Friday, June 21, 2013

ሙሰኞችን ተጠያቂ በማድረግ እንጂ ከክፍል ወደ ክፍል በማዘዋወር ሙስናን መዋጋት አይቻልም

በቤተ ክርስቲያን የተንሰራፋውንና ቅጥ ያጣውን ዝርፊያ ለመከላከል በፓትርያርክ ማትያስ የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ የፀረ ሙስና አቢይ ኮሚቴም ተሰይሟል ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ በሙስና እንደተዘፈቁ የሚነገርላቸው ሰዎች ተጠያቂ የሚሆኑበትን ስርአት በፍጥነት መዘርጋትና መጠየቅ ሲገባ፣ ከአንዱ ክፍል አንስተው ወደሌላ በማዛወር ሙስናን ማባባስ እንጂ መቀነስ እንደማይቻል በርካታ የቤተክህነት ሰራተኞችና በአንዳንድ አድባራት የሚገኙ ካህናት እየገለጹ ነው፡፡ ስለሙስና ከዚህ ቀደም በአቡነ ጳውሎስ ዘመን ይወራ እንደነበርና በተለይ አባ ሳሙኤል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በነበሩ ጊዜ ለሚዲያ ፍጆታ የሚውል ስብሰባ ተደርጎ ሙስናን መዋጋት እንደሚገባ መመሪያ ተሰጥቶበትና በዜና ቤተክርስቲያን ላይ እስከ መዘገብ ደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን ትልቁን ሙስናና የስልጣን ብልግናን ይፈጽሙ የነበሩት አባ ሳሙኤል እንደነበሩ የሚረሳ አይደለም፡፡ ዛሬ በሙስና ላይ ተከፈተ የተባለው ዘመቻ የአንድ ሰሞን ወሬ ሆኖ እንዳይቀር ከፍተኛ ስራ መሰራት እንዳለበት ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ አሊያ በቤተ ክህነት በሙስና ላይ እንዲህ አይነት አቋም የተወሰደው መንግስት በአንዳንድ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ከመንግስት ጋር ለመመሳሰል ነው የሚሉ አሉ፡፡

ሙስናውን መዋጋት ሳይውል ሳያድር መጀመር አለበት፡፡ መጀመር ያለበትም በሙስና ተጠርጥረው ከቦታቸው እንዲነሱ በተደረጉ ሰዎች ላይና ከዚህ ቀደምም የገንዘብ ጉድለት የተገኘባቸውና ልዩ ልዩ ሙስናዊ ወንጀል የፈጸሙ የቤተክህነት ባለስልጣናት ሁሉ መሆን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በሙስና ተጠርጥረው ከቦታቸው በተነሱት በአባ ህሩይና በአቶ ደስታ ላይ ክስ ተመስርቶ ጉዳያቸው በሕግ መታየት አለበት እንጂ ከነበሩበት ቦታ ተነስተው ወደሌላ ቦታ በመዛወር ብቻ መታለፍ የለባቸውም፡፡ ከሰሞኑም ከሃላፊነታቸው በተነሱት በአቶ ተስፋዬ እና በአቶ እስክንድር ላይ ተመሳሳይ እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡

በአቶ ተስፋዬ ላይ የተለያዩ አቤቱታዎች ሲቀርቡ ነበር፡፡ በቅርቡ እንኳ እህትና ወንድምን ባልና ሚስት አድርጎ ወደ ውጪ ለመላክ ደብዳቤ ፈርሞ ወደመዝገብ ቤት ሲልክ የመዝገብ ቤት ሃላፊ የነበረችው አጸደ “እኅትና ወንድም መሆናቸውን እያወቅሁ ደብዳቤውን ወጪ አላደርግም” በማለቷ፣ እንደገናም የቤተክርስቲያኒቱን ስርአት በጣሰ መልኩ በሌለው ስልጣነ ክህነት ያለ ሀገረ ስብከቱና ያለ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ ጽላት ተቀርጾ እንዲላክ በአቶ ማንያዘዋልና በእስክንድር አግባቢነትና በአቡነ ፊልጶስ ፊርማ ጸድቆ ከመዝግበ ቤት ሊወጣ ሲል ደብዳቤውን አሁንም አጸደ ይዛ “አቡነ ጳውሎስ ካላዩት አላወጣም” በማለቷ የአቡነ ጳውሎስን ሞት ጠብቆ አጸደን ከቦታዋ ማንሳቱን ጳጳሳቱ በተገኙበት በርክበ ካህናቱ ስብሰባ ላይ በአካል በመገኘት አጸደ አቤቱታዋን ያሰማች መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በቅርቡ የጠቅላይ ቤተክህነት ሰራተኞችን ሰብስበው በነበረ ጊዜ የተለያዩ የቤተክህነት ሰራተኞች አለቦታቸው ተቀምጠው ቤተክርስቲያንን ሲበጠብጡ የቆዩ ሰዎችን አስመልክተው ከተናገሩ ሰራተኞች አንደብት እንደ ተሰማው “የቤተክርስቲያኒቱን ምስጢራት የማያውቁ ሰዎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያንን እንዲዳኙ መደረጉ ለቤተክርስቲያን ትልቅ ውድቀት ነው፡፡ አንዳንዶች ከመንግስት መስሪያ ቤት በአቅም ማነስና በሙስና ሲባረሩ ቤተክህነት ይቀበላቸዋል” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ ይህም ጽላት ይሰጥ አይሰጥ የሚለውን ይዳኙ የነበሩት ጨዋዎቹ እስክንድርና ተስፋዬ እንደ ነበሩ የሚጠቁም አስተያየት መሆኑን ብዙዎች ግንዛቤ ወስደውበታል፡፡

ይሁን እንጂ እንዲህ ያደረጉት ሰዎች ተቀምጠውበት ከነበረውና ለእነርሱ ከማይመጥነው ቦታ እንዲነሱ መደረጋቸው ተገቢ ቢሆንም ከላይ የተገለጸውንና ሌሎችንም ሙስና ነክ ድርጊቶች ፈጽመው በሕግ የማይጠየቁ ከሆነና በዝውውር ብቻ «ከተቀጡ» ሙስናን ማስፋፋት እንጂ መዋጋት አይቻልም፡፡ አጸደ ያቀረበችው አቤቱታና ሌላውም ጥፋታቸው ታውቆ ሰሞኑን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ እንዲታጠፍና እስክንድር ተነስቶ ወደ እቅድና ልማት መመሪያ እንዲዛወር ተስፋዬም ወደቤቶችና ህንጻዎች አስተዳደር ልማት እንዲዛወር ተደርጓል፡፡

ከዚህ ቀደም በዝርፊያና በሙስና ምክንያት ከደብር ደብር ሲዛወር የኖረውና በተለይም እንጦጦ ማርያም ላይ የደብሩ ጸሀፊ ሆኖ ሲሰራ ወደሙዚየም ጎራ ብሎ ከንብረቶቹ መካከል ዕርፈ መስቀል ሰርቆ ሲወጣ ተይዞ በአንድ ወር ውስጥ ከእጦጦ ማርያም የተባረረውና ለእርፈ መስቀል እንኳ ያልታመነውን ሰለሞን ቶልቻን በርካታ የብራናና ሌሎችም መጻሕፍትና የአምስቱ ጳጳሳት የከበሩ የወርቅ ስጦታዎች የሚገኙበትን የመንበረ ፓትርያሪክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርና ቅርስ መምሪያ ሃላፊ አድርጎ መመደብ ንብረቶቹን ለአደጋ ማጋለጥ ይሆናል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡

ከሁሉም የሚገርመው ከላይ የተገለጸው ጥፋታቸውን እያወቀ የእርሱን ዓላማ ስለደገፉለት ብቻ እነዚህን ቤተክህነቱን ሲያምሱ የከረሙትን ግለሰቦች አፍቃሬ ማቅ የሆነው ሀራ ማሞካሸቱና አለቦታቸውና አለችሎታቸው በስልጣን ወንበር ላይ መቀመጣቸውን በተመለከተ የተጋለጡበትን እውነተኛ ታሪካቸውን ለመሸፋፈንና ምሁራን አስመስሎ ለማቅረብ የሞከረበት መንገድ ብዙዎችን አስደምሟል፡፡ ሆነው የአይጥ ምስክር ድንቢጥም አሰኝቷል፡፡


3 comments:

 1. i was read the above message regarding kesis Solomon completely it is wrong i know him

  ReplyDelete
 2. atsede? is she your evidence? yayit miskirua .... mallet endih new. Atsede eko bekumua chirak nat

  ReplyDelete
  Replies
  1. ምንዋ ጭራቅ ይመስላል በእግዚአብሔር? ይህችን መሳይ ቆንጆ እንዲህ ማለት የቅናት ይመስላል፣ ይልቁኑ የተስፋዬ ጭካኔ የሚገርም ነዉ፣ በእርስዋ የደረሰዉ ሀዘን እሱ ላይ የማይደርስ መስሎት ከሆነ ተሳስቱዋል፣ ለእርሱም ከእርግማን ይልቅ ልቦና ይስጠዉ ማለት ይቀለኛል፣

   ለአጸደ፣ ይህንን ገጽ ዕደሉን አግኝተሽ ካነበበሺዉ የምትወጂዉ ጌታ ይህንን ሁሉ ፈተና እንድታልፊ ከጎንሽ ነዉና ደስ ይበልሽ ለማለት እፈልጋለሁ፣ ስላንቺ ሳስብ ልቤ ይሰበራል፣ እጸልይልሻሁ።
   ካስታወስሽኝ እህትሽ ሐና ነኝ

   Delete