Monday, February 18, 2013

የፓትርያርክ ምርጫው ወዴት እያመራ ነው?

በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የተጀመረው የዕርቅ ሂደት ከተደናቀፈ ወዲህ የአዲስ አበባው ሲኖዶስ በብዙ ውዝግብ ተሞልቶ 6ኛውን ፓትርያርክ ለማስቀመጥ ወደ ጫፍ እየደረሰ ይመስላል፡፡ ሁሉም የየራሱን ፓትርያርክ ለማሰቀመጥ እየተራወጠ ባለበት በዚህ ወቅት ማህበረ ቅዱሳን የእኔ ያላቸውን ከአባ ማቴዎስና ከአባ ሉቃስ አንዱን ለማስቀመጥ የተቻለውን እያደረገ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የማቅ ድጋፍ እንዳይለያቸው ማቅን በጥንቃቄ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የቆዩት አባ ሳሙኤል የማቅ ድጋፍ የተለያቸው መሆኑ እየታየ ቢሆንም በራሳቸው መንገድ ከፍተኛ በጀት መድበውና ቀስቃሾችን አሰማርተው በከፍተኛ ሁኔታ እየሠሩ ይገኛል፡፡ በቀስቃሾቹ አማካይነትም ብዙዎችን የማሳመን ስራ እየሰሩ ነው ተብሏል፡፡ በዚህ በኩል የቅድስት ስላሴ ኮሌጅ ተማሪዎችንና የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ስራ አስኪያጆችንና የደብር አስተዳዳሪዎችን በተለያየ መንገድ በማሳመን ቀጣዩ ፓትርያርክ አባ ሳሙኤል ናቸው የሚል ነገር በስፋት እንዲወራ እየተደረገ ነው፡፡ በየሀገረ ስብከቶችም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ ይነገራል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ደግሞ ኦዲህ ባለ መንገድ ፓትርያርክ መሆን አይገኝም እያለ ነው፡፡ የአባ ሳሙኤል ስብእና ግን ለፓትርያርክነት የሚያበቃ እንዳልሆነ ከዚህ ቀደም ያወጣናቸው የተለያዩ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡
ቤተክርስቲያኗ 6ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ ደፋ ቀና እያለች ባለችበት በዚህ ወቅት ይህ ሁሉ ፉክክር ለዓለማዊ ሥልጣን እንጂ ለመንፈሳዊ ሥልጣን የሚደረግ አይመስልም፡፡ መንፈሳዊ ስልጣን ብዙ ሀላፊነት ያለበትና በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ብዙ ተጠያቂነት ያለበት ስልጣን መሆኑ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባውም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን የተደበላለቀና ግራ የሚያጋባ ሆኗል፡፡ በዚህ በኩል እንዲህ እየተሰራ በሌላ በኩል እግዚአብሔር የራሱን ሰው እንዲያስቀምጥ ጸልዩ የተባለው የምህላ ጸሎት እንዲያዝ እየተነገረ ነው፡፡ ይህም ለይምሰል እንጂ ልባዊ አይደለም፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የተጀመረው መከፋፈልና ሁሉም የየራሱን ሰው ለማስቀመጥና አንዳንድ ጳጳሳትም ፕትርክናውን ለራሳቸው ለማድረግ ከሚያደርጉት ትግል ጋር ተያይዞ በቀጣይ በአባቶች መካከል መከፋፈል እንዳይፈጠርና መቀባበል እንዳይጠፋም ትልቅ ስጋት አለ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በዚህ የስልጣን ትግል ውስጥ ስማቸው እየተነሳ ካለው ጳጳሳት መካከል እንደተባለው በማንኛውም መንገድ ይሁን ወደፕትርክና ቢመጡ ሊገጥማቸው የሚችለው ተግዳሮት ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ለይምሰል ሳይሆን ጌታ በትክክል ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ሰው በመንበሩ ላይ እንዲያስመቀጥ ከልብ መጸለይ ይገባል፡፡ እንደዓለማዊ ስልጣን እየተደረገ ያለው የምረጡኝ ቅስቀሳ ለቤተክርስቲያኒቱ በቀጣይ መጥፎ አርአያ ከመሆኑም በላይ ወደዚህ ስልጣን ለሚመጣው አባት ከባድ ፈተና እንደሚሆንበት አይጠረጠርም፡፡

1 comment:

  1. Please please leave this post with PDF

    ReplyDelete