Thursday, June 14, 2012

እሪ… በይ ቤተ ክርስቲያን… እሪ እንበል ወገኔ…!!!

በ ከንፈ ገብርኤል (ምንጭ፥ ዐውደ ምህረት)
‹‹በኃይል ጩኽ፣ አትቆጥብ፣ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ…፡፡›› (ኢሳ 581)፡፡
የሚጮኹና ለመጮኽ ዕድል ያልተነፈጋቸው ሰዎች የታደሉ ወይም ዕድለኛ ይመስሉኛል፡፡ ቢያንስ ተናግረውና ጩኸው የልባቸውን አድርሰው እፎይ ለማለት ይችላሉና፡፡ በእርግጥ ሰሚ ጆሮ በሌለበት ቢጮኽ ድካም እንጂ ምን ትርፍ አለ? ብለው የሚከራከሩም ባይጠፉም፤ ቢሆንም… ቢሆንም መጮኽ ግን ደግ ነው እንላለን፡፡ በእርግጥ በዚህች አጭር ጹሑፍ በመጠኑ ለመዳሰስ የፈለግነው የጩኸት ዓይነት ከንቱ፣ ተራና ሰሚ ጆሮ የሌለው ሳይሆን ወደ ጸባዖት የሚደረግ ቅዱስ ጩኸት… አዎን… ቅጥሩን ለማፍረስ፣ ኢያሪኮን ለመናድ ብርቱ ኃይል ስላለው ልዩና ቅዱስ ጩኸት ጥቂት ነገሮችን ለማለት ነው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ አሉ አንዳንዶች እንደ መረግ በከበደ ዝምታቸው ዓለምን የሚያደባልቅ፣ ጠላቶቻቸውን መውጫ መግቢያ የሚያሳጣ፣ ወደረኞቻቸውን የሚያስጨንቅና እረፍት የሚነሳን ጩኸትን የሚጮኹ፡፡ ዝምታቸው የፍርሃት ደመናን፣ የድንቁርናን ጨለማ የሚገፍ፣ የእውነትን ጠላት የሚያሳድድ… ስለ እነዚህ በታላቅ ዝምታቸው ብርቱውንና ኃይለኛውን ጩኽት ስለሚጮኹ ጀግኖች ሳስብ በአንድ ወቅት አሁን በሕይወት የሌለሉ አረጋሽ የተባሉ ገጣሚና ባለቅኔ የቋጠሩት ስንኝ ወደ አእምሮዬ መጣ፡-
እዬዬም… ጩኸት ነው፣
ዋይ ዋይም… ጩኸት ነው፣
እሪታም… ጩኸት ነው፡፡
ይሄ ሁሉ ሲጮኽ ዝም በል ይሉታል፣
ዝ-ም-ታ… ሲጮኽስ እንዴት ያደርጉታል?!
የራማው ጩኸት… የራሄል እንባ ከመቅደሱ አድማስ አድማሳትን ተሻግሮ፣ አየር አየራትን ሰንጥቆ ወደ ጸባዖት፣ ወደ ልዑሉ መንበር ወደ አርያም እየነጎደ፣ እየተረጨ ነው፡፡ አባሽ ያጡ እንባዎች፣ ሰሚ ያጡ ጩኸቶች ዛሬም ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር በቅድስናው ስፍራ እንደ ጅረት ያለማቋረጥ እየፈሰሱ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጩኽቱን ተቀምቶ ታፍኖና ተረግጦ ያለው ወገናችን ደግሞ በዝምታው የውስጡን ብሶት የልቡን ጩኸት፣ እሪታ ወደ ጸባዖት ወደ አምላኩ እያሰማ ነው፡፡ በመጮኽም ሆነ በዝምታው የሰው ያለህ… የፍትህ ያለህ በሚል የተጮኽው ጩኸት፣ እሪታና ዋይታ በመቅደሱ አደባባይ ነግሶአል፣ በጎዳና ጩኸት፣ በየመንገዱ ማዕዘን፣ በፍርድ አደባባይ የብዙዎች ጩኸት ተበራክቷል፡፡
ለጩኸታችን፣ ለእሪታችንና ለዋይታችን… መፍትሔ አመላካች ናቸው ብለን ተሰፋ ያደረግናቸውና የተማጸንናቸው ቤተ ክርስቲያንና አባቶቻችን ጩኸታችን ሊጮኹልንና ጩኸታችንን ሊሰሙልንና ሊያሰሙልን ቀርቶ እርስ በርሳቸው በራሳቸው ጩኸት ውስጥ ላይደማመጡ ተውጠው የዘረኝነቱ፣ የጥላቻው፣ የመወጋገዙና የመፈራረዱ እኩይ ጩኸት በአባቶቻን መካከል ያለቅጥ ነግሶ እኛ ልጆቻቸው በእፍረት ተከድደናል፣ በእፍረት አቀርቅረናል፡፡
ቅዱሱን ጩኸት የሚያጯጩኹን፣ በፊታችን የተጋረጠውን የኢያሪኮን ቅጥር ይናድ ዘንድ በመንፈሳዊ ወኔና ጀግንነት ጀግነው የሚያጀግኑን ኢያሱዎች፣ በርቱ ልጆቻችን የሚሉን አባቶች ቁጥራቸው ቢመናመን አድራሻቸው ቢሰወርብን ‹‹እሪ በይ ቤተ ክርስቲያን፣ እሪ በል ወገኔ …!›› ለማለት ወደድን እንጂ እንዲሁ ደርሶ የመጮኽ አባዜ ተጣብቶን አይደለም እንጩኽ እሪ እንበል ማለታችን፡፡ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ምነው ዓይኔ የእንባ ጎርፍ ፈሳሽ ምንጭ በሆነ ነው ያለው ያ የኢየሩሳሌም ጥፋት፣ የእግዚአብሔር መቅደስ መደፈርና መቃጠል፣ የሀገሩ ውርደት የሕዝቡ ጉስቁልና የእግዚአብሔር ቅዱስ ከተማ መፍረስ፣ የሕዝቡ ምርኮና ፍልሰት ነፍሱ ድረስ ዘልቆ እረፍት የነሳው ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ፡፡
ዛሬም እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ኡ…ኡ…ኡ የሚያስብለን እሪ የሚያሰኝ የእንባን ምንጮችን ሁሉ የሚነድል ግፍና በደል በእግዚአብሔር ቤት በእጅጉ ተንሰራፍቷል፡፡ የግፍ፣ የመከራ፣ የድረሱልን ጥሪ፣ የሰው ያለህና የፍትሕ ያለህ… ጩኸት፣ ዋይታና እዬዬ በየአቅጣጫው በዝቶአል፡፡ ጩኸት፣ ዋይታና እዬዬ በፍርድ አደባባይ፣ ጩኸት በጎዳና፣ ጩኸት በቤት፣ ጩኸት በጓዳ፣ ጩኸት በድሆች መንደር፣ ጩኸት በቤተ ክርስቲያናችን፣ ጩኸት ዋይታና እዬዬ የተቀደሰ መቅደሱን አደባባይ የሐዘን ከል አልብሶታል፡፡
ማን አለ እንደ እኛ በመከፋፈል በመለያየት እርስ በርስ በመወጋገዝ በመረጋገም በመጠላላት ዓለምን ጉድ ያሰኘ፡፡ የኢትዮጵያ ሲኖዶስ፣ የአሜሪካው ሲኖዶስ፣ የገለልተኛ… በዓይነ ቁራኛ የሚተያዩ በስድብና በእርግማን ሠይፍ የሚተራረዱና የሚተላለቁ የሚመስሉ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆኑ ማኅበራትና ቡድኖች ብዛት እና ዓይነት ለሚታዘብ ለጉድ ነው፡፡ እርስ በርሳችን በመነቃቀፍና በመለያየት ማን ይመስለናል?… ማንስ ያክለናል?…፤ በዚህ ሁሉ ውስጥ የነገ መድረሻችን ሲታሰብ ደግሞ ልብ በእጅጉ ይደክማል፣ መንፈስም ይዝላል፡፡ ነገ ደግሞ ምን ሊመጣ እንደሚችል ማን ያውቃል!!!!!
አባቶቻችን ለልጆቻቸው ፍቅርን፣ ምህረትንና ተስፋን ለተራበው ሕዝባቸው የሚያበረታና የሚያጽናና መልእክት ይዘውልን ለመምጣት ደክመዋል፤ እናም በራሳቸው ጉዳይ ተጠምደው የሌት ተቀን አሳባቸው የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው የደመወዝ ጭማሪ፣ ሞዴል መኪና፣ ምርጥ ሕንጻ ስለመገንባትና የአውሮፓ ወይም የአሜሪካዊ ዜግነት የማግኘት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱም ይህን ምድራዊ አጀንዳ በመስማትና በመዳኘት በስሞታና በአሉባልታ ሲናጥና እንደ ሽንብራ ሲንገረገብ ሰንብቶ ያለአንዳች ዘላቂ መፍትሔ ይበተናል፡፡
በዚህ ሁሉ ሁከት፣ በዚህ ሁሉ ቀውስ መካከል ደግሞ ለንስሐ የሚያነቃን በፈረሰው ቅጥር በኩል በመቆም አቤቱ ለሕዝብ ራራ እያሉ በመጮኽ በመቅደሱ አደባባይ ተግተው ያተጉናል ያልናቸው አባቶቻችን ውሎ አዳራቸው ከቄሳር አደባባይ ሆኖብን ልባችን በእጅጉ አዝኗል፡፡ በዚህ ልባቸው የተከፋ፣ በአባቶቻቸው በእጅጉ ተስፋ የቆረጡና ያዘኑ፣ በቅዱስ መቅደሱ ክፋትና አመጻ በመንገሱ ኃዘናቸው ቅጥ ያጣ አንዳንድ ልጆቻቸውም በየብሎጉና በየድረ-ገጹ የአባቶቻቸውን በደልና እፍረት በአደባባይ በመገለጽ ላይ ናቸው፡፡
ልጆቿን ተመለሱ፣ ተመከሩ ብላ በፍቅር ለመቀበልና ለመገሰጽ አቅም፣ ጉልበትና ድፍረት ያጣች ቤተ ክርስቲያን ከገዛ ከአብራኳ ክፋዮች ጋር እየተቋሰለች፣ እየተዳማች፣ ገመናዋንና ኃጢአቷን በየአደባባዩ እየገለጠች ሌላ የውርደት ሌላ የእልቂት ታሪክ ለመጻፍ ደፋ ቀና እያለች ይመስላል፤ በበርካታ በተገፉ ልጆቿ ልብ ውስጥም የተሰወረው የበቀል ድማሚትም አንድ ቀን የፈነዳ ጊዜ ሊያደርሰው የሚችለውን ጥፋት ለሚያስብ ደግሞ ወዮልን ለእኛ የሚያሰኝ ነው፡፡ የልጆቿን ጩኸትና ዋይታ እና እሪታ ላለመስማት ‹‹የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ!›› ያለች እናት ቤተ ክርስቲያን ዛሬም በ21ኛው መቶ ክዘመን ማውገዝ ማስወገዝን፣ መውገር ማስወገርን፣ መለየትን ስራዬ ብላ የቀጠለች ይመስላል፡፡ ልጆቿ ነን የሚሉ ተቆርቋሪ መሳዮችም በሕይወት የሌሉና ለሀገራቸው ባለውለታ የሆኑ ሰዎች አስክሬናቸው እንኳን አርፎ እንዳይተኛ ይወገዙልን በሚል ስም ዝርዝራቸው ቀርቦ ውሳኔ ይሰጣቸው ዘንድ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡
መቼም ማውገዝ ማስወገዝ፣ መውገርና ማስወገር ለእኛ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ታሪካችን አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል ለመጥቀስ በቅርብ የታሪካችን ዘመን እንኳን በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በሃይማኖት ሰበብ ውግዘትና ውግረት ስለደረሰባቸው ወገኖቹ 20ኛው ክ/ዘመን የሀገራችን ጥቂት ምሁራን መካከል ቁንጮ የሆነው ወጣቱ ምሁር፣ ጸሐፊ፣ የኢኮኖሚ ተንታኝ የሆነው ፖለቲካል ኢኮኖሚስቱና የታሪክ ተመራማሪው ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ ‹‹የነጋድራስ ገብረ ሕይወት ሥራዎች›› በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፋቸው ላይ ገብረ ሕይወት በሀገሩ ያጋጠመውን ጉድ እንዲህ ሲል ትዝብቱን በአግራሞትና በትልቅ ቁጭት ውስጥ ሆኖ ይገልጻል፡-
. . . አንድ ልበ ብሩህ ያበሻ ሰው መሬት ትዞራለች ብሎ ቢያስተምር አሁን በቅርቡ በሀረርጌ በዳኛ ተይዞ አልነበረምን… አሁን በ19ኛው መቶ ዓመታት ከክርስቶስ ልደት በኋላ አልፈን ሃያኛውን መቶ ዓመት ስንጀምር አንድ ሰው የተዋህዶን ሃይማኖት ቢነቅፍ ካዲስ አበባ ገበያ ላይ በድንጋይ አልተወገረምን እስከዛሬስ ድረስሳ ወደ ሩቅ ሀገር ተሰደው ወደ አበሻችን ከሚመጡት ፈረንጆች ጥቂት ጥበብ ተምረው ያገራቸውን መንግሥት ሊጠቅሙ የሚፈልጉ ወንድሞቻችን ጵሮተስታንት፣ ካቶሊክም፣ መናፍቃን የሌላ መንግሥት ሰላዮች እየተባሉ ሲራቡ ሲከሰሱም እናይ የለምን የእንዚያም መከረኞች ስም ስንት ብለን እንቁጠር . . . ፡፡
አሰገራሚው ነገር እንደ ገና ከመቶ ዓመትም በኋላ እነዚሁ ሰዎች መጽሐፋቸው መወገዝ እነርሱም መለየት አለባቸው በሚል ስም ዝርዝራቸው ተጠቅሶ ውግዘት እንዲተላለፍባቸው አቤት የሚል ማኅበር በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን መከሰቱ ሌላ እንቆቅልሽ ሌላ ግርምትን የሚፈጥር ነገር ሆኖብናል፡፡ ይህን የጀመረውን የማውገዝና የማስወገዝ ዘመቻ ዓላማውንም ለማሳካት ይኽው ማኅበር ላይ ታች  እያለ በመሯሯጥ ላይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ትጥራንና እንነጋገር በእውቀትም ሆነ ያለ እውቀት ያጠፋነውም ስህተት ከተገኘብንና ከአባቶቻችን ትምህርት የተለየ ነገር ካስተማርን እንመከር እንገሰጽ በሚሉበት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማውገዝንና መለየት ምን የሚሉት አካሄድ እንደሆነም ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
በመሠረቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮና ስርዓት ውጭ የሚሄዱ ሰዎችም ሆኑ ማኅበራት ካሉ ልቅ መለቀቅ አለባቸው የሚል ጭፍን አቋም የለንም፤ ግን ማውገዝና መለየት የመጨረሻ እንጂ የመጀመሪያ አማራጭ ሊሆን አይገባውም፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲህ አልተነገረንም፣ አልተጻፈምም፡፡ የዘመናችን ጩኸትና እሪታ መሆን ያለበት አንገብጋቢው ጉዳያችንስ የትኛው ነው፣ ሌሎችን ስለማወግዝና ስለመለያየት ነው እንዴ… ስንት እሪ የሚያሰኘን ክፋትና አመጻ በእግዚአብሔር ቅዱስ መቅደስ በነገሰበትና ጆሮን ጭው የሚያደርግ ጉድ በሚሰማባት ቤት እንዴት ዝኆኑን ውጠን ትንኟን ለማጥራት እንዲህ ወደር የሌለው በሚመስል ግብዝነትና ፈሪሳዊነት ውስጥ ተዘፍቀን ራሳችንና ሕዝባችን እናታልላለን፡፡
መጮህ… ኡ…ኡ…ኡ…! ዋይ… ዋይ… ዋይ…! እሪ… እሪ…እሪ…! ማለት ካለብን ፍቅርን ስለማጣታችን፣ ስለመለያየታችን፣ ቅንና በጎ ኅሊና ስለማጣታችን፣ እስከ አንገታችን ስለተዘፈቅንበት የዘረኝነት የጥላቻና የመለያየት አባዜ እንጂ፣ መጮኽ ካለብን በቀቢጸ ተስፋ ተውጠው በጫትና በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ ተጠምደው ለቤተሰባቸውና ለሀገራቸው ሸክም ስለሆኑ፣ ስደትን ተስፋ አድረገው በእግር፣ በባሕር፣ በበረሃ እየተጓዙ የሞት ሲሳይ እየሆኑ ስላሉት በሺህ ስለሚቆጠሩ ወጣት ስደተኛ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እንጂ፣ መጮኽ እሪ ማለት ካለብን ፍርድን ፍትህን ስለተነፈጉ በኃጢአት ባርነት ቀንበር ስር ስለሚማቅቁ ሕዝቦች እንጂ… ኡ ኡ ኡ ማለት ካለብን ለአባቶቻችን ፍቅር፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ለሀገር ሰላም፣ ለወገን ብልጽግና፣ ለገዢዎችና ለመንግሥታት ከአርያም የሆነ ማስተዋልና ጥበብ እንዲሆንላቸው መጮኽ አለብን እንጂ እንዴት በከንቱ ጩኸት በባዶ እሪታ ጉልበታችንን እንፈጃለን፣ ኃይላችንን እናባክናለን፡፡
ቅዱሱን ጩኸት ከመጮኽና ከመማለድ የሚበልጠው ጩኸት የሚበልጠው እሪታስ … የቱ ይሆን የተወደዳችሁ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እኛ ግን በስተመጨረሻ አንድ ነገር ለማለት እንወዳለን ቅዱሱን ጩኸት በአንድነት ለመጮኽ አንድከም፣ እንዛል… እግዚአብሔር የሕዝቡን ጩኸት የሚያደምጥ ቅዱስ፣ የተፈራ፣ በምድር ላይ ፍርድን፣ ፍትህንና ምሕረትን የሚያደርግ፣ እጅግም የሚራራ አምላክ ነውና!!!
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ያስብ!

10 comments:

 1. ምን ይሁን ነው የምትሉት? ሲኖዶስ ሲወስን ለረጅም ጊዜ አስጠንቶ በዝርዝር ተወያይቶበት ሰዎቹ ያስተማሩት ትምህርት ሆነ ተብሎ ቤተ ክርስትያንን ለማጥቃት መሆኑን አረጋግጦ ነው፡፡ መጣራት የሚገባቸው ሰዎችን በቀጣይ ተጣርቶ እንዲቀርብ አዟል፡፡ ከዚህ የበለጠ የብልህ አካሄድ ሊኖር አይችልም፡፡ የተወገዙት ሰዎቹ የጻፏቸው መጻህፍት እና ያስተማሩት ትምህርት ሆነ ተብሎ ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ልጆቿን በተሳሳተ ትምህርት ለመውሰድ በተደራጀ መልኩ መሆኑን በማስረጃ የተረጋገጠ ስለሆነ ተወግዘዋል፡፡ ከዚህ በላይ ለነዚህ ሰዎች ጊዜ መስጠት የጥፋት ጊዜያቸውን ማራዘም በመሆኑ ውሳኔው ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ሰዎች ላይ በሮቿን አልዘጋችም፡፡ እንደ አማኝ በንስሃ መመለስ ይችላሉ፡፡ እንደ መምህር ግን ……፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ውንድሜ መጀመሪያ እውነታውን ለማወቅ ምን ያደረከው ጥረት አለ? ዝም ብለህ የተሰማህን ብቻ ለምን ታወራለህ? ሁኔታውን በዝርዝር ብታውቀው ከጸሀፊው ጋር መቶ በመቶ ትስማማ ነበር? ሲኖዶሱ መቼ ነው ረዥም ጊዜ ያስጠናው? ሊቃውንት ጉባኤው ሁሉን ሊያነጋግር ሲገባው ከተወገዙ ማህበራት አንዱንም ሳያነጋግር ከተወገዙት ግለሰቦችም አንዱንም ሳነጋግግ እንዲሁ እደል በደመ ነብስ የወሰነው? አባሰረቀንና ጌታቸው ዶኒን እንጂ ሌላ ማንን አነጋገረ? እንዲህ ያለው አሰራር እንኳን በመንፈሳዊ ቦታ በአለማዊ ፍርድ ቤትስ ይደረጋል? በዝርዝርስ መቼ ተወያየበት? በሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ እንኳ አረ የተከሰስንበት ጉዳይ አልታየልንም አባቶቼ አነጋግሩኝ ብለው ደብዳቤ ያስገቡ ሰዎችን እንኳን ሲኖዶሱ እናንተን ከማነጋገር ሞተን ብንገኝ አይደለም እንዴ ያሉት? እነዚህን አባት ለማለት እንዴት ይቻላል?እንኳን ብልህ አስመሳይ ፖለቲከኛ እንኳ ከዚህ የተሻለ አካሄድ ያቃል። አንተም ወይ ጉዳዩ አልገባህም አሊያም ደግሞ አውቀህ ተጨፍነሃል። እና ነገሩን እንደገና ለማጣራት ሞክር፡፡ አዎ እንደ ቤተክርስቲያኒቱ አስተምሮ ሊወገዙ የሚችሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል። የእነርሱም ጉዳይ ቢሆን ግን በአግባቡ ተጣርቶ ተጠይቀውበት ምላሻቸው ተሰምቶ ነው እንጂ እንዲያው በደመ ነብስ ሊሆን አይገባም። ግን ከተወገዙት መካከል አንዳንዶቹ ግን በፍጹም ሊወገዙ የሚገባቸው አይደለም። ከመቼ ወዲህ ነው ተግሳጽ የሚያስወግዘው? ከመቼ ወዲህ ነው እርዳታ መስጠት የሚያስወግዘው? ነው ሲኖዶሱ እራሱ ሰው በምን ምክንያት ሊወገዝ እንደሚችል የሚያውቅ አንድም አባት የለበትም ማለት ነው? ሰው የዶግማ ስህተት ሲኖርበት ብቻ ነው መናፍቅ ሊባል የሚችለው። ከዛ ውጭ ያለ ነገር ግን እንደ ሃይማኖት ጉዳይ እንኳን ሊታይ አይገባም። ስለዚህ እሪታው ትክክል ነው። ጩኸቱ ተገቢ ነው። ከዛ በላይም ግን መሆን ነበረበት ሲኖዶሱ በይፋ በፈጸመው የአካሄድ ስህተት ቤተክርስቲያኒቱ ያለችበትን የውድቀት ደረጃ ያሳየ ነው። ልብ ካላቸው የሲኖዶሱ አባለት ንስሀ ገብተው ትክክለኛ አካሄዱን ተከትለው የሚተወውን ይተዉ የሚወገዘውንንም ያውግዙ። አሊያ ቃሉ እንደሚል ተወጋዦቹን ሳይጠይቁ ሳይመክሩ ሳያስመክሩ ስላወገዙ በሰማይ መንግስት ፊት አይቶ በማያዳለው ጌታ ችሎት መጠየቃቸው አይቀርም። ማኅበረ ቅዱሳንን ለማስደሰት ብቻ በከስ ወረቀቱ ላይ ተመርኩዘው ማውገዛቸው ወገኝተኝነታቸውንና የሁሉ አባት መሆን የማይችሉ ደካሞች መሆናቸውን ያሳየ ነው። ማውገዝ ቢኖርባቸው እንኳ አካሄዳቸው እንደ እግዚአብሔር ቃል ትክክለኛውን አካሄድ ስላልጠበቀ ውግዘታቸው አይሰራም። በእግዚአብሔር ፊትም ተቀባይነት የለውም።

   Delete
 2. አጻጻፉ ለአባ ሰላማ አዘጋጆች ትምህርት ሰጭ ነው ፡፡ የቤተ ጳውሎስ ድረ ገጽ ከሚያዘጋጁት የቅሬታን ስሜት መግለጫ ጽሁፍ በብዙ መልኩ ይመሳሰላል ፡፡ አቤቱታው ማንንም በጎሣና በገጽ ፣ በሥልጣንና በዕድሜ ፣ አልከፋፈለም ፣ ግለሰቦችንም ለማጥቃት በማለት ፣ አራትና አምስት አባቶችን ለይቶ አላብጠለጠለም ፤ አልኰነነም ፡፡ አጠቃላይ መልዕክቱን በሚገባ እንደምንረዳ በማድረግ አስፍሯል ፡፡

  በተረፈ "ልባቸው የተከፋ፣ በአባቶቻቸው በእጅጉ ተስፋ የቆረጡና ያዘኑ፣ በቅዱስ መቅደሱ ክፋትና አመጻ በመንገሱ ኃዘናቸው ቅጥ ያጣ አንዳንድ ልጆቻቸውም በየብሎጉና በየድረ-ገጹ የአባቶቻቸውን በደልና እፍረት በአደባባይ በመገለጽ ላይ ናቸው፡፡" ይህንን ገልጾ ሃይ አለማለቱ ቅር ብሎኛል ፡፡ ምናልባት ወዳጆቹን ላለማስከፋት በማሰብ ይመስለኛል ፡፡

  ሌላም ቦታ ላይ "ወንድሞቻችን ጵሮተስታንት፣ ካቶሊክም፣ መናፍቃን የሌላ መንግሥት ሰላዮች እየተባሉ ሲራቡ ሲከሰሱም እናይ የለምን" ፤ ይኸኛውን ቃል ያገኘው ከሌላ ጸሐፊ ቢሆንም ያለውን ሃቅ ከታሪክ መዛግብት አፈላልጐ አንድ ማለት ነበረበት ፡፡ አይደሉም እንዳይባል ጸሐፊዎች በጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ መጽሐፍት ምን ሲሠሩ እንደ ነበር አስነብበውናልና አይካድም ፡፡

  የሃገራቸውን ህዝብ በሙሉ አጥምቀው ክርስቲያን አድርገው ሳይጨርሱ ነው ፣ በአገራችን ክርስትና በተቀበለው ህዝብ ላይ ዳግም ክርስትናን ለመስበክ የዘመቱት ፡፡ ወንጌል ያልደረሰውን ወገን እየመረጡ አልነበረም ግልጋሎት የሚሰጡት ፡፡ ይኸ አሁንም የምናየው ግልጽ ችግር ነው ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን የተፈጠረው ሙግትም ተውን እኛ ክርስቲያኖች ነን ከማለት የተነሳ ነው ፡፡ ለክርስትና እምነት መስፋፋት የሚል ርዕስ ብቻ ቢሆን አጀንዳቸው በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚገኙት አገሮችን ሁሉ አልፈው /ዘለው/ መምጣት አልነበረባቸውም ፡፡

  አሁንም እንኳን የእናት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማና ቀኖናዋን ለመናድ ከመታገልና ከመናቆር በዳር አገር ለሚኖረውና ክርስትና ላልደረሰው ፣ ወንጌልን ለመማር ፣ ለመጠመቅና ክርስትናን ለመቀበል ፣ ዓይኑን ወደ ተማረው ወገን ለሚያነሳው ህዝብ ፣ ለመድረስ ብንታገል ለእግዚብሔር መንግሥት እጅግ መልካም ሥራ ሠርተን ባለፍን ነበር ፡፡ አዝናለሁ ከስሜት ሆኘ ሳላውቅ ጭብጥ ለቀቅሁ ፡፡

  በተረፈ ግን ቆንጆ የአቤቱታ አገላለጽ ስልት ነው ፡፡

  ReplyDelete
 3. ጩኸቱ መልአካም ነበር ዳሩ ግን አስጯሂ ደስ እንዳይለው በቆይታ የሃይማኖት ጎራዴ መዞ የጸሎት ሰይፍ ይዞ መቃወም፤ እናም መቃወም እንዳይገኙ ቢገኙም እንዳይጎዱ ሆኖ
  ነው፤ክፍፍሉም ዘንድሮ ሳይሆን ድሮ ነበር እነሱም ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ ደቂቀ ተ/ሃይማኖት፣ ደቂቀ ኤዎስጣቴዎስ በሚል ሥያሜ ሲናሸሩና ሲራሸኑ ነው ያለፉት ያን ጊዜስ ምን ተገኘ አሁንስ ምን ሊገኝ? አንደኛው ወገን ፈሪሳዊ ሁለትኛው ወገን ሰዱቃዊ እየተባባሉ
  ስም እየተሰጣጡ ራሳቸውን ከመበጥበጥና ሕዝብን ከማበጥ በስተቀር ምንም የበጎ ሥራ ልምላሜ አበባና ፍሬ አያሳዩም ብቻ እርሱ ፊቱን ይመልስ!

  ReplyDelete
 4. The comment is factual and interesting! The writer desrves appreciation for expressing the very deep concerns of all concerned followers of the Church. However, what is so paradoxical or puzzling about dealing not only with our religious but also our secular challenges is when it comes to the meaningful and strong connection between our rhetorical abilities and our practical performances . For example, the writer of comment above have just told us about the very self-evident story arround the Church and the lack of genuine commitment from religious leaders and other clergymen . I did not come across any sensible and desirable recommendation on the question of what is to be done. I strongly argue that simply telling the horrible stories which have become the day-to-day experiences of the innocent people of Ethiopia , talking about talks with all kinds of jargonized expressions , making well-selected bibilical or philosophical qoutations or citations ,and the tradition of blaming and countr- blaming will never make any meaningful difference. It is only when we come up with a genuine undestanding of our problems as well as ideas about how to solve our common problems that we would be able to make a difference.

  May God help us!

  ReplyDelete
 5. yetewegezachihut einanite nachihu yebetekirisitiyan lijoch mingizem bihon eiyetemekeru kesihitetachew eindimelesu yideregal einanite gin yebaeidin metif amelekaket yeweresachihu silehone bitimekerum atimelesum silezih kebetekirisitiyanitu bewugizet meleyet new yalebachihu abatachihu diyabilos wede nisiha einiditimelesu silemayifelig beakuwamachihu eiditisenu aderegachihu

  ReplyDelete
 6. Melkam newu hulun le egezeabeher eyeset mechoh ketechal.
  keleb yehon chuhet amelak yesemewal.chuhetachen gin wed semayawe amelak mehon alebet. wedet mchoh endaleben mawek tiru newu.andenet betefa bet selam be tatabet gize wed serawet geta amelak mecho yasefelegal.

  ReplyDelete
 7. ክንፈ ገብርኤል ዕድሜዎን ያርዝምልን! በእውነት ድንቅ መልእክት ነው ያስነበቡን ምናለ እንደእነዚህ ዓይነቶቹን የቤተ ክርስቲያናችንን እንቁዎች እየፈለጋችሁ ቁም ነገር ብታስነብቡን እንዴት በነጋ ጠባ እርግማን፣ ስድብን፣ ዘለፋን፣ ውግዘትና የሰዎችን ገመና ስንሰማ ስናነብ ጆሮአችን ይመግላል፣ ዓይናችን ይፈዛል፣ ነፍሳችን ትቆስላለች፣ መንፈሳችንስ ይዝላል… እረ ባካችሁ እርስ በርስ መሰዳደቡና መጠላላቱ ምን ይጠቅመናል ለምን መስማት የማንፈልገውን እያሰነበባችሁን ልባችንን ታቆስሉታላችሁ፡፡


  እኛ የፍቅርን፣ የምሕረትን፣ የይቅርታን አዋጅን/ስብከት ነው እንጂ የተጠማነው የሰው ገመና ለማንበብማ የሀገራችን ጋዜጦችና መጽሔቶች አሉልን አይደል እንዴ! ዛሬ በእውነት ጥሩ ነፍስን የሚያሳርፍ ድንቅ መልእክት ነው ያስነበባችሁን አአውደ ምሕረቶች እንደ ስማችሁ የምሕረትንና የይቅርታን ስብከትን እንዲህ ብታቃምሱን እንመርቃችኋለን፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ ጹሑፉን እያነበብኩ ጩኽ… ጩኽ… እሪ በል… እሪ በል ነው ያሰኘኝ… በቤተ ክርስቲያናችን፣ በአባቶቻችንና በአገልጋዮቻችን የምንሰማው ጉድ ጩኸት… ዋይታና… እሪታ ሲያንሰው ነው፡፡ ‹‹ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይራዳም›› ይላሉና አበው በተረታቸው እስቲ እኔም ወደ እልፍኜ ልግባና በሬን ዘግቼ ኡ…ኡ…ኡ… እሪ… እሪ… እሪ… ዋይ… ዋይ… ዋይ … ልበል ጎረቤት ቢቀር የአካሌ ክፋይ ሚስቴና ልጆቼ ቢያግዙኝ… እናም የሰሙኝ ሁሉ ይራዱኝ ዘንድና ቅዱሱን ጩኸት በአንድነት እንጮኸ ዘንድ… ኦ! የአባቶቻችን አምላክ ስማን እባክህን!

  ዘርዓያቆብ ዘሀገረ ኢየሩሳሌም ጽዮን ሰማያዊት!

  ReplyDelete
 8. we must also cry against the tehadiso who want to ruin our church, we must also cry against the corrupted system of bete khnet; we must cry against the racist and poor administration system prevailed in our church; we must cry for unity of separeted synods.we must cry against the western powers who deploy menafkans in our church through tehadso ( our persons) using their money as an instrument

  ReplyDelete
 9. the bible says ;be haileh chuh not be haail chuh read the scripture again

  ReplyDelete