Monday, April 29, 2013

የጻፍሁትን ጽፌአለሁ!

     ‘‘የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ’’    ዮሐ 19፡22
      ከንጉሥ ጲላጦስ  የተላከ
ጲላጦስ የይሁዳ አውራጃን ያስተዳድር የነበረ ሮማዊ ገዥ  ሲሆን   በስልጣን ዘመኑ ከተመለከታቸው ጉዳዮች እና ከአስቻላቸው ችሎቶች የኢየሱስ ጉዳይ የሚመስል እና ለመወሰን  የተቸገረበት ዘመን የለም።የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት በዓለም   ከታዩት የፍርድ መጉደል ሁሉ የበለጠ ነው። አንድ ሰው በመስቀል ተስቅሎ  ከመሞቱ በፊት መገረፍ እንዳለበት የሮማውያን ህግ ይናገራል። ግርፉቱ  በጣም አደገኛ በመሆኑ  በግርፉቱ ብቻ  ብዙ ሰው ሞቷል ምክንያቱም መግረፊያው የሚሰራው ከቆዳ ሲሆን  በጫፉ ላይ ብረታ ብረት፡አጥንት ወይም ሹል ነገር ይቋጠርበታል። ወንጅለኛ የተባለው ሰው ሲገርፍ  እነዚያ ሁሉ ነገሮች በጀርባው ላይ ያርፉሉ፡ ከዚህ በኋላ ጉዳቱ የባሰ ሰለሆነ ሥጋው በማለቅ  አጥንቱ ከዚያም አልፎ ውሳጣዊ የሰውነት ክፍሎች  ይታያሉ።ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ  ሲገረፍ   ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ ደርሰውበታል። ጲላጦስ ብዙ ይተገረፈውን   ስጋው አልቆ አጥንቱ የታየውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚገባውን  ቅጣት ስለተቀበለ በነፃ ለማሰናበት በማለት በህዝቡ ፊት አቀረበው(ሉቃ 23፡16_22) አይሁድ ግን በደም የተሸፈነውን የኢየሱስን አካል በማየት ቅንጣት ያህል አላዘኑለትም፡ይልቁንም ምራቅ እየተፉ  በጥፊ ይመቱት ነበር(ማቴ 27፡27_31)። ኢየሱስ  እኛን ሰለሚወደን ይህን ሁሉ ታግሷል።ጲላጦስ ጌታ ኢየሱስን  ነፃ ለማድረግ  ብዙ መንገዶችን ሞክሯል ፦  እንዲለቁት ብሎ አስገርፎታል፡እናንተ ካልፈለጋችሁት  ግሪክ ሂዶ ያስተምር ብሎቸዋል፡ በየአመቱ የፉሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ  ኢየሱስን ከአደገኛው ወንበዴ ከበርባን ጋር ለምርጫ አቅርቧል። አይሁድ ግን ልባቸው በክፋት ስለ ተያዘ ኢየሱስ እንዳይፈታ በኃይል ይጮሁ ነበር፡የምትፈታው በርባንን ነው አሉ(ዮሐ18: 40)። ጩ ኸቱ ሁሉ  ወንበዴን ፈቶ ንጹሑን   ለመግደል ነው ። ጲላጦስ የ ሮምን  ሕግ ማስፈጸም ተሳነው ። ህጕ ወንጅል የሌለበትን አይቀጣምና። ጲላጦስ አንድ ንጹሕ መግደል ነው ያለበት? ወይስ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ውሸተኞችን መስማት?  በነገሩ ግራ ተግብቶ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ምን  ላድረገው (ማቴ 27፡22)  ሲላቸው  አይሁድም በአንድነት ስቀለው ስቀለው አሉ።  ጲላጦስ ግን አንዳች በደል አላገኘሁበትም   እናንተ ስቀሉት ሲላቸው እኛ ህግ አለን እንደ ህጋችን ሊሞት ይገባዋል ብለው  ወዲያዉኑ ኢየሱሰን ለመስቀል ወንጅል ያሉትን እራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” ብሏል በማለት ነገሩን ከሮም ህግ  ወደ እግዚአብሔር ህግ ቀየሩት( ዮሐ198_11)   ጲላጦስ  ውሳኔ ግን ጌታን መልቀቅ ነበር ። የአይሁድ ካህናት ግን  እየሱስ  እንዳይለቀቅ ጲላጦስን በማስጠንቀቂያ   ብትፈታው የቄሳር  ወዳጅ  አይደለህም በማለት  ጉዳዩን  ከሃይማኖታዊ ወደ ፖለቲካዊ ይዘት ለወጡት።

አባ አብርሃም እና ማኅበረ ቅዱሳን በአሜሪካ ያለውን የሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንዲያስረክቡ ቋሚ ሲኖዶሱ ወሰነ

                        ምንጭ፡- http://awdemihreet.blogspot.com/
 በማኅበረ ቅዱሳን አይዞህ ባይነት የአሜሪካውን ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት ለብጹዕ አቡነ ፋኑኤል አላስረክብም ብለው የነበሩት አባ አብርሃም የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት እንዲያስረክቡ ቋሚ ሲኖዶሱ ወሰነ፡፡ ይህ በቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ፊርማ የወጣው እና አድራሻውን ለአባ አብርሃም ያደረገው ደብዳቤ እንዳስታወቀው አባ አብርሃም ሀገረ ስብከቱን በዝውውር ለቀው ከወጡ በኃላ የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት አላስረክብም ማለታቸው ህገ ወጥ ድርጊት ነው፡፡
አባ አብርሃም ቤተክርሰቲያን አንዲት መሆንዋን መረዳት ከብዷቸው እና እሳቸውን ለማዘዝ ሙሉ ስልጣን ያለውን ቅዱስ ሲኖዶስ ተጋፍተው ላለፉት ሁለት አመታት የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት አላስረክብም በማለት በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሽፍታ ሠራዊት ማስፈራቸው አስገራሚ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ እኚህ ጉድ አያል ቅበት የሆኑት ጳጳስ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሳካው እሺ ብሎ በመታዘዝ መሆኑ ከዲቁና እስከ ጵጵስና ድረስ አለመረዳታቸው በብዙዎች ዘንድ የሚያስተዛዝብ ሆኗል፡፡

Sunday, April 28, 2013

ሆሳዕና በአርያም ለወልደ ዳዊት

እናንት መኳንንት በሮችን ክፈቱ የክብር ንጉሥ ይግባ
ሆሣዕና ከጌታችን ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፡፡ ጌታችን በተነገረው ትንቢት መሠረት በአህያ ላይ ተቀምጦ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሚታሰብበት በዓል ነው፡፡ በዓሉን ቤተክርስቲያን በሚታይ ትእምርት የምታከብረው ቢሆንም ትእምርቱ የሚወክለውን እውነት ግን ቦታ ሰጥታዋለች ማለት አይቻልም፡፡ በሆሣዕና ዕለት ቅዳሴው የሚጀመረው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ነው፡፡ ቀዳሾች ሥጋ ወደሙን ከቤተልሔም ይዘው ወደመቅደስ የሚገቡት  እንደወትሮው በምሥራቁ በር ሳይሆን በወንዶች መግቢያ ነው፡፡ መዘምራን በቀኝና በግራ ሥጋ ወደሙ የያዙትን ቀዳሾቹን አጅበው እየዘመሩና ምንጣፍ እያነጠፉ ይገቡና ቅድስቱ ላይ ቆመው፣ በመዝሙረ ዳዊት “እናንት መኳንንቶች፥ በሮችን ክፈቱ፥ የዘላለም ደጆችም ይከፈቱ፥ የክብርም ንጉሥ ይግባ። ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው? እግዚአብሔር ነው፥ ብርቱና ኃያል፥ እግዚአብሔር ነው፥ በሰልፍ ኃያል።” (መዝ. 23፡7-8) የሚለውን ክፍል ዲያቆኑና ቄሱ ሕዝቡም እየተቀባበሉ ያዜማሉ።

Friday, April 26, 2013

የሺ ፍልጥ ማሠሪያው ልጥ

ከአባ ዕዝራ ዘደቂቀ እስጢፋኖስ
ሀራ ዘተዋህዶ የተሰኘው አፍቃሬ ማህበረ ቅዱሳን ድረገጽ በApril 19, 2013 ባወጣው ጽሁፍ እንደተለመደው በርካታ በሀሰት የተሞላ የፈጠራ ወሬ አስነብቧል፡፡ ከዚያም ባለፈ ቤተክርስቲያንን በዘረኛ ፖለቲካው ለመከፋፈል በዘረኝነት የተለወሰ መርዙን ረጭቷል፡፡ የትግራይ ተወላጆች የግቢውን አመራር ሙሉ በሙሉ እንረከበዋለን፡፡ ከዚህ በኋላ ቤተ ክርስቲያን በትግራዎች እንጂ በአማራ አትመራም፡፡” ብለዋል በማለት ዘረኛ አመለካከቱን እግዚአብሔርን ሳይፈራ ሰውንም ሳያፍር በገሃድ ተናግሯል፡፡

የማቅ ሰዎች ፈሊጥ የጐደላቸው በመሆናቸው በሃይማኖት ሽፋን የሚያራምዱትን ፖለቲካ በቅጡ የተረዱት አይመስልም፡፡ ፖለቲካን ለማራመድ ቅድሚያ ፖለቲካን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በጭንጫ ላይ የበቀለ ሣር ፀሐይ ሲወጣ እንደሚጠወልግ እነርሱም እንደዚያ ከመሆን አያልፉም፡፡  ዘርን ጠቅሶ ማንቋሸሽና አንዱን ወገን ከሌላው ወገን ጋር ለማጋጨት ቤተክርስቲያንን መጠቀሚያ ማድረግ ለቤተክርስቲያንና ለአገር አስባለሁ ከሚል ወገን አይጠበቅም፡፡ ለራስ የሚተርፈው ኪሳራም ቀላል አይሆንም፡፡

Thursday, April 25, 2013

ክርስቶስ ሰምራ ዘብሔረ ቡልጋ በቀን ሦስት ሺህ ነፍሳት ከሲኦል ታወጣለች

«ወወሐባ ኪዳነ ከመ ታውጽእ ነፍሳተ እምሲኦል ሠለስተ እልፈ ነፍሳተ በበዕለቱ» ትርጉም "ጌታም በየቀኑ ከሲኦል ሦስት ሺህ ነፍሳትን እንድታወጣ ሥልጣን ሰጣት ወይም ቃል ኪዳን ሰጣት» ገድለ ክርስቶስ ሠምራ ዘጥቅምት ቁ 61.
ክርስቶስ ሠምራ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የታወቀች ቅድስት ሴት ናት። በየዓመቱ ግንቦት 12 መታሰቢያዋ ይከበራል። በዚህ ቀን በርካታ ምዕመናን እርሷን ከሲኦል እንድታወጣው ለመማጸን ወደ ቤተ መቅደሷ በመሄድ ሲሰግድ ይውላል። ንፍሮ በመቀቀል፣ ዳቦ በመጋገር፣ ጠላ በመጥመቅና ገድሏን በማንበብ ልመናና ጸሎት ያቀርብላታል። እርሷ የኖረችበት ነው በተባለው በጣና አካባቢ በሚገኘው ገዳሟ የሚሰበሰበው ሕዝብ ብዙ ነው። በዚያ ሰንጣቃ አለት የሚገኝ ሲሆን አንድ ሰው መጽደቅ እና አለመጽደቁን ለማወቅ በሰንጣቃው አለት በማለፍ እራሱን ይፈትናል። በዓለቱ ሾልኮ ካለፈ ጸድቋል ይባላል ካላለፈ ግን ተኮንኗል ይባላል። በብልሃት እንደምንም ያለፈ ሰው ጸድቄያለሁ ብሎ እራሱን አዘናግቶ ይኖራል።

Wednesday, April 17, 2013

የወንድሞች ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ማሳደዱን ቀጥሏል

(በጽሑፉ የተጠቀሰውን ደብዳቤ ከጽሑፉ መጨረሻ ያገኙታል)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ቁጥር በ7 ሚሊዮን መቀነሱን ቀደም ብላ በ2002 ዓ.ም ቤተ ክርስቲያኗ በይፋ አምናለች፡፡ “ኤጲስ ቆጶስ ጠባቂ ነውና ይጠብቅ ተብሏል። እንደ ተባለው መንጋው ተጠብቋል ወይስ አልተጠበቀም? መንጋው አልተጠበቀም የሚለው መልስ እንደሚጎላ ግልጽ ነው። ይህንንም የሚያሳየው ያለፈው ዓመት የሕዝብ ቈጠራ ነው። መንጋው በትክክል ከተጠበቀ 7,000,000 (ሰባት ሚሊዮን) ያህል ሕዝበ ክርስቲያን ለምን ቀነሰ? ይህን ያህል መንጋ በመናፍቃን ተሰርቋል ወይም ወደ ሌላ ሃይማኖት ተወስዷል ማለት ነው።” (የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ 17ኛ ዓመት የፓትርያርክነት በዓለ ሲመት 2002 ገጽ 34)።
ቤተክርስቲያን እንዲህ ስትል በአንድ ወገን መንጋው አለመጠበቁንና በዚህ ምክንያት መሰረቁን አምናለች፡፡ በሌላ በኩል ግን ሌሎች ሰረቁኝ ወሰዱብኝ ከማለት ባለፈ ምክንያቱን በሚገባ ያጤነችው አይመስልም፡፡ ሌሎች በውጪ አግኝተው ከወሰዷቸው በላይ እንደማኅበረ ቅዱሳን ያለ የወንድሞች ከሳሽና አክራሪ ቡድን እኔን አልመሰላችሁምና መናፍቃን ሆናችኋል በሚል በህገ ወጥ መንገድ ያሳደዳቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ምናልባት ለቁጥሩ መቀነስ የማቅ እጅም እንዳለበት መታመን አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ለወንድሞች ከሳሽ ለማቅ ይህ እንደሃይማኖተኝነት የሚቆጠር ትልቅ ገድል ነው፡፡ ማኅበሩ በዚህ ድርጊቱ ከማፈር ይልቅ “ቤተክርስቲያንን ከመናፍቃን እየጠብቅኩ ነው፡፡ እኔ ባልኖር ይህች ቤተክርስቲያን ትጠፋ ነበር” እያለ በመለፈፉ ብዙዎች ማቅን እንደቤተክርስቲያን ጠበቃ ያዩታል፡፡ ቢያስተውሉት ግን ይህ ቤተክርስቲያንን ሰው አልባ እያደረገበት ያለ የማቅ አጋንንታዊ ስራ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ 7 ሚሊዮን ምእመናን የጎደሉት ማቅ እኔ እየጠበኳት ነው እያለ አሳዳጅነቱን እንደ ገድል በሚያወራበት ዘመን ላይ መሆኑ ነው፡፡

Sunday, April 14, 2013

የአቶዎቹ ስፖንሰርሺፕ ጥያቄ አነጋጋሪ ሆኗል

Read in PDF
በጥቅምት 2004 ዓ.ም. የሲኖዶስ ስብሰባ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋናው ቤተክርስቲያኒቱን በቅጡ የማያውቋት ትምህርቷም የሌላቸውና በቤተ ክህነቱ አስተዳደር ቦታ ላይ የተቀመጡ አቶዎች ጉዳይ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ ያን ተከትሎም አቶ ተስፋዬ ከምክትል ስራ አስኪያጅነት ቦታ እንዲነሳ የተደረገ ቢሆንም አቡነ ፊልጶስ ቤት ገብቶ እግራቸው ላይ ወድቆ በማልቀስ ከዚህ ጉድ አውጡኝ አሊያ የት እደርሳለሁ ብሎ ተማጽኖ በአባ ፊልጶስ ጥያቄ ዳግም እንዲመለስ መደረጉን ምንጮቻችን ያስታውሳሉ፡፡ ከተመለሰ በኋላ እርሱ ብቻውን ኢላማ እንዳይሆን በማሰብ የእርሱ ቢጤ አቶዎችን በተቻለው ሁሉ ቦታ ቦታ አስያዘ፡፡ ከዚያም ከአባ ሳሙኤልና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በማበር የቤተክርስቲያኒቱን ሊቃውንትና መምህራን ወንጌል ሰባኪዎችንም ማሳደዱን በተለይም በደቡብ ክልል ማቅ በእውነተኛ የቤተክርስቲያን ልጆች የተነጠቀውን እስትራቴጂክ ቦታ ለማስመለስ ስልጣኑን ተጠቅሞ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ሲታገል መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

Thursday, April 11, 2013

የተስፋዬ ውብሸትና እስክንድር ኪራይ ሰብሳቢ ዕቅድ ከሸፈ

ቤተክህነቱን እያመሱ የሚገኙትና በኪራይ ሰብሳቢ ተግባራቸው እጅና ጓንት የሆኑት ተስፋዬ ውብሸትና እስክንድር ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለማጋበስ አልመው የወጠኑትና እንቅስቃሴ የጀመሩበት ደብዳቤ ከበላይ አካል በተጻፈ ደብዳቤ መታገዱ ተሰማ፡፡ እስክንድርና ተስፋዬ «አትራፊ ስራ» ብለው በህዝብ ግንኙነት መምሪያው ስም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሕይወት ታሪክ ዙሪያ 112 ገጽ ጋዜጣና መጽሔት አዘጋጅተናልና እስፖንሰር ሁኑን ብለው ለስድስት አብያተ ክርስቲያናት ደብዳቤ ከጻፉና ገንዘብ ለመሰብሰብ አሰፍስፈው ባሉበት ሁኔታ በስማቸው ሊነገድ መሆኑን መረጃ የደረሳቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በውጪ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ሃላፊ በብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማ ፊርማ የእነእስክንድር ደብዳቤ እንዲታገድ አዘዋል፡፡

Tuesday, April 9, 2013

የግንቦት 15ቱ ውግዘት መነሻ፣ ሂደት፣ ፍጻሜና ቀጣዩ ሲገመገም

ክፍል 13

«የእውነት ቃል አገልግሎት» ላይ የግንቦቱ (ግንቦት 15/2004 ዓ/ም) ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤው ያሰፈራቸውና «ኑፋቄ» ብሎ ካቀረባቸው ነጥቦች መካከል ቀጣዮቹን ነጥቦች መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርገን ኑፋቄ የተባሉት ነጥቦች ኑፋቄ መሆን አለመሆናቸውን እንመረምራለን።

 

«ሐ. የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ (ሥልጣነ ክህነት) ለጴጥሮስ ብቻ እና ለተወሰኑት ተተኪ ነን ባዮች የተሰጠ አይደለም» በማለት ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣውን የቤተክርስቲያናችንን ሥልጣነ ክህነት በመቃወም ጽፏል፡፡ የእውነት ቃል መጽሔት ሰኔ 2003 ዓ.ም እትም  ገጽ 11»

«መ. ለጴጥሮስ የተሰጠው የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ሥልጣነ ክህነት አይደለም፡፡ በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሆናል፡፡ በምድር የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሆናል የሚለው ሀይለ ቃል ኃጢአትን እንደሚያስተሰርይ አያሳይም በማለት ጽፏል፡፡  እውነት ቃል መጽሔት ሰኔ 1993 እትም ገጽ 13»

ቤተክርስቲያናችን የእግዚአብሔርን ቃል ለራሷ በሚመቻት መንገድ በመተርጎም ከምትጠቀምባቸው ጥቅሶች መካከል ከላይ የተጠቀሱትና እንደ ብሉይ ኪዳን ሁሉ በአዲስ ኪዳን ለተወሰኑ ሰዎች ክህነት ተሰጥቷል የሚለው ይገኝበታል፡፡ በፊደል «ሐ» የተጠቀሰው ከእውነት ቃል መጽሔት ላይ ሙሉ በሙሉ የተጠቀሰ አይመስልም፡፡ የሚፈለገው ክፍል ብቻ ተቆርጦ የወጣ ነው የሚመስለው፡፡ ይሁንና በቀረበው ላይ ተመስርተን ጉዳዩን ስንመረምረው ለጴጥሮስ የተሰጠው የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻ ስልጣነ ክህነት ነው ወይ? በፍጹም አይደለም፡፡

Sunday, April 7, 2013

ደብረ ዘይት

ምንጭ፦ የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ መጋቢት 28 2005 ዓ.ም (http://www.ashenafimekonen.blogspot.com/)
የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ ደብረ ዘይት ተብሎ ይጠራል፡፡ የጌታችን ዳግም መምጣትና የዘመኑ ምልክት የሚነገርበት ቀን በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተብሎ ተጠርቷል፡፡ ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ መምጣቱ ምልክት የተናገረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት ተባለ (ማቴ. 24÷ 3)፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ደብረ ዘይት ብሎ መሰየሙ ብቻ ሳይሆን በዕለቱም ያቀረበው ዝማሬ እንዲህ የሚል ነው፡-

ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወሰ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአን ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት

ትርጉም፡-
የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ሠራዊት ሁሉ ይነቃነቃል። ያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ ጌታችንም ከአእላፍ መላእክት ጋር በትእዛዙና በቃሉ መሠረት ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል፡፡ የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፡፡ በዚያች ሰዓት እርሱ ያድነን። እርሱ የሕይወት ባለቤት ነውና።

ቅዱስ ያሬድ የዘመረው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ነው፡፡ ጌታችን ሲመጣ ፍጥረት እንደማይፀና ኃጢአተኞች ደስታ እንደማይሰማቸው ይገልጣል፡፡ በኃይሉ ፊት ፍጥረት፣ በፍርዱ ፊት ኃጥአን መቆም አይችሉምና፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል። በብሉይ ኪዳን እመጣለሁ ብሎ መጥቷል፡፡ በአዲስ ኪዳንም እመጣለሁ ብሎ ቤተ ክርስቲያንን በተስፋ አስገዝቷታል፡፡ ፍጥረት ሁሉ የሚጠብቀው አንድ ታላቅ እንግዳ ከፊታችን ባለው ባልራቀው ዘመን ይመጣል፡፡ የሚመጣው በትሕትና ሳይሆን በልዕልና ነው፡፡ በከብቶች በረት ሊጣል ሳይሆን በደመና በዙፋን ተገልጦ ይመጣል፡፡ ስምዖን አረጋዊ እንደ ታቀፈው ሆኖ አይመጣም፣ ሰማይና ምድር የማይችሉት ሆኖ ይመጣል፡፡ ከእናቱ ጡትን እየለመነ አይመጣም፣ ለፍጥረት ሁሉ የሩጫውን ዋጋ ለመስጠት ይመጣል፡፡ ከሄሮድስ ፊት የሚሸሽ ሆኖ አይመጣም፡፡ ሰማይና ምድር ሲያዩት ከፊቱ ይሰደዳሉ፡፡ ለእኛ ለክርስቲያኖች መጣልን የምንለው እንግዳችን፣ ፈራጃችን እንጂ መጣብኝ የምንለው አይደለም፡፡

Thursday, April 4, 2013

አቶ ደስታ በጉቦ ቅሌትና ሊቀጳጳስን በመሳደብ ከሀላፊነቱ ተነሳ

በአቡነ ህዝቅኤል ላይ ክስ መስርቷል

አለችሎታው ለማቅ በነበረው ቅርበት ብቻ የምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጸሀፊ ሆኖ የተመደበው አቶ ደስታ በጉቦ ቅሌትና ሊቀጳጳስ አቡነ ህዝቅኤልን በስልክ “ባሪያ” ብሎ በመሳደብ ከሥራው ሀላፊነት መነሳቱ ተገለጸ፡፡

ደስታን በቅርበት የሚያውቁት የሊቀ ህሩያን ያሬድ ከበደው የሚይዙትን መኪና በማጠብ የቤተክህነት ስራ መጀመሩን ይገልጻሉ፡፡ ወደቤተክህነት ግቢ ለመግባት ምክንያት የሆነውም ለድግስ የሚሆን ጐላ ብረት ድስት ተሸክሞ መምጣቱ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ እግሩን ያስገባው አቶ ደስታ ቀስ በቀስ ወደቢሮ ስራ በመዘዋወር በሰበካ ጉባኤ መምሪያ ውስጥ ስራ አግኝቶ የልደት፣ የጋብቻ ….. ሰርተፌኬት ለማሰራት የሚመጡትን ገንዘብ መቀበል ጀመረ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ  ማህበረ ቅዱሳን በቤተ ክህነት ውስጥ የሚፈልጋቸውን ደብዳቤዎች በህገ ወጥ መንገድ ከመዝገብ ቤት እያስወጣ የደጀ ሰላምን ጽሁፎች ለሚያዘጋጀውና አሁን ወደሀራ ለተገለበጠው ለአሉላ ጥላሁን አዘውትሮ መስጠት መጀመሩንና ለዚህም የማኅበሩ ዋና ጸሀፊ አቶ ሙሉጌታ የኪስ ገንዘብ ይመድብለት እንደነበር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

Monday, April 1, 2013

ማኅበረ ቅዱሳን መዳናችን መቀደሳችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ መፈጸሙን ያምናል?

መጽሐፉ በውስጡ የያዛቸውን በርካታ እውነቶች ማኅበሩ እንደማያምን ይታወቃል፡፡ ሳያምንበት ታዲያ በስሙ እንዴት ሊያሳትመው ቻለ? የሚለው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም፡፡ ማኅበሩ መጽሐፉ ብዙ ፈላጊ እንዳለው እያወቀና አሮጌ ተራ ላይ ዋጋ ሰማይ መድረሱን እየሰማ በድጋሚ ሊያሳትመው ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ከዚህ ይልቅ አሳትሞ ያሰራጨውን ሰዎች እያነበቡ “እንዳይሳሳቱበት” ሰብስቦ አብዮታዊ እርምጃ ቢወስድበት ደስ ባለው፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን አሳታሚነት ለንባብ የበቃው የታላቁ ሊቅ የሊቀ ጉባኤ አባ አበራ “ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት” መጽሐፍ ከታተመ 10 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ማህበሩ መጽሀፉ የያዘውን እውነት በአንድም በሌላም መንገድ ሲቃወመው እንደኖረ አይካድም፡፡ ታዲያ የማያምንበትን መጽሐፍ ለምን አሳተመ? ካመነበትስ ይህንኑ እውነት ያመኑትን የቤተክርስቲያን ልጆች ተሀድሶ መናፍቅ እያለ ለምን ያሳድዳቸዋል? እስኪ በተጠቀሰው መጽሐፍ ከገጽ 176-178 ላይ የመንፈስ ቅዱስን ስራ በተመለከተ የሰፈረውን እናካፍላችሁ፡፡