Saturday, November 3, 2012

ቀልብ ያልሳበው የአዲስ አበባው የጥቅምት ሲኖዶስ ስበሰባ ተጠናቀቀ

እንደ ወትሮው የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ያልሳበውና በአብዛኛው ሲኖዶስ ለተባለው የቤተክርስቲያን የበላይ አካል በማይመጥኑና ተራ አጀንዳዎች ሲወያይ የሰነበተው የአገር ቤቱ ሲኖዶስ ስበሰባ ባለፈው ሳምንት ጥቅምት 21/2005 ዓ/ም ተጠናቋል። በማኅበረ ቅዱሳን እዝ ስር በመሆን ቅዱስ ፓትርያርኩን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ለመጣል አንድ ሆነው የነበሩት ጳጳሳት ከቅዱስነታቸው ዕረፍት በኋላ ያለ መሪ ፓትርያርክ በዐቃቤ መንበር አንድነታቸውን ጠብቀው መቀጠል እንዳልቻሉ በታየበት በዚህ ስብሰባ ላይ ፓትርያርክ ጳውሎስ የሲኖዶስ ስበሰባ ለሚያገኘው ትኩረት ዋና እንደነበሩ መታዘብ ተችሏል። ሲኖዶሱ በዋናና ለቤተክርስቲያን መንፈሳዊ እድገትና ጥንካሬ የሚረዱ፣ ቤተክርስቲያንም በአገራችን ተገቢ ሚናዋን እንድትጫወት የሚያደርጉ አጀንዳዎችን ከመቅረጽና ከመወያየት፣ ጠቃሚ ውሳኔዎችንም ከማሳለፍ ይልቅ በአብዛኛው ተራ በሆኑና ሲኖዶስ ላይ ሳይደርሱ መፈታት ባለባቸው ጥቃቅን አጀንዳዎች ላይ ሲወያይ አብዛኛውን ጊዜውን ማቃጠሉ፣ የሲኖዶሱ አባላት የሚገኙበትን ደረጃ ያሳየ ክስተት ሆኖ አልፏል።
 
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአራት መከፈሉ አንዳንዶችን ያላስደሰተ ቢሆንም፣ ሲሚና ጉዳዩን የሚመለከትለት ላያገኝ በየዕለቱ በሀገረ ስብከቱ በር ላይ ተኮልኩሎ ለሚንገላታውና ከዘበኛ ጋር ለሚወዛገበው የቤተክርስቲያን አገልጋይ ቢያንስ እንኳን አቤቱታውን ለማቅረብ የተሻለ እድል ይፈጥርለታልና ከዚህ አንጻር መልካም እንደሆነ በርካታ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር የሚከገኙ ማኅበረ ካህናት እየተናገሩ ነው፡፡ ችግሩ ግን ሀገረ ስብከቱን አንድ ጳጳስና ሥራ አስኪያጅ ብቻ ከሚበሉት ለ4 እንካፈለው እንዳይሆን ነው ስጋቱ። ሰዎችን በመለዋወጥ ብቻ የሚመጣ ለውጥ የለም። ምናልባትም «የጠገበውን አንስቶ የተራበውን ማምጣት» እንዳይሆን ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ሀገረ ስብከቱ ለ4 መከፈሉ ብቻ ሳይሆን ሥር ነቀል አስተዳደራዊ ተሀድሶ መደረግ ያስፈልገዋል። አሠራሩ ሁሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት፥ ከሙስናና ከዘመድ አዝማድ አሠራር የተላቀቀ፥ ቅጥርና ዝውውር በትክክለኛ አሰራር የሚከናወንበት ሊሆን ይገባል። በሥራ አስኪያጅነትም ሆነ በሊጳጳስነት የሚቀመጡ ኃላፊዎች ወደቦታው ከመምጣታቸው በፊት ያላቸው ሀብትና ንብረት በግልጽ የሚታወቅበት፥ ነገር ካለቀና ከተበላሸ በኋላ ከማንሳትም በየጊዜውም የሚገመገሙበትንና ለውጣቸውና ያስመዘገቡት ውጤት የሚታይበትን ሥርአት መዘርጋትና የመሳሰሉትን ሥራዎች መሠራት ይጠበቃል። አሊያ «ጉልቻ ቢለዋወጥ …» ይሆናል ነገሩ።
አንዳንዶቹ የሲኖዶሱ ስብሰባ አጀንዳዎች የቤተ ክርስቲያን ሳይሆኑ የግል ቂምን መወጫና የማኅበረ ቅዱሳንን ጥቅም ለማስከበር የተቀረጹ ነበሩ። ለምሳሌ ሲኖዶሱ በማይመለከተውና ሊቀጳጳሱ በሚወስነው ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ከአሜሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ስዩማን ኃይለ ጊዮርጊስ ይነሣ የሚል አጀንዳ መያዝና በዚያ ላይ መከራከር፥ የማኅበረ ቅዱሳንን ጥቅም ለማስከበር ካልሆነ በቀር ሊቀጳጳሱ እስካመኑበትና ተስማምተው እየሠሩና ቤተክርስቲያንን የማይጎዳ እስከ ሆነ ድረስ የግለሰቡ እዚያ መቀመጥ በአጀንዳነት ባልተነሣ ነበር። አጀንዳውን ማንሣት የተፈለገው ለሌላ ሳይሆን የማኅበረ ቅዱሳንን ጥቅም ለማስከበር ተፈልጎ ብቻ ነው። በዚህ አጀንዳ ማኅበረ ቅዱሳን የእርሱን ጥቅም አለአግባብ ለማስጠበቅ ሕግና ስርዓት የማይገዛው ሁሉንም አማራጭ ከመጠቀም ወደኋላ የማይል መሆኑን ያሳየ ሲሆን፣ ለዚህ አላማው የሚጠቀምባቸው ጳጳሳት እንዳሉትም መረዳት ይቻላል።

ሥራ አስኪያጅን የሚሾመውና የሚሽረው ሊቀጳጳሱ መሆኑን እያወቀ፣ ባያስኬደውም ብዙዎችን ጠልፎ በጣለበት የክስ ስልቱ «መናፍቅ ነው» ብለው ከስልጣኑ የሚነሳበትን መንገድ እንዲያመቻችሉት አጀንዳውን በጳጳሶቹ አባ ኤልያስንና አባ ሉቃስ ላይ ጭኖ ሲኖዶሱን እንዲያውኩ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ በሲኖዶሱ ውስጥ ኅሊና ያላቸው እውነተኛ አባቶች አሉና ብፁዕ አቡነ ማርቆስ አልበዛም ወይ ያንንም ያንንም እየተነሳችሁ መናፍቅ ነው የምትሉት፡፡ የምንናገረውን እንወቅ እንጂ የተሰጠንን ኃላፊነት መዘንጋትም አግባብ አይደለም፡፡ ለመሆኑ አታፍሩም ወይ? አያሳፍረንም ወይ? ለኅሊናችንስ አይከብደንም ወይ? እየተነሳን በሀሰት ስም እየለጠፍን ተሀድሶ ምናምን እያልን ልጆቻችንን የምናበረው እስከ መቼ ነው? አያሳዝናችሁም ወይ እንዲህ ያለው ስራ? እንዴት ያልሆነ ነገር ይወራል፡፡ እኛ እኮ አባቶች ነን እንጂ የሰው ጩኸት አድማቂዎች አይደለንም፡፡ በማለት ኅሊናቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን የሸጡትን ጳጳሳት መገሰጻቸውን አውደ ምሕረት ብሎግ ዘግቧል።

ብሎጉ አክሎ እንደገለጸውም «በሲኖዶሱ ስብሰባ ወቅት ድምጻቸው ፈጽሞ ያልተሰማው ብፁዕ አቡነ ገሪማ ይናገሩ እንጂ ለምን ዝም ይላሉ? ተብለው ብፁዕ አቡነ ገሪማም ‘እኔ እንኳ ልናገር አልፈልግም ተናገር ካላችሁኝ እናገራለሁ፡፡ በጣም የምታሳዝኑ ጉዶች ናችሁ፡፡ እየተቀባበላችሁ እገሌ መናፍቅ ነው እገሌ እንደዚህ ነው ማለት ምን ማለት ነው፡፡ ኃይለ ጊዮርጊስ ልጃችን ነው፡፡ ለመሆኑ ከመቼ ወዲህ ነው ሥራ አስኪያጅን እናንተ የምታነሱት እና የምታስቀምጡት? ስራ አስኪያጅ መሾምም ሆነ መሻር የሊቀ ጳጳሱ መብት ነው፡፡ ስራ አስኪያጅን ለመሾም ሊቀ ጳጳሱ እና ፓትርያርኩ እየተማከሩ የሚያደርጉት እንጂ ከመቼ ወዲህ ነው በሲኖዶስ የሚታየው? ይህ አካሄድ ትክክልም ተገቢም ያልሆነ አካሄድ ነው፡፡ ይሄ የሊቀ ጳጳሱ ጉዳይ ነው እኛን አይመለከተንም፡፡ አይነሳም የሚነሳበትም ምክንያትም የለም፡፡ በቀደም ዝም ብዬ አይቻችኋለሁ የኔን ስራ አስኪያጅ ተሀድሶ ነው መናፍቅ ነው አላችሁ፡፡ እየተነሳችሁ ተኃድሶ እየተነሳችሁ መናፍቅ ለመሆኑ የምትሰሩትን ስራ ታውቁታላችሁ ወይ? የምትሰሩት ስራ ሁሉ የቡድን ስራ ነው? አንድ የሁሉ አባት ሊሆን የተቀባ ጳጳስ ይህን ማድረግ አለበት ወይ? እንዲህ ያለው ቡድንተኝነት በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ መስተካከሉ ይበጃል፡፡በማለት ተናግረዋል’ ዘግቧል።
አገራችን በንጉስ ሥርአት ትመራ በነበረ ጊዜ፥ «ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ» ይባል ነበር። ንጉሳዊው ስርአት ከቤተ መንግስት ጠቅልሎ ከወጣ እነሆ 40 ዓመታት አልፈዋል። ይሁን እንጂ አብዛኛው ንጉሳዊ ስርአት ጓዙን ጠቅልሎ ወደቤተክህነት እንደገባና ጳጳሳቶቻችን እንደወረሱት መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ያ የቀድሞው ተረት «ጳጳስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ» በሚለው ተተክቷል ለማለት ያስደፍራል። ምክንያቱም አንዳንድ ጳጳሳት በሚያሳዩት የስነምግባር ችግር በየጊዜው እየተከሰሱ ጉዳያቸው በዝግ ለሲኖዶስ ቢቀርብም የማስተካካያ እርምጃ ሲወሰድ፥ አሊያም ሲጠየቁ አይታይም። ማን ማንን ይከሳል? አለቃ ገብረ ሐና አሉ እንደሚባለው «ዋ! እዚያም ቤት እሳት አለ» እየተባባሉ ገበናን መደበቅ ሥራዬ ተብሎ ተይዟል። አንዳንዱ ገበና ደግሞ የሚደበቅ ስላልሆነ ወደሚዲያ እየወጣ ጳጳሳቱን ትዝብት ላይ ከመጣሉም በላይ የቤተክርስቲያኒቱ ስም እየተነቀፈ ይገኛል።
ማኅበረ ቅዱሳን በስምአ ጽድቅና በሐመር ልሳኖቹ በካቶሊክና በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የሚታዩ ተመሳሳይ የሥነምግባር ችግሮችን የተመለከቱ ዜናዎችን በፊት ለፊት የሽፋን ገጹ የካቶሊክ መነኮሳት እንዲህ ሆኑ የፕሮቴስታንት ፓስተሮች ይህን ፈጸሙ እያለ በሌሎቹ ላይ ሲፈርድና ሌሎቹን ሲያሳጣ እንዳልነበር፥ የእኛውም ችግሩ ሥር የሰደደና የቆየ ቢሆንም ሚዲያ ላይ ባለመውጣቱ ብቻ የእኛዎቹ አንዳንድ መነኮሳትና ጳጳሳት ችግር ታፍኖና ከሚዲያ ተሰውሮ ይኖር ነበር። አሁን ግን እንደገፋ ጽንስ ሊደበቅ ከማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ በአንዳንድ ጳጳሳትና መነኮሳት ላይ በተጨባጭ እየተሰማና እየታየ ያለው የስነምግባር ችግር ጆሮን ጭው የሚያደርግ ከሆነ ሰነባብቷል። ይህን ችግር መፍታትና ራስን ማስተካከል በግልጽም ንስሐ መግባት ሲገባ፣ ጳጳሳቶቻችን ግን ለምን ስማችን ተነሳ ባዮች ሆነዋል። አንዱ የሌላውን ገበና እንዳያወጣ የተማማሉ እስኪመስል ድረስ እየቀረበባቸው ያለውን ክስ እያፈኑ በማስቀረት ችግሩ እየሰፋ እንዲሄድ እያደረጉ ይገኛሉ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዜና ቤተክርስቲየን ጋዜጠኛ ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር ጳጳሳቱ እየተጓዙበት ያለውንና ለጵጵስናቸው ተገቢ ያልሆነውን አካሄድ እንዲያርሙ የሚመክር መጽሐፍ በመጻፉ፣ ጠቃሚ ምክሩን ከመቀበል ይልቅ «ጳጳስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ» በሚል ብሂላቸው ለምን እንዲህ ተባልን በሚል በካህሳይ ላይ ጥርስ ነክሰዋል። «ብፁዓን እነማናቸው?» በሚል ርእስ የጊዜው መልእክት የተባለለትን ምርጥ መጽሐፍ የጻፈው ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር ሰድቦናልና ይወገዝ የሚል አጀንዳ ይዘው በፈረደበት የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ መወያየታቸው ብዙዎችን አስገርሟል። ባይሆን «ራሳችንን እንፈትሽና እንታረም» የሚል አጀንዳ ነበር መቀረጽና ለውይይት መቅረብ የነበረበት። ካህሳይም እንደ ውጭ ነቃፊ ሳይሆን እንደ ውስጥ አራሚ መታየትና መመስገን ነበረበት። ነገር ግን በዚህ ፈንታ ተወቀሰ፤ ለውግዘትም ታጨ፤ ያሳዝናል!
ለእውነት የቆመውና ሳይፈራና ሳያፍር በስሕተት ጎዳና ላይ እየነጎዱ ያሉትን አባቶች በትሕትናና በተገቢው መንገድ የገሰጸው ጋዜጠኛ ካሕሳይ፣ «ብፁዓን» ጳጳሳት አሁን የሚገኙበት ሁኔታ ለተሸከሙት መንፈሳዊ ኃላፊነት የማይመጥንና ቤተክርስቲያንን እየጎዳ ያለ መሆኑን አስረድቷል። የዘመኑ ጳጳሳት አኗኗር ከቀደመው ህገ ቤተክርስቲያን ያፈነገጠና ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን በማስረጃ አስደግፎ ተችቷል። ከዚህ ቀጥሎ በመጽሐፉ ከገጽ 37-39 ያሰፈረው ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል።
 አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንደዛሬው ለሚኖሩበት ብለው ሳይሆን ሰዎች ናቸውና ሲደክማቸው አረፍ የሚሉበት፣ ምግብ የሚቀምሱበት፣ ምእመናንን ተቀብለው የሚባርኩበት፣ የሚያጽናኑበት፣ መጻሕፍትን የሚፈትሹበት ቤት (መንበረ ጵጵስና) በቤተ መቅደስ ጓሮ የሚሠሩበት ምስጢርም ይኸው ነው። ባለንበት ዘመን ግን አንዳንድ «ብፁዓን አባቶች ይህንን ህግ ጥለው «በባቢሎን» መካከልና በነጋዴዎች ሰፈር መለስተኛ ቤተመንግስት የሚያክል ሕንጻ ሲሰሩ፣ ተራራውን ትተው «ወደየሸለቆው» ሲገቡ ይታያሉ።
እነዚህ «ብፁዓን» አባቶች ዓለምን ወደው የጀመሩትን የተራራ መንገድ መውጣት አቅቷቸው ቁልቁል ወደከተማ የተመለሱ [እንደዴማስ] (1ጢሞ. 4፡10)፣ ከጌታ የተቀበሉትን የወንጌል እርፍ ይዘው ወደፊት ማረስ ሲገባቸው ወደኋላ ተንሸራተቱ፣ (ሉቃ 9፡6)፣ የጣፈጠ ነገር ለመብላት ሲሉ በመንገድ የጠፉ (ሰ.ኤር. 4፡5) «ስለስጋ ማሰብ ሞት ነው፣ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው» (ሮሜ 8፡6) የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል «ሥጋዬ ከሞተ ነፍሴ ሰርዶ አይብቀልባት» በሚል ዓለማዊ ብሂል ለውጠው በመንፈስ እያነሱ በስጋ እየገዘፉ የመጡ፣ ወደባቢሎን ለመሄድ የመልስ ጉዞ የጀመሩ ናቸው (ተ.ባ. 5፥31፣ ተ.ኤ. 11፥31)።
እነዚህ ገና በጠዋቱ ለዚህ ከፍተኛ ሐዋርያዊ ኃላፊነት ሲታጩ አስቀድመው እንደ ሙሴና ዳዊት ‹‹እኔ ማነኝ?›› (ዘፀ. 3፥12፣ 1ሳሙ. 18፥18) ብለው በመጠየቅ ውስጣቸውን መፈተሽ ሲገባቸው፣ ከተሾሙ በኋላም ‹‹ሰዎች ማን ይሉኛል (ሉቃ. 9፥18፣ ማቴ. 16፥13፣ ማር. 8፥27) በማለት ሌላውን ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት ራሳቸውን መስበክ ረስተው፣ በራሳቸው ዓይን የተጋደመውን ምሰሶ ሳያወጡ በሌላው ዓይን ያለውን ጉድፍ አግዝፈው ለማሳየት የሚሞክሩ ‹‹አላዋቂ ተራች ለራሱ አመልካች›› ዓይነቶች ናቸው፡፡
        ጳጳሳት የረገጡት ቦታ (ዐፈር) እንደ እምነት ሆኖ እንዳላገለገለ ሁሉ ዛሬ ዛሬ ሊቃነ ጳጳሳት በምእመናን እየተከሰሱ ዓለማዊ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት፣ ‹‹አካባቢያችን ለቀው ይውጡልን›› የሚል ተቃውሞ የሚሰማበት ጊዜም ተደርሷል፡፡
        በእርግጥ የቤተ ክርስቲያናችን ጠላቶች የጠንካራ አባቶችን ስም ለማጥፋትና ቤተ ክርስቲያናችንን ለማዳከም ከሚል ስውር ዓላማዎች በመነሣት በብፁዓን አባቶች መሠረተ ቢስ ክስ የሚያሰሙ እንዳሉ እውነት ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ የጠላት እንቅስቃሴ ዛሬ ቀርቶ በሐዋርያት ጊዜም የነበረ ነውና አያስደንቅም፡፡
        ይሁን እንጂ አንዳንድ ‹‹ብፁዓን አባቶች ምእመናንን አስተምሮ ለማሳመን የሚያስችል የዕውቀት ብቃት ካለመያዛቸው የተነሣ ምእመናን በወንጌል ጥም በሚቃጠሉበት ጊዜ ከተቆርቋሪነት ክርስቲያናዊ ስሜት በመነሣት በብፁዓን አባቶች ላይ የሚያነሱአቸው ቅሬታዎች እንዳሉም መታወቅ አለበት፡፡ ጥንትኮ በአንድ ሀገረ ስብከት ከእምነትና አስተዳዳር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን የሚፈታው ሊቀጳጳሱ ነበር (የሐዋ. 15፥22)፡፡ አሁን አሁን ግን ሊቃነ ጳጳሳቱ አቅም ስለሚያንሳቸው ከማእከል ሊቃውንተ ቤተ ከርስቲያን እየተላኩ ነው ሁኔታዎችን የሚያረጋጉትና የሚያጣሩት፡፡
        ከሁሉ ከሁሉ በላይ ግን ሊቃነ ጳጳሳቱ በዓለማውያን እየተከሰሱ ‹‹ስማቸው የሚጠፋውና›› በዓለማዊ ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡት ከመጀመሪያው ራሳቸው ከቤተ መቅደሳቸው እየወጡ ከተማ ስለሚገቡና ‹‹ለሁለት ጌታ መታዘዝ አይችልም›› የሚለውን ረስተው አንድ እግራቸው በቤተ መቅደስ ሌላውን በከተማ ለማቆም በመሞከራቸው ነው፡፡  ንብ ከቀፎውና ከሠራዊቱ ከተለየ እንደ ዝንብ ተልከስካሽ ሆኖ መቅረቱ የግድ ነውና፡፡
        ሊቃነ ጳጳሳቱ ግን እየተከሰሱ ያሉት በሌሎች አካላትና ምእመናን ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳቸው ጭምር ነው፡፡ የዚህ ምንጭ ደግሞ በዋናነት ቅዱስ ጳውሎስ፡-                                       
‹‹ቅናትና ክርክር ስለሚገባችሁ ሥጋውያን መሆናቸሁ አይደላችሁምን (1ቆሮ. 3፥3) እንዳለው ‹‹የተራራው›› ሥራቸውን ትተው በሥልጣንና በገንዘብ ምኞት የፈተና ወጥመድ ስለወደቁ ነው (1ጢሞ. 5፥9-10)
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ካሕሳይ እንደተናገረው ለዚህ ሁሉ ችግር ዋና ምክንያቱ ለስብከተ ወንጌል ትኩረት አለመሰጠቱና ተገቢው ሰራተኛ በተገቢው ቦታ አለመቀመጡ መሆኑን አመልክቷል። ከገጽ 35-36 ላይ እንዳሳየው በ1945 ዓ.ም በወጣው ሕገ ቤተክርስቲያን ላይ ለስብከተ ወንጌል ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ ነበር፡፡ «ከዚህ በኋላ የወጡ ደንቦች ግን አንዳቸውም ቢሆኑ ስለ ስብከተ ወንጌል ሥራ ዝርዝር ያወሱበት ጊዜ የለም፡፡
ሌላው አስገራሚ ጉዳይ በ1984 ዓ.ም በወጣው ሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ 20 ስር ከቅዱስ ሲኖዶስ በቀጥታ መመሪያሪያ አለመጠቀሱ ነው። ለመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ከስብከተ ወንጌል የሚበልጥ ምን አይነት ሥራ ቢኖረው ይሆን እንዲህ ያደረገው? ወይስ ሕዝቤ የጠፉ በጎች ሆነዋል፣ እረኞቻቸው አሳቱአቸው፣ በተራሮች ላይ የተቅበዘበዙ አደረጓቸው፤ ከተራራ ወደ ተራራ አለፉ፣ በረታቸውንም ረሱ፣ ያገኟቸው ሁሉ በሉአቸው፣ (ኤር 50፥6-7)። የሚለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ይሆን? ወይስ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ ስለዚህ የአፌን ቃል ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። እኔ ኃጢአተኛውን፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። ሕዝ. 3፥17-18) የሚለው መልእክት እነርሱን የሚመለከት መሆኑን ልብ አላሉት ይሆን?
ዛሬ ቤተ ክርስቲያንዋ ማንም ግለሰብ እየተነሣ ያሻውን የሚናገርባት፣ በዐውደ ምሕረቷ የሚጨፍርባት፣ በስብከትና በመዝሙር ስም የግል ሀብቱን የሚያከማችባት፣ ሲያሻው ፖለቲካ የሚሰብክባት፣ ሲያሻው ንግድ የሚያካሂድባት በአጠቃላይ መንገደኛው ሁሉ ያሻውን የሚፈጽምባት የሆነችው እረኞቿ በጎቻቸውን ሜዳ ላይ ጥለው በመሄዳቸው ነው፡፡ ይህ ሁሉ ድክመት እየተከሠተ ያለው የቤተክርስቲያንዋ ዓይን የሆኑ ሰባክያነ ወንጌልና ወጣት የከፍተኛ መንፈሳዊ ተቋማት ምሩቃን እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየታዩ በተቃራኒው ትኩረቱም፣ ደመወዙም፣ ስልጣኑም ዕርፍ መያዝ ለማይችሉ ሠራተኞች መሰጠቱ ነው።»
እውን ይህ ገንቢና ጠቃሚ ምክር ያሸልማል እንጂ ለውግዘት ያሳጫል? ፍርድ ለአንባቢ ትተናል።

5 comments:

 1. ምን ይደረግ ከበለዐም አህያ የማይሻል ሲኖድ እስካለ ድረስ ...

  ReplyDelete
 2. አበው ሊቃነ ጳጳሳት እንደዛሬው ለሚኖሩበት ብለው ሳይሆን ሰዎች ናቸውና ሲደክማቸው አረፍ የሚሉበት፣ ምግብ የሚቀምሱበት፣ ምእመናንን ተቀብለው የሚባርኩበት፣ የሚያጽናኑበት፣ መጻሕፍትን የሚፈትሹበት ቤት (መንበረ ጵጵስና) በቤተ መቅደስ ጓሮ የሚሠሩበት ምስጢርም ይኸው ነው። ባለንበት ዘመን ግን አንዳንድ «ብፁዓን አባቶች ይህንን ህግ ጥለው «በባቢሎን» መካከልና በነጋዴዎች ሰፈር መለስተኛ ቤተመንግስት የሚያክል ሕንጻ ሲሰሩ፣ ተራራውን ትተው «ወደየሸለቆው» ሲገቡ ይታያሉ።

  ReplyDelete
 3. ይህን መጽሐፍ ክልል ላይ እንዴት ማግኘት እንችላለን፤ እርግጠኛ ነን ማቅ ሱቆች ውስጥ ይሄ መጽሐፍ አይገኝም፡፡

  ReplyDelete
 4. yemote sinodos betekirtianun gedelew. enersu gena ende solomon 700mistochin saycherisu aymelesum! egzio!!

  ReplyDelete
 5. በእርግጥ የቤተ ክርስቲያናችን ጠላቶች የጠንካራ አባቶችን ስም ለማጥፋትና ቤተ ክርስቲያናችንን ለማዳከም ከሚል ስውር ዓላማዎች በመነሣት በብፁዓን አባቶች መሠረተ ቢስ ክስ የሚያሰሙ እንዳሉ እውነት ነው፡hahhhahhhaha you are indicating yourself

  ReplyDelete