Tuesday, July 30, 2013

የስደተኛው ሲኖዶስ ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸው ተሰማ


ብፁዕ አቡነ ዮሴፍን  ከምክትል ከጸሓፊነት ለማውረድና በተለያየ ምክንያት ጥርስ ውስጥ የገቡ የታወቁ አባቶችንና ወንድሞችን ሊያስወግዙ እንዳሰቡ ምንጮቻችን ገምተዋል።

ይህ ስብሰባ ጁላይ 4 በኦክላንድ ሊደረግ የነበረ ሲሆን ሌሎች ጳጳሳት እና ቅዱስ ፓትርያርኩ ስለተቃወሙ ወደ አትላንታ ቅዱስ ፓትርያርኩ በሚገኙበት በዛሬው ዕለት እንዲሆን ተደርጓል። የስብሰባው አጀንዳ በትክክል ያልታወቀ ሲሆን አንዳንድ ምንጮቻችን ግን የሚከተሉት ሐሳቦች እንደሚገኙበት ይገምታሉ።

-       ብጹዕ አቡነ ዮሴፍን ከምክትል ጸሐፊነት ማውረድ። ባለፉት የሲኖዶሱ መደበኛ ስብሰባዎች አቡነ ዮሴፍን ለማውረድ ሙከራ አድርገው ያልተሳካ ቢሆንም አሁንም እንደሚሞክሩ ይጠበቃል።

-       ለስደተኛው ሲኖዶስ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ታላላቅ የወንጌል መምህራን የሆኑትን እነ ዶ/ር አባ ገብረ ሥላሴ ጥበቡን፣ አባ ወልደ ትንሣኤ አያልነህን፣ አባ ቃለ ጽድቅን፣ ቀሲስ መላኩ ባወቀን፥ መምህር ተከስተ ጫኔን  የመወያያ ርዕስ እንደሚያደርጉ ይታሰባል።

ብጹዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ሳያውቁትም ቢሆን በዶክተር ነጋና በዲያቆን አንዱአለም አማካኝነት የማበረ ቅዱሳን ረጅም እጅ ላይ ወድቀዋል ሲሉ የተደመጡም ካህናት ነበሩ።  ሰባክያነ ወንጌልን የማጥቃቱ እንቅስቃሴም ከዚህ የመነጨ ይመስላል። በርግጥ ብዙዎች ከላይ የተጠቀሱት ሰባክያነ ወንጌል በኦክላንድ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን (አቡነ መልከጼዴቅ ከሚኖሩበት ከመድኃኔ አለም ተገንጥሎ የወጣው የ አባ ቃለ ጽድቅ ቤተ ክርስቲያን) ተገኝተው አገልግሎት በመስጠታቸው የአቡነ መልከጼዴቅ ጥርስ ውስጥ እንደገቡ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት አገልጋዮችን የመበቀል ሁኔታ ሊኖርበት እንደሚችል ይገመታል። ሆኖም ግን ፓትርያርኩና ሌሎች ጳጳሳት ግን ይህንን ሁኔታ እንደማይቀበሉት ብዙዎች በድፍረት ይናገራሉ።

ዝርዝሩን በሰፊው እንደደረሰን እናቀርባለን

Saturday, July 27, 2013

ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለማትረፍ ማቅ እየሰራ ያለው ስራ ተጋለጠ

ወ/ሮ ዘውዴ የምሳ ግብዣ አዘጋጅታለች፤ ለምረቃውም ሰንጋ ልትጥል ነው
የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች በኮሌጁ ዲንና በአስተዳደሩ ባለስልጣናት ለዓመታት ሲፈጸምባቸው የነበረውን አስተዳደራዊ በደል በመቃወም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ሲጠይቁ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በቅርቡ ተጠናክሮ የቀጠለውን ጥያቄያቸውን ተከትሎ ቋሚ ሲኖዶስ በቅርብ ካሉ አንዳንድ ጳጳሳት ጋር ስብሰባ አድርጎ አባ ጢሞቴዎስን በጥቅምቱ ሲኖዶስ ውሳኔ እስኪያገኙ ድረስ ኮሌጁን ከመምራት ተግባራቸው በማገድ ንቡረ እድ ኤልያስን በመወከል መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ የተማሪዎቹ ጥያቄ ትክክለኛና ተገቢ በመሆኑ ላይ ሁሉም ይስማማል፡፡ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ ሳያገኙ በመቆየታቸው ደቀመዛሙርቱ ላይ ልዩ ልዩ በደሎች ሲፈጸሙ ቆይተዋል፡፡
ይህን የደቀመዛሙርቱን ችግርና ጥያቄያቸውን በመታከክ ቀድሞ ከአባ ጢሞቴዎስ ጋር ወግኖ “ኮሌጁ የተሀድሶ መፈልፈያ ነው” እያለ ስሙን ሲያጠፋ የነበረው ማኅበረ ቅዱሳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለተማሪዎቹ ተቆርቋሪ መስሎ በመቅረብ ኮሌጁን የመቆጣጠር ሕልሙን እውን ለማድረግ ተልእኮ ሰጥቶ ባሰረጋቸው ግለሰቦች በኩል ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሚያስችለውን ስራ ሲሰራ መቆየቱን ምንጮች ገለጹ፡፡ በዚህ በኩል ለዚሁ አላማ ወደ ኮሌጁ አስርጎ ያስገባትና ከዚህ ቀደም በግልጽ የማቅን ተልእኮ በመፈጸም በምትታወቀውና ዘውዴ በተባለች አባሉ በኩል ኮሌጁን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን የመንገድ ጠረጋ ተልእኮውን ሲሰራ መቆየቱን የሚናገሩት ምንጮች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ የቀጠለውን የተማሪዎቹ ተቃውሞ ተከትሎ ከኮሌጁ የምግብ አቅርቦት መቋረጡን መነሻ በማድረግ ለተማሪዎቹ ምግብ በማቅረብ ከጎናችሁ ነን የሚል መልእክት ሲያስተላልፍ መቆየቱ ታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው የተማሪዎች ተቃውሞ ላይም በተመሳሳይ ለምግብ የሚሆን ገንዘብ በመስጠት ዘውዴ የተማሪዎቹን ልብ ለመስረቅ ጥረት ስታደርግ መቆየቷ የሚታወቅ ነው፡፡   

Tuesday, July 23, 2013

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለምን ተሐድሶ ያስፈልጋታል? ክፍል ሁለት

ምንጭ፦ www.tehadeso.com
 
ላደግንባት፣ ቃሉን ላወቅንባት እና አሁንም እያገለገልንባት ላለችው ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ሁሉ ዐዲስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል በመደገፍ እንደ ቃሉ የሆነ እና የሰላም አለቃ የሚሰለጥንበት ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት፣ በሙሉ ልባችን እናምናለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተዘፍቃበት ካለው ሁሉን አቀፍ ችግር ለመውጣት የሚያግዛት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የሚከናወን ተሐድሶ አስፈላጊ ነው፡፡
“…እንደ ምሕረቱ መጠን ለዐዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን..”  የሚለው ዐረፍተ ነገር፣ ተሐድሶ በእግዚአብሔር መንግሥት አስፈላጊው እና ፍሬያማው እውነት እንደሆነ ያሳያል፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረት ከፍተኛነት በመንግሥቱ ውስጥ ለሚኖረን ቦታ የሚያበቃን፣ በመንፈስ ቅዱስ በኩል የሆነው መታደስ ነው፡፡ ይህ እውነት ለግለሰብም ለቤተ ክርስቲያንም በእኩልነት ይሠራል፡፡ አንድ ሰው ከጠፋው ማንነቱ ተመልሶ ለእግዚአብሔር መንግሥት ዜጋ እንዲሆን ከመንፈስ ቅዱስ የሆነው ተሐድሶ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ቤተክርስቲያንም የቀበረችውን እውነት ቆፍራ እንድታወጣ እና ለእግዚአብሔር ሐሳብ እሺ በጄ ብላ እንድትታዘዝ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነው ተሐድሶ ያስፈልጋታል፡፡

Monday, July 22, 2013

የተሐድሶ እንቅሥቃሴና አስፈላጊነቱ

ተሓድሶ ማለት የፈረሰውን መጠገን ያዘመመውን ማቅናት የቆሸሸውን ማጽዳት ማለት ነው። አንድ ቤት እድሜው ሲረዝም ሊያዘም ወይም ውበቱ ሊጠፋ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱን ቤት፤ ያለውን ይዘትና ቅርጽ ሳይለይቅ እንደገና ማደስ፤ መጠገን፤ ማሳመር ማደስ ይባላል። እያንዳዱ ፍጥረት ተሃድሶ የሚያስፍልገው ሆኖ ነው የተፈጠረው። ግኡዝ አካል [ማቴሪያልም] ይታደሳል፤ ለምሳሌ ብረት ሲዝግ ወደ እሳት አስገብተው ሲጠራርቡት ብረትነቱን ሳይለቅ አዲስ ይሆናል። ኅብረተ ሰብእ፣ ማህበር፣ መንግስት የመሳሰሉት የሰው ልጅ የጋራ ግንኙነቶችም እንደ ጊዘው ሁኔታ ይታደሳሉ። የማይታደስ ነገር ጨርሶ ከመጥፋት አይድንም። የማይታደሰው አንዱ እግዚአብሔር ብቻ ነው።
  ቤተ ክርስቲያንም ተሐድሶ ያስፈልጋታል፤ ተሐድሶ እጅግ በጣም ከሚያስፈጋቸው ተቋማት መካከል የእግዚአብሔር ቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ናት። በዓለም ውስጥ ከዓለም ተለይታ የምትኖር የጌታ ቤት በመሆኗ በየጊዜው እራሷን ማየት፤ በጌታ ቃል ሕይወቷን መመርመር ይኖርባታል። ይህች ቤት በዚህ ሰይጣን በሚገዛው ክፉ ዓለም ውስጥ የምትኖር ስለሆነ የዓለም ርኩሰት ሊገኝባት ይችላል፤ የዓለም ፍልስፍና ወይም ርእዮተ ዓለም ገብቶባት ሊሆን ይችላል፤ የስይጣን አሠራር እና እውነት የሚመስል የአጋንንት ትምህርት ሾልኮ ገብቶ ሊሆን ይችላል፤ ጥንቆላ እና መተት ሰማያዊ ታምራት መስለው ተቀላቅለው ሊገኙ ይቻላሉ፤ ሥጋዊነት፣ ዓለማዊነት፣ ገንዘብን መወደድ፣ ሥልጣንና ሹመት ፍለጋ፣ ስግብግብነት፣ ሞልተውባት ሊሆን ይችላል፤ ጥላቻ፣ ስድብና እርግማን፤ የርስ በርስ መነካከስ፣ ዘርኝነት፣ ስንፍና፣ ሊኖር ይችላል፤ እራይ አልባ ሆና ስኬት ርቋት ሊሆን ይችላል፤ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲገኙ ነገር ተገለባብጧል ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን ወደ ዓለም ገብታ ዓለምን መቀደስ ሲገባት፡ ዓለም ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ርኩሰቷን ፈጽማለች ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያንን ከዓለም መለየት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰን እያየነው ተሐድሶ አያስፈልገንም ማለት የሚያስገርም ነው።

Sunday, July 21, 2013

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ትግል አባ ጢሞቴዎስን ከቦታቸው በማስነሳት ተጠናቀቀ፡፡

ከአቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና ጀምሮ ያሉባቸው አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲቃለሉ ሲጠይቁ የቆዩትና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኮሌጁ አስተዳደር ጋር የከረረ ጠብ ውስጥ የገቡት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች በአባ ማትያስ ዘመነ ፕትርክና ፈጽሞ ያልጠበቁት “ኮሌጁ ተዘግቷል” የሚል ምላሽ ማግኘታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለተጻፈባቸው ህግና ስርአትን ያልተከተለና አባ ጢሞቴዎስን ለማስደሰት በሚል ብቻ በተጻፈባቸው ደብዳቤ ሳይደናገጡ ሰላማዊ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለው ባሉበት በአሁኑ ጊዜ ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እያገኙ የሚመጡ ለመሆናቸው ፍንጭ ያገኙበት አጋጣሚ መፈጠሩን ማወቅ ተችሏል፡፡

በዚሁ መሠረት በዛሬው የስብሰባ ውሎ ቋሚ ሲኖዶሱ ፓትርያርኩን “ኮሌጅ የመዝጋት ስልጣን የለዎትም” በማለት የወሰዱት እርምጃ ከህግ ውጪ መሆኑን የነገራቸው ሲሆን፣ የኮሌጁን መምህራን ጠርቶ ያነጋገረ መሆኑም ታውቋል፡፡ መምህራኑም ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸው ፈተና ሊወስዱና ሊመረቁም እንደሚገባ ተናግረዋል ተብሏል፡፡ በዚሁ መሠረት እንዲፈጸምም ቋሚ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን “ምርቃት የለም” እያሉ ሲያስፈራሩ የነበሩትን አባ ጢሞቴዎስንና ግብረአበሮቻቸውን ከቦታቸው ላይ በማንሳት ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ፣ እንዲፈተኑና እንዲመረቁ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ይሁን እንጂ ከመምህራኑ በኩል የቀረበው አስተያየት ያበሳጫቸው አባ ጢሞቴዎስ መምህራኑን “ሌባ ሁሉ” ሲሉ መሳደባቸው ተሰምቷል፡፡ የሀይል ሚዛኑ አባ ጢሞቴዎስን እየከዳቸው መሆኑን የተረዱት አባ ማትያስም ወዳጃቸውን አባ ጢሞቴዎስን ከድተዋቸዋል፡፡ ከቦታቸው እንዲነሱ በተወሰነው ውሳኔም ተስማምተዋል ተብሏል፡፡ የኮሌጁን ተማሪዎች አስመልክቶ የተላለፈውን ውሳኔ እንዲያስፈጽሙና የበላይ ኀላፊ እንዲሆኑ ንቡረ እድ ኤልያስ ተመድበዋል፡፡

Thursday, July 18, 2013

“ነገረ ድኅነት በአሚነ አበው” የተሰኘው የዲያቆን አግዛቸው ተፈራ መጽሐፍ ተመረቀ

ከዲያቆን ዘመድኩን
ነገረ ድኅነት በአሚነ አበው በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ የድኅነትን ነገር አባቶች ባስተማሩት መንገድ የሚተነትነው መጽሀፍ ባለፈው እሁድ ሰኔ 30/2005 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በ8፡00 ሰዓት ላይ በርካታ እንግዶች በተገኙበት ተመረቀ፡፡
ደራሲው ምዕራፍ አንድን የመዳን እውቀት ምንጭ በሚል ርዕስ የጀመረው ሲሆን ይህን የመዳን እውቀት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን በመግለጽ በስፋት አብራርቷል፡፡ ጸሀፊው ሀሳቡን በማጠናከርም እንዲህ ሲል ጽፏል፡፡
“በቤተክርስቲያናችን ውስጥ የተገኙ መጻህፍት ሁሉ በልማድ “ቅዱሳት መጻህፍት” ተብለው ሲጠሩ እንሰማለን፡፡ “ቅዱሳት” የሚለው ቅጽል ግን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከተጻፉት ከብሉያትና ከሀዲሳት መጻህፍት ውጪ ለሌሎች መጻህፍት ሁሉ የሚስማማና ሊቀጸል የሚገባ አይደለም፡፡ ከጥንት የቤተክርስቲያን አባቶች መካከል አንዱ አትናቴዎስ ለንጉስ ቆስጠንጢኖስ ልጅ ለዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ በጻፈው ትእዛዝ ላይ እንዲህ ብሏል፤ “የሚበልጠውም ትእዛዝ በኦሪት በነቢያት በወንጌል በሐዋርያት ቃል እናምን ዘንድ ነው። ንጉሥ ሆይ! ለነፍስህ መድሀኒት ይሆኑህ ዘንድ እግዚአብሔር ሊገልፅልህ የወደዳቸው መጻህፍት እኚህ ናቸው፡፡” (ሃይማኖተ አበው 1986 ገጽ 89፡90) በማለት ሰው ድኅነትን ያገኝ ዘንድ ከእግዚአብሔር የተሰጠው መጽሀፍ መጽሀፍ ቅዱስ ብቻ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

Wednesday, July 10, 2013

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲዘጋ ተማሪዎቹም ከግቢ እንዲወጡ ፓትርያርኩ ደብዳቤ መጻፋቸው ተሰማ


ደብዳቤውን ተከትሎ አባ ሉቃስና አባ ጢሞቴዎስ ዱላ ቀረሽ መዘላለፍ ውስጥ ገቡ
ሰሞኑን ተጠናክሮ የቀጠለውን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችን ጥያቄ አልቀበል ያሉትና ሲኖዶሱ የወሰነውን ውሳኔ ለማስፈጸም ዝግጁ ያልሆኑት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን አባ ጢሞቴዎስ ወዳጃቸውን ፓትርያርክ ማትያስን ደብዳቤ በማጻፍ ኮሌጁ እንዲዘጋና ተማሪዎችም ግቢውን እንዲለቁ፣ ምረቃም እንደማይኖር እንዲደረግ ትእዛዝ ማስወጣታቸው ተሰማ፡፡ ደብዳቤው ተግባራዊ መሆኑ ግን አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ ፓትርያርኩ የጻፉት ደብዳቤ ዛሬ የተሰበሰበውን ቋሚ ሲኖዶስ ያጨቃጨቀ ሲሆን በዋናነት ኮሌጅን መዝጋት የሚያበቃ ችግር አልተፈጠረም፡፡ የተፈጠረ ቢሆንም እንኳ በሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንጂ በእርስዎ ደብዳቤ ኮሌጁ ሊዘጋ አይችልም የሚል ጠንካራ ተቃውሞ ከጳጳሳት በኩል ቀርቧል፡፡ በተለይም አባ ሉቃስ ደብዳቤውን ከተቃወኑት መካከል ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎም አባ ጢሞቴዎስ በአባ ሉቃስ ላይ የስድብ ውርጅብኝ ያወረዱባቸው ሲሆን “አንተ ሰዶማዊ አዋሳ ላይ ስታሳድም የኖርህ ባለፈውም ቀሚስ አሰፍተህ ፓትርያርክ እሆናለሁ ብለህ ስታሳድም አልነበርህም?” ማለታቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በአጸፋውም አባ ሉቃስ “አንተ መሃይም እውር መቼም ከትምህርቱ የለህበት ለዚያ ነው ኮሌጁ ይዘጋ የምትለው” ማለታቸውን ምንጮቻችን አክለዋል፡፡ ይህን ዱላ ቀረሽ መዘላለፍ ተከትሎ ፓትርያርኩ ቆመው “ኧረ ስለ ማርያም ብላችሁ ተዉ” ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

Saturday, July 6, 2013

በነጻነት አገር ነጻነት አጣን

 
ውድ አባ ሰላማዎች ይህችን መልእክት በካሊፎርንያ ግዛት በሳን ሆዜ ከተማ ለሚገኙ ምዕምናን አስነብቡልኝ። 
ታዛብ ከሳንሆዜ ካሊፎርኒያ
 
 በዚህ ዘመን ያለን ኢትዮጵያዊያን በአጠቃላይ የባሕሪያችን ጽመት ጎልቶ የወጣበትና እርስ በራሳችን ተቻችለን የማንኖር አስቸጋሪ ሰዎች መሆናችን የታየበት መጥፎ አጋጣሚ ቢሆንም በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ በተለይ ብዙ ወንድሞች “ማኅበረ ሰይጣን” ብለው የሰየሙት ድርጅት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ትርምስ በቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደለም። ጳጳሳት በገንዘብ ተገዝተው ክብራቸውን አዋርደዋል፤ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችም ለይቶላቸው የማኅበሩ አገልጋይ ሆነው ተቀጥረዋል። ለእውነት የቆሙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተሰደዋል፤ ወይም አፋቸውን ለጉመው ተቀምጠዋል። ቤተ ክርስቲያንችን በርካታ ልጆቿን አጥታለች። ማኅበሩን ያልተቀበለ ወይም ለማኅበሩ እውቅና ያልሰጠ ኦርቶዶክሳዊነቱን ይነጠቃል። መናፍቅ የሚል ታርጋ ይለጠፍለታል። ችግሩ አሁንም መቋጫ አልተገኘለትም። በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው አጠቃላይ ውድመት ወደፊት በጥናት የሚረጋገጥ ይሆናል።  
ለልዩ ተልዕኮ እያሰለጠኑና ለማኅበሩ ታማኝነታቸውን የሚያረጋግጡበት የቃል ኪዳን ምልክት በአንገታቸው ላይ እያጠለቁ የሚልኳቸው የክርስትና መንፈስና ኢትዮጵያዊ ለዛ የሌላቸው ወጣቶች በየቦታው በሚፈጥሩት ሁከትና ሽብር የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ታውኳል። በየቤተ ክርስቲያኑ ጤናማ አገልግሎት መስጠት አልተቻለም።

Friday, July 5, 2013

ተሐድሶ እና የፓትርያርክ ለውጥ

ተሐድሶ የእግዚአብሔር ሐሣብ መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ፀረ ተሐድሶ የሆኑት እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉት “ፕሮቴስታንታዊ” የሚል ዘርፍ አበጅተውለት ቢያጣጥሉትም፣ የቤተክህነት ምንደኞችም “መናፍቃን” ከሚል ቃል ጋር አዛርፈው ለማስጠላት ቢሞክሩም ተሐድሶ ግን የእግዚአብሔር ሐሳብ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ሐሣብ ላይ ለሚነሣው የሰው ሐሳብ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላፈነገጠውና በኑፋቄ አረም ለተዋጠው የቤተ ክርስቲያን ትምህርትና ስርአት፣ አስተዳደራዊ ጉድለት ሁሉ ተሐድሶ ያስፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያኗ ቃሉን ስትጠቀም የምትታየው በተገቢው ጊዜና ሁኔታ ሳይሆን አንድ ፓትርያርክ በሞት ወይም በፖለቲካ ምክንያት መንበሩን ሲተው ወይም ሲታገድ ብቻ ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በራሷ ፓትርያርክ መመራት ከጀመረችበት ጊዜ አንሥቶ “ተሐድሶ” የሚቀነቀነው በዋናነት አንድ ፓትርያርክ በሞት ሲለይና ሌላው ሲተካ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኗ ከብዙ ምእተ ዓመታት ትግል በኋላ የራሷን ፓትርያርክ በሾመች ጊዜ ማለትም በ1951 ዓ.ም ሁኔታው የቤተክርስቲያን መታደስ እንደተባለ በዚያ ዘመን የተጻፉ ጽሑፎች ይመሰክራሉ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የወንጌልን እውነት የተረዱ ስለመሆናቸውና ቤተክርስቲያንን ወደ መንፈሳዊ ተሐድሶ ለማምጣት ያደረጉት ጥረት ስለ መኖሩ ግን መናገር የሚቻል አይደለም፡፡ በዘመናቸው የተወሰዱ አንዳንድ የተሐድሶ እርምጃዎች መኖራቸው ባይካድም ያን ያህል ለውጥ አምጥተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ለዚያም ነው አቡነ ቴዎፍሎስ በእርሳቸው እግር ተተክተው ፓትርያርክ ሲሆኑ ለቤተክርስቲያን ተሐድሶን ያመጣሉ ተብሎ ብዙ የተባለላቸው፡፡ በተለይም በተሾሙ ጊዜ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የተሰኘው የመንግስት ጋዜጣ እንዲህ ሲል ዘግቦ ነበር፤ “የሌሎች አገሮች አብያተ ክርስቲያኖች እንደ ታደሱ ሁሉ የእኛም እንደ ዘመኑ መራመድ ይኖርባታል። የአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች አስተሳሰብና የሃያኛው ክፍለ ዘመን ፍልስፍና በጣም የተራራቀና የተለያየ ስለ ሆነ ሊያሳምን በሚችል በአዲስ ዘዴ መቅረቡ የተሻለ ውጤት ያስገኛል። ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ይህን ሁሉ በማመዛዘን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ፣ በአሠራር፣ በአስተሳሰብና በአፈጻጸም የታደሰችና የዘመኑን ሥርአት የተከተለች እንደሚያደርጓት ከፍተኛ ኀላፊነት ይጠብቃቸዋል” (የሚያዝያ 2/1963 እትምን ይመልከቱ)፡፡

Monday, July 1, 2013

የዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ የሰኔ 2005 ዓ.ም እትም ርእሰ አንቀጽ


ሐናንያና ሰጲራ ዛሬም አሉ እንዴ?
መቼም ሙስና በቤተክርስቲያን ዙሪያ ይኖራል ተብሎ በጭራሽ አይገመትም፣ አይጠረጠረም፡፡ ይህ የንጹሐን ምእመናን አስተሳሰብ ነው፡፡ ሙስና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ይኖራል ተብሎ ቢገመትና ቢጠረጠርማ ኑሮ ምእመናን እጃቸውን ወደ ሙዳየ ምጽዋት ሊዘረጉና ለቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ መብዐዎችን ለማስገባት አይችሉም ነበር የሚለው ሐሳብ ከገጸ ሕሊናችን ድቅን ቢልብን ሊገርመን አይገባም፡፡

ለነገሩ “ሙስና ያስፈልጋል አያስፈልግም@” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣችን በቅርቡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር እሰጥ አገባ ገጥሞ በክርክሩ ላይ የሕግ ባለሙያዎችም ተጨምረውበት እስከ አሁን ድረስ ፋይሉ አልተዘጋም እንደ ተንጠለጠለ ነው  ያለው እኮ!

ሙስናን ከሥሩ፣ ከምንጩ እንተርከው ብለን ከተነሣን ግን በዘመነ ብሉይ ሙስናን በምኩራብ አይሁድ የጀመሩት አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉት የሊቀ ካህናቱ የኤሊ ልጆች ሲሆኑ በዘመነ ሐዋርያት ደግሞ ሙስናን የጀመሩት ባልና ሚስቱ ሐናንያና ሰጲራ መሆናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ስለሚነግረን ጉዳዩ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በመሆኑ ዛሬም የሐናንያና የሰጲራ ደቀ መዛሙርት በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ቢከሰቱ እምብዛም አንገረምም፡፡