Wednesday, June 26, 2013

ሐረርን የሚበጠብጡ አባ አብርሃምና ግብረ አበሮቻቸው ናቸው

ሐረርን የሚበጠብጡ አባ አብርሃምና ግብረ አበሮቻቸው ናቸው
ለሐራ ዘተዋሕዶ ሐሰተኛ ዘገባ የተሰጠ ትክክለኛ ምላሽ
ክፍል ሁለት
ታዛቢ ከሐረር
 አስመሳዩ ጳጳስ አብርሃምና ጉዱ
አባ አብርሃም ብዙ ጉዶች ያሉበት ሰው መሆኑን ከዚህ ቀደም “የጉድ ሙዳይ” በሚል ስም ማንነቱ ሲገለጽ መኖሩ የሚታወስ ነው፡፡ በእርግጥም ሰውዬው የጉድ ሙዳይ ነው፡፡ ከባሕር ዳር እስከ አዲስ አበባ ራጉኤል፣ ከአዲስ አበባ እስከ አሜሪካ አሁንም በሐረር ብዙ ጉዶች ያሉበት የጉድ ሙዳይ ነው፡፡ የጵጵስና ልብስ የለበሰውና በማንነቱ ግን ነውረኛ የሆነው አባ አብርሃም ምሥራቅ ሐረርጌ ከተመደበበት ጊዜ አንስቶ ከሰራቸው ኢክርስቲያናዊ ስራዎች መካከል አንዳንዶቹን ለመጥቀስ እንሞክራለን፡፡
1.    ዘረኛ ነው
አባ አብርሃም ወደሀገረ ስብከታችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ 98% የሚሆኑትን ከምስራቅ ጎጃም የሆኑትን የወንዙን ልጆች ሲጠቅም ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ፦
·        አቡነ ማርቆስ በስነ ምግባር ብልሹነቱ ያባረሩትንና መሰሉን “መነኩሴ” ከደብረ ማርቆስ በማስመጣት በሌለበትና ባልሰራበት ከታህሳስ 1 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ደሞዝ እንዲከፈለው አድርጓል፡፡ መነኩሴው  ሀገሩን የረገጠው ግን ጥር 9/2005 ዓ.ም. ነበር፡፡
·        ቄስ ፋሲል አጥናፉ የተባለውንና ለዘረኛ አላማው ዋነኛ አቀንቃኝ የሆነውን ሰው፣ አካሉ ብቻ ሳይሆን ልቡም የጎበጠበት ጊዜው አሸናፊ የተባለው ሰው አቅራቢው ሆኖ የቅርሳ ቅርስ መምሪያ ሃላፊ ተደርጓል፡፡ ይህም የሆነው ለቦታው የሚመጥኑትን የዲግሪ ምሩቅ የሆኑትን መምህር ባዩን ከሚሰሩበት የቅርሳ ቅርስ መምሪያ ያለ ምንም ምክንያት ለፋሲል ሲባል በማፈናቀልና ከሀገረ ስብከቱ ወደ ወረዳ በማዛወር ነው፡፡ አባ አብርሃም ፋሲል አጥናፉን የቅርሳ ቅርስ ክፍል ማድረጉ አላረካ ቢለው፣ ከዚያ አንሥቶ የጽ/ቤቱ ገንዘብ ያዥ የነበሩትን በኩረ ትጉሃን በላይሁን ሞልቶትን በተመሳሳይ ሁኔታ በማባረር ፋሲል አጥናፉን የሀገረ ስብከቱ ገንዘብ ያዥ በማድረግ ሾሞታል፡፡ ይህም የሆነው የኪዳነ ምህረትን ገንዘብ ያለተቀናቃኝ ለመዝረፍ እንዲያመቸውና በተጠናወተው የዘረኛነት ልክፍት ምክንያት ነው፡፡

Sunday, June 23, 2013

ሐረርን የሚበጠብጡ አባ አብርሃምና ግብረ አበሮቻቸው ናቸው

ሐረርን የሚበጠብጡ አባ አብርሃምና ግብረ አበሮቻቸው ናቸው
ለሐራ ዘተዋሕዶ ሐሰተኛ ዘገባ የተሰጠ ትክክለኛ ምላሽ
ክፍል አንድ
ታዛቢ ከሐረር
ሰሞኑን ሐራ ዘተዋህዶ የተሰኘው የማቅ አንድ አንጃ ድረገጽ በሀገረ ስብከታችን በአባ አብርሃምና በግብረ አበሮቹ እየተፈጸመብን ያለውን የዐመጽ ሥራ ጽድቅ አስመስሎና ሸፍኖ እውነተኞቹን ሐሰተኛ ሐሰተኞቹን ደግሞ እውነተኛ ለማስመሰል የሞከረበት የሐሰት ዘገባ በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡ ሐራ “የተሐድሶ መናፍቃንና ጥቅመኞቻቸው የሐረር ///ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን ከሀ/ስብከቱ አስተዳደር ለመለየት እየቀሰቀሱ ነው” በሚል ርእስ ጁን 15/2013 እና ጁን 18/2013 ደግሞ “ከሓላፊነቱ የታገደውአባጳውሎስ ከበደ ከአስተዳዳሪነቱ ተነሣ” በሚሉ ርእስ የጻፈው የሐሰት ዘገባ ከእውነታው ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ የደብሩን ካህናትና ምእመናንም በእጅጉ ያሳዘነ ነው፡፡ እርግጥ ከማቅና ከነፍስ አባቱ ከአባ አብርሃም ከግብር አበሮቻቸውም ከዚህ የተሻለ ነገር አንጠብቅም፡፡ ሆኖም እውነቱ መገለጡ ስለማይቀር ከዚህ ቀጥሎ በተዛባ መንገድ ለቀረቡት ሀሰተኛ ዘገባዎች ተራ አሉባልታዎችን ትተን እውነተኛውን ነገር ለማቅረብ ተገደናል፡፡

1.    ሀገረ ስብከቱ የደ////ቤ/ክ/ሰ/ት የጌቴሰማኒ ቅድስት ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያንን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲያስተዳድር እንደነበር እና ከእርሱ የሚያገኘውንም ገቢ መ/ጽዮን አባ ጳውሎስ ከበደ እና ሌሎች ምእመናን ሲዘርፉት እንደነበር ተደርጐ ተገልጦአል፡፡

Friday, June 21, 2013

ሙሰኞችን ተጠያቂ በማድረግ እንጂ ከክፍል ወደ ክፍል በማዘዋወር ሙስናን መዋጋት አይቻልም

በቤተ ክርስቲያን የተንሰራፋውንና ቅጥ ያጣውን ዝርፊያ ለመከላከል በፓትርያርክ ማትያስ የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ የፀረ ሙስና አቢይ ኮሚቴም ተሰይሟል ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ በሙስና እንደተዘፈቁ የሚነገርላቸው ሰዎች ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርአት በፍጥነት መዘርጋትና መጠየቅ ሲገባ፣ ከአንዱ ክፍል አንስተው ወደሌላ በማዛወር ሙስናን ማባባስ እንጂ መቀነስ እንደማይቻል በርካታ የቤተክህነት ሰራተኞችና በአንዳንድ አድባራት የሚገኙ ካህናት እየገለጹ ነው፡፡ ስለሙስና ከዚህ ቀደም በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ይወራ እንደነበርና በተለይ አባ ሳሙኤል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በነበሩ ጊዜ ለሚዲያ ፍጆታ የሚውል ስብሰባ ተደርጎ ሙስናን መዋጋት እንደሚገባ መመሪያ ተሰጥቶበትና በዜና ቤተክርስቲያን ላይ እስከ መዘገብ ደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን ትልቁን ሙስናና የስልጣን ብልግናን ይፈጽሙ የነበሩት አባ ሳሙኤል እንደነበሩ የሚረሳ አይደለም፡፡ ዛሬ በሙስና ላይ ተከፈተ የተባለው ዘመቻ የአንድ ሰሞን ወሬ ሆኖ እንዳይቀር ከፍተኛ ስራ መሰራት እንዳለበት ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ አሊያ በቤተ ክህነት በሙስና ላይ እንዲህ አይነት አቋም የተወሰደው መንግስት በአንዳንድ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ከመንግስት ጋር ለመመሳሰል ነው የሚሉ አሉ፡፡

ሙስናውን መዋጋት ሳይውል ሳያድር መጀመር አለበት፡፡ መጀመር ያለበትም በሙስና ተጠርጥረው ከቦታቸው እንዲነሱ በተደረጉ ሰዎች ላይና ከዚህ ቀደምም የገንዘብ ጉድለት የተገኘባቸውና ልዩ ልዩ ሙስናዊ ወንጀል የፈጸሙ የቤተክህነት ባለስልጣናት ሁሉ መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በሙስና ተጠርጥረው ከቦታቸው በተነሱት በአባ ህሩይና በአቶ ደስታ ላይ ክስ ተመስርቶ ጉዳያቸው በሕግ መታየት አለበት እንጂ ከነበሩበት ቦታ ተነስተው ወደሌላ ቦታ በመዛወር ብቻ መታለፍ የለባቸውም፡፡ ከሰሞኑም ከሃላፊነታቸው በተነሱት በአቶ ተስፋዬ እና በአቶ እስክንድር ላይ ተመሳሳይ እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡

Wednesday, June 19, 2013

የዘመን ምስክር

(ምንጭ፦ ጮራ www.chorra.net)
በዚህ ዐምድ ለቤተ ክርስቲያን መሻሻልና መለወጥ የተጋደሉ፥ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራን የሠሩ አበውን ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ አሁን ላለውና ለቀጣዩ ትውልድ አርኣያ እንዲሆን እናስተዋውቃለን፡፡


ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ቀዳማዊ የወንጌል እስረኛ (1888 - 1974 ዓ.ም.)
በዘመናት ውስጥ የተፈጸመና ታሪክ የመዘገበው መልካምም ሆነ ክፉ ሥራ ሊረሳ አይችልም፡፡ ለጊዜው እውነት እንደ ሐሰት ይቈጠር$ ሐሰት ደግሞ የእውነትን ስፍራ ይቀማ ይሆናል፡፡ በደካሞች ግምትም እውነት ርቆ ሊቀበርና የሐሰት ዐፈር ሊጫነው ይችላል፡፡ እውነት ግን ለጊዜው እንጂ ተቀብሮ ሊቀር፥ ፈጽሞ ሊሰወርና ሊረሳ አይችልም፡፡ እውነት ሲወጣ ቀድሞ ተሰጥቶት የነበረው ዝቀተኛ ግምት ይለወጣል፡፡ በተቃራኒው ሐሰትም ከተሰቀለበት የክብር ማማ ላይ ይወርዳል፡፡ የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የተጋድሎ ታሪክ ከተቀበረበት መውጣቱና ተገቢውን ስፍራ ማግኘቱ እውነትና እውነተኞች ተቀብረው እንደማይቀሩ ያሳያል፡፡

Thursday, June 13, 2013

በሙስና ላይ የተከፈተው ዘመቻ ተሐድሶን በማንቀሳቀስ ማቅን በማስታገስ ስብከተ ወንጌልን በማጠናከር ቢጀመር

ላይፍ መጽሔት በግንቦት 2005 ዓ.ም እትሙ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከተሾሙ ወዲህ  በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በተለይም ሙስናን በተመለከተ ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን  ዘግቧል፡፡ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ መጽሄቱ እንደዘገበው ፓትርያርኩ በእጅ መንሻነት የተበረከተላቸውን የወርቅ መስቀል እንዲመለስ ማድረጋቸው ይጠቀሳል ብሏል፡፡ “አቡኑን እንኳን ደስ ያለዎት በማለት ታማኝነታቸውን ለማሳየት የተወሰኑ የቤተክርስቲያንና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ገንዘብ በማዋጣት የወርቅ መስቀሉን በመግዛት ወደ ፓትርያርኩ ይመጣሉ፡፡ መስቀሉ በአስተዳዳሪዎቹ ደሞዝ እንደማይሸፈን የጠረጠሩት ፓትርያርኩ ለመሆኑ ይህንን መስቀል የገዛችሁበት ገንዘብ ከየት ተገኘ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ መልሱ ቀላልና ግልጽ ነበር፡፡ አስታዳዳሪዎቹ እጅ መንሻ ለማቅረብ የሚያስተዳድሩትን ቤተክርስቲያን ካዝና ገልብጠዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ነገር የተለመደ በመሆኑ አስተዳዳሪዎቹ በአሁኑ ፓትርያርክ አቋም ተደንቀዋል፡፡ አቡኑ እንዲህ ዓይነት ነገር ማንም እንዳያደርግ በማስጠንቀቅ መስቀሉ ለቤተክርስቲያን ገቢ እንዲደረግ አዘዋል፡፡” (ላይፍ ገጽ 21)፡፡

Wednesday, June 12, 2013

አዲሱ የዶክተር አባ ገ/ሥላሴ ጥበቡ መጽሐፍ፦ ሲኖዶሳዊ ጉዞ በኦርቶዶክሳዊ ቀኖና ሲመዘን

 
(ከክንፈ ገብርኤል - ሲያትል)

«ሲኖዶሳዊ ጉዞ በኦርቶዶክሳዊ ቀኖና ሲመዘን» በሚል ርእስ በ2013 ዓ.ም ታትሞ ለንባብ የበቃው የዶክተር አባ ገ/ ሥላሴ መጽሐፍ በቅርቡ በተካሄደው የውጭው ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ከአንዳንድ የሲኖዶሱ አባላት ተቃውሞ እንደደረሰበት፤ መጽሐፉንም ለማገድ ኮሚቴ እንደተቋቋመ እንዲሁም በከተማችን ያሉ ጳጳስ መጽሐፉ እንደተወገዘ አድርገው እንደተናገሩ  ከአንድ ወዳጄ ሰማሁና ለማንበብ ወሰንኩ። ብዙ ጊዜ ተቃውሞ የሚገጥመው ነገር ቁም ነገር እንዳለው ስለሚሰማኝ ትኩረቴን ይስበዋል።እውነትም ቁም ነገር አገኘሁበትና  ለአንባቢያን ለማካፈል ወሰንኩ።
  
ጸሐፊው አንዳንድ የቤ/ክርስቲያን አስተዳደራዊ የስሕተት መንገዶች የሚሏቸውን አካሄዶች አጋልጠዋል። የጥንት ኦርቶዶክሳውያን አባቶች በመንፈስ ቅዱስ እገዛ ይመሩበት የነበረውን የቤተ ክርስቲያን መመሪያ አጭርና ግልጽ በሆነ መንገድ ግልጥልጥ አድርገው አቅርበውታል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የፖለቲከኞች መንጠላጠያ መድረክ መሆኗንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ከነገሥታት ጋር በመቀማጠል ክብሯን አሳልፈው መስጠታቸውን፤ የክርስቶስን ተልእኮ ወደ ኋላ ትተው የነገሥታቱን ተልእኮ ማገልገል መጀመራቸውን የገለጡ ሲሆን፣ ዛሬ ላይ የሚገኙ ጳጳሳትም ከጥንቱ በባሰ ሁኔታ ያለ ይሉኝታ ከፖለቲከኞች ጉያ ሄደው መለጠፋቸውን አጥብቀው ኮንነዋል። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም መጠለያ ከአድልዎ እና ከምድራዊ ሥርዓት ነጻ ሆና ሁሉንም በእኩልነት ማገልገል እንደሆነ ትኩረት ሰጥተው ያብራራሉ። ሁሉንም በየቦታው ማስኬድ ሲገባ ፖለቲካን እና ሃይማኖትን መደበላለቅ ጤና የሚሰጥ እንዳልሆነም ያስረዳሉ።

Monday, June 10, 2013

የደቂቀ እስጢፋኖስ ገዳማት በሊባኖስ ተገኙ

ለብዙ ምእት ዓመታት ታሪካቸው ተቀብሮ የኖረውና በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አማካይነት ከመቃብሩ እንዲወጣና ትንሣኤን እንዲያገኝ የተደረጉትና በአንድ ጥራዝ የታተሙት የአባ እስጢፋኖስና የተከታዮቻቸው የገድል መጻሕፍት  ማለትም ገድለ አባ እስጢፋኖስ፣ ገድለ አበው ወአኀው፣ ገድለ አባ አበከረዙንና ገድለ አባ ዕዝራ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ትልቅ መነቃቃትን እየፈጠሩ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች ደቂቀ እስጢፋኖስን ሌላ ዓላማ የነበራቸው እንጂ የተሐድሶ እንቅስቃሴ መሪዎች አይደሉም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቻቸው ግን የተሐድሶ እንቅስቃሴ መሪዎች መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሩቅ ሳንሄድ በገድላቸው የተንጸባረቁት ተሐድሶአዊ ሐሳቦችና በእነርሱ ላይ ስደት ካወጀባቸው ከአፄ ዘርአ ያዕቆብ በኩል የተሰጣቸው ስምና ከተጻፈባቸውና ከተነገረባቸው ውንጀላ መረዳት ይቻላል፡፡

Thursday, June 6, 2013

ሰሚ ያጣው የጉጂ ቦረና ሃገረ ስብከት ምእመናን አቤቱታ በሲኖዶሱ ስብሰባ ላይ ድንጋጤ መፍጠሩ ተሰማ

ምእመናኑ ለጥያቄያቸው ምላሽ ካላገኘ አብያተ ክርስቲያናቱን በገለልተኛ
አስተዳደር ለማስተዳደር እንደሚገደዱ አስታውቀዋል
“በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንደሚባለው ማኅበረ ቅዱሳን እያመሳቸው ካሉ አህጉረ ስብከቶች አንዱ የሆነው የጉጂ ቦረና ሀገረ ስብከት በጥቂት የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎችና ከእነርሱ ጋር ትስስር በፈጠሩት አባ ገብርኤልና በቤተክህነት ሥራ አስኪያጆች ምክንያት ከአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና ጀምሮ እስካሁን ድረስ እየታመሰ ይገኛል፡፡ ምእመናኑ “ከጉጂ ቦረና ሊቀ ጳጳስ ጀምሮም ስራ አስኪያጁና አንዳንድ የወረዳ ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጆች ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ለአንድ ማኅበር ህልውና የሚደክሙ መሆናቸውን” ቢገልጹም፣ ለአቤቱታቸው እየተሰጣቸው ያለው ምላሽ አታካችና ተስፋ አስቆራጭ እየሆነባቸው ስለመጣ ግንቦት 27 ቀን 2005 ዓ.ም. በጻፉት ማመልከቻ በመንግስት በኩል በተደረገው ማጣራትና በቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት ጥያቄያቸው የማይመለስ ከሆነና ገለልተኛ ሊቀ ጳጳስ ካልተመደበላቸው ሥር የሰደደው ችግራቸው እስኪቀረፍ ድረስ ሁኔታውን በቅርብ ለሚከታተለው ለመንግስት አሳውቀው አብያተ ክርስቲያናቱን በገለልተኛነት ለማስተዳደር የሚገደዱ መሆኑን አሳወቁ፡፡ ለሲኖዶሱ አስደንጋጭ የሆነው አቤቱታም ይኸው መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

Tuesday, June 4, 2013

ሲኖዶሱ አባ ኤዎስጣቴዎስ ላይ ውሳኔ አሳለፈ፤ የእስክንድርን ቢሮ አጠፈ፤ አለቦታው የተቀመጠውን ተስፋዬ ውብሸትን ከምክትል ስራ አስኪያጅነቱ አነሣ

Read in PDF

ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገው ስብሰባ በወሲብ ቅሌት ከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ የተባረሩት አባ ኤዎስጣቴዎስ ወደአገር ቤት ተመለስውና በሲኖዶስ ፊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ እንዲያስረዱ ካልሆነ ግን እንዲወገዙ ውሳኔ ማሳለፉ ተነገረ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው አባ ኤዎስጣቴዎስ ስለፈጸሙት የወሲብ ቅሌት ከሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ በውጭ በሚገኘው ሀገረ ስብከት በኩል በደብዳቤ ለቤተክርስቲያኗ ስለ ተጻፈ መሆኑ ታውቋል፡፡ ውሳኔው ለሌሎቹም አስተማሪ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ግን እንዲህ ተጽዕኖ ሊፈጥር የሚችል ደብዳቤ ካልተጻፈስ በቀር በሴት ጉዳይ የሚታሙና ሚስት አግብተው ጭምር እንደተቀመጡ በስፋት የሚወራባቸው ጳጳሳት ላይጠይቁ ነወይ? የሚል ጥያቄን አጭሯል፡፡ አባ ኤዎስጣቴዎስ በዚህ ውሳኔ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚገቡ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም አባው በአቡነ ጳውሎስ ዘመን አሜሪካ ተልከው በዚያው የቀሩ በመሆናቸውና በሲኖዶስ ስብሰባ ላይ አልገኝም ወደአገር ቤትም አልመለስም ብለው መወሰናቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ጥገኝነት ጠይቀው ይሁን ወይም አይሁን ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም፡፡ የግንቦቱ ሲኖዶስ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ አባ ኤዎስጣቴዎስ ተመልሰው እንዲመጡና ስለተከሰሱበት ጉዳይ እንዲያስረዱ መወሰኑ ትልቅ አጣብቂኝ እንደሚሆንባቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ወደአገር ቤት መመለስ ለእርሳቸው ትልቅ ሽንፈት እንደሚሆን ሲጠበቅ አለመምጣትም ብዙ ዋጋ ያስከፍላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው መወገዝ ሲሆን፣ ሁለተኛ ሊሆን የሚችለው በተመሳሳይ ጥፋት ከአሜሪካ ዲፖርት እንደተደረጉትና “አሜሪካን ረግሜያት ነው የመጣሁት ፊቴን ወደእርሷ አላዞርም” እያሉ እንደሚያስወሩት አባ ሳሙኤል አይነት እጣ እንደሚጠብቃቸው የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ አባ ኤዎስጣቴዎስ የቱን ይመርጡ ይሆን? የሚለውን አብረን የምንከታተል ይሆናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐራና መሰሎቿ ይህን ትልቅ ዜና እንዳልሰማ ሆነው አልፈዉታል መሰል በጉዳዩ ምንም ያሉት ነገር የለም፡፡

Saturday, June 1, 2013

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የሚመራው ስደተኛው ሲኖዶስ ሌሎች ጳጳሳትን ለመሾም ወሰነ።

በቴክሳስ ዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተናጋጅነት ከግንቦት 19 ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አርብ ግንቦት 23 ዕለት ተጠናቀቀ። በጉባኤው ሊቃነ ጳጳሳት፥ መነኮሳት፥ ካህናት፥ ዲያቆናት መምህራነ ወንጌል፣ የቦርድ አባላትና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተሳተፉበት ነው ተብሏል። በአጀንዳ ከተያዙት መዋያያ ርዕሶች መካከል ዋናዋናዎቹ የተቋረጠው የእርቅ ሂደት፤ የሊቃነ ጳጳሳት ሹመት፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት መቋቋም፤ የዲሲ ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክርስቲያን እና የኦክላንድ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ናቸው።

የተቋረጠው የእርቅ ጉዳይ እንዲቀጥል አስፈላጊ መሆኑ ቢታመነብትም ተስፋ የሚሰጥ ውሳኔ የተወሰነ አይመስልም። የተሻረው ቀኖና እስከተከበረ ድረስ እርቁን እንቀጥላለን የሚል የጥንቱ አቋም እንደተያዘ ነው። ጉዳዩም ከመንግሥት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ እርቁ ከመንግሥት ጋርም መሆን እንዳለበት ታምኖብታል። ሲኖዶሱ ይዞታውን ለማስፋትና ጠንከር ያለ እንቅሥቃሴ ለማድረግም ሌሎች ተጨማሪ ሊቃነ ጳጵሳትን ለመሾም እና ወደ አፍሪካና አውሮፓ አውስትራሊያ ለመላክ ውሳኔ አስተላልፏል።