Friday, May 31, 2013

በዘርፈ ብዙ ችግሮች ለተተበተበችው ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ያስፈልጋታል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ያወራንላትና ያስወራንላት፣ ብዙ ምዕት ዓመታትን ያስቆጠረች፣ ብዙ ሊቃውንትን ያፈራች፣ ለአገር ትልቅ ባለውለታ የሆነች ቤተክርስቲያን ነች፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ይህ ማንነቷ እየተሸረሸረ መጥቶ፣ ሊቃውንቷ ዝም እንዲሉ የተደረገባት፣ እንናገራለን ካሉም “ተሐድሶ-መናፍቅ” የሚሰኙባት፣ ከዚህ የተነሳ የስሕተት ትምህርቶች ያለአንዳች ከልካይ እንዳሻቸው የሚናኙባት፣ በሃይማኖት ትምህርት ረገድም ቢሆን ሊቃውንቱ ሳይሆኑ ህዝባውያኑ የሚመሯት፣ በከፍተኛ ደረጃ የምግባር ልሽቀት የሚታይባት፣ ዘረኛነት፣ ሙስናና ብልሹ አስተዳደር የሰፈነባት፣ እግዚአብሔር የማይፈራባት ሰው የማይታፈርባት የጉቦና የዝርፊያ ቤት ሆናለች፡፡ በብዙ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ችግሮች የተተበተበች ሆና ስናያት ታዲያ መታደስ ብቻ ሳይሆን ከተቻለ ፈርሳ መሠራት ያለባት ቤተ ክርስቲያን መሆኗ አያጠራጥርም፡፡

አምና እውነተኞችንና እውነተኛ ትምህርታቸውን ፍትሐዊና መንፈሳዊ ባልሆነ መንገድ ያወገዘው ፍርደ ገምድሉ ሲኖዶስ፣ አሁን ደግሞ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መሪነት በሙስና ላይ ዘመቻ ሊከፍት መሆኑ ተሰምቷል፡፡ ሙስና የተባለው ወንጀል የተለያዩ ስሞች እየተሰጡትና በተለያዩ ስሞች እየተጠራ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሕጋዊነት ያህል ቦታ ተሰጥቶት ሲሰራበት የኖረና አሁንም ድረስ ያለ በመሆኑ ዘመቻውን እንዲህ ቀላል አያደርገውም፡፡ መጠኑና የመጠየቂያው መንገድ ይለያይ እንጂ ሙስና አንዳንዶች እንደሚሉት በአቡነ ጳውሎስ ዘመን የተጀመረ አይደለም፡፡ ባይሆን ወደላቀ ደረጃ ከፍ ብሎ ሊሆን ይችላል፡፡

በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ በዳላስ ቴክሳስ በሚገኘው የሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

የዛሬ 2ወር አካባቢ ወደ ስደተኛው ሲኖዶስ የተቀላቀለችው የዳላስ ደብረ ምኅረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሲኖዶሱን መደበኛ ጉባኤ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች።

ሲኖዶሱ ተጨማሪ ጳጳሳትን በመሾም ዙሪያና በቤተ ክርስቲያን አንድነት እና እርቅ ጉዳሆች ላይ እየተወያየ ሲሆን ሌሎችም በርካታ የመወያያ ርዕሶች እንዳሉት ምንጮቻችን ጠቁመዋል። የስብሰባውን ሂደትና ውጤት በተመለከተ የሚደርሱንን መረጃዎች እየተከታተልን እናቀርባለን። 

Thursday, May 30, 2013

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለምን ተሐድሶ ያስፈልጋታል?

ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር እና በክርስቶስ ደም የታደሱና የተቀደሱ የምእመናን ጉባኤ ናት፡፡ ይህቺን አማናዊት ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ታሪኳን ስናጠና በእግዚአብሔር ሐሳብ ውስጥ የሰው ሐሳብ እየተቀላቀለ እና ጤናማውንና ርቱዕ የሆነውን አስተምህሮ የሚያደፈርሱ ሰብኣዊ፣ አጋንንታዊና ዓለማዊ ሐሳቦች በተለያየ ሁኔታና መንገድ ወደ አማናዊቷ ቤተ ክርስቲያን ዘልቀው እየገቡ እውነተኛ የሆነውን መንፈሳዊ ትምህርትም ሲያደፈርሱ እናያለን፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ያሉ ለእውነተኛው የእግዚአብሔር ሐሳብ ቀናዕያን የሆኑ ቅዱሳን የእግዚአብሔርን ሐሳብ በሚያደፈርሱ አስተሳሰቦች እና ግለሶቦች ላይ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሲሰጡና አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ ሲወስዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናነባለን፡፡ ምክንያቱም ተሐድሶ አዲስን ነገር አፍልቆ ማምጣትና በነበረ እውነት ላይ መጨመር ሳይሆን ከጌታችንና ከሐዋርያት የተቀበልነውን የሚያድነውን መለኮታዊ መገለጥ (አስተርእዮ) የሚጋርድ ትምህርትና ድርጊት ሲከሠት መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት ለመጠበቅ የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ስለሆነ ነው፡፡

Sunday, May 26, 2013

ሐራ ለምን ተቈጣች?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሐራ ዘተዋሕዶ የተባለችው የደጀሰላምና መሰሎቿ ታናሽ እህት በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ከፍታለች፡፡ ዘመቻው በምዕራብ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተንሰራፋውን ሙስና የታከከ ሆንም በዋናነት ግን የማቅ ዋና መጠቀሚያ የነበሩትና ሀገረ ስብከቱን በሙስና ያስቸገሩትን አቶ ደስቢታ እና አባ ኅሩይ ከሀላፊነታቸው መነሣታቸው እንደሆነ ከሐራ ቁጣ የተሞላበት ሀተታ መረዳት ይቻላል፡፡ እውነት ነው፤ ሙስናና ብልሹ አሰራር ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ አህጉረ ስብከቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በሙስና እየተጠረጠሩ ጩኸት ሲበዛ ከቦታቸው የሚነሱ ሰዎች በሌላ ሹመት ወደሌላ ክፍል መዛወራቸው ከዚህ ቀደም እንዳልነው የጠገበውን አንስቶ የተራበውን የመተካትና የአበላሉን ስልት ረቂቅ ማድረግ ነው፡፡ ሐራ እንደጻፈው አባ ሕዝቅኤል በሙስና መዘፈቃቸውን ካወቀ እስከ ዛሬ ለምን ዝም አለ? ለምን በጊዜው ይፋ አላደረገም? ለምን የእነአባ ህሩይን መነሳት ምክንያት አድርጎ ሊከሳቸው አሰበ? የሚሉትና ይህን የመሳሰሉት ጥያቄዎች በሐራ ላይ ይነሳሉ፡፡

Thursday, May 23, 2013

የግንቦት 15ቱ ውግዘት መነሻ፣ ሂደት፣ ፍጻሜና ቀጣዩ ሲገመገም

ክፍል 15

የግንቦቱ ሲኖዶስ በእውነት ቃል አገልግሎት ላይ ያቀረበውን የ“ኑፋቄ” ነጥቦች መመልከታችንንና በእግዚአብሔር ቃል መመዘናችንን በዚህ ጽሑፍም እንቀጥላለን፡፡ ለዛሬው የምንመለከታቸው የሚከተሉትን ሁለት ነጥቦች ይሆናል፡፡

“ለ. ‘ቤዛ ዓለም ኢየሱስ ብቻ እንጂ ማርያም ቤዛ ዓለም መባል አይገባትም’ በማለት በአማላጅነቷ ቤዛ የሆነችን የእመቤታችን አማላጅነት ይቃወማል፡፡ መጽሐፈ ሰዓታት በመቅደሱ ሚዛን ገጽ 12 እና 13”
“ሐ. ጸሎታ ለማርያም ወስእለታ ያድኅነነ እመዓተ ወልዳ - የሚለውን ጸሎት ‘እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ፍቅር የተነሣ ያደረገውን የማዳን ሥራና የከፈለውን መሥዋዕትነት የሚቃወም ልመና ነው’ በማለት በቤተ ክርስቲያናችን የሚጸለየውን የቤተ ክርስቲያን ጸሎት ያጥላላል፡፡ መጽሐፈ ሰዓታት በመቅደሱ ሚዛን ገጽ 20”

“ቤዛ” የሚለውን የግእዝ ቃል የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት የሚፈታው በቁሙ (ቤዛ) ዋጋ፣ ካሳ፣ ለውጥ፣ ምትክ፣ ዐላፊ፣ ዋቢ፣ ዋስ፣ መድን፣ ተያዥ፣ ጫማ፣ ጥላ፣ ጋሻ የመሰለው ሁሉ” ነው በማለት ነው፡፡ (ገጽ 266) የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ደግሞ “ቤዛ የተያዘን ወይም የተወሰደን ነገር ለማስመለስ የሚከፈል ዋጋ፣ ካሳ፣ ለውጥ” ነው ይላል፡፡ (ገጽ 116) ቤዛ የሚለው ቃል ካለው ይህን መሰል ፍቺ አንጻርና እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትም “ቤዛ” የሚለው ስም የሚቀጸለው ለእውነተኛው ቤዛ ማለትም ስለ ሰው ልጆች ምትክ ሆኖ ለሞተውና ሕይወቱን ሰጥቶ ያመኑበትን ነጻ ላወጣው ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ይህን በግልጥ ይመሰክራል፡፡ ከእርሱ በቀርም ለሰው ልጆች ቤዛ አለ አይልም፡፡

Monday, May 20, 2013

“ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” የተሰኘ አዲስ ብሎግ ሥራ ጀመረ

ተሐድሶ ከእግዚአብሔር መንገድ የወጡ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንገድ የሚመለሱበት የንስሐ መንገድ ነው፡፡ ተሐድሶ የእግዚአብሔር ሐሳብ ቢሆንም ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ሕግ ከመመራት ይልቅ በራሳቸው ፈቃድ መመራትና መኖር የሚፈልጉ ሰዎች የተሐድሶን ግብር ሲቃወሙ ኖረዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ግብሩን ብቻ ሳይሆን ስሙንም ጭምር እየጠሉና እያስጠሉ፣ ቀንድና ጭራም እያበቀሉለት እየተቃወሙት ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በመነሣት ተሐድሶ የሚለው ስም በአሉታዊና በአፍራሽ መልኩ እንዲታሰብ፣ አዲስ ሃይማኖት ተደርጎም እንዲቆጠር ለማድረግ እየጣሩና ተሐድሶ የእግዚአብሔር ክቡር ሐሳብ መሆኑን ያልተረዱ ወገኖችን እያሳሳቱ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

የእግዚአብሔር ሐሳብ የሆነውን የቤተ ክርስቲያንን ተሐድሶ እውን ለማድረግ ተሐድሶን በትክክለኛ ገጽታው ማቅረብ ጊዜው የሚጠይቀው ዓቢይ ተግባር በመሆኑ የብሎጉ መከፈት ተሐድሶን በተሳሳተ መንገድ እያቀረቡ ያሉ ክፍሎችን የተዛባ አመለካከት ሚዛን እንደሚያስጠብቅና የቤተክርስቲያንን መታደስ ለማፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ብሎጉን ለመጎብኘት የሚከተለውን አድራሻ ይጫኑ http://www.tehadeso.com

Friday, May 17, 2013

የማቅ ታማኝ አገልጋይ አባ ኅሩይ ወንድ ይፍራው ከሥራ አስኪያጅነታቸው ታገዱ

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለ4 ከተከፈለ በኋላ የምዕራብ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት አባ ሕሩይ ወንድይፍራው ከስራ አስኪያጅነታቸው መታገዳቸውን የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለመነኩሴው በጻፈው የእግድ ደብዳቤ አስታወቀ፡፡ በደብዳቤው እንደ ተገለጸው ለአባ ሕሩይ መታገድ ምክንያቶቹ የተመደበቡበትን የሥራ ሃላፊነት በአግባቡ አለመወጣትና ከሊቀ ጳጳሱ መመሪያ ሳይቀበሉና ትእዛዝ ሳይሰጥ ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ የሰራተኛ ቅጥር፣ የደመወዝ ጭማሪና የሰራተኛ ዝውውር ማድረግን እንደሚመለከት ለማወቅ ተችሏል፡፡ እነዚህን ህገወጥና ከፍተኛ ጉቦ የሚበላባቸውን ተግባራት ሲፈጽሙ መቆየታቸው ስለተደረሰበት ከስህተታቸው እንዲታረሙ በየደረጃው ከቃል እስከ ጽሑፍ ምክርና ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም አባ ሕሩይ ማስጠንቀቂያውን ከቁብ ሳይቆጥሩ በተበላሸ አሰራራቸው በመቀጠላቸው ምክንያት የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁእ አቡነ ሕዝቅኤል ከሥራ አስኪያጅነት እንዳገዷቸው ደብዳቤው ያመለክታል፡፡

Tuesday, May 14, 2013

ልደታ በአታ እና ኪዳነ ምሕረት ማናት?

ይህ ጥያቄ ላልተማሩ ካህናትና ምእመናን ቢቀርብ “እመቤታችን ናታ!” እንደሚሉ አያጠራጥርም፡፡ ምክንያቱም “ልደታ” “በአታ” እና “ኪዳነ ምሕረት” በሚሉ ስሞች ጽላት ተቀርጾአል፤ ቤተክርስቲያን ታንጿል፤ መጽሐፍም ተጽፎ ሊሆን ይችላል፡፡ ሊቃውንቱና የተማሩ ምእመናን ግን እነዚህ ስያሜዎች በሂደት የማርያም መጠሪያ ስሞች ተደርገው ተወሰዱ እንጂ ልዩ ልዩ ተግባራት የተከናወኑባቸውን ዕለታት ለማሰብ የተሰጡ ስያሜዎች እንደሆኑ ሊነግሩን ይችላሉ፡፡ አክለን “ቤተክርስቲያንን የሚመሯት ሊቃውንቱ ናቸው ወይስ ያልተማሩና ትምህርተ ሃይማኖት የሌላቸው ካህናትና ደባትራን?” ብለን ብንጠይቅ ደግሞ ምላሹና እውነታው ለየቅል ይሆንብናል፡፡ ምክንያቱም ሊቃውንቱ ናቸው ካልን ማርያም የተወለደችበትን ቀን ለማሰብ ቀን መለየታቸው ልክ ባይሆንም ልክ ይሁን እንበልና ለዚህ መታሰቢያነት በተለየው ቀን ስም ጽላት መቅረጽንና ቤተክርስቲያን ማነጽን ግን ምን አመጣው? የሚል ጥያቄ ያስከትላል፡፡ ምክንያቱም ዕለቱ ከመታሰብ አልፎ በሴት ስም ተሰይሞ ወደመመለክ እየተሸጋገረ ነውና፡፡ ስለዚህ ሊቃውንቱ ይህን ሊያደርጉ እንደማይችሉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ካደረጉ ግን ሊቃውንት የሚል የሙያ ስም ሊሰጣቸው አይገባም፡፡

Wednesday, May 8, 2013

የግንቦት 15ቱ ውግዘት መነሻ፣ ሂደት፣ ፍጻሜና ቀጣዩ ሲገመገም

ክፍል 14

«የእውነት ቃል አገልግሎት» ላይ የግንቦቱ (ግንቦት 15/2004 ዓ/ም) ሲኖዶስ ቃለ ጉባኤው ያሰፈራቸውና «ኑፋቄ» ብሎ ካቀረባቸው ነጥቦች መካከል ቀጣዮቹን ነጥቦች መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት አድርገን ኑፋቄ የተባሉት ነጥቦች ኑፋቄ መሆን አለመሆናቸውን እንመረምራለን።

 

«ሀ. ብቃት ያለውን አማላጅነት ትቶ እንደኛው ድካምን የሚለብሱና ለእነርሱ ለራሳቸው የክርስቶስ አማላጅነት የሚያስፈልጋቸውን አማላጅ ማድረግ ወይም በክርስቶስ ላይ ተጨማሪ አማላጅ አድርጎ ማዳበል ትልቅ ውደቀት ነው» በማለት ክርስቶስን አማላጅ አድርጎ የቅዱሳንን አማላጅነት ውድቀት በማለት ተሳድቧል።  መጽሐፈ ሰዓታት በመቅደሱ ሚዛን - ገጽ 64»

ስለአማላጅነት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውና በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚታመነው የአማላጅነት ትምህርት ፈጽሞ አይገናኝም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳን በሕይወተ ስጋ ሳሉ ምልጃ ሲያቀርቡ እናነባለን፡፡ ካንቀላፉ በኋላ ግን ምልጃ ያቀረቡበት ሁኔታ የለም፡፡ ካንቀላፉ ቅዱሳን ጋር ሕያዋን ቅዱሳን የሚገናኙበት እድል ስለሌለም «ለምኑልን አማልዱን» ብለው ቢጮሁ ሰሚ የሌለው ጩኸት ነው የሚሆነው፡፡

Monday, May 6, 2013

እንኳን ለብርሃነ ትንሳኤው በሰላም አደረሳችሁ!ትንሣኤን በትንሣኤ በሚል ርዕስ ዲያቆን አሸናፊ ብሎግ ላይ  የተጻፈውን ጽሑፍ እንዲያነቡ እንጋብዛለን።