Monday, September 30, 2013

ከሰማይ ወረደ በተባለው መስቀል ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አባ እስጢፋኖስ ቃለመጠይቅ ሰጡ


ለሚያየው ምድራዊ የሆነውና በላዩ ላይ የሚገኘው የስነ ስቅለት ምስል ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት የተከተለ አይደለም እየተባለ በመተቸት ላይ ያለው የገላንጉራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት የመጋቤ ሐዲስ ፍስሀ መስቀልን በተመለከተ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ መስከረም 18/2006 ዓ.ም. ከታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ቃለምልልስ አደረጉ፡፡ ሊቀጳጳሱ እንዳሉት ከሰማይ ወረደ የተባለውን መስቀል ከወደቀበት መሬት ያነሡትና ወደቤተክርስቲያን እንዲገባ ያደረጉት እርሳቸው መሆናቸውን ገልጸው፣ “በወቅቱ ከመሬቱ ላይ እንዲነሳ እነርሱ (መስቀሉ ወረደ ያሉት ክፍሎች) ብዙም ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ እዚያው ላይ እያለ ቤተክርስቲያን እንዲሠራለት ነው የፈለጉት፡፡ ነገር ግን ቤተክርስቲያን የሚሰራለት ከሆነም መስቀሉ መሬት ላይ ሆኖ አይደለም የሚቆፈረውና የግድ ወደ መቅደሱ መግባት አለበት አልናቸው፡፡” ብለዋል፡፡ ሲጀመርም “መስቀል ከሰማይ ወረደ” የተባለውን ድርሰት በድጋሚ የደረሱት (የመጀመሪያዎቹ ደራሲዎች ደብረሊባኖሶች ናቸው) እንዲህ ያለ ትርፍ ለማግኘት እንጂ ለሌላ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም እዚያው ጎረቤታቸው ታቦቷ ሕንጻ ካልተሠራልኝ አልገባ አለች ተብሎ ሕንጻ እንደተሠራላት እኛም በዚህ መንገድ ሕንጻ ማስገንባት እንችላለን በሚል ስሌት ይህን እንዳደረጉ መገመት አይከብድም፡፡

Thursday, September 26, 2013

ከሰማይ ወረደ በተባለው መስቀል ላይ ሳይንሳዊ ምርመራ ማድረግ ክልክል ነው ተባለ ነገሩ “በሃይማኖት ጉዳይ ሳይንስ ጣልቃ አይገባም” የሚል ቃና ያለው ይመስላል


ከሰሞኑ ከሰማይ ወረደ ስለተባለው መስቀል ከዘገቡት የፕሬስ ውጤቶች መካከል አንዱ የሆነው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በመስከረም 11/2006 ዓ.ም. እትሙ ላይ “ከሰማይ ወረደ ለተባለው መስቀል የሳይንስ ምርመራ አይፈቀድም ተባለ” የሚል ርእስ ይዞ በድጋሚ ወጣ፡፡ ጋዜጣው እንደ ዘገበው መስቀሉ ከሰማይ ወርዷል ለሚለው የብዙዎች ጥርጣሬ ማረጋገጫ መስጠት እንዲቻል “ወረደ” በተባለው መስቀል ሳይ ሳይንሳዊ ምርመራ ይደረግ ዘንድ ስለመጠየቁ ሐሳብ ቀርቦ እንደሆን የተጠይቁት፣ መልስ የሠጡትና የዚህ “ተአምር ብቸኛ የዓይን ምስክር የሆኑት” መጋቤ ሐዲስ ፍስሃ እስካሁን “ከሰማይ የወረደውን መስቀል” አድናቂዎች እንጂ ምርምር እናካሂድ የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ምሁራን አለመኖራቸውን ጠቅሰው ጥያቄውን የሚያቀርቡ ቢኖሩ ግን “የማይሞከር ነው” ሲሉ ተከላክለዋል፡፡

ይህ “ተአምር” ለሳይንሳዊ ምርምር ክፍት እንዳይሆን መከልከሉ ሰዎች በጉዳዩ ላይ ከፊት ይልቅ እንዲጠራጠሩ ሰፊ በር የሚከፍት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጂ “ያደረገችውን ታስታውቅ ከወደደረቷ ትታጠቅ” እንዲሉ መጋቤ ሐዲስ ፍስሀ ያደረጉትንና የሆነውን ስለሚያውቁ “የማይሞከር ነው” በሚል “በሃይማኖት ጉዳይ ሳይንስ ጣልቃ አይገባም” አይነት መከራከሪያ አቅርበው ለምርምር በሩ ዝግ መሆኑን ፈርጠም ብለው ተናግረዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ “ወረደ” የተባለውን መስቀል ሳይንስ ቢያረጋግጠው ከሰማይ የወረደ እስከሆነ ድረስ ምንም የሚያስፈራ ነገር አይኖርም ነበር፡፡ ነገር ግን አስቀድመን በእርግጠኛነት እንደተናገርነው መስቀሉ ከምድር የተገኘ ስለሆነ “ከቶም አይሞከርም” ብለው “የነገርኳችሁን ማመን እንጂ መመርመር አትችሉም” የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ይህ ግን ትክክል አይደለም፡፡

Monday, September 16, 2013

እፎኑ መስቀል ዘደብረ ሊባኖስ ጽርሑ
ወረድኩ እምነ ሰማይ ይቤለነ ናሁ
እንዘ ነአምሮ ለሊነ ከመ ሊቀ ጸረብት አቡሁ
ትርጓሜ፦
ቤቱ ደብረ ሊባኖስ የሆነው መስቀል
አባቱ (ጠራቢው) የአናጺዎች አለቃ መሆኑን ስናውቅ
እንዴት ከሰማይ ወረድሁ ይለናል?

“ ‘ከሰማይ ወረደ’ ተብሎ በጳጳሳት የተጐበኘው መስቀል ለህዝብ ይታያል” ይህ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ርእሰ ዜና ነው፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በመስከረም 4/2006 ዓ.ም. እትሙ በፊት ገጹ ካስነበባቸው ዜናዎች መካከል ዋና አድርጎ ያቀረበው “ ‘ከሰማይ ወረደ’ ተብሎ በጳጳሳት የተጎበኘው መስቀል ለህዝብ ይታያል” በሚል ርእሰ ዜና የቀረበው ዜና አንዱ ነው፡፡   

መስቀሉ “ከሰማይ ወረደ” የተባለው ከ5 ዓመታት በፊት አቃቂ ውስጥ በተተከለው የገብርኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲሆን ነገሩ ሆነ የተባለውም ነሐሴ 23/2005 ዓ.ም. ለ24 አጥቢያ ሌሊት ላይ ነው፡፡ ወረደ ለተባለው መስቀል የዓይን እማኝ ነኝ ያሉት ደግሞ መጋቤ ሐዲስ ፍስሐ የተባሉ ሰው መሆናቸውን ጋዜጣው ዘግቧል፡፡ መጋቤ ሐዲሱ መስቀሉ በኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት ተጠቅልሎ ከሰማይ በዝግታ እየተገለባበጠ ሲወርድና መሬት ላይ ሲያርፍ በአይኔ በብረቱ አይቻለሁ ማለታቸውን የዘገበው ጋዜጣ፣ ጊዜው ከሌሊቱ በ9 ሰዓት ገደማ መሆኑን መናገራቸውን ጠቅሷል፡፡ የመስቀሉን መውረድ ለማየት የቻሉትም ሌሊት በቤተክርስቲያን ውስጥ ከነበረው ማሕሌት ላይ ነፋስ ለመቀበል በወጡ ጊዜ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በወቅቱ ቤተልሔሙ የተቃጠለ መስሏቸው ሲጮኹ ሰምተው ከመጡ አገልጋዮች መካከል አንዱ ወጣት አገልጋይ አያለሁ ብሎ ሲቀርብ “አንዳች ነገር አስፈንጥሮ መሬት ላይ እንደጣለውና ምላሱ ተጎልጉሎ እንደወጣ፣ ለአራት ቀናትም ራሱን ስቶ ከቆየ በኋላ መስቀሉ ከወደቀበት መሬት ላይ ተነሥቶ ወደቤተክርስቲያን በአጀብ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ መንቃቱንና አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ወጣቱም ተጠይቆ መስቀሉን ሊያነሳው ሲል “አንዳች ህጻን ልጅ የመሰለ ነገር” ጎትቶ መሬት ላይ እንደጣለውና ከዚያ በኋላ ራሱን እንደ ሳተ ተናግሯል ብለዋል መጋቤ ሀዲስ ፍስሀ፡፡

Friday, September 13, 2013

ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤
አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።
(2ቆሮ. 5፥17)
እንኳን ለ2006 ዓ.ም በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ!
2005 ዓ.ም. ሲብት አዲስ እንዳልተባለ እነሆ አሁን አርጅቶ አሮጌ ተባለ። 2006 ዓ.ም. ደግሞ በተራው አዲስ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ዓመታትን አዲስ እና አሮጌ ስንል የሰየምናቸው እኛው ነን፡፡ 2005 ዓ.ም. ከማለፉ እና 2006 ከመግባቱ በቀር ቀኑ ሁሉ ግን ያው ነው፡፡ የዘመን መለወጫን ወቅት በመንተራስ ስላለፈው አሮጌ ዓመትና ስለጀመርነው አዲስ ዓመት በተለያየ ርእስ ብዙ ማለታችን የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ አዲስ ካልሆንንና በአዲስ አስተሳሰብ ለአዲስ ተግባር ካልተነሳሳን አዲስ ያልነው ዓመት ከስሙ በቀር በተግባር አዲስ ሊሆን አይችልም፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ አዲስ ፍጥረት ካልሆንንና አዲስ ያልነውን ዓመት በአሮጌው ማንነት የምንቀበልና የምንኖርበት ከሆነ “አሮጌውን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ” ለማኖር መሞከር ነው የሚሆነው፡፡ እንዲህ ቢደረግ ደግሞ እንደተጻፈው አቁማዳው ይቀደዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፡፡ ስለዚህ አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፡፡

Monday, September 9, 2013

የዘመን ምስክር

(ከጮራ ድረ ገጽ የተወሰደ)
በዚህ ዐምድ ለቤተ ክርስቲያን መሻሻልና መለወጥ የተጋደሉ፥ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም መልካም ሥራን የሠሩ አበውን ሕይወትና የተጋድሎ ታሪክ አሁን ላለውና ለቀጣዩ ትውልድ አርኣያ እንዲሆን እናስተዋውቃለን፡፡


አለቃ ታየ ገብረ ማርያም (1853 - 1916 ዓ.ም.)
አይሁድ መሲሑን ይጠባበቁ የነበሩ ሕዝብ ናቸው፤ መሲሑ ሲመጣ ግን አልተቀበሉትም፡፡ የመሲሑን ደቀ መዛሙርትም አሳድደዋል፡፡ እነርሱን መስሎ የሚኖረውን ሰው እውነተኛ አይሁዳዊ ሲሉ፥ ዐዲስና እንግዳ ትምህርትን ሳያመጣ በመጽሐፋቸው የተገለጠውንና እነርሱ ያላስተዋሉትን እውነት የሚያምነውንና የሚኖረውን የመሲሑን ተከታይ ደግሞ መናፍቅ እያሉ ሲኰንኑ ኖረዋል፡፡

Tuesday, September 3, 2013

የጉድ ሙዳዩ አባ አብርሃምና በኢየሱስ ስም ላይ የከፈተው ዘመቻ

(አናኒመስ ከሐረር)
አሁን የምነግራችሁ የምሥራች ሳይሆን መርዶ ነው፡፡ በተለይ ለእኛ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች አንገት የሚያስደፋ ትልቅ ውርደት ነው፡፡ ሐረርን ለማህበረ ቅዱሳን ለማስከበር ተልዕኮ ተሰጥቶት ወደ ሐረር የመጣው የጉድ ሙዳዩ አባ አብርሐም ተልዕኮውን ለመፈፀም ደፋ ቀና ማለት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለስራዬ እንቅፋት ናቸው ያላቸውንና የቤተክርስቲያን እንጂ የማህበር አገልጋይ አንሆንም ያሉትን የቤተክርስቲያን ልጆች እያደነ ከቤተስርቲያን ማፈናቀሉን ቀጥሎበታል፡፡

የደ/ሣ/ቅ/ሚካኤል ቤ/ክ አስተዳዳሪ የተነሡት ቃለአዋዲ ባለማክበራቸው መስሎኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በ22-10-2005 ዓ.ም. የየአድባራቱን ሰበካ ጉባኤ፣ ሰንበት ት/ቤት፣ ስብከተ ወንጌልና ልማት ኮሚቴ አባላትን ሰብስቦ ውይይት መሰል የማስፈራሪያ መልእክት ያስተላለፈው የጉድ ሙዳዩ ከአንድ ስብሳቢ “የሚካኤል አስተዳዳሪ ለምን ተነሳ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ሲመልስ እንዲህ አለ፡፡ “ሰውየው ኢየሱስ ኢየሱስ ማለት ያበዛል፡፡ ከአንዴም ሁለቴ ጠርቼ ነገርኩት፡፡ ኢየሱስ የሚሉት አምላክነቱን እና አዳኝነቱን ያልተረዱት ናቸው፡፡ ኢየሱስ የሚለው ስም ማንነቱን አይገልፅም፤ ክብሩን ያንሰዋል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ኢየሱስ አትበል አልኩት፡፡ እሱ ግን ሰዓታቱ፣ ኪዳኑ፣ ቅዳሴው ሁሉ እኮ ኢየሱስ ኢየሱስ ነው የሚለው እያለ ሊከራከረኝ ሞከረ…” በማለት መልስ ሲሰጥ ንቀት በተሞላበት እና ኢየሱስ የሚለውን ስም በማጥላላት ነበር፡፡” አለ፡፡