Thursday, October 31, 2013

አባ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ እየፈጸሙ ያለው ሙስናና እየነፈጉ ያለው ፍትሕ ብዙዎችን እያማረረ ነው

አባ ገብረ ሚካኤል ለጵጵስና ሲታጩ የዑራኤል አስተዳዳሪ የነበሩት አባ ላእከ የተባሉ አባት ለአቡነ ጳውሎስ “ምነው አባታችን የምናውቃቸውን አባ ገብረ ሚካኤልን ልንድራቸው ሲገባ እንዴት ያጰጵሳሉ? እነዚህ በሚመሯት ቤተክርስቲያን ውስጥ በኀላፊነት መሥራት አልፈልግም” ብለው “ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢየሩሳሌም” ወይም “የኢየሩሳሌምን ጥፋቷን አታሳየን” እንዳለው ነቢይ የኦርቶዶክስን ጥፋት ላለማየት በመወሰን ወደ መርጡለማርያም ገዳም እንደገቡ ይነገራል፡፡ መልአከ ገነት አባ ኀይለ ማርያም የተባሉ አራዳ ጊዮርጊስ አለቃ የነበሩ አባትም በጊዜው በጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የነበረውን ገንዘብ ለመዝረፍ ታስቦ እርሳቸው ለጵጵስና ሲታጩ (ከእነአባ ገብረሚካኤል ጋር)፣ “ወቅብዐ ኃጥኣንሰ ኢይትቀባዕ ርእስየ” እና “ወኢይደመር ውስተ ማኅበሮሙ ለእኩያን” የሚሉትን የቅዱሳት መጻሕፍት ቃል በመጥቀስ የሚያስተዳድሩትን ደብር ለቀው ገዳም ሊገቡ ሲሉ በፓትርያርኩ ተለምነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ነበር፡፡ ነገር ግን የአባ ገብረሚካኤል የድራፍት ቡድን አላላውስ አላንቀሳቅስ ስላላቸው የሚወዷትን አገራቸውንና ቤተክርስቲያናቸውን ጥለው በመሰደድ በብስጭትና በንዴት በስደት አገር ሳሉ ዐርፈዋል፡፡ እነዚህ አባቶች ያኔ የተናገሩት ቢሰማና አባ ገብረሚካኤል ወደ ጵጵስና ሳይሆን ወደ ትዳር እንዲገቡ ቢደረግ ኖሮ ዛሬ በእርሳቸው እየደረሰ ያለው ጥፋት በቤተክርስቲያን ላይ ባልደረሰ ነበር የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

Sunday, October 27, 2013

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሆይ ከእንቅልፍ የምትነቂበት ሰዓት አሁን ነው

ሰሞኑን በተካሄደው 32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ “የሃይማኖት መቻቻል” በሚል ርእስ በተካሄደው አንድ ውይይት ላይ፣ አንዳንድ ጳጳሳት ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በስብሰባው ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከመጡ ባለሥልጣናት ጋራ ባደረጉት ውይይት፣ በሃይማኖት ጉዳይ በተለያዩ ክልሎች በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ተጽእኖ በመግለጽ የመንግስትን ባለሥልጣናትን መውቀሳቸው ትክክለኛ የአባትነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ ያደረገ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች እንደ ሃይማኖት አባትነታቸው ጥፋት ሲፈጸም በተገቢው መንገድ ፊት ለፊት መናገራቸውና የመንግሥት ባለሥልጣናትን መውቀሳቸውና መገሠጻቸው ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ወቀሳውን ተቀብለው እንደ ሕዝብ አገልጋይነታቸው በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ በቤተክርስቲያኒቱ አማኞች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ሊያስተካክሉ ይገባል፡፡ እንዲህ ካልሆነ የሃይማኖት መቻቻል የሚለው ነገር ፍሬ ቢስ ይሆናል፡፡ ውጤቱም የከፋ ነው የሚሆነው፡፡

Monday, October 21, 2013

የ32ኛው የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ተጠናቀቀ የአቋም መግለጫው ማኅበረ ቅዱሳን ሒሳቡን በቤተክህነት ሞዴላሞዴል እንዲሠራ ያዛል


ባለፈው ሳምንት ሲካሄድ የሰነበተው የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት ቅዳሜ ጥቅምት 09/2006 ዓ.ም. ከሰዓት በፊት ተጠናቀቀ፡፡ በአቋም መግለጫው ላይ ከተነሡት ነጥቦች አንዱ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳንን የተመለከተ ሲሆን፣ የአቋም መግለጫውም የሚከተለው ነው፡፡
“ማኅበረ ቅዱሳን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉት ማእከላትና የግንኙነት ጣቢያዎች በየሀገረ ስብከቱ እያበረከተ ያለው ሁለንተናዊ ልማት ጉባኤው ከየሪፖርቱ በማወቁ አገልግሎቱን ተቀብሎታል። ከዚህ አንጻር እየሰራበት ያለውን የገቢና የወጪ ሂሳብ በቤቱ የቁጥጥር ሥርዓት እያስመረመረ የቤቱን ሞዴላሞዴሎች እየተገለገለ ማዕከልንም በመጠበቅ የቤተክርስቲያንን መብትና ሃብት ሃይማኖትና ሥርዓት እንዲጠብቅ መልካም ምሳሌ እየሆነ አገልግሎቱን በጥበብ እንዲቀጥል ጉባኤው ያስገነዝባል። ከዚህም ጋር ማኅበሩ አቅጣጫ ያልጠበቀ አሰራር እንዳይታይበት በቅዱስ ሲኖዶስ የማስተካከያ መመሪያ እንዲሰጠው ጉባኤው ያሳስባል።”
ከዚህ የአቋም መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው በስብሰባው ላይ ማኅበሩ ሂሳቡን ባለማስመርምሩ ትችት ተሰንዝሮበት የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ የማኅበሩ ተወካይ የነበረው አባልም “ቤተ ክህነቱ የተመሰከረለት የሂሳብ አያያዝ የሌለው በመሆኑ ነው ለቤተክህነቱ የማናስመረምረው” ሲል ለጠቅላይ ቤተክህነቱ ያለውን ንቀት አሳይቶ ስለነበር እየሰራበት ያለውን የገቢና የወጪ ሂሳብ በቤቱ የቁጥጥር ሥርዓት እያስመረመረ የቤቱን ሞዴላሞዴሎች እየተገለገለ” ሥራውን እንዲያከናውን መመሪያ ተሰጥቶታል፡፡ ይሁን እንጂ ማኅበሩ ይህን በቀላሉ ይተገብረዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ከዚህ ቀደምም ከአባ ሠረቀ ብርሃን ጋር ያጋጨው ይኸው “ሒሳብህን አስመርምር” የሚለው ጥያቄ ነበር፡፡ ማኅበሩ ግን ጥያቄውን በአዎንታዊ መንገድ ከመቀበል ይልቅ ወደመቃወምና አባ ሠረቀን ወደመክሰስ ነው የሄደው፡፡ ይሁን እንጂ ወትሮም ቢሆን ሕገወጥ ሆኖ መቀጠል ስለማይቻል፣ ያንጊዜ ለተነሳበት የሂሳብህን አስመርምር ጥያቄ ሌላ መልክ በመስጠት ሊያልፈው ቢሞክርም ጥያቄው አሁንም መነሣቱ፣ በዚህ ስብሰባ ላይ በከፍተኛ ድጋፍ ውሳኔው መተላለፉና በአቋም መግለጫ መጠቀሱ ለማኅበሩ ትልቅ ሽንፈት ነው የሚሆንበት፡፡ ማኅበሩ የገንዘብ አቅሙን ከዚህ በበለጠ ለማጠናከርና ጡንቻውን ለማፈርጠም ከሚያደርገው እንቅስቃሴና ቤተክርስቲያን ውስጥ “ተሐድሶ መናፍቃን” በሚላቸው የቤተክርስቲያን ልጆች ላይ ለሚፈጽማቸው ጥቃቶች ማካሄጃና ለሌሎቹም ሕገወጥ ድርጊቶቹ ከሚያወጣቸው ወጪዎች አንጻር በቤተክህነት ሞዴላሞዴሎች እንዲጠቀም መደረጉ በቤተ ክርስቲያን ስም እየሰበሰበ ያለውን ገንዘብ ለራሱ ድብቅ ዓላማ ሳይሆን መልሶ ለቤተክርስቲያን ጥቅም እንዲያውል ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል። 

Wednesday, October 16, 2013

ማኅበረ ቅዱሳን በአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ በደረሰበት ተቃውሞ ተወካዮቹ ስብሰባ ረግጠው ወጡ


32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተክህነት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ከየሀገረ ስብከቱ የተወከሉ የአህጉረ ስብከቶች ሥራ አስኪያጆች፣ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎችም በተገኙበት ጥቅምት 3/2006 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡ በስብሰባው ላይ ከየአህጉረ ስብከቶች በመጡ ሥራ አስኪያጆች የሥራ ሪፖርት እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን ውይይትም እየተደረገ ነው፡፡

በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን በጠቅላይ ቤተ ክህነት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ሊቀ ካህናት ኃይለ ስላሴ ዘማርያም ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አስጊ ኃይል እንደ ሆነና ከተለያዩ የንግድ ተቋማቱ የሚሰበስበውንና በቤተክርስቲያን ስም ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚሰበስበውን ገንዘብም ኦዲት እንደማይደረግ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህም ማቅ ኪራይ ሰብሳቢ ድርጅት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

Wednesday, October 9, 2013

ዳንኤል ክብረት “ማቅ አክራሪ አይደለም” አለ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ወቀሰ

የማቅ አክራሪነት በሁሉም አንድ እየታወቀ በመጣበትና ማቅም ትልቅ ጭንቀት ውስጥ በገባበት በዚህ ወቅት፣ ማኅበረ ቅዱሳን ካፈራቸው “ሊቃውንት” አንዱ የሆነውና ራሱን “የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመራማሪ” ብሎ የሚጠራው ዳንኤል ክብረት “ማቅ አክራሪ አይደለም” ሲል ተከላከለ፡፡ ዳንኤል ይህን ያለው ማቅ በገንዘቡ ከሚጠቀምባቸውና እንደጋዜጠኛ ሳይሆን እንደማህበረ ቅዱሳን ሆነው በሚጽፉ (አንዳንዴም ተጽፎ ነው የሚሰጣቸው) “የግል” መጽሔቶች መካከል አንዱ ከሆነው ከዕንቁ መጽሔት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ነው፡፡ ዳንኤል ከአክራሪነት ጋር በተያያዘ ማቅ በአክራሪነት መፈረጁን በመቃወም ማኅበረ ቅዱሳን ግን እስከ አሁን ድረስ አክራሪ ሆኖ ያመጣው ነውጥ፣ ያስነሳው ነገር፣ የደበደበው፣ የገደለው ሰው፣ ያቃጠለው ቤተ እምነት የለም፡፡”  በማለት እርሱ አክራሪነትን በተመለከተ ከደሙ ንጹሕ ነው ብሏል፡፡

Friday, October 4, 2013

አክራሪው ማኅበረ ቅዱሳን ‘አክራሪ አይደለሁም፤ አክራሪ ነው የሚል ማስረጃ ያቅርብብኝ’ አለ

አክራሪው ማኅበረ ቅዱሳን ‘አክራሪ አይደለሁም፤ አክራሪ ነው የሚል ማስረጃ ያቅርብብኝ’ አለ

ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያን ውስጥ በፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ባሉት ተግባራት በአክራሪነት የተፈረጀውና ቀድሞም ቢሆን በዚሁ ግብሩ የሚታወቀው ማኅበረ ቅዱሳን በሐመር መጽሔት የነሐሴ 2005 እትም ርእሰ አንቀጽ ላይ “ክርስትና ‘አክራሪነት’ን የሚያበቅል ነገረ ሃይማኖታዊ መሠረት የለውም” በሚል ርእስ ባቀረበው ሐተታ አክራሪ አለመሆኑንና አክራሪ ነው የሚል ካለ ማስረጃ ሊያቀርብበት እንደሚገባ ገለጸ፡፡

ርእሰ አንቀጹ ክርስትና ከአክራሪነት ፈጽሞ የተለየ መንገድ መሆኑን በወርቃማ ቃላት ለመግለጽ የሞከረ ቢሆንም በገለጻው መሠረት እንኳን ማኅበረ ቅዱሳንን መፈተሽና እስካሁን የተጓዘበትን መንገድ መመርመር ከተቻለ ማኅበሩ እልም ያለ አክራሪ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በዚህም ማኅበረ ቅዱሳን የጻፈውን ያልኖረና የማይኖር፣ ንግግሩና ስራው ለየቅል የሆኑበት ስብስብ መሆኑን ራሱ በራሱ መስክሯል፡፡