Sunday, January 13, 2013

እርማችሁን አውጡ! ክፍል ሁለት

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
ከባለፈው የቀጠለ
ባለፈው ክፍል አንድ ሰፊ ንባባችን ርእሱ ጠብቀው የሚነሱ በርከት ያሉ የተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች እንስተን መወያየታችን የሚታወስ ነው። በዛሬ ለትም እንዲሁ ከባለፈው በመቀጠል ዋና ዋና ነጥቦች በማንሳት ጥቂቶቹን የምንዳስስ ሲሆን ከሁለትና ከሦስት ገጽ በላይ ጽሑፍ የማንበብ ነገር የማይሆንላቸው አምስትና ስድስት  ገጽ ረዘመ/በዛ በማለት የሚያማርሩ ወገኖቻችን ግምት ውስጥ በማስገባት ተጨማሪ  ሦስተኛ ክፍል ማዘጋጀቱ ግድ ስላለ ከተጨማሪ ሃሳቦች ጋር ጸሐፊው ክፍል ሦስት በቀጣይነት መኖሩንም  ሲያሳውቁ በአክብሮት ነው::
ምሥጋና:
ከጊዜ መጣበብ የተነሳ በኢ-ሜይል አድራሻዬ ለተጻፈልኝ ለእያንዳንዱ ኢ-ሜይል መልስ መስጠት ባለመቻሌ በዚህ አጋጣሚ ጊዜአችሁን መስዋዕት አድርጋችሁ አስተያየታችሁን ለገለጻችሁልኝና ለጻፋችሁልኝ ወገኞች በሙሉ ምስጋናዬ የላቀ ነው:: ምንም እንኳ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የሰፋ የሃሳብ ልዩነት ቢኖረንም እንደ አንድ ሰው አንድ ልብ ሆነን እየተቀባበልን በትጋት መስራት በሚጠበቅብን ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ግን እጅና ጓንት ሆነን ሀገርና ሕዝብን ማገልገል በመቻሉ ሊበረታታና ቀጠይነትም ይኖረው ዘንድ የሚገባ ጅምር: አንድ ቀንም ልዩነት በልዩነት ወደ ማስተናገድ ደረጃ የሚወስድ ነውና የተለያዩ ኢትዮጵያውያን ድረ ገጾች ባለቤት የሆናችሁ በግንባር ቀደምትነት አቶ ኤልያስ ክፍሌ (ethiopianreview): አቶ አብርሃ በላይ (ethimedia): አቶ ሳምሶን አስፋው (quatero): እንዲሁም የዘሐበሻ ድረ ገጽ አዘጋጅ አቶ ሄኖክ ምስጋናዬ የላቀ ነው:: በተጨማሪም ጊዜአችሁ: ጉልበታችሁና: ገንዘባችሁ አውጥታችሁ ድረ ገጾች ገብቶ የማንበብ እድሉ የሌለው ማህበረሰብ ጽሑፎቼን በማተም በማዳረስ ረገድ የተጋችሁ በለንደን የኢ/ት/ኦ/ተ/ቤ/ያን ቅድስት ድንግል ማሪያም ምእመናን እግዚአብሔር ሰላሙ ይስጣችሁ ይባርካችሁም ለማለት እወዳለሁ::
ርዕሰ አንቀጹ ማቴ. 21: 22 መነሻ/መሰረት ያደረገበት ዋና ምክንያት:
ጸሐፊው በማቴዎስ ወንጌል 21: 22 ላይ ተንተርሰው ለመጻፍ ተየገደዱበት ዋና ምክንያት ቀደም ሲል ሁላችንም እንደምናስታውሰው ምን ብለው እንደጸለዩና ስለተጸለዬም ጸሎት በውል የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ባለፈው ጊዜ በሀገር ቤት የሚገኘው ሲኖዶስ በርከት ላሉት ቀናት የሱባኤ አዋጅ አውጆ መኖሩንና ከዚህም በኋላ የሁለቱ ባለንጣ ተወከዮች በዳላስ ቴክሳስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተገናኝተው አብረው እንደጸለዩ: “በይደርም” ተለያይተው ሲያበቁ ሁለቱም አካላት ተደረገ የተባለውን ጸሎትና ጸሎቱን ተከትሎ የታየው ከቀድሞ አለመግባባት ይልቅ ሊቃነ ጳጳሳቱ እያሳዩት ያለው አቋም ከዘብተኛ ሰይጣን በመልኩ እንጅ በዓይነቱ የማይለይ መልስም የሚሻው ዓብይ ጉዳይ ሆኖ በመገኘቱ ርዕሰ አንቀጹ ማቴ. 21: 22 መነሻ/መሰረት ያደርግ ዘንድ ግድ ብለዋል 
ማሳሰቢያ:
ጸሐፊው ከዚህ ቀደም "ዜማ እስኪታደስ ጆሮ ዳባ ልበስ"  ሲሉ ለንባብ ባበቁት ጽሑፍ ከምንም በላይ የጸሎት አስፈላጊነት ትኩረት ሰጥተው ከመጻፋቸው በተጨማሪ በዋናነት በአሁን ሰዓት የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የኃይማኖት መሪዎች በገዛ እጃቸው የጠነጠኑት ችግርና የገቡበት አዘቅትም መውጣት የሚቻለው "በፍሬ ከርስኪ ጸሎት" ሳይሆን በማሰብ እንደሆነ በሰፊው ሐሳባቸው ማካፈላቸው ይታወሳል። ቅድሳት መጻሕፍት እያጣቀሱ ያለው ችግር በማሰብ የሚፈታ ችግር ነው ሲሉ ማሳብ ሲባል ምን ማለት እንደሆነም በሰፊው ማብራሪያ መስጠታቸውም ይታወቃል:: በተጨማሪም ጸሎት ከተጸለዬም በድብብቆሽ የሚሆን ነገር እንደሌለም ጸሐፊው አስምረውበት እንዳለፉ ልብ ማለቱ በዛሬው ዕለት ደግሞ ርዕሰ ጉዳዩ በጸሎት ዙሪያ የሚያጠነጥን/የሚያተኩር ሆነው ሲያገኙት በመጠኑም ቢሆን ግር እንዳይሎት በሰከነ አእምሮና በተረጋጋ ልብ ያነቡት ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ጸሐፊው በዚህ ጽሑፋቸው የሚጸለየው ጸሎትም ሆነ የሚቀርበው የልመና ዓይነት መልስ ሊያገኝ የሚችለው መጀመሪያ (መልእክቱ ለሁለቱም የሃይማኖት መሪዎች ይመለከታል) ኃጢአታችሁ ለእግዚአብሔር ስትናዘዝዋት፤ ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋርም ያላችሁ ግኑኝነት ስታስተካክሉና ስትታረቁም ብቻ ነው ለራሳችሁ አርፋችሁ ሌላውን ማሳረፍ የምትችሉ ባይ ናቸው። በተረፈ ግን የጽሑፉ አዘጋጅ የሚጠበቅባችሁ/ድርሻሁን ሳትወጡ እንዲሁ እግዚአብሔር በጅምላ ሥራችንን ይሰራልናል ብሎ በሃሳብ ደረጃ ማሰቡ ራሱ ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ሌብነት ጭምር ነው የሚለውን ጽኑ አቋም ያንጸባርቃሉ።
የሐተታው ውስኑነት፡
ሐታተው ርዕሰ ዓንቀጹ መነሻ ያደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በከፊል ሥነ መልኮታዊ ትርጓሜውን አይዳስስም።
ሐተታ:
በቀደመ ንባባችን በሰፊው እንደዳሰስነው አሁንም ቢሆን ከምንም በላይ ለኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የሃይማኖት መሪዎች በድጋሜ አጽንዖት ሰጥቼ ለማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ቢኖር ሊቃነ ጳጳሳት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ግልጽ ያድርጉ ዘንድ ነው። ለመሆኑ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ “ማን ነህ?” ተብሎ ስሙ ሲጠየቅ ያዕቆብ ከሆነ ጌታ ሆይ ያዕቆብ ነኝ! ማለቱን ትቶ ኤሳው ነኝ! ማለት እንዴት ይቻለዋል? መገናኛ ብዙሐን ላይ የለመዳችሁትን የመሸምጠት አባዜ የእግዚአብሔር ፊት ድረስ የተከተላችሁ እንደሆነ ወዮ ለእናንተ! ሰው ደግፎ የማይደግፋችሁ አንስቶም የማያነሳችሁ የጭንቅ ቀን በደጅ ናት:: ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነኝና እንቅልፍ የሚነሳኝ ነገር ቢኖር ግን ልብሳችሁና በእጃችሁ የያዛችሁት መስቀል አይቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተታለለው: እውነት ማየት ያቃተው: እናንተን አምኖ የሚከተላችሁ መሄጃ የሌለው ይዛችሁት የምትጠፉት የዋኁ ሕዝብ ነው።
ወደ ዋና መወያያ ርዕሳችን ስንመለስ የዛሬው ዕለት ንባብ/ጽሑፍ በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ 21 ቁጥር 17 ላይ "አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው" ሲል “በወንጌላዊ ማቴዎስ” ጻፈ ቃል ላይ ትኩረት ሰጥን እንደምንያይ ነበር በጨረፍታው ተነጋግረን በይደር የተለያየነው። እነሆይ በተቀጠረለት ቀን የተባለውን ርሰ አንቀጽ ሐተታ እንደሚከተለው ይነበባል መልካም ንባብ!  
ወደ ዝርዝር ነጥቡ ከመግባታችን በፊት  ግን  ጌታ ተከታዮችሁ ለሆኑት ለሐዋሪያት ይህን ቃል ይናገር ዘንድ ግድ ያለበት ምክንያት ማየቱ አስፋላጊ ነው:: በነገራችን ላይ በጌታና በሐዋሪያት መካከል ያለውን ግኑኝነት በተመለከተ ሐዋሪያትና ጌታ ምንድና ምንድን ናቸው? ተብሎ ቢጠየቅ መቼም የአፍ ክርስቲያን ካልሆነ በስተቀር ጤናማ ሰው "አሰሪና ሰራተኛ ናቸው" ብሎ መልስ የሚሰጥ ያለ አይመስለኝም::
ከኢየሩሳሌም ሦስት ኪሎ ሜትር ራቅ ብላ የምትገኝ ከኢያሪኮ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣም መዳረሻ ከሆነችው መንደር ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም እየተመለሰ ሳለ ቁ. 18 "ኢየሱስ በማግስቱ ማለዳ ወደ ከተማዪቱ በመመልስ ላይ ሳለ  ተራበ በመንገድ ዳርም አንድ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ ሲሄድ ከቅጠል በስተቀር ምንም አላላገኘባት 'ከእንግዲህ ፍሬ አይኑርብሽ' አላት የበለሷ ዛፍ ወዲያውኑ ደረቀች።" ይልና ኢየሱስ ነገሩ እዚህ ላይ ጉዳዩ ዘግቶ ሲያበቃ ይህን ያዩ ደቀ መዛሙርት ግን እንዲህ አሉ ይላል (ቁጥር 20 ማለት ነው) "ደቀ መዛሙርቱም የሆነውን አይተው በመደነቅ 'የበለሷ ዛፍ እንዴት በአንዴ ልትደርቅ ቻለች?” አሉ" ይላል።
ይህ የጌታ ደቀ መዛሙርት አነጋገር በቀላሉ እንዲገባን የደቀ መዛሙርቱ አባባል በእኛ አማርኛ ያስቀመጥነው እንደሆነ መምህራቸው የሆነ ኢየሱስ ያደረገውን አይተው አንዱ ሌላው (አጠገቡ ያለውን ደቀ መዝሙር) ስም እየጠራ "አንተዬ … ኧረግ ኧረግ ምን ይሉት ድንቃ ድንቅ ነው? ... የሆነው አይተሃል ወይ? ... እንደው እኮ ቃል ከአፉ ሲያወጣ ነው በለስዋ ክው ብላ የደረቀችው ... ድሜ የሰጠው ብዙ ያያል! ... ኧረ ጉድ ነው ... አቤት ብልሃት … እንዴት ያለ ጥበብ ነው! አጀብ ነው እንተዬ!..."  እየተባባሉ እርስ በርሳቸው በአግራሞት መነጋገራቸው ያስተዋለ ኢየሱስ ነገሩ ደቀ መዛምርቱ እንደሚያስቡት የብልሃት ጉዳይ ሳይሆን አስቀድሞ ስለ እምነት አስፈላጊነት በመቀጠል ደግሞ ስለ ጸሎት ሃይል  እንደሚከተለው ተናገረ (ቁጥር 21) "ኢየሱስም መልሶ እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል" ይልና አክሎም በቁጥር 22ላይ እንዲህ ይላል "አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው።" ይላል።       

ቀደም ብሎ በጽሑፉ ውስኑነት ገለጻ ላይ እንደተገለጸ ሌላው ለጊዜው ትተን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ "አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው" ብሎ ተናገግረበት በርካታ ምክንያቶች መካከል:
v ክርስትናና ጸሎት የማይነጣጠሉ የአንዲት ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ለመሆናቸው ለማስገንዘብ:
v ጸሎት በስሙ ለሚያምኑ ለቅዱሳን ሁሉ ክብራቸው እንደሆነ ለማስተማር። አንድ ሰው የሚፈልገውን ለመስራትና ለማድረግ የሚያችለው መሳሪያ ሳይዝ መሳሪያው የሚሰጠውን አገልግሎት ተጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ የጸሎት ሕይወት የሌለው ክርስቲያንም ሌላው ቢቀር አፉን መልቶ አማኝ ነኝ ማለትም አይችልም።
v ያለ ጸሎት የሚሰራ መንፈሳዊ ስራ እንደሌለ ለማሳየት:
v ጸሎት ማለት ከአእምሮ የሚያልፍ ድንቅን የሚያደርግ የተአምራት ባለቤት ከሆነው ከእግዚአብሔር የሚያገናኝ ብቸኛ መሳሪያ ለመሆኑ ይማሩ ዘንድ:
v የማይቻል ነገር ሁሉ በጸሎት እንደሚቻል እንዲማሩ:
v ጊዜው ሲደርስ በተኩላዎች መካከል መሰማራታቸው የማይቀርላቸው ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በበለስዋ በኩል በመጪው የአገልግሎት ዘመናቸው ለሚገጥማቸው እንቅፋትና መሰናክሎች በጸሎት ድል መንሳት እንደሚችሉ አስቀድሞ እያስተማራቸው ነው::
v ከምንም በላይ ደግሞ ጸሎት አለን በማለት ሊመኩበት የሚገባ (ለሰው አይደለም) ኃይላቸው መሆኑ እንዲያውቁ ይህን ተናገረ
በአጭሩ የሐዋሪያት ህይወትና አገልግሎት የሚያውቅ ሰው ሐዋሪያት በዘመናቸው እንዴት ያለ የእግዚአብሔር ሥራ ሰርተው እንዳለፉ የሚዘነጋው አይሆንም። አይደለም እጅ ጭነውበት ጥላቸው ያረበት ሰባራ ሲቃናና ሲዘል፣ ተነስና ተመላለስ ብለው የእነት ቃል ብቻ በመናገር የወደቀውን ሲነሳ፣ የልብሳቸው ቁራጭ ጨርቅ የዳሰሰ ለምፃም ከለምጹ ሲነጻና ሲፈወስ በአምላካውያን መጻሕፍት የሰፈረው ሐቅ የቅድሳት መጻህፍት ምስክርነት የታመነ ነው። ጥያቄው የኃይማኖት "መሪዎቻችን" እምነት ባይኖራቸው/ባያምኑና የጸሎት ህይወትም ባይኖራቸው ነው እንጂ "ሊቃነ ጳጳሳቶቻችን" ለሌላው መትረፍ ይቅርና እርስ በርሳቸው መስማማት እንዴት ያቅታቸዋል? በእውነት ወደ እግዚአብሔር ቢጸልዩ ነው ሰላም ማውረድ ያቃታቸው? ወይስ ሊቃነ ጳጳሳቱ የይስሙላ/"ፎርጅድ": ያይደሉ አስመሳዮች መሆናቸው ነው? ቢሆኑ ነው እንጂ ይዋሽ ዘንድ ሰው ያይደለ እግዚ አብሔር ከሰው ልጆች መረባበሽ ሰላም ማጣት ምን ያተርፋል ብለው ነው?   
ለማንኛውም እርቅ ከተፈለገ:
1ኛ. ዳኛ ይኑራችሁ። ከሆናችሁ ደግሞ እግዚአብሔር ዳኛችሁ ይሁን:: እንደ ልባችሁ መሆንና አፋችሁ እንዳመጣላችሁ ከመናገርም ተቆጠቡ። ስለ ክብራችሁ ከመሟገት ይልቅ ደግሞ ፈሪሐ እግዚአብሔር ይኑሩባችሁና እውነት እውነቱን ተነጋገሩ:: እውነቱን ደብቃችሁ ስታበቁ አይደለም አራት ጊዜ አርባ አራት ጊዜ ብትገናኙ ምን ዋጋ አለው? እውነት የመናገር አቅም ከሌለው ሰው ጋርስ ምን ይጠበቃል ብላችሁ ነው አስር ጊዜ የምታሰባሰቡ? ማናችሁም ብትሆኑ ስህተታችሁን/ጥፋታችሁን አምናችሁ ለመቀበል ራሳችሁ አዘጋጁ። ይህ የምለው ሰው ሲባል "በተፈጥሮው" ስህተቱን አሜን ብሎ የመቀበል ጸባይ ስለሌለው ነው። እናንተ ደግሞ "መንፈሳዊያን" ነን እስካላችሁ ድረስ እንዲህ ያለ የሥጋ ፍሬ ይታይባችሁ ዘንድ የተገባ አይደለም ለሰሚ ጆሮም ይሰቀጥጣል።
2.             “እናንተ ናችሁ ይህን ያደረጋችሁ … እናንተ ናችሁ በዚህ የወጣችሁ … እናንተ ናችሁ … ይህን የጣሳችሁ" የሚለውን ክስ አቁሙ። ካልሆነ ደግሞ "እናንተ እኮ ናችሁ … " ባላችሁ ቀጥር "እኛም …" የሚል ጨምሩበት። እንዲህ ሲሆን ወደ ስምምነት የመምጣታችሁ ዕድሉ የሰፋ ይሆናል ማለት ነው።
3.             ስሜታችሁን ተቆጣጠሩ:: የዕለት ዕለት አዳዲስ አጀንዳ ይዛችሁ እየመጣችሁ በስሜት እየተነዳችሁ እርስ በርሳችሁ ከምትበጣበጡ ይልቅ ጉዳያችሁ በምክንያት ማስረዳት የምትችሉበት አቅም ይኑራችሁ። የሰሜን ሰው ሲናገር "ሌባን ሌባ ሌባ ሲሉት ጎበዝ ጎበዝ ያሉት ይመስለዋል" እንዲል መገናኛ ብዙሐን ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ሲያራውጥዋችሁ እውነት ከእናንተ ዘንድ አለች ማለት አይደለም። ግልጽ በሆነ አማርኛ ስሜታችሁን ተቆጣጠሩ እያልኩ ነው።
4.             እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ። (ስለ ቅዳሴ አይደለም የማወራው) በጠረጴዛ ዙሪያ ላይ ስትቀመጡ ያለፈውን መዝገብ እየመዘዛችሁና እያገለባበጣችሁ በአሉታዊ መንፈስ አትቀመጡ። እዚህ ላይ አንዱ ሌላውን የሚከስበት መብትም ሆነ የሞራል ብቃት የለውም። ሁላችሁም በዘመናችሁ ቤተ ክርስቲያን በድላችሃል። ለምን የ20 ዓመቱ ብቻ ይነገራል? ከዚያ በፊት የነበረ የጨለማ ዘመንስ ቢሆን ምን መልካም ሥራ ተሰርተዋል ነውና? ሁላችሁም እልል ያላችሁ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች ናችሁ። ስለዚህ እርቅ ከፈለጋችሁ እንዲህ ዓይነቱን ዋጋ የማያወጣ ብልጣ ብልጥነት አስወግዱ።
5.                  ሌላው በስማ በለው በሚዘገቡ ዜናዎችና ወሬዎች ጆሮቻችሁ ሞልታችሁ ወደ ጉባኤ አትግቡ። ከምትሰሙት ነገር ራሳችሁን ቆጥቡ "ምንጮቻችን እንዳረጋገጡት … ውስጠ አዋቂዎች እንደሚጠቁሙት"  እየተባለ ከሚለፈፈው ወሬ ራሳችሁን ጠብቁ። በእነዚህ ቆርጠህ ቀጥል ዘገባዎች ተሞልታችሁ ወደ ጉባኤ ለመወያየት ላለመግባታችሁም ራሳችሁን መርምሩ።
6.            መረዳት ይኑራችሁ። የለም! በማለት ድርቅ የምትሉበት አጀንዳ ማንን ያማከለ ነው? ቤተ ክርስቲያን ወይስ ራሳችሁን? እንዲሁ አቅጣጫ ሳትለዩ ከነፈሰ ጋር መንፈስን አቁሙ። ስትናገሩ፣ ስትወያዩም ሆነ ስትሞግቱ ነገን እያሰባችሁ እንጅ መሬት መሬት እያያችሁ ለራሳችሁ ጠፍታችሁ ሌላውን አትጨምሩ። ከተራ ስሜትና  አስተሳሰብ ራሳችሁን አርቁ።
7.             ፖለቲካ? ማፈሪያዎች:: እንዳችሁም ስለ ፖለቲካ የማውራት አቅሙ የላችሁም:: ለነገሩ ችግሩ እናንተ ጋር ብቻም አይደለም ያለው እናንተን ጋብዘው የሚያስለፈልፍዋችሁ ሰዎች ከእናንተ የማይሻል በደመ ነፍስ እውቀት የተነከሩ ግለሰቦች ጭምር እንጅ::
ይቀጥላል
ሳምንት:
ከእሾህ በለስ አይለቅሙም፥ ከአጣጥ ቍጥቋጦም ወይን አይቈርጡም!
(እርማችሁን አውጡ! ክፍል 3)

ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው? (ማቴዎስ ወንጌል 7፣ 7- 12) እንዲህ ባለ ሁኔታ ሁለቱም እውነት ሊሆኑ አይችሉም። ወይ "ሊቃነ ጳጳሶታችን" አልያም ደግሞ ላይሰጥ ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ላይገኝ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ ላይከፍት መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል ያለ የቃሉ ባለቤት እግዚአብሔር ሐሰተኛ ነው። ማን ይሁን እውነተኛ? እግዚአብሔር ወይስ እነ አቡኑ? መልሱ በክፍል 3 ላይ ያገኙታል እርማችሁን አውጡ! ክፍል አንድ ለማንበብ ከስር ዝቅ ብለው የተቀመጡትን ድረ ገጾች “ሊንክ” ይጨቁኑ
http://ethiomedia.com/assert/ermachehun_awtu.pdf  እንዲሁም ከሌሎች ድረ ገጾች ያገኙታል።

ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
United States of America
January 11, 2013

4 comments:

  1. The devil tried to advise people on reconciliation. Please try to see yourself before criticizing others.

    ReplyDelete
    Replies
    1. you didn't not well said. Think many times before you send bad comment.

      Delete