Thursday, December 27, 2012

አቡነ መርቆሬዎስን የመመለስ አለመመለሱ ምርጫ በአገር ቤቱ ሲኖዶስ እጅ ላይ ወድቋል

ረቡዕ ታኅሣሥ 17/2005 ለንባቢ የበቃው “ሰንደቅ” የተባለው የግል ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ “መንግስት አቡነ መርቆሬዎስ ቢመለሱ እንደማይቃወም አስታወቀ” በሚል ርእስ ዜና አውጥቷል፡፡ አቡነ መርቆሬዎስን የመመለስ አለመመለሱ ምርጫ በአገር ቤቱ ሲኖዶስ እጅ ላይ ወድቋል፡፡
ከአቶ ስብሀት ነጋ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስም አቶ ስብሀት የእምነቱ አመራር ቢሆን የአማኙን መንፈሳዊ ህይወት ሊያረካ አልቻለም፡፡ … የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመራር ለሃይማኖቱም ሆነ ለአጠቃላይ ስርአቱ አደጋ ወደመሆን ተቃርቧል” ማለታቸውንና “የአሜሪካው ሲኖዶስ የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ እንደሚደግፍ ይወራል፡፡” የሚል አስያየት መሰንዘራቸውን አስነብቧል፡፡ ሁለቱን ጉዳዮች ለአንባብያን ቀጥሎ አቅርበናል፡፡
መንግሥት አቡነ መርቆርዮስ ቢመለሱ እንደማይቃወም አስታወቀ
“ለፓትርያርክነት በመንግሥት ተመልምለዋል የተባሉ ሁለት ጳጳሳት የሉም”
የፌሬደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር

          በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፕትርክና 4ኛው ፓትርያርክ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በስደት በአሜሪካ አገር የሚኖሩት አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ ተቃውሞ እንደሌለው መንግሥት አስታወቀ፡፡
          የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዳስታወቀው መንግሥት በህገ-መንግሥቱ መሠረት       በሃይማኖቶች የውስጥ ተግባር ጣልቃ መግባት ስለማይችል አቡነ መርቆርዮስ ይመለሱ ወይም አይመለሱ የማለት ህገ-መንግሥታዊ መሠረት የለውም፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ 4ኛው ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ መርቆርዮስ ይመለሱ ብሎ ካመነ ተቃውሞ እንደሌለው አስታውቋል፡፡
          የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ወርቁ  በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት መንግሥት ለሰላምና ፀጥታ ሲባል የተጀመረውን እርቀ-ሰላምን ሲደግፍ መቆየቱን በመግለፅ የፓትርያርክ ምርጫው በሰላምና በመከባበር እንዲሁም በቤተ ክርስቲያንዋ  ህግ፣ ደንብና መመሪያ እንዲፈፀም ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል፡፡
          ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር «የፓትርያርክ አሰያየሙ ሰላማዊ ሆኖ እንዲፈፀም፤ ቅሬታ እንዳይፈጠር፣ በሁሉም ምዕመናን ዘንድ ተቀባይነት ያለው የሃይማኖት መሪ እንዲመረጥ ድጋፍ ያደርጋል» ያሉት አቶ አበበ ይህንን ድጋፍ በማየት ጥቂት ቀስቃሽ ኃይሎች «መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ ገብቶአል» በሚል ቢያራግቡትም በሂደቱ ግጭት እንዳይፈጠር የመከላከል ሥራ ከማከናወን ውጪ ያደረገው አለመኖሩን አብራርተዋል፡፡
          በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት ኃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ በመሆናቸው «እገሌን ሹም እገሌን ሻር» ብሎ የመወሰን ሥልጣኑ ከሃያ ዓመታት በፊት ማክተሙን ያብራሩት አቶ አበበ «ጥቂት ቀስቃሽ ኃይሎች» ግን በዚህች ሀገር ሰላማዊ የአምልኮ ስርዓት እንዳይካሄድ፤ በሃይማኖት መካከል መበጣበጥ ለመፍጠር በሃይማኖት ሰበብ አክራሪነትን ለማስፋፋት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የፓትርያርኩን ምርጫ ምክንያት በማድረግ ሕዝቡን ውዥንብር ውስጥ በማስገባት በውጪና በውስጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ደርሶበታል ብለዋል፡፡
          «መንግሥት ለራሱ የሚጠቅም ፓትርያርክ ሊሾም ነው፤ በቤተክርስቲያንዋ አሠራር ጣልቃ ገብቶአል የሚሉ ህገ-ወጥ ቅስቀሳዎች በሰላማዊ መንገድ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለመናድ የሚጥሩ ግለሰቦች መሆናቸውን ተገንዘበናል» ብለዋል፡፡
          ይሁን እንጂ ለሲኖዶሱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች መንግሥት «ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማስኬድ» በሚል ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣኑ መመደቡን እየገለፀ ነው፡፡ በተለይም በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የሃይማኖትና የእምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የፓትርያርኩን ምርጫ በተመለከተ ገደብ ባለው ሁኔታ ጣልቃ መግባቱን እያወገዙ ነው፡፡
          አቶ አበበ የተባለው ጣልቃ ገብነት «ልብ ወለድ ነው » በማለት ያጣጣሉት ሲሆን በአንፃሩ የፓትርያርኩን አሰያየም ምክንያት በማድረግ ከምዕመናን ጋር ለማጋጨትና አክራሪነትን ለማስፋፋት ታስቦ የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
          በፓትርያሪክ ምርጫው መንግሥት ጣልቃ ከመግባት አልፎ የሚመረጡ ፓትርያርኮች መካከል የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እንዲሁም በመጠባበቂያነት ደግሞ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ሲሆኑ፣ የቀድሞው ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለአንዳንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲተኩዋቸው ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል የተባሉት የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ መሆናቸውን የተለያዩ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፡፡ ይህን በተመለከተ አቶ አበበ ተጠይቀው መረጃው ስህተት መሆኑን ጠቁመው እንዲህ ዓይነቱ መረጃ ምዕመናንን በመንግሥት ላይ ለማስነሳት የሚደረግ ጥረት ነው ብለዋል፡፡
          በሌላ በኩል መንግሥት በሕግ የሚያውቀው አንድ ሲኖዶስ መሆኑን ያብራሩት አቶ አበበ በመንግሥት ስደተኛ ሲኖዶስ አያውቅም ብለዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ለፓትርያርኩ ምርጫ ሁሉንም ያሳተፈ ሁሉንም የሚያስማማ የሃይማኖቱን ደንብና መመሪያ መሠረት አድርጎ እንዲፈፀም ይፈልጋል ብለዋል፡፡
          መንግሥት ለፓትርያርኩ ምርጫ ብሎ ህገ-መንግሥቱን አይሽርም ያሉት አቶ አበበ፣ «ሲኖዶሱ ከፈለገ ከኢየሩሳሌም፣ ከፈለገ ደግሞ ከዋሽንግተን ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ማምጣት ይችላል፡፡ መንግሥት በምንም ተአምር ይሄንን አምጡ ያንን አታምጡ አይልም» ሲሉ መልሰዋል፡፡
          ሲኖዶሱ በስደት ላይ ያሉትን ሊቀ ጳጳስ እንዲመጡ ቢያደርግ የመንግሥት አቋም ምን እንደሆነም የተጠየቁት አቶ አበበ፤ መንግሥት የሚቃወምበት ህገ-መንግሥታዊ መሠረት የለውም ሲሉ መልሰዋል፡፡ በጉዳዩም ላይ መንግሥት ጣልቃ አይገባም ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
          በቅርቡ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በአሜሪካ የሚገኙት 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ በደብዳቤ መጠየቃቸውን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ አበበ፤ «ፕሬዝዳንቱ እንደ ግለሰብ ደብዳቤ ፅፈዋል፡፡ ምናልባትም ግለሰቦች በሚፈጥሩት ውዥንብር ገብተው ጉዳዩ ወደ ብጥብጥ የሚሄድ መስሎአቸው እንዲህ ቢደረግ በሚል ግለሰባዊ እይታቸውን አንፀባርቀው ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ሥልጣን ላይ ሆነው ግለሰባዊ ዕይታም ቢሆን መስጠት የማይችሉ መሆኑን ወዲያው ተገንዝበው አርመዋል» ሲሉ መልሰዋል፡፡
          የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባካሄደው ስብሰባ 6ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ አስመራጭ ኮሚቴ ማቋቋሙ አይዘነጋም፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው እስከ ጥር 3ዐ ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም. እጩዎችን እንዲያቀርብ በሲኖዶሱ ታዞአል፡፡ ነገር ግን ከፓትርያርኩ ምርጫ በፊት ቅዱስ ሲኖዶሱ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ በአንዳንድ አባቶች ዘንድ ተቃውሞ ተነስቶበታል፡፡ አሜሪካ ከሚገኘው ስደተኛው ሲኖዶስ ጋር የሚደረገው የእርቀ ሰላም ውይይት አለመሳካቱ ይታወሳል፡፡ ወደ አሜሪካ የሄዱት የእርቀ ሰላም ኮሚቴ አባላትም ከ4ኛ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዮስ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት ያለውጤት መበተኑም ተዘግቦአል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፓትርያርኩ ምርጫው በፊት እርቀ ሰላም ይካሄድ በሚሉና እርቀ ሰላሙ እየተከናወነም ቢሆን የፓትርያርኩ ምርጫው ይከናወን በሚሉ ወገኖች መካከል ልዩነቶች ቢኖሩም በቅርቡ ግን ለስድስት ወራት ክፍት በሆነው ቦታ አዲስ ፓትርያርክ ይመረጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከአቶ ስብሐት ነጋ ቃለ ምልልስ ላይ ስለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከተናገሩት በከፊል የተወሰደ
          የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ምንም እንኳን የመንግሥት ጥገኛ ሆኖ በመቆየቱ እጅግ ቢጎዳም በሀገሪቱ በሁሉም መስኮች የነበረው ሚና መተኪያ የለውም፡፡ ከመንግሥት ይለይ፣ ከፖለቲካ ነፃ ይውጣ ቢባልም አሁንም ከፖለቲካ መድረክነቱ ሊወጣ አልቻለም፡፡ የእምነቱ አመራር ቢሆን የአማኙን መንፈሳዊ ህይወት ሊያረካ አልቻለም፡፡ ከዚህ አልፎም አሁን ባለው ሁኔታ ሳይረባበሽ እንደማይቀር ነው የሚገመተው፡፡ ለሁለት ተከፋፍለዋል፡፡ ይህን መሰል አደጋ ቤተክርስቲያኒቱ አጋጥሞት አያውቅም፡፡
          ቤተክርስቲያኒቱ ለሁለት የከፈለው ውጭ ያለው ፓትርያርክ የሚያራምዱት እንቅስቃሴ መሆኑ በስፋት ይታመናል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ የአሜሪካው ሲኖዶስ የእስልምና አክራሪ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚደግፍ ይወራል፡፡ አገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስም የቤተክርስቲያኒቱ ህልውና ቆርቁሮት ተነስቶ ይህን ድርጊት አላወገዘም፡፡ የእስልምና አክራሪነት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ደጋፊ ከሆነም መንግሥት እርምጃ መውሰድ ነበረበት፡፡ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችም እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትኩረት ካልሰጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመራር ለሃይማኖቱም ሆነ ለአጠቃላይ ለስርዓቱም አደጋ ወደ መሆን ተቃርቦአል፡፡ እነዚህ ችግሮች ፈጥነው ከተወገዱ ግን እምነቱ በእምነቱ ፀጋነቱ ይቀጥላል፡፡ እስካሁን ድረስ የፖለቲካ መድረክ ሆኖ መቀጠሉ ግን ብልሽቱ የውስጡ የአመራሩ የራሱ ነው፡፡ በርካሽ ጥቅማቸው ውስጡ ቢዳከም ሌሎችን መጫወቻ ማድረግ ነበረባቸው ማለት አይደለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡
4 comments:

 1. “... በወቅቱ የነበረውን የመንግስት ተጽዕኖም በጊዜው ከነበረው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ታምራት ላይኔ የተጻፈው በጀትን የማገድ ደብዳቤ ግልጽ ያደርገዋል።”
  አባ ዲያብሎስ( አንተ ) እንደ ፃፍከው።

  እንደው ሰው ጴንጤ ሲሆን ይሉኝታና ማሰቢያውንም ነው እንዴ ከነፍሱ ጋር ለገንዘብ የሚሸጠው? ትናንት እኮ መንግስት ጣልቃ ገብቷል ብለህ ዜና ተብዬ አውጥተህ ነበር። ዛሬ ደሞ መንግስት ጣልቃ አይገባም ብለህ ልታሳምነን ነው? በቃ እናንተ አክራሪ ጴንጤዎች እንዲሁ ሁለቱም ዛፍ ላይ እንደተንጠለጠላችሁ በሁለት ልብ እንዳነከሳችሁ እስከመቼ? ምስኪኖች።

  ReplyDelete
 2. ለመሆኑ በወያኔዎች ውስጥ ሰውነት የሚባለው የተፈጥሮ ባህርይ ጨርሶ ጠፋ ማለት ነው ? ማንን ነው የሚያታሉት ? መንግሥታቸው አይደለም እንዴ ፓትርያርኩ እንዲሰደዱ ያደረገው ? ድርጊቱን የፈፀሙት የያኔው ጥቅላይ ምንስቴር (ጠቅላይ አጥፊ) ራሳቸው ዛሬ እየመሰከሩ እኮ ነው። ተደብቆ የነበረው ሰነድ ሁሉ እኮ ይፋ ሁኗል ።

  ReplyDelete
 3. ይህ መንግስትን የሚያስመሰግን ጉዳይ ነው። የሀይማኖት ነፃነት ለሁሉም እኩል ነው የፈቀዱትን የመከተል መብት አላቸው ብሎ ብግልጽ መናገሩ በራሱ መልካም አካሄድ ነው። ኦርቶዶክሳዊያን አባቶችም ሆኑ ህዝቡ መንግስት ጣልቃ ሳይገባ መምረጥ መብታቸው ነው በማለት ለአባቶች ሁሉ ነገር ትቶላቸዋል እጅግ ደስ ያሰኛል። ለመሆኑ መንግስት ከፈለገ የፈቀደውን አባት ፓትርያርክ አድርጎ ማስመረጥ ማንም አይከለክለውም ነገር ግን መብቱ አማኙ ህዝብ ነው ብሎ ቃሉን ሰጥቶዋል።የአቡነ መርቆርዮስን ስኖዶሱ ከፈቀደ እኛ አያገባንም ብሎአል። ታዲያ ለምንድነው በግድ በመንግስት ላይ ነገሮችን የሚናጣብቀው። የራሳችን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች ማቅ ያጎረሳቸውን ገንዘብ እያነቃቸው እዉነት መስራት ትተው በክፋት እየተጓዙ ናቸው። የውስጥ ችጎሮቻቸው በመንፈሳዊ መንገድ ከመፍታት ለሌላ ጥቅምና የስልጣን ጥመኞች እራሳቸውን አሳልፈው በመስጠታቸው ሰላም ጠፍቶ ህዝብ ግራ ያጋባሉ። ይህ ክፉ ድርግት በእግዚአብሔር ፊት ሆነ በሰው ፊት መልካም አይደለም። ከመንፈሳዊያን አባቶች የምንማረው እንደ ክርስቶስ ቃል በይቅርታና በፍቅር ህዝበ ክርስቲያኑን መመራት ስችሉና ሰላምን ስያወርዱ ብቻ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ስህተት በእልከኝነትና በትዕብት የሚቀጥል ከሆነ የኦርቶዶክስ አማኝ አንቅሮ ይተፋቸዋል በያዙትም መስቀል እንኳን ብሆን አይባረክም፡፤መስቀሉ የሰላም የፍቅር ምልከት ነው እንጅ የመለያያ መሳርያ አይደለም። ሐዋርያ ጳዉሎስ እንደተናገርው እኔ ክርስቶስን እመስላለሁ እናንተም እነን ምሰሉ በማለት የተናገረው ታላቅ ትምህርትና ህይወት ልሆነን ይገባል። ክምንም በላይ ሰው ለእግዚአብሔር ከተመቸ ለሰዉ ሁሉ ይመቻል።

  ReplyDelete
 4. tfatn ende sket yemikotru weyanewoch zares mn enadrg new yemilut?

  ReplyDelete