ሸፋፍኖም ቢሆን ጋዜጣው አረጋግጦልናል። ጳጳሳቱ እንደዚህ ላለ ውርደት የተዳረጉበት ምክንያት ለቤተክርስቲያን ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የደነገጉትና ሀብት ንብረት እንዲያፈሩ የሚፈቅደው ሕግ ነው። ሕጉ የምንኩስናን ስርአት የናደና ጳጳሳቱ በሙስናዊ መንገድ ባለሀብትና ንብረት እንዲሆኑ በር የከፈተ ነው። ሀብት ማፍራት ብቻ ሳይሆን ማውረስን የተመለከተው ሕግ ደግሞ በጳጳሳት ተነግሮም ሆነ ተሰምቶ የማያውቅ ጉድ እየጎተተ መሆኑ እጅግ አስደንጋጭ ነው። ጳጳሳቱ በአዲሱ ደንባቸው እናወርሳለን ያሉት በቁማቸው ይረዷቸው ለነበሩት እጓለ ማውታና ችግረኞች ነው። ከሞቱ በኋላ ለውርስ እየተሰበሰቡ ያሉት ግን፣ ሚስትና ልጆች ሆነው ተገኝተዋል። ጳጳሳቱ በሚሊየን የሚቆጠር ብር በባንክ ከማስቀመጥ፣ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ቪላዎችን በውድ ዋጋ ከመገንባት፣ ያለፈ የሚረዷቸው እጓለ ማውታም ሆኑ ችግረኞች መኖራቸው አልተሰማም። ገበናችን እንዳይገለጥ የሚል ስጋት ከአሁኑ ያደረባቸው እንደአባ ሳሙኤል ያሉና በተመሳሳይ ህይወት ውስጥ የሚገኙ ተሟጋቾቻቸው ጳጳሳት ደግሞ የሟቹን ጳጳስ ሀብትና ንብረት የሚወርሱት የስጋ ዘመዶቻቸው ናቸው ሲሉ ነው ሲሟገቱ የነበረው። ለምሳሌ አባ ሳሙኤል የአቡነ ሚካኤል ሚስትና ልጅ ለወራሽነት ሲቀርቡ ይህን ህግ ተገን አድርገው «የስጋ ዘመዶቻቸው ናቸው የሚወርሱት፣ እርሳቸው ድንግል ናቸው፤ ጳጳስ መውለድ አይችልም ወዘተ» ብለው ነበር ሲሟገቱ የነበረው። ታዲያ በ1991ዱ ህግ የተቀመጠው ለእጓለማውታና ለችግረኞች የሚለውን የት አስቀምጠውት ነው ለስጋ ዘመዶቻቸው ለማውረስ የተከራከሩት? እርግጥ የሌሉ እጓለማውታዎቻቸውንና ችግረኞቻቸውን ከየት ያመጣሉ? ያው ሊመጡ የሚችሉት ህጋዊ ወራሾቻቸው ናቸው፤ ማለትም በምንኩስና ውስጥ ሆነው ያገቧቸው ሚስቶቻቸውና የወለዷቸው ልጆቻቸው። በአጠቃላይ ምንኩስናም ሆነ ጵጵስና ተንደላቆ መኖሪያ እንጂ ራስን ገዝቶና ጨምቶ እግዚአብሔርንና ቤተክርስቲያንን ማገልገያ አልሆነም። ስለዚህ የተከበረው ጵጵስና እጅግ እየተዋረደ ይገኛልና አባቶች ከምን ጊዜውም በላይ የጠበቀና የቀደመ ስማቸውን የሚያድስ ውሳኔ በዚህ ስብሰባ ላይ መወሰን ይጠበቅባቸዋል።  
«ከዚሁ ከሀብት ጋር በተያያዘ ሌላም መነሣት ያለበት ነጥብ ነው፡፡ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ኤጲስ ቆጶሳት የግል ሀብትና ንብረት እንዳያፈሩ ከመከልከሉም በላይ አኗኗራቸው ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ውጭ መሆኑን እንደሌለበት፡- ‹‹ኤጲስ ቆጶስ ከተሾመ በኋላ በቤተ መቅደስ ውስጥ ፅሙድ ይሁን፣ በቤተክርስቲያን ይቀመጥ (ፍ.መ.5፡112፣118) በማለት ደንግጓል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ለሚኖሩበት ብለው ሳይሆን ሰዎች ናቸውና ሲደክማቸው አረፍ የሚሉበት፣ ምግብ የሚቀምሱበት፣ ምእመናን ተቀብለው የሚባርኩበት፣ የሚያጽናኑበት፣ መጻሕፍት የሚፈትሹበት ቤት (መንበረ ጵጵስና) ብቻ ነበራቸው፡፡ ይህ መንበረ ጵጵስና የሚመሠረተው በቤተክርስቲያን (ቤተ መቅደስ) ጓሮ ብቻ ነበር፡፡
ዛሬ ግን አንዳንድ አባቶች ይህንን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በመሻር በከተማ (በባቢሎን) መሃል መለስተኛ ቤተ መንግሥት የሚያከላክሉ ሕንጻዎች ሲገነቡ ይታያሉ፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ይህንን እያደረጉ ያሉት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊቃነ ጳጳሳት ክብር ደረጃ የጠበቀ የብፁዓን አባቶች ዘመናዊ ማረፊያ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ቅጽረ ግቢ ተሠርቶ አገልግለት መስጠት ከጀመረ በኋላ ጭምር መሆኑ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ አካሄድ ‹‹ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ው፣ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው›› (ሮሜ 8፣6) የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል የሚጥስ፣ የወንጌል ዕርፍ ይዞ ወደ ኋላ ለማረስ መሞከር (ሉቃ. 9፣6)፣ በመሆኑ ብዙኀን አበው ሥር ሳይሰድ ሊያስቡበት ይገባል እንላለን፡፡
ጳጳስ ሆነው ፎቅና ቪላ ያልሰሩ ጥቂቶች ይኖሩ ይሆናል። ብዙዎቹ ግን ባለቪላዎች ናቸው። እንደቤተክርስቲያን ሕግ እንዲህ ያደርጉ ዘንድ አልተፈቀደም። መኖሪያቸው በቤተ ክርስቲያን አጠገብ እንዲሆን ነው የተደነገገው። እነርሱ ግን ቀድመው ይህን ጥንታዊ ህግ ለራሳቸው እንዲመች አድርገው አሻሽለው ከቤተክርስቲያን ይልቅ ከተማን ወደዱ፤ እንደዜና ቤተክርስቲያን ቅንፋዊ ማብራሪያ «ባቢሎንን» መረጡ። ለአሁኖቹ ጳጳሳት ብዙ ሚሊዮን ብር ፈስሶ የተገነባ እጅግ ዘመናዊ የጳጳሳት መኖሪያ እያለ ብዙዎቹ እዚያ አያድሩም። በከተማ ባስገነቧቸው ቪላዎቻቸው ውስጥ ነው የሚኖሩት። ለምን? ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ነው። አንዳንዶቹ በአብሳይና በረድእ ስም ከመንበረ ጵጵስና ውጪ በከተማ ባስገነቧቸው ቪላዎች ውስጥ ሴት አስቀምጠዋል እየተባለ በሰፊው ይወራል። ባለትዳር የሆኑም አሉ ነው የሚባለው። ግን «ጳጳስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ»።
በሚሌኒየሙ አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ ታትሞ የወጣ ሰሞን አንዱ አነጋጋሪ ጥቅስ «ጵጵስናን የሚሾም እንዲህ ሊሆን ይገባል፤ የአንዲት ሚስት ባል» የሚለው ጥቅስ ነበር (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፡2)። በዚህ ጥቅስ ላይ ቀልድ ይሁን እውነት የሚነገር አንድ ነገር ነበር። ጥቅሱን ካነበቡ ጳጳሳት መካከል ከወጣትነት በቅርቡ የወጡት እጅግ ደስ አላቸው ይባላል። ሽማግሌዎቹ ግን ደስ አልተሰኙም። እነዚያ ለምን ደስ እንዳላቸው፣ እነዚህ ደግሞ ልምን እንደተከፉ ግልጽ ነው። ይሁንና ለመጽሀፍ ቅዱሱ አዘጋጆች ለምንድን ነው ቀድሞ ኤጲስ ቆጶስ የሚለውን ጳጳስ ብላችሁ የተረጎማችሁትና የአንዲት ሚስት ባል ሊሆን ይችላል ያላችሁት ተብለው ሲጠየቁ፣ «እንደው በአንድ ቢወሰኑ ብለን ነው» አሉ ይባላል። ይህ በቀልድ መልክ የተነገረ ቢሆንም እንደዚህ አይነት አባቶች የሉም ማለት አይቻልም። ይህ ለአንዳንዱ ሰው አስደንጋጭ ቢሆንም አንዳንዶቹ አባቶች ከዚህ ነጻ እንዳይደሉ ግን እርግጥ ነው። ስለዚህ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተሰራው ህግ መውጣትና ወደመጽሐፍ ቅዱሱ ህግ መመለስ ተገቢ መሆኑ ከታመነበት ማግባት የሚፈልጉ ጳጳሳት እንዲያገቡ ህጉን በቅዱስ ሲኖዶስ ማሻሻል ሳያስፈልግ አይቀርም። ጥሪው ሳይኖረው ለመጰጰስ ብሎ ወደምንኩስናው እየተመመ ያለውን ወጣትም መገደብ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን በምንኩስና ውስጥ ያለ «ትዳር» ግን ለሰሚው ግር ያሰኛልና ጳጳሳቶቻችን ወደተሰራላቸው ማረፊያ መመለስና የገነቧቸውን ቪላዎች እንደ አቡነ ፋኑኤል ሲሞቱ ለቤተክርስቲያን ለማስረከብ ቃል መግባት፣ ከተቻለም ለቤተክርስቲያን ስም መታደስና እነርሱም በምእመናን ዘንድ እየተሸረሸረ የሚገኘውን ተአማኒነታቸውን ወደቦታው ለመመለስ፣ ማንኛውንም በሙስናዊ መንገድ ያካበቱትን ሀብትና የገነቧቸውን ቪላዎች ለቤተክርስቲያን የማስረከብ አባታዊም ህሊናዊም ግዴታ አለባቸው እንላለን። ምክንያቱም ዜና ቤተክርስቲያን እንደሚለው «ብፁዓን አባቶች በጠቅላይ ቤተ ክህነት ከተሠራላቸው የተሟላ ማረፊያ በተጨማሪ ከደረጃቸውና ክብራቸው ጋር የሚመጣጠን በቂ ወርሃዊ ደመወዝ፣ ነጻ ሕክምናና ነጻ ምግብ ያገኛሉ፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን እየተዳደረች ያለችው ቅዱስን አባቶች ሠርተው በተውዋቸው ሕንጻዎች ብፁአን ምዕመናን ከልጆቻቸው በፊት ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን አስቀድመው ለቤተ ክርስቲያን አውርሰዋቸው ከሄዱ ሕንጻዎች ከሚገኘው ኪራይ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ዓለማውያን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቀሪ ሀብት ንብረታቸውን እያስመዘገቡ ባሉበት ወቀት ብፁዓን አባቶች በቤተ ክርስቲያን ስም ያገኙት ሀብትና ንበረት ለቤተሰብ ማውረስ ምን ይሉታል?»

ይቀጥላል

2 comments:

 1. እንኳን ማኅበረ ቅዱሳን ሃይማኖተ አበውም ታግዷል

  አንደኛ ማኅበረ ቅዱሳን ተቋቋመው ልክ እንደ ሃይማኖተ አበው የኢትጵያ ተማሪዎች ማኅበር ነው፡፡ በቀጥታ ትናንሽ ለውጦችና የስም መተካት ብቻ ነው የተደረገበት፡፡ ሃይማኖተ አበው ከዐርባ ሽህ በላይ አባላት ነበሩት፡፡ ግን ደርግ ወጣቱ ሃይማኖተኛ እንዲሆን ስለማይፈልግና አን ሀገራ የወጣቶች ማኅበር ስላቋቋመ በአንድ ደብዳቤ ማኅበሩ ታገደ አባቶችም ወጣቶች አባላት እንዳይበተኑ በማለት ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት እንዲታቀፉ አደረጉ፡፡ ማኅበሩም ለማደራጃ መምሪያውና ለሰንበት ትምህርት ቤት እድገት ከፍተኛ ስተዋጽኦ አደረገ፡፡

  ቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበረ ቅዱሳንን ያቋቋመችበት ሕግ ዶግማ አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ያቸው አባቶች ካሉ እንኳን ካህናት ገና ክርስቲያን አይደሉም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ተባለው ማኅበር ከአእማደ ምስጢር ስድስተኛው የሃይማኖት መገለጫ ወይም ስምንተኛው የቤተ ክርስቲያን ምስጢር ነው ብለው ከሚያምኑ ሰዋች ይሠውረን፡፡ ለእኔ ማኅበረ ቅዱሳን ፕሮጀክት ነው እስከ አሁን በጣም የተወሰ ስኬታማ ውጤት አምጥቷል የጣሩትን አመስግኖና የምስክር ወረቀት ሰጥቶ ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ መሠራት አለበት፡፡ አሁነ ማኅበረ ቅዱሳን ወጥ ረግጧል፣ የፖለቲካ፣ የንግድ፣ የመንደር፣ የኑፋቄ ማኅበር ሆኗል ማመን ካልፈለጋቸውሁ በብቁ ማስረጃ በሂደት ሁሉንም እናጋልጣለን እኛ የሰው ገመና ለምን ይጋለጥ ብለን ነው እንጅ፡፡

  አሁንም የምንጠብቀው ምንም እንኳ መደራጀት መብት በሕገ መንግሥት የተሰጠን ቢሆንም እንኳን ማኅበረ ቅዱሳንና ንጉሠ ነገሥቱ ሳይቀሩ የክብር አባል የነበሩበት፣ ፓትርያርኩ የሚመሩት፣ በሲኖዶስ ታወቀ፣ ከቤተ ክህነት በጀት የነበረው፣ ታላቁ ሃይማኖተ አበውም በዓለማዊውና ደርግ በሾመው ሥራ አስኪያጅ በአንድ ደብዳቤ ታግዷል፡፡

  ReplyDelete
 2. ማቅ ዓቅሙን እስቲያውቅና ንስሓ እስኪገባ ድረስ መታገድስ ይቅርና መበታተን የሚገባው አካል ነው
  ምክንያቱም አስመሳይና የመልካም ነገር ተቃራኒ ከመሆኑም ባሻገር ራሱን አኩሪ ሳይቀስ የተቀደሰ ደፋር
  አሸባሪ በመሆኑ፤

  ReplyDelete