Thursday, January 17, 2013

ቤተ ክርስቲያን እንደ ተከፈለች ልትቀጥል ነው? ወይስ ሌላ እድል ይኖራት ይሆን?

 • በስደት ያለውና በ 4ኛው ፓትርያርክ የሚመራው ሲኖዶስ በዚህ ሳምንት በሎስ አንጀለስ ከተማ ስብሰባ እያካሄደ ነው። መግለጫም ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ብዙዎች የተጀመረው እርቅ ሰምሮ ቤተ ክርስቲያን እንድ ትሆናለች ብለው ተመኝተው ነበር፡፡ እርቁ እንደማይሰምር ግን ከአያያዙ ያስታውቅ ነበር፡፡ የአገር ቤቱ ሲኖዶስ እርቁ በሂደት ላይ እያለ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ እርቁን እንዳልፈለገው ገና ከማለዳው ግልጽ አድርጓል፡፡ ጉዳዩ ነገሩን ይበልጥ አጋግሎት ሰንብቷል፡፡ በትናንቱ መግለጫ ላይ እንደተተቀሰው እስካሁን ለተፈጠረው ችግር አቡነ መርቆሬዎስንና አብረዋቸው ያሉትን ጳጳሳት ብቻ ተጠያቂ ማድረግም እርቁ ወደፊት እንዳይቀጥል እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚለው የብዙዎች ግምት ነው፡፡
 
በሌላ በኩል ለአቃቤ መንበሩ ስልጣን ክብር ባለመስጠትና ባለመታዘዝ ቤተ ክህነቱ ጥቂቶች ያሻቸውን የሚያደርጉበት ባለቤት የሌለው ቤት መስሎ ከርሟል፡፡ ከእርቁ ጋር በተያያዘ ጳጳሳት በሀሳብ ተከፋፍለው ሲራኮቱና ሁሉም እርቁን ተገን አድርገው የራሳቸውን ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህም እርቁን የማይፈልገውና እርቁን ለፖለቲካዊ አጀንዳው ሲጠቀምበት የቆየው ማህበረ ቅዱሳን አንዱ ነው፡፡

የአዲስ አበባው ሲኖዶስ ከአንገት በላይ የጀመረው የእርቅ ሂደት ለእርቁ እንቅፋት የሆነው የፓትርያርክ ምርጫ አጀንዳ፣ 6ኛውን ፓትርያርክ ለመሾም በመወስንና የአቡነ መርቆሬዎስን ወደ መንበራቸው መመለስ በመቃወም ተደምምድሟል ማለት ይቻላል፡፡ ሁኔታው ቤተ ክርስቲያን እንደ ተከፈለች ትቀጥላለች ወይስ ሌላ እንድ የምትሆንበት እድል ይፈጠር ይሆን? የሚለው አሁን ላይ ቆመን ለመመለስ የማንችለው ጥያቄ ሆኗል፡፡

በአገር ቤት መንበሩ በዐቃቤ መንበር እየተመራ ቢገኝም ጳጳሳቱ አቃቤ መንበሩን ከቁብ ባለመቁጠርና በሥልጣናቸው ምንም እንዳያደርጉ በማድረግ ለወራት ቤተ ክህነቱ ውስጥ ስርአተ አልበኝነት ሰፍኖ ቆይቷል፡፡ ማን አለቃ ማን ምንዝር መሆኑ ሳይታወቅ አጋጣሚው የረዳቸው ጥቂት ደፋሮች እንዳሻቸው ሲሆኑ፣ በአቃቤ መንበሩና በሥራ አስኪያጁ መካከል መደማመጥ ጠፍቶ እስከ መኳረፍ የደርሰ ጠብ ውስጥ ገብተው ይገኛሉ፡፡ ሁለት ጊዜ በቋሚ ሲኖዶስና በG8 አማካይነት እንዲታረቁ ለማድረግ ቢሞከርም መግባባት እንዳልቻሉ ነው ምንጮች እየተናገሩ ያሉት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ምክትል ስራ አስኪያጁ ተስፋዬ ውብሸትና እስክንድር በአቃቤ መንበሩ ላይ ካመጹትና ህገ ወጥ ስራዎችን እየሰሩ ከሚገኙት መካከል ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተደማምረው አቃቤ መንበሩ እንደ አቡነ ጳውሎስ ነገሮችን መሸከም ስላልቻሉና ነገሩ ወዳላስፈላጊ አቅጣጫ እንዳያመራ በሚል ጉዳዩን ለመንግስት በደብዳቤ አሳወቁ፡፡

አቡነ ጳውሎስ ስንቱን ጉድ ተሸክመው ነበር? የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ እርሳቸው ይህን ሁሉ ጉድ ተሸክመው በዝምታ ከመቀመጥ በቀር እዚህ ግባ የሚባል እርምጃ ባለመውሰዳቸው እንደ ማቅ ያሉት እንዳሻቸው ለመፋነን ሰፊ እድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ብዙዎች ዛሬ አቡነ ናትናኤል በአቃቤ መንበርነታቸው የወሰዱትን ይህን እርምጃ አቡነ ጳውሎስ ቀደም ብለው ወስደው ቢሆን ኖሮ ነገሮች ይቀየሩ ነበር ብለው ይገምታሉ፡፡ ነገር ግን እርሳቸው ማንም ላይ ደብዳቤ አልጽፍም በሚል ነገሮችን በዝምታና በቸልታ በማለፋቸው ራሳቸውንም ጎድተዋል ለቤተ ክርስቲያንም አልጠቀሟትም፡፡

በአሁኑ ወቅት አቡነ ናትናኤል ቤተ ክህነት ውስጥ የሰፈነውን ስርአተ አልበኝነት መንግስት እንዲያስታግስ ለመንግስት በጻፉት ደብዳቤ መነሻነት ቤተ ክህነቱ አንጻራዊ መረጋጋት እየታየበት ነው ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ ደብዳቤው በተለይ አላሰራ ያለኝ ቡድን አለ ባሏቸው ጳጳሳትና አንዳንድ የቤተክህነት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል፡፡ ቡድን ተባለው የወሎ ጳጳሳት ቡድን መሆኑን የሚናገሩት ተንታኞች አንዳንድ ባለስልጣናት የተባሉት ደግሞ እነተስፋዬ ናቸው ይላሉ፡፡ አቃቤ መንበሩን አላሰራ ብለው ከፍተኛ ጫና ውስጥ የከተቷቸው እነዚሁ ክፍሎች መሆናቸውን ምንጮቻችን ይናገራሉ፡፡ አባ ህዝቅኤል ስብሰባ ረግጠው በመውጣት ራሳቸውን የገለጡ ሲሆን፣ የእነተስፋዬም መገለጫ ሩቅ አይሆንም እያሉ ነው፡፡

እነዚህ ተባብረው በአንድ በኩል ለእርቁ ትልቅ እንቅፋት የሆነውን የፓትርያርክ ምርጫ ወደፊት ሲገፉ ፕትርክናውን ወደራሳቸው ለመሳብ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ታውቋል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ ለአራት በተከፈለው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ የደቡብና የምዕራቡን ክፍል በሊቀ ጳጳስነት የሚመሩት አባ ህዝቅኤል በአቡነ ጳውሎስ የተሾሙ አንጋፋና ብዙ ልምድ ያላቸውን ተሰሚነትም ያተረፉ የሚባሉትን የደብር አስተዳዳሪዎች ለምሳሌ የቦሌ መድሀኔ ዓለም፣ የጊዮርጊስና የልደታ አስተዳዳሪዎችን በጡረታ ለማግለል ከነተስፋዬ ጋር ሴራ ሸርበው መንቀሳቀሳቸውና በአስተዳዳሪዎቹ በኩል ተቃውሞ ማስነሳቱን ለአቃቤ መንበሩና ለመንግስት ደብዳቤ እንዲጽፉ አስገድዷል፡፡ እንደ ምንጮቻችን ከሆነ አስተዳዳሪዎቹ በምርጫው ሂደት ላይ ድምጽ የሚሰጡና ተጽዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ ስለሆነ፣ እነርሱን አንስተው በሌሎች በመተካት ፕትርክናውን የእነርሱ ለማድረግ አልመዋል ነው የሚሉት፡፡ ከበስተጀርባ ማቅም የራሱን ሰዎች በአስተዳዳሪነት በማሾም ለጊዜው ፕትርክናው ላይ አሻራውን ለማሳረፍ ትግል ማድረጉን ያላቋረጠ ሲሆን፣ በሂደትም ከስር ወደላይ ለመምጣት በጡረታ በሚገለሉት አስተዳዳሪዎች ምትክ የሚሾሙት አዲስ ምልምሎች ለማቅ ሜዳውን እንዲያመቻቹለት አስቧል ነው የተባለው፡፡ ቀደም ብሎም ከአባ ሰረቀ መነሳት በኋላ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሃላፊ ሆነው የተሾሙትንና ማቅ ሆነው የተገኙትን አባ ህሩይን በአዲስ አበባ ደቡብ ሀገረ ስብከት ላይ ሌላውን ቀንደኛ የማቅ ሰው አባ ዮሐንስን  ደግሞ ምዕራብ ላይ ሥራ አስኪያጅ አድርገው ያሾመውም ማቅ እንደሆነ ምንጮች ይናገራሉ፡፡

አቡነ ናትናኤልን “ከእኛው ጋር ናቸው” በማለት ማቅና በጊዜው ሁሉን እኛ ነን የምንቆጣጠረው ብለው በማቅ ደላላነት የG8 አባላትና የወሎ ጳጳሳት ቡድን አቃቤ መንበርነቱን ቢሰጧቸውም ሁሉም ዛሬ ላይ ጥርስ ነክሶባቸዋል፡፡ ማቅ አለኝ የሚለውን ዋና ጉዳይ አስፈጻሚውን ማንያዘዋልን በደብዳቤ ያገዱና ቤተክህነት ግቢ እንዳይገባ ያስከለከሉትን እንዲሁም ለመንግስት ደብዳቤ በመጻፍ ትልቅ እርምጃ የወሰዱትን ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ቁጭ ብለው የሰቀሏቸውን ያህል ቆመው ለማውረድ አልቻሉም፡፡

በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኘው ቤተክህነት ወደ 6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ መግባቱ ለብዙዎች አልተዋጠም፡፡ አንዳንዶች እርቁን ሳይፈልጉ ስለ እርቅ ብዙ በማውራት ለራሳቸው ጥቅም ቢሯሯጡም የቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፍሎ መቀጠል ወደየት እንደሚያመራ አሁን ላይ ቆሞ መተንበይ ያስቸግራል፡፡ የአሜሪካው ሲኖዶስ ምን ይል ይሆን የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡ የአሜሪካው ሲኖዶስ በዚህ ሳምንት በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ስብሰባ እያደረገ ነው። የወቅቱን ጉዳይ አስመልክቶ መግለጫ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንደደረሰን ለአንባብያን እናቀርባለን።

እግዚአብሔር ቤተክርስቲያናችንን እንዲያስብ ሁላችንም እንጸልይ

4 comments:

 1. Who said Mahibere Kidusan can FULFILL its POLITICAL AGENDA under the UMBRELLA OF THE EOTC? THAT IS WHAT MK ARE DOING!!!

  Mahibere Kidusan is the political party that is destroying our mother church.

  ReplyDelete
 2. thank u Aba Selama. I know Ato Tesfaye and Ato Eskindir that they are working for MK. God is with His Church. There day for Judgement. Those who are working for the Church are being persecuted. I know this fact closely. Tesfaye and Eskindir Must leave the Church and go to Kebele becuase it is their place not the Church. They know nothing about the Church. But they are working for MK. May God be with us to solve this problem!

  ReplyDelete
 3. we do not see any good thing in the future for our church. too bad ,,,,,,,,,,,,,,,,

  ReplyDelete
 4. Pray as a christian and God will solve the problem.

  ReplyDelete