Tuesday, January 15, 2013

መንግሥትና ቤተ ክህነቱ፣ የሁለቱ ሲኖዶሶች ሰላማዊ ድርድር፣ የአቡነ መርቆዮስ ጉዳይ፣ የፓትርያሪክ ምርጫና ውዝግቡስ ወዴየት እያመራ ይሆን!?

ክፍል ሁለት፣ ምንጭ - ሪፖርተር ጋዜጣ የእሁድ እትም
በፍቅር ለይኩን
befikir12@yahoo.com/fikirbefikir@gmail.com
ባለፈው አስራ አምስት ቀን ጽሑፌ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ አጠር ባለ መልኩ አጠቃላይ የሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱን የረጅም ዘመን ታሪክን ተንተርሼ አንድ መጣጥፍ ለማቅረብ ሞክሬ ነበር፡፡ አንዳንድ አንባቢዎቼ የጽሑፌን ጭብጥ ካለመረዳት ይሁን ወይም በሃይማኖት ካባ ሥር ተሸሽገው ፖለቲካዊ አጀንዳቸውን ለማራመድ ከሚፈልጉና አሊያም ስሜታዊነት ካየለበት የሃይማኖት አርበኝነት መንፈስ ተነሳስተው ነው መሰል ‹‹አንተ ከማን ወገን ነህ፣ ሚናህን ለይ…›› የሚል ሰም ለበስ ጥያቄያቸውን በማስቀደም ‹‹ለመሆኑ በአባቶችና በቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ ዙሪያ እንዲህ ዓይነቱን ጽሑፍ ለማቅረብ ማን መብት ሰጠህ?!›› ዓይነት አስተያየታቸውን ለግሰውኛል፡፡
ይህን ለማለት ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን የእነዚህን ወገኖቼን አስተያየት አከብራለሁ፡፡ በጨዋነትና በቅን መንፈስም ለእነዚህ ወገኖቼ አሳቤን ለማስረዳት ሁሌም ዝግጁ እንደሆንኩ ጭምርም ልገልፅላቸው እወዳለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ‹‹ይህን ልትናገር ይህን ልትፅፍ አይገባህም›› በማለት የመናገርና የመፃፍ መብቴን ለመገደብ ከሚሞክሩ አምባገነኖች ጋር ግን መቼም ቢሆን ድርድር አይኖረኝም፡፡
ስለዚህም አንድም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቴና እንዲሁም ደግሞ እንደ Professional Historian ቤተ ክርስቲያኒቱ ካለፈችባቸው የታሪክ ውጣ ውረዶች በመነሳት የቤተ ክርስቲያኒቱንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመሩ አባቶችን መንፈሳዊ ክብርና ልእልና በማይነካ መልኩ መፃፌን እቀጥላለሁ፡፡ እናም ቃል በገባሁት መሠረት ለዛሬ ከባለፈው የሚቀጥለውን ጽሑፌን በዚህ መልኩ አዘጋጅቼዋለሁ፡፡
ከፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እልፈት በኋላ የተፈጠረው ቤተ ክርስቲያኒቱን ማን ይምራት ጥያቄ፣ በአገር ውስጥና በውጭ ዓለም ባሉት ሲኖዶሶች መካል የተጀመረው ድርድርስ በምን መልኩ ይቀጥል፣ በግፍ ነው ከመንበሬ የተሰደድኩት የሚሉት የአቡነ መርቆርዮስ ጉዳይስ መቋጫው ምን ሊሆን ይችላል… እና ወዘተ በሚሉትና እነዚህ ተከትለው በተነሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያለው ሲኖዶስ ተከታይ የሆኑ ስብሰባዎችን ተካሂደዋል፡፡ ተደጋጋሚ የሆኑ መግለጫዎችም ወጥተዋል፣ በቅርቡም በአሜሪካ ዳላስ ለሰላምና ለአንድነት ሲባልም በሁለቱ ሲኖዶሶች ያሉ ተደራዳሪ አባቶች በጋራ ቀድሰዋል፣ በአንድነት ሆነው ማዕድም ቆርሰዋል፡፡
ይህን ያዩና የሰሙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናንም በዚህ አንድነትና ሰላም ተስፋ ጭላንጭል ውስጥ ሆነው በማኅበርና በየግላቸው ለፈጣሪያቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ይኸው የሰላምና የአንድነት መልካም ጅማሬ ፍጹም ሆኖ ይቀጥልም ዘንድ እግዚአብሔር አንድነትና ሰላምን ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲሰጥ ምህላ፣ ጸሎትና ሱባኤን አድርገዋል፣ አሁንም እያደረጉ ነው፡፡
ይሁን እንጂ አሁን አሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ሰላምና አንድነት ዙሪያ እየታዩና እየተሰሙ ያሉት ነገሮች የብዙዎችን ተስፋ እያደበዘዘ ያለ ነገር እየሆነ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደገመቱት የችግሩ ዋንኛ ምክንያትና ተጠያቂ ናቸው በሚል ከተፈረጁት ከአቡነ ጳውሎስ እልፈት በኋላም እንኳን አሁን ያሉ አባቶች ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ መረጋጋትና አንድነት ለማምጣት ዳገት እንደሆነባቸው እየታዘብን ነው፡፡ እንደውም በተቃራኒው የአቡነ ጳውሎስ እልፈት ለዘመናት ሲንከባለል የቆየውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ ቀውስና አስተዳደራዊ ችግር ከመቼውም በላይ ገሀድ አውጥቶታል ሲሉ አንዳንድ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡
ለቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት መከፈልና ለአስተዳደራዊ ቀውሱ ዋንኛ ምክንያት ናቸው የተባሉት አቡነ ጳውሎስ እረፍት በኋላ ግን የተናፈቀው ሰላም፣ እግዚኦ የተባለለት አንድነት በተቃራኒው ለያዥ ለገራዥ ባስቸገረ መልኩ ውሉ እንደ ጠፋ ልቃቂት እየተወሳሰበ መሄዱን በየቀኑ እያየንና እየሰማን ነው፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ለገባችበት አጣብቂኝና የነገ ዕጣ ፈንታዋ ዙሪያ ውዝግቡና ክርክሩ አሁንም የበረደ አይመስልም፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባዎች በፊትና በኋላ ከሚሰጡ ቅድመ ትንታኔዎችና ትችቶች ጀምሮ በየድረ ገጹ፣ በየብሎጉ፣ በጋዜጦችና በመጽሔቶች የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ የመነጋገሪያ ርዕስ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ሁሉ ጩኸትና እግዚኦታ መካከል ጎልቶ የሚሰማው ድምፅ ግን በቤተ ክርስቲያኒቱና በአባቶች መካከል ሰላምና አንድነት ይወርድ ዘንድ የሚናፍቅና አጥብቆ የሚሻ እንደሆነ ነው ያስተዋልኩት፣ በትክክልም የተረዳሁት፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለገባችበት ቀውስ ተጠያቂው ማን ነው? በሚል አንዱን አጽድቀው ሌላውን ኮንነው የሚራገሙና ጎራ ለይተው በቃላት ጦርነት የሚሞሻለቁም አልጠፉም፡፡ በዚህ መካከልም መንፈሳዊ ሽታና ለዛ የራቃቸው፣ ዘረኝነትና ወገኝነተኝነት የሚንጸባረቅባቸው መጣጥፎች፣ መግለጫዎችና አስተያየቶችም እየወጡ ነው፡፡
በዘመኑ የብሔር ፖለቲካ አቅላቸውን የሳቱ አንዳንዶች አሁን ደግሞ ተራው የእኛ ብሔር ነው በሚል ያዙን ልቀቁን የሚሉ ሰዎችም በአደባባይ ድምፃቸውን እየሰማን ነው፡፡ በእርግጥም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዙሪያ እየታየና እየተሰማ ያለው ነገር ልክ እንደ ካህኑ ዔሊ ዘመን ጆሮን ጭው የሚያደረግ አሰደንጋጭና አስጨናቂ እየሆነ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ጭራሽ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ መዓዛና ለዛ የሌላቸው፣ ደፋሮች፣ ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው የሆኑ መንፈሳዊ ካባን የደረቡ የዘመናችን ተኩላዎችም ዓይናቸውን በጨው አጥበው የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብትና ንብረት መዝረፉን አጥበቀው ተያይዘውታል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቤተ ክህነቱ ሠራተኛ እንደነገሩኝ፡-
ከመቼውም ጊዜ በላይ ሥርዓተ አልበኝነቱ፣ ዘርኝነቱ፣ እኔ ልሾም ባይነቱ፣ መሰሪነቱ፣ አንዱ አንዱን ጠልፎ ለመጣል የሚያደርገው ሸፈጥ፣ ሴረኝነቱ፣ ወገንተኝነቱ፣ የስም ማጥፋቱ ዘመቻ …ወዘተ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔርና መንፈሳዊነት ከቤተ ክህነቱ ጓዙን ጠቅሎ የተሰደደ ነው የሚመስለው ይላሉ እኚሁ አባት ሐዘንና ትካዜ በተጫነው ድምፅ፡፡
እንደ ቀደመው ዘመን ፍቅርንና ትህትናን እንደ ሸማ የለበሱ፣ በጸሎት የተጠመዱ፣ የሌተ ተቀን አሳባቸው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የሆነ፣ እንደ ንጉሥ ዳዊት ‹የቤትህ ቅንአት በላችኝ› የሚሉ፣ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ‹በእውነት ስለ እውነት ቆመው ከበዓል ነቢያት ጋር ፊት ለፊት የሚጋጠሙ መንፈሳዊ አርበኛ የሆኑ አባቶች› በዘመናችን አድራሻቸው የት እንደሆነ ግራ ተጋብተናል ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀውስ ዙሪያ አስተያየታቸውን የለገሱኝ እኚሁ አባት፡፡
ዛሬ ዛሬ የቤተ ክርስቲያኒቱን አባቶችና አገልጋዮች እንዲሁም በሚያስደንቅ ሁኔታ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ደግሞ ምእመናን ጭምር ወንድ ሴት ሳይሉ በአትኩሮት እየተከታተሉት ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች የዕለት ተዕለት የመነጋገሪያ አጀንዳ ወደ መሆን እየተሸጋገረ ነው፡፡ ዓላማው ምንም ይሁን ምን ይህ ዓይነቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ እኔም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቴ ያገባኛል በሚል መንፈስ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከአፈ-ነቢብ እስከ ምሁር ድረስ ድምፃችን መሰማቱ መልካም እንደሆነ አሳባለሁ፡፡
በአዎንታዊም ሆነ አሉታዊ በሆነ መንገድ በቤተ ክርስቲያኒቱ በዘመናት ጉዞዋ እየተንከባለሉ በመጡ ችግሮቿና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተንጸባረቁ ያሉ አሳቦች፣ አስተያየቶች፣ ትችቶችና ውይይቶች እስከነ ብርታታቸውም ሆነ ድካማቸው ይበል የሚያሰኙ እንደሆነ በግሌ አጥብቄ አምናለሁ፡፡
ኑሮአቸውን በአሜሪካ ያደረጉት እውቁ የታሪክ ምሁርና Church and State በሚለው ዘመን አይሽሬ (Classic) የምርምር ሥራቸው የቤተ ክርስቲያኒቱንና የቤተ ክህነቱን ለሺህ ዘመናት የዘለቀ ግንኙነትና ትስስር በሚገባ የተነተኑ፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጥንታዊ ገዳማትና ድርሰቶች ዙሪያ ሰፊ ምርምርና ጥናት በማድረግ የሚታወቁት ፕ/ር ታደሰ ታምራት፣ የዛሬው ትውልድ በቤተ ክርስቲያኑ የውስጥና የውጭ ጉዳዮች ላይ እያሳየ ያለውን ተሳትፎ፣ ቁጭትና እኔም ያገባኛል መንፈስ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን በአንድ ወቅት ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዲህ ገልጸውት ነበር፡-
በአሁኑ ዘመን በምእመኑና በወጣቱ በኩል ያለው የቤ/ን ፍቅርና ከበሬታ እጅግ በጣም ተለየና በጣሙን የሚያስደንቅ ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ወጣቱም ሆነ ጎልማሳው ለቤተ ክርስቲያኗ ያለው የባለቤትነት ስሜት በጣም እጠነከረ መምጣቱም ግልፅ ነው፡፡ ፕ/ር ታደሰ እንደሚገልጹት ምእመኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ቤ/ን እየጎረፈ ነው፡፡
እንደዚህ ልቡን በሙሉ ከፍቶ ቤተ ክርስቲያኒቱን የመቅረቡን ያህል የኅሊናውን ጭንቀት፣ ሥጋዊና መንፈሳዊ ችግሮቹን ተረድቶ የሚያረጋጋው ጠንካራና ያልተከፋፈለ መንፈሳዊ መሪ ግን የታደለ አይመስልም፤ ሕዝቡ በአስተሳሰቡም ሆነ በአኗኗሩ መልካም አርአያ የሚሆነው አባትን ይሻል፡፡
በእርግጥም ፕ/ር ታደሰ እንዳሉት እኔም እንደምስማማበት በምእመኑ ዘንድ ብዙ ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቤተ ክርስቲያን በኩል ግን ለዚህ ሰፊ ሕዝባዊ አመኔታ የሚያረካ ወይም መልስ የሚሆን፣ ለወጣቱ ከዛሬ አርባ ዓመት በተሻለ የተሟላ መንፈሳዊ እርካታ ሊሰጥ የሚችል መንፈሳዊና በሳል አመራር ድል ነስቶ ለመውጣት የቻለ አይመስልም፡፡ እናም በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ጉስቁልና እና አስተዳደራዊ ቀውስ ላይ ያሉ ሮሮዎችና ጩኸቶች ዛሬም ተበራክተው ቀጥለዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉም፡- ‹‹ይህን ያህል የምእመናን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለበት፣ የሃይማኖት መሪዎች አመኔታ ያጡበት፣ መሠረታዊ እምነትን ሚያናጋ፣ ሕዝቡን ከቤ/ን የበለጠ ሊያርቅ የሚችል መንፈሳዊ ዝቅጠት፣ የሞራል ውድቀትና እንዲህ ያለ ውዝግብ በቤተ ክርስቲያኒቱ የረጅም ዘመን ታሪክ እንዲህ እንደ አሁኑ ቅጣ ባጣ መልኩ ስለመከሰቱ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡›› ሲሉ በአሁኑ ወቅት ቤ/ቱ የገባችበትን መንፈሳዊ ክስረትና ውድቀት ይገልፃሉ ፕ/ር ታደሰ በቃለ ምልልሳቸው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአመራር አካላትና በራሱ በተቋሙ ውስጥ የተፈጠረውን ውዝግብና ውስጣዊ አለመስማማት በረጋ መንፈስ እንደ ጥንቱ የሐዋርያትና የቅዱሳን አበው ዘመን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሪ በሆነበት ውይይትና ክርክር በቅንነት ተነጋግሮ ‹‹እኛና መንፈስ ቅዱስ እንዲህና እንዲያ ወስነናል›› የሚል ድምፅ መስማት ከናፈቀን በርካታ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ አባቶቻችን እርስ በርሳቸው የሚነጋገሩበት ቋንቋ የሃይማኖት ሳይሆን የሥልጣን፣ የኃይል፣ የእልህ እንዲያው በአጠቃላይ ፍጹም ዓለማዊ ቋንቋ እየሆነ መጥቷል፡፡
በዚህ ሁሉ ውዝግብ፣ መንፈሳዊ ክስረትና አስተዳደራዊ ቀውስ ያለችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሁን ደግሞ እጅግ ወሳኝ በሆነ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ከሁለት አስረተ ዓመታት በፊት ለሁለት የተከፈለቸው ቤተ ክርስቲያን ዳግም አንድነቷን ለማደስና በመካከሏ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ እየጣረች ብትሆንም፤ ይህ ጥረት ግን እምብዛም ሥር ያለውና ፍሬ የሚያፈራ እንዳልሆነ በግልፅ እየታየ ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ቀኖና መፍረስ ጉዳይና በዚህም የተነሣ የአቡነ መርቆርዮስ ከመንበራቸው በግፍ መሰደድ ጉዳይ በሁለቱ ሲኖዶሶች በሚገኙት አባቶች መካከል ለሰላማዊ ድርድሩ መቀጠል እንቅፋት ሆኖ መውጣቱ  በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ከሰሞኑ በሰላሙ ድርድር ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የውጩ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ መልከ ጸዴቅ፡-
ከኢትዮጵያው ሲኖዶስ በኩል ‹‹አቡነ መርቆርዮስ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው መምጣት ይችላሉ፤ ነገር ግን ፓትርያርክ መሆን አይችሉም፡፡›› በሚል የወጣው መግለጫ በጭራሽ በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ነው ከረር ባለ ቃል የገለጹት፡፡ እንደውም አሉ አቡነ መልከ ጸዴቅ፡-
አቡነ መርቆርዮስ ወደ አገራቸው የመግባት ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው መብታቸው እንጂ ሲኖዶሱ የሚያጸድቅላቸው ጉዳይ አይደለም ሲሉ ሲኖዶሱ መንፈሳዊ ሥልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ምን መሆኑን የዘነጋና ማንኛውም ሰው በአገሩ የመኖር መብት እንዳለው እንኳን ያለየ በሚል ስሜት የሰላ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ለሃያ ዓመታት ያህል በፕትርክና መንበር ላይ የተቀመጡት አቡነ ጳውሎስ ሕጋዊ አይደሉም የሚሉት አቡነ መልከ ጸዴቅ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የተላለፈው ውግዘት ገና የተነሳ አለመሆኑን መግለፃቸውም ለእኔና ለእንደኔ ዕይነቶቹ ሌላኛው አስደንጋጭ ዜናና ሰላማዊ ድርድሩም ገና በጽንስና በጭንገፋ መካከል ላይ የሚዋልል መሆኑን ያሳየ ሆኖ ነው የተሰማኝ ያደረገ ነው፡፡
ለመሆኑስ የሆነስ ሆነና ‹‹ውጉዝ ከመ አርዮስ›› ተባብለው የተወጋገዙ እነዚህ የሃይማኖት አባቶች የተወጋገዙበት የውግዘት ቃል ሳይነሳ፣ ልዩነቶቻቸውንና የጠባቸውንም ምክንያት በረጋ መንፈስ ተወያይተው ሳይተማመኑና ሳይፈቱ፣ በመካከላቸውም እርቅና ሰላም ሳይወርድ፣ አብረው የቀደሱበትና ማዕድ የቆረሱበት ሁኔታ በግሌ በእጅጉን አስገርሞኛል፡፡
መጽሐፍ እንደሚነግረን እነኚሁ መንፈሳዊ አባቶቻችንም ደጋግመው እንዳስተማሩን ‹‹በመጀመሪያ መባህን በመሰዊያው ላይ ትተህ አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ ነው››፡፡ ታዲያ አሁንም ድረስ በመለያየት መንፈስ ውስጥ ያሉ አባቶቻችን በምን ሂሳብ አብረው እንደቀደሱና ማዕድ እንደቆረሱ ምንም ግልፅ አይደለም፡፡ እነርሱም እስካሁን የነገሩን ነገር የለም፡፡
የእስካሁኑ በሁለቱ ሲኖዶሶች ባሉ አባቶች መካከል በነበረው ውይይት ‹‹የስማ በለው›› መሆኑንና በተጨማሪም በአገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም ያሉ የየሲኖዶሶቹ አባቶች በእንደዚህ ዓይነቶቹ ወሳኝ አጀንዳዎች ላይ ቢያንስ ቅድመ ስምምነት ላይ ለመድረስ አለመቻላቸው ሰላማዊ ድርድሩ ቀድሞውኑ የይስሙላና ይኸው እንዲህ ሞክረን ነበር ነገር ግን በሚል አንዱ አንዱን ለማሳጣት የሚደረግ ከንቱ ሩጫና ልፋት እንደሆነ ፍንጭ የሚሰጥ ነው ሲሉ በርካታ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
የአቡነ መልከ ጼዴቅም ከኢሳት የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅም ይኸንኑ እውነታ የሚያስረግጥ ነው፡፡ ብፁዕነታቸው ሲገልፁም፡- ‹‹ሰላማዊ ድርድሩ ምንም ዓይነት የመቀራረብ ሁኔታ ያልታየበት እንዲሁ የይስሙላና ብዙም ተስፋ የሌለው በማለት ነው፡፡›› በአጭር ቃል የገለጹት፡፡
በቅርቡም ዶ/ር ተክሉ አባተ የተባሉ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ምሁር Ethiopian Orthodox Tewahdo Church at a Crossroads በሚል ርዕስ በተለያዩ ድረ ገጾች ባስነበቡት ጽሑፋቸውም፡-
The two synods come up with preconditions for negotiation and reconciliation, some of which are irrelevant to the noble cause- unity. Mainly because of the extremely rigid and egoistic nature of the preconditions put forward, previous reconciliation efforts ended in fiasco. በማለት በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የቀጠለው ድርድር ቁልፍ ባልሆኑ ተራ ምክንያቶች የተነሳ ገና ከጠዋቱ እንቅፋት እንደገጠመው ገልጸውታል፡፡
የሆኖ ሆኖ አሁን እንደሚታየውና እንደሚሰማው ሰላማዊ ድርድሩ ተስፋ ያለው አይመስልም፡፡ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱ የመንፈስ አንድነትና ሰላሙ›› ይቅደም የሚለው ድምፅም ብዙም ሰሚ ያገኘ አይመስልም፡፡ በተጨማሪም ደግሞ ብዙ የተባለለትን ሰላማዊ ድርድር በይበልጥ የሚያወሳስበው ደግሞ የአሜሪካው ሲኖዶስና በዛ ያሉ አባቶች ኢህአዴግን ከሚቃወሙ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ጋር በተደጋጋሚ አጋርነታቸውን የገለጹና እየገለጹ ያሉ የመሆናቸው እውነታ ነው፡፡
ይህ የእነዚሁ በውጭ አገር በስደት የሚገኙ አባቶች ተቃውሞ መነሻ ደግሞ በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ግልፅ የሆነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሆነ ብዙ የተባለለት ነገር ነው፡፡
መንግሥት ቀድሞውኑ በፓትርያክ መርቆርዮስ ጉዳይም ሆነ አሁን ባለው በወቅታዊው የቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ያራሱን ፍላጎት ላማስፈፀም ትናንት በቀደደው በር ዛሬም ገብቶ ያሻውን ለማድረግ የሚያግደው ኃይል እንደሌለ የሚያሳዩ በርካታ መሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል የሚሉት እነዚሁ ታዛቢዎች፤ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በቅርቡ ለአቡነ መርቆርዮስ የላኩት ደብዳቤ ከመንግስት በኩል ሳይውል ሳያድር የገጠመው ብርቱ ተቃውሞ በቂ ማሳያ እንደሆነ በተጨባጭ በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡
ይህም ክርክር በድምዳሜው ምንም እንኳን ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አልገባም፣ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሀገር ሰላምና ልማት ካላት አዎንታዊ ተጽእኖና ጉልህ ተሳትፎ የተነሳ ከመንግስት አሰፈላጊው የሆነ፣ አድልዎ የሌለበት እገዛና ድጋፍ እናደርጋለን›› ቢልም፤ ብዙዎች እንደሚተቹት በዚህ ሰበብ መንግሥት እንደትላትናው ሁሉ ዛሬም በብልጣ ብልጥና መሰሪ አካሄዱ በቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ጉዳይና ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ በመግባት እርሱ የወደደውንና የፈቀደውን ሰው ለመሾም በማንአለብኝነት መንገዱን አገባዷል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በዚህ መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ህጋዊ ፓትርያርክ የሆኑትን አቡነ መርቆርዮስን እስከማውረድ ድረስ የተጓዘበትን ድፍረቱንና አጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የሚያራምደውን ፖለቲካዊ አቋሙንና ውሳኔዎቹን እንዲሁም የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቹን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በመተቸት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአሜሪካና በምዕራቡ ዓለም የኢህአዴግን መንግሥት በመቃወም በሚካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በተደጋጋሚ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ሲያሰሙ የነበሩና አሁንም እያሰሙ ያሉትን እነዚህን አባቶች መንግሥት በበጎ ዓይኑ ያያቸዋል ብሎ ማሰብ ትልቅ የዋኽነት ነው የሚሆነው፡፡
በአንፃሩም በሃይማኖታችን ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት አድርጎ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለሁለት እንድትከፈል ምክንያት ሆኗል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕጋዊ ፓትርያርክ በማጋዝ የቤተ ክርስቲያናችንን ክብርና ህልውና ተዳፍሯል፣ በሀገሪቱ የጎሳ ፖለቲካና ዘረኝነትን በመዝራት ሕዝቡን ከፋፍሏል…ወዘተ በማለት በኢህአዴግ መንግሥት ላይ የተቀየሙና መሠረታዊ የሆነ ተቃውሞ ያላቸው የእነዚህ አባቶች ፖለቲካዊ አቋምም ድርድሩን በይበልጥ የተወሳሰበ እንደሚያደረገው ግልፅ ነው፡፡
በቅርቡ እንኳን በአሜሪካው ሲኖዶስ ያሉ አንድ አባት የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ሽብረተኛ›› በሚል ከሰየመው ቡድን የጦር አባላት ጋር በአንድነት የተነሱትን ፎቶ በኢህአዴግ መንግሥት በኩል ሊፈጥር የሚችለው አንድምታ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ልብ ይሏል፡፡
የቤተ ክህነቱ ተቋምና መሪዎቹ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ከእውነትና ከፍትህ ጋር ከመቆም ይልቅ በየጊዜው አቋማቸውን ከሚለዋውጡ ፖለቲከኞች ጋር መወገናቸው ሌላው እንቆቅልሽና የአገሪቱም ሆነ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሌላ ተጨማሪ ፈተና ሆኖ መውጣቱ ግልፅ ነው፡፡
ልክ እንደ ቅዱስ አትናቴዎስ If the World stand aginst the Truth Atnatewos stands against the World በሚል መንፈሳዊ ድፈረት ለፍትህ እና ለእውነት የሚቆሙ ጽኑ አባቶች በዘመናችን መጥፋታቸው ቤተ ክህነቱና ቤተ መንግሥቱ እርስ በርሳቸው ሊኖራቸው የሚገባውን ኃላፊነትና ድርሻ የተደበላለቀ አድርጎታል፡፡ ከዚህም የተነሣ የቤተ ክህነቱ ተቋሙና ተቋሙን የሚመሩት አባቶች መንፈሳዊ ልእልናቸውን፣ ክብራቸውንና ሥልጣናቸውን በሚገባ መጠቀም ያልቻሉና ለሚሰሩት ቀርቶ ለሚያስቡት እንኳን በተቃራኒው የመንግሥት ቡራኬና ፈቃድ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ብዙዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ ምሁራንና ታዛቢዎች እንደሚናገሩትም፡-

በይበልጥም ቤተ ክርስቲያኒቱን የመንግሥት ጥገኛ የሚያደርጓት የቤተ ክህነቱ መሪዎች ራሳቸው ናቸው ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚተቹት ጳጳሳቱ በራሳቸው አይተማመኑም፡፡ እግዚአብሔርን ሳይሆን የሚፈሩት ባለሥልጣናቱን ነው፡፡

ሥልጣንን እንደ ምድራዊ መሳሪያ እንጂ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደሚያገለግሉበት ኃይል አይቆጥሩትም፡፡ ስለዚህ በእነሱ መንፈሳዊ የመሆን ጉድለት የተነሳ እንደ ጎርፍ ከሚያልፉ መሪዎች ጋር ዘላለማዊቷን የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ለጥፈዋት ለችግር ሲያጋፍጧት ኖረዋል፡፡ ከዚህ የተነሳ መጪውንም ዘመን ፍቺ የሌለው አድርገን እንድንመለከተው አወሳስበውብናል ሲሉ አምርረው ይተቻሉ፡፡

ቤተ ክህነቱ ራሱን ከመንግሥት ጥገኝነት አላቆ ወደ ቀደመ መንፈሳዊ ክብሩ፣ ልእልናውና ሥልጣኑ የሚመለስበትን ፍፁም መንፈሳዊና ቅን ወደሆነው የእውነት መንገድ ለመመለስ ካልወደደ የምንናፍቀው ሰላምና አንድነት ሩቅ ሊሆንብን ይችላል፡፡

ሰላም… ሰላም… አንድነት… አንድነት… በሚል አስቀድሞ ለሰላማዊ ድርድሩ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ሰላም ጉዳይ ቅድሚያ ይሰጥ፣ ለፓትርያርክ ምርጫው ይደርስበታል የሚሉ ድምፆች ጎልተው በወጡበት በዚህ ወቅት የሰላሙና የአንድነቱ ጉዳይ ብዙም ተስፋ ሰጪ አይመስልም፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት ደጋግመን መናገራችንን፣ ደጋግመን መፃፋችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምም መዘመራችንን መቼም ቢሆን አናቋረጥም፡፡

v ርሱ በክቡር ደሙ ፈሳሽነት ንጽሕት፣ ቅድስትና ያለ ነቀፋ ለሆነችው ለቤተ ክርስቲያን ልጆች እንሆን ዘንድ ያበቃን፡- እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ወልደ ዋህድ፣ የማርያም ልጅ ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ ሰላም አለቃ፣ የፍቅር አምላክ ነውና!!!
v ቢሆን ቢሆን አባቶቻችን በመጀመሪያ እርስ በርሳቸው ያላቸውን ልዩነት በፍቅር፣ በትህትና እና በቅንነት መንፈስ በመነጋገር ፈትተው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የመንፈስ አንድነትንና ሰላምን በማስፈን የሰላም ሐዋርያ መሆናቸውን ቢያሳዩን እንዴት በወደድን፡፡
v ከዛም አልፈው አባቶቻችን መንግሥታትን በቅን መንገድ በመምራት፣ ክፉዎችንና ኃያላኑን በመገሰጽ፣ ለፍትህና ለነፃነት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ፣ ከድሆችና ከተገፉ፣ ከፈጣሪ የተሰጣቸውን መብታቸውን ከተገፉፉና ከታፈኑ የምድራችን ምንዱባን ጋር በመቆም የእውነት ጠበቃ መሆናቸውን ቢያሳዩን እንዴት በተደመምንና ደስ ባለን፡፡
v ምናለስ በሁለቱም ሲኖዶሶች ያሉ አባቶች ድህነት ዕጣ ፈንታዋና መለያዋ ለሆነባት ኢትዮጵያችን፣ ራብና ጠኔ ሕዝቦቿን ለሚያጭድባት ምድራችን፣ ለተሻለ ሕይወት በሚል እንደ ጨው ዘር በዓለም ሁሉ ተበትነው ውረደትን ለተከናነቡ የአብራኳ ክፋዮች
v የጥላቻና የጽንፈኝነት አባዜ ቁም ስቃዩን ለሚያሳየው የአገራችን የፖለቲካ ሰማይ እንደ ማንዴላ፣ እንደ ማርቲን ሉተር፣ እንደ ጋንዲ የወንድማማች ፍቅርን፣ እርቅንና ሰላምን ደግመው ደጋግመው ቢሰብኩልን በወደድን፡፡

እንዴት ክፉዎችን፣ አመጸኞችን፣ የምድራችንን ኃያላኖችንና አምባገነኖችን ኃይልና ብርታት ባለው በመንፈሳዊ ቃል ያወግዙልናል፣ ያሳፍሩልናል የምንላቸው አባቶቻችን፣ መጽሐፍ እንደሚልም፡- ‹‹በአሕዛብ ላይ በቀልን፣ በሰዎችም መካከል ቅጣትን ያደርጉ ዘንድ፣ ንጉሦቻቸውን/መንግስታትን በሰንሰለት፣ አለቆቻቸውንም በእግር ብረት ያስሩና የተፃፈባቸውን ፍርድ ሁሉ ያደርጉባቸው ዘንድ›› የሚል መንፈሳዊ ሥልጣንና ክብር በምድርና በሰማይ የተሰጣቸው አባቶቻችን እንዲህ እንደ አሁኑ ዘመን ስለ ፍትህ መጮኽ፣ ስለ እውነት ጠበቃ ሆነው መቆም ሲያቅታቸው ምን ለማለት ይቻለን ይሆን?!
በመጨረሻም ወደ ዛሬው ጽሑፌ ማጠቃለያ ርዕሰ ጉዳይ ስመለስም በአቡነ መርቆርዮስና በፓትርያርክ ምርጫ ጥድፊያ ዙሪያ እየተነሱ ባሉ አሳቦችና አስተያየቶች ላይ ጥቂት ነገሮችን በማለት አሳቤን ላጠናቅቅ፡፡
በመንግሥት ቀጥተኛ በሆነ ጣልቃ ገብነት በግፍ የተሰደዱት አቡነ መርቆርዮስ መመለስ አለባቸው እስከሚሉና አይ እሳቸውማ መንጋውን በትነው የቤተ ክርስቲያኒቱን መከራና ሰቆቃ እዚሁ ከመንፈሳዊ ልጆቻቸው ጋር ሆነው መሸከም ተስኗቸው ከእናት ምድራቸው ገዳማት ይልቅ አሜሪካን መርጠው ጥለውን ሄደው የለ ታዲያ ምን ሲሉ በተኗቸው ወደሄዱት መንጋዎች ተመልሰው ለመምጣት ይችላሉ እስከሚሉት ድረስ በአቡነ መርቆርዮስ ዙሪያ የተለያዩ እሳቤዎች አሁንም ድረስ እየተንሸራሸሩ ነው፡፡
በአንፃሩ ደግሞ ‹‹አቡነ መርቆርዮስ ወደ አገራቸው መምጣት ይችላሉ፤ ፓትርያሪክ ለመሆን ግን አይችሉም፡፡›› በሚል በቅርቡ ከኢትዮጵያው ሲኖዶስ የወጣው መግለጫ ቢያንስ ለጊዜውም ቢሆን በእርሳቸው ዳግም ወደ ፓትርያርክነት መመለስ ጉዳይ ላይ ያለው አቋም አሉታዊ መሆኑን ግልፅ አድረጓል፡፡
ደግነቱ በዚህ ሁሉ ጩኸትና ውዝግብ ውስጥ እንደ መርግ በሆነ ዝምታ ውስጥ ያሉት እኚሁ አባት ድምፃቸው አለመሰማቱና ምን እያሰቡ እንዳለም አለመታወቁ አንዳንዶቹ ሁሉንም ነገር ትተው በፍፁም አርምሞ ውስጥ ናቸው ያሉት ወደሚል ድምዳሜ እንዲደርሱ እያደረጋቸው ነው፡፡
በበኩሌ በመሠረቱ አቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው ይመለሱ ወይስ አይመለሱ፣ ከተመለሱስ ሥልጣናቸውና ኃላፊነታቸው ምን ድረስ ሊሆን ይገባዋል፣ አሊያም ደግሞ አምስተኛ ፓትርያርክ ብለን እንደገና ወደኋላ ተመልሰን አራት አንልም ስድስተኛ እንጂ የሚል ምንም መንፈሳዊ አመክንዮትና ሽታ የሌለበት ቅድመ ሁኔታዎችና ሙግቶች መቼም ቢሆን የሰላሙንና የአንድነቱን መንፈስ ጎዳና ሊያጨልሙት አይገባቸውም ባይ ነኝ፡፡
እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሁኔታዎች አባቶችን ሊነጋግሩባቸው የሚገባ ከሆነም በሁለተኝነት መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው የሚመስለኝ፡፡ ከሁሉ አስቀድመን መነጋገር፣ መወያየት ካለብን ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት ጉዳይ ነው መሆን ያለበት ነው የሚመስለኝ፡፡
መሠረታዊውና አንገብጋቢ የሆነውም ጥያቄ ይኸው ነው፡፡ አንድነትና ሰላም ይሻለናል ወይስ እንደ ትናንቱ በመለያየትና በመወጋገዝ የጀመርነውን ጉዞ መቀጠል፡፡ እኛ ግን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ፍፁም የሆነው የፍቅሩ፣ የሰላሙና የአንድነቱ መንገድ ሁሌም ቢሆን መልካም መሆኑን በቃል ከመናገር በተግባርም ከማሳየት እንዳንዘነጋና እንዳንደናቀፍ የአባቶቻችንን አምላክ እንማጸናለን፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ፊት የቀረበው ይህ አማራጭም አባቶቻችንን በእግዚአብሔር፣ በታሪክና በትውልድ ፊት ወይ የሚያስመሰግናቸው አሊያም ደግሞ ሲያስወቅሳቸው የሚሆን ውሳኔ ሊሆን ይችላል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች የሆኑ አባቶቻችን የፍቅርን፣ የእርቅን፣ የሰላምንና የአንድነትን መንገድ ይመርጡ ዘንድ ከአርያም የሆነ መንፈሳዊ ወኔና ቆራጥነት ከአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ዘንድ እንዲሆንላቸው ከልብ በመመኘት ልሰናበት፡፡
ሰላም! ሻሎም!

2 comments:

  1. thanks a lot aba selama keep it up!ሰላም ፍቅር i also share ur idea too

    ReplyDelete
  2. “……..ቤተ ክህነቱ ራሱን ከመንግሥት ጥገኝነት አላቆ ወደ ቀደመ መንፈሳዊ ክብሩ፣ ልእልናውና ሥልጣኑ የሚመለስበትን………..” ቤተ ክህነቱ ባለው የአጭር ጊዜ ታሪክ ከመንግስት ጥገኝነት ተላቆ አያውቅም፤ የቤተ ክህነቱን የ 50 ዓመት ታሪክ ወደ ኃላ ለማየት ሞክሩ፡፡

    አባ ሰላማዎች በተረፈ በጣም ጥሩ የሆነ ጽሁፍ ነው በርቱ
    እናመሰግናለን

    ReplyDelete