Thursday, January 10, 2013

እርማችሁን አውጡ!

/ ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
Las Vegas, NV

መሪ ጥቅስ:
ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ በዚያም አደረ በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና። ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ። ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው(የማቴዎስ ወንጌል 21 17- 22)
መግቢያ:
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶቤተ ክርስቲያንየሃይማኖት መሪዎች ጉዳይ ለልባሞች ዕዳ ሲሆንባቸው ለጥቂቶች ደግሞ ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸው ሥራ በዝቶላቸዋል። ያም ሆነ ይህ ግን አበው መነኮሰ/ፈለሰ = ሞተ ሲሉ እንደ ቃላቸውና እንደ ግሡም ፍቺ መሰረት ኑረውበትና አስተምረውት ለእኛም ትተዉልን ያለፉትን እውነት ቀርቶ በተገላቢጦሽ መነኮሰ/ፈለሰ = ነገሠ ሆኖ ብዙዎች “መነኮሳቶቻችንልብ አጥተው ሥመ እግዚአብሔር የደቂቃን መሳቂና መሳለቂያ ከሆነና ካደረጉት ከራርመዋል። ጽሑፉ ሁለት ክፍሎች ሲኖረው ቀዳሚው ክፍል በዋናነት መንፈሳዊ የሆነች የቅድስት ቤተ ክርስቲያንና መንፈሳዊ አሰራርዋን የሚያስተዋውቅበተጨማሪም የኃይማኖት መሪዎች ንዝህላልነትና የግብር ይወጣ ስራ የሚያስተዋውቅ ሲሆን ክፍል ሁለት ደግሞ ዕርቅን ማውረድ ከተፈለገ ከኃይማኖት መሪ የሚጠበቀውን የሚያትት፣ አክሎም በቀጥታ የኃይማኖት መሪዎችን የሚመለከት መልዕክት ያዘለ ክፍልም ይገኝበታል። ሁለቱም ተከታታይ ጽሑፎች በይዘታቸው አንድስንኳ ደግ፣ ቅንና መልካም አሳቢ የለም የሚል ድምዳሜ የላቸውም።

የጽሑፉ ዓላማ:
በሁኔታው ልባቸው ስለተሰበረ፣ አንገታቸውንም ስለደፉ አበው ካህናት መምህራን ደቀ መዛሙርት በአንጻሩ ደግሞ ገበያው ስለደራላቸውና በሁከቱ ተጠቃሚዎች ስለሚሆኑና ስለሆኑ ለቃሚዎች ዙሪያ ላይ የሚሰሙ እሮሮዎችና እየተመታ ስላለው የቂል ከበሎ ለማሰማትና ለማተት ሳይሆን በጽሑፉ መግቢያ በመጠኑ የጦማሬን ውስጣዊ ይዘት ለማሳየት እንደተሞከረ የጽሑፉ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉ እስከ ዛሬ ዕለት ድረስ የተጋረደበት፣ የተሰወረበትና ያላየውን ሐቅ ለማሳየትና ለማሳወቅ ሲሆን ከምንም በላይ ደግሞ የኃይማኖት መሪዎች ማለትም መነኮሳት የሆኑት ሊቃነ ጳጳሳትን ለመውቀስ ሳይሆን ዓይናቸውን ከፍተው የቆሙበትን የድጥ ስፍራ ይመለከቱ እንደሆነ በሚል ተስፋና እምነት ነን እንደሚሉት እንደመንፈሳውያንመሪዎች ያለመታከት ሰላምን ይሹና ያወርዱም ዘንድ አማራጭ የሌለው ግዴታቸው ለመሆኑ ለመመስከር የተዘጋጀ ሥራ ነው።ሐተታ:
ቤተ ክርስቲያን እንደ መንፈሳዊ ተቋም በደሙ ከመሰረታት ከክርስቶስ ኢየሱስ የተሰጣት ተልዕኮ የምትፈጽምበት፣ ዓላማዋንም ከግቡ የምታደርስበትና እውን የምታደርግበት፣ እንዲሁም ሥራዎችዋንና አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችዋን በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ በወቅቱ በተሳካ መልኩ ለመከናወናቸው የምትመርምርበት:
·         ራሱ የቻለ፣
·         ያልተበረዘ፣
·         ያልተቀላቀለ፣
·         ከሌላ ምንጭ ያልተቀዳና ያልተኮረጀ፣
·         በተውሶ ያልተገኘ፣
·         የጥበብ መንገድ የእውቀትም ቤት ከሚያውቅና ከሰራ፣ ከሁሉም በላይ፣ የነገሮች ሁሉም ምንጭ ከሆነ የተገኘ፣
·         የጠራ፣
·         እንከን የማይወጣበት፣
·         አስተያየት የማይሰጥበትና ትችት የማይሰነዘርበት፣
·         በዘመን ብዛት የማያረጅ/የማይሻር፣
·         ማሻሻያ የማይሻው/የማይደረግበት፣
·         ልባቸውን ለሚጥሉበት፣ ለሚሰሙት፣ አሜን ብለው ለሚቀበሉትም ሁሉ ህይወት የሆነ፣
·         የሚያሳርፍ፣
·         የላቀና ለሌላ የሚተርፍ፣ ከሁሉም በላይ ብልጫ ያለው መንፈሳዊ አሰራር ያላት መንፈሳዊ ቤት ናት። በነገራችን ላይ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ አሰራር እንዳላት በምእመናን ዘንድ ይቅርና በመነኮሳቱ/ሊቃነ ጳጳሳቱ ሳይቀር የተዘነጋ ለመሆኑ ሰው የሚያየውና እየሆነ ካለ የኃይማኖትመሪዎቻችንፍሬ በማየት ለመረዳት ይቻላል።
መንፈሳዊ መሪም እንደዚሁ የጣቢያ ማዘዣውም ሆነ የስራዎቹ ሁሉ ምንጭ መንፈስ ቅዱስ ነው። በግላጭ እየታዬ ያለው ግን የኃይማኖትመሪዎቻችንየመርጃ ምንጭ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ ቀርቶ ትምህርት ያልጠገቡ አነብናቢዎችና ወሬ አመላላሾች ለመሆናቸው አሌ የማይባል የአደባባይ ምስጢር ነው። ታድያ እንዲህ ባለ ሁኔታ የኃይማኖት መሪዎች ኮከቡ ጠፍቶባቸው የሚይዙትና የሚጨብጡትም አጥተው ከሚፈጽሙት ግራ የተጋባ ድርጊቶቻቸው የተነሳም ጥርስ አልባ ሁላ ከማዶ ተሰብስቦ/ተቀምጦ ይሄ እግዚአብሔር እግዚአብሔር ሲሉ የሚጠሩትን ወዴት ሄደ? የለም ማለት ነው?” እያሉ በፌዝና በምጸት ክት ብለው ቢስቁና ቢሳለቁ ምን ይደንቃል?
አንባቢ ሆይ! እርምህን አውጣ:
·         ብዙዎች ሊቃነ ጳጳሳት ኃይማኖት እንጅ እምነት የላቸውም።
·         አንባቢ ሆይ! የሌለውና የተሳነው እግዚአብሔር ሳይሆን የጠፋው በእግዚአብሔር የሚያምን መነኩሴ/የሃይማኖት መሪ ነውና።
·         አንባቢ ሆይ! ያበዱም መነኮሳቱ እንጅ ለህዝቡ ሰላም የማይሻ እግዚአብሔር አይደለምና ህውከትንና መበጣበጥን የመረጡየእኛዎቹየኃይማኖትመሪዎቻችንሊቃነ ጳጳሳት ናቸው።
·         አንባቢ ሆይ! ብዙዎች መነኮሳት/ሊቃነ ጳጳሳቱ እግዚአብሔርን የሚያምን ልብ የላቸውም ብል እንግዳ/መርዶ እንደማይሆኑቦት ተስፋ አደርጋለሁ።
·         አንባቢ ሆይ! ቤተ ክርስቲያንም እንደሆነች ሳይወጡና ሳይወርዱ በተቀመጡበትእዛዝ በገላዬ!” እያሉ ተንፈላፍሰው ሆዳቸውን የሚሞሉባት፣ ዲቃላዎቻቸውንም የሚያሳድጉባት፣ የገቢ ምንጫቸው እንጅ እንደ እግዚአብሔር ቤት አምነው አልተቀበልዋትም ብዬ ብጨምርሎት መቼም አሁንም ዱብእዳ እንደማይሆንቦት አምናለሁ።
የሃይማኖት መሪዎች ሆይ! ምን አለፋችሁ መልክ እንጅ ኃይል (የእምነት ኃይል) የላችሁም።የሚያምኑ አይመስለኝም/የምታምኑ አይመስለኝምአይደለም እያልኩ ያለሁ። የተጻፈውን በደንብ የሚነበብላችሁና አንብቦም የሚነገራችሁ ሰውም በደንብ የሚነበብለት ከሆነ እያልኩ ያለኹተይ አያምኑም/አታምኑም! ነው። በአጭሩ የያዛችሁት መስቀልም ሆነ የለበሳችሁት ልብስ ፊት አይቶ ፍርድን ከማጓደል፣ ልብስንም አይቶ ላለው ከማድላትና ረዳት ለሌለው ድሃን በመበደል ፍትህንም በማጣመም የሚታወቀው/በሚተጋ በሰው ዘንድ መንፈሳዊ ሰው መስላችሁ ለመታየት የምታደርጉት ጥረት እንጅ እውነት መንፈሳዊያን ሆናችሁ አይደለም ነው ነጥቤ።
እንደው የአንዳንዶቻችሁ መነኮሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ነገርማ ሆድ ይፍጀው። ሀገርና ሕዝብም ይፈወስ ዘንድ እውነቱን እንናገር ብለን የሞከርነው እንደሆነ እንዱላና ቆመጥ ይዞ ቀጥቅጦ ለመግደል እንዲሁም ባልተገራ አንደበት ብዙና ጥቂት ማለት በሚቀናው ማህበረሰብ መካከል ሆን እንጅ እዚህ ደርጃ ላይ የሚያደርስ ችግር ለመፍጠርም አቅም ባላገኛችሁ ነበር። የአንዳንዶቻችሁ መነኮሳትና ሊቃነ ጳጳስት እንደ መዥገር በቤተ ክርስቲያን ላይ የተጣበቃችሁት የምትሰሩት ቁምነገር ኖራችሁ ሳይሆን ተሸክማችሁ፣ የሀገር ዳር ድንበር የህዝብ ሰላም ለመጠበቅና ለማስጠበቅም በታማኝነት ታጥቃችሁ ላለመሰለፍና በድለላ፣ በአናጺነትና በግንበኝነት የሥራ መስክም ተሰማርታችሁ ኑሮአችሁን መኖር ስለማትፈልጉ ብቻ እንደ ሆነ በየዋህነት የሚከተላችሁ ሕዝብ አዚሙ የለቀቀው ቅጽበት፣ ዓይኑ ከፍቶም ማየት የጀመረ፣ የበራለትና ከተኛበት ከባድ ዕንቅልፍ የነቃ ዕለት እግዚኦ የት ይሆን መሸሽያችሁ?
ጎበዝ ሆይ! እውነቱ ይህ ነው:
·         መንፈሳዊ ቋንቋ መናገር፣
·         በወርቅ የተለበጠ መስቀል መጨበጥና አንገትህ ላይ በማንጠልጠል፣
·         በሽቶ የሰከረ፣ በውድ ዋጋም በባለ ሞያ የተሰፋ ዘረፍያ መልበስና አስኬማ መድፋት ማለት መንፈሳዊ ከመሆን ጋር ምንም የሚያገናኘው የወጣ ነጥብ የለውም። መንፈሳዊነት በቁሙ ሲተረጎም/ትርጓሜው የሚታይ፣ የሚዳሰስና የሚጨበጥ፣ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበት ህይወት ማለት ነው። አሁን ይህን አባባልህ አልገባኝም በማለት ማብራሪያ የሚጠብቅ ወይም የሚጠይቅ ሰው ካለ/ያለ እንደሆነ በእውነቱ ነገር እንደ ////ያን ሥርዓተ ትምህርት መሰረት እንዲህ ያለ አዲስ ውልዶ ማብራርያ መስጠትና ትምህርት ማስተማር ሳይሆን የሚያስፈልገው ጥምቀት ነው።
በጽሑፌ መንደርደሪያ በመሪ ጥቅስነት ወደ አስቀመጥኩት ቃል ልመለስ። ወደ ቁጥር አሥራ ሰባት ከመዝለቃችን በፊት የታሪኩ ተያያዥነትና የቃሉ መንፈሳዊ ፍቺም በሚገባ እናገኘው ዘንድ ከፍ ብለን የምዕራፉ ክፍል የሆኑትን ቁጥሮች መመልከቱ አስፈላጊ ስለሆነ ጥቂቶቹን በግርድፉ እንናያለን።
እንግዲህ ማቴዎስ እንደጻፈው ኢየሱስ ትቶአቸው ወደ ቢታንያ ከመውጣቱና ተመልሶም ከመምጣቱ በፊት ከተማይቱ ተብላ የተጠቀሰችው ኢየሩሳሌም እንደሆነች ልብ ማለት ያስፈልጋል። ወደ ከተማይቱ በሚገባበት ወቅትም በከተማይቱ ነውጥ እንደሆና በደማቅ አቀባበል፣ በታላቅ ጩኸትም ታጅቦ እንደገባ እናነባለን። ከዚህ አልፎ ወደ ቤተ መቅደስ ባመራበት ጊዜ ግን ኢየሱስ የጠበቀው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየና ግር የሚሰኝ ትዕይንት ነበር። ይኸውም: በኢየሩሳሌም የሚኘው ቤተ መቅደስ የካህናት አለቆችና ጻፎች በበላይነት የሚመሩትና የሚቆጣጠሩት ገዢና ሸያጭ የሚገናኙበት፣ ደንበኛ የንግድ ማዕከል ሆኖ ነበር ያገኘው። በቁጥር 17 ላይትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ በዚያም አደረእንዲል ትቶአቸው የሄደም ሕዝቡን ሳይሆን የካህናት አለቆችና ጻፎች ነበሩ። ቀደም ሲል በቁጥር 14 ላይበመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸውተብሎ ተጽፎ እንደምናገኘው።
በመጀመሪያ ኢየሱስ የካህናት አለቆችና ጻፎችን ትቶአቸው የሄደበትን ምክንያት ማየቱ መልካም ነው። ቤተ መቅደስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ በቤተ መቅደስ ውስጥም ምን ዓይነት ሥራ እንደሚሰራና እንደሚከናወን፣ ቤተ መቅደስን በኃላፊነት የሚያስተዳድርና የሚመራ ማን እንደሆነ፣ መሪውም ሆነ በቤተ መቅደስ ዙሪያ የሚያገለግሉ ካህናት ምን ዓይነት የሥነ ምግባር ሰው መሆን  እንደሚጠበቃቸው የምንስተው አይመስለኝም። አሁን ግን ይህ ሁሉ እውነት ተፋልሷል። ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር ክብር የሚቀርበውን መስዋዕት መገልገያ መሆኑ ቀርቶ ዓይኔ ግንባር ያድርገው፣ ከምላሴ ጸጉር ይነቀል፣ እየነገርኮትበቃ እንግዲህ ካላመኑኝ በልጄ ይሁነኝ …”በሚሉ ዓይናቸውን በጨው ባጠቡ ነጋዴዎች ተጥለቅልቋል። የካህናት አለቆችና ጻፎች እንደሆኑም ሕዝቡን የእግዚአብሔር ሕግ በማስተማር ከማትጋትና መንፈሳዊ ስራም ከማከናወን ይልቅ/ፈንታ አንዳንዶቹ ገዢና ሸያጭ በማገናኘት (በድለላ) ሥራ ላይ ተጠምደዋል፤ ሌሎቹ አንተስ ስንት ሽጠሃል ዛሬ? … እና አሁን ለእኔ ይህ ብቻ ነው የሚደርሰኝ ማለት ነው? ኧረግ ኧረግ በል ነገ ለእኔ ብቻ ይህን ያህል ገቢ ካላመጣህ የሚቀጥለው ቀን ቦታውን ለሌላ ነው አሳልፌ ነው የምሰጠውእያሉ ፐርሰንት ሲሰበስቡ፤ ገሚሰቹ ደግሞ በተቀመጡበት ሆነው በከፈቱትየጨለማ ገበያከቀሚሳቸው ስርነገርእያስተላለፉ የጦፈ ንግድ ሲያካሂዱ ወፍረውና አባብጠውም ነበር ያገኛቸው። በዚህም ወቅት ነበር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁትሲል በሚገባቸው መንገድ በጅራፍ እየገረፈ ያባርራቸው ዘንድ ግድ ያለው።
ከምንም በላይ ግን የቃሉና የመልዕክቱ ምሥጢር ያለው እንደሚከተለው ነው። ሰዎቹ (የካህናት አለቆችና ጻፎችን ማለቴ ነው) ይህን የመስለ ለሰሚ ጆሮ የሚሰቀጥጥ፣ አሳፋሪና የወረደ ሥራ ላይ መሰማራታቸው፣ መዘፈቃቸውና መጨማለቃቸውን ያላሳፈራቸውየእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም የገበያ ማዕከል ማድረጋቸው ያላስቆጣቸው ኢየሱስ ዕውሮችና አንካሶች በመፈወሱ፣ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹ ልጆችም ባዩና በሰሙ ጊዜ ግን ቁጣ ነደደባቸው። በሌላ አነጋገር ባሳለፍነው ጥቂት ሳምንታት የኢ... መንግሥት ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በማስመልከትሰላም አውርዱሲሉ ግልጽ ባለ ቋንቋና አገላለጽ ያስተላለፉትን መልዕክት/የጻፉትን ደብዳቤ ተከትሎ ሃያ አራት ሰአት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ከቤተ ክህነት አከባቢ የሰማነውን የአገር ይያዝልን ጩኸት እንደ ማለት ነው። ኢየሱስ የካህናት አለቆችና ጻፎችን ትቶአቸው የሄደበት ምክንያትም ይህ ነበር። የእግዚአብሔር ቤት ክብር በአደባባይ ሲዋረድና ሥሙም በማያምኑ በአህዛብ መካከል ሲፌዝበት ያልተሰማችሁ ሕመም ክብራችን ተነካ ስትሉ ግን ጦርነት ከማወጅ ባልተናነሰ መልኩ ጩኸቱን አቀለጣችሁት።
ጥበብ በዚህ አለ! የፕሬዝዳንቱ ደብዳቤ እንደሆነ የተዋረደው/ያዋረዳችሁት ክብር የሚመልስ ጥበብ የተሞላበት ጽሑፍ እንጂ የማንም ግለሰብ ክብር የሚነካና በማንም ሥልጣን ላይ ጨርሶ ጣልቃ የመግባት አዝማምያ ያለው መልዕክት ያዘለ ደብዳቤ አልነበረም። በሰው ፊት ያከበራችሁ፣ ክብራችሁ የሆነ እግዚአብሔር በአደባባይ አዋርዳችሁት ስታበቁክብራችንተነካ ማለታችሁስ ቀድሞውኑ ክብር ማለት ምን ማለት እንደሆነና ክብር ሲኖራችሁ አይደለም ወይ? ለሰላም፣ ለለውጥ፣ ለልማትና ለዕድገት ልታበረክቱትት የምትችሉት አስተዋጽኦ በህይወት ከሌሉ የማትሻሉና ለመኖራችሁ ራሱ እስከማትታወቁ ድረስ ሀገርና ሕዝብ የማያውቃችሁ ግለሰቦች ክብራችሁን ለማስጠበቅ ግንሃይማኖት አሳብባችሁ ሀገርና ሕዝብን ለማተረማመስ እንዲሁም ትውልድም ለመቅጨት ያላችሁ ፈርጣማ ጡንቻ ግን የሚገርም ነው።
የጦማሬ ሁለተኛ ክፍል እንዲሁም ዋና መልዕክቴ ወደሆነው ሐተታ ስናልፍ ደግሞ ኢየሱስ ወጥቶ ካደረበት ከቢታንያ ተመልሶ ወደ ከተማይቱ በሚያመራበት ሰዓት በመንገድ ላይ ሳለ የሆነውን ነገር የሚዳስስ ይሆናል። ሙሉ የቃሉ ይዘት ከጽሑፉ መሪ ጥቅስ የሚገኝ ሲሆን በዋናነት ጸሐፊው በዚህ ቀጣይ በሆነ ጽሑፋቸው ለማስተላለፍ የሚፈለጉት መልዕክት በቁጥር 22 ላይ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸውበሚለው ዓረፍተ ነገር ዙሪያ መሰረት ያደረገ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጸሎት ስላቆሙ ይሆን ወይስ ተገቢ የሆነ ኃይል ያለው ኃይል የሚወርድ ጸሎት መጸለይ ስለማይችሉና ስለማያውቁ ነው? ማን ይሁን እውነተኛ ይዋሽ ዘንድ ሰው ያይደለ ቃሉን የሰጠ እግዚአብሔር ወይስሊቃነ ጳጳሶቻችን“? እና ሌሎች በርካታ የታያዥነት ያላቸው ወቅታዊ የኃይማኖትመሪዎቻችን መዋዥቅም የሚመረመርበት ጠንከር ያለ መልዕክት ይሆናል።

ይቀጥላል


እንዲህ ያለ ነገር ለምን ነገርከኝ!
/ ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
Las Vegas, NV
January 07, 2013

4 comments:

 1. የተሰቀለው ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታ ነው !January 10, 2013 at 8:06 AM

  በአጭሩ የያዛችሁት መስቀልም ሆነ የለበሳችሁት ልብስ ፊት አይቶ ፍርድን ከማጓደል፣ ልብስንም አይቶ ላለው ከማድላትና ረዳት ለሌለው ድሃን በመበደል ፍትህንም በማጣመም የሚታወቀው/በሚተጋ በሰው ዘንድ መንፈሳዊ ሰው መስላችሁ ለመታየት የምታደርጉት ጥረት እንጅ እውነት መንፈሳዊያን ሆናችሁ አይደለም ነው ነጥቤ።

  Lord Jesus Bless you, my brother ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል

  ReplyDelete
 2. ere gobez einideti new negeru higawi weyinm sidetegna sinodosi yemibalew zuriyawin be poletika yetater heger wisti yalew sinodos zuriyawin betikimi na be poletika yetater mini yischalali hulu neger keditu wedematu hone ko amilaki bemihiretu daso firid yisten minew zimi alen lesu kebir yalikomutin hulu ke zemari eisk patiriyrik yalutin be mulu terarigo adis neger bifetir Egizeo belu..

  ReplyDelete
 3. እምነታችንን ለመጠበቅ እኔ የሚመስለኝ ማድረግ ምዕመናን ማድረግ ያለብን፤
  የሀገር ቤቱን ጳጳሳትና በውጭ የሚገኙትን ጳጳሳት ወደ ገዳም ሰዶ ንጹህ መነኮሳትን በንዋይ ፍቅር፣ በዘር፣ በሙስና ያልዛቀጡትን በቦታው ላይ ማስቀመጥ ብቻ ነው።

  ReplyDelete