Friday, September 13, 2013

ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤
አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።
(2ቆሮ. 5፥17)
እንኳን ለ2006 ዓ.ም በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ!
2005 ዓ.ም. ሲብት አዲስ እንዳልተባለ እነሆ አሁን አርጅቶ አሮጌ ተባለ። 2006 ዓ.ም. ደግሞ በተራው አዲስ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ዓመታትን አዲስ እና አሮጌ ስንል የሰየምናቸው እኛው ነን፡፡ 2005 ዓ.ም. ከማለፉ እና 2006 ከመግባቱ በቀር ቀኑ ሁሉ ግን ያው ነው፡፡ የዘመን መለወጫን ወቅት በመንተራስ ስላለፈው አሮጌ ዓመትና ስለጀመርነው አዲስ ዓመት በተለያየ ርእስ ብዙ ማለታችን የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን እኛ አዲስ ካልሆንንና በአዲስ አስተሳሰብ ለአዲስ ተግባር ካልተነሳሳን አዲስ ያልነው ዓመት ከስሙ በቀር በተግባር አዲስ ሊሆን አይችልም፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ እንደእግዚአብሔር ፈቃድ አዲስ ፍጥረት ካልሆንንና አዲስ ያልነውን ዓመት በአሮጌው ማንነት የምንቀበልና የምንኖርበት ከሆነ “አሮጌውን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ” ለማኖር መሞከር ነው የሚሆነው፡፡ እንዲህ ቢደረግ ደግሞ እንደተጻፈው አቁማዳው ይቀደዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፡፡ ስለዚህ አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፡፡


አንባቢ ሆይ! አንተ/አንቺ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ሆነሃል/ሆነሻል? ወይስ በአሮጌው ማንነት ነው ያለኸው/ያለሽው? ትልቁና መመለስ ያለበት የሕይወት ጥያቄ ይኼ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።” በማለት እንደሚናገረው ሰው ከአሮጌው ማንነት ወደ አዲሱ ማንነት የሚሸጋገረው በክርስቶስ በመሆን ብቻ ነው፡፡ በክርስቶስ መሆን ማለት ክርስቶስን በታሪክ ደረጃ ማወቅ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያሰተምረው መሠረት ክርስቶስን በማወቅ፣ ስለኃጢአቴ ሞቶልኛል፣ የኃጢአቴን ዕዳም ከፍሎልኛል፣ በእርሱ የማዳን ሥራ የዘላለምን ሕይወት አገኛለሁ ብሎ ማመንና ክርስቶስን አዳኝ አድርጎ በመቀበል የሚገኝ አዲስ ማንነት ነው፡፡ ልብ ይበሉ! “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤” ተብሎ ተጽፏል (ዮሐ. 1፥12)፡፡ በዚህ መንገድ ክርስቶስን የተቀበለና መዳንን በእምነት የወረሰ ክርስቲያን ሊኖር የሚገባው ክርስቶስን በእምነት እንደ ተቀበለ ሰው ነው፡፡ “እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ። ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ።”  (ቆላ. 2፥6-7) ተብሎ ተጽፏልና፡፡ በሌላም በኩል መጽሐፍ ቅዱስ አሮጌውን ሰው እንድናስወግድና አዲሱን ሰው እንድንለብስ ይናገራል፡፡ “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” (ኤፌ. 4፥22)፡፡

አዲሱ ዓመት 2006 ዓ.ም. በክርስቶስ ያልሆንን በክርስቶስ በመሆን፣ በክርስቶስ የሆንን ደግሞ ለክርስቶስ በመኖር ጌታችንን የምናገለግልበትና ለእርሱ ክብር የምንኖርበት ዓመት እንዲሆንልን እንመኛለን!!

No comments:

Post a Comment