Friday, August 30, 2013

ቤተክህነት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን አንደኛ ዓመት የመታሰቢያ ሥነሥርዓትን ማደብዘዙ ብዙዎችን አሳዝኗል

ቤተክህነት የዛሬ ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አንደኛ ዓመት መታሰቢያን እንደ ደሃ ፍታት አደብዝዞት መዋሉ ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ የቅዱስነታቸው የሙት ዓመት መታሰቢያ ባለፈው ነሐሴ 10/2005 ዓ.ም ሲከበር በቤተከህነት በኩል ምንም አይነት ዝግጅት እንዳልተደረገበትና ምንም አይነት ትኩረት እንዳልተሰጠው በዕለቱ የታየው ዝግጅት በቂ ምስክር ነው፡፡ ለዚህም በዋናነት ተጠያቂው ጠቅላይ ቤተክህነቱ ነው፡፡ ክብር ለሚገባው ክብርን መስጠት ሲገባ የቤተክርስቲያኗ መሪ የነበሩትን የቅዱስነታቸውን መታሰቢያ ማደብዘዝ ለምን አስፈለገ? የሚለው በብዙ እያነጋገረ ይገኛል፡፡ መታሰቢያቸው የመገናኛ ብዙኃንን ሽፋን በተገቢው መንገድ አላገኘም፡፡ ይህም ለዝግጅቱ ከተሰጠው አናሳ ትኩረት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሪፖርተር ጋዜጣ ግን ሽፋን ሰጥቶታል፡፡ የቅዱስነታቸው የመታሰቢያ ሥነሥርአት ሰፊ የሚዲያ ሽፋን የተነፈገው ምናልባት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሙታመት መታሰቢያ ከፍተኛ ትኩረት ስለተሰጠው ሊሆን ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን “ባለቤቱ ያቃለለውን ባለዕዳ አይቀበለውም” እንደሚባለው ቤተክህነቱ ቸል ያለውን ሌላው እንዴት ሊያተኩርበት ይችላል የሚለው ብዙዎች የተስማሙበት ነጥብ ሆኗል፡፡

Tuesday, August 20, 2013

ማቁ ታደሰ ወርቁ በቀድሞ ማኅበሩ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ትችት ሰነዘረ ከጥምቀት ተመላሾች ማቅ ለአመጽ ያዘጋጃቸው ሰራዊቱ መሆኑን ታደሰ ፍንጭ ሰጥቷል


ማቅን እየከዱ ከሚገኙት ታማኞቹ መካከል አንዱ የሆነው ታደሰ ወርቁ ከማቅ ጋዜጠኛነቱ ከተሰናበተ በኋላ በማቅ ላይ ትችት ሰንዝሯል፡፡ ታደሰ ወደዚህ ሁሉ ትችት የገባው በዋናነት የማኅበሩ አካል ሆኖ ሲታገልለት የኖረው በሃይማኖት ካባ የተሸፈነው ፖለቲካዊ አላማው በመክሸፉ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡ እርሱም በተደጋጋሚ አጽንኦት ሰጥቶ የተናገረው ይህንኑ ነው፡፡ ታደሰ ትችቱን የሰነዘረው “ፋክት” በተሰኘው መጽሔት ቅፅ 2 ቁ.6 የሐምሌ እትም 2005 ዓ.ም ላይ “በቄሳራውያን መዳፍ ስር ያለ አስኬማ” በሚል ርእስ በጻፈው ፖለቲካዊ ጽሑፍ ነው፡፡ በቀጣዩ ቁጥር 7 የነሐሴ 2005 ዓ.ም እትም ላይም “የተቋማዊ ለውጥ ጅምሮች” በሚል ርእስ አንዳንድ የአክራሪውን የማቅን እስትራቴጂዎች ለማስቃኘት ሞክሯል፡፡

ታደሰ “የወንድሞች ከሳሽ” የሆነው ማቅ አይምረኝም ይከሰኛል ብሎ ነው መሰል ማቅን በተቸበት ጽሑፉ ላይ ማቅን በሙሉ ስሙ “ማኅበረ ቅዱሳን” ብሎ ሳይሆን “ማኅበር” እያለ ነው የጠራው፡፡ እንዲህ ቢልም ታደሰ የሚለውን ሥራ የሠራ ሌላ ማኅበር በአገራችን ስለሌለ ዞሮ ዞሮ የተቸው ማቅን መሆኑ አላጠራጠረም፡፡ ታደሰ የማቅን ስም ሸርፎ ለመጥራት ያደረበት ፍርሀት ግመልን ሰርቆ አጎንብሶ የመሄድ ያህል “ብልሃቱ”ን ነው የሚያሳየው፡፡ ለማንኛውም ታደሰ ከዚህ ቀደም ማቅን ክፉኛ የተቸውና ሰድቦ ለሰዳቢ የሰጠውን የዳንኤል ክብረትን ያህል ባይሆንም ከዳንኤል ክብረት በኋላ ማቅን በጽሑፍ የተቸ ሌላው የማቅ ጋዜጠኛ ነው ብሎ መናገር ሳይቻል አይቀርም፡፡ ትችቶቹ በአብዛኛው ያተኮሩት ከፓትርያርክ ምርጫ ጋር በተያያዘ ሲሆን ከሞላ ጎደል የሚከተሉት ናቸው፡፡

Friday, August 16, 2013

ማኅበረ ቅዱሳን በውስጥ ችግር መታመሱ የአደባባይ ምስጢር እየሆነ ነው ታማኝ የተባሉ አገልጋዮቹን እያባረረና እነርሱም እየከዱት ይገኛሉ

ማኅበረ ቅዱሳን በውስጥ ችግሮቹ እየታመሰ መሆኑን ከማኅበሩ አካባቢ ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ላለፉት ዓመታት አቡነ ጳውሎስን መቃወምን ትልቅ አጀንዳው አድርጎ ሲሰራ የነበረው ማቅ ከእርሳቸው ዕረፍት በኋላ ድምጹ ብዙም እየተሰማ አለመሆኑ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄን ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ለተቃውሞው አብረው የነበሩት የማቅ ዋና ዋና ሰዎችም ከአቡነ ጳውሎስ ሞት በኋላ በራሳቸው የቤት ስራ መጠመዳቸው አልቀረም፡፡ ልዩነታቸውም እየጎላ በመምጣቱ በተለያየ ክፍል የሚሰሩ የማኅበሩ ቁልፍ ሰራተኞች እየተባረሩና አንዳንዶችም ለመልቀቅ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ስንታዘብ ቆይተናል፡፡
በዋናነት ልዩነቶች እየተፈጠሩ የመጡት በዋልድባው ጉዳይ ሲሆን፣ በዋልድባ ገዳም አካባቢ መንግስት እየሠራ ያለውን የወልቃይት ጠገዴ የስኳር ልማት ፕሮጀክትን ለማደናቀፍና ለፖለቲካ ፍጆታ በማዋል ገቢ ለማሰባሰብ አንዳንድ የማቅ ሰዎች ሲያራግቡትና ጉዳዩን የተለየ አቅጣጫ እንዲይዝ ሲያደርጉት እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ማቅ በእርሱ በኩል ፕሮጀክቱን የተመለከተ ጥናት አድርጎ ሪፖርት እንዲያቀርብ እድሉ ተሰጥቶት በነበረ ጊዜ ሶስት አባላት ያሉት የጋዜጠኞች ቡድን ወደስፍራው ልኮ የነበረ ሲሆን የማቅ የጎንደር ንኡስ ማእከል በጊዜው ከቡድኑ አባላት አንዱ ሆኖ የመጣውን ባያብል ሙላቱን ለምን እርሱን ይዛችሁት መጣችሁ? ማለታቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም በማጣራቱ ሂደት ባያብልም ተሳትፎ ቡድኑ ተገቢውን ማጣራት ካደረገና ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ሪፖርቱን አዘጋጅቶ በማኅበሩ የሌሊት ስብሰባ ላይ አመራሮቹ ባሉበት ገለጻ አድርገው የነበረ ሲሆን፣ ገለጻውን ተከትሎ ለሁለት ተከፍለዋል፡፡

Monday, August 12, 2013

ማኅበረ ቅዱሳን ቤተክርስቲያንን ልምራ የሚል ጥያቄ ማቅረቡ ተሰማ

ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም! አሉ አበው፡፡ ማህበረ ቅዱሳን በራሱ ደጋፊ ፓትርያርክ ሊቆጣጠር ፈልጎ ያልተሳካለትን የጠቅላይ ቤተክህነትን መዋቅር ለ3 (ሶስት) አመት ለመምራት ጥያቄ ማቅረቡን የቤተክህነት የውስጥ ምንጮች አጋለጡ፡፡

አዳምና ሔዋንን በገነት ያሳታቸው ባለ አንድ እራሱ እባብ ነበር፡፡ ክፉ ሃሳቡ በሔዋን ተቀባይነት አግኝቶለት የሰውን ልጅ ከገነት አስወጥቶ ለሞት ዳርጎት ለ5500 አመታት በባርነት ሲገዛው የኖረ ቢሆንም በአምላካችን በመድሀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ተቀጥቅጦ ከሰው ልብ እንዲወገድ ቢደረግም  በቤተ አይሁድ (ጸሐፍት ፈሪሳውያን) ልብ ቦታ በማግኘቱ ዮሐንስ በራእይ እንዳየው ይህ እባብ ሰባት እራስና አስር ቀንዶች አውጥቶ ታላቅ ዘንዶ ሆኖ ፋፍቶና አድጎ ከባህር ሲወጣ ዳግም ታየ፡፡ እንዲያውም በመጨረሻ ይህ ዘንዶ ሙሉ ለሙሉ ስልጣኑን ለአውሬው (ለሰው ልጅ) በመስጠት በመጨረሻ ዘመን ከመንገድ ዘወር ብሎ በአውሬው (በሰው ልጅ) ሙሉ ሆኖ  እንደሚሰራ ባለራእዩ ነግሮናል፡፡

Thursday, August 8, 2013

ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም

ጾመ ፍልሰታ ማርያም “ተነሥታ ማረጓ” የሚተረክበትና በስህተት ትምህርት ላይ የተመሠረተ ጾም ነው፡፡ የትምህርቱ ደራሲዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተጻፈው መሠረት ሳይሆን ከተጻፈው በማለፍ የጌታችንን እናት እመቤታችን ድንግል ማርያምን ለማክበርና እርሷን ከአምላክ ጋር ለማስተካከል ሲሉ የደረሱት ድርሰት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስንና ቀደምት የቤተክርስቲያን አባቶችን ትምህርት በመመርመር ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ 
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ከሙታን ተለይቶ የተነሣና በክብር ያረገ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ እርሱ ለሙታን ሁሉ በኩር ተብሏል፡፡ ሌሎቹ ሙታን ሁሉ ግን በመጨረሻው ቀን ጌታችን በተነሣበት መንፈሳዊ አካል እንደሚነሡና በጌታ ሆነው ያንቀላፉ ቅዱሳን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ወደተዘጋጀላቸው የዘላለም ሕይወት እንደሚገቡ ተጽፏል፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ጌታ እናቱን ከሰው ሁሉ ለይቶ እንድትነሣና እንድታርግ ወደመንግስተ ሰማያትም ከሁሉ ቀድማ እንድትገባ አድርጓል የሚለው ትምህርት ከቃሉ ውጪ ነው፡፡ ቀደምት አባቶችም ይህን ትምህርት እንደማያውቁትና በእነርሱ ዘመን እንዳልነበረ እንረዳለን፡፡ በሃይማኖተ አበው ላይ የሚከተለው ተጽፏል፡፡ እርሱ በመዋቲ ስጋ ይነሣ ዘንድ በፍቃዱ ሞተ። ከተነሳም በኋላ ዳግመኛ አይሞትም ከትንሣኤው በኋላ ግን ጌታ ይህን አልተናገረም። ከሰውም ወገን ማንንም ተነሣ ከመቃብር ውጣ አላለም። ዳግመኛ እስከሚመጣበት ቀን ደረስ ለሰዎች ሁሉ አንድ ሆነው በሚነሡበት ጊዜ ሙታን ይነሣሉ አላቸው። ከሙታንም ተለይቶ ከተነሳ በኋላ ከሞቱት ሁሉ ማንንም በሥጋ እንዳላስነሣ አስተውል።” (ሃይማኖተ አበው ምዕራፍ 59 ቁጥር 49-50)።

Wednesday, August 7, 2013

የወ/ሮ ዘውዴ የዋዜማ ድግስ መርሀግብር ሲገመገም


ባለፈው ማቋ ዘውዴ አንዳንድ የማቅ ምርኮኛ የሆኑ የቅድስት ሥላሴ ተማሪዎችን ግብዣ ጠርታ እንደነበር ዘግበን ነበር፡፡ እንደተባለውም ማቋ ዘውዴ እሁድ ሀምሌ 21/2005 ኣ.ም ሰሜን ገበያ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ ያዘጋጀችው ግብዣ ጥሪው ከቀኑ 6 ሰዓት የነበረ ሲሆን ለዘውዴ ደቀመዛሙርቱን የመማረክ ተልእኮ የሰጣት የማቅ አባላት በሰዓቱ ተገኝተዋል ተብሏል፡፡ ከምርኮኞቹ ደቀመዛሙርት አንዳንዶቹም በተለይም አራት መነኮሳትና ጥቂቶቹ ደቀመዛሙርትም ቀደም ብሎ የተሰጣቸውን ቲሸርት ለብሰው ነበር ወደ ስፍራው የደረሱት፡፡ ሌሎቹ ግን በጣም ዘግይተው ነበር የመጡት፡፡ በእነርሱ መዘግየት ምክንያት በ6 ሰዓት የመጡት የማቅ አባላት ማቋ ዘውዴ ካዘጋጀችው ቡፌ በልተው መሄዳቸው ታውቋል፡፡

በእለቱ ሰባኪ ሆነው የተሰየሙት ከተማሪዎች አንዱ አባ ክንፈ “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” በሚል ርእስ በስብከት ስም ከምንም ጋር ያልተገናኘና ማቆች ዘወትር መስበክና መስማት የሚፈልጉትን ዲስኩር ነበር ያሰሙት፡፡ በዲስኩራቸው “ኢየሱስ ኢየሱስ አትበሉ እርሱ የሚገኘው እናቱ ባለችበት እንጂ እርሷ በሌለችበት አይገኝም” ሲሉ ጆሯቸው የጠገበውንና እንደሞኝ ዘፈን በማቅ መንደር ዘወትር የሚቀነቀነውን ፀረ ኢየሱስ ዲስኩር አሰምተዋል፡፡ በወንጌል እንደተገለጸው ማርያም ኢየሱስ ባለበት የተገኘችው በቃና ዘገሊላው ሰርግ ላይ ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ያን አንድ ጊዜ ብቻ የተከናወነውን ድርጊት ለኢየሱስ መገኘት ሁሌ እንደ መስፈርት አድርጎ ማስቀመጥ ከየት የመጣ ፈሊጥ ይሆን? መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሁለት ወይም ሶስት በስሜ ባላችሁበት በዚያ በመካከላችሁ እገኛለሁ” አለ እንጂ እናቴ ባለችበት ብቻ ነው የምገኘው አላለም፡፡ ደግሞስ እናቱ በመካከላችን እንዴት ልትገኝ ትችላለች? እርሷ በቦታ የተወሰነች ፍጡር ደግሞም በአጸደ ነፍስ የምትገኝ እንጂ እንጂ እንደ አምላክ በስፍራ ሁሉ የምትገኝ ፈጣሪ አይደለችም እኮ፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ እንደአባ ክንፈ ካሉ “ጨዋ” መነኮሳት አንደበት የሚሰማ የድፍረት ንግግር ነው፡፡

Saturday, August 3, 2013

በአሰበ ተፈሪ የሆነውና እየሆነ ያለው ምንድን ነው?

ሐራ ዘተዋህዶ አይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ አይነት ሐሰተኛ ወሬ ማስነበቡን ተከትሎ ከስፍራው የደረሰን ጽሁፍ እንደሚሳየው ሀራ እውነታውን ገልብጦ የዘገበ መሆኑን ነው፡፡ መቼም ከሀራ ከዚህ የተሻለ ነገር አይጠበቅም፡፡ ሲጀመር አላማው እውነት ማቅረብ ሳይሆን እውንትን በማዛባትና ሀሰትን እውነት አስመስሎ በማቅረብ ማቅ አለአግባብ ለመበልጸግና በቤተክርስቲያን ተቆርቋሪነት ስም ቤተክርስቲያንን የመዝረፍ ተግባሩን እንዲቀጥልበት ሽፋን መስጠት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሌሎችን ስም አክፍቶ ማቅረብን እንደ አንድ ስልት እየተጠቀመበት ነው፡፡

ባለፈው ጽሑፍ ላይ ለማሳየት እንደሞከርነው የማቅ ሰዎች ከእነርሱ ጋር በሀሳብና በአካሄድ የተለየውን ሰው ሁሉ ከእኔ ጋር የሐሳብ ልዩነት ነው ያለው ነው ከማለት ይልቅ “ተሐድሶ መናፍቅ ነው” ማለት ይቀናቸዋል፡፡ በምዕራብ ሐረርጌ አሰበ ተፈሪ ላይ ከማኅበረ ናታኒም ጋር የተፈጠረውን አለመግባባትም ከማቅ ጋር የተፈጠረ አለመግባባት ሳይሆን ተሐድሶ መናፍቅነት ነው ማለታቸው ይኸው ክፉ ጠባያቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆችን ምን ያህል እየጎዳ እንዳለ ያመለክታል፡፡ ሰሞኑን ሐራ ዘተዋህዶ ብሎግ አሰበ ተፈሪን በተመለከተ የሰቀለው ጽሑፍ እንኳን ሌሎችን ሊያሳምን ይቅርና የራሱን አንባቢዎችንም ግራ ያጋባ መሆኑን ብሎጉ ላይ ከተሰጡት አስተያየቶች መረዳት ይቻላል፡፡ በአሰበ ተፈሪ በትክክል የሆነውና እየሆነ ያለው ምንድነው ለሚል ጠያቂ ከመሪጌታ የሻውወርቅ የደረሰን ጽሁፍ ምላሽ ይሰጣልና እንዲያነቡት እንጋብዛለን፡፡

Friday, August 2, 2013

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍን ከጸሐፊነት ለማውረድ የተደረገው እንቅሥቃሴ አሁንም አልተሳካም

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍን ከጸሐፊነት ለማውረድ የተደረገው እንቅሥቃሴ አሁንም አልተሳካም።

ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የብፁዕ አቡነ ዮሴፍን ከጸሐፊነት የይነሱልን ጥያቄ አልተቀበሉትም። በብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የተጠራ ነው የተባለ አስቸኳይ ስብሰባ በአትላንታ ቅድስት ማርያም የተደረገ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል። ይህ ስብሰባ ብዙ ትዝብቶችን አትርፎ ተጠናቋል በማለት በቅርብ ስብሰባውን ሲከታተሉ የነበሩ አባቶች ሲተቹ ተደምጠዋል። ስብሰባው በቀልን አላማ አድርጎ የተጠራ እንጂ መንፈሳዊ ሥራ ለመሥራት የተጠራ አለመሁኑን ታዛቢዎቹ ተናግረዋል። የቤተ ክርስቲያን አባቶች የሚጠሉትን ሲያጠቁ፣ የሚወዱቱን ሲመሩቁ ይታያሉ እንጂ የእግዚአብሔርን መንግስት ጉዳይ ከተውት ሰነበባብቷል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ስብሰባው ጳጳሳትን ብቻ የሚመለከት ነው ተብሎ የተነገራቸው ካህናት አንዳድ ሥውር እንቅሥቃሴዎችን በንቃት ለመከታተል አስችሎናል ይላሉ። በተለይም የስብሰባው አቀናባሪ የነበሩት አባ ጽጌ ድንግልና ዲያቆን አንዷለም በብዞዎች ወንድሞቻቸው ዘንድ ታላቅ የጥያቄ ምልክት ተቀምጦባቸዋል። አባ ጽጌ ድንግል በስብሰባው ላይ የተገኙ መሆኑን ያረጋገጥን ሲሆን የዲያቆን አንዱዓለም የስብሰባ ተሳትፎ ግን አልታወቀም። ታዛቢዎች እንደሚናገሩት የአቡነ መልከ ጼዴቅን አካሄድ የማይደግፉ ካህናትን ለመቀነስና በስብሰባው ላይ እንዳይገኙ በማድረግ ይፈለጋሉ በተባሉ አገልጋዮችና አባቶች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ታስቦ ሳይሳካ ቀርቷል። የአቡነ መልከጼዴቅን አካሄድ የሚደግፉ ካህናት ግን በስብሰባው ተገኝተዋል። ለምሳሌ መላከ ገነት ገዛኸኝ ከኒዮርክ፣ አባ ጽጌ ድንግል ስጦታው ከሎስ አንጀለስ ሊቀ ካህናት ምሳሌና አቶ አሥራት የተባለው የኦክላንድ መድኃኔ ዓለም የቦርድ አባል ተገኝተው ነበር። ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ከጸሐፊነት ይውረዱ የሚል አጀንዳ ተይዞ ያነጋገረ ሲሆን፣ እራሳቸው ብፁዕ አቡነ ዮሴፍም ይህን ኃላፊነት አልፈልገውም ተረከቡኝ ብለው እንደነበር ምንጮቻችን ተናግረዋል። ቅዱስ ፓትርያርኩ ግን የአቡነ ዮሴፍንም ሆነ የአቡነ መልከ ጼዴቅን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ አቡነ ዮሴፍ በጸሐፊነታቸው እንዲቀጥሉ አስፈላጊ ከሆነም ጉባኤው በተሟላበት በጥቅምቱ ሲኖዶስ እንዲታይ አድርገዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ሊቀ ጳጳስ ከራሱ ሀገረ ስብከት ውጭ ሲንቀሳንቀስ የክፍለ ሀገሩን ጳጳስ እንዲያስፈቅድ፤ ከዚህ ውጭ ማንም ወደ ማንም ሀገረ ስብከት እንዳይንቀሳቀስ የሚል ውሳኔ ተወስኗል። ይህ ውሳኔ አቡነ ዮሴፍን ወደ ካሊፎርኒያ እንዳይሄዱ ለማገድ ነው ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ይወገዛሉ ተብለው ከተጠበቁት ውስጥ በሃይማኖት ጉዳይ የተከሰሰ አልነበረም ተብሏል። ነገር ግን የዶ/ አባ ገ/ ሥላሴ ጥበቡና የአባ ቃለ ጽድቅ ጉዳይ ተነሥቶ የነበረ ሲሆን የአባ ቃለ ጽድቅ ጉዳይ ወደ ጥቅምቱ ሲኖዶስ ሲተላለፍ ዶ. አባ ገ/ ሥላሴ ጥበቡ ወደ ሲያትል ሄደው እንዳያስተምሩ ታግደዋል ተብሏል። በዳላስ ቴክሳስ በቅርቡ አዲስ የተከፈተው የፈለገ ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ሲኖዶስ ስር በማካተት ዙሪያ አጀንዳ ተነሥቶ የነበረ ሲሆን ጉዳዩ ተጠንቶ ለጥቅምቱ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ተወስኗል። የዲሲ ቅዱስ ገብርኤል ጉዳይም በዚያው በጥቅምት እንዲታይ ነው የተወሰነው። በመጨረሻም አዲስ ቋሚ ሲኖዶስ በማቋቋም ስብሰበው እንደተፈራው ሳይሆን ተጠናቋል። የቋሚ ሲኖዶስ አባላት ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ፣ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል፣ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ናቸው።

Thursday, August 1, 2013

የወንድሞች ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ “ከእኔ በቀር ማንንም አልይ” እያለ ነው

የወንድሞች ከሳሽ ማኅበረ ቅዱሳን በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ “ከእኔ በቀር ማንንም አልይ” እያለ ነው
ከእርሱ በቀር ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ እንደሌለና ብቸኛው የቤተክርስቲያን አለኝታ እርሱ እንደሆነ በየአጋጣሚው ሁሉ አፉን ሞልቶ የሚደሰኩረው ማህበረ ቅዱሳን በየስፍራው ሁከትና ብጥብጥ ማስነሣቱንና የቤተክርስቲያን ልጆችንም ለምን የእኔ ተከታይ አትሆኑም በሚል ያልተቀበሉትንና የተቃወሙትን ሁሉ ክፉ ስም እየሰጠ ከቤተክርስቲያን ማሳደዱን ቀጥሏል፡፡ በተለይም በቤተክርስቲያን ውስጥ ከእኔ በቀር ማንም መደራጀትና መንፈሳዊ ተግባርን ማከናወን የለበትም የሚል አቋም በመያዝ መንፈሳዊ እውርነት ያጠቃው ማኅበረ ቅዱሳን እየወሰደ ባለው ሰይጣናዊ እርምጃ ማንነቱን እያጋለጠ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር በአላማ ያልተስማሙትን ሁሉ “ተሀድሶ መናፍቅ” የሚልና በየዋሁ ምእመን ዘንድ “ማስፈራሪያ” ባደረገው የስድብ ስም እየተጠቀመ የቤተ ክርስቲያንን ሰላማዊ አየር እየበከለ ይገኛል፡፡

በተለይም ሀራ የተባለው ብሎግ ማኅበሩ በአካፋ እያስገባ በማንኪያ እንደሚያወጣው ሳይሆን ከማህበሩ በተሻለ ሁኔታ በቅንነትና በታማኝነት ለቤተክርስቲያን የሚጠቅም ስራ በተጨባጭ በመስራት እየተንቀሳቀሱ ያሉትን “ለምን በእንጀራዬ ትገባላችሁ” በሚል መንፈስ እየተነሳሳና በመንገዱ ላይ የቆሙበት የመሰለውን ሁሉ ሃይማኖታዊ ሕጸጽ የተገኘባቸው በማስመሰል በሐሰት ወሬ ማሰራጫ ብሎጎቹ እየለቀቀ ምእመናንን ማወናበዱን ቀጥሏል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ ሰሞኑን July 31, 2013በሕዋስ እና በማኅበር የተደራጁ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆች የምሥራቅ ኢትዮጵያ አህጉረ ስብከትን እያናወጡ ነው” የሚል ጯኺ ርእስ የሰጠው ሐሰተኛ ወሬ ይጠቀሳል፡፡ የወሬውን ይዘት ያነነበ ሰው የሚገነዘበው ሀራ እንዳለው ያለ ችግር ተፈጥሮ ሳይሆን ከማቅ ጋር አለመግበባት ተፈጥሮ ነው፡፡