Tuesday, May 15, 2012

በዛሬው ጠዋት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ይቀርባሉ የተባሉት የዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ አዘጋጆች ሳይቀርቡ ቀሩ

Read in PDF
ስብሰባው አሁንም በቅዱስነታቸው እየተመራ ይገኛል
አቡነ ሳሙኤልና አቡነ አብርሃም የጋዜጣው አዘጋጆች ይወገዙልን እያሉ ነው።
ሲኖዶሱ በትናንትናው ዕለት ቀኑን ሙሉ በዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ ላይ በወጣው ጽሁፍ ላይ ሲወያይ የዋለ ሲሆን ወደማምሻው ላይ ፈራ ተባ እያለ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅና ምክትል ዋና አዘጋጅ እንዲጠሩ የወሰነ መሆኑ ታውቋል። ጋዜጣው ላይ ከተጻፈው ሁሉ አብዛኛዎቹን ያበሳጨው ሀብታሞች ናቸው ተብሎ የተጻፈው ሲሆን ነገ ብንለምን ማን ያምነናል በማለት ቁጣቸውን ገልጸዋል። 
ማሕበረ ቅዱሳንን ደግሞ ያቃጠለውና በአባቶች በኩል ሾልኮ ሊገባ የፈለገው በጋዜጣው መንግስት በአሸባሪነት እንደፈረጃቸው መጻፉና ዶ/ር መስፍን መወገዙ መዘገቡ ነው። የማህበሩ አመራሮች በጋዜጣው ክፉኛ የተበሳጩ ሲሆን ወዳጅ ፍለጋና ህዝብ ማሳሳቻ የጋዜጣው አዘጋጅ የማያውቁትና ከውጭ የተዘጋጀ ነው በማለት አለቃቅሰዋል። የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ግን በጻፉት ጽሁፍ እንደሚኮሩና በእውነተኛነቱም እንደማይጠራጠሩ እየገለጹ ይገኛሉ።
በዛሬው ዕለት በነበረው የሲኖዶስ ስብሰባም ተጠርተው ይቅረቡ የተባሉት የጋዜጣው አዘጋጆች ወደ ስብሰባው ለመግባት ደጅ እየጠኑ የነበረ ቢሆንም በትናንትናው እለት ተጠርተው ይቅረቡ ያሉት አባቶች ዛሬ ደግሞ ይግቡ አይግቡ በሚለው ስለተወዛገቡ ሳይገቡ ቀርተዋል። ዋና አዘጋጁ ንስሐ ግቡ ብለን መጠቆማችን ስህተት ከመሰላቸውማ ጉዱን ሁሉ እንዘረዝርላቸዋለን እያሉ የነበረ ቢሆንም ደፍሮ ይግቡ የሚል ጠፍቶ የጠዋቱ ስብሰባ ተብትኗል።
በስብሰባው ዕለት አቡነ አብርሃምና አቡነ ሳሙኤል ይወገዙልን እያሉ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ አባቶች ግን እንዴት ነው ነገሩ እኛው ከሳሽ እኛው ዳኛ ሆነን ነገሩን ማየት እንችላለን ወይ? ጹሁፉን በመጻፋቸው ብናዝንም ከሰን ፈራጅ መሆናችን ግን አያስኬድም በማለት ሀሳቡን ተቃውመዋል። ሌሎቹም አስገብተን ደግሞ ስድባችንን እንስማ እንዴ? እንዲሁ የምንለውን ብለን እንወስን እንጂ በማለት ተናግረዋል።
አቡነ ፋኑኤል እኔ ቤት ሰርቻለሁ። አለኝ። ስሞት ግን ለቤተክርስቲያን ነው የማወርሰው። ቤት ያለን አሁን ለቤተክርስቲያን እንናዘዝ እንጂ ሰዎቹን ምን ብለን ነው የምናወግዘው? ብለው መናገራቸው የተሰማ ሲሆን ይሕም ንግግር አብዛኛዎቹን ጳጳሳት ያረገበ መሆኑ ተነግሯል። ካልተወገዙ እያሉ ሲወራጩ የነበሩት አባ አብርሃምና አባ ሳሙኤል ለአቡነ ፋኑኤል ንግግር ምላሽ ያልሰጡ ሲሆን ያላቸውንን የተንጣለለ ቪላም ለቤተክርስቲያን እናወርሳለን ለማለት አልደፈሩም። ምናልባትም እንዲያወርሱት ሕግ የሚያስገድዳቸው አካል ስላላም ለቤተክርስቲያን አወርሳለሁ ለማለት እንዳልደፈሩ ታውቋል።
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ማርቆስ ቅዳሜ ዕለት እኔ ሳላውቅ እንዴት ይጻፋል በማለት የተናደዱ ሲሆን በእሳቸው ስልጣን ደረጃ የሚጻፈውን ሁሉ አንብቦ ማጣራት እንደሚከብድ ስለተረዱ ግን በሰኞው ዕለት እና በዛሬው ስብሰባ ረገብ ብለው መዋላቸው ታውቋል። እንዲያውም ጉዳዩ መታየት የነበረበት በሲኖዶስ በኩል ሳይሆን በስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ ተልዕኮ በኩል ጉዳዩ ታይቶ ብጹዕነታቸው አቡነ ማርቆስ የፈለጉትን አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ መተው ነበረበት ሲሉ ይገልጻሉ::
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዱስነታቸው አቡነ ጳውሎስ የሲኖዶስን ስብሰባ እየመሩ የሚገኙ ሲሆን ህልሙን እያስወራ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳንም ሊፈጥረው የፈለገው ውዥንብር ስላልሰራለት ነገሬን በምን ልዋጠው እያለ በመጨነቅ ላይ መሆኑ ታውቋል። እንዲያውም አንዳንዶች ሲኖዶሱ ላይ ባለው የይወገዙልን አረ ይቅር ጭቅጭቅ ቅዱስነታቸው ያልከፈሉትን ቲያትር በነፃ እየተመለከቱ ይገኛሉ በማለት ይገልፃሉ።
በተለይም እነ አቡነ ሳሙኤል የጋዜጣው አዘጋጆቹ ይወገዙልን ማለታቸው የሚያሳፍር ሲሆን እነዚህ ጳጳሳት በየትኛው የሃይማኖት ዕውቀታቸው ጳጳሳት እንደሆኑ እያነጋገረ ነው። ምክንያቱም ውግዘት የስነ መለኮት ትምህርት ስህተት ውጤት ነው እንጂ ተዘለፍኩኝ በማለት የሚፈጸም አለመሆኑን ማወቅ እንዴት ያቅታቸዋል? አንዲህ ያለው ሀሳብ የሚመነጨው ከትምህርት ማነስ እንጂ ከሌላ ሊሆን አይችልም እያሉ ይገኛሉ። መካሪዎቻቸው ማኅበረ ቅዱሳኖች የመንፈሳዊ ዕውቀት ድሃ በመሆናቸው እንደአባቶቻቸው እነ አቡነ አብርሃምና አቡነ ሳሙኤል ባለፈው ጥቅምት ሲኖዶስ አነበቡ፣ አስነበቡ፣ ጨበጡ፣ ሀሳብ ሰጡ በማለት አገሩን ሁሉ ይወገዙልን ማለታቸው ይታወሳል።

1 comment:

  1. TEZEKER MAHIBERINE ZAKIDEMIKE FETIREMay 17, 2012 at 7:22 AM

    በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4:8-9።

    ReplyDelete