Sunday, August 12, 2012

የግንቦት 15ቱ ውግዘት መነሻ፣ ሂደት፣ ፍጻሜና ቀጣዩ ሲገመገም

Read in PDF

ክፍል 6
በከሣቴ ብርሃን ማኅበር ላይ ኑፋቄ ተብለው ከቀረቡት መካከል ገድል ወይስ ገደል በተሰኘው መጽሐፍ ላይ የሊቃውንት ጉባኤውና ሲኖዶሱ በኑፋቄነት የፈረጁትንና አውግዘናል ያሏቸውን ሐሳቦች በክፍል 3 ጽሑፋችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ከዚያ የቀጠለውን ሐሳብ ደግሞ በዚህ ክፍል እናቀርባለን፡፡ ብዙዎቹን የከሳቴ ብርሃን የተባሉትን ጽሑፎች ለማግኘት ስላልቻልን፣ ሲኖዶሱ ቀንጭቦና አዛብቶ ያቀረበውን ለመተቸት ተገደናል፡፡ የከሳቴ ብርሃንን ብዙዎቹን ጽሁፎች ማግኘት ብንችል ግን ከሲኖዶሱ ቅንጫቢ ጽሑፍ ጋር በማስተያየት ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ በቻልን ነበር፡፡ እስካሁን ካቀረብናቸው ዘገባዎች ለመረዳት እንደተቻለው፣ ሲኖዶሱ ያጸደቀው የሊቃውንት ጉባኤው ጥናት በአብዛኛው የተወገዙትን ግለሰቦችና ማኅበራት ለመክሰስ እንዲመች ተቆርጦና ተቀጥሎ አንዳንዴም እነርሱ ያልጻፉትንና ያላሉትን እንዳሉ አስመስሎ ያቀረበ መሆኑን መጥቀስ እንፈልጋለን፡፡ የሊቃውንት ጉባኤውና ሲኖዶሱ ያስወግዛል ብለው ቆርጠውና ቀጥለው ያቀረቡት «ኑፋቄ» በእነርሱ እይታ እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስና በአበውም ትምህርት ትክክለኛ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ ያወገዙት እውነትን ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ ለሁሉም በከሳቴ ብርሃን ላይ ኑፋቄ ተብለው የቀረቡትን ነጥቦች ወደ መተንተንና ኑፋቄ መሆን አለመሆናቸውን በእግዚአብሔር ቃል ወደመፈተሽ እንለፍ፡፡

«‘ሀ. በቤተ ክርስቲያናችን ታቦት የለም ነገር ግን በኢትዮጵያ ታቦት ሳይኖር ለታቦት ስገዱ፥ አምልኩ እያሉ የሚሰብኩና የሚጽፉ ብዙ ናቸው፡፡ ታቦት በክርስትና ቦታ ባይኖረውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባለመሆኑ ሕዝቡ ታቦት ከማምለክና ገንዘቡንም ከመገበር መዳን አለበት፤ በብሉይ ኪዳን ከነበሩና በሐዲስ ኪዳን ከተሻሩት ሥርዓቶች አንዱና ዋናው ታቦት ነው፥ ከታቦቱ ጋር የነበሩ ብዙ ስርአቶችም ከታቦቱ ጋር ተሽረዋል’ እያሉ ምእመናን ለታቦት የሚሰጡትን ክብር ነቅፈዋል፡፡ መጥቅዕ መጽሔት - 2000 ዓ.ም እትም ገጽ 9»
‹‹ ‘ለ. ታቦት በሀገራችን የለም እንጂ ቢኖርም እንኳ ለታቦት የሚሰግድ ለእንጨት የሚሰግድ መሆኑ ግልጽ ነው›› በማለት ታቦቱን ወይም በጽላቱ ላይ ለተጻፈው ስመ እግዚአብሔር የምናቀርበው ስግደት ለእንጨት መስገድ ነው’ በማለት በታቦት ላይ የምንፈጽመውን ሥርዓተ አምልኮ በመቃወም ጽፈዋል፡፡ መጥቅዕ መጽሔት- 2000 ዓ.ም. እትም ገጽ 10»

በሊቃውንት ጉባኤው ጥናትና በሲኖዶሱ ውሳኔ ውስጥ እነዚህ ነጥቦች የሚያስወግዙ ኑፋቄዎች ናቸው ቢባልም፣ ስለታቦት በሁለቱ ነጥቦች ስር የተገለጸው ሐሳብ ቤተክርስቲያን ራሷን እንድታስተካከል የተላለፈላት መልእክት እንጂ የሚያስወግዝ ኑፋቄ አይደለም፡፡ በቤተክርስቲያናችን ታቦት እየተባለ የሚጠራው ዝርግ ሰሌዳ የብሉይ ኪዳኑን ታቦት ስም ከመዋስ በቀር በመልክም፣ እየሰጠ ባለው አገልግሎትም ከብሉይ ኪዳኑ ታቦት ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም፡፡ ብሉይ ኪዳን በሐዲስ ኪዳን ተተክቷል፡፡ ለክርስቶስ ምሳሌ የሚሆኑና በብሉይ ኪዳን የነበሩ ነገሮች በሙሉ በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ተፈጽመዋል፡፡ ስለዚህ የብሉይ ኪዳንን ሥርአቶች በሐዲስ ኪዳን ይዘን እንድንቀጥል የታዘዘ ትእዛዝ የለም፡፡ ኢየሱስም እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ ባለው መሠረት ኦሪትና ነቢያት በእርሱ ፍጻሜ ማግኘታቸውን አብራርቷል፡፡ ምንም እንኳ ብዙዎች ጥቅሱን የኦሪት ነገሮች አልተሻሩም ለማለት ቢጠቅሱትም፣ ጥቅሱ ታቦት አልተሻረም የሚል አንድምታ ፈጽሞ የለውም፡፡ ክርስቶስ ልፈጽም መጣሁ ያለው፣ የኦሪት ነገሮች በአዲስ ኪዳንም ይቀጥላሉ ለማለት ሳይሆን፣ በእኔ ፍጻሜ ያገኛሉ ለማለት እንደሆነ ከጠቅላላው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እንገነዘባለን፡፡

ኦሪት በክርስቶስ መፈጸሙን የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት በተለይም የዕብራውያን መልእክት በስፋት ያብራራል፡፡ ስለዚህ እንኳን የብሉዩን ስም የተዋሰውና ኢትዮጵያ ውስጥ የቤተክህነት ሰዎች በሆኑ የቅርጻ ቅርጽ ባለሙያዎች የተቀረጸው ኢትዮጵያዊው ታቦት ይቅርና ለእስራኤል ልጆች እግዚአብሔር የሰጠው ታቦት አገልግሎቱ ማብቃቱን መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል፡፡
 «በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን፦ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም።» (ኤር. 3፡16)፡፡
እንዲሁም «እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ቃል ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር፣ ከግብጽ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደ ገባሁት ያለ ቃል ኪዳን አይደለም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፦ ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር፦ በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።» (ኤር. 31፡31-34)፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የታቦት አገልግሎት በዚያው በብሉይ ኪዳን ዘመን ማለትም ከባቢሎን ምርኮ በኋላ እንዳበቃ ያስረዳሉ፡፡
አንዳች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለውና በየትኞቹም አብያተ ክርስቲያናት የማይገኘው የኢትዮጵያ ታቦትና ለእርሱ እየቀረበ ያለው ስግደትና አምልኮት ሊነቀፍ እንጂ ሊከራከሩለት የሚገባ አይደለም፡፡ ሕዝቡን በመንፈሳዊ ስም ከቀረበለት ከዚህ አምልኮ ባዕድ እንዲድን ማድረግ ይገባል እንጂ «ታቦትን አላመለከም ለታቦት ክብርን ሰጠ እንጂ» ብሎ መሸፋፈን በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአት ነው፡፡ በክርስቲያኖችም ፊት ተቀባይነት የለውም፡፡

«የምንሰግደው ለዕንጨቱ ሳይሆን በታቦቱ ላይ ለተጻፈው ስመ አምላክ ነው» ማለትም አንዱ ማምለጫ እየሆነ መጥቷል፡፡ ነገር ግን «እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚሰግዱለትም በእውነትና በመንፈስ ሊሰግዱለት ይገባል» ተብሎ በራሱ በጌታችን ታዟልና፣ የእግዚአብሔርን ስም የዕንጨት ወይም የድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፈን እዚያ ላይ ለተጻፈው ስም ነው የምንሰግደው የሚለው መከራከሪያ ቢቸግር ነው፡፡ እውን ታቦት በየበዓላቱ ሲወጣ ሕዝቡ የሚሰግደው ለማን ነው? ሊቃውንት ተብዬዎቹ እንደሚሉት በታቦቱ ላይ ለተጻፈ ስመ አምላክ ነው? ወይስ ለታቦቱ? ሰዉ እየሰገደ ያለው ለታቦቱ ነው፡፡ እያመለከ ያለውም ታቦቱን ነው፡፡ ዘወትር ከታቦት ጋር ተያይዞ ለሚነሳባችሁ ጥያቄ ላለማፈር ስትሉ እንዲህ ያለ የተውተፈተፈ መልስ ከመስጠት ይልቅ፣ አምልኮተ ታቦትን ለማስቀረት ብትሠሩና አምልኮትና ስግደት ብቻውን አንድ አምላክ ለሆነው ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ብቻ እንዲቀርብ ሕዝቡን ብታስተምሩት ሊቅነታችሁ ይታወቅ ነበር፡፡

ለመሆኑ በታቦት ላይ ስመ አምላክ ጻፉና በታቦቱ አማካይነት ለእግዚአብሔር ስም ስገዱ ሲል ማነው ያዘዘው? በብሉይ ኪዳኑ ታቦት ላይ ስመ አምላክ ተጽፏል ወይ? በፍጹም አልተጻፈም፤ ከአሥሩ ትእዛዛት በቀር የተጻፈ ነገር የለም (ዘዳ. 4፡13፤ 10፡4)፡፡ ስለዚህ ዛሬ ታቦት የምንለው ዝርግ ሰሌዳ ከስሙ በቀር ሌላ ከብሉዩ ታቦት ጋር የሚመሳሰልበት አንድም ነጥብ ስለሌለ፣ በእርሱ በኩል የሚፈጸመው አምልኮት ሁሉ አምልኮ ባእድ እንጂ አምልኮተ እግዚአብሔር ሊሆን በፍጹም አይችልም፡፡ ምንም ይሁን ምን እስከ ዛሬ ይዘን የመጣነው ነገር ስለሆነ አንተወውም ከሆነ ያ ሌላ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ በታቦት ስም ቤተክርስቲያኗ እያፈጸመች ያለው ሁሉ ሲፈተሽ አምልኮ ባዕድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ኑፋቄ ያለው ከማን ዘንድ አንደ ሆነ አንባቢው ያስተውል!

‹‹‘ሐ. ቤተ ክርስቲያናችን ከተመሠረተችበት የወንጌል መሠረትና ትምህርት አፈንግጣለች፤ ስለሆነም ወደ ቀደም ክብሯ መመለስ አለብን’ በማለት ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ተችተዋል፡፡ መጥቅዕ መጽሔት- ሰኔ 1995 ዓ.ም. እትም ገጽ 2»

አሁን ማን ይሙት ይህ ሐሰት ነው? ያስወግዛልስ? እንዲያውም የሰጣችሁን ጥቆማ ጥሩ ነውና ራሳችንን ፈትሸን የተባለው ነገር ካለ በሚመለለተው አካል የማስተካከያ እርምጃ ይወሰዳል ነበር መባል የነበረበት፡፡ የሊቃውንት ጉባኤው ግን ቤተ ክርስቲያኗ ባሉባት ችግሮች አንጻር ለምን ተተቸች ነው የሚለው፡፡ ይህም ቤተክርስቲያኗ ስሕተተቿን አርማ እንዳትታደስና ባለችበት እንድትረግጥ የፈረደባት መሆኑን ያሳያል፡፡

ቤተክርስቲያኗ አሁን የቆመችው በተመሰረተችበት የወንጌል መሰረት ላይ ነው ብሎ ማንም ሊከራከር አይችልም፡፡ እንዳልሆነ ይታወቃልና፡፡ በዚህ የሲኖዶስ ውሳኔ የተላለፈው ውግዘት እንኳን ለዚህ በቂ ምስክር ነው፡፡ ሲኖዶሱ ያወገዘው በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውነት ነው፡፡ ለምን ተነኩብኝ ሲል የተከራከረው ደግሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለተቃረኑ የአዋልድ መጻህፍት ትምህርትና ለልማዳዊ ድርጊቶች ነው፡፡ ቤተክርስቲያኗ ለአፏ የምመራው በሐዋርያትና በነቢያት፣ እንዲሁም በሠለስቱ ምእት ትምህርት ነው ብትልም እውነታው ግን ያ አይደለም፡፡ እነርሱን እየተቃወመችና እያወገዘች እንደሆነ ተግባሯ ይመሰክራል፡፡ ስለዚህ ከተመሠረተችበት የወንጌል እውነት አላፈነገጠችም ማለት አይቻልም፡፡ ስላፈነገጠችም ወደ ቀደመ ክብሯ መመለስ አለባት፡፡ አሊያ ምእመናኖቿ እውነትን ፍለጋ ወደሌሎች መፍለሳቸው፣ የእርሷም ሀይል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መሄዱ አይቀርም፡፡ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት አዳራሾች የተሞሉት በዋናነት በኦርቶዶክስ አማኞች ነው፡፡ ቤተክርስቲያኗ ጆሮ ዳባ ልበስ ብላ ከምትቀመጥ፣ ራሷን ብትፈትሽና እንደ እግዚአብሔር ቃል መመራት ብትጀምር ግን ያሉትን በቤታቸው ማጽናት ብቻ ሳይሆን፣ የሄዱትን ደግሞ መመለስ ይቻል ነበር፡፡ ለዚህ ግን የሊቃውንት ጉባኤውም ሆነ ሲኖዶሱ፣ ሌሎች አካላትም ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ይህም የሚጎዳው ቤተክርስቲያኗን ነው፡፡ በቅርቡ ጊዜ መረጃ መሰረት ምእመናኖቿ በ8 ሚሊዮን መቀነሳቸው ለብዙዎች ምንም አልመሰላቸውም፡፡ ያለው ይበቃናል በሚል በዝምታ የተቀመጡ ነው የሚመስለው፡፡ እነርሱ እንዲህ ናቸው፤ ወደ እነርሱ አትሂዱ፤ ሰላም አትበሏቸው፤ ወዘተርፈ በማለት ብቻ ሰውን ከመሄድ መግታት አይቻልም፡፡    

‹‹‘መ. ለሥዕል ስግደት አይገባም፤ ተዝካርና ፍትሐት እርባና የላቸውም›› በማለትም ጽፈዋል፡፡ መጥቅዕ መጽሔት- ሚያዝያ 1996 ዓ.ም.እትም ገጽ 9
በመጀመሪያ ለሥዕል ስግደት ይገባል የሚለው ትምህርት ክርስቲያናዊ ትምህርት ነው ወይ? እንዲህ ያለውን ልማድ እግዚአብሔር ከኦሪት ዘመን ጀምሮ አልከለከለውም ወይ? ሥዕል በማንም አምሳል ይሣል የሰው እጅ ሥራ ነው፡፡ ይሁን ከተባለም ሥዕል የማስተማር ተግባር ነው ያለው፡፡ ከዚህ ውጪ በሥዕል በኩል ምልጃ ማቅረብም ሆነ ለስዕል መስገድ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊና አሕዛባዊ ልማድ ነው፡፡

እግዚአብሔር የተቀረጹ ምስሎችን እንዳናደርግና አምልከናቸውም እንዳንገኝ ከልክሎናል (ዘፀ. 20፡4፤ ዘዳ. 4፡15-19፤ 5፡8)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የከለከለውን ነገር እኛ ተፈቅዷል፤ ለሥዕል መሰገድ የለበትም ያለ ውጉዝ ነው ብንል ራሳችንን ነው ትዝብት ላይ የምንጥለው፡፡

ተዝካርና ፍትሐት እርባና የለውም ብለዋል የተባለው ሌላው ክስ ነው፡፡ ፍትሐትና ተዝካር ለሆድ የተሠሩ ስርአቶች መሆናቸውን ሁሉም ያውቃል፡፡ ሰው በሕይወቱ እያለ ነው ሁሉን ነገር ማስተካከል ያለበት ከሞተ በኋላ ይግባኝ ማለት አይቻልም፡፡ ለሰዎች አንድ ጊዜ መሞት ከዚያም በኋላ ፍርድ ተመድቧል ነው የሚለው መጽሐፍ ቅዱስ (ዕብ. 9፡27) እንጂ ከሞት በኋላ በተዝካርና በፍትሐት የቦታ ዝውውር ይደረጋል አይልም፡፡ ስለዚህ ተዝካርና ፍትሐት ለሞተ ሰው የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ያንቀላፉ ምእመናንን በክርስቲያናዊ ሥርአት መሸኘትና እግዚአብሔርን ማመስገን ግን ተገቢ ነው፡፡ ተዝካር ስንቶችን ደሃ እንዳደረገ የሚያውቀው ሕዝቡ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ተዝካር እንዲቀር ሕዝቡ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እንዲያውም ተዝካር ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ተብሎ የተፈረጀበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እናንተ ቀድማችሁ ብታስተካክሉትና ሕዝቡን ባትበዘብዙት ኖሮ፣ ይህን ሥርአት ሌላው ባለወጠውም ነበር፡፡ ስለዚህ ነገሮች ከእጃችሁ እየወጡና ሕዝቡ እያደሳቸው ያሉትን እንደ ተዝካር ያለውን ሥርአተ ከርስ እርባና አለው ብትሉ ማንም አይሰማችሁም፡፡
     
‹‹‘ሠ. የሰማይ ንግሥት ስንል ማርያም ማለታችን እንዳልሆነና ነገር ግን የአሕዛብ ሴት አምላክ የሆነችውን ማርያም የሚለውን ስም የያዘችውን አስታሮትን (ጣኦትን) መሆኑን አንባቢ ሁሉ ሊረዳው ይገባል’ ሲሉ እመቤታችንን ጣኦት በማለት ተሳድበዋል፡፡ መጥቅዕ መጽሔት -መስከረም 1994 ዓ.ም. እትም ገጽ 11»

ከመጥቅዕ መጽሔት የተወሰደው ይህ ሐሣብ በትክክል መስፈሩን ማረጋገጥ ያስፈልግ ነበር፡፡ ሆኖም መጽሔቱ በእጃችን ስለሌለ ማረጋገጥ አልቻልንም፡፡ ነገር ግን ክርስቲያኖች እስከ ሆኑ ድረስ ማርያምን ጣኦት ብለው እንደማይሳደቡ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ብቻውን የሰማይና የምድር ንጉሥ የሆነው እግዚአብሔር ነው እንጂ በክርስትና ትምህርት በሰማይ ሌላ ንግሥት እንደሌለች ግልጽ ነው፡፡ የጌታችን እናት ድንግል ማርያም ንግሥተ ሰማይ ወምድር እየተባለች በአዋልድ መጻሕፍት ብትጠራ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አንጻር ሲታይ ስሕተት ነው የሚሆነው፡፡ እግዚአብሔር ብቻውን ንጉሥ ነውና፡፡ እንደ አሕዛብ ልማድ ሄደንና በእግዚአብሔር ላይ ሌላ ንጉሥ ሾመን ስሟን ማርያም ናት ብንል፣ በእርግጥ እርሷ ማርያም ልትሆን አትችልም፡፡ ዞሮ ዞሮ ትምህርቱን ከወሰድንበት ከአሕዛብ መንደር ትምህርት ጋር ካስተያየነው ከስሟ በቀር የሰማይ ንግሥት አድርገን ያስቀመጥናት ድንግል ማርያም ልትሆን አትችልም፡፡ እርሷ የጌታችን እናት ከሴቶች መካከል ተለይታ የተባረከች ብትሆንም፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ ከምእመናን አንዷ ናት እንጂ የተለየች አይደለችም፡፡ ከሐዋርያት ጋር አብራ ስትጸልይ ነበረ እንጂ ከሐዋርያት ተለይታ ሌላ ስፍራ ይዛ አናገኛትም (የሐዋርያት ሥራ 1፡14)፡፡ ስለዚህ ንግሥተ ሰማይ የሚለው ትምህርት ምንጩ የአሕዛብ አምልኮተ ጣኦት ነው እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም፡፡ 

«‘ረ. ኅዳር 21 ቀን በየዓመቱ ከታቦተ ሕጉ በረከት ለመቀበል ወደ አኲስም ጽዮን ለመሳለም መሔድ አያስፈልግም’ ብለዋል፡፡ መጥቅዕ መጽሔት - መስከረም 1994 ዓ.ም. እትም ገጽ 8»

አሁንም ይህንን ሐሳብ መጥቅዕ መጽሔት በዚህ መንገድ ማስፈር አለማስፈሩን ማረጋገጥ ያስፈልግ ነበር፡፡ ሆኖም የሊቃውንት ጉባኤው ባቀረበው ጥቅስ ላይ ተመስርተን ነገሩን እንየው፡፡ በቅድሚያ በረከት የሚገኘው ከየት ነው? የበረከት ምንጭስ ማነው? የሚለውን ሐሣብ ብንመለከት መልካም ነው፡፡ በረከት የሚገኘው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ሰው ሰውን ቢባርክ እንኳ ያ በረከት የሚመጣው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው፡፡ «በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።» ተብሎ ተጽፏልና (ያዕቆብ 1፡17)፡፡

ስለዚህ ወደ አክሱም በመሄድ ከታቦተ ሕጉ የምንቀበለው በረከት ሊኖር አይችልም፡፡ ከዚያ ይልቅ ታሪካዊውን ያን ስፍራ በመጎብኘት የምናገኘው የመንፈስ እርካታ አለ፤ የምንጨምረው እውቀት ይኖራል፡፡ አገራችንንና ታሪካችንን ለማወቅ እድል ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ ጉዳዩ ከጉብኝት ጋር እንጂ ከበረከት ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ነገሩ እንዲህ ቢሆንም ሲሰበክልን የኖረው ግን እዚህ ገዳም የሄደ ይህን በረከት ያገኛል፤ ይህን ስፍራ የረገጠ እንዲህ ይሆንለታል የሚል ስለሆነ የሊቃውንት ጉባኤውም ያን ይዞ ይሆናል እንዲህ መናገርም ኑፋቄ ነው ሲል በጥናቱ ያካተተው፡፡

በዚህ ዘመን እንኳን አክሱም ጌታ ብዙ ሥራ የሰራባትን ኢየሩሳሌምን መሳለም ከጉብኝት ያለፈ ተግባር የለውም፡፡ የሚገኘውም ከጉብኝት የሚገኘው እርካታ ብቻ እንጂ መንፈሳዊ የሚባል በረከት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ስለዚህ በረከትን ለማግኘት ወደበረከት ምንጭ ወደ እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል መቅረብ እንጂ እንደቱሪስት ከቦታ ቦታ መንከራተት አያስፈልግም፡፡

«ሰ. በቃና ዘገሊላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያቀረበችውን የእናትነት ምልጃ በመቃወም ጽፈዋል፡፡ መጥቅዕ መጽሔት - መስከረም 1994 ዓ.ም. እትም ገጽ 11)

የቃና ዘገሊላ ዋና ነገር ምንድን ነው? የጌታችን ክብር መገለጥ ነው፡፡ ይኸውም ሊታወቅ ሐዋርያው ዮሐንስ ተአምሩ ከተፈጸመ በኋላ ክፍሉን የሚደመድመው «ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።» (ዮሐ. 2፡11) በሚል ነው፡፡ ስለ ማርያም አማላጅነት ግን ያለው አንዳች ነገር የለም፡፡ ታዲያ ከየት አምጥታችሁ ነው ማርያም በቃና ዘገሊላ ሰርግ ቤት ምልጃ አቀረበች የምትሉት? በዚህ ክፍል የቀረበ ምልጃ የለም፡፡

እመቤታችን «የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም» ማለቷ ዛሬ አማላጅነት ከሚባለው ትምህርት ጋር እንዴት ሊዛመድ እንደሚችል ግልጽ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ጸሎት አይደለም፡፡ በሰርግ ቤቱ የተገኘችው ድንግል ማርያም የወይን ጠጁን ማለቅ ተረድታ በስፍራው አብሯት ላለው ጌታ ለልጇ ነገረችው፤ እርሱም አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም ሲል መለሰላት፡፡ ይህም የሚያሳየው እርሷ ለእርሱ ስለ ወይን ጠጁ ማለቅ ከመናገሯ በፊት ኢየሱስ እዚያ የተገኘው ውሃውን ወደ ወይን ጠጅ ለውጦ ክብሩን ለመግለጽ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ስለዚህ የእርሷ ጥያቄ ቀረበም አልቀረበም ጌታ ውሃውን ወደ ወይን ለመለወጥና ክብሩን ለመግለጽ በዚያ እንደተገኘ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ጊዜውን እየጠበቀ ነበር፡፡ ከጊዜው ቀደም ብላ ነው እርሷ ጥያቄውን ያቀረበችው፡፡ በኋላም የሚላችሁን አድርጉ አለች፡፡ እርሱም ጋኖቹ በውሃ እንዲሞሉ አዘዘና ድንቅን አደረገ፡፡ ክብሩንም ገለጠ፡፡

በአንድ በኩል ይህ ነገር የሆነው ማርያም በምድር ላይ እያለች ስለሆነ እንደምልጃ ይወሰድ ቢባል እንኳ በአጸደ ሥጋ ለሆነው ምልጃ እንጂ በአጸደ ነፍስ አለ ለሚሉት ምልጃ ለመጠቀስ የሚበቃ ጥቅስ አይደለም፡፡ መቼም ቅዱሳን በአጸደ ስጋ ሳሉ አንዱ ለሌላው እንዲጸልዩ ታዘዋል (ያዕቆብ 5፡16)፡፡ መጸለይም ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የሚከናወነው ዛሬ ብዙዎች እንደሚያስቡት አንዱ ወደ ሌላው (በሕይወት ያለው ምእመን ወዳንቀላፋው ቅዱስ) በመጸለይ አይደለም፡፡ ወይም እኛ ወደ ማርያም አማልጂን ብለን እንጸልያለን ማለት አይደለም፡፡ በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ጸሎት ሊቀርብ የሚገባው ወደ አምላክ ብቻ እንጂ ወደ ፍጡር አይደለም (መዝ. 64፡1)፡፡ ከእዚህ አንጻር እመቤታችን አምላክ ስላልሆነች የእኛን ጸሎት ለመቀበል ባለመብት አይደለችም፡፡ የእኛን የአማልጂኝ ልመና ለመስማት የምትችልበትም አምላካዊ ማንነት የላትም፡፡ እርሷ የከበረች የጌታችን እናት ብትሆንም፣ በስፍራ የተወሰነች፣ በዕውቀት የተወሰነች፣ በችሎታ የተወሰነች ናት፡፡ ጸሎት ተቀባይ ባትሆንም፣ ከዚህ ምድር ወደ እርሷ የሚቀርበውን የአማልጂን ልመና ለመስማት እንዳትችል ውስንነቷ ይከለክላታል፡፡ ይህ ችሎታ (ሁሉን ማወቅ፣ በሁሉ ቦታ መገኘትና ሁሉን መቻል) በዚህ ምድር እያለችም ቢሆን አልነበራትም፡፡ እነዚህ ባሕርያት የአምላክ ብቻ ናቸው፤ አምላክንም ከፍጡራን የሚለዩት ባህርያት ናቸው፡፡

እርሷ ብቻ ሳትሆን ሌሎቹም ቅዱሳን እንደዚሁ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የገለጸላቸውን የተሰወረ ነገር ማወቅ ስለቻሉ ቅዱሳንን ሁሉን አዋቂ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አይጠፉም፡፡ ለምሳሌ ጴጥሮስ የሐናንያና የሰጲራን ድብቅ ሤራ አውቋል፡፡ የገለጠለት ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ይህ ግን ጴጥሮስ ሁልጊዜ ያውቃል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ጴጥሮስ ከቆርኔሌዎስ መልእክተኞች እየመጡ ሳለ የተገለጠለትን ራእይ ምንነት በሚገባ አላስተዋለም ነበር፤ «ጴጥሮስም ስላየው ራእይ። ምን ይሆን? ብሎ በልቡ ሲያመነታ» (የሐዋርያት ስራ 10፡17) ይላል ቃሉ፡፡ መልእክተኞቹ እንደመጡም ቀድሞ ራእዩን ማስተዋል ያልቻለው ጴጥሮስ፣ ስለመጡት መልእክተኞች ያወቀው አንዳች ነገር አልነበረም፡፡ «ጴጥሮስም ወደ ሰዎቹ ወርዶ። እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበትስ ምክንያት ምንድር ነው? አላቸው።» ይላል (የሐዋርያት ስራ 10፡21)፡፡ ስለዚህ ለአንድ ጊዜ እግዚአብሔር ክብሩን ለመግለጥ የገለጠላቸውን ነገር የእነርሱ ባሕርይ አድርጎ መውሰድና ቅዱሳንን ሁሉን አዋቂ ማድረግ ትልቅ ስሕተት ነው፡፡

የምልጃን ነገር በሚመለከት እመቤታችንን ጨምሮ ሌሎቹም ቅዱሳን፣ በአጸደ ነፍስ እንደማይለምኑ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ «ሰአሊ ለነ ቅድስት» «ቅድስት ሆይ ለምኚልን» ለሚለው የውዳሴ ማርያም አረፍተ ነገር የሰጡት አንድምታዊ ማብራሪያ «[አሁን/ በአጸደ ነፍስ] ልመና እንኳን በእርሷ በሌሎችም [ቅዱሳን] የለባቸውም፡፡ በቀደመው ልመናዋ ስለምታስምር እንዲህ አለ እንጂ» ይላል፡፡ ሊቃውንቱ እንዲህ ብለው የሚያምኑ ቢሆንም፣ በልማድ ሲሰራበት የኖረውን ልምድ የያዙ ሌሎች ምእመናንና ካህናት ግን እነርሱ ወደ እርሷ ሲጸልዩ እርሷ ወደ እግዚአብሔር እንደምትለምንላቸው ያስባሉ፡፡ ይህ ግን ስሕተት ነው፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለትን ስለማርያም አማላጅነት ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ ትልቅ አላዋቂነትን ነው የሚያሳየው፡፡ አሁን ያለው የሊቃውንት ጉባኤውና ሲኖዶሱ ግን ይህ ምዕራፍ ስለ ማርያም ምልጃ ይናገራል ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ እንዲያውም ለቤተክርስቲያኗ በታተመው የሚሌኒየሙ እትም (የ2000 ዓ.ም.) መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለዚህ ክፍል «ስለእናቱ ምልጃ» የሚል ርእስ እንዲሰጠው መደረጉ ቤተክርስቲያኗ እውነትን ላለመቀበልና ልማድን ላለመተው ስትል መጽሐፍ ቅዱስን እያዛባች መሆኗን የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ ለዚህ ክፍል በግእዙ አዲስ ኪዳን ላይ ተሰጥቶት የነበረው ርእስ አንድ ነበር፤ እርሱም «በቃና ዘገሊላ ሰርግ እንደ ተደረገ» የሚል ነበር፡፡ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ለዚህ ክፍል በማይስማማና ባልተለመደ ሁኔታ ሶስት ርእስ ተሰጥቶት እናገኛለን፡፡ እንዲህ ማድረግ የተፈለገው ክፍሉ ስለማርያም አማላጅነት ነው የሚናገረው የሚለውን የሀሰት ትምህርት ለማጽናት ነው፡፡ እውነትን እያወገዝን ሐሰትን የምናነግሠው እስከ መቼ ይሆን? 
       
«4ኛ. ‘ጾመ ማርያም’ በተሰኘው መጽሔታቸው፡-
‹‹ሀ. ጾመ ማርያም ከቅዱስ ወንጌል አሳብና ትዕዛዝ ጋር የሚቃረን ነው’ ብለዋል፡፡ ገጽ 3
‹‹ለ. ማርያም ተነሣች፣ አረገች የሚለው አፈንጋጭ ትምህርት ጸረ ወንጌል የሆነ ጸሓፊ የጻፈው ነው’ በማለት የእመቤታችን ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ይቃወማሉ፡፡ ገጽ 8»

በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ ተረቶች የእውነትን ስፍራ ቀምተዋል፡፡ አንዱ ተረት ማርያም እንደ ልጇ ተነሥታ አርጋለች የሚለው ኢመጽሀፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ነው፡፡ ለዚህ ሐሰተኛ ታሪክ በጾም እንዲታሰብም ሥርአት ተሰርቷል፡፡ ይህን ተረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለማድረግ ስለማርያም ያልተጻፉትን ጥቅሶች ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በመጥቀስ ማርያም ተነስታለች አርጋለች እየተባለ ነው፡፡ «አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።» (መዝ. 131፡8)፡፡ እንዲሁም «ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ።» (መኃ. 2፡10) የሚሉት ጥቅሶች ለዚህ ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ስለእርስዋ ተነግረው ቢሆኑ ኖሮ ግን ቢያንስ፣ ማርያም ተነስታለች አርጋለች ብለውና እነዚህ ጥቅሶች ማስረጃ አድርገው ሐዋርያት በጻፉልን ነበር፡፡ ነገር ግን ከሀዋርያት መካከል እነዚህን ጥቅሶች የጠቀሰ፣ ማርያም ተነስታለች አርጋለች ብሎ የጻፈልን አንድም የለም፡፡ አዋልድ መጻሕፍት ግን ብዙ ብለዋል፡፡

የምትሞትበት ጊዜ ሲደርስ ማርያም አልሞትም ብላ እንዳስቸገረች አዋልድ መጻህፍት ይተርካሉ፡፡ ከዚያ ጌታ ብዙ ነፍሳት ተኮንነው ወደ ሲኦል ሲወርዱ በራእይ አሳያት፡፡ እርስዋም እነዚህ ምንድን ናቸው? ብላ ጠየቀች፡፡  ጌታም የተፈረደባቸው ነፍሳት ናቸው አላት፡፡ እርሷም ልጄ ሆይ እባክህን ማርልኝ አለችው፡፡ እርሱም መልሶ እኔ አዳምና ሔዋንን ያዳንኩት ሞቼ ነውና እንዲድኑ ከፈለግሽ ሙቺላቸው አላት፡፡ በዚህ ጊዜ እነርሱ ከሲኦል ሚወጡ ከሆነ እንኳን አንዴ አስሬም ልሙት አለችና ለመሞት ፈቃደኛ ሆነች፡፡ ይህ ከእውነት ጋር መላተም ነው፡፡ ስለሰው ሁሉ የሞተውና ቤዛ የሆነው ክርስቶስ ብቻ ነው የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነው የሚቃረነው፡፡

ሞት በሃጢአት ምክንያት ወደሰው የደረሰና ሁሉ የሚካፈለው ርስት ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ድንገት ይጠራል እንጂ ምት መጥቶ ድርድር ውስጥ አይገባም፡፡ እመቤታችንም ጊዜዋ ሲደርስ አንቀላፍታለች እንጂ አልሞትም ብላ ሞትን የምታስቸግርበት አንድም ምክንያት የለም፡፡ ለነገሩ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ አይደለም አደረጉ የሚባለው? ለመሞት የሚያበቃ ምንም ክፉ አልሠራሁም፤ እንዳንተ የእናቴን ጡት አልጠባሁም ብለው ጌታን እንደተከራከሩትና አልሞትም አሻፈረኝ እንዳሉ ገድላቸው ይተርክ የለምን? እንዲህ አይነቱ የገድላት ታሪክ በምንም መለኪያ እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሰው በሞት ድንገት ሲጠራ ይሄዳል እንጂ ሊወስደው ከመጣው ሞት ጋር መከራከርም ሆነ የጥሪውን ቀን ሊሰርዝ ወይም ሊያራዝም አይችልም፡፡

ከእውነታ የራቀ ልቦለድ መጻፍ ልማዳቸው የሆነው አዋልድ መጻሕፍት ግን ማርያም የሞተችው በግድ ነው በማለት ሞቷን የተለየ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ ይህም ተነሥታ አርጋለች ወደሚለው ሐሰተኛ ትምህርት ለመሸጋገር እንደ መንገድ ጠራጊ ነው የተወሰደው፡፡ ሌላው የአዋልድ ደራሲ ደግሞ ጌታ በዘመድ እንደማይሠራና ሞት ለሰው ሁሉ የተመደበ መሆኑን እንዲህ ሲል ስንኝ ቋጥሯል «… ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ፤ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፤ ሞታ ለማርያም የዐፀብ ለኩሉ»  «በሞት ላይ ክርሰስቶስ ለሥጋ ዘመዱ (ለማርያም) አላደላም፡፡ ሟች ለሆነ ሰው ሁሉ ሞት ተገቢው ነው፡፡ የማርያም ሞት ግን ያስደንቃል» ብሏል፡፡ በሞት ላይ ካላደላ በትንሣኤ አያደላም፡፡ ስለዚህ ማርያም ተነስታ አርጋለች የሚለው ትምህርት የማርያም ወዳጅ ሳይሆን ፀረ ወንጌል አቋም ያለው ጸሐፊ ነው የጻፈው የሚለው ትክክል ነውና፣ ይህን የጻፈው የከሣቴ ብርሃን መጽሔት ሐሰትን በማጋለጡ እውነትን በመመስከሩ ሊመሰገን እንጂ ሊወገዝ ባልተገባው ነበር፡፡ መወገዝ ያለበትስ ማርያም ተነስታለች አርጋለች ሲል የሚቀላምደው የተሳሳተ ትምህርት ነው፡፡

ጌታ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ ማንንም ከሙታን መካከል እንዳላስነሣና ሰው ሁሉ ትንሳኤን ወደፊት እንደሚጠብቅ የቀደሙት አበው መስክረዋል፡፡ «እርሱ በመዋቲ ሥጋ ይነሳ ዘንድ በፍቃዱ ሞተ፡፡ ከተነሳም በኋላ ዳግመኛ አይሞትም ፤ ከትንሳኤው በኋላ ግን ጌታ ይህንን አልተናገረም፡፡ ከሰውም ወገን ማንንም ተነሳ ከመቃብር ውጣ አላለም፡፡ ዳግመኛ እስከሚመጣበት ቀን ደረስ ለሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው በሚነሡበት ጊዜ ሙታን ይነሣሉ አላቸው፡፡ ከሙታንም ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ከሞቱት ሁሉ ማንንም በሥጋ እንዳላስነሣ አስተውል፡፡” (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 59 ቁጥር 49-50)፡፡
“አብ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ከሰጠው ከምእመናን አንዱንስ እንኳ አላጠፋም፤ ፈጽሞ አዳናቸው፤ በኋለኛይቱ ቀን አስነሣቸው (ያስነሣቸዋል) እንጂ እንደምን ያስነሣቸዋል? ከሙታን ተለይቶ እርሱ ብቻ ስለተነሣ ነው እንጂ፡፡ . . . ከሰማይ የመጣ የእግዚአብሔርን ቃል በሥጋው ብቻውን ከሙታን ቀድሞ እንደተነሣ እናውቃለን በተነሣ ጊዜ አባቱ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ለርሱ የሰጣቸው ምእመናን በትንሣኤ ይመስሉት ዘንድ እንግዲህ ወዲህም በቀድሞው ሰው አዳም ትእዛዝ በማፍረስ ምክንያት ፈርሰው በስብሰው አይቀሩም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እሺ በጀ ብሎ እስከ ሞት በመድረሱ እነርሱ ፈጽመው ይድናሉ እንጂ” (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 7 ክፍል 50 ቁጥር 51 እና 52)፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ሰለባ የሆነውና የሊቃውንት ድርቅ ያጠቃው የግንቦቱ ሲኖዶስና ገድል ተቃሹ የሊቃውንት ጉባኤው ግን ያን ሲወርድ ሲዋረድ መጣውን ልማዳዊ የስሕተት ትምህርት ከማጽደቅ በቀር በእውነት ሚዛንና በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አስተምህሮ ነገሮችን ለመመርመር ብቃቱም ፈቃደኛነቱም ያላቸው አልመሰለም፡፡ እንዲያማ ቢሆን ይህን ልማዳዊ ትምህርት የሚያስጥለውን የአበውን ሃይማኖት ጠቅሰው ይህስ አያስወግዝም፤ እንዲያውም ማርያም ተነስታለች፤ አርጋለች የሚለው በልማድ የተያዘው ትምህርት መስተካከል ነው ያለበት ባሉ ነበር፡፡

ለነገሩ ሊቃውንቱ «ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር፣ የማይመስል ነገር፣» ብለው የለ!

ይቀጥላል

32 comments:

 1. እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር- silezih wongel mesbek ayasfeligim malet new?

  ReplyDelete
  Replies
  1. አይ ልብ አውልቄ!
   የእግዚአብሔርን ሐሳብ እንዲህ ቆርጦ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ጌታ ለምን እንዲህ አለ? አንተ እንደመሰለህ ወንጌል መስበክ አያስፈልግም ለማለት ነው ወይ? አይደለም፡፡ አንተም ብትሆን እንዲህ ለማለት ይህን ቃል እንዳልተናገረ ኅሊናህ ያውቀዋል፡፡ ለምን እንዲህ አለ ብትል መልሱን ከፍ ብለህ ብታነብ ታገኘዋለህ፡፡ እንዲህ ይላል፤ «ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።» ቀድሞ በጽላት ላይ የተጻፈው ህግ አሁን በአማኞች ልብ ውስጥ ስለሚጻፍና በውስጣቸው ስለሚሆን ሁሉ እግዚአብሔርን ያውቀዋል ማለት ነው፡፡ የታቦት አገልግሎት መቆሙ ግን እውነት ነው፡፡ እርሱን ላለመቀቀበል ስትል ያልሆነ ነገር መሰንቀር አላዋቂነት ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አድ ቃል ኪዳን እንደገባ ልትቀበል የቀደመው ኪዳን በአዲሱ ኪዳን እንደተተካ ልታምን ይገባል፡፡ በአዲሱ ኪዳን ውስጥ ታቦት የለም!!!!!!!

   Delete
  2. ምን አድርቁ ነህ እባክህ ፤ ትንቢትን ለገዛ ራሳችሁ አትተርጉሙ ሲልህ ፣ አሻፈረኝ በማለትህ አደናብረህ ገደል ይዘኸን ልትገባ ነበር ፡፡

   ኤር 31፡33 - 34 ከእነዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፥ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል።
   እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን። እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና።

   የወደድከው ሙሉ ቃል ከላይ የሠፈረው ስለሆነ እንግዲህ ተጠየቅልኝ ፡-
   - መጀመሪያ ይህን የትንቢት ቃል ጌታ መናገሩን በምን አወቅህ ? ወይስ የእግዚአብሔርን ማለትም የአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ስም ሁሉ ለጌታ አወረስክ ማለት ነው ?

   - እነዚያ ወራት የሚላቸው የትኞቹን ወራት ነው ?
   - በዚህ ትንቢት መሠረት እስራኤላውያንስ ሕዝቡ የሆኑትና የተባሉት ከመቼ ጀምሮ ነው ?
   - ገና ከብሉይ እንኳን ያልተሸጋገሩ ሆነው ሳለ እንደምን ቢደረግ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል ፤ ህጌንም በልቡናቸው አኖራለሁ ይለናል ?

   - እንዲያ ከሆነስ ደግሞ ሐዲስ ከቶም አታስፈልግም ማለት አይሆንብህም ? የኢየሱስንስ የመስቀል ላይ መስዋዕትነትንስ ሁሉ ነጻ አላስቀረኸውም ?

   - ሐዋርያው በህግ መዳን የለም በእምነት እንጅ እያለ ፣ የትኞቹን የእግዚአብሔር ህጐች ወይም ህግ ነው እንዳይዘነጉ በልቡናቸው የሚያኖረው ? አይሁዳውያን አሁንም ገና የሚዳክሩበትን የብሉይን ሥርዓት ለማለት ወይስ በልቡናቸው የማናውቀው የተሰወረ ህግ ይኖራቸው ይሆን ?

   ስለዚህ ሁላችንንም ሊያግባባ የሚችል ቃል ስለማይኖረን ፣ አንዱም ሌላውን ማስተማር ስለማይሆንለት ፣ እርስ በርስም ከምንጠላለፍ እያንዳንዳችን የምናምነውን ይዘን ያለ ነቀፋ ሆነን ብንቀጥል መልካም ይመስለኛል ፡፡ ቀና ልቡና እስከ ሌለ ድረስ አንዱ ሌላውን ሊረዳና ሊያርም አይችልም ፡፡ በሰለጠነው ዓለም ሰይጣንን እንኳን አመልካለሁ ብሎ የሚንገዛገዘውን ትንፍሽ የሚልበት የለም ፤ እንኳንስ በቃላት ትርጓሜ መለያየት ብቻ የሚከፈለውን ወገን ለመውቀስ ፡፡ እኛ ታድያ ሃይማኖት መተዳደሪያችን ፣ የጉረሮ ነገር ስለሆነብን ወይስ የመቻቻል ባህል ስለሌለን ይሆን የምንዋቀስ ?

   Delete
  3. To anonymous August 13

   So why don't Muslims & others don't know God (Jesus),if the lawas are written at their heart?

   Delete
 2. **** ኤር 3፡16 – 17 ተጠቅሶ ለቀረበው ፡- መጀመሪያ ኢየሩሳሌም መች የእግዚአብሔር ዙፋን ተብላ ተጠራች ? አሕዛብስ ሁላ መች ተሰበሰቡባትና ትንቢቱ ተፈጽሟል ይባላል ? እንዲየውም ፍልስጥኤሞች ከወሰዷት ትንቢቱ እስከወዲያኛው አይታሰብም ፡፡ ቀንጭባችሁ የሚስማማችሁን ፣ የናንተን ቃልና ፍላጐት የሚያጸናውን ጐርዳችሁ አቀረባችሁ እንጅ ፣ ተከታዩን ቁጥር ቀጥላችሁ ብታነቡት “እግዚአብሔርስ በበዛችሁ ጊዜና በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ” የሚል ቃል አስከትሏል ፡፡ በዛችሁ የሚባለው የእሥራኤል ሕዝብ ቁጥር ስንት ሲሆን ? በየትኛውስ የምድር ክልል ተራብተው ሲታይ ነው ትንቢቱ ተደምድሟል ፤ ታቦትም ቀርቷል ለማለት የሚቻለው ?

  **** ኤር 31፡31 – 34 ተጠቅሶ ለቀረበው ፡- ይኸኛውም ትንቢት ተፈጽሟል ለማለት ለእኔ ገና እጅግ ብዙ ይቀረዋል ፡፡ እግዚአብሔርን እናውቃለን የምንለው ይኸው እኛና እናንተ እንኳን መች ተግባብተን ፣ አንድ ቃል ተናግረንና ነው ትንቢቱ በብሉይ ዘመን ተፈጸመ ለማለት የተፈለገው ? በሌላው ክፍለ ዓለምና አገር ሳይሆን ፣ በአገራችን እንኳን ገና ስንት የአምላክ ስምን ያልሰማ አሕዛብ እያለ ፣ የታቦት አገልግሎትና ሥርዓት ቀርቷል ለማለት ብቻ ፣ እግዚአብሔርን እወቅ ማለትና ማስተማር አያስፈልግም ለማለት ተደፈረ ? ወይስ የወንጌል ስብከትን ማስተጓጐልም ነው ተጨማሪው ተልዕኰአችሁ ?

  ከዚህ ቀደም የተገለጸ ቢሆንም ፣ በዚህኛው ዘመን መስዋዕታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ በመቅረቡ ፣ የጥንቱ እንስሳ የመሰዋትና የማቅረብ አገልግሎት ተሽሯል ፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያናችን ታቦትን የአዲስ ኪዳኑን መስዋዕት ለመፈተት /ለመቁረስ/ ትጠቀምበታለችና የተሻረውን ካልተሻረው ወይም ከተሻሻለው ለይቶ ለመረዳት አባቶችን መጠየቅ መልካም ነው ፡፡

  **** «እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚሰግዱለትም በእውነትና በመንፈስ ሊሰግዱለት ይገባል» የሚለውን የመጽሐፍ ቃል እኛም የምንገለገልበት ነው ፡፡ ታቦት አጠገባችን ቢገኝና ብናየውም /በንግሥ ቀን ሲወጣ ማለት/ ፣ የምናመልከው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን ስለሆነ ፣ ጸሎትና ስግደታችን ሁሉ የምናቀርበው በመንፈስ ነው ፡፡ ታቦቱን እየዳበስንና እየዳሰስን አልሰገድንለትም ፡፡ ሆኖም ግን የአምላክ ስም አለበትና የአክብሮት ስግደት ይፈጸማል ፡፡ በማይነግሥበት ቀናት ደግሞ ፣ ታቦትን ባናይም ጸሎትና ልመናችንን በመንፈስ ሆነን ለአምላካችን እናቀርባለን ፡፡

  **** “ቤተክርስቲያኗ አሁን የቆመችው በተመሰረተችበት የወንጌል መሰረት ላይ ነው ብሎ ማንም ሊከራከር አይችልም፡፡ እንዳልሆነ ይታወቃልና፡፡”
  ዓላማችሁ ዓይን ጨፍኖ ለመካድና ለመቃወም ከሆነ ፣ ኢየሱስንም እንኳን አልሞተም አልተነሳምም ማለት ትችላላችሁ ፡፡ ስለ ኢኦተቤ ካለመረዳትና ካለማወቅ ከሆነ ግን አሁንም የሚያውቁ ሊቃውንትንና ካህናትን እንዲያስረዷችሁ ጠይቁ ፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ እንዳለ ቃል በቃል የሚተረጎምባት ፣ በወረቀት ላይ የሰፈረው ቃል ፣ በተግባር የሚታይባት ፣ አገልግሎቷና ሥርዓቷ በሙሉ ከመጽሐፍ የተስተካከለባት ቤተክርስቲያን የሆነች ፣ ይህችው የኛዋ ብቻ ናት ፡፡ ሌሎች ኦርቶዶክስ የሚለውን ስም ቢይዙም ሌላ ቀርቶ ታቦቱ የሚባል እንኳን የላቸውም ፤ በአምሳያ ነገር ነው የሚገለገሉት ፡፡

  በተረፈ የምእመንን ቁጥር ማነስና መጨመር የችግር መለኪያ አድርጎ የማቅረብ መልዕክቱ አይገባኝም ፤ የሐዋርያነት ሥራ የቁጥር ሳይሆን የወንጌል መልዕክትን ላልሰማ ሁሉ የማዳረስ ተግባር ነው ፡፡ በሐዋርያነቷ የምትታገለውም ወንጌልን ሁሉም ወገን እንዲሰማና የክርስቶስን አዳኝነት እንዲቀበል ለማድረግ ብቻ ነው ፡፡ መጽሐፍ እራሱ ከተጠራው በስተቀር ማንም አይመጣም ይላልና /ሮሜ 9፡11/ ፣ ትምህርቷን ተምሮ መከተል ለማይፈልግ ምንም ማድረግ አይቻልም ፡፡ መጥፋት የሚፈልግ በማንኛውም ሰዓት መፍለስ ይችላል ፤ መብት ነው ፤ አስገድዶና አሥሮ ማቆየት አይሞከርም ፡፡ እንደምረዳው ስለሚፈልሱ ወይም ከሚፈልሱ ተብሎ ግን ዶግማን የሚሽር ፤ ሃይማኖትንም የሚቀለብስ አባት አይኖርም ፡፡ እንዲያውም እየጠራ ሲሄድ ለሁላችንም መልካም ይሆን ይመስለኛል ፡፡ ትምህርቷን አምነው የሚቀበሉና የሚከተሏትን ምእመን ይዛ ትቆያለች ፡፡ እንዲያውም አሁን ወንጌል ገብቶናል ብለው የሚፈላሰፉብንንና ውጭ ውጭ የሚያዩት ሁሉ ፣ አንድ ቀን እውነቱ ተገልጾላቸው ፣ የሄዱበትም ቤት የባሰ ቁሻሻና እሳት እንዳለ አይተውና ፈትሸው በንስሐ ሊመለሱ ይችላሉ የሚል ተስፋ አለኝ ፡፡ ሞክረውት የተመለሱ ብዙ ስላሉ ይህን እላለሁ ፡፡

  የተቀረውን ጽሁፍ ለማንበብ ጊዜና ትዕግሥቱ ከተገኘ ማርከሻው ይቀጥላል ፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ማርከሻ ጽሁፍ እያቀረብክ እንዳለህ ይሰማሃል? የሚገርመው ግን የረከሰ ጽሁፍ እንዳቀረብክ አለማወቅህ ነው። ሌላውን ዝባዝንኬ ተወውና ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ስጥ።
   1/ ታቦት ማለት ምን ማለት ነው? አዎ ታውቀዋለህ። ግን የኦሪቱን ልኩንና ስፋቱን ታስተውላለህ?
   2/ ጽሌ ማለት ምን ማለት ነው? አዎ ይህንንም ታውቀዋለህ። ግን የኦሪቱን ማን እንደጻፈባቸውና ምን እንደተጻፈባቸው ታውቃለህ?
   3/የኦሪቱ ኪዳን የተሰጠው ለማን ነው? ይህንንም ታውቃለህ። ግን የሐዲሱ ኪዳንስ ለማን ነው?
   4/ ዛሬ አለን የምትለው ታቦትና ጽላት ኪዳኑ ለማነው? የእግዚአብሔር ኪዳን በቃሉ ይጸናል። ወርዱን፤ ስፋቱን፤ ርዝመቱን፤ አገልግሎቱንና አፈጻጸሙን የገለጸበት የቃሉ ኪዳን ምንድነው?
   5/ የእስራኤሎች የኪዳኑ ታቦት ሁለት ናቸው። ያንተ የኪዳኑ ታቦት ስንት ናቸው?
   ጽላት በኢትዮጵያ ብቻ አገልግሎት ይሰጣል፤ ለኢትዮጵያ የተሰጠ የጽላት ቃል ኪዳን አለ? በመጽሐፍ ቅዱስ የትኛው ክፍል ላይ ይገኛል።
   ምክንያትና ግብስብስ ሃሳብ ተቀባይነት የለውም። እስኪ ይህንን ጥያቄ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ መልስ ስጥበት።

   Delete
  2. የምን ሸፈፍ ሸፈፍ ፡፡ እንደ ጽሁፉ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ከእንስሳ መሰዋት በስተቀር ታቦት ቀርቷል ይላል በለኝና ምዕራፍና ቁጥር እየጠቀስክ አስረዳኝ እንጅ ፡፡ ለምን አናጺ ይመስል ልኬት ትጠይቃለህ ፡፡ አስመስሎ ለመስራት ከሆነ በቅርብ ውስጠ ምስጢሩን የሚያውቁትን ጠይቅና ተረዳ ፡፡ እንደ አባባልህ ለኢትዮጵያ የተሰጠ የጽላት ቃል ኪዳን ላይኖር ይችላል ፡፡ ነገር ግን ለኢትዮጵያ የተባለና የታዘዘም ክርስትናም ከመጽሐፍ አታገኝም ፡፡ ስለዚህ ጥያቄህ ሁሉ አግባብነት የሌለው ነው ፡፡ ለእሥራኤላውያን የተነገረውን ሁሉ ለዓለም በሙሉ እያዳረስክ ለመተርጎም እንደምትሞክር ከቶም አልታወቀህም ማለት ነው ፡፡ ለልጆች ከመጣው ውሾችም ፍርፋሪ ይጠግባሉና ፡፡የሃይማኖትን ሥርዓት በኬላ ልትገድበው የምትሞክር በመሆንህ ሥራህን ከንቱ ልፋት ብየልሃለሁ ፡፡

   Delete
  3. you man, you have different views than him and orthodox church; though, you share 100% of Pente's teaching about everything. so why don't you stop your own ዝባዝንኬ and start believing in whatever God you want to believe? the one which doesn't have Tabot in their hall.
   Q. do you have one teaching in which Pentes accept and you don't?

   መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ መልስ ስጥበት። ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ ያሉት ሁሉ ለምሳሌ ቁጥሩ ስንት እንደሆነ ማን እንደፃፈው መጽሐፍ ቅዱስ ጠቅሰህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ መልስ ልትሰጠኝ ትችላለህ? ለራስህም "ምክንያትና ግብስብስ ሃሳብ ተቀባይነት የለውም።" ያልከውን አስታውሰው::

   Delete
  4. ትንቢቱ መፈጸሙን በዕብራውያን መልእክት ውስጥ በመመልከት ማረጋገጥ ትችላለህ፡፡

   «ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር።
   እነርሱን እየነቀፈ ይላቸዋልና። እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ፤
   ከግብፅ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው ይላል ጌታ።
   ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል።
   እያንዳንዱም ጐረቤቱን እያንዳንዱም ወንድሙን። ጌታን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና።
   ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም።
   አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል።»
   (ዕብ. 8፡8-13)
   «መንፈስ ቅዱስም ደግሞ ስለዚህ ይመሰክርልናል፤ ከዚያ ወራት በኋላ ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው ይላል ጌታ፤ በልባቸው ሕጌን አኖራለሁ በልቡናቸውም እጽፈዋለሁ» (ዕብ. 10፡15)
   ሐዲስ ኪዳን ብሉይ ኪዳን መፈጸሙን እንዲህ እየነገረን አንተ ግን የኢትዮጵያ ታቦት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው በማለት ጉንጭ አልፋ ክርክር ትከራከራለህ፡፡ ምናለበት ለእግዚአብሔር እውነት እጅ ብትሰጥ፡፡ ምናለበት ከልማድ ወጥተህ በቃል ብታምንና የዘላለም ሕይወት ባለቤት ብትሆን? አንተ ሰው ስለ ወግህና ልማድህ የእግዚአብሔርን ቃል ለምን ታጣምማለህ? ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣላ እንዳትገኝ ለራስህ ብታስብበት ይበጃል እላለሁ፡፡

   Delete
  5. የፊተኛው ኪዳን የሚለው የእንስሳ መስዋዕቱን ፣ የደም መርጨቱን ሥነ ሥርዓት የነበረውን በኢየሱት መስቀለ ሞት መሻሩን ለማመላከት ብቻ ነው ፡፡ አሁንም ታቦት ተሽሯል የሚል አንድም ሥፍራ ላይ አታስነብበኝም ፡፡ ካልተጻፈ ደግሞ በስሜት ሆነን ተሽሯል ፣ ቀርቷል ብለን አናውጅም ፡፡ የአዲስ ኪዳኑን መስዋዕት ለመቁረሻ እንጠቀምበታለን ፡፡

   Delete
 3. ayi minfikinaa!!! demo akim norachihu litechu tifeligalachuuuu!!! lemin ayhonim, esmealbo neger zeyisano leigziabher???????????

  ReplyDelete
 4. please please please collect this things and print them.

  ReplyDelete
 5. ውሸት ሲሰነብት እውነት ይመስላል በገድላገድልና በውሸት ታሪክ የተመረዘ አ'እምሮ
  በል እውነትን ተቀበል ቢሉት ዘጠኝ ምክንያት ይፈጥራል እንጂ ሊመለስ አይችልም፤
  ምክንያቱም የፈጠራ ጽሑፎቹ የገቢ ምንጮቹ ናቸውና የሰው ልጅ ሳይወድ ተገዶ እውነትን የሚቀበልበት ጊዜ አለ ይሄውም የያዘውን የረዘዘውን በሚያጣበትና የሻውን የተመኘውን በማያገኝበት እንዲሁም የእግዜር መቻያ ድንገት በሚደርስበት ጊዜ ይሆናል
  ያን ጊዜ በሌላ እጅ መውደቅ ሲመጣ እጅ ወደላይ ይሆናልና በውሸት የተካት እውነት
  ጸጸት ትሆንበታለች (የማታ ማታ እውነት ትረታ)ለሥጋ ጥገና ተብሎ ዓይን ያወጣ ውሸት የልብ ትዝብት(ሆድ ሲያውቅ ማታ ዶሮ)ገድል ተአምር ድርሳን አነባለሁ
  እየተባለ በዚህ ምክንያት ወንድምን ማሳደድና በባለእንጀራ መፍረድ በራስ ፈቃድ
  ወደሲኦል መውረድ ነው፤ እናም ለዘመኑ ቅዱሳን ልብ ይተካላቸው፤

  ReplyDelete
 6. ውሸት ሲሰነብት እውነት ይመስላል በገድላገድልና በውሸት ታሪክ የተመረዘ አ'እምሮ
  በል እውነትን ተቀበል ቢሉት ዘጠኝ ምክንያት ይፈጥራል እንጂ ሊመለስ አይችልም፤
  ምክንያቱም የፈጠራ ጽሑፎቹ የገቢ ምንጮቹ ናቸውና የሰው ልጅ ሳይወድ ተገዶ እውነትን የሚቀበልበት ጊዜ አለ ይሄውም የያዘውን የረዘዘውን በሚያጣበትና የሻውን የተመኘውን በማያገኝበት እንዲሁም የእግዜር መቻያ ድንገት በሚደርስበት ጊዜ ይሆናል
  ያን ጊዜ በሌላ እጅ መውደቅ ሲመጣ እጅ ወደላይ ይሆናልና በውሸት የተካት እውነት
  ጸጸት ትሆንበታለች (የማታ ማታ እውነት ትረታ)ለሥጋ ጥገና ተብሎ ዓይን ያወጣ ውሸት የልብ ትዝብት(ሆድ ሲያውቅ ማታ ዶሮ)ገድል ተአምር ድርሳን አነባለሁ
  እየተባለ በዚህ ምክንያት ወንድምን ማሳደድና በባለእንጀራ መፍረድ በራስ ፈቃድ
  ወደሲኦል መውረድ ነው፤ እናም ለዘመኑ ቅዱሳን ልብ ይተካላቸው፤

  ReplyDelete
 7. what new thing you added, this is already said by pentes.No d/c b/n u & them. pls I want to know in what you differ from protestants? up to now nothing d/t. The d/c is they r ur boss & u r servants.

  ReplyDelete
  Replies
  1. አሜን:: ልዮነታቸውን ሊነግሩህ አይችሉም ምክንያቱም የላቸውምና:: አንድነታቸውንም አያምኑም ምክንያቱም ስራቸውን ያጣሉና::

   Delete
 8. please i would rather get out of your( protestant) evil act. gay marriage is almost acceptable in western countries.the marriage is blessed by the so called "churches". you have to think about this sin rather than insulting God and the Servants.you and the protestants( in fact identical) have no moral to insult our church. THERE IS A SAYING THAT 'AMED BE DOKET YISKAL'

  ReplyDelete
 9. ይህ ጉዳይ በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት የእግዚአብሔር ቃል በልብ ውስጥ ሲበራ የሚታወቅና እጅን በአፍ ላይ በማስጫን ከመታወቅ የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር የተረዱ ሰዎች ብቻ የሚረዱት እውነት እንጂ 'ሰው' የተባለ ሁሉ ሊረዳው የሚችል ጉዳይ አይደለምና ሁሉን ማድረግ ለሚችለው አምላክ ዓይኖቻቸውን እንዲያበራ መጸለዩ ይሻላል:: እጅግ የሚያሳዝነው አብዛኛውን የዋህ ሕዝብ በዚህ ምድር በሚቀር የአገርና የሃይማኖት አጉል ፍቅር ስም ወደ ዘላለም ሞት መንዳታቸው ነው:: እንግዲህ የሚሰማ ጆሮ ያለው የመፈስ ቅዱስን ድምጽ ይስማ! ዓይን ያለውም ይይ!! ከማለት በስተቀር ምን ይባላል??? ክፉውን መልካም! መልካሙን ክፉ! ብርሃኑን ጨለማ! ጨለማውን ብርሃን! የሚሉትን በሰው አቅም ምን ማድረግ ይቻላል??? ወደ ሰማይ ከማልቀስ በስተቀር!
  ከሳቴ ብርሃኖችን ግን አሁንም የተደበቀውንና በሕዝባችን ሕይወት ላይ እየተጫወተ ያለውን ድብቅ የአጋንንት የማስመሰል ሥራ የማጋለጡን ተግባራችሁን አታቋርጡ ማለት እወዳለሁ:: አንዳንዶቻችንን መሪዎቻችን ከፈረዱብን ካጋንንት አምላኪነት እየነጠቃችህ ታወጡናላችሁና በርቱ!!! የተታለለ በርካታ ሕዝብ ዛሬ ጌታ እራሱን ስቅለው ስቀለው እንዳለ እናንተንም ቢላችሁ ከእውነት ጋር ደስ የሚለውና ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከእናንተ ጋር ነውና በርቱ በርቱ!!!

  ሰላም ለሕዝባችን በሙሉ!!!

  ሰላም ነኝ

  ReplyDelete
 10. የከሳቴ ብርሃንን ብዙዎቹን ጽሁፎች ማግኘት ብንችል ግን ከሲኖዶሱ ቅንጫቢ ጽሑፍ ጋር በማስተያየት ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ በቻልን ነበር፡፡
  if you didn't get, how can you say 'kinichabi'

  ReplyDelete
  Replies
  1. ምነው ጌታው!
   የከሳቴ ብርሃንን ጽሑፍ ቆርጦና ቀጥሎ ያቀረበውን የሲኖዶሱን ቃለጉባኤ በክፍል 3 ተመለከትን አነበብን ወይ? በተለይ የማይረሳው ተአምረ ማርያም ላይ የሰፈረውን የተአምረ ማርያም ቃል፣ ከሳቴ ብርሃን የጽሑፉ ርእስ አድርጎ አቅርቦ ሳለ፣ ሲኖዶሱ ግን ከሳቴ ብርሃን እንዲህ ብሏል ማለቱንና በዚህ የተነሳ ማውገዙን ረሳኸው እንዴ? የዲያቆን አሸናፊን ጽሑፍስ ምን ያህል እያዛባና እየለወጠ፣ ገልብጦም እያነበበ ለውግዘት እንዳመቻቸው አባ ሰላማ አስነበብ አይደለም ወይ? ታዲያ ይህም ጽሑፍ ቅንጫቢ ላለመሆኑ ምን ማስተማመኛ አለ? እንዲህ ከዋናው መንገድ ወጥተህ በተራ ትችት ጊዜህን ከምታቃጥል ምናለ በቀረበው ትምህርት ሕይወትህን ብትፈትሽ? ስለዚህ ዋናው ነገር ትተህ በተራ ነገር አቅጣጫ ለማስለወጥ አትሞክር፡፡ ግመልን ውጠህ ትንኝን አታጥራ፡፡

   Delete
 11. ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የጽርፈትና የጥፋት ዘመቻ የሚያካሂዱት በዋናነት የራሳቸው ማንነት የጠፋባቸው ምዕራባውያን(ሉተራውያን) ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ከመቶ ዓመታት በላይ በራሳቸው ጥረትና ስልት የወጡትን ያህል ወርደዋል፤ የወረዱትንም ያህል ወጥተዋል፤ ነገር ግን የተመኙትንና የፈለጉት በእጃቸው ማድረግ አልቻሉምና ሌላ ስልት ሌላ ስትራቴጂ መቀየስ ግድ ነው፡
  ፡ ይህ ስትራቴጂ ደግሞ ከዘመኑ ሥልጣኔ ጋር ሻማና ክር ሆኖ በመመሳሰል እንዲቀረጽ የተደረገ በመሆኑ ብዙዎቻችን የተሃድሶአውያን ተላላኪነት በፍጹም ሊገባን አልቻለም፡፡

  ተሃድሶ የፕሮቴስታንቱ ዓለም ተላላኪ መሆኑ ግልጥ ያለ ነገር ነው፡፡ ማስረገጫው ደግሞ በዚሁ አዚም የተማረኩ ወገኖች ይኸው ቡድን በሚያደረግው የጸሎትና የዝማሬ ዝግጅት ላይ ሲገኙ የገጠማቸው ፕሮቴስታንታዊ ሥርዓት ነው፡፡

  በመሠረቱ ማንም ሃሳቡን ማራመድ ይችላል፤ የፈለገውን ማመንም እንዲሁ፤ ዓለማመንም የራሱ መብት ነው፡፡ በእኛ ቅኝት ዝፈኑ ማለት ግን በእኔ ሳንባ ተንፍሱ፣ በእኔም አፍ ተናገሩ ማለትን ግን የትኛውም የሰው ልጅ ሊቀበለው የማይችል ጉዳይ ነው፡፡

  ልጅ የቤተሰቡ ነገር ካልተመቸው ወጥቶ በራሱ መንገድ ራሱን መምራት የሚጠበቅ ነው፤ የቤተክርስቲያን ነገር በልበ ደንዳናነቱ አልዋጥለት ያለውም እንዲሁ፡፡ ልጅ ነውና ይመከራል፣ ይዘከራል፣ የሚጠቅመው ይነገረዋል፣ እኔ ነኝ የማውቀው ካለ መንገዱ ሰፊ ነው መጓዝ ይችላል፡፡

  የተሃድሶአውያን መሠረታዊ ችግር ሁለት ነው፥ በእኔ እምነት፥

  አንደኛ
  ግብዝነት፥ እንደ ፈሪሳዊ፡፡ በእውቀት የደረጀን፣ ለወንጌል አገልግሎት ቀሚስ የታጠቅን፣ የበሰበሰ የአስተዳደር ሥርዓትን መቀየር የምንችል ምሩቃን፣ ልሂቃን ብሎ መኮፈስ፡፡ በመሠረቱ ክርስትና በእውቀት ሳይሆን በልጅነት፣ በጸጋ፣ በሰማዕትነት፣በየዋህነት የሚወረስ መንግሥት ነው፡፡ ሊቀ ሐዋርያ ቅዳስ ጴጥሮስ በሮም አደባባይ የቁልቁሊት ተሰቅሎ ያገኘው መንግሥት ነው፣ የሐዋርያት መሪ የነበረውም በትምህርቱም ልሂቅነት አይደለም፡፡ አስተውሉ!!!

  ሁለተኛ፥
  ከፍጹማዊው ሕግ ይልቅ ለሰው ሠራሹ ሕግ ቅሩብ መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከላይ የተገለጹት በሕግ ውስጥ በስውር የተቀመጡ ኢክርስቲያናዊ አሠራሮችን በመተግበር ለመፈጸም መሞከር፡፡ ተኩላ በበግ ለምድ እንዲሉ በሕግ ማዕቀፍ ስም በሰው ልጆች ላይ የተቀመጡትን አሳሪ ሕግጋትን ከዲያብሎሳዊ መንገድ ከሚከለክሉ የእግዚአብሔር ትዕዛዛት ይልቅ ሙጭጭ ብሎ መያዝ፡፡ አካሄዱ ሥጋዊነትን ያጋለጥ እንደሆነ እንጂ መንፈሳዊነትን የሚያውጅ አንዳች ኃይል የለውም

  ReplyDelete
  Replies
  1. አንተን «ቅዳሴ ሲያልቅበት ቀረርቶ አለበት» የሚለው ብሂል ነው የሚገልጽህ፡፡ አዋቂ ከሆንህ የቀረበውን በማስረጃ የተደገፈ ሂስ አንተም በማስረጃ ማፍረስ ነበረብህ፡፡ አቅም ስለሌለህ ግን ወደስድብና ዘለፋ ነው የዞርኸው፡፡

   Delete
 12. በመጽሓፍ ቅዱስ የተጻፈው ሁሉ የእግዚአብሔር ስራ እና ጥበብ ሲሆን የሚገለጠውም ባለቤቱ እግዚአብሔርን በማመን፣ ትእዛዛቱን ሁሉ በማክበር፣ በንጹሕ ልቡና ፈቃዱን በመጠየቅ ነው እንጂ በሰዎች ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ አለመሆኑ መገንዘብ ይገባናል፡፡ በስመ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በአንዳንድ ደራስያን እየተጻፈ ያለው ከመጽሓፍ ቅዱስ እና ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ እና ትውፊት ውጭ በመሆኑ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ሲኖዶስ እነዚህ ወገኖቻችን ከቤተ ክርስቲያናችን መለየቱ (ማውገዙ) ትክክል ነው፡፡
  አሁን በዚህ ብሎግ ለሲኖዶሱ መልስ ተብሎ እየተጻፈ ያለው ሁሉ አንብቤዋለሁ፡፡ ይሁን እና ከመጽሓፍ ቅዱስ ፣ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ እና ትውፊት ውጭ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ ይህ አስተምህሮ ምናልባትም ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ለማደስ የተነሳው የመናፍቃን (ፕሮቴስታንታዊ) አስተምህሮ መሆኑ በግልጽ ያሳያል፡፡
  እግዚአብሔር አምላካችን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንን እና ማሕበረ ምእምናንዋን ከተኩላዎች ይጠብቅልን፡፡ አሜን!!!

  ReplyDelete
  Replies
  1. ዘመንፈስርኩስ ምነካህ

   Delete
 13. ስለ ቅዱሳን ስዕል ጊዜ ስላላገኘሁ አስረጅ መጻፍ አልቻልኩም ፡፡ ማመኑን ብትተውት እንኳን አእምሮአችሁ ትንሽ ስንቅ እንዲያገኝ የሚከተሉትን ትመለከቱ ፣ ታዳምጡና ታነቡ ዘንድ ተጋብዛችኋል ፡፡

  http://www.youtube.com/watch?v=EGkRmBUR5ls
  ወይም
  http://www.youtube.com/watch?v=TAudg_HyE1c

  http://rejipvm.blogspot.com/2009/11/miracle-at-st-marys-jacobite-syrian.html

  http://www.youtube.com/watch?v=vytoX-9c9lU

  http://www.youtube.com/watch?v=eHnUaj8TMJk

  http://www.cbsnews.com/stories/2005/11/29/earlyshow/living/main1081235.shtml

  http://wongelforall.wordpress.com/2009/12/17/icons-in-orthodoxy-frequent-questions-and-answers/

  ReplyDelete
 14. Mk has poisen with silent killer chemical to killed abune paulos. The game was planed by aba,abrham.

  ReplyDelete

 15. ከንቱ ቃል ፡ እናንተ የጨዋይቱ
  የ ወሮ ም
  አና ፍቅ ልጆች ናችው

  ቀሲስ መምህር ዘበነ ለማ የፌስቡክ ፕሮፋይል የላቸውም

  ይህን ነገር እናንተው ለቀቃችውት እናንተው
  የጨዋይቱ ልጆች
  ተቃወማች ሁት
  ይቅር ይበላችው ፡ መድሐኔዓለም ብቸኛው መድህን
  የድንግል ማርያም ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስ
  እግዚአብሔር
  ወልደ እግዚአብሔር

  ReplyDelete
 16. ሁየኞ ሙሉወንጌልአማኝ እስኪ መጀመሪያ ትንቢተኢሳያስን አንበዉ እና ተከራከር አሁንም ያለ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አለም አይድንም አይድንም አይድንም ሞኝ ሁናችሁ ነው እንጅ እኮ የብርቱካንን ጣዕም የሚያውቀዉ የቀመሰው ነው የቀመሰው ነው ኢሳ ፷።፩፪ለአንች የማይገዛ መንግስት እና ሕዝብ ይጠፍል ይላል እውሩ ሰው በማሳሳት ፅድቅ አይገኝም

  ReplyDelete
 17. ሁየኞ ሙሉወንጌልአማኝ እስኪ መጀመሪያ ትንቢተኢሳያስን አንበዉ እና ተከራከር አሁንም ያለ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አለም አይድንም አይድንም አይድንም ሞኝ ሁናችሁ ነው እንጅ እኮ የብርቱካንን ጣዕም የሚያውቀዉ የቀመሰው ነው የቀመሰው ነው ኢሳ ፷።፩፪ለአንች የማይገዛ መንግስት እና ሕዝብ ይጠፍል ይላል እውሩ ሰው በማሳሳት ፅድቅ አይገኝም

  ReplyDelete
 18. ሁየኞ ሙሉወንጌልአማኝ እስኪ መጀመሪያ ትንቢተኢሳያስን አንበዉ እና ተከራከር አሁንም ያለ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አለም አይድንም አይድንም አይድንም ሞኝ ሁናችሁ ነው እንጅ እኮ የብርቱካንን ጣዕም የሚያውቀዉ የቀመሰው ነው የቀመሰው ነው ኢሳ ፷።፩፪ለአንች የማይገዛ መንግስት እና ሕዝብ ይጠፍል ይላል እውሩ ሰው በማሳሳት ፅድቅ አይገኝም

  ReplyDelete