Thursday, March 28, 2013

የግንቦት 15ቱ ውግዘት መነሻ፣ ሂደት፣ ፍጻሜና ቀጣዩ ሲገመገም

ክፍል 12

በግንቦት 15/2004 «ውግዘት» ስማቸው ከተካተተው መካከል «የእውነት ቃል አገልግሎት» አንዱ ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት ላይ የግንቦቱ ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤው ያሰፈረው «ኑፋቄ» ብሎ ያቀረባቸው ነጥቦች የሚከተሉት ሲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስንና መሰረት አድርገን ኑፋቄ የተባሉት ነጥቦች ኑፋቄ መሆን አለመሆናቸውን እንመረምራለን።


«ሀ. ወልድና መንፈስ ቅዱስ አማላጆች ናቸው ይላል» በማለት ጽፏል፡፡የእውነት ቃል መጽሔት 2001 ዓ.ም እትም  ቅጽ 5 ቁጥር 22»

በአማላጅነት ዙሪያ ቤተ ክርስቲያናችን የምታራምደው አቋም ከመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ፈጽሞ የራቀና በሰው ሐሳብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ምንም እንኳን «ወልድና መንፈስ ቅዱስ አማላጆች ናቸው» የሚለው አነጋገር «አማላጆች ቅዱሳን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ እና መንፈስ ቅዱስ አይደሉም» ተብሎ ሲነገረው ለኖረ ህዝብ የሚከብድ መስሎ ቢታይም ወልድና መንፈስ ቅዱስ አማላጆች የተባሉበትን ምክንያት ከመጽሐፍ ቅዱስ መመልከቱ ተገቢ ነው እንጂ እርሱን ሳያገናዝቡ ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ማውገዝ የክርስቶስ ነኝ ከምትል ቤተክርስቲያን ከቶ አይጠበቅም፡፡

Monday, March 25, 2013

በሰሜን አሜሪካ ዳላስ የደብረ ምኅረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደሚመራው ሲኖዶስ ተጠቃለለ

በሰሜን አሜሪካ ዳላስ የደብረ ምኅረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደሚመራው የውጭ ሲኖዶስ እንደተጠቃለለ ምንጮቻችን ገለጹ። የዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከብዙ ውይይት በኃላና በመጨረሻም በአባላት ምርጫ ዲሚክራሲያዊ በሆነ አካሄድ እንደነበረ ምንጮቻችን ገልጸዋል። እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት በሚከተሉት አማራጮች ዙሪያ ምርጫ አካሂደዋል።

1) ቤተ ክርስቲያኑ በአገር ቤቱ ሲኖዶስ እንዲመራ  =  2 ድምጽ
2) ቤተ ክርስቲያኑ በውጭው ሲኖዶስ እንዲመራ = 142 ድምጽ
3) ቤተ ክርስቲያኑ እንደቀድሞው በገለልተኝነት እንዲቀጥል = 86 ድምጽ

ምዕመናን ሰላማዊ በሆነ የምርጫ ሂደት በድምጽ ብልጫ በውጭው ሲኖዶስ ለመካተት ወስነዋል። የምርጫውንም ውጤት አባላቱ በስምምነት ተቀብለውታል።

ይህ አንጋፋ ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ጊዜ በማህበረ ቅዱሳን ሲበዘበዝ የኖረ ሲሆን በምዕመናን ተጋድሎ ማህበሩን ነቅለው ካስወጡ በኃላ ቤተ ክርስቲያኑ የሰላም አየር መተንፈስ እንደጀመረ ይነገርለታል። በሁዋላም ምዕመናን በአንድ ሲኖዶስ ስር ለመጠቃለል ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን እረፍትና የ 6ኛ ፓትርያርክን ሹመት ተከትሎ የአንድነቱ ተስፋ በመሟጠጡ ከላይ በተገለጸው አካሄድ በውጭው ሲኖዶስ ስር ሊጠቃለል ችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰሜን አሜሪካ ማህበረ ቅዱሳን የሚከፍታቸው አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን እየለዩ እንደሆነ ምንጮቻችን ገለጹ። እነዚህ አብያት ክርስቲያናት ሲኖዶሱ ወክሎ የላካቸውን የብጹዕ አቡነ ፋኑኤልን ስም (በቅዳሴ) ባለመጥራት ሥራዓት አልበኝነታቸውን በግልጽ እያሳዩ ነው። ሲኖዶስ የላከውን ሊቀ ጳጳስ አለመቀበል ሲኖዶሱንም አለመቀበል ማለት ነው፤ ሊቀ ጳጳሱን የሚሾመው ቅዱስ ሲኖዶስ ነውና።  በዚህ አካሄዳቸው ከቀጠሉ የገለልተኛ ቡድን ወይንም የራሳቸውን ሃይማኖት (ዲኖሚኔሽን) ማቋቋማቸው የማይቀር ነው።

ያለስራ መደብ ተንሳፎ የሚገኘው ሰሎሞን ቶልቻ በእስራኤሏ አምባሳደር ፊት ወደ መንበረ ፓትርያርክ እንዳይገባ ተከለከለ

“ጅብ በማያውቁት አገር …” እንደሚባለው ከዚህ ቀደም ራሱን የቤተ ክህነት ከፍተኛ ባለስልጣን አድርጎ በመቁጠር በልቡ የያዘውን አስጎብኚ የመሆን ህልም በራሱ ጥረት ሳይሆን ቤተክህነት ውስጥ የሌለውን ስልጣን አለአግባብ በመጠቀም ለማሳካት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በክብርት ወ/ሮ በላይነሽን ለማደናገር ሲሞክር የነበረው ሰለሞን ቶልቻ በዛሬው እለት በአምባሰደሯ እንዳይገባ መደረጉን ምንጮች ገለጹ፡፡ እንደ ምንጮቻችን ከሆነ ክብርት አምባሳደሯ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ለማነጋገር በቅዱስነታቸው ጽ/ቤት መገኘታቸውን ተከትሎ በለመደ አፉ እየቀባጠረና የቤተክህነት ዋና ሰው መስሎ ተከትሏቸው ሊገባ ሲል በአምባሳደሯ ፊት እንዳይገባ መከልከሉንና አንገቱን ደፍቶ አፍሮ ወደኋላ መመለሱን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ ምንጮቻችን አክለው እንደገለጹት ካፈርኩ አይመልሰኝ ያለው ሰለሞን የደረሰበትን ሀፍረትና መሸማቀቅ ለማካካስ በሚል ለውጭ ግንኙነት መምሪያው ሊቀጳጳስ ለአቡነ ገሪማ አቤት ቢልም እርሳቸው እንዳልሰሙት ታውቋል፡፡

Saturday, March 23, 2013

በሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎችና በአስተዳደሩ መካከል ያለው ችግር አልተፈታም

ፍስሐ ጽዮን፣ ዘላለም፣ ፋዘር ጆሲና ማቅ ምን እያደረጉ ነው?
የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎች ትምህርት ካቆሙ ቀናቶች የተቆጠሩ ሲሆን በኮሌጁ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙት ፍስሐ ጽዮን ደሞዝና ዘላለም ረድኤት፣ እንዲሁም የኮሌጁ ዲን አባ ጢሞቴዎስ ካልተነሡ ትምህርት አንጀምርም በሚል አቋማቸው እንደጸኑ ሲሆን ኮሌጁም በበኩሉ እስከ 12/7/2005 ዓ.ም ድረስ ትምህርት ካልጀመሩ በፖሊስ ከኮሌጁ እንዲወጡ እንደሚያደርግ በማስታወቂያ አስታውቋል ተብሏል፡፡

እነዚህ ስማቸው የተጠቀሰው የኮሌጁ ኃላፊዎች በርካታ ችግሮችን በኮሌጁ ተማሪዎች ላይ ሲፈጥሩ የቆዩ መሆናቸው ሲታወቅ በተለይም ፍስሐ ጽዮን ደሞዝ የማቅ ወኪል በመሆንና በጥቅም በመተሳሰር ኮሌጁን ለማቅ ሰዎች መጠቀሚያ በማድረግና እውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆችን ተሀድሶ መናፍቅ እያስባለ እንዲባረሩ ሲያደርግና ለማቅ ብሎግ ለደጀሰላም ወሬዎችን በማቀበል ሲሰራ መቆየቱን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮቻችን ይናገራሉ፡፡ ፍስሀ ጽዮን በተለይም ማታ የሚማሩ የማቅ ሰዎች የሚያቀርቧቸውን መሰረተ ቢስ ክሶች በመቀበልና ጉዳዩን በማራገብ መምህራንን ከማስቀየር ተማሪዎችን እስከማስባረር ደርሶ የማቅን ጥቅም በማስጠበቅ ይታወቃል፡፡ ኮሌጁ በቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ ሳይሆን በማቅ ተረታተረት እንዲመራ ለማድረግ በከፍተኛ ሁኔታ ድጋፍ አየሰጠ እንደሚገኝም ምንጮቻችን ይናገራሉ፡፡

Friday, March 22, 2013

ራስፑቲን: ደብረ-በጥብጥ ሐሳዊው መነኵሴ

ምንጭ፦ www.ethiomedia.com
በወንድሙ መኰንን፡ (
ኢንግላንድ 11/03/2013)
መግቢያ
ራስፑቲን በ19ኛው መጨረሻና በ20ኛው መጀመሪያ መቶ ክፍለ ዘመናት የኖረ፣ የውሸት ራሻዊ መንኵሴ ነበር። በጣም አስገራሚና አሳሳች የቀበሮ ባሕታዊ ነበር። የሱን የሕይወት ታሪክ መዳሰስና ማወቁ፣ በዘመናችን ዳግማዊ ራስፑቲኖች ካሉ ለየቶ ለመጠንቀቅ ይረዳናል። በጽሞና አንብቡልኝ።

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

Sunday, March 17, 2013

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ተቃውሞ እያሰሙ ነው ከተቃውሞው በስተጀርባ የአባ ሳሙኤል እጅ አለ


የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎች ከሰሞኑ የተቃውሞ ድምጽ እያሰሙ ሲሆን በ5/7/2005 ዓ.ም አርብ እለት ጥቁር ቀሚሳቸውን ለብሰው በጠቅላይ ቤተክህነት በር ላይ ተሰልፈው መታየታቸውና ወደውስጥ ሳይገቡ በመቅረታቸውም ወደኮሌጃቸው ተመልሰው ለተወሰነ ጊዜ ተማሪም ሆነ ሰራተኛ እንዳይገባ ሲከለክሉ እንደነበር ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ፡፡ ተማሪዎቹ በኮሌጁ ብልሹ አስተዳደር ምክንያት ከአቡነ ጳውሎስ ዘመን ጀምሮ በኮሌጁ ውስጥ ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያሏቸውን ችግሮች መሰረት አድርገው የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን ጥያቄዎቻቸው ሙሉ በሙሉ ሳይመለሱ እስካሁን ዘልቀዋል፡፡ ከሰሞኑም አዲስ ተቃውሞ መቀስቀሱ እየታየና እየተሰማ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ እስካሁን ሳይሰተካከሉና ሲንከባበሉ የቆዩ አስተዳደራዊ ችግሮችና የምግብ አቅርቦት ጉዳይ ሲሆን ከካፌ ምግብ አቅራቢዎች እስከ ዲኑ አቡነ ጢሞቴዎስ ይነሱልን የሚል ጥያቄ እንደአዲስ ማንሳታቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

Thursday, March 14, 2013

"ሰባኪው" ምሕረተአብ ከኮተቤ ኢያቄም ወሃና ቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በስካር ቅሌት ወረደ

ዐቢይ የተባለው የጌታችን ጾምን ደግመን በምንጾምበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ጾሙ ትውፊትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በልማድ መጾማችን እንደተጠበቀ ሆኖ ዋናው ጾም ከመብል መጠጥ ብቻ ሳይሆን ከኃጢአት መጾሙ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ በጾም ወራት ስለምናከናውነው መንፈሳዊ ተግባር ከማሰብና ከመጨነቅ ይልቅ ለ54 ቀናት ከምንለየው ስጋና ሌሎችም የጥሉላት ጋር የመጨረሻ ስንብት ለማድረግ ለቅበላ የምናደራው የሥጋ ገበያ አይሎ ስለሚታይ ጿሚዎች ሳንሆን ስጋን ናፋቂዎች እያስመሰለን ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥታችን በጾም ወቅት ሥጋንና ሌሎቹንም የጥሉላት ምግቦች ብቻ ሳይሆን የሚያሰክር መጠጥንም እንድንጾም ያዝዘናል፡፡ ነገር ግን ማን ሰምቶ? እነ ሆድ አምላኩ ለመብልና ለመጠጥ እንጂ ለጾም አያደሉም፡፡ አድልዉ ለጾምን ሳይሆን አድለዉ ለሆድን ነው የሚያስቀድሙት፡፡ በተለይም ቤተክርስቲያን በዝክርና በተዝካር ሰበብ በአልኮል መጠጥ የተሞላች ስለሆነች መጠጥ የሚበረታታባት ቤት ሆናለች፡፡
አንዳንድ ወጣቶች አልኮልን ትተው በሻይና በለስላሳ መጠጥ የጽዋ ማኅበር ይጠጡ በነበረባቸው በ1980ዎቹ ዓመታት፣  ጠላና ጠጅ ከጽዋ ማሕበር ለምን ቀረ? በሚል እንዲህ ያለው አካሄድ የተሐድሶ ነውና ንቁ እየተባለ ይሰበክ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ መጠጥ የኦርቶዶክስነት ምልክት ተደርጎ እንዲታሰብ እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡ የማይጠጣ ተሐድሶ ነው እያሉም በመጠጥ ጉዳት እንጂ ጥቅም ኪሳራ እንጂ ትርፍ እንደማይኖር የተረዱና መጠጥ አንጠጣም ያሉ አንዳንድ አገልጋዮችን  ሲያሳድዱና ስማቸውን ሲያጠፉ እንደኖሩና አሁንም በብዙ ስፍራዎች እያሳደዱ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ጠጪዎቹ እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው ቢባል የማይጠጡት አገልጋዮች ሕይወት ስለሚኮንናቸውና ህሊናቸው ስለሚወቀስ ነው፡፡ እኛን ካልመሰሉ መናፍቃን ተሐድሶዎች ናቸው ብለው ያስባሉ፡፡
ከሰሞኑ ስለ ትክክለኛው መናፍቅ ምሕረተአብ (እንዳሻው) የወጣው ዘገባ የዚህ አንዱ ማሳያ ነውና እንድታነቡት ጋብዘናል፡፡
ምንጭ፡- http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
"ሰባኪው" ምሕረተአብ ከኮተቤ ኢያቄም ወሃና ቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በስካር ቅሌት ወረደ

"ከእኔ በላይ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰባኪ ለአሣር"!! ባዩ ምሕረተአብ አሰፋ (እንዳሻው) በትላንትናው ዕለት በስካር ምክንያት መስበክ አቅቶት ከኮተቤ ኢያቄም ወሃና ቤተክርስቲያን ዐውደ ምሕረት መውረዱን ከዚያው አካባቢ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

Monday, March 11, 2013

የሊቀ ጳጳሱ የሲሚንቶ ሽያጭ ቅሌት

በከፋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የዋሻ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ህንፃ ሥራ ከተጀመረ 4 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ይህ የአካባቢው ምዕመናን አስተዋጽኦና በበጎ አድራጊዎች እርዳታ እየታነፀ የሚገኘው ቤተክርስቲያን በአስተዳዳሪውና የህንፃ አሰሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ የገንዘብ ምዝበራ ተካሂዶበታል በሚል በተደጋጋሚ ክስ ቢቀርብበትም ሀገረ ስብከቱ አባ ሕዝቅኤል ክሱን እየሸፋፈኑና የሕዝበ-ክርስቲያኑን ጥያቄ በማፈን በልመና የሚሰበሰበው ገንዘብ እንዲመዘበር ሽፋን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

በአባ ሕዝቅኤል ፍርደ-ገምድልነት የተከፉ የአካባቢው የሀገረ ሽማግሌዎች በሰኔ ወር 2ዐዐ4 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ቀርበው ጉዳዩን ለብፁዕ ውቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ያስረዳሉ፡፡ ለገንዘቡ መመዝበር እንደ ምክንያትም እንደ ሽፋንም የሆኑት የሀገረስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አባ ሕዝቅኤል መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡ ፓትርያርኩም አጣሪ ወደ ሀገረስብከቱ በመላክ የሀገር ሽማግሌዎቹ አቤቱታ አግባብነት መሆኑን፣ በህንፃ ቤተ-ክርስቲያኑ ምክንያት የተመዘበረ ገንዘብ መገኘቱን ወዘተ በመገንዘብ የደብሩ አስተዳዳሪ ከቦታቻው እንዲታገዱና የሒሳብ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ “የበላ ዳኛ የወጋ መጋኛ” እንዲባል ይህን እንዲያስፈፅሙ የታዘዙት የሀገረስብከቱ ሊቀጳጳስ አባ ሕዝቅኤል የብፁዕ ወቅዱስን ማለፍ ተገን በማድረግ ትዕዛዙን ሳያስፈፅሙ፣ ሒሳቡም እንዳይመረመር ሲከላከሉ ቆይተው አስተዳዳሪውን ወደ ሥራው እንዲመለስ በማድረግ የሕዝበ-ክርስቲያኑን ልፋት ከንቱ ያደርጉታል፡፡

Saturday, March 9, 2013

ፍሬ-አልባ ጩኸት

Read in PDF
አንሰ እቤ አምግዕዝየ ኵሉ ሰብእ ሐሳዊ ውእቱ!
(የዳዊት መዝሙር 115)
መስፍን ወልደ ማርያም
የካቲት 2005

አቶ ዳንኤልን አላውቀውም፤ ለካ ብዙ ጭፍሮች ያሉት ሰው ነው፤ በጣም ተንጫጩለት፤ የሎሌ ነገር ሆነና ጩኸታቸው አንድ ነው፤ ጉዳዩን ጭራሽ አያውቁትም፤ ያንገበገባቸው መሪያቸው መነካቱ ነው፤ ለሎሌዎቹ መልስ መስጠት ባልተገባ ነበር፤ ነገር ግን ያደረጉት ትክክል መስሎአቸው እንዳይኩራሩና በያዙት የመክሸፍ መንገድ አንዳይቀጥሉ አንዳንድ ነጥቦችን ላብራራላቸው ፈለግሁ፤ ውጤት ይኖረዋል ብዬ ሳይሆን ለኔው ለራሴና ለማኅበረሰባችን ጤንነት ነው፤ ራሴን ከአቶ ዳንኤል ጭፍሮች ለመከላከል ፈልጌ እንዳይመስል፤ አትኩሮት በጉዳዩ ላይ እንዲሆን ለመሞከር ነው።

አንዳንዶቹ ዲያቆን የሚል ቅጽል ባለመጨመሬ ሆን ብዬ መስሎአቸዋል፤ ባለማወቅ ነው፤ ራሴን ተጠራጥሬ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ከፈትሁና የማውቀውን ነገረኝ፤የተካነ፣ ምሥጢር ያየ፤ ቀዳሽ የሚል፤ በዚህ መስፈርት እኔም ዱሮ ዲያቆን ነበርሁ፤ ዛሬም ይህንን የሚያሙዋሉ ወጣቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በሚልዮን ባይሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ይኖራሉ፤ በዚያ ላይ እኔ እንደማውቀው ዲያቆን ሦስት ደረጃዎች ሲኖሩት የዲያቆኖች አለቃ ሊቀ ዲያቆናት ይባላል፤ አቶ ዳንኤል ሊቀ ዲያቆናትም አልሆነም፤ የአቶ ዳንኤል ዲያቆንነት የቱ ዘንድ እንደሚወድቅና ምን ማለትም እንደሆነ አላውቅም፤ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም እንዲህ ያለማዕርግ መስጠት ጀምራ እንደሆነና ለነማን እንደምትሰጥ አላውቅም፤ እኔ ዱሮ የማውቀው ዲያቆን የቅስና ሥልጣን (በምድር ያሰራችሁት በሰማይም የታሰረ ይሆናል፤) ሲያገኝ መምሬ መባሉን ነው።

Friday, March 8, 2013

የግንቦት 15ቱ ውግዘት መነሻ፣ ሂደት፣ ፍጻሜና ቀጣዩ ሲገመገም

ክፍል 11
በግንቦቱ 15/2004 የሲኖዶስ ስብሰባ በሕገወጥ መንገድ ከተወገዙት ማኅበራት መካከል አንዱ ቅድስት ልደታ ለማርያም መንፈሳዊ ማኅበር ነው፡፡ በማኅበሩ ላይ ኑፋቄ ተብለው የቀረቡትና ማኅበሩ ተጠርቶ ሳይጠየቅ የተወገዛባቸው ሁለት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

“ሀ. የገሃነም ደጆች አይችሏትም የተባለችው የሰማያዊ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን ጥሪዋን በመዘንጋቷ በራሷ ችግር ተይዛ ባልታዘዘችበት መንገድና ባልተወከለችበት ስፍራ በመጠመዷ የንስሐ አዋጅ ማድረግ አቅቷታል፡፡ ታላቋ የእግዚአብሔር መንግሥት ዛሬ የደረቁ አጥንቶች የመሉባት ሸለቆ ሆናለች’ በማለት ቤተክርስቲያንን ይዘልፋል፡፡’ በሃይማኖት ቁሙ፣ 13ኛ ዓመት እትም ቁ. 3 ገጽ 1”

እንደተባለው ቤተክርስቲያን ትልቅ አሸናፊነት የተሰጣትና ጌታ በገሃነም ደጆች ላይ ያሰለጠናት በምድር ላይ የእግዚአብሔር መንግስት ወኪል ናት፡፡ ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያን ይህን ተልእኮዋን በመዘንጋቷና ባልተጠራችበት አላማ በመሰማራቷ ከላይ የተገለጹት ነገሮች አልደረሱባትም ብሎ ሊያስተባብል ማን ይችላል? ቤተክርስቲያን በዘመናት ሁሉ በውስጧ ስለተፈጸመው ኃጢአትና በደል፣ አንዳንዶች በግልጽ ስለፈጸሙትና ዛሬም እንኳን እየፈጸሙ ስላለው የግፍ ሥራ ንስሐ ስትገባ አልታየም፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ “ቤተክርስቲያን አትሳሳትም፤ የምንሳሳተው እኛ ነን” በሚለው የተላሎች ብሂል ስለታሰረች ተሳስቻለሁ ብላ በአደባባይ ንስሐ መግባት በሚገባት ጉዳይ ላይ እንኳን ንስሐ አልገባችም፡፡ ቤተክርስቲያን ማለት እኛው አይደለንም ወይ? እኛ ደግሞ የምንሳሳት ነን፡፡ ስለዚህ የሰዎች ስብስብ የሆነችው ቤተክርስቲያን አትሳሳትም እንዴት ይባላል? ምናልባት አባባሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ትክክል ነው፤ በእርሱ ላይ የተመሰረተው የአበው ትምህርትም እውነት ነው ለማለት ተፈልጎ ከሆነ ያን ግልጽ ማድረግ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ትናንትም ዛሬም ቤተክርስቲያን ልትሳሳት ትችላለች፡፡

Thursday, March 7, 2013

በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መግለጫ አወጣ

በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ከጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊውን የቤተክርስቲያናችን ሁኔታ አስመልክቶ የወጣ የአቋም መግለጫ፡፡

‹‹እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና›› (ዮሐ/ወ፡ 8፥44)፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊትና ቀዳማዊት እንደመሆኗ መጠን በረጅም ጊዜ ጉዞዋ ታላላቅ ፈተናዎች አጋጥመዋታል፡፡ በአይሁዳዊቱ ጉዲት፥ በግራኝ መሀመድ፥ በ
07¨ው መ/ክ ዘመን የቫቲካን መልእክተኞች፥ በፋሽስት ኢጣሊያና በኮምኒስቱ የደርግ ዘመነ-መንግሥት የደረሰባትን መጥቀሥ ይቻላል፡፡ እነዚያን የፈተና ጊዜያት በጽናት ተቋቁማ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በመቀጠል ከዚህ ደርሳለች፡፡

እንዳለፈቻቸው ፈተናዎች ሁሉ እስክታልፈው ድረስ እያስጨነቃት በሚገኝ በሁለት ሲኖዶስና በሌላ ሦስትኛ አካል የመከፋፈል መከራና ፈተና ውስጥ ፳፩
ዓመታትን እንዳሳለፈች ለሁሉ ግልጽ ነው፡፡ የአቡነ ጳውሎስ ዕረፍት ፈተናዋን ፈጽሞ ሰላምና አንድነቷን ይመልስላታል የሚል ተስፋ በክርስቲያኖች ዘንድ አጭሮ ነበረ፡፡ ይሁን እንጂ በመንግሥት ሕገ ወጥነት አበቃላት የተባለው ፈተናዋ በባሰ ሁኔታ እንዲቀጥል ሆኗል፡፡ በመሆኑም በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ የጽርሐ-አርያም ቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ይህንን መግለጫ ለማውጣት ተገዳለች፡፡
ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

Wednesday, March 6, 2013

ቅዱስ ሲኖዶስ «አጽናኑ ሕዝቤን አጽናኑ» በሚል ርዕስ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ አወጀ

(ተስተካክሎ የወጣ ፕሮግራም)
በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ዓለም አቀፋዊ የወንጌል አግልግሎት በተቀናጀ መልኩ ጀመረ። ከዚህ በታች ያስቀመጥነው ማስታወቂያ እንደሚያመለክተው የስብከተ ወንጌሉ ፕሮግራም በበርካታ የሰሜን አሜሪካ አብያት ክርስቲያናት፣ በአውሮፓ፣ በካናዳ፣ በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያ እንዲሁም በኒውዚላንድ ባሉ አብያት ክርስቲያናት ይከናወናል። የስብከተ ወንጌሉ ፕሮግራም በአውስትራሊያ ቀደም ብሎ የተጀመረ ሲሆን ሌሎች ጉባኤያት የሚከናወኑት ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ወራት ውስጥ ነው።

Tuesday, March 5, 2013

ክሽፈት እንደ ማኅበረ ቅዱሳን በ6ኛው ፓትርያርክ ምርጫ

(ይህችን ጽሁፍ ለአንባቢ እንድትመች ከፓትርያርክ በዓለ ሲመቱ ዜና ለይተን ለብቻዋ አስቀምጠናል)
“ክሽፈት” የሚለው ሰሞነኛ ቃል የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም መጽሐፍ ርዕስ ሆኖ በየጋዜጣውና በየመጽሔቱ ትልቅ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ መጽሐፉ በኢትዮጵያ ያልከሸፈ ነገር የለም፤ ያልከሸፈ ነገር ቢኖር ኢትዮጵያውያን ለውጭ ወራሪዎች ያላቸው የጋራ አቋም ወይም ኢትዮጵያዊ ወኔ ብቻ ነው ይላል፡፡  እኛም ክሽፈት በሚለው ቃል ማኅበረ ቅዱሳንን መፈተሽ ወደድን፡፡ ከአቡነ ጳውሎስ ህልፈት በኋላና ከምርጫው ጋር በተያያዘ ሁሉም ከሽፎበት ያልከሸፈበት አንድ ነገር ብቻ የቀረ ይመስለናል፡፡ እርሱም በአስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ ኮታ ማግኘቱና በባያብል ሙላት መወከሉ ብቻ ነው፡፡ ክሽፈቶቹ ምን ምን ናቸው? ለሚል ጠያቂ እነሆ ክሽፈቶቹ፦

ክሽፈት አንድ
ያገለግሉኛል ይተባበሩኛል ይረዱኛል ብሎ ተሯሩጦ አቃቤ መንበር ያደረጋቸው ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ባልተጠበቀ ሁኔታ ፊታቸውን ገና ከማለዳው ነበር ያዞሩበት፡፡ በዚህ ምክንያት አቃቤ መንበሩን መለወጥ አለብን ለማለት የዳዳቸው እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡

Monday, March 4, 2013

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓለ ሲመት በታላቅ ድምቀት ተፈጸመ

6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው የተመረጠት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዓለ ሲመት የካቲት 24/2005 ዓ.ም. የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርኮችና ሊቃነ ጳጳሳት፣ የልዩ ልዩ ሃይማኖት አባቶች፣ ክቡር አቶ አባ ዱላ ገመዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፣ የፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ተወካይ፣ የአዲስ አበባ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል፡፡ ቅዱስነታቸው ሥርአተ ሲመታቸው ከተፈጸመ በኋላ ባደረጉት ቃለ መሐላዊ ንግግር በክርስቶስ ትምህርት ላይ የተመሠረተውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ትምህርትን ጠብቀው ለማስጠበቅ እንደሚተጉ፣ የሁሉም አባት እንደመሆናቸው ምእመናንንና ምእመናትን ያለአድልዎ በቅንንት በታማኝነትና በትህትና እንደሚያገለግሉ የገለጹ ሲሆን፣ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የጎደለውን ለመሙላት የጠመመውን ለማቅናትና አባጣ ጎርባጣውን ለማስተካከል ብልሹ አስተዳደርን ለማቃናት ከቅዱስ ሲኖዶስ ብዙ እንደሚጠበቅና ለዚህም እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

Sunday, March 3, 2013

ጥንቆላ - በሀገራችን ፣ በቤተ ክርስቲያናቸን እንዲሁም በእያንዳንዳችን ላይ ሊኖረው የሚችለው ተጽዕኖ

ክፍል ሁለት
ባለፈው ጽሑፌ ጥንቆላ ምን እንደሆነ ጥቂት ለማሳየት ሞክሬያለሁ፤ በሰፊው ግን አልገለጥሁትም። የሰይጣንን ክፋት በሰፊው ከመግለጥ የእግዚአብሔርን ደግነት አጉልቶ መግለጥ ይሻላል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። ነገር ግን ወገኖቼ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ጥንቆላን እንደቀላል ልማድ በማየት በጨለማው ገዢ ሥር ሲወድቁ እያየሁ ስለማዝን እውነታውን ለማሳየት ምክሬያለሁ። ዛሬ ደግሞ አንዳድ መናፍስት ጠሪዎችና ደጋሚዎች የሚያጠምቁበትን ዘዴ ከአንድ ደብተራ ጓደኛዬ ያገኘሁትን ምስጢር በጥቂቱ መግለጥ እሞክራለሁ።
አስማቱ በመስቀል፤ በጣት ቀለበት እና በመቁጠሪያ ሊሠራ ይችላል። በመስቀል ቅርጽ እንዲሁም በመቁጠሪያነት ለድግምቱ የሚያገለግሉ እጸዋት ሁለት ናቸው። አንደኛው አርግፍ የሚባል ሲሆን ሁለተኛው ጠንበለል ይባላል። እጸዋቱ በደጋማ ሥፍራዎች ይገኛሉ። በትክል ድንጋይና በሰከላ በብዛት ይገኛሉ። የአስማቱ ባለሙያዎችም ከላይ በጠቅስሁአቸው ቦታዎች አሉ። በተለይ አርግፍ የሚባለውን እንጨት በአካባቢው ያሉ ገበሬዎች እየጠረቡ ለሕጻናት ከሰይጣን እና ከቡዳ ይጠብቃል እያሉ ባንገታቸው ያደርጉላቸዋል።

Friday, March 1, 2013

ሰበር ዜና- አባ ሳሙኤል እና አባ አብርሃም ብፁዕ አቡነ ማትያስ እግር ላይ ወድቀው ይቅርታ ጠየቁ

አባ ሳሙኤል እና የጉድ ሙዳዩ አባ አብርሃም አቡነ ማትያስን ይቅርታ መጠየቃቸው ተሰማ፡፡ ይቅርታ እንዲጠይቁ ያደረጉት በ6ኛው የፓትርያርክ ምርጫ ሁለት መለያ አጥልቀው ሲሻቸው ለማቅ ዞረው ደግሞ በሽምግልና ስም እየተጫወቱ የቆዩት የመንደሩ ቀኛዝማች ሀይሉ ቃለወልድ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የመንደሩ ቀኛዝማች በሐዘን ድባብ የተዋጠውን የማቅን መንደር ባለበት ትተው “ኧረ ጉድ እንዳንሆን እነአባ ሳሙኤልን ከአቡነ ማትያስ ጋር እናስታርቃቸው” ብለው የማቅ እጩ ወደነበሩት (“ነበር እንዲህ ቅርብ ነው ለካ?” አሉ እቴጌ ጣይቱ) ወደአባ ማቴዎስ በመደወል ከአቡነ ማትያስ ጋር እንዲያስታርቋቸው ይጠይቃሉ፡፡ አባ ማቴዎስም ሌሎች ጳጳሳትን ይዘው ወደአቡነ ማትያስ እንደገቡና ይቅርታ እንዲጠይቁ እንዳደረጓቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚያም አባ አብርሓም እግራቸው ላይ ወድቀው ስቅስቅ ብለው በማልቀስ “ይቅርታ አድርጉልኝ አባቴ፣ እኔ እኮ በሽተኛ ነኝ የምለውንም አላውቅም” በማለት ይቅርታ ጠይቀዋል ተብሏል፡፡ አባ ሳሙኤልም በተመሳሳይ መንገድ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ግን “እኔን ምን አደረጋችሁኝ? ይቅርታ መጠየቅ ያለባችሁ እኔን ሳይሆን የደፈራችሁትን ሲኖዱሱን ነው፡፡ አልሰማ ያላችኋቸውን ሰብሳቢውን ነው ይቅርታ መጠየቅ ያለባችሁ፡፡” ማለታቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡