Friday, January 25, 2013

ጥንቆላ - በሀገራችን ፣ በቤተ ክርስቲያናቸን እንዲሁም በእያንዳንዳችን ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ

ራሳችንን ከጥንቆላ ስራዎች ለመጠበቅ ወይንም ሳናውቅ የጥንቆላ ስራዎች ተባባሪ ከመሆን ለመዳን ስለ ሀገራችን የጥንቆላ ዘዴዎች መጠነኛ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል። ጠንቋይ ማለት ጠንቅ ዋይ ወይም ጠንቀኛ ማለት ነው። በሀገራችን ሁለት ዓይነት የጠንቋይ አይነቶች አሉ። አንደኛው ወገን ባለ ዛር፣ ባለ አውሌ (ውቃቤ) የሆኑትን ሲያካትት ሁለተኛው ወገን ደግሞ ደብተራ የሚባሉትን ያካትታል።  
ባለ ዛር ወይንም ባለ ውቃቤዎች
አውሌ ወይም ዛር የሚባሉት በሰው ላይ ሰፍረው አምልኮን ለራሳቸው የሚወስዱ የአጋንንት ወገን ናቸው። ባለ አውሌዎች በመላው ኢትዮጵያ ይገኛሉ። በኦሮሞው፣ በአማራው፣ በጉራጌው ወዘተ በየትኛውም ብሔር ብሔረ ሰብእ ዘንድ በብዛት አሉ። ብዙዎቹ ሃይማኖታቸው እስልምና ወይም ኦርቶዶክስ ክርስቲያን እንደሆኑ ይናገራሉ።  ብዙውን ጊዜ አማኞች ለመምሰል የአላህን ወይም የእግዚአብሔርን ስም ያነሳሉ። እንዲህ የሚያደርጉት ብዙዎች ደንበኞቻቸው ከእስልምና ወይም ከክርስትና የመጡ ስለሆኑ ይመስላል። ኢየሱስ የሚለውን ስም ግን ተሳስተውም እንኳ አይጠሩትም።

«እስላም» ነኝ የሚለው ባለውቃቤም ሆነ «ክርስቲያን» ነኝ የሚለው ባለ ውቃቤ ገብርኤልን ሚካኤልን እና አቡየ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ይወዳሉ። በየዓመቱ ዝክራቸውን ይዘክራሉ ቤተ ክርስቲያናቸውን ይሠራሉ በየቤታቸውም ስእሎቻቸውን አንጠልጥለው እጣን ያሳጥናሉ፤ በበአላቸው ቀን ጃንጥላ፤ በሬና ጊደር የመሳሰሉ ስእቶችን ያደርጋሉ። ይህን የሚያደርጉት ክርስቲያን ባለውቃቤዎች ብቻ አይደሉም፤ እስላሞችም ጭምር ናቸው እንጂ። እኛ ካህናቱም ይህን እያወቅን መባቸውን (ስዕለታቸውን) እልል ብለን እንቀበላቸዋለን። በቁልቢ ገብርኤል ከሚገኘው መባእ ውስጥ አብዛኛውን የሚሰጡት የእስላምናና ክርስቲያን ባለውቃቤዎች ናቸው። በቁልቢ ገብርኤል ከመተካቱ በፊት ባለ አውሌ ያሟርትበት የነበረ ሥፍራ ነበር ሲባል ሰምቻለሁ። ዛሬም በስፍራው ባለውቃቤዎች አይታጡም። ባለ ውቃቤዎች በሚካኤልና በገብርኤል ቀን ደመቅ ያለ ዘፈን አላቸው ዝክርም ይዘክራሉ። ጽድቅን ለማግኘት ይሆን? የነሱ ደግሞ እስከ ስንት ትውልድ ይማር ይሆን? ለምሳሌ ምእራብ ሽዋ ውስጥ የሚገኘው የሙገሩ ታዋቂ ጠንቋይ የሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ ህዳር ሚካኤልን ሞቅ ባለ ድግስ ይዘክራል። በዚያ ቀን ከአዲስ አበባ ወደ ባለ ውቃቤው የሚጓዘው ሕዝብ እጅግ ብዙ ነው። በጎጃም አዲስ ቅዳም ውስጥ የሚገኘው ታዋቂ ጠንቋይ የገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን አሠርቷል። በወሎ ያለው ታዋቂ ባለዛር ግን መስጊድ አሰርቷል። ታዋቂ ጠንቋዮችን ለምሳሌ ያህል ጠቀስሁ እንጂ ሁሉም ባለውቃቤ የራሱ የሆነ ታቦት አለው። ነገር ግን በሚካኤልና በገብርኤል ስም የሚነግደው ያ ጥንተ ጠላታችን ሰይጣን እንደሆነ ጥርጥር የለውም።
 ዛሩ በነርሱ ላይ የሚወርደው በልዩ ልዩ አምልኮ ሲለማመጡት ነው። ቡና ይፈላለታል ዶሮ ወይም በግ ይታረድለታል፤ ስግደት ይቀርብለታል፤ ዘፈን ይዘፈንለታል፤ አታሞና ከበሮ ይመታለታል። በዚህ ጊዜ ባለውቃቤው ከመጋረጃ ውስጥ ሆኖ ያጓራል። በዚህ ጊዜ መንፈሱ ወረደ ይባልና እልልታ ይደረጋል። እርሱም የሚረግመውን ይረግማል የሚመርቀውን ይመርቃል። ከዚያም ለማስጠንቆል የመጡ ደንበኞቹ ሁሉ በተራ እየሰገዱ እጣ ፈንታቸውን ይጠይቃሉ የተጣሉትን ያስረግማሉ። እባክህ አትርሳኝ እያሉ ይማጸናሉ። በማግስቱ ደግሞ በማርያም ስእል ፊት ወድቀው እባክሽ አማልጅኝ እያሉ ይጸልያሉ። ወይ ያላረፈች ነፍስ!
 ደብተራ
ደብተራ ማለት ድንኳን ማለት ነው። ደብተራ የሚለው ስያሜ ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የተሰጠው በዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ነው ይባላል። በድንኳን ውስጥ በጽሑፍና በድርሰት በማህሌት የሚያገልግሉ የዘርዓ ያዕቆብ ሰራተኞች ካህናተ ደብተራ ይባሉ ነበር። በድንኳን ውስጥ ስለሚኖሩ ስማቸው ደብተራ ተብሎ ይጠራ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በማህሌት ክፍለ አገልግሎት የሚመሰማሩ አገልጋዮች ደብተራ ይባላሉ። ሚስታቸው የሞተችባቸው ቄሶች ወደ መቅደስ ገብተው መቀደስ አይችሉም፤ ቅኔ ማህሌት ገብተው ግን ማገልገል ይችላሉ። በዚህ ምክንያት ደብተራ ይባላሉ።
 የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የጸነነባቸው ማለት ቅኔው ያልገባቸው፤ ዜማው ያልተቃኘላቸው ሰዎች በአቋራጭ ዘወር ብለው የሰሎሞን ጥበብ የሚሉትን ጥንቆላ ይማራሉ። ትምህርቱ የገባቸውም አንዳንዶች ጥንቆላውን ይማሩታል። በጥንቆላ ትምህርት የታወቀ መሪጌታ፣ ቄስ ወይም ገበሬ ያልተማረ እንኳ ቢሆን ደብተራ ይባላል።
የደብተራ ጥንቆላ ከድግምት ጋር የተያያዘ ነው። ድግምቱ ትርግሙ የማይታወቅ ስም ቋንቋና አሠራር አለው። ሆኖም ሥራው የሚሠራው በአጋንንት ኃይል ነው። ከአጋንንት ጋር ቃል ኪዳን በማድረግ ከፍተኛ መተቶችን ይሠራሉ። ብዙ ጊዜ ደብተራዎች ቃል ኪዳን ለማድረግ የሚመርጧቸው የአጋንንት አለቆች በደብተራዎች አጠራር የሚከተሉት ታዋቂዎች ናቸው።
 አየረ ጴጥሮስ፦  አየረ ጴጥሮስ የሚባለው ሰውን ለመግደል፤ ለማፍዘዝ፤ ለማሳበድ፤ የሚዋረሱት አደገኛ የአየር ጋኔን ነው። አየረ ጴጥሮስን የተዋረሱ ደብትራዎች ሴትና ሽቱ ይወዳሉ። ገንዘብ ያገኛሉ ግን አይበረክትላቸውም። በየጊዜው ለጋኔኑ ደም የሚገብሩ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን ገብተው ማገልገል በጣም ይወዳሉ።
 አፈ ሕጻን፦  አፈ ሕጻን የሚባለው ደግሞ የምድር ጋኔን ነው። ልክስክስ ደካማ ጋኔን ሲሆን በሰው ላይ የሚፈጽመው ተንኮል ግን ከባድ ነው። በቡና በአረቄና በጠላ የሚሳብ ነው፤ አፈ ሕጻን የተባለበት ምክንያት በሕጻን ልጅ የሚሳብና በሕጻኑ አንደበት የሚናገር ስለሆነ ነው። ጋኔን የተሳበበት ሕጻን የኋላ የኋላ እብድ ሊሆን ወይም የአእምሮ ዝግመት ሊያጋጥመው ይችላል።
 ስሙ ለአብ፦  ይህ ጋኔን ለአቃቤ ርእስ ለሀብትና ለሥልጣን የሚዋረሱት ሰይጣን ነው። ባለ ሥልጣን ባለሀብት ሆነው ትዕቢተኞች ይሆናሉ፤ ጠባያቸው ከማንም ጋር አይስማማም። ይህን ጋኔን የተዋረሱ ሰዎች እጅግ አመንዝራዎች ናቸው። በዚህ ጋኔን የሚገለገሉ ጠንቋዮችም ሆኑ አስጠንቋዮች በብዛት ታንቀው ይሞታሉ። ወይም በድንገት ሞተው ይገኛሉ። በነገራችን ላይ ደብተራዎች ስሙን እየቀያየሩ ይጥሩት እንጂ ያው አንዱ ዲያብሎስ ነው።
 ደብተራዎች የተለያየ ዓይነት ናቸው። ሰይጣንን ሳይዋረሱ በድግምትና በሟርት የሚሠሩ፤ ሰይጣንን ተዋርሰው [ቃልኪዳን ገብተው] የሚሠሩ፤ መናፍስትን የሚጠሩ፤ ምሕሳበ ቅዱሳን የሚደግሙ፤ መልክአ ሳጥናኤል ብቻ በመድገም የፈለጉትን የሚያደርጉ አሉ። እንዲህ ዓይነት ሥራ አይሠራም ሰይጣንም ይህን ያህል አይሰራም የምትሉ አንባብያን ካላችሁ ሰይጣንም የሚፈልገው እንዲህ አይነቱን መዘናጋት እንደሆነ  እንድትረዱትና እንድታስቡበት እጠይቃለሁ።  
በመጽሐፍ ቅዱስ ጠንቋዮችና መናፍስት ጠሪዎች የተወገዙ ናቸው።
«ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጉአቸው እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ» ዘሌ 19፥31።
«መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን በሚከተል በሥራቸውም በሚያመነዝር በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ» ዘሌ 20፥6።
«ወንድ ወይም ሴት መናፍስትን ቢጠሩ ወይም ጠንቋዮች ቢሆኑ ፈጽመው ይገደሉ በድንጋይ ይውገሯቸው በማቸው በላያቸው ነው» ዘሌ 20፥27።
«አስማተኛም መተተኛም፣በድግምት የሚጠነቁልም፣ መናፍስትንም የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም፣ ባንተ ዘንድ አይገኝ»  ዘዳ 18፥11።
ከላይ እንደዘረዘርሁት አስማተኛ ማለት ትርጉማቸው የማይታውቁ ስሞችን መጥራት ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱን አስማት ለማየት «መልክአ ራጉኤል» እየተባለ የሚጠራውን በተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት የታተመውን የጸሎት መጽሐፍ እንደ ምሳሌ ያህል መመልከት ነው።
መተት ማለት ማስመስል ማለት ነው።  በአይን ላይ የሚደገም አስማት ነው።  ለምሳሌ ኢያኔስና እያንበሬስ የተባሉ የግብጽ ጠንቋዮች መተት አዋቂዎች ነበሩ ዘጸ 7፥11።
ድግምት ደግሞ ፍለጠው ቁረጠው እያሉ በአጋንንት ስም መራገም ነው። ድርሳነ ሚካኤል በጥቂቱ ይህ ዓይነቱ ድግምት ይገኝበታል፤ የሕዳር ሚካኤል የሚነበበውን ይመልከቱ።
መናፍስትን መጥራት ከላይ እንዳየነው የተለያዩ አጋንንትን መጥራት ሲሆን በቃል ኪዳን ተዋርሰው የታዘዙትን ሁሉ ያደርጋሉ።
ሙታን ሳቢ፦ ይህ ጥንቆላ በአገራችን ደብተራዎች ቋንቋ ምህሳበ ቅዱሳን ይባላል። የሞቱ ቅዱሳንን ለመጥራት የሚያገለግል ድግምት ነው። እንዲህ አይነቱን አስማት ባሕታውያን እየተባሉ የሚጠሩ ደብተራዎች አዘውትረው ይጠቀሙበታል። ሆኖም ግን በሙታን ስም የሚመጣው ያው የታወቀው ጠላታችን መሆኑ አያጠያይቅም። ሙታንን የሚስቡ ሰዎች እራሳቸውን ከሰው አግልለው መኖር ይመቻቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ሙታንን መጥራት የቻሉ ጠንቋዮች እንደነበሩ ተጽፏል  1 ሳሙ 28፥9።
ደስ የሚያሰኘው ነገር
እነዚህ በሰማይና በምድር ያሉ ኃይላት በባለ ውቃቤም ሆነ በደብተራ ስም ይምጡ እንጂ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይንበረከካሉ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም አጋንንት የማይቋቋሙት ስም ነው። «ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስም ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው» ፊልጵ 2፥10-11። ሟርትም አስማትም በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ስሙን በሚጠሩ ላይ ፈጽሞ አይሰራም። ወደ እግዚአብሔር የተጠጉ ሁሉ ከሰይጣን ወጥመድ ያመልጣሉ።
«በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።
እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ።
በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል።
በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም።
በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ ወደ አንተ ግን አይቀርብም።
አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ።
ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም።
በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና
እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል።
በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ።
በእኔ ተማምኖአልና አስጥለዋለሁ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ»። መዝ 90 [91]


አማላክችን ከጨላማው ስልጣን አድኖ ወደ መንግሥቱ አፍልሶናል  ቈላ 1፥13። እባቡን እና ጊንጡን እንረግጥ ዘንድ ሥልጣን ሰጥቶናል  ሉቃ 10፥19።ጠላታችን ከእግራችን በታች ፈጥኖ የሚቀጠቅጠው እርሱ ጠላቶቹን ከግሮቹ በታችን የረገጣቸው ዛሬም በደሙ ይሸፍነናል። ሮሜ16፥20። ክርስቲያኖች በዚህ እጅግ ደስ ልትሰኙ ይገባል።
ኢትዮጵያዊ ወገናችንን ለመርዳት የምንፈልግ ሁሉ ወንጌልን እንስበክ፤ ለነጻነት፤ ለልማት፤ ለዲሞክራሲ፤ ለፍትሕ እንታገል። ሕዝባችን በመናፍስት ጠሪዎች እጅ ስለወደቀ በረከት ርቆት በችግር ላይ ይገኛል። ነጻ የሚያወጣን የይሁዳ አንበሳ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው።
በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን እቃ ጦር ሁሉ ልበሱ መጋደላችን ከሥጋና ከደም ጋር አይደለምና ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዥዎች ጋር በሰማያዊም ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሰራዊት ጋር ነው እንጂ ኤፌ 6፥10-13።
አጥማቂው ግርማና ሌሎች አጥማቂዎች የሚያጠምቁበትን የአስማት አሰራርና አደራረጉን በሚቀጥለው አቀርባለሁ።
 በክርስቶስ ያመለጥሁ ደብተራ ነኝ


 
   

    


26 comments:

 1. የተሰቀለው ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታ ነው !January 25, 2013 at 12:01 PM

  «ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስም ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው» ፊልጵ 2፥10-11። ሟርትም አስማትም በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ስሙን በሚጠሩ ላይ ፈጽሞ አይሰራም። ወደ እግዚአብሔር የተጠጉ ሁሉ ከሰይጣን ወጥመድ ያመልጣሉ።

  Our savior is Jesus is Lord!

  ReplyDelete
 2. betamm ewenetegna tsehuf new and negrn astawesegn bealhubet hager kifelager nebr negeru yetfeterew and debtera Qes negn yemilu nebru balhubet sefer ke gorebet bet hule mata mata yimetalu betu yebaletdar bet new metetim yishetal enhi debtera eyemetu min endemeseru begziew alawekim neber and ken gin tanash hete betam hetsan nebrech eyasteru ke enate gar yihedalu enate ere yigermal hetsanewa seyanageruat awo sew ayehu benfas west yihen ayew eyalech esachew yemluten tenageralech bela setnegregn yenberew tezz alegn lekaasss seytanenn nebr siteru yenebreww Egziabehr yikir yebelachew yibelen Ebakachehu ABASELAMAWOCH kebtekersetyanachen endezhi ayenet neger eyetketatelachehu askumulin min alebet mk yihen neger biyaskom ewenetegna kiersetyanochen kemyasaded

  ReplyDelete
 3. አባ ሰላማዎች ሰላም ለእናንተ ይሁን
  ስሜ ማሙሽ ይባላል
  በእኔ ላይ ቤተሰቦቼ እያደረጉብኝ ያለውን የሰይጣን ስራ ልንገራችሁና የአባ ሰላማ አዘጋጆች ወይም አንባብያን ለችግርህ መፍትሔ ይሆናል የምትሉትን ሀሳብ እንድትለግሱኝ በትህትና እጠይቃለው፡፡
  1. ሳንቲም
  ብዙ ጊዜ በአልጋዬ ርብራብ ውስጥ (ትራስጌ አካባቢ) ድፍን ሃምሳ ሳንቲም ተቀምጦ አገኛለሁ ግን ሳንቲሙን ከየት የመጣ ነው ብዬ በመገረም ሳንቲሙን ለህጻናት ሰጥቼ እተዋለሁ፤ ይህ ነገር ሲደጋገም እናቴን መጠራጠር ጀመርኩ እናም ብዙ ከተጣላን በኃላ ሳንቲሙን የምታስቀምጠው እሷ እንደሆነች አመነች ግን እስከዛሬ ድረስ እያስቀመጠችብኝ ነው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ይህ ነገር ያመጣብኝ ችግር ቤት መጽዳት በጣም ያስጠላኛል፤ አልጋ ላይ እንደመተኛት እና እንደ እንቅልፍ የሚያስደስተኝ ነገር የለም 11፡00 ከስራ እንደወጣሁ ወደ መኝታዬ ነው የምሮጠው እተኛለሁ 3፡00 አካባቢ እራት ከበላሁ በኃላ ተመልሼ እተኛለሁ ጠዋት ከ 1፡30 አካባቢ እነሳለሁ…..ብዙ ጊዜ ይህንን ለመተው ብሞክርም አልቻልኩም፡፡

  2. ድግምት

  ማታ በር ዘግቼ ከተኛሁ በኃላ ደስ የማይል /የቁጣ የሚመስል/ የሰው ደምጽ /ድግምት/ ብዙ ጊዜ እሰማለሁ፡፡ ይህንን የመሰለ ድምጽ አንዳንድ ጊዜ ምሽቱ ሊነጋጋ ሲል እሰማለሁ፡፡ ይህንን የምታደርገው እህቴ ናት ምክንያቱም እንዲህ አይነቱን ድምጽ የምሰማው አርብ ማታ፤ ቅዳሜ ጥዋትና ማታ ፤ እሁድ ጥዋትና ማታ እና ሰኞ ጠዋት ብቻ ነው፡፡ እህቴ የስራ ቦታዋ እኛ ካለንበት ከተማ ራቅ ያለ ቦታ ስለሆነ ከሰኞ እስከ አርብ ከእኛ ጋር አትኖርም፤ አርብ ማምሻውን ትመጣና ሰኞ ጥዋት ትሄዳለች፡፡ ከነዚህ መረጃዎች በመነሳት እህቴ በእኔ ላይ ድግምት እየሰራችብኝ መሆኑን ለወንድሜ ስነግረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህንን አቆመች እና ሌላ ዘዴ መጠቀም ጀመረች፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን መጥፎ ድምጽ/ድግምት/ በሰማሁ ማግስት የመጨነቅ፤ ያለምክንያት ማልቀስ፤ እኔ አልረባም ብሎ ማሰብ፤ ሞትን መመኘት….ወዘተ ዓይነት ሁኔታ ይንጸባረቅብኛል፡፡ ሌላው ሰዎች እንደ ሽንት/ሰገራ/ ተጸይፈውኝ ከእኔ ይርቃሉ……ወዘተ

  3. በክፉ መንፈስ መታነቅ

  ከላይ እንደገለጽኩት/ለአባቴ/ እኔንም ማታ ከተኛሁ በኃላ የሰው እጅ ያንቀኛል ይህ በሚሆን ሰዓት ከፍተኛ የሆነ የመርበትበት፤የመንቀጥቀጥ/የፍረሀት/ ስሜት ይይዘኛል፤ እኔ እንደሚመስለኝ ይህንን ባደረጉብኝ ማግስት ቀኑን ሙሉ አለመረጋጋት ወይም መረበሽ ሰውን አለምክንያት መፍራት….ወዘተ ዓይነት ሁኔታ ይታይብኛል፡፡ እናቴ እና እህቴ ይህንን የሚያደርጉብኝ በተለይ መንገድ ለመሄድ ሲዘጋጁ ነው፤ በተለይ እህቴ ለስራ በየሳምንቱ መጀመሪያ ራቅ ያለ ቦታ ስለምትሄድ ሁል ጊዜ ይህንን እንደምታደርግብኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የዚህ ነገር ትርጉም የሚመስለኝ የእኔን የተረጋጋ የበረከት መንፈስ ወይም ጸጋ ወደ እነርሱ ወስደው የእነርሱን የተረበሸ መንፈስ ወደ እኔ ለማድረግ ይሆናል፡፡

  4. ምግብ ከእርግማን ጋረ

  እናቴ ለእኔ ምግብ ከማቅረቧ በፊት ገና ዕቃ ቤት እያለች ለእኔ የምታቀርበውን ምግብ ታዘጋጅና ሆድህን ይያዝ፤ አንጀትህን ይያዝ እያለች ምግቡ ላይ እንደምትደግምበት እህቴ በአንድ ወቅት ነግራኝ ነበር፤ በወቅቱ ነገሩ ቀልድ ስለመሰለን ሁላችንም ስቀን ተውን……….ከጊዜ በኃላ ግን እናቴ አዘውትራ ምግብ ስታቀርብ ልጆች እንዳንሰማ በቀስታ/በሽኩሽክታ/ የምትናገራቸው ግልጽ ያልሆኑ ቃላቶች አሉ፤ በኃላ ስለዚህ ነገር ያለኝ ግንዛቤ እየዳበረ ሲመጣ ምግብ ለእኔ አታቅርቢልኝ ስላልኩኝ ከእናቴ ጋር ተጣልተን በአሁኑ ጊዜ ምግብ የሚያቀርብልኝ ሌላ ሰው ነው……….ግን በከንቱ ነው የደከምኩት ምክንያቱም ምግቡን የምትሰራው እናቴ ስለሆነች ከዚህ ክፉ ነገር ያመለጥኩ አይመስለኝም፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም ይህ ነገር ያመጣብኝ ችግር የሰውነቴ ውፍረት፤ መጥፎ የሰውነት ጠረን፤ መጥፎ የአፍ ጠረን…..ወዘተ ይመስለኛል

  5. ስራ ጀምሬ መጨረስ አለመቻል

  እህቴ በተለያዩ ጊዜያት ምንም ነገር እንደማይሳካልኝ በቁጣ ቃል ትነግረኛለች /ዝም ብለህ ነው የምትለፋው አይሳካልህም/ ትለኛለች፤ እርሷ ይህንን የምትለው በምትሰራብኝ ድግምት ተማምና መሆኑን የተገነዘብኩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ትልቅ ዋጋ ያላቸውን ስራዎችን እጀምራለሁ ግን አልጨርስም፤ ትምህርት ጀምሬ ልጨርሰው ትንሽ ሲቀረኝ ችግር ይበዛና እተዋለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ምንም ነገር ብሰራ አይሳካልኝም የሚል እምነት አድሮብኛል፡፡ በነገራችን ላይ ከላይ እንደገለጽኩት አባቴም ከብቶቹ ለገበያ ደረሱልኝ ብሎ ሲያስብ ድንገት እንደሚሞቱበት ነው በእኔ ላይ እየሆነ ያለው፡፡

  6. ማታ ወደ መኝታዬ ከመሄዴ በፊት በጸሎት ላይ እያለሁ እኔ ያለሁበት ክፍል/ሰርቪስ/ በር ወይም ቆርቆሮ በድንገት በድንጋይ ይመታል፤ በታጠረ ግቢ ያለን መኖሪያ ቤት በር በድንጋይ የሚመቱ የገዛ ቤተሰቦቼ እንጂ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡ ቤቴ በድንጋይ ሲመታ በእኔ ላይ የመደናገጥ ስሜት ይፈጠራል፡፡ እኔ ያልተረዳሁት ይህ ነገር በእኔ ህይወት ላይ የሚሳድረውን ተፅዕኖ ነው ፡፡
  7. በተደጋጋሚ በህልሜ እባብ ደስ በሚሉ ትናንሽ ወፎች ዙሪያ ተጠምጥሞ ሲንከባከባቸው አያለሁ፤ የህልሜ ትርጉም እናቴ እንደሆነች እርግጠኛ ነኝ፡፡

  ከላይ በዝርዝር የጻፍኩት ሁሉ እውነት
  አባ ሰላማዎች ሁሉንም ነገር በዝርዝር ልጻፈው ካልኩ በጣም ይበዛል፤ ለአባ ሰላማ ብሎግ ተሳታፊዎች ትምህርት እንዲሆንና እኔንም በሃሳብ /በጸሎት/ የሚረዱኝ ሰዎች ካገኘሁ በሚል እምነት ይህንን ጽፌያለሁ፡፡
  ደህና ሁኑ
  ማሙሽ

  ReplyDelete
  Replies
  1. በመጀመሪያ እግዚአብሔር ይርዳህ ፤ ይማርህም እላለሁ ፡፡
   የአንተ ችግር ጥርጣሬን በላይህ ያለዕውቀት በማንገስህ የተፈጠረ መስሎኛል ፡፡ ይኸም ልጅነትህ (ስለስምህ) ያመጣው ይመስላልና የመፍትሄ ሃሳቦች የመሰሉኝን ከጠቀሙህ ለማካፈል እሞክራለሁ ፡፡ አሁንም ቢሆን በቅድሚያ ማመን አለብህ የምለው ፣ ለችግርህም መንስዔውና ምክንያቱ ፣ ቤተሰቦቼ እንዲህ እያደረጉኝ ስለሆነ እንዲህ እሆናለሁ ብለህ እያንዳንዱን ሥራቸውን በእምነት መከታተልህና እውነት አድርገህ መቀበልህ ብቻ መሆኑን ነው ፡፡

   መጽሐፍ ቅዱስ በገሃዱ ዓለም ወደሚንበለበል እሳት የተጣሉትን አማኞች እንኳን እግዚአብሔር እንደጠበቃቸውና እንደአዳናቸው አስተምሮናል ፤ እንኳንስ ለማይታየው የብልጦች መንፈሳዊ ቅዠት ሊያንበረክከንና አሳልፎ ሊሰጠን ፡፡ ስለዚህም ወንድሜንና ልጄን እላለሁ

   1. በቅድሚያ በእምነትህ መጠንከር ይገባሃል ፤ ዘወትር ርሱን የፈጠረህን አምላክ ብቻ አስበው ፤ እርሱ አብሮህ እንዳለ በማመን በመንፈስህ አናግረው (Dream living always with him, Jesus, our Lord)፡፡ የፈጠረኝ አምላክ ለእንደዚህ ሰንካላ የብልሆች ምግባር እንድንበረከክ አያደርገኝም ብለህ በራስህ ተማመን ፡፡ ይኸ ከራስህ የሚመነጭ የእምነት ኃይል ነው እንጅ ፣ ሰው ከውጭ የሚሰጥህ ፣ የሚጭንልህ ወይም የሚሰፍርልህ አይደለም ፡፡ “ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው ፣ የኔ ጌታ ፣ ለሰዎች ጥበብና ብልሃት አይሸነፍም ፤ እኔንም ልጁን አሳልፎ አይሰጥም ፤ ይጠብቀኛል ፤ ርሱ ዘወትር ከኔ ጋር ነው ፡፡” እያልክ ድምጽ አውጥተህ መስክር ፡፡ በአፍህ መመስከር ብቻ ሳይሆን ደግሞ ልቦናህን በሙሉ ኃይል በምትናገረው ቃል ላይ አንጸው ፤ አጽናው ፡፡ ጥንካሬና ጉልበት ይሆንሃል ፡፡

   መተት ፣ ጥንቆላና የቃልቻ ሥራ በእኔ ላይ ኃይል አለው ብለህ ማመኑ በራሱ ተሸናፊነትን በራስህ ላይ ስለሚያነግስ ፣ እንዲህ ዓይነቱን እምነት ከመነሻው መካድ ያስፈልግሃል ፡፡ ቅዱሱንና ርኩሱን በአንድነት ማመንና ማምለክ በራሱ ጸያፍ ነው ፡፡ ወይ የጌታ መሆን አለበለዚያም የዚያኛው ወገን ፡፡ በጌታ የሚያምን የርኩስን መንፈስን ኃይል ሊቀበል አይገባም ፡፡ ይኸ የእምነት ማሳከር ነው ፡፡ የርኩስ መንፈስ ኃይሉ የሚሠራው ካመንክና ከተንበረክለት ብቻ ነው ፡፡

   2. የጻፍካቸው አንዳንድ የችግርህ መገለጫዎች ፣ የአእምሮ ጤና መታወክን (Depression) ያመለክታሉ ለምሳሌም
   - “እንደመተኛት እና እንደ እንቅልፍ የሚያስደስተኝ ነገር የለም”
   - “የመጨነቅ፤ ያለምክንያት ማልቀስ፤ እኔ አልረባም ብሎ ማሰብ፤ ሞትን መመኘት”
   - “ቀኑን ሙሉ አለመረጋጋት ወይም መረበሽ ሰውን አለምክንያት መፍራት”
   - “የሰውነቴ ውፍረት፤ መጥፎ የሰውነት ጠረን፤ መጥፎ የአፍ ጠረን”
   - “ምንም ነገር ብሰራ አይሳካልኝም የሚል እምነት አድሮብኛል”

   ከላይ እንደጠቀስኩልህ በእምነት መደገፉን ባምንበትም (ችግሮችህን ራስህ መገንዘብ ስለቻልካቸውና ለእኛም ማቅረብ ስለሞከርክ በማለት) ፣ እንዲህ የተወሳሰበ ስሜተ ሲሰማህ ሃኪም (Psychiatrist) ብታማክር ፣ የህክምና እርዳታ ወይም ምክር ሊሰጡህ ይችላሉ ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ባለሙያ ማማከር ማለቴ አብደሃል ፣ ለይቶልሃል ጨርቅህን ልትጥል ነው ለማለት አይደለም ፡፡ በሰዎች ላይ ለረጅም ጊዜ የሚያድረው ጭንቀት የብዙ በሽታዎች መነሻ ስለሆነ መታከም ስለሚገባው ነው ፡፡

   3. ማሙሽ ብትባልም እድሜህን ቢያንስ አሥራዎቹ መጨረሻ ወይም ሃያዎቹ ውስጥ እገምታለሁ ፡፡ ተምረሃል ፤ ሥራ መሥራት ጀምረሃል ፤ ማለትም ራሰህን ለማስተዳደርና ለማኖር የሚያስችል የዕለትም ሆነ የወር ገቢ አለህ ፡፡ ስለዚህም ቅሌን ጨርቄን የሚል ምክንያት ሳታቀርብ በእንደዚህ ዓይነት አምልኮ ከተመላ ቤተሰብ ተለይተህ በራስህ ኑር ፡፡ ማለቴም ሌላ አካባቢ ወይም ከተማ ሄደህ የራስክን ቤት ተከራይተህ ፣ የሚያማክርህና ደግ ሃሳብ የሚያጋራህ ጥሩ ጓደኛ (ወንድ ወይም ሴት) ይዘህ በራስህ ለመኖር ወስን ፡፡

   4. አይ መለየት አልችልም ፤ ስለዚህና ስለዚያኛው ምክንያት የምትል ከሆነ የሚሠሩትን ሥራ ፣ ራሳቸውን መልካም ሙያተኛ ለማድረግ የሚከወን ልምምድ ብለህ ተዝናናበት ፡፡ ሳንቲም ሲያስቀምጡም በስመ አብ ፣ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፣ በስምህ የተባረክ ይሁን ብለህ እየለቀምክ ተጠቀምበት ፡፡ በስሙ ከባረክከው ቀድሰኸዋልና ችግር አይሆንብህም ፡፡ ምንም እንደማያደርግህ ራስክን ከፈተንከው በኋላ ቢቻልስ ብር አድርጉት በላቸው ፡፡ የነርሱን ገንዘብ ለመጠቀም የማትፈልግ ከሆነም ለተቸገሩ ብትመጸውተው ርሱ ብድርህን በሰማይ ያስቀምጣል ፡፡ ምግብም ላይ የሚያወሩትን ምሥጢር ከምትከታተል አንድ ቆንጆ መዝሙር ዘምር ፤ ቤቱን በመንፈስ ቅዱስ ትሞላዋለህ ፡፡ ምናልባት እነርሱም ከመዝሙር ቃልህ ይማራሉ ፡፡

   ወንድሜና ልጄ በክርስትናህ ጠንክር ፤ ጌታ ስለሚረዳህም ተጽናና ፤ በእምነትህም በርታ ፡፡ ቢዘገይም እንኳን ትድናለህ ፡፡

   Delete
  2. የተሰቀለው ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታ ነው !January 26, 2013 at 11:06 AM

   ምእመን

   God Bless you! your advice is extraordinary, “ኢየሱስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳው ፣ የኔ ጌታ ፣ ለሰዎች ጥበብና ብልሃት አይሸነፍም ፤ እኔንም ልጁን አሳልፎ አይሰጥም ፤ ይጠብቀኛል ፤ ርሱ ዘወትር ከኔ ጋር ነው ፡፡” እያልክ ድምጽ አውጥተህ መስክር ፡፡ በአፍህ መመስከር ብቻ ሳይሆን ደግሞ ልቦናህን በሙሉ ኃይል በምትናገረው ቃል ላይ አንጸው ፤ አጽናው ፡፡ ጥንካሬና ጉልበት ይሆንሃል ፡፡ I can't believe "I read a word from talking about Lord Jesus." Now you are my brother! You made me happy for now, I hope! I will read a lot more biblical or spiritual concerning words.

   Delete
  3. ለየተሰቀለው
   ለእኔ የይለፍ ቃል ከምታስቀምጥልኝ ፣ በእምነቱ ተጎድቶ ፣ በጤና ችግር ለሚሰቃይ ወንድም ፣ የሚሰማህንና መፍትሄ ይሆናል የምትለውን ሃሳብ ብታቀርብለት ብዙ በረዳው ነበር ፡፡ የምታካፍለው ቁም ነገር ብታጣ ፣ ቢያንስ ወደ ደም መላሽ ግርማችን ብታመላክተው ወይም ቤቱን ጸበል እንዲያስረጭ ብትመክረው እንኳን ሌሎች አማራጮች ይሆኑት ነበር ፡፡

   Now you are my brother! ለሚለው ቃልህ
   ወንድሜ ለሠራኸው በደል ንስሓ አስቀድመህ ስላልገባህ ፣ ያች የምታውቃት እናታችን የጋራችን ትሆንብሃለች ፡፡ እንደ እኔ ምክርና እንዳስቀመጥኩልህ የአደራ ቃል ሁለት ወር ጠብቀህ የጻፍከውን በድጋሚ ካነበብክ በኋላ ፣ የተሰማህን ስሜትክን ስትገልጥ ቀስ ብለን ወዳጅነታችንን በወግ መመሥረቱ ይበጅ ይመስለኛል ፡፡ ምክንያቱም የአንተ የbrother ትርጓሜ ለየት ያለ ስለሆነ ነው ፡፡

   ሰላም ሁንልኝ ፤ ጸጋውን ያብዛልህ ፡፡

   Delete
  4. ምእመን about nebure id i am also confused ,may be he has his own doctrine!!try these blogs about spritual forces like above ባለ ዛር ወይንም ባለ ውቃቤዎች (but the second one made me confused) http://antiglobalconspiracy.blogspot.com/ http://rafatorael.com/index.php/conspiracy-theory

   Delete
  5. የተሰቀለው ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታ ነው !January 27, 2013 at 8:25 AM

   ቢያንስ ወደ ደም መላሽ ግርማችን ብታመላክተው ወይም ቤቱን ጸበል እንዲያስረጭ ብትመክረው እንኳን ሌሎች አማራጮች ይሆኑት ነበር ፡፡

   There is no option or alternative but only Lord Jesus. Are you still taking about devil Girma?
   My only advice to ማሙሽ is to believe and have a relationship with Lord Jesus,that is the best medicine. I also advice you to take that medicine (Lord Jesus), to get cure from your suffering of dabilos. By the way, what do I confessing? confessing being I discounted or condemned Grima's magics? You must be crazy ምእመን.

   Delete
  6. ለማሙሽ ተጨማሪ አስተያየትና ምክር
   በተሰጠህ ምክርና አስተያየት ላይ ምንም ነገር አለማለትህ ስላሳሰበኝ ዛሬ ደግሞ ከእምነታችን ወጣ ያለ በንባብ ሰሞኑን ከቃረምኩት ተጨማሪ ምክር ላካፍልህ ተመለስኩ ፡፡ ምክንያቱም ካስቀመጥካቸው የድብርት (Depression) መገለጫዎች ውስጥ በመጥፎ ውጤታቸው ምክንያት ከፍተኛ ትኩረት መሰጠት ያለባቸው ጉዳዮች ስለሚገኙ ነው ፡፡ እነርሱም

   1. “የመጨነቅ፤ ያለምክንያት ማልቀስ፤ እኔ አልረባም ብሎ ማሰብ፤ ሞትን መመኘት” በማለት የጠቀስካቸው ሃሳቦች የመጨረሻ መደምደሚያቸው አስከፊ ስለሆነ ፣ የግድ አስቸኳይ የኃኪም እርዳታን ማግኘትን ይፈልጋሉ ፡፡ ጤናማ ሰው ማንኛውም ዓይነት ጊዜያዊ ፈተናና ችግር ሲያጋጥመው ፣ ለጊዜው ቢያዝንም ወቅታዊ መሆኑንና ኃላፊነቱን በማመን ይረጋጋል እንጅ ምንም ቢሆን ዕለተ ሞቱን አይመኝም ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች በሂደት ራስን ወደ ማጥፋት ወይም ለአደገኛ ዕጽ ሱሰኝነት አንዳንዴ ደግሞ ጠላፊ ካጋጠመ ሃይማኖትን እስከማስቀየር ይደርሳሉ ፡፡ ስለዚህም ቃልህ አሳስቦኛልና እንደ አንድ ወገንህ የምትለውን ማወቅ እፈልጋለሁ ፡፡

   2. “የሰውነቴ ውፍረት፤ መጥፎ የሰውነት ጠረን፤ መጥፎ የአፍ ጠረን” እና “እንደመተኛት እና እንደ እንቅልፍ የሚያስደስተኝ ነገር የለም” የሚሉት መግለጫዎችህ ደግሞ የሚያያዙና ለማስወገድ ብትታገላቸው ለጤናህ የሚረዱህ ስለሆኑ በአንድ ላይ በአጭሩ ለማስረዳት እሞክራለሁ ፡፡

   ብዙ መተኛት ሰውነታችን ለዕለት ፍጆታው ማቃጠል የሚገባውን ከምግብ የሚገኝ እምቅ ኃይል (Calorie) መጠቀም ይቀንሳል ፤ የዚህ የእምቅ ኃይል በሰውነታችን ከተፈላጊው በላይ መከማቸት ደግሞ ፣ ወደ ስብነት (Fat) ይቀየርና ውፍረታችንን ያባብሰዋል ፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ የሚተኛ ሰው ምንጊዜም ወፍራም ነው ፡፡ በጣም ወፍራም የሆኑ ሰዎች ቆዳቸው ብዙ ቦታ ላይ እንደ ህፃን ገላ ስለሚተጣጠፍና (በተለይም መገጣጠሚያ አካባቢ) አየር እንደልቡ ስለማያገኝ አይናፈስም ፡፡ ይህ ደግሞ ጥቃቅን ሕዋሳትን (Bacteria & Fungus) ለማራባት አመች ሁኔታ ስለሚፈጥር ጥቂት እንኳን ቢያልብህ የሰውነትህ ጠረን ያስቸግርሃል ፡፡

   የአፍ ጠረን መቀየርም የሚፈጠረው ይኸንኑ በመሰለ መንገድ ነው ፡፡ ሰው በተፈጥሮው የሚኖረው በላዩ ከሚገኙ ጥቃቅን ሕዋሳቶች (Normal flora Bacteria) ጋር ተስማምቶ ነው ፡፡ በቆዳው ላይ ፣ በአፉና በጉሮሮው ፣ በአፍንጫውና በአንጀቱ ውስጥ በሽታ ላይ የማይጥሉ ጥቃቅን ሕዋሳቶች አሉት ፡፡ መደበኛ መኖሪያቸውን ሲቀይሩ ወይም ክምችታቸው ከመጠን በላይ ሲያልፍ ግን የማይፈለግ የጤና ችግር ያስከትላሉ ፡፡

   አፋችንንም ጠዋትና በተለይም ከመተኛታችን በፊት በሥርዓቱ የማናጸዳው ከሆነ ፣ አፍ ውስጥ የሚኖሩት ባክቴሪያዎች የጥርሳችንን ውስጥ ፍርፋሪ በመጠቀም ከመጠን በላይ ይራባሉ ፡፡ ይህ ደግሞ የአፍ ጠረን መቀየርን ያስከትላል (የአደረ አፍ የሚባለው ነው) ፡፡ እነዚህ ሁለት የጠረን ችግሮች ደግሞ በራስህ እንዳትተማመንና ከሰዎች እንዳትቀላቀል ስለሚያደርጉህ የጤና ችግርህን (ድብርት) ይበልጥ ያባብሱታል ወይም የከፋ ያደርጉታል ፡፡ ሰው ለሰው መድኃኒቱ ነው የሚባለውንም አስብ ፤ በሃሳብ መደጋገፍ ከገንዘብ ስጦታ በላይ ስለሚሆን ነው ፡፡

   የመፍትሄ ሃሳቦች
   ሀ/ ጥርስህን ቢቻል ምግብ ከበላህ በኋላ ሁል ጊዜና ፤ ቢያንስ ግን በቀን ሁለት ጊዜ በተለይም ከመተኛትህ በፊት ትኩረት ሰጥተህ በሥርዓቱ ማጽዳት ፡፡ ከመተኛታችን በፊት መቦረሻችን ጠቃሚ የሚሆንበት ምክንያት ምላሳችን እንደ ቀኑ ስለማይነቀሳቀስና ብዙ ምራቅም እየተመረተ ሲያጸዳ ስለማያድር የአፍን አሲድነት ስለሚጨምረው ነው ፡፡ የአፍን አሲድነት መቀነስ መቻልም የባክቴሪያዎችን መራባት ይቀንሳል (ጡት ሲጠቡ የሚያድሩ ህጻናትን ያደረ የአፍ ጠረን ልብ በል)፡፡ በተረፈ ለየት ያለ ችግር (የጥርስ መቦርቦር ፣ የድድ መቁሰል) ካለህ የጥርስ ኃኪሞችን ብታማክር የተሻለ ርዳታና ምክር ይሰጡሃል ፡፡

   ለ/ ዘወትር (ቢያንስ በሳምንት ለአምስት ቀናት ከአንድ ሰዓት ላላነሰ ጊዜ) የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ፡፡ ለእንቅስቃሴ ከመውጣትህ በፊት ቢያንስ በግማሽ ባልዲ ውሃ ሰውነትህን ተለቃልቀህ የጠረን መከላከያ (Deodorant) በመጠቀም ያለጭንቀት ብዙ ሰዓት ከሰዎች ጋር ተቀላቅለህ መሥራት ይጠቅምሃል ፡፡ ያንንም ካልወደድክ ለብቻህ መሮጥም አማራጭ ነው ፡፡

   የሚገኙት ጥቅሞች፡-
   - የደም ዝውውርህ የተሻለ ይሆናል ፤ የልብህና የሳንባህ አሠራር የተስተካከለ ይሆናል
   - ከምግብ የምታገኘውን ብዙውን ካሎሪ ስለምታቃጥል ፣ አመጋገብህን አብረህ ካስተካከልህ የሰውነትህ ክብደት (ውፍረትህ) ቀስ በቀስ በወራት ውስጥ ይቀንሳል
   - የሰውነት ቅርጽህ አሁን ካለህ ያማረና የተዋበ ስለሚሆን የውስጥ ስሜትህ ይነቃቃል
   - ሰውነትህ የተሻለ ጥንካሬና ቅልጥፍና ስለሚያገኝ በራስህ መተማመንን ይፈጥርልሃል
   - እየለመድከው ስትመጣ ዘወትር አላግባብ የመተኛተ ስሜትህ ይቀንሳል ፡፡ በምትተኛበትም ሰዓት ጥሩ እንቅልፍ ይኖርሃል ፡፡ ያለ ህመም ምክንያት ምንም ቢሆን አልጋህ ላይ በቀን ውስጥ ቢበዛ ከስምንት ሰዓት የበለጠ አትጋደም
   - ዘወትር ደስተኛ ትሆናለህ ፡፡ ምክንያቱም ለረጅም ሰዓት በፈጣን አካል እንቅስቃሴ ላይ ከቆየህ ሰውነትህ ኤንዶርፊን (Endorphin) የተባለ ንጥረ ነገር ስለሚያመነጭ እንደ ሞርፌን የደስታና የርካታ ስሜት ይፈጥርልሃል ፡፡ ይህን እንዲያመነጭ ግን በደንብ በላብ እስከምትነከርና ትንፋሽ እስከሚያጥርህ ለረጅም ሰዓት መልፋት ያስፈልግሃል (በሩጫ ብትገምተው ቢያንስ 1ዐ - 2ዐ ኪሎሜትርን መሸፈን ማለት ነው)፡፡ ሌላውም የሰውነትህ መስተካከልና ጥንካሬህ መጨመሩ ፣ ከሰዎች ጋር አብረህ ጊዜ ማሳለፉ በራስህ ሳይኰሎጅ ላይ ተጽእኖ ስለሚኖረው ጭምር ነው

   ሙሉ ጤናማነትህን በመመኘት

   Delete
  7. ለ፤ ምዕመን
   ማሙሽ ነኝ
   ለጤናህ እንደምን አለህ…..እግዚአብሄር የተመሰገነ ይሁን፡፡ ዓሜን
   ስለእኔ በማሰብ በድጋሚ ለሰጠኸኝ ምክር ከልብ አመሰግንሃለው፡፡ ስለአፍ ጠረንና የሰውነት ውፍረትን በተመለከተ የሰጠኸኝ ምክር መልካም ናቸው ነገር ግን የእኔ ችግር እሱ አይመስለኝም፤ ለምሳሌ እንቅልፍ ይወስደኝና ከተኛሁ በኃላ ከአፌ ምራቅ (ለሀጭ) ይፈሳል እናም የሄ ለሃጭ የነካው ቆዳዬም፤ልብሴም ይሁን አንሶላዬ መጥፎ ሽታ ይኖረዋል፤ ይህ መጥፎ ሽታ ደግሞ ከተለመደው የአፍ ጠረን የተለየ ነው፡፡ የሰውነት ክብደት መጨመርን በተመለከተ 68 ኪ.ግ ከ 1.84 ቁመት ነኝ፤ በአሁኑ ሰዓት ይሄ ማለት ጥሩ ነው፡፡ ክብደቴ ጨመረ ያልኩህ በአንድ ጊዜ ከ 55 ኪሎ ወደ 68 ኪሎ በማደጉ ነው፤ በዚህ ጉዳይ ልጨነቅ የቻልኩትም አንዳንድ ከማነባቸው ድረ ገጾች/website/ ለመረዳት እንደቻልኩት ከተለመደው ውጪ የሆነ የአፍ ጠረን፤ የክብደት መጨመር …..ወዘተ ድግምት የተደረገባቸው ወይም በክፉ መንፈስ የተጠቁ ሰዎች ምልክት ነው ስለሚል ነው፡፡
   ይልቅ ይህን ጉዳይ ካነሳነው አይቀር እኔ በዚህ ክፉ መንፈስ እንዴት እንደተጠቃሁ ላጫውትህ፤
   የቤተሰባችን ኑሮ አንዴ ከፍ አንዴ ዝቅ ይል እንደነበር ልጅ ሆኜ አስታውሳለሁ፤ የዛሬ 13 ዓመት አካባቢ ግን አባቴና እናቴ ተጣሉና ተለያዩ አባታችን ቤቱን ለቆ ወጣ፤ ሁለት ወንድሞቼና ሁለት እህቶቼም በየዘመድ ቤትና በተለያየ ቦታ ተበታተኑ፤ እኔን ጨምሮ ሶስት ልጆች ብቻ ከእናታችን ጋር በቤት ውስጥ ቀረን፡፡ እናታችን የቤት እመቤት እኛም በቤት የቀረነው ልጆች ለአቅመ አዳም ያልደረስን በመሆኑ በጣም ተቸገርን ተሰቃየን…….፤ በዚህ መሐል ለከብቶቹ ማቆሚያ ያጣ ሰው ለምን በጋራ አናረባም ብሎ ቤታችን ድረስ ከተፍ አለ፤ ሰውየው ለጥቅሙ እኛም ለችግራችን ስንል ተስማማንና ስራውን ቀጠልን……የከብቶቹን ቀለብ የሚችለው ሰውየው ነበር፤ ግን ምን ይሆናል ብዙ ወተት ይሰጡናል ብለን ስንጠብቅ ከብቶቹ ታማሚ ሆኑና የጠበቅነው ሳይሆን ቀረ፤ በዚህ ጊዜ አንድ የማልረሳው ነገር ሰውየው ለከብቶቹ ቀለብ ብሎ ነቀዝ የበላው ቦሎቄ በብዛት አምጥቶ ስለነበር ያለማቋረጥ 3 ወር ሙሉ ከከብቶቹ ጋር መመገባችንን አስታውሳለሁ፤ ምክንያቱም ሌላ ምግብ አልነበረንም…...፡፡
   ከሙሴ ጀምሮ ነብያትና ሐዋርያት ሁሉ “እግዚአብሔር የሚገስጸው ሰው የተባረከ ነው” የሚሉት ለምንድ ነው
   ከላይ የጠቀስኩልህን ጨምሮ ሌሎች ችግሮች በቤተሰባችን ላይ ከመድረሱ በፊት ትንሽ ዱርዬ ቢጤ ነበርኩ፤ ከዚያ በኃላ ግን ጸባዬ ሙሉ በሙሉ ታረመ፤ ዘወትር መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብና ጸሎት ማድረግን ተማርኩ፤ ከሰውየው ጋር የከብት እርባታ አላወጣም ስላለን እሱን ትቼ በወር የ 70 ብር ስራ ጀመርኩ……የቤተሰባችን ኑሮ መለወጥ የጀመረው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ አስራት የተጻፉ ጥቅሶችን አንብቤ ስለነበር ከማገኛት 70 ብር ላይ አስራት መክፈል ጀመርኩ……
   አስራት በመክፈሌ ምክንያት ያገኘሁት ጥቅም፡-
   1. ደመወዜ በሚገርም ፍጥነት አደገልኝ
   2. 7 ወንድሞቼንና እህቶቼን አስተማርኩ ( ከ 7 ውስጥ 4 ባለ ድግሪ 2 ዲፕሎማና አንድ ነጋዴ ሆነዋል)
   3. ይሄ ሁሉ ችግር ሲደርስብን ብተሰባችንን ሞትና በሽታ አልጎበኘውም
   4. ብዙ ጠላቶች ነበሩብኝ በተለይ መሬታችንን ለመንጠቅ የሚፈልጉ ሰዎች ግን አላሸነፉንም
   5. ለእራሴ ቦታ ተመርቼ የሞኖሪያ ቤት ሰራሁ
   6. ሌሎች ብዙ ጥቃቅን ነገሮችን ሰርቻለሁ( እንዳይሰለችህ ብዬ አልጽፈውም)
   ይህንን ሁሉ ስሰራ የእኔ ደመወዝ ከ 400 ብር አይበልጥም ነበር፤ በእርግጥ አሁን በጣም አድጓል፡፡ በዚህች ደመወዝ ይህን ሁሉ በአጭር ጊዜ ልሰራ የቻልኩት ፈጣሪ ከሌሎች እየነጠቀ ስለሰጠኝ ነው፤ የምልህን የበለጠ እንድትረዳው ይህንን ጥቅስ አንብበው፤
   ይቀጥላል

   Delete
  8. ካለፈው የቀጠለ
   በዘፍጥረት 28፡20-22 ያዕቆብ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል ቃል ኪዳን ገባ፤ ከእኔ ጋር ብትሆን፤ በሄድኩበት ሁሉ ብትጠብቀኝ፤ የሚያስፈልገኝን ምግብና ልብስ ብትሰጠኝ፤ ወደ አባቴም ቤት በሰላም ብትመልሰኝ…….አንተ አምላኬ ትሆናለህ፤ ይህ ያቆምኩት አለት ወደፊት የእግዚአብሄር ቤት ይሆናል፤ ከምትሰጠኝ ነገር ሁሉ ከአስር አንዱን ለአንተ እሰጣለሁ፡፡
   ያዕቆብ ከፈጣሪ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ስንመለከት፡-
   1. ጌታ ከእኔ ጋር ብትሆን
   2. በምሄድበት ስፍራ ሁሉ ብትጠብቀኝ
   3. በቂ ምግብና ልብስ ብትሰጠኝ
   4. ወደ አባቴም ቤት በሰላም ብትመልሰኝ
   5. አንተም አምላኬ ትሁናለህ
   6. ይህ ያቆምኩት አለት ወደፊት ቤተ ክርስቲያን ይሆናል
   7. ከምትሰጠኝ ሁሉ ከአስር አንዱን ለአንተ እሰጣለሁ፡፡
   ያዕቆብ ይህንን ሁሉ ብታደርግልኝ አስራት ለአንተ እከፍላለሁ በማለት ከፈጣሪ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ባለጸጋ እንዳደረገውና ወንድሙ ኤሳውን ጨምሮ ከብዙ ጠላቶቹ እንዴት እንደዳነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፤ በተጨማሪ ላስታውስህ የምፈልገው የአብረሃም ወንድም ልጅ የሆነው ሎጥ ልክ እንደ አብረሃም ሀብታም ነበረ፤ ነገር ግን ሎጥ በተደጋጋሚ በጠላት ይጠቃ እንደነበረ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንማራለን፤ ይህ የሚያሳየን ሎጥ እንደ አብረሃም ባለጸጋ ቢሆንም አስራት ባለመክፈሉ ምክንያት ለጥቃት የተጋለጠ መሆኑን ነው፡፡ መጽሐፈ ኢዮብን ስናነብ ሰይጣን ኢዮብን ሊፈትነው ፈቃድ መጠየቁ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ የኢዮብን ሀብትና ንብረት ሁሉ በሰላም ይጠብቅለት አንደነበር ይናገራል፡፡
   የእኔን በክፉ መንፈስ መጠቃት በተመለከተ
   ቤተሰቦቼ በሙሉ ፕሮቴስታንት ቢሆኑም እኔ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ነኝ፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አስራቴን በወቅቱ እከፍል ነበር፤ አሁን አሁን ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘረኝነት፤ ሙስና እና የስነ ምግባር …..ወዘተ ችግሮችን ብቻ በማየት ለምን አስራት እከፍላለሁ ለምን ገንዘቡን ለድሃ አልሰጥም…..ወዘተ የሚል ሃሳብ በልቦናዬ አደረና ይኸው አስራት ሳልከፍል አመት አለፈኝ፤ ጠላት ቤተሰቦቼን ተጠቅሞ እኔን ማጥቃት የጀመረውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይመስለኛል፤ በእርግጥ ከዚያ በፊት ጠላት አልነበረኝም ማለቴ አይደለም፤ ብዙ ጠላቶች ነበሩብኝ ግን ተሸንፌ አላውቅም ነበር፤ አሁን ግን ጠላት እያሳደደኝ ነው፡፡
   በነገራችን ላይ የዘረኝነት ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ በእስልምና እና በፕሮቴስታንት ሀይማኖት ውስጥ ጎልቶ አይታይም በእኛ በኦርቶዶክስ ሀይማኖት ግን በጣም የጎላ ችግር እየሆነ ነው፡፡ ሙስናና የስነምግባር ችግርም በእኛው ላይ የነገሰ ይመስለኛል፤ አባቶቻችን ለራሳቸው ተፈትነው እኛንም ለፈተና ያጋለጡን ይመስለኛል፡፡
   አንድ ነገር ሳልነግርህ የማላልፈው ድግምት ወይም በክፉ መንፈስ የተጠቃ ሰው አንድ ሌላ መለያ ባህሪው ለቤተክርስቲያን ያለው አመለካከት ይቀየራል፡፡ የገንዘብ ቦርሳ ያዥ የነበረው ሌባው ይሁዳ ትናንተ እንደነበረ አውቃለሁ፤ የእርሱ የግብር ልጆችም ዛሬ እንዳሉ ወደፊትም እንደሚኖሩ አውቃለሁ፤ ታዲያ ምን ይሁን ብዬ ነው ለቤተክርስቲያን የምከፍለውን አስራት የማቋርጠው በማለት ዘውትር እራሴን እጠይቃለሁ፤ ችግሩ በአንድ ሀሳብ መርጋት አልቻልኩም ነገ ደግሞ ለምን ለድሃ አልሰጥም እላለሁ፡፡ እንዲህ እንደውሃ ስዋልል አንድ አመት አለፈኝ፡፡
   ከላይ በዝርዝር እንደጻፍኩልህ የእኔ መጠቃት ዋነኛ ምክንያቱ አስራት መክፈልን በማቋረጤ ምክንያት የመጣ ነው የሚል እምነት ይዣለሁ፤
   የአባ ሰላማ አዘጋጆችም ለክፉ መንፈስ ጥቃት የተጋለጡ ብዙ ሰዎች ያሉ ስለሆነ በዚህ ዙሪያ ብዙ ብዙ መስራት የሚጠበቅባችሁ ይመስለኛል፡፡
   ምእመን በጣም አመሰግናለሁ
   ማሙሽ

   በተጨማሪ እነዚህን ዌብ ሳይት ብትጎበኙ መልካም ነው
   http://www.saulat.com/29.htm
   http://wiki.answers.com/Q/What_are_the_symptoms_of_black_magic
   http://www.spellsofmagic.com/spells/life_spells/revenge_spells/12165/page.html

   Delete
  9. ምእመን በጣም አመሰግናለሁ
   ማሙሽ

   Delete
  10. ጌታ አሁንም በጸጋው ይጐብኝህ ፡፡ እኔ አንተን የረዳሁ መስሎኝ ስዳክር ፣ አንተ በግልባጭ ብዙ አስተማርከኝ ፡፡ ተስፋ አትቁረጥ ፤ ለምንም ነገር አትንበርከክ ፡፡ ሁላችንንም የጓዳ ታሪካችንን አደባባይ ብናወጣው ብዙ ይመሳሰላል ፡፡ ገጠመኝህ የብዙዎችን የሚመስል ነው ፡፡ አሁንም በረከቱ አይለይህ ፡፡ ከእኔም የተሻለ ክርስትና እንዳለህ ተመልክቻለሁና ፤ በርታ ፤ አንዳንዶች እንዲህ እንደ ቀልድ የተናገሩ መስለው ፣ ላይመለሱ ያመለጡ ወዳጆቻችን ስላሉ ፣ ከገጠመኜ ስላስጨነቀኝ ነበር ውትወታዬ ፡፡

   ስለቃልህ አንተንም በጣም አመሰግናለሁ

   Delete
  11. ጠንክረህ በማግኘቴ ፣ ከደስታዬ ብዛት ሁሉንም ሳልፈትሽ የሆነች የምስጋና መልዕክት አስተላለፍኩ ፡፡ አሁን ደግሞ ካስቀመጥክልን አድራሻ የተረዳሁትን ለማለት በድጋሚ ተመልሻለሁ ፡፡

   1. በአንደኛ ተራ ስለተመዘገበው ፡- በዚህ አድራሻ ያለውን ተመልክቼው ፣ አንተን ለማሳመን የአስማትና የመጥፎ መናፍስት ሥራ እንዳለ ከመሰከረ በኋላ መፍትሔ ሥራይ በሃምሳ ዶላር ግዛኝ ይልሃል ፡፡ የምትገዛቸው ነገሮች ደግሞ አንተን ወደ ጣዖት አምላኪነት የሚያሸጋግሩ መሪጌታ እየፈሩ የጻፉትን የመቁጠሪያ ንግድ የመሰለ ነገር መሰለኝ ፡፡ የተጻፈ ምናልባትም የማታውቀው የመናፍስት ጸሎት ግድግዳ ላይ ስለተሰቀለ አንተን የሚጠብቅበት ኃይል ፣ ካላመንክበትና በልብህ አድርገህ ካልጸለይከው ከየት የሚመነጭ ነው ? በቁጥር 4ዐ የዕጣንስ እንጨት ማጠን ልምምድ ምን ይባላል ? የቸገረው እርጉዝ ያገባል የሚሉት እንዳይሆን ተጠንቀቅ ፤ ለእኔ ግን ብልጦች የሰውን ገንዘብ ለመቃረም የሚፈጥሩት ብልሃት ነው ፡፡
   2. በሁለተኛ ተራ ያቀረብከውም ሃይማኖትክን ሊያስቀይርህ የሚጋብዝ ነው ፡፡ መላውን ለማንበብ አልታገስኩም ፡፡ ከላይ በጽሁፌ የድብርትና የጭንቀት መደምደሚያ ብዬ እንደገለጽኩት ውስጥ ለእንደዚሀ ዓይነት ርምጃም ያደፋፍራል ፡፡ እኔ እፈውስሃለሁ የማይል ከቃልቻ ያልተናነሰ ሰባኪ በየትኛውም ሃይማኖት የለም ፡፡ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ፡፡ ለማዳን የመቃብር አፈር ያስበላሉ የሚል ሁሉ ሰምቻለሁ ፡፡ በእርም የመዳን ቋንቋ ለእኔን በምንም መንገድ አይገባኝም ፡፡
   3. በሦስተኛ የተቀመጠውም የርኩስ መናፍስት ጥሪ ልምምድ ነው ፡፡ ነገሩ እውነት ባይሆን እንኳን የሰውን አእምሮ ስላጠበ ወይም ስለለወጠ የርካታ መንፈስን ሊፈጥር ይችላል ፡፡ ይህም ለእኔ የሳኮሎጂ ጨዋታ ነው ፡፡ የመጸዳጃ ወረቀት ራሱ የተፈጠረው በቅርብ ዘመን ነው “Joseph C. Gayetty of New York started producing the first packaged toilet paper in the U.S. in 1857.” ይላል በጉግል ያገኘሁት መረጃ ፡፡ እናም ዘመን አመጣሽ የብልሆች ልምምድ ነው ማለት ነው ፡፡
   ስለዚህ ወንድሜ አሁንም የምመክርህ ሁሉንም ችግርህን ለእግዚአብሔር አሳልፈህ እንድታስረክብ ነው ፤ በርትተህ ጹም ፤ ጸልይ ፤ የማታሸንፈው ጠላት ፣ የማትወጣው ምንም ዓይነት ችግርና መከራ አይኖርም ፡፡ ሁሉም ቢሆን በስሙ የተገዛ ነው ይለዋልና መጽሐፋችን ፡፡
   ይኸን ስል ግን የመንፈስ ጐታቾች የሉም ማለቴ አይደለም ፡፡ የሰለጠኑት አገሮች ወንጀል መርማሪዎች (አባ ዲናዎች) ከሠላሳ እና አርባ ዓመት በፊት የተፈጸመ የወንጀል አሻራን የሚያገኙት ፣ በነዚህ ግለሰቦች እገዛ ነው ፡፡ ጥበባቸውን እንደ አገራችን ጠንቋይ መሳዮች ለካቲካላ መጠጫና ለእንጀራ ሥራ ስለ አላዋሉት ብዙ ጊዜ ለመሥራት ፈቃደኛ አይደሉም ፡፡ ምክንያቱም በመንፈስ በሚሆኑበት ጊዜ በትግል እጅግ ስለሚጐዱና ፤ የሚያዩትም የወንጀል ዓይነትና የተፈጸመ ሥቃይ ፣ ወንጀል በገሃድ ከነቦታውና ከነሰዓቱ ጭምር ስለሆነ በአጭር ጊዜ ከአእምሮአቸው ስለማይጠፋላቸው ነው ፡፡ ስለዚህም በዓመት ቢበዛ ከሦስት ጊዜ በላይ በዚህ ሥራ ላይ አይሠማሩም ፡፡
   ቴሌፓቲ የሚባሉት ደግሞ ያለ አንዳች የመሣሪያ እገዛ ፣ አገርና ወንዝ በመንፈሳቸው ተሻግረው የሚደረገውን በግልጽ የሚረዱ ጠበብቶች ናቸው ፡፡ እነርሱ ፈልገውት እንዲያ ይሁኑ ወይም የተሰጣቸው አላውቅም ፡፡ ይህ ችሎታ ያለውን ሰው ባገኘው ለመፈተንና እውነትነቱን ለማረጋገጥ እመኝ ነበር ፡፡ በወሬ ከመስማት ውጭ ፣ በአካል ግን አንድም ጠቢብ አላጋጠመኝም ፡፡ በወሬ መሆኑም መሰለኝ በጥርጣሬ እንድመለከተው የሚያደርገኝ ፡፡ ሌላውም የሚከለክለኝ ደግሞ እምነቴ ነው ፡፡ በተቻለኝ ሁሉ የተዳቀለ እምነት እንዳይኖረኝ ስለምጠነቀቅና ስለምፈራ ላለመቀበል እታገላለሁ ፡፡ እግዚአብሔርም ፍርሃቴን ስለሚያውቅ አላጋለጠኝም ፡፡
   በተረፈ ክብደትህ የሚያስቀናኝ ነው ፤ ጨመርኩ ብለህ ሳይሆን ፣ መግለጽ የነበረብህ ደስ ብሎኛል አሁን ተስተካክያለሁ ፣ ሰውን መሰልኩ በማለት ነበር ማስቀናት ያለብህ ፡፡ እኔ 1ዐ5 ኪሎ እመዝናለሁ ቁመቴ 178 ሴሚ ነው ፡፡ ይኸን ክብደት ይዤ ግን በሳምንት ሦስት ቀን በሰዓት 12 ኪሎሜትር እሮጣለሁ ፡፡ በእድሜዬ ካሉ ሰዎች በፍጥነት ሁለተኛ ነኝ ፡፡ ህንዳዊው የማራቶን አንበሳ ይቀድመኛል (ትንሽ ለራሴ ሞራል መስጠቴን አስብ)፡፡ በሽታ የሚባል ነገር አልተመዘገበብኝም (የእኔን ክብደት ቢይዝ ኃይሌም እንኳን አይቀድመኝም እላለሁ ፤ ሊወዳደረኝ ከፈለገ ፣ የክብደታችንን ልዩነት በከረጢት የሚሸከም ከሆነ ለመወዳደር ፈቃደኛ ነኝ) ፡፡ ያሸነፈ አንድ ኪሎ ሜትር ተሸክሞ ይሄዳል ፡፡

   በበረከት ያለህ ሰው ነህና ፣ ፈጣሪአችንን እያመሰገንን በረከታችንን እናጣጥም ፡፡ ሁሉን ጭንቀት ፣ ፍርሃት ፣ ሃሳብ ፣ ችግር ፣ መከራ ፣ ጥርጣሬ ፣ ፈተና ሁሉ እርሳው ፡፡ ያለችን በጣም አጭር ዘመን ስለሆነች በተቻለህ በአግባቡ ተጠቀምባት ፡፡ በአዲስ መንፈስ አዲስ ሰው ሁነህ በእምነት ተገኝ ፤ እስከዚህ ያደረሰህ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ያግዝሃል ፡፡

   ሰላም ሁንልኝ

   Delete
  12. ለምዕመን
   ዌብ ሳይቶቹን የጠቀስኩት እኔን ካጋጠሙኝ ችግሮች ጋር ተመሳሳይ ስለሆኑብኝ ነው፤
   http://www.saulat.com/29.htm ይህንን ዌብ ሳይት የጠቀስኩልህ ማታ በር ዘግቼ ከተኛሁ በኃላ ደስ የማይል /የቁጣ የሚመስል/ የሰው ደምጽ /ድግምት/ ብዙ ጊዜ እሰማለሁ፡፡ ይህንን የመሰለ ድምጽ አንዳንድ ጊዜ ምሽቱ ሊነጋጋ ሲል እሰማለሁ፤ በቤት ውስጥ ምንም ስራ ለመስራት አለመቻል/የድካም ስሜት/Negative energy/፤ ማንኛውንም ስራም ሆነ ትምህርት ጀምሮ አለመጨረስ ወይም ገና ከመጀመሬ በፊት የሄ ለእኔ አይሆንም/አይሳካልኝም/Bad Lack/ ብሎ ማሰብ ወይም ማመን…….ወዘተ እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ስለሚያጋትሙኝ ነው
   http://wiki.answers.com/Q/What_are_the_symptoms_of_black_magic ይህንን የጠቀስኩት በክፉ መናፍስት የጠቁ ሰዎች የሚስተዋልባቸው ምልክቶች ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ በእኔ ላይ የተመለከትኩት በጥቂቱ ከዚህ በታች የተጠቀስኩት ናቸው፡፡
   Feeling anxiety
   Starts hating your self
   You have fear in your heart
   Feeling tired without any reason
   Become lazy. and sleep for longer durations
   You have all the happiness in life but still you don't feel happy.
   You don't wish to offer prayer and day by day you go away from religion
   Back-ache or has pain in kidneys
   Get scared in dreams. Sometimes sees snakes, spiders, lizards, and cockroaches in dream
   http://www.spellsofmagic.com/spells/life_spells/revenge_spells/12165/page.html ይህንን የጠቀስኩት እህቴ እኔን እበቀለዋለሁ እያለች ታወራ ነበር፤ ቤተሰብ በሙሉ ምናልባለት እኔና እህቴ ከተጋጨን በፖሊስ ታሲዘዋለች/ታሳስረዋለች/ ብለው ነበር የገመቱት እንጂ ማንም ሰው ይህን ክፉ መንፈስ ተጠቅማ እንዲህ ታደርጋለች ብሎ አልገመተም፡፡ ይህንን ዌብ ሳይት ባየሁ ቀን ማታ ከስራ ወጥቼ ቤት ወንድሜን አገኘሁት እና ነገርኩት….እርሱም ለእነርሱ ነገራቸው መሰለኝ ከዚያን ቀን ጀምሮ ይህንን ዘዴ መጠቀም ተዉ……በአሁኑ ሰዓት በሌላ ዘዴ በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡
   ከላይ ከጠቀስኩት ሌላ ቤተሰብ ይህንን ክፉ ስራ እንደሚሰሩ ትልቅ ምስክር የሆነኝ እህቴ ከእኔ የመሸሽ ዓይነት ባህሪ ማሳየቷ ነው፤ እሷ ከእኔ የምትሸሽበት ምንም ቅራኔ በመሀከላችን የለም፤ሌላ ጸብና ክርክር ይቅርና ለምን እንዲህ ታደርጊያለሽ ብዬ እንኳን አልጠየቅኳትም፤ ከዚህ በፊት በደረሰብኝ ነገር እንዲሁ ዝም ብዬ አለቅስ ነበር እንጂ ምንም ግንዛቤ አልነበረኝም፤ ነገር ግን ከላይ የጠቀስኳቸውን ዌብ ሳይቶችንና ሌሎች ጽሁፎችን ሳነብ ሁሉም ነገር ግልጽ እየሆነልኝ መጣ፡፡
   ወንድሜ ጎጃም ላይ ነዋሪ ነበረ እና የጎጃም ጠንቋዮች እርስ በእርስ ሲጣሉ በመብረቅ ነው የሚደባደቡት ብሎ ትንሽ አጋኖ ሲነግረኝ ባክህ ውሸት/ተረት/ ነው እያልኩ እስቅበት ነበር፤ አባቴም በልጅነቱ ገጠር ሰው ሞቶ በቀብር ሰዓት አካባቢ ዝናብ እየዘነበ ካስቸገረ ጠንቋይ ተጠርቶ ደመናውን እንደሚያባረው አጫውቶኝ ነበር፤ ይህ የሚያሳየን እኛ ክርስትያኖች በመንፈስ የሚዋጉን ጠላቶች እንዳሉብን ነው፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጸባችን ከስጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከጨለማው የመናፍስት ሀይል ጋር ነው በማለት በትክክል ገልጾታል፡፡
   እኔ የመናፍስትን አሰራር ለመመርመር ፍላጎቱ የለኝም ግን ከደረሰብኝ ችግር የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስንና አንዳንድ ጽሁፎችን አንብቤ የተረዳሁት ነገር ቢኖር አንተ እንዳልከው በክርስቶስ ኢየሱስ ማመን፤ ማመን ብቻ ሳይሆን እምነቱንም በተግባር መግለጥ የሰውን ልጅ ሁሉ ከማንኛውም ዓይነት የክፉ መንፈስ አሰራር ይጠብቀዋል የሚል እምነት አግኝቻለሁ፡፡
   ደጀ ሰላም ብሎግ ላይ ችግሬን ስለተነፈስኩ ነው መሰለኝ አሁን ትንሽ ቀለል ብሎኛል
   መዕመን ስለመልካም ምክርህ ከልብ አመሰግናለሁ
   ማሙሽ ነኝ

   Delete
  13. ሰላም ማሙሽ ፤ መደማመጥ ስለቻልን ቤተሰብ እየሆንን መሰለኝ

   ከላይ በጽሁፍህ ከእኔ በስተቀር ቤተሰቦቼ በሙሉ ፕሮቴስታንት ናቸው ብለኸናል ፡፡ ይኸ አባባልህ የእህትህን እምነት የሚጨምር ከሆነ ፣ እንዴት ወደዚህ ክፉ ልምምድ አመራች ? ወይንስ የይስሙላ ኘሬቴስታንት ነች ማለት ይሆን ? እስከ ዛሬ የነርሱን አምልኮ የማልቀበለው የዶግማ ልዩነት ስላለን ነው እንጅ በአባይ ጠንቋይ ጥበብ ውስጥ የገቡ በመሆናቸው አልነበረም ፡፡ የነርሱ ከጥንቆላ ያልተናነሰ ማታለያ ፣ ስሜታዊ ሆነው ተከታይ ለማፍራት የሚሠሩተ ቲያትር መሰል የመድረክ ወይም የጉባኤ እንቅስቃሴ ነው ፡፡ አሁንም እውነተኛ አማኝ ከሆነች በአለቃቸው ወይም በደንብ በሚቀርባት የነሱ እምነት ተከታይ በኩል ብታስመክራት ፣ እርስ በርሳቸው በጣም ስለሚፈራሩ እርግጠኛ ነኝ ከምግባሯ ትታቀባለች ፡፡
   ለሰዎች ችግርህን በማካፈል የጤና ለውጥ በማግኘትህ በጣም ደስ ብሎኛል ፡፡ አሁንም ግን ጥርጣሬንና ፍርሃትን ሙሉ በሙሉ ከላይህ ማስወገድ ይጠበቅብሃል ፡፡ በእምነት ሆነህ ከጸለይክ የማይቻል የለም ፡፡ የጎጃም አባይ ጠንቋይ የጠላ ሻጯን ልጅ ሁሉ እንጀራው ቤተ መንግሥት ፣ ዳኛና ጄኔራል እያለ ጠላና ካቲካላውን በነጻ ሲጠጣ ነው የኖረው ፡፡ አንድ ጓደኛዬ የመስተፋቅር መፋቂያ ገዝቶ ድዱ እስከሚቆስል ፍቆም የሚመኛትን ልጅ አንድ ቀን እንኳን ሰላም ሳይላት ፣ በቅርብ እንደተከታተላት እያለ ትዳር ያዘችበት ፡፡ የምታምንበት ነገር ከሆነ ምናልባት ሊሠራ ይችል ይሆናል ፡፡ ምክንያቴም የአዲስ ቅዳሙን አሥራትን ገንዘብ እርሱ አስገኘልን ብለው የሚያመልኩ ቱጃሮች ስለ አሉ ነው፡፡ እንግዲህ የአገሩን ሃብታም ሁሉ ርሱ በጥበቡ ያክብረው ወይም አጋጣሚ የፈጠረው መለየትና መመስከር አልችልም ፡፡ ነገር ግን ሰውን ሁሉ ሃብታም ማድረግ የሚያስችል ብልሃት ካለው ፣ ለምን ከዓለም አንደኛ ባለጸጋ እስከሚባል ያገሪቱን ሃብት ሁሉ የራሱ አያደርግም ነበር የሚል ጥያቄ ሳቀርብ ፣ ነገሩ ውሸት ነው የሚለውን እንድቀበል ያስገድደኛል ፡፡ ምክንያቱም ከአገር አገር ገንዘብ ለማግኘት ሁሎችም ሲሯሯጡ ስለምታያቸው ነው ፡፡

   በተረፈ በ.... እፈውሳለሁ ብሎ የደረደራቸውን የመሰለ ፣ ከሞላ ጐደል በሚከተለው አድራሻ ለተጨማሪ ዕውቀት ያህል ተመልከት ፡፡
   http://www.mayoclinic.com/health/depression/DS00175/DSECTION=symptoms

   Delete
 4. ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደምናየው እስራኤልም እንኳ እንደ ሕዝብ
  ለእግዚአብሔር ራሳቸውን የሰጡ ታዛዥ ሕዝብ ሆነው አያውቁም።
  እንዲህ ለመሆን የተጠጉበት አንድ ጊዜ ቢኖር በሲና ተራራ ግርጌ
  የነበሩባት ያቺ ሕጉ የተሰጠባት ወራት ናት። ያም ቢሆን ለአጭር
  ጊዜ ብቻ ነበር። የማይታዘዘው እልከኛ ልባቸው ያላመነው
  ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ በጺን ምድረ በዳ ለ38
  ዓመታት እንዲንከራተቱ አደረጋቸው። ወደ ከነዓን መግባታቸውም
  ታማኞችና የተለዩ፥ የተባረኩና የተቀደሱ አላደረጋቸውም። አልፎ
  አልፎ እዚህና እዚያ ከነበሩ መነቃቃቶች በስተቀር ጠቅላላው
  መልካቸው ሃይማኖታዊ መልክ ያለው ይሁን እንጂ ታማኝነት
  የጎደለው ሕዝብ መሆናቸው ነው። እስራኤልም እንኳ ዓመጸኛ
  ሕዝብ ነበሩ። ሆኖም እስከ አዲሱ ኪዳን ድረስ የእግዚአብሔር
  ሕዝብ ሆነው ተጠርተዋል። በዚህ ዘመን የጌታ ሕዝብ
  እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን
  በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ
  ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ የተባለው ሕዝብ ነው፤ 1ጴጥ.
  2፥9። በዚህ ዘመን የጌታ ሕዝብ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን
  የተጠራውና የጠሪውን በጎነት የሚናገረው ሕዝብ ብቻ ነው።ኢትዮጵያዊ ወገናችንን ለመርዳት የምንፈልግ ሁሉ ወንጌልን እንስበክ፤ ለነጻነት፤ ለልማት፤ ለዲሞክራሲ፤ ለፍትሕ እንታገል። ሕዝባችን በመናፍስት ጠሪዎች እጅ ስለወደቀ በረከት ርቆት በችግር ላይ ይገኛል። ነጻ የሚያወጣን የይሁዳ አንበሳ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው።source...http://mekrez.org/books/ezra/%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8A%93.pdf

  ReplyDelete
 5. ምነው በየሱስ ስም የሚነግዱትን በየአዳረሹ የሚገኙትን ነብይ ነን ባዮቹን ጠንቋዮች እረሳችኋቸው ታዲያ??

  ReplyDelete
 6. ሰይጣን
  ሲሆንለት ማታለል ሳይሆንለት ሲቀር ማሳደድ ይጀምራል። ከሁለት
  አንዱ ብዙ ጊዜ ይሠራለታል። ለሰነፎች ማታለልና መሸንገል
  ይሠራለታል። ለፈሪዎች ደግሞ ማሳደድ ይሠራለታል።

  ReplyDelete
 7. ራሳችንን ከጥንቆላ ስራዎች ለመጠበቅ ወይንም ሳናውቅ የጥንቆላ ስራዎች ተባባሪ ከመሆን ለመዳን ስለ ሀገራችን የጥንቆላ ዘዴዎች መጠነኛ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል። በዘመናዊው ካሪዝማዊ እንቅስቃሴ ውስጥ manifestation እየተባሉ የሚጠሩ ልምምዶች የዚህ ሁነኛ ምሳሌዎች ናቸው።
  Manifestation ለሚለው ቃል የአማርኛ አቻ ስላላገኘሁለት ነው እንዳለ የተጠቀምኩት። ቃሉ በዐይን የሚታዩ፥ በጆሮ የሚደመጡና በሰውነት የሚገለጡ
  ወይም አካላዊ በሆነ ሁኔታ የሚደረጉ ትዕይንቶችን ምንነት የሚገልጥ ነው።
  እነዚህ ትዕይንቶች በአንድ ቦታ በአንድ ወይም ጥቂት ሰዎች ተከስተው የሚያልፉ ልምምዶች ሳይሆኑ የሚሰነብቱና የሚከርሙ እንዲሁም በርካታ አማኞችን
  የሚነኩ ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየመጡ ከሄዱትና ካሉትም መካከል ጥቂቶቹን ልጥቀስ።
   በጉባኤ ውስጥ እንደ አራዊትና እንደ እንስሳት መጮኽ። እንዲህ የሚያደርጉት ነገሩን መንፈሳዊ ሲያስመስሉት እንደ ውሻ ከጮኹ አውሬ ማባረራቸው፥
  እንደ አንበሳ ካገሱ ጠላትን ማስደንገጣቸው እንደሆነ ይነገርላቸዋል። ዱሮ እንዲህ የሚያደርጉ ተወስደው ይጸለይላቸው ነበር። አሁን እንደ ጤናማ
  ይታያሉ። ይልቅስ የነሱን ጤንነትና መንፈሳዊነት የሚጠይቁት አጋንንት እንዳለባቸው ይጠረጠራሉ። ይደንቃል።
   ማማጥ። ይህ በ90ዎቹ መጨረሻ ከቶሮንቶው ንቅናቄ በኋላ የተጀመረ ትእይንት ነው። በዚህ ልምምድ ሰዎች (ወንዶችንም ጨምሮ) ወገባቸውን ይዘው
  ተንበርክከው ወይም ተጋድመው ልክ ነፍሰ ጡር ሴት ልትወልድ እንደምታምጥ በመጮኽ፥ በማቃሰት፥ በመወራጨት፥ በወሊድ ሂደት ውስጥ ያልፋሉ።
  ይህን የሚያስደርጉ ሰባኪዎችም እነዚያ ሰዎች አንዳች መንፈሳዊ ነገር ወይም ሰው እየወለዱ እንደሆኑ ያስረዳሉ። የምንም ነገር የልደት ወረቀት ወይም
  የመውለዳቸው ማረጋገጫ ተሰጥቶአቸው ግን አያውቅም።
   ቅዱስ ሳቅ። ይህ ያለ ማቋረጥ እየተንከተከቱ ለረጅም ጊዜ መሳቅ ነው። ስብከት መሃልም ሊሆን ይችላል፤ ለሳቁ ሲባል ስብከቱ ቢቋረጥም ምንም
  እንዳልሆነ ይቆጠራል። ይህ ልምምድ አንድ ወቅት የዘመኑ የካሪዝማዊነት ፋሽን ሆኖ በብዙዎች ዘንድ እየተሰበሰቡ ጥርስ የማስጣት ነገር ሆኖ ከረመ።
   መገንደስ። ይህ ከሌሎቹ ቆየት ያለና አሁን ቀነስ ቢልም ጥቂት ባልሆኑ ካሪዝማውያን የሚደረግ ልምምድ ነው። ወደ ፊት የተጠሩ ወይም ሊጸለይላቸው
  የመጡ ሰዎች በትንፋሽ፥ በጣት፥ በልብስ፥ በመዳፍ እየተነኩ ወይም በጣት ማመልከት ወዘተ እንደ ዛፍ ይገነደሳሉ። ከአወዳደቃቸው የተነሣ
  ተደጋግመው የደረሱ አደጋዎች ስላሉ ሲወድቁ የሚደግፉና እርቃን የሚሸፍኑ አጋፋሪዎች የሚማስኑበት ልምምድ ነው።
   የማይተረጎም ልሳን። ይህ ተናጋሪው የማይተረጉመው፥ ሌላም የማይተረጉመው ምን እንደተባለ ማንም የማያውቅበትና ስለዚህም የማይታነጽበት ልሳን
  ብዙዎች በሚገኙበት የመናገር ልምምድ ነው። በ1ቆሮ. 12-14 ስለዚህ በግልጽ ቢጻፍም የተጻፈውን ከመታዘዝ በልምምድ መታገዝ አይሎ ሲገዛ ይታያል።
  እነዚህ የውሸት ፈውሶችን፥ የማይፈጸሙ ትንቢቶችን፥ የግምትና መላ-ምት ‘መገለጦችን’ነብይ ነን ባዮቹ = ጠንቋዮች ናቼው ።

  ReplyDelete
 8. ሰይጣናዊ አሰራሮችን ለማጋለጥ ጌታ እየተገለገለባችሁ እንደሆነ አምላለሁ ፡፡ እዉነተኛ የጌታ አገልጋይ እንዲህ ነዉ ፡፡ በርቱ በሰፊዉ የሰይጣንን ሴራ አጋልጡ ፡፡ ወደ ኋላ አትበሉ ፡፡ የማንንም ትችት አትፍሩ ፡፡

  ReplyDelete
  Replies

  1. አለሚቱ እባላለሁ ፦ስለ አጥማቂው ግርማ በሚቀጥለው አቀርባለሁ ብለው ነበር እኔም በጣም ለማወቅ ስለጓጓሁ እባካችሁ አሳውቁኝ ቤተሰብ በጣም ሳላስቸገረኝ ነው በጣም አመሰግናለሁ።

   Delete
 9. KEHULUM BELAY YEDAWITIN MEZIMURE TSELYE

  ReplyDelete
 10. i want to use magic for poetical revenge like prominent leaders in ethiopia

  ReplyDelete
 11. ውድ አዘጋጆች እንዲሁም
  ውድ ተከታታዮች
  የውበት ማጣት ችግሬ ከበደ
  ሁሉን ነገር እጅጉን ከፈጣሪ የተሰጠሁም ቢሆን የመልኬ አስቀያሚነት በህይወቴላይ ምንም አይነት መልካም ነገርን ማግኜት እንዳልችል ለከባድ መከራና ስቃይ ተጋላጭ እንድሆን አስገድዶኛል።የብዙሀን ሰወች አመለካከት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ውበት ላይ ያመዘነ ይሆንብሀል።ብዙ መልካምና ትልቅ ነገሮች ውስጤ ላይ ያሉ ቢሆንም ይህንን አቅምና ብቃቴን ለማውጣት በቅድሚያ ለማገኛቸው አጋጣሚወችና ግንኙነቶች ላይ ዋናው ቁልፍ ጉዳይ ውጫዊ ፐርሴፕሺን እጅግ ከባድ ተግዳሮት ሆኖብኝ ይገኛል።
  የመፅሀፉን ይዘትና ውስጥ ከመታየቱ በፊት ውጫዊ ከቨሩ እየታየ ወደ ዋናው ጉዳይ እንዳይገባና እንዳይገለጥ ሆነ ይሉት አይነት ነገር ሆኖብኝ እጅግ ተቸግሬ እገኛለሁ።
  የሚሰጡህ ውጫዊ ግምት በጣም ተፈታትኖኝ ብዙ ጊዜ ለውድቀት የተዳረኩበትን እውነታ እየፈጠረብኝ እጅግ ምርር ብሎኝ እገኛለሁ፤ከሰውም መሸሽን የምመርጥበትን ሁኔታ አስገድዶኛል።እናም በዚህ ረገድ ምናልባት ከሰው ልጅ መፍትሄ አይጠፋም እና ምን ትመክሩኛላችሁ ለማለት ነው፤ እጅግ አመሰግናለሁ።

  ReplyDelete
 12. I visited various web pages however the audio feature for audio songs
  current at this website is in fact excellent.

  ReplyDelete