Thursday, July 26, 2012

የግንቦቱ ሲኖዶስ ካወገዛቸው ግለሰቦች መካከል ሦስቱ ውግዘቱን በመቃወም ጠቅላይ ቤተክህነቱን ይግባኝ ጠየቁ

Read in PDF
ክፍል 2
የዲያቆን አግዛቸው ተፈራ አቤቱታ
ህልውናውንና የሚመራውን መንፈስ ቅዱስን ወደጎን ትቶ ለማኅበረ ቅዱሳን በማደር በህሊና፣ በታሪክና በእግዚአብሔር ፊት አሳፋሪ ስህተት የፈጸመው የግንቦቱ ሲኖዶስ ስብሰባ እፎይ ብዬ ተቀመጥኩ ለማለት ቢሞክርም፣ እፎይ የማያሰኙ አቤቱታዎች እየቀረቡበት መሆኑን ከዚህ ቀደም ገልጸናል፡፡ እስካሁን ድረስ ባለን መረጃ ዲያቆን አሸናፊ፣ ዲያቆን አግዛቸው እና መምህር ጽጌ አቤት ያሉ ሲሆን፣ አቤቱታቸውን ሰምቶ ችግራችሁ ምንድን ነው ብሎ ሊያነጋግራቸው የቻለ አካል ይኑር አይኑር እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ ባለፈው ጊዜ የዲ/ን አሸናፊን አቤቱታ አቅርበንላችሁ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የዲ/ን አግዛቸውን አቤቱታ እናቀርባለን፡፡ ሙሉውን የዲያቆን አግዛቸውን ደብዳቤ ከዚህ ጽሑፍ በታች ያገኙታል . . .
ዲ/ን አግዛቸው ተፈራ እስካሁን ድረስ 4 መጻህፍትን የጻፈ ሲሆን፣ እነርሱም፦ የተቀበረ መክሊት፣ ጥላና አካል፣ የለውጥ ያለህ!!! አልተሳሳትንምን? የተሰኙ ናቸው፡፡ የተቀበረ መክሊት የተሰኘው የመጀመሪያው መጽሐፍ ብዙዎችን ያነቃ ወደ እግዚአብሔር እውነት እንዲደርሱ የረዳ እና የተቀበረውን መክሊት ፍለጋ ተግተው እንዲቆፍሩ ያነሳሳ መጽሐፍ ነው፡፡ የተቀበረውን እውነት እውነቱን የሸፈነውን ሐሰትና ለስሕተት መግቢያ ከሆኑት በሮች ዋናውን የአተረጓጎም ችግር የሚያሳየው ይህ መጽሐፍ፣ አሁንም ድረስ በርካታ የአብነት ትምህርት መምህራንና ተማሪዎች፣ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችና ምዕመናን እንደ ጥሩ ምንጭ ኮለል ያለውን እውነት የሚቀዱበት መጽሐፍ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ 
ጥላና አካል የተሰኘው ሁለተኛው መጽሐፍም ብሉይ ኪዳንንና ሐዲስ ኪዳንን በማነጻጸር በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እያታየ ያለውን ከፊል ኦሪታዊ ሥርአትን የሚገመግም፣ ብሉይ ኪዳን የአዲሱ ኪዳን ጥላና ምሳሌ እንደሆነና አማናዊውና አካሉ አዲስ ኪዳንም ለዚህ ዘመን ዋና ነገር መሆኑን የሚያብራራ መጽሐፍ ነው፡፡ ከብሉይ ኪዳን ዋና ዋና የሆኑ ነገሮችን ነቅሶ በማውጣት በሐዲስ ኪዳን ያላቸውን ትርጉም የሚያብራራ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሚታዩ አንዳንድ የብሉይ ኪዳንን ስም የያዙ ንዋያተ ቅድሳትና ልምምዶች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡ በአሁኑ ሰዓት መጽሐፉ በገበያ ላይ የሌለ ሲሆን ብዙዎች እየፈለጉት እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዲያቆኑ ከጻፋቸው መጻሕፍት ሁሉ በገጽ ብዛት ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው የለውጥ ያለህ!!! የተባለው መጽሀፉ አሁንም በገበያ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ እንደእነዚህ ላሉት መጻሕፍት የማስታወቂያ ሰራተኛ ሆኖ እያገለገለ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን፣ ባለፈው አመት የግንዛቤ ማስጨበጫ በሚል በከፈተው ዘመቻ መጽሐፉን በቪዲዮ እያሳየ እንዳታነቡ የሚል መልዕክት ካስተላለፈ ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እየተሸጠ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አያ ዘባርቄ ምሕረተ አብ እውነትን በማዛባት በታቦት ላይ «አልተሳሳትንም» በሚል ርእስ የሰጠው ትምህርት «አልተሳሳትንምን?» የሚል መጽሐፍን ወልዷል፡፡ መጽሐፉ ዲ/ን አግዛቸው ስለ ታቦት ምሕረተ አብ በደመ ነፍስ ለገበያ በሚስማማ መልኩ እንደቸረቸረው ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውንና በታሪክ የተመዘገበውን እውነት ያብራራበትና የምህረተ አብን ውትፍትፍ “ስብከትም” በድንቅ ብዕር የተቸበት መጽሐፍ ነው፡፡ በምሕረተ አብ ደንባራ በቅሎ ተጭነው ሲጓዙ የነበሩና የሌሎች ምዕመናንን ጥያቄ የመለሰ መጽሐፍ መሆኑን ያነበቡ ሁሉ የሚመሰክሩት እውነት ነው፡፡ ጥላና አካል እና አልተሳሳትንምን? የተሰኙት መጻሕፍት ከገበያ ፈጽሞ የጠፉ ሲሆን ፈላጊያቸው ብዙ ሰው ሆኖ ሳለ ደራሲው ለምን መልሶ እንደማያሳትማቸው ጥያቄ ሆኖብናልና በማሳተሙ ላይ ቢያስብብበት ጠቃሚ ነው እንላለን፡፡
እነዚህን መጻሕፍት የጻፈውና ተጠርቶ ሳይጠየቅ የተወገዘው ዲ/ን አግዛቸው የተላለፈበትን ውግዘት በመቃወም ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አቤት ያለ ሲሆን፣ የጻፈው ደብዳቤ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ያለውን «ህጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” (ዮሐ. 7፡51)» የሚለውን ጥቅስ በማስቀደም ይጀምራል፡፡ በመቀጠልም በቤተክርስቲያን ያሳለፈውን ጊዜ በአጭሩ ያስቀኛል፡፡ ይህም ማኅበረ ቅዱሳን እስካሁን ድረስ ስለእርሱ ጭሮ ጭሮ ሊያገኝ ያልቻለውንና እያዛባ ያቀረበውን አስተካክሎ ያቀረበ ነው፡፡
ዲ/ን አግዛቸው በሲኖዶሱ  በቀረበበት ውግዘት እጅግ ማዘኑን የገለጸ ሲሆን፣ ምክንያቱን እንዲህ ሲል አብሯርቷል፡፡ “…. ‘ደጀ ሰላም’ በተባለ ድረ ገጽ ላይ የወጣውንና የሊቃውንት ጉባኤ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረበውን ጥናታዊ መግለጫ እና የውሳኔ ሀሳብ ስመለከት ስሜ በተጠቀሰበት በገጽ 32 ላይ ‘… አልመለስ ሲል’፣  እንዲሁም በገጽ 34 ላይ ከሌሎች ሁለት ግለሰቦች ጋር “በፈጸሙት የመናፍቅነት ተግባር ቀርበው ከተጠየቁ በኋላ የማይመለሱ በመሆናቸው’ የሚሉ ሀረጎችን ሳነብ እጅግ አዝኛለሁ፡፡ ተጠርቼ ሳልጠየቅና ምን እንዳደረግሁ ሳይነገረኝ ስሜ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት በቤተ ክርስቲያን አውደ ምሕረት የጠፋው ሚያዝያ 17/1991 ዓ.ም ሲሆን፣ ስብሰባ ተደረገ የተባለው ግን ሰኔ 4/1991 ዓ.ም ነው፡፡ እኔ ስብሰባውን እጠብቀው የነበረ ቢሆንም፣ ጥሪው አልደረሰኝም፡፡ ቀድሞም ቢሆን በደፈናው ማውገዝ እንጂ እኔን ጠርቶ የማነጋገር ፍላጎት በሀገረ ስብከቱ በኩል እንዳልነበረ አውቃለሁ፡፡ ስሜ ከጠፋ ከ15 ቀናት በኋላም እንኳን ተጠርቼ አለመጠየቄና ጥሪው ሳይደርሰኝና ተጠርቼ እንቢ ሳልል በሌለሁበት ‘መወገዜ’ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርአተ ቤተ ክርስቲያንን ያልተከተለ በመሆኑ ሳልቀበለው ቆይቻለሁ። ነገር ግን ሂደቱ ይህ ሆኖ ሳለ ተጠርቼ እንደ ተጠየቅሁና አልመለስም እንዳልሁ ተቆጥሮ በሊቃውንት ጉባኤው ጥናታዊ መግለጫና የውሳኔ ሀሳብ ላይ የቀረበው ገለጻ ፍጹም የተሳሳተና ሐሰት ነው። በዚያ ላይ ተመስርቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈው ውግዘትም በእጅጉ አሳዝኖኛል።” ብሏል፡፡
እንግዲህ ከሱን በደጀ ሰላም፣ ‘ተጠርቶ መጠየቁን’ በደጀ ሰላም፣ ‘አልመለስ’ ማለቱንም ሆነ ‘ውግዘቱን’ የሰማው በደጀ ሰላም መሆኑና ስለ ራሱ እሱ የማያውቀውን  ታሪክ ማንበቡ በእርግጥም አሳዛኝ ነው፡፡ ሊቃውንት ጉባኤውም ቢሆን ከቀደሙት አባቶች እና በ1990 ከነበረው የሊቃውንት ጉባኤ ተምሮ ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ክሱ ምንም ይሁን ምን ተከሳሹን ጠርቶ ለማነጋገር አለማሰቡ ሳያንስ፣ ከቶ ያላደረገውን ነገር «ተጠርቶ ተጠይቆ አልመለስ ስላለ» ብሎ መጻፉ እጅግ የሚያሳዝን እና በታሪክ ፊትም የሚያስጠይቅ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ሲኖዶሱም ለልጆቹ የእንጀራ አባት ያህል እንኳ ፍቅርና ርህራሄ ሳያሳይ፣ ጊዜ ሲጠብቅለት እንደነበረ ጠላት በማኅበረ ቅዱሳን ጦር መውጋቱ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡
የሚያምነው “… እምነት ከቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያልወጣና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተማሩት መሆኑን…” አሁንም ድረስ የሚያምነው ዲ/ን አግዛቸው፣ እነዚህን መጻሕፍት ለመጻፍ ያነሳሳው የቤተ ክርስቲያንን መጻህፍት ማንበቡና መመርመሩ መሆኑን በአቤቱታው ላይ ገልጧል፡፡ እንግዲህ የጻፋቸው መጻህፍት ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮና መጻሕፍት ካልወጡ ሲኖዶሱ፣ ዲያቆኑን ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለስ ወይም ደግሞ እርሱ የጠቀሳቸውን መጻሕፍት ጨምሮ ማውገዝ የሚል አጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን ገና በአሰላ ሳለ ተጠርቶ ሳይጠየቅ፣ በከሳሹ ክስ መነሻነት ብቻ መታገዱ ስላሳዘነውና በተከሰሰባቸው ጉዳዮች ቀርቦ የሚያስረዳበት አጋጣሚም ስላላገኘ እምነቱ ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያልወጣ መሆኑን ለማሳየት ሲል መጽሐፍ መጻፍ መጀመሩን የገለጠው ዲ/ን አግዛቸው፣ ለጻፋቸው መጻህፍት እንደ ዋቢ የተጠቀመው መጽሐፍ ቅዱስንና የቤተክርስቲያን መጻሕፍትን እንደሆነ ገልጾአል፡፡ አክሎም «በእነርሱ ከተገለጸው የወጣ የጻፍኩት ነገር የለም» ይላል፡፡ እርሱ ይህን መከራከሪያ ማቅረቡ እኔን «ተሳሳተ» ካላችሁ ከራሴ አመንጭቼ «የሳትኩት» ነገር የለምና እንደ እናንተ አስተያየት «ስህተት» ላላችሁት እምነት ያበቁኝ መጽሐፍ ቅዱስንና የቤተክርስቲያን መጻህፍትን ምን ልትሏቸው ነው? የሚል አንድምታ ያለው ጥያቄ የጠየቀ አስመስሏል፡፡ በእርግጥም እነዚህን መጻህፍት ዋቢ አድርጎ በጻፋቸው መጻህፍት የሚወገዝ ከሆነ የመጻህፍቶቹም እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል አጠያያቂ ነው፡፡ መምህሩ እያለ ደቀ መዝሙር አይወገዝምና፡፡
መጻህፍቶቹን የጻፈባቸውን አላማዎች ሲያስረዳም፥
§  «ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት እንዲያስተውሉና በወንጌል የተገለጠውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ የሞተበትን መዳናችንን በእምነት ተቀብለው ድህነተ ነፍሳቸውን እንዲያገኙ የድርሻዬን ለመወጣት፣
§  ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቼ «እውነት» በቤተ ክርስቲያናቸው የሌለ መስሏቸው እውነትን ፍለጋ ወደ ሌላ እንዳይሄዱ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማድረግና 
§  ቤተ ክርስቲያናችን እንደ እግዚአብሔር ቃል ያልሆኑትን የአስተምህሮዋ፣ የስርአቷና የባህሏ አካሎች የሆኑትን፣ በሌሎች ዘንድ የሚያስነቅፏትንና በሕዝቡም ላይ ቀንበር ሆነው በልዩ ልዩ መንገድ ወደ ኋላ የጎተቱትን ነገሮች፣ ሕዝቡ በመሰለው መንገድ እያሻሻለና እየለወጠ ነገሮች ሌላ መልክ ከመያዛቸው በፊት፣ ቤተ ክርስቲያኗ ከሕዝቡ ቀድማ በቅዱስ ሲኖዶስ እየመረመረች መፍትሄ እንድትሰጣቸው ለማመላከት ነው» ብሏል፡፡
ፍትሕ የቤተክርሰቲያኒቱ ትልቅ እሴት ነው ሲል የገለጸው ዲ/ን አግዛቸው ነገስታት እንኳ የሀይማኖት ልዩነቶችን ለመፍታት ያደርጉት የነበረው ጉባኤ ጠርቶ ሊቃውንቱን የማከራከሩን ሂደት ሲኖዶሱ አለመከተሉ፣ የፍትህ ምንጭ መሆን ከሚገባት ቤተክርስቲያን ከቶውንም የማይጠበቅ እና ታሪኳንም የሚያበላሽ መሆኑን ገልጾ እንደህጉ ተከሳሽ እኔ እና ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳንን ፊት ለፊት አገናኝታችሁ ማከራከር ነበረባችሁ የሚል አንድምታ ያለውን መከራከሪያ በማቅረብ አቤቱታውን ይቀጥላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃንን ለማውገዝ ትጠቀምበት የነበረውን መንገድ ያላገናዘበው እና ያልተጠቀመውን ሲኖዶስ አካሄድ የፈጠረበትን ዘርፈ ብዙ ጥያቄ እንዲህ ሲል ይዘረዝራል፡፡
“… ለእነአርዮስ፣ መቅዶንዮስ፣ ንስጥሮስና ለሌሎቹም የተሰጠው ጠርቶ የማነጋገርና ምላሽ የመስማት ዕድል ለእኔ መነፈጉ፣ ከአርዮስ የከፋ ምን ተናግሬ ይሆን? ምንስ ጽፌ ይሆን? ለምን ማህበረ ቅዱሳን አቀረበ በተባለውና ከየግል መጽሔቱ ባነበብሁት ክስ መሰረት አቤቱታ ሰሚው ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2004 ዓ.ም ስብሰባው ተከሳሾች ቀርበው እንዲጠየቁና የተሰየመው አጣሪ ኮሚቴ የደረሰበትን ሀሳብ ለግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ እንዲያቀርብ ባዘዘው መሰረት ጉዳዩ አልተፈጸመም? ይኸው እስከ ዛሬ ተጠርቼ አልተጠየቅሁም፤ ጥፋቴ ምን እንደ ሆነም አልተነገረኝም፡፡”
ክሱንም ውግዘቱንም እንደ አልፎ ሂያጅ ተመልካች ከሌሎች የሰማው ዲ/ን አግዛቸው «የፍትህ አገርዋ ወደየት ነው?» ሲል አቤት ብሏል፡፡ ክሱም ሂደቱም ውሳኔውም የቤተክርስቲኒቱን ሥርአት ያልተከተለ እና ከከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን እስከ ሲኖዶስ አንዳቸውም እንኳ ነጋ ጠባ የሚያወሩለትን የቤተክርስቲያኒቷን ስርዓት ለማክበር አለመፈለጋቸው አነጋጋሪ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡
ዲያቆኑ አቤቱታውን ሲጨርስ ሲኖዶሱ ሊያደርግ ይገባል ብሎ ያመነባቸውን አራት ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡
ይህንን አቤቱታ ያነበብን ሰዎች በእርግጥም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ “ህጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው ይፈርዳልን?” (ዮሐ. 7፡51) ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡ አዎን ከዛሬ 2000 ዓመት በፊት የነበረው የአይሁድ ህግ ከተከሳሽ ሳይሰማ ምን እንዳደረገም ሳይጠይቅ በከሳሽ ክስ ላይ ብቻ ተመሥርቶ በሰው አይፈርድም ነበር፡፡ በዘመናት መካከል ባለው የቤተክርስቲያን ስርዓትና ታሪክም ቤተክርስቲያን ልጆችዋን ሳትጠይቅ፣ ጊዜና ዕድል ሰጥታ ሳታነጋግር፣ ይቅርባችሁ ብላ ሳትለምን አትፈርድም ነበር፡፡ የዓለም ስርዓትም በፍጹም የተከሳሽን ድምጽ ሳይሰማና ሁለቱን ሳያሟግት አይፈርድም፡፡ በአሁንዋ ዘመን ቤተክርስቲያናችን ግን እርስዋን በቋሚነት በሚወክላት ሲኖዶስ በኩል ሕግ ተጥሶ የከሳሽ ድምጽ ብቻ ተሰምቶ ፍርድ ተሰጥቷል፡፡ እንዲያውም አንድ ጳጳስ በመንፈስ ልጃቸው በኩል እንዲህ መደረጉ ስህተት መሆኑና ውሳኔያቸውንም ተቀባይነት እንደሚያሳጣው ሲገለጽላቸው «ማኅበረ ቅዱሳን ያጠናው በቂ ስለሆነ እነሱን ማዳመጥ አያስፈልግም ብለን ወስነናል፡፡ ይህንን እኔም አምንበታለሁ፡፡» ብለው መናገራቸው ሲኖዶሱ ትምህርተ ሃይማኖት በሌላቸው፣ የቤተክርስቲያኒቱን ስርዓት በማያውቁ፣ ሕግና ሥርአትን ባልተረዱ፣ ለታሪካቸው ዋጋ በማይሰጡ ጳጳሳት መወረሩን ያሳያል፡፡
መንፈሳዊ ነገር እንደ ወፍጮ ሲሻ አድቅቀው ሲሻ ደግሞ ሸርክተው ፍላጎትን የሚያሳኩበት መንገድ አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ነገር ጳጳስም ይሁን ምዕመን ለእግዚአብሔር ሀሳብ እኩል ተገዝተው የሚያልፉበት ነገር ነው፡፡ የሲኖዶሱ አባላት ማኅበረ ቅዱሳንን ለማስደሰት የደከሙትን ያህል፣ የጠራቸውን እና ከምንም አንስቶ ያከበራቸውን እግዚአብሔርን ለመስማት መጠነኛ ፍላጎት እንኳ ቢኖራቸው ኖሮ እንዲህ ያለውን ስህተት ከመፈጸም ይድኑ ነበር፡፡
እንደ ኒቆዲሞስ ያለ አንድ እንኳ ስለህጉ የሚከራከር አስተዋይ ሰው ሲኖዶሱ እንዴት ያጣል? የሚለው ጥያቄ የበርካታ አስተዋይ ሰዎች ጥያቄ ነው፡፡ እዚህ ላይ ተዉ አይሆንም ብለው እንደኒቆዲሞስ የተከራከሩ አባቶች እንደነበሩ በጊዜው ተደምጧል፡፡ የያኔው የአይሁድ ሸንጎ ኒቆዲሞስን እንዳልሰማው ሁሉ የአሁኑም የጳጳሳት ሸንጎ (ሲኖዶስ) እነዚህን ጳጳሳት አልሰማቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ታሪክ በታወሰ ቁጥር እነርሱም እንደኒቆዲሞስ መወሳታቸው አይቀርም፡፡ በርግጥም ህጋችን አስቀድሞ ከእርሱ ሳይሰማ ምንስ እንዳደረገ ሳያውቅ በሰው አይፈርድም፡፡ የስው ስሜት በህግ ላይ ሲሰለጥን ግን እንዲህ አይንን ጋርዶ ሕጉን አሽሮ ለተዛባ ፍርድ ያነሳሳል፡፡ የቅዱሳን አምላክ ሕያው እግዚአብሔር ያባቶቻችንን ዓይነ ልቦና ያብራልን፡፡

3 comments:

 1. This comment has been removed by a blog administrator.

  ReplyDelete
 2. የቅዱሳን አምላክ ሕያው እግዚአብሔር ያባቶቻችንን ዓይነ ልቦና ያብራልን፡፡
  leke new

  ReplyDelete
 3. መሸዋወድ ድሮ ቀረ አሁን ከዚህም በላይ ብዙ ብታወሩ ……………የለም!!!

  ReplyDelete