Monday, June 25, 2012

የግንቦት 15ቱ ውግዘት መነሻ፣ ሂደት፣ ፍጻሜና ቀጣዩ ሲገመገም

የግንቦት 15/2004 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውግዘት ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡ ውግዘት ያስተላለፈው በ7 ድርጅቶችና በ16 ግለሰቦች ላይ ነው፡፡ ሲኖዶሱ አውግዣለሁ ቢልም፣ የጉዳዩ አነሳሽ፣ ጥናት አቅራቢውና ውግዘቱ እንዲተላለፍለት ተግቶ ሲሰራ የቆየውና እቅዱን በተሳካ ሁኔታ ያስፈጸመው ማኅበረ ቅዱሳንና ደጋፊዎቹ በተላለፈው ውግዘት ደስተኛ ሆነዋል፡፡ ውግዘቱ በተላለፈባቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ እንዲሁም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ በነበሩት በርካታ ተመልካቾች ዘንድ ግን የጌታችንን ትምህርት ያልተከተለ፣ ህግ ቤተክርስቲያንን የጣሰ፣ ግብታዊነት የተሞላበት፣ ሥልጣንን አለአግባብ እንደመጠቀም የተቆጠረ፣ በአጠቃላይም ቤተክርስቲያኒቱ በምን አይነት ይዞታ ላይ እንዳለች ያመላከተና ውግዘት ዘበከንቱ ሆኖ ያለፈ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡  

Thursday, June 21, 2012

እውነት የተጨቆናባት ሐሰት የነገሠባት ቤተክርስቲያን

Read in PDF

ክብር ለስሙ ይሁንና ጌታ ኢየሱስ ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ጀምሮ አነጋጋሪ ሆኖ ዘልቋል፡፡ የእርሱ ጉዳይ ዛሬም ዋና አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ኢየሱስ ዛሬ ለብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ አንድ ቀንም ለጥያቄያቸው ሁሉ መልስ ይሆናል። እርሱ የእባቡን ራስ ይቀጠቅጣል ተብሎ ገና ከኤዶም ገነት ጀምሮ የተነገረለት አዳኝ ነው፡፡ በመሆኑም በጊዜው የሰይጣንን ራስ ቀጥቅጦ በዲያብሎስ ግዛት የነበሩትንና አዳኝነቱን ተረድተው በስሙ ያመኑትን ሁሉ ነጻ አውጥቷል፡፡ በዚህ ደስ የማይለውና የክርስቶስ የአዳኝነቱ ዜና የሆነው የክብሩ ወንጌል ብርሃን በሰዎች ልብ እንዳያበራ የማያምኑትን ሐሳብ በማሳወር እየሰራ የሚገኘው ሰይጣን በልዩ ልዩ ተንኮል እያሳተ ሰዎች በኢየሱስ አዳኝነት አምነው እንዳይድኑ ይተጋል፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ሲንቀሳቀስ ዋና አላማው ሰዎች ከመዳን መንገድ እንዲወጡና መዳን በማይገኝበት ጎዳና ላይ እንዲነጉዱ ማድረግ ነው፡፡

Tuesday, June 19, 2012

ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎቹን አስመረቀ

(ምንጭ፦ ዐውደ ምህረት)
  • መምህር አሰግድ ሳሕሉም ከተመራቂዎቹ አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በስሯ ከምታስተዳድራቸው መንፈሳዊ ኮሌጆች መካከል አንዱና የ69 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው አንጋፋው ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በተገኙበት አስመረቀ። የምረቃ ፕሮግራሙ ደማቅ የነበረ ሲሆን ተማሪዎቹ ቤተክርስቲያንን በቅንንነትና በመልካም ሥነ ምግባር ለማገልገል ቃል ገብተዋል። አዳራሹ በተመራቂዎችና በቤተሰቦቻቸው የተሞላ የነበረ ሲሆን በእያንዳንዱ ተማሪ ፊትም የሚታየው ደስታ ስሜት ልዩ ነበር። በዕለቱ አባታዊ ቡራኬ የሰጡት  ቅዱስ ፓትርያርኩም  “…ያለፉትን ዘመናት መሰናክሎችን እያለፍን መምጣታችን ስለምናውቅ ያለፉትንም ያለፍነው በራሳችን ስላልሆነ አሻጋሪውን አምላክ ከሁሉ በፊት እናመሰግናለን። እናንተ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በኃላፊነት ላይ ነው ያላችሁት እያስረከብናችሁ ነው። በዚህ የተመደበ ሌላ ሥራ የለውም የወንጌል ሥራ በትርፍ ጊዜ የሚሰራ አይደለም። ሁሉንም የምንማረው በጊዜ ነው። ከዚህ በፊት ተምረው የወጡ ብዙ ናቸው። በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ የገቡትን ኪዳን ይፈጽሙ አይፈጽሙ ተመልካቹ አምላክ ነው። መለኮታዊ አደራ ስለሆነ።….” በማለት አባታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል።

Monday, June 18, 2012

«ፍቅር ለይኩን ያቀረበው ትችት ውሃ የማይቋጥር ወንፊት ነው»

(ምንጭ፦ ደጀ ብርሃን ድረ ገጽ)


በአባ ሰላማ ድረ ገጽ ላይ «ፍቅር ለይኩን» የተባለ ሰው ስለየትኞቹ ስም አጥፊ ብሎጎች ለመናገር እንደፈለገ ስማቸውን ባይገልጽም እሱን ደስ ያላሰኘውን ነጥብ በማመልከት፤ የሰዎችንም ኃጢአት መዘርዘር ጥሩ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን በማስረጃ አቅርቦ ምክርና ተግሳጽ ለመስጠት ሲሞክር ተመልክተናል። 


ይህ የአባ ሰላማ ድረ ግጽ ላይ ጽሁፉን ያቀርበው «ፍቅር ለይኩን» የተባለው ሰው፤ በፖለቲካው ዓለም ደከመን፤ ሰለቸን ሳይሉ የኢሕአዴግን መንግስት  በመቃወም ሌሊትና ቀን በሚደክሙት ድረ ገጾች ላይ የተለያዩ ፖለቲካዊ  መጣጥፎችንና  አንዳንዴም መንፈሳዊ መሰል የነቀፋ ጽሁፎችን የሚያቀርበው የደቡብ አፍሪካው «ፍቅር ለይኩን» መሆኑን የምናውቀው ከስሙ ባሻገር «ሻሎም፤ ሰላም» በሚለው የጽሁፉ ማሳረጊያ ቃል የተነሳ እሱነቱን ብንገምት ከእውነታው የራቅን አይመስለንም።


ከዚህ ተነስተን ስለ አቶ ፍቅር ለይኩን ጽሁፍ ጥቂት ለማለት እንወዳለን።


አቶ ፍቅር ስለ አባቶች መዋረድና አለመከበር ተገቢ መሞገቻ የሆነው የመከራከሪያነት የተጠቀመበትን ዐውደ ጥቅስ በማስቀደም እንጀምር።


ቀሪውን ከደጀ ብርሃን ብሎግ ለማንበብ ይህን ይጫኑ

Sunday, June 17, 2012

ይድረስ በአባቶቻችን ላይ የስደብና የማዋረድ ዘመቻ ለከፈታችሁ ብሎጎች፡- አባቶችን ማዋረድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር ማዋረድ ህልውናዋንስ መዳፈር እንደሆነ አታውቁምን…?!

በፍቅር ለይኩን
‹‹ደፋሮችና ኩሩዎች ሆነው ሥልጣን ያላቸውን ሲሳደቡ አይንቀጠቀጡም፣ ዳሩ ግን መላእክት በኃይልና በብርታት ከእነርሱ ይልቅ ምንም ቢበልጡ በጌታ ፊት በእነርሱ ዘንድ የስድብን ፍርድ አያመጡም…፡፡›› ፪ጴጥ ፪፣፲፩፡፡
መንፈሳዊ ድባብ ያላቸው የሚመስሉና ግን መንፈሳዊ ወዝና ሽታን የተራቆቱ በቤተ ክርስቲያን ስም በተከፈቱ መጦመሪያ መድረኮችና ድረ-ገጾች ዛሬ በእኛ ዘመን በአባቶች ላይ እየወረደው ያለው ስድብና እርግማን፣ እየተገለጸ ያለው ገመና ጆሮን ጭው የሚያደርግ ነው፡፡ እንዲህ የቤተ ክርስቲያኒቱን ገበና ለአደባባይ በማብቃትስ የሚገኘው ትርፍና ጥቅም ምንድን ነው? እባካችሁ ቆም ብለን እናስብ፣ እናስተውል እንጂ ወገን፡፡ ምን ዓይነት ድፍረት ምን ዓይነት ዝቅጠት ነው ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የተባሉትን ሊቀ ጳጳስ- የአንተ ያለህ…! ‹‹ቀውስ እና ጦስ›› ናቸው ብሎ መጻፍና ማዋረድ፤ ሰውን ያህል ክቡር ፍጥረት ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ‹‹የጉድ ሙዳይ›› በማለት የመንፈሳዊነቱ ክብር ቢቀር ከሰብአዊ ክብር ማውረድ፣ ይህ በምንም ዓይነት መለኪያ፣ በምንም ዓይነት መንገድ ክርስቲያናዊነት ሊባል ይችላል፣ በምንስ መስፈርት ሞራላዊና ግብረ ገብነት ሊሆን ይችላል???

Friday, June 15, 2012

ዓለማየሁ ሞገስ ስለጥንተ አብሶ ይናገራሉ፤ በጥንተ አብሶ ዙሪያ ላነሡት ሀሳብ የሰጡት ርእስም የሚከተለው ነው

(ማርያም) ከጥንተ አብሶ ነጻ ናት ወይ?

በብሥራት ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ያለውን ይዘው እመቤታችንን ጥንተ አብሶ አልነካትም ከአዳም ጀምራ ስትወርድ ስትዋረድ የመጣች ንጹሕ ዘር ናት የሚሉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ጸጋን የተሞላች ከተወለደች በኋላም፣ መንፈስ ቅዱስ ካነጻት በኋላም ሊሆን ይችላል፤ ዘላለማዊ ድንግልናዋም በነቢያት ሲነገር ከጥንተ አብሶ ግን ነጻ ናት ያለ አንድም ነቢይ ስለሌለ፤ መልአክም መንፈስ ቅዱስ ይጸልልሻል ብሎ እንደሚያነጻት ተናገረ እንጂ እኔ ወንድ አላውቅም እንዴት ይሆንልኛል? ስትለው ሳለ ያለ ጥንተ አብሶ መወለዱን ለመናገር ምቹ ጊዜ ሳለው የመንፈስ ቅዱስን ማንጻት ተናግሮ ነው ያለፈው፡፡ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት መንፈስ ቅዱስ እንዳነጻት፣ «አንጺሖ ሥጋሃ ኀደረ ላዕሌሃ ሥጋዋን አንጽቶ በላይዋ ላይ አደረ፡፡» ቅዱስ ያሬድ «ገሊላዊት ሐቀፈተከ፣ ነፍሳ ቀደስከ፣ ወሥጋሃ አንጻሕከ ገሊላዊት ታቀፈችህ፣ ነፍሷን ቀደስህ ሥጋዋን አነጻህ» መ. ቅ.ገ. 438፡21 እያሉ ስለሚናገሩና አብዛኛዎቹ አባቶችም እንደ ዳዊትና ሰሎሞን የመሳሰሉት ወንጀለኞችና አመንዝሮች ስለነበሩ በየት አልፋ ነው እሷ ከጥንተ አብሶ ነጻ የምትሆነው ይላሉ፡፡ ለሁሉም የቅዱሳት መጻሕፍትንና የቅዱሳን አበውን ትምህርት ከዚህ ቀጥለን አቅርበናልና አንባቢ በጥንቃቄ አንቦ እንዲከተለው አደራ እንላለን፡፡

Thursday, June 14, 2012

እሪ… በይ ቤተ ክርስቲያን… እሪ እንበል ወገኔ…!!!

በ ከንፈ ገብርኤል (ምንጭ፥ ዐውደ ምህረት)
‹‹በኃይል ጩኽ፣ አትቆጥብ፣ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ…፡፡›› (ኢሳ 581)፡፡
የሚጮኹና ለመጮኽ ዕድል ያልተነፈጋቸው ሰዎች የታደሉ ወይም ዕድለኛ ይመስሉኛል፡፡ ቢያንስ ተናግረውና ጩኸው የልባቸውን አድርሰው እፎይ ለማለት ይችላሉና፡፡ በእርግጥ ሰሚ ጆሮ በሌለበት ቢጮኽ ድካም እንጂ ምን ትርፍ አለ? ብለው የሚከራከሩም ባይጠፉም፤ ቢሆንም… ቢሆንም መጮኽ ግን ደግ ነው እንላለን፡፡ በእርግጥ በዚህች አጭር ጹሑፍ በመጠኑ ለመዳሰስ የፈለግነው የጩኸት ዓይነት ከንቱ፣ ተራና ሰሚ ጆሮ የሌለው ሳይሆን ወደ ጸባዖት የሚደረግ ቅዱስ ጩኸት… አዎን… ቅጥሩን ለማፍረስ፣ ኢያሪኮን ለመናድ ብርቱ ኃይል ስላለው ልዩና ቅዱስ ጩኸት ጥቂት ነገሮችን ለማለት ነው፡፡

Tuesday, June 12, 2012

ይድረስ ለመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሽፈራው ዴንቨር ኮሎራዶ - ክፍል ሁለት

ባለፈው መልእክቴ ያቀረብሁለዎት አስተያየት ይድረስዎት አይድረስዎት አላውቅም። እስከ አሁን ድረስ መልስ ስላላገኘሁ ስሕተትዎንም ሊያርሙ ባለመቻልዎ አስተያየቴን እቀጥላለሁ።
የእግዚአብሔርን የአምላክነት ሥራ ለመላእክትና ለሌሎች ፍጡራን እየሰጡ ምስጋናውን ለማጋራት ወይም ለመንጠቅ እየተሸረበ ያለውን ሴራ ከማጋለጥ ወደ ኋላ አልልም። ቤተ ደጀኔ በሚለው ብሎግዎ ላይ የሚያስተላልፉትን የስሕተት ትምህርት ቢያርሙ መልካም ነው፤ አለባለዚያ በዚህ ምድር ምንም ባያገኝዎት በክርስቶስ የፍርድ ዙፋን ፊት ግን ቀርበው ይጠየቁበታል። ጌታ «በእኔ ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል የወፍጮ ድንጋይ ባንገቱ ታሥሮ ወደ ጥልቁ ቢሰጥም ይቀልዋል» ያለውን የማያልፍ ቃል መፍራት ጥበብ ነው። በእኔ ከሚያምኑ አለ እንጂ በሚካኤል ከሚያምኑ አለማለቱን ልብ ይበሉ።እርስዎ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑትን ምእመናን እያስኮበለሉ(እያሰናከሉ) በመላእክትና በፍጡራን እንዲያምኑ እያደረጉ ነው።

Monday, June 11, 2012

“በረከታችሁም” ሆነ “ውግዘታችሁ” ማንንም አያድንም አይገድልምም!

በዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
Read in PDF
በትናንቱ ዕለት በምዕራቡ ዓለም የሰዓት አቆጣጠር ከለሊቱ 12: 00 (pm) ይሆናል (በሀገር ቤት የሰዓት አቆጣጠር ማለዳ መሆኑ ነው) ወደ አገር ቤት ስልክ መትቼ ነበር። የረጅም ዘመን ትውውቅና ወዳጅነት አለን ከትውውቅም ያለፈ የአባትነትና የልጅነት ያክል የጠበቀ ግኑኝነት ካለን አንድ የዕድሜ ባለፀጋ፣ የመጻህፍት አዋቂ፣ የሲኖዶስ አባልም የሆኑት አባት (ሊቀ- ጳጳስ) በስልክ ተገናኝተን “አውግተን” ነበር። ስልክ የመደወሌ ምክንያት ለሰላምታ ነው። መንፈስን የሚያሳርፍ መንፈሳዊ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላም “ጨዋታ ጨዋታን ያመጣዋል” እንደሚባለው አገልግሎትን በተመለከተ አንዳንድ ነገሮች ስናነሳ ያመራነው ወደ ቤተ-ክርስቲያናችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ነበር። አንስተን ከተነጋገርንባቸው ዓበይት ቁምነገሮች መካከል እጅግ የገረመኝና ያሳዘነኝ በመጨረሻው ዕለት በመጨረሻዋ ሰዓት በጥቂት የሲኖዶሱ አባላት ተከሰተ ሲሉ ዝቅ ባለ ድምጽና በስብራት ያወጉኝን በጥቂቱ ለንባብ በሚያመች መልኩ ላካፍላችሁ ወደድኩ።

Sunday, June 10, 2012

ኢትዮጵያ ግብረሰዶምንና አራማጆቹ ምዕራባዊያንን አወገዘች !ምንጭ፦ ደጀ ብርሃን

‹‹
ትልቁ ሀብታችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ነው›› አቡነ ጳውሎስ

 
ሪፖርተር ጋዜጣ፤ሰኔ 10/2012 -ትናንት በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ‹‹ግብረሰዶምና ተያያዥ ማኅበራዊ ቀውሶች›› ላይ ለመነጋገር በተጠራው አገራዊ ኮንፈረንስ የተገኙት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፓርላማ አባላት፣ ወጣቶችና ሌሎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ‹‹ግብረሰዶምንና ግብረሰዶም የሚያስፋፉ ምዕራባዊያንን›› አወገዙ፡፡ በዚሁ ታሪካዊና አንገብጋቢ በተሰኘው አገራዊ ኮንፈረንስ ላይ 2,000 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ አምስቱ ዋና ዋና የሃይማኖት ተቋማት የኦርቶዶክት ተዋህዶ፣ የእስልምና፣ የካቶሊክ፣ የወንጌላዊት መካነ ኢየሱስና የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ያወጡትን የግብረሰዶማዊነት የተቃውሞ መግለጫ በአንድ ድምፅ እንደግፋለን ብለዋል፡፡ ግብረሰዶማዊነትን ካልተቀበላችሁ በማለት የሰብዓዊ መብት ጥያቄ የሚያነሱና ዕርዳታ እንከለክላለን ለሚሉ የምዕራብ አገሮችም ‹‹ዕርዳታቸው በአፍንጫችን ይውጣ›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የሃይማኖት ተቋማትን በሙሉ ወክለው ጉባዔውን በፀሎት የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ሕግ ሳይጻፍ ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ትውውቅ ነበራቸው፤ የዛሬ ሳይንቲስቶችም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ መሆንዋን ይናገራሉ፤›› በማለት በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች በሙሉ እርስ በርስ ተረጋግጠዋል፤ ብቸኛ ነፃ አገር ኢትዮጵያ ነች ብለዋል፡፡ ‹‹አሁንም የተረገጡትና የማንነት ቀውስ ያለባቸው ወገኖች ተናገሩ ብላ የምትሰማ አይደለችም፡፡ ባህላችን አልተለወጠም፣ ታሪካችን አልተቀነሰም፣ ማንነታችን አልተበረዘም፤ እንዲሁ ዝም ብለን የምንለወጥ አይደለንም፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ንግግራቸው በከፍተኛ ጭብጨባ የታጀበው አቡነ ጳውሎስ፣ በተለይ የግብረሰዶማውያንን መብት ካላከበራችሁ ዕርዳታ እንከለክላለን ለሚሉት፣ ‹‹ማንም ይሁን ማንም ታላቅነቱና ሀብታምነቱ ለራሱ ነው፡፡ እኛን ዝም ብሎ ድሆች አድርጎ አልፈጠረንም፤ ትልቁ ሀብታችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ነው፡፡ ሕዝባችን በእግዚአብሔር እምነት የሚኖር ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አዘጋጅ ድርጅት ‹‹ዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ›› ፕሬዚዳንት / ሥዩም አንቶንዮስ ባቀረቡት ጥናት መሠረት፣ የግብረሰዶም ድርጊት ምንጭ የአስተዳደግ ችግርና ማኅበራዊ ቀውስ ነው፡፡ ሆኖም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንና ሌሎች ምዕራባዊያን፣ የአፍሪካ መሪዎች የግብረሰዶማውያን መብት በአፍሪካ እንዲከበር አለበለዚያ ዕርዳታቸውን በመቋረጥ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆናቸውን የመሪዎቹን የተለያዩ ጊዜያት ቀጥታ ንግግር በማሰማት በማስረጃነት አቅርበዋል፡፡  የተመድ ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን ጭምር ስብሰባው በተደረገበት በዚያው የስብሰባ አዳራሽ የአፍሪካ መሪዎች የግብረሰዶማያውያን ሰብዓዊ መብት እንዲያከብሩ መጠየቃቸውን አስታውሰው፣ ምዕራባዊያን የራሳቸው የማንነት ቀውስ የፈጠረውን ቆሻሻ ባህል በአፍሪካ ለማስፋፋት ከዕርዳታ ጋር ማያያዛቸው አሳፋሪ ተግባር ነው ብለውታል፡፡ በጉዳዩ ላይ ምርምር አደረግን ያሉ የጠቃቀሱዋቸው አንዳንድ ምሁራን ባዮችም፣ ከሞላ ጎደል ራሳቸው ግብረሰዶማውያን ሆነው ከመገኘታቸውም ባሻገር፣ ከሃይማኖትም ሆነ ከተፈጥሮ ሕግ አንድም ተጨባጭ መረጃ አለማቅረባቸውን አውስተዋል፡፡ የአስተዳደግ ችግር፣ የፆታ ማንነት ቀውስ፣ ወሲባዊ ጥቃትና ሌሎችን እንደ መንስዔ የጠቃቀሱት / ሥዩም፣ ግብረሰዶማውያን ይጠቀሙባቸዋል ያሉዋቸውን አንዳንድ አስነዋሪ ድርጊቶችን አሳይተዋል፡፡ በቀዶ ሕክምና ዕርዳታ በፊንጢጣቸው ገብተው አንጀታቸው ውስጥ ቆይተው የተገኙ አደገኛ ነገሮችን አሳይተዋል፡፡ ‹‹ግልጽ የውጭ የባህል ወረራ ነው ያሉት›› / ሥዩም፣ ግብረሰዶማዊነት ኤችአይቪ/ኤድስን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎችና የሥነ ልቦና ቀውስ እንደሚዳርግ አብራርተዋል፡፡  በማጠቃለያቸውም፣ ‹‹አንዴ በዚህ ችግር የተጠቁ ኢትዮጵያዊያንን በምክር መርዳት አለብን፤›› ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ በተረፈ ግን፣ ‹‹ኢትዮጵያ የግብረሰዶም መቃብር እንጂ መፈልፈያ አትሆንም›› ብለዋል፡፡ ‹‹ችግሩ የዓለም ሕዝብ አደጋ ነው፤ ኢትዮጵያ ግን ፈውስ አለ ብለው የሚመጡባት አገር ትሆናለች፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹
ሰው ከሕግ በታች የሚኖረው በሕይወት ካለ ብቻ ነው›› ያሉት አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹የተፈጥሮ ሕጋችንና የተከበረ ባህላችን ይጠበቅልን ነው የምንለው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የተከበረውን የሰው ልጅ ክብር የሚነካ ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲገታ እንፈልጋለን፡፡ የተሳሳቱ ካሉም እኔና እኔን መሰል በአስተማሪነት ላይ የምንገኘው ነው የምንወቀሰው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በዓለም ላይ ያሉትን እንጨቶችም ሴትና ወንድ አድርጎ ነው የፈጠራቸው፡፡ አለበለዚያ እንዴት እንራባለን?›› በማለት በሰው ልጅ ላይ የመጣ አደጋ መሆኑን አሳስበዋል፡፡ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ማኅበርን ወክለው የተገኙት አባት አርበኛ በበኩላቸው፣ ‹‹ወደ ምድር እንድንመጣ የፈቀደው እግዚአብሔር እኛ ሳንጠይቀው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ ይኼን ቅዱስ ቃል ሊሽሩ የመጡ ሰዎች ራሳቸው ከየት እንደመጡ ማግኘት አቅቶአቸዋል፤›› በማለት፣ ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የማይቀበለው ርኩሰት ነው›› ብለው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወረራውን እንዲታገለው አሳስበዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር የተወከለ የአመራር አባል፣ ‹‹የምዕራባዊያን ረዥሙ እጅ ባህር ተሻግሮ እዚህ ደርሷል፡፡ ይህንን ዓይነት ቆሻሻ ባህል የሚሸከም ህሊና ግን የለንም፡፡ ጉዟችንን የሚያቀጭጭ ነቀርሳ ነው፡፡ በሕጋችንም ወንጀል ነው፤ በባህላችንም ነውር ነው፤›› ብሏል፡፡ ሌላ ወጣት ተናጋሪም፣ ምዕራባዊያን ኃጢአት ሥሩና ዕርዳታ እንስጣችሁ ከሆነ እያሉን ያለው፣ ‹‹በኃጢአት የመጣ ገንዘብ በአፍንጫችን ይውጣ›› የሚለውን ንግግሩ በከፍተኛ ጭብጨባና ተቀባይነት የታጀበ ነበር፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ወክለው የመጡ አንድ ተናጋሪም፣ የአውሮፓ ፓርላማ ኅብረት እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ በአጀንዳነት ለመነጋገር ብዙ ጊዜ ግፊት ማድረጉን ጠቅሰው፣ የአፍሪካ-ካሪቢያንና-ፓስፊክ ፓርላማ ኅብረት ግን መቃወሙን ገልጸው፣ ‹‹ከዕርዳታ ጋር የምታያይዙት መብት ከሆነ ዕርዳታችሁ በአፍንጫችን ይውጣ፣ አንፈልግም፤›› ብለናቸዋል የሚለውን የወጣቱን ንግግር ደግመው አረጋግጠዋል፡፡ ተሰብሳቢዎች የመንግሥት አቋም የሃይማኖት መሪዎች ያወጡት ጠንካራ አቋም መሆኑ አስደስቶአቸዋል፡፡ የፓርላማ አባሉም ከፍተኛ ጭብጨባ ተደርጎላቸዋል፡፡ ተሳታፊዎቹም በዚህ በኩል ለግብረሰዶም ያላቸውን ተቃውሞና ውግዘት ገልጸዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ በመጨረሻ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ሁሉም በአቡነ ጳውሎስ የቀረበውን የአቋም መግለጫ ደግፈው፣ መንግሥት በውጭ ሰዎች በጉዲፈቻ በሚያድጉ ልጆች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ ድርጊቱን እንዲያወግዝና የተሳሳቱትንም መምከርና ማረም እንዳለበት፣ ሕዝቡም ከዚህ ወረራ ራሱን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡   አንድ ስሙን ያልጠቀሰ ወጣት በዘመዱ በስድስት ዓመቱ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ 20 ዓመታት ያህል ለግብረሰዶምነት መጋለጡን፣ አሁን ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር እንደሚኖር ገልጾ፣ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ አሁን ወደ ጤነኛ ሕይወቱ ለመመለስ በትግል ላይ መሆኑን ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ ችግር የተጠቁ ኢትዮጵያዊያን ግብረሰዶማውያን የሚረዳቸው ካገኙ ከችግሩ ለመውጣት እንደሚፈልጉ ተናግሯል፡፡