Monday, July 1, 2013

የዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ የሰኔ 2005 ዓ.ም እትም ርእሰ አንቀጽ


ሐናንያና ሰጲራ ዛሬም አሉ እንዴ?
መቼም ሙስና በቤተክርስቲያን ዙሪያ ይኖራል ተብሎ በጭራሽ አይገመትም፣ አይጠረጠረም፡፡ ይህ የንጹሐን ምእመናን አስተሳሰብ ነው፡፡ ሙስና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ይኖራል ተብሎ ቢገመትና ቢጠረጠርማ ኑሮ ምእመናን እጃቸውን ወደ ሙዳየ ምጽዋት ሊዘረጉና ለቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ መብዐዎችን ለማስገባት አይችሉም ነበር የሚለው ሐሳብ ከገጸ ሕሊናችን ድቅን ቢልብን ሊገርመን አይገባም፡፡

ለነገሩ “ሙስና ያስፈልጋል አያስፈልግም@” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣችን በቅርቡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር እሰጥ አገባ ገጥሞ በክርክሩ ላይ የሕግ ባለሙያዎችም ተጨምረውበት እስከ አሁን ድረስ ፋይሉ አልተዘጋም እንደ ተንጠለጠለ ነው  ያለው እኮ!

ሙስናን ከሥሩ፣ ከምንጩ እንተርከው ብለን ከተነሣን ግን በዘመነ ብሉይ ሙስናን በምኩራብ አይሁድ የጀመሩት አፍኒንና ፊንሐስ የተባሉት የሊቀ ካህናቱ የኤሊ ልጆች ሲሆኑ በዘመነ ሐዋርያት ደግሞ ሙስናን የጀመሩት ባልና ሚስቱ ሐናንያና ሰጲራ መሆናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ስለሚነግረን ጉዳዩ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በመሆኑ ዛሬም የሐናንያና የሰጲራ ደቀ መዛሙርት በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ቢከሰቱ እምብዛም አንገረምም፡፡

ሙስና በቤተ ክርስቲያን ብዙ ትርጉም አለው፤ የገንዘብ ዝርፊያና የሀብት ምዝበራ ብቻ አይደለም ትርጉሙ፡፡ ክህነትን በማርከስ ቅድስናን ማጣት የከፋ ሙስና ነው፡፡ ያለችሎታ በቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ላይ ተቀምጦ መንጋዎችን በአውሬ ማስበላትና በተኩላዎች ማስነጠቅም የሙስና ሙስና ነው፡፡ ለእግዚአብሔር መንግሥት መስበኪያ የተመደበውን የእግዚአብሔርን ገንዘብ የራስ መንደላቀቂያና የዘመድ አዝማድ ማቋቋሚያ ማድረግም መቅሰፍት አምጭ ሙስና ነው፡፡

የሃይማኖት መሪዎች የሚጠየቁት በራሳቸው ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ባለመምከራቸውና ባለማስተማራቸው በሕዝቡም ኃጢአት ጭምር ይጠየቃሉ፤ ለመቅሰፍትም ይዳረጋሉ፡፡ የላይኞቹም ሆኑ የታችኞቹ ዓላማውያን ከመስመር ሲወጡና ኃጢአት ሲሠሩ እያዩ ዝም ማለት የለባቸውም፡፡ እነሱ ዝም ቢሉ እግዚአብሔር ዝም ስለማይል ትርፉ መዳንም ማዳንም ከማይችልበት ደረጃ ላይ መድረስ ብቻ ይሆናል፡፡ ሊቀ ካህናቱ ኤሊ ልጆቹን ባለመምከሩ እሱም፣ ልጆቹም አብረው ነው የጠፉት፡፡ ልባችንን ሞራ ካልሸፈነው በስተቀር አሁንም ይህ ስህተት እየተስተዋል ነው፡፡

ሐናንያና ሰጲራ ለሥጋዊ ሕይወታቸው ጓግተው ለሐዋርያት የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰው የእርስታቸውን ሽያጭ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ ጊዜ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ሐናንያ ሆይ መንፈስ ቅዱስን ትዋሸው ዘንድ በልብህ ውስጥ ሰይጣን እንዴት ሞላበት@” ብሎ በተናገረው ጊዜ ነው ወዲያውኑ የተቀሰፈው፡፡ የሚስቱ የሰጲራም ቅስፈት ቅጽበት አልወሰደም፤ ባለቤቷ ሐናንያ በተቀሰፈበት ዕለት ነው የተቀሰፈችው፡፡ ዛሬ ይህ ዓይነቱ ክስተት ቶሎ ቶሎ ሲከሰት የማይታየው ግን አለቃውም ምንዝሩም አንድ በመሆናቸው ነው፡፡ ውሎ አድሮ ግን ሁሉም ተያይዘው ሲጠፉ መስተዋላቸው በኤሊና በልጆቹ ተረጋግጦአል፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ የሆኑትንና ሳር ቅጠሉ አፍ አውጥቶ ቅድስናቸውን የመሰከረላቸውን ያን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጻድቅ አባ ገሪማን በዜማ ድርሰቱ ሲያወድሳቸው “ኤስኬማከኒ አልባቲ ሙስና” ማለት ቆብህ ሙስና የለባትም ብሎ የመሰከረላት ቆብ  ዛሬም በአባቶች ዘንድ መገኘት አለባት፡፡ የሙስና ዋሻ የሆነ የፀሐይ ቆብ በከተማም ሆነ በቤተክርስቲያን ዙሪያ መታየት የለበትም፡፡ ሃይማኖት የሙስና ጸር እንጂ የሙስና ከለላ ሊሆን አይገባውም፡፡

ጊዜው ሲደርስ አዲሱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ የማዕዶት ዕለት ለካህናትና ለምእመናን ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን “ክርስቶስ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ እንደተነሣ እኛም ሙስናን ከቤታችን ማጥፋት አለብን፡፡ የካህን ሙሰኛ፣ የካህን ሌባ፣ የካህን ጉቦኛ መኖር የለበትም” በማለት ያሰሙት ትምህርትና የሰጡት አባታዊ መመሪያ አጉል ርኅራኄ ሳይጨመርበትና ይዋል ይደር ሳይባል ተግባራዊ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ስለዚህ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እጅግ የተንሰራፋውንና ክፉኛ ሥር የሰደደውን የሙስና ተግባር ለመዋጋት በሚደረገው መንፈሳዊ ዘመቻ ሁላችንም በሚቻለን ሁሉ መረባረብ ይኖርብናል፡፡ የዛሬዎቹን ሐናንያና ሰጲራን እንደቀድሞዎቹ ሐናንያና ሰጲራ በቃል ለማጥፋት እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብቃቱ ባይኖርም ግብረ ሙስናን አጥብቆ የሚጸየፍ አባትና የመንግሥት እገዛን አግኝተን ሳለ በሕግ በመከታተል ቤተ ክርስቲያናችንን ከግብረ ሙስና ነፃ ልናወጣትና ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ እንዳሉት ወደ ጥንተ ቅድስናዋ ልንመልሳት ይገባናል፡፡

6 comments:

 1. አይደል? አዛኝ ቅቤ አንጓች።ምን አገባችሁ።ውሻ ምን አገባት እርሻ።።ምንፍቅናችሁን ስናውቀው ለቤተክርስቲያን ማሰባችሁ ሰው ሁሉ ማስተዋሉን ተነጥቋል ብላችሁ ነው?አዎ የማያውቁ ሕጻናትን በማደናገርና በማሳት ጊዜው ደርሶ ቅጣቱን እስክታገኙ በድፍረት ኃጢአት ትኖራላችሁ።ይቅር ይበላችሁ

  ReplyDelete
 2. What "Aba girma" of Debre Tsion Kidist Mariam, London does is no less than Hananian & Sepiera.
  very consumed with control of the church to spike personal fortune. Shame!Shame!Shame!. If this things continue un treated in our church, It will lead to the unfortunate legalization of corruption deeds in every church. I thank Aba Selama for bringing this issue.

  ReplyDelete
 3. የቀረበው አሳብ መልካምና ይበል ያሰኛል ዳሩ ግን ሰዎች ይህን አሉ ይኸን ተባሉ
  ከመባልና ከማለት አልፈው ትክክለኛ ርማት ሊሰጡ አይችሉም አቅሙስ ከየት ይመጣል
  ይሁንጂ በግዙፉ ዓለም የሚኖረው ግዙፉ ዓለም ሳይሆን፤በረቂቁ ዓለም የሚኖረው
  ረቂቁ ዓለም የማያዳግመውን ርማት መስጠት ይችላል።

  ReplyDelete
 4. የቀረበው አሳብ መልካምና ይበል ያሰኛል ዳሩ ግን ሰዎች ይህን አሉ ይኸን ተባሉ
  ከመባልና ከማለት አልፈው ትክክለኛ ርማት ሊሰጡ አይችሉም አቅሙስ ከየት ይመጣል
  ይሁንጂ በግዙፉ ዓለም የሚኖረው ግዙፉ ዓለም ሳይሆን፤በረቂቁ ዓለም የሚኖረው
  ረቂቁ ዓለም የማያዳግመውን ርማት መስጠት ይችላል።

  ReplyDelete
 5. Ithink this is amazing message God bless the editor of the news paper

  ReplyDelete