Saturday, December 29, 2012

ተጠያቂው ማን ነው?

በመንግስትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን መልካም አስተዳደር እንዲኖር ከተፈለገ ግልጽ የሆነ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባዋል። ተጠያቂነት ካለ በነዚህ ተቋማት ስር የሚተዳደረው ህዝብ ወይንም ምዕመን ትክክለኛ እርምጃ/ግንዛቤ ሊወስድ ይችላል።  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመላው ዓለም እያነጋገረ ያለው የወቅቱ ጉዳይ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ጉዳይ ነው። እግዚአብሔር ራሱ ነገሮችን በተዓምሩ ካላስተካከለ አሁን እያየናቸው ያሉ ብዙ ምልክቶች የሚጠቁሙት የአብዛኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ምኞት የነበረው እርቅ እና አንድነት ህልም ብቻ ሆኖ የቀረ ይመስላል። የአዲስ አበባው ሲኖዶስ 6ኛ ፓትርያርክ የመሾሙን እንቅስቃሴ በፍጥነት እያራመደ ነው። ብዙ የደከመው የሰላም እና አንድነት ኮሚቴ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባው ሲኖዶስ ጀርባ እየተሰጠው ይገኛል። ሐራ ተዋሕዶ የተሰኘው ድረ ገጽ እንደዘገበው በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የተላኩ ሁለት የኮሚቴው አባላት ቤተ ክህነት እንዳይገቡ መከልከል ብቻ ሳይሆን እንደኛው በመንግስት ታፍሰው ወደ መጡበት አሜሪካ በግድ እንዲመለሱ ተደርገዋል። ይህ ሁሉ የሚጠቁመው በሰላም እና አንድነት ላይ በር እየተዘጋበት መሆኑን ነው።

በርግጥ እግዚአብሔር በአውሎና በወጀብ መካከል መንገድ አለው። አምላካችን እግዚአብሔር ነውና ተስፋ አንቆርጥም፤ አሁንም እርቅና ሰላም ሊመጣ ይችላል። ተግተን ከጸለይን እና እግዚአብሔር ፍቃዱ ከሆነ በአንድነት ለዘመናት የኖረችውን ይህችን ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር ይታደጋታል። አሁን የተጀመረው እና እየተዳከመ ያለው የእርቅ እና አንድነት ጉዞ ባይሳካ ግን ተጠያቂው ማን ነው? የአዲስ አበባው ሲኖዶስ ነው?  በስደት ያለው ሲኖዶስ ነው? መንግስት ነው?  ማን ነው?  በርግጥ ዘመኑ የመረጃ ዘመን ነውና ህዝቡ እነዚህን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ብዙም ጊዜ የሚፈጅ አይሆንም። በአሁኑ ሰዓት ግን ተጠያቂው ማን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።  መንግስት በመገናኛ ብዙሃን እኔ አያገባኝም ብሏል። የአዲስ አበባው ሲኖዶስም መንግስት ተጽዕኖ እያሳደረብኝ ነው አላለም።  መንግስት አዲስ አበባ ባሉ አባቶች ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ብለው የዘገቡም የመገናኛ ብዙሃን አሉ።  ምን አይነት ተጽዕኖ? ማስፈራሪያ?  ምን አይነት ማስፈራሪያ?  የሞት ቅጣት? እስራት?   የመንግስትም ተጽዕኖ ካለበት ከአባቶች መካከል እውነቱን ለመናገር አንድ ደፋር መንፈሳዊ ይገኝ ይሆን? 

እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች የመረጃ ኃይልና ጊዜ ይፈታቸዋል። ሆኖም ግን እስካሁን ያስተዋልናቸው ነገሮች ተጠያቂነቱን አዲስ አበባ ባሉ አቦቶች ላይ እንድናስቀምጥ ያስገድዱናል። በእርቁ ዙሪያ አባቶቹ ተከፋፍለዋል። ግን ታዲያ ለምን እርቅ የማይፈልጉት ጠንክረው ተገኙ? ብዙዎች ስለሆኑ? መንግስት ከጎናቸው ስላለ?  ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ተጠያቂነትን ለህዝቡ ግልጽ ለማድረግ ሊሰሩ ይገባል።

ከአባሰላማ አንባቢ

3 comments:

 1. ተመስገን አምላኬ ዛሬስማኅበረ ቅዱሳንን ተጠያቂ አላረጋችሁም አሁንትንሽ ወደ እውነት የተጠጋችሁ ትመስላላችሁ

  ReplyDelete
 2. መረጃው እውነት ይሁን ውሸት አይታወቅም እንጂ ነገሩ ያለቀለት ጉዳይ ይመስላል ፡፡ በሚከተለው መክፈቻ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተገኘ ተብሎ የተለቀቀውን ሥርቅ ዜና ተመልከቱ ፡፡

  http://www.zehabesha.com/archives/15174
  "Breaking News (ሰበር ዜና)፡ 6ኛውን ፓትርያርክ ለማስመረጥ ለተሾሙት ሰዎች ከሲኖዶስ የተጻፈላቸው ምስጢራዊ ደብዳቤ እጃችን ገባ ፡፡" ይላል ርዕሱ

  የግለሰቦች የፈጠራ ወሬ እንዳይሆን እጠረጥራለሁ ፡፡ ምክንያቶቼም
  - ከገጹ በግራ በኩል ላይ የተወሰነ የተጐረደ የገጽ ክፍል ይታያል ፤ ምናልባት የተላከለት ሰው እንዳይለይ ለማድረግ ከሆነ አላውቅም ፤ ነገር ግን የተቆረጠው ክፍል ከስም ዝርዝራቸውም ያልፋል ፡፡
  1- በመጀመሪያው ገጽ ያለው የዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ማኀተም ከጽሁፉ በታች ነው (በመስቀሉ ላይ ፊደሉ በደንብ ይታያል)፡፡ የአሥራ ሦስቱ አስመራጭ ኮሚቴዎች ሥም ዝርዝር ሰፍሯል ፡፡
  2- በሁለተኛው ገጽ ላይ የኘሮቶኮል ቁጥርና የቀን መጻፊያ ቦታ ክፍት ነው ፡፡
  3- ድረ ገጹ "Ze-Habesha Website is not responsible for accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors." በማለት ራሱን ከጉዳዩ ያገላል ፡፡

  እግዚአብሔር የሚያደርገውን እጠብቃለሁ ፡፡

  ReplyDelete
 3. ውድ አባሰላማ። የተለያዩ አሳቦች መኖራቸው ምዕመኑንም ለያይቷል። ከላይ እንዳቀረብከው "እከሌ ነው፣ አያገባኝም፣ እኔ የለሁበትም" የመሳሰሉት አባባሎች የሚጠቅሙት በሕግ ወይም ያለ ሕግ ሊፈጽሙት የሚፈልጉትን ያወቁ ክፍሎች ናቸው። ሰሞኑን ከታች የተመለከተውን አስፈንጣሪ አግኝቼ ይልቅ ሕዝቡን ግልጽ በሆነ አንድ ዓላማ ዙሪያ ሊያሰባስብ የሚችል ስለ መሰለኝ ልኬላችኋለሁ። ሕዝቡ ሌላ ሌላውን ትቶ እግዚሐር ይፍረድ ቢል ይሻል ይመስለኛል። አዚ ነኝ ከዳላስ http://www.ethiopianchurch.org/essay1/150-%E1%8D%93%E1%89%B5%E1%88%AD%E1%8B%AB%E1%88%AD%E1%8A%AD-%E1%89%A0%E1%8B%95%E1%8C%A3.html

  ReplyDelete