Wednesday, February 20, 2013

አባ ሳሙኤል በምረጡኝ ዘመቻቸው ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠማቸው ነው

ለፕትርክና የምረጡኝ ዘመቻ ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሹመቱ መንፈሳዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ራስን ከማቅረብ ይልቅ የእግዚአብሔር ጥሪ  ያስፈልገዋል፡፡ የሚያገለግለው ህዝብም ይሁንታ ያስፈልገዋል፡፡ ለሹመቱም በትምህርትና በልምድና በምግባር ብቁ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ መንፈሳዊ ሹመት ያሰፈረው መመዘኛ እነዚህን ጉዳዮች ያካተተ ነው፡፡ 1ኛ ጢሞቴዎስ ምእራፍ 3ን ይመልከቱ፡፡ ከዚህ ውጪ በኃይል ወይም በሌላ ዘዴ ወይም እንደዓለማዊ ሥልጣን በምረጡኝ ዘመቻ ወደ መንፈሳዊ ስልጣን መምጣት ቢቻል እንኳን የዚያ ሰው የስልጣን ዘመን በችግሮች የተሞላ እንደሚሆንና ተቀባይነት እንደሚያጣ ብዙ መሰናክሎችም ከፊቱ እንደሚደቀኑበት ኃላፊነቱንም እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ መወጣት እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡
ዛሬ በሚዲያ ላይ ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆኖ ለመመረጥ አንዳንድ ከጳጳሳት መካከል እከሌ የምረጡኝ ዘመቻ ጀምረዋል ማለትን መስማት በእጅግ ያሳፍራል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክም ይህ ቤተክርስቲያኗ ትልቅ መንፈሳዊ ውድቀት እንደደረሰባት ትልቅ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል አጋጣሚ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በቀደሙት ዓመታት ብዙ ታላላቅና በዕውቀታቸውም በምግባራቸውም የተመሰከረላቸው መምህራን እንኳን ምረጡኝ ብለው በዘመቻ መልክ መቀስቀስ ይቅርና ለጵጵስና ሲታጩ ፈቃደኛ እንዳልነበሩና ሹመቱን ይሸሹት እንደነበር አንዳንድ በቃልም በጽሁፍም የሚነገሩ ታሪኮች ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ ዛሬ ግን ያ ተገልብጦ ብዙዎች ጳጳሳት ለመሆን የምንኩስናውን ዓለም እያጨናነቁት እንደሆነ ይታያል፡፡ ከጰጰሱትም መካከል ፓትርያርክ ለመሆን የምርጫ ህግን በልክ ከማሰፋት እስከ ምረጡኝ ዘመቻ የደረሰ ተጋድሎ እየፈጸሙ ያሉ አሉ፡፡

ዛሬ ረቡዕ የካቲት 13 ለንባብ የበቃው ሰንደቅ ጋዜጣ ያለብቃታቸው ቀጣዩ ፓትርያርክ ለመሆን የምረጡኝ ዘመቻ የጀመሩትን አባ ሳሙኤልን ኮንኖ ዜና ጽፏል፡፡ ጋዜጣው አባ ሳሙኤል
§  ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የቤተክህነት አመራሮችን፣ የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ስራ አስኪያጆችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በማግባባት ላይ ናቸው
§  ለምርጫው ዘመቻ ከፍተኛ ገንዘብ መድበዋል፤ ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ ብሩን እየረጩ ነው
§  ድምጽ ለሚሰጧቸው እና ከጎናቸው ለሚሆኑ ሰዎች ፓትርያርክ ሆነው ከተመረጡ በኋላ በተሻለ የኃላፊነት ቦታ እንደሚሾሟቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው የውጭ ዕድል እንደሚያመቻቹላቸውና ቤተክርስቲያኒቷ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በምታስገነባቸው ህንጻዎች ውስጥ የንግድ ቦታ እንደሚሰጧቸው ቃል እየገቡላቸው ነው፡፡
§  አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናትን አግባብቻለሁ መንግስትም ፓትርያርክ ሆኜ እንድመረጥ ይፈልጋል ብለዋል፡፡
§  አንዳንድ ሊቃነጳጳሳትንና የቤተክህነት አመራሮችን አቡነ ሳሙኤል እያደረጉት ያለው ተግባር ከአንድ ኃላፊነት የሚሰማው የሃይማኖት አባት የማይጠበቅ እና ሃይማኖታችን የማይፈቅደው ተግባር ነው ብለዋል፡፡
§  በአዲስ አበባና በአሜሪካው ሲኖዶስ መካከል ሲደረግ የነበረው እርቀ-ሰላም እንዲቋረጥ እና የቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር እንዳይገቡ አቋም ከነበራቸው ጳጳሳት መካከል አቡነ ሳሙኤል ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡
§  አቡነ ሳሙኤል እድሜያቸው ከ50 የማይበልጥ በመሆኑ እና በስነምግባራቸውም በተደጋጋሚ ከሲኖዶሱ አባላት ጋር ግጭት ሲፈጥሩ የነበሩ አባት በመሆናቸው ለቤተክርስቲያኒቷ ትልቅ ኃላፊነት እንደማይመጥኑ አንዳንድ ምእመናን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የዜናው ሙሉ ቃል ከዚህ ቀጥሎ የቀረበው ነው
አባ ሳሙኤል ቀጣዩ ፓትርያርክ ለመሆን
የምረጡኝ ዘመቻ ጀመሩ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን የሚተካ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ለማስመረጥ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚህ የፓትርያርክ ምርጫ ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያኒቷ የተራድኦ ኮምሽን ሊቀጳጳስና ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በነበሩበት ወቅት ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው የነበሩት አቡነ ሳሙኤል በቀጣዩ ምርጫ ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆነው እንዲመረጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የቤተክህነት አመራሮችን፣ የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ስራ አስኪያጆችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በማግባባት ላይ መሆናቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

ሊቀጳጳሱ ለዚህ ይረዳቸው ዘንድ ከፍተኛ ገንዘብ መድበው እየተንቀሳቀሱ ሲሆን በጥቅምት ወር በተካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 31ኛው ጉባኤ ወቅት ተሳታፊ ለነበሩ ቁጥራቸው ወደ 900 የሚጠጋ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተሰባሰቡ ተሳታፊዎች 500 ሺህ ብር በአበል መልክ እንዲከፈል አድርገዋል፡፡ ይህም ለሚካሄደው የፓትርያርክ ምርጫ ይጠቅማቸው ዘንድ ያከናወኑት መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም ገንዘቡ በሱማሌ እና በአፋር ክልሎች ለሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲውል ከእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች የተገኘ እንደሆነና ተሳታፊዎቹም ከየሀገረ ስብከታቸው አበል ተከፍሏቸው የመጡ መሆናቸውን ነገር ግን አቡነ ሳሙኤል ተወዳጅነት ለማግኘት ሲሉ የልማት ኮምሽን ሊቀጳጳስነታቸውን በመጠቀም ገንዘቡ ለተሳታፊዎች እንዲበተን ማድረጋቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

በዚህ የምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ድምጽ ለሚሰጧቸው እና ከጎናቸው ለሚሆኑ ሰዎች ፓትርያርክ ሆነው ከተመረጡ በኋላ በተሻለ የኃላፊነት ቦታ እንደሚሾሟቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው የውጭ ዕድል እንደሚያመቻቹላቸውና ቤተክርስቲያኒቷ በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በምታስገነባቸው ህንጻዎች ውስጥ የንግድ ቦታ እንደሚሰጧቸው ቃል እየገቡላቸው እንደሆነ ምንጮቻችን አስረድተዋል፡፡

ከአቡነ ጳውሎስ ህልፈት በኋላ በአዲስ አበባና በአሜሪካው ሲኖዶስ መካከል ሲደረግ የነበረው እርቀ-ሰላም እንዲቋረጥ እና የቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር እንዳይገቡ አቋም ከነበራቸው ጳጳሳት መካከል አቡነ ሳሙኤል ግንባር ቀደሙ እንደሆኑ ከምንጮቻችን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቡነ ሳሙኤል አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናትን እንዳግባቡና መንግስት ፓትርያርክ ሆኜ እንድመረጥ ይፈልጋል የሚለውና አቡነ ሳሙኤል ተናግረውታል የተባለው ወሬ በአሁኑ ሰዓት በጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ በሰፊው እየተነዛ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ሊቃነጳጳሳትንና የቤተክህነት አመራሮችን በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርን ሲሆን አቡነ ሳሙኤል እያደረጉት ያለው ተግባር ከአንድ ኃላፊነት የሚሰማው የሃይማኖት አባት የማይጠበቅ እና ሃይማኖታችን የማይፈቅደው ተግባር ነው ብለዋል፡፡  ፓትርያርክነት የሚገኘው በምረጡኝ ዘመቻ ሳይሆን በአምላካችን ፈቃድ ስለሆነ ምእመናን ቤተክርስቲያኒቷን በበለጠ መንገድ የሚያገለግላትን ፓትርያርክ ቸሩ እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው በጸሎት ለይ መሆናቸውና ጸሎታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እየመከሩ እንደሚገኙ ምንጮቻችን ይገልጻሉ፡፡

አቡነ ሳሙኤል እድሜያቸው ከ50 የማይበልጥ በመሆኑ እና በስነምግባራቸውም በተደጋጋሚ ከሲኖዶሱ አባላት ጋር ግጭት ሲፈጥሩ የነበሩ አባት በመሆናቸው ለቤተክርስቲያኒቷ ትልቅ ኃላፊነት እንደማይመጥኑ አንዳንድ ምእመናን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የአስመራጭ ኮሚቴው ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት በእጩነት ከቀረቡት አምስት አባቶች መካከል የሚመረጡት 6ኛው ፓትርያርክ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በዓለ ሲመታቸው ይፈጸማል፡፡

3 comments:

  1. ሳሙኤል እኮ ውርጋጥ ነው፡፡ ከውርጋጥ ከዚህ የበለጠ ምን ይጠበቃል፡፡ እንዴትስ ምረጡኝ ይባላል? በእውነት ጥሩ ዜና ነው ያስነበባችሁን፡፡ ለሳሙኤል ልብ ይስጥልን

    ReplyDelete
  2. ....እኮ ውርጋጥ ነው!!! Oh My God! please don't you know that you will be asked for the mess(arrogant) things you speak in front of God??? or are you a pagan? please think well what are you doing. i am sure you, the loggers of this() aba selama)will be equally responsible for the sin(crime). you are doing satanic mission in the name of our holly father, aba selama.

    ReplyDelete
  3. ሲያልቅ አያምር ተወው ገደል ይግባ

    ReplyDelete