Wednesday, November 27, 2013

ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ


ዳንኤል ክብረትን ካበ ማኅበረ ቅዱሳንን ተረበ
አንጋፋው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ በጥቅምትና ኅዳር/2006 ዓ.ም. እትሙ በርእሰ አንቀጹ “፴፪ኛውን አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ እንደ ታዘብነው” በሚል ርእስ ባስነበበው ጽሑፍ ዳንኤል ክብረትን አለቅጥ የካበውና “ዕውቅ ጸሐፊና የበጎ ፈቃድ  ሐዋርያ” የሚል ማዕረግ ሰጥቶ እላይ የሰቀለው ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳንን ደግሞ በዚህ አያያዝህ ዕድሜህ ዐጭር ነው ሲል ተርቦታል፡፡ በመካብም በመናድም የማይታማው ዜና ቤተ ክርስቲያን ዳንኤልን የካበው በአውስትራሊያ የሜልቦርን ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ምእመናንን አስተባብሮ 18,500 ብር ለ32ኛው የሰበካ አጠቃላይ የፐርሰንት ክፍያ ፈጽሟል በማለት ነው፡፡

እንዲህ ማለት ይገባ ነበር ወይ? እውን ዳንኤል የፈጸመው የፐርሰንት ክፍያ ነው ወይስ ስጦታ? እንደሚታወቀው የፐርሰንት ክፍያ ከአብያተ ክርስቲያናት ገቢ ላይ ለቤተክህነት የሚደረግ የ20% ፈሰስ ነው፡፡ ታዲያ በምን ሒሳብ ነው ዳንኤል ምእመናንን አስተባብሮ አስገባ ያለውን ገቢ “ፐርሰንት” ነው ሲል የጠራው? ነው ወይስ ማቅን ለመናድ የዳንኤልን ስጦታ እንደ መቅድም መጠቀሙ ይሆን?  ምናልባትም በአካል ከማቅ ቢወጣም በመንፈስ ግን  መቼውንም ቢሆን ከማቅ የማይለየው ዳንኤል እንደ ግለሰብ ለዚያውም ቤተክርስቲያን በመደበኛ ሠራተኛነት ሳትመድበው ፐርሰንት ከከፈለ፣ ማቅ ፐርሰንት የማይከፍለው እስከ መቼ ነው? ብሎ ለማሳጣትና ማቅን ለመናድ የልብ ልብ እንዲሰጠው ብሎ የድፍረት መርፌ ለመወጋት ሲል ዳንኤልን “ፐርሰንት አስገባ” ሲል አሞግሶታል፡፡ እርግጥ ይህን ያልህ የሚያጽፍ ባይሆንም ዳንኤል እንዲህ ማድረጉ ለማቅ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል ተብሎ ተገምቷል፡፡

Sunday, November 24, 2013

ጾማችን ይታደስ


የዚህ ጽሑፍ ርእስ ምናልባት ሊያስቆጣ ይችል ይሆናል፤ ቢሆንም አይቈጡ! “አንብብዋ ለመልእክት እምጥንታ እስከ ተፍጻሜታ” ትርጓሜ “መልእክቲቱን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያንብቧት” የሚለውን የአበው ትክክለኛ አስተያየትም እዚህ ላይ በሥራ ላይ ያውሉ፡፡ ጥያቄው የነቢያት ጾም ለእኛ ምናችን ነው? የሚል ነው፡፡

በቤተክርስቲያናችን ከሚጾሙ ሰባት አጽዋማት አንዱ የነቢያት ጾም ነው፡፡ ጾሙ ከኅዳር 16 እስከ ታኅሣሥ 28 ድረስ ባሉት ቀናት ይጾማል፡፡ ይሁን እንጂ በሚጀመርበት ቀን ላይ ውዝግብ አለ፡፡ በ15 ነው መጀመር ያለበት የሚሉ አሉ፤ የለም በ16 ነው የሚሉም አሉ፡፡ ጾሙ ነቢያት በተለያየ ጊዜ የጾሟቸው አጽዋማት በአንድ ላይ ሆነው የሚዘከሩበት ጾም ሲሆን፣ ነቢያት በየዘመናቸው የክርስቶስን ሰው መሆን በመናፈቅ የጾሙት ጾም እንደሆነ ይነገራል፡፡ በዚህ ርእስ የጾመ ነቢይ በመጽሐፍ ቅዱስ ይኖር ይሆን? የሚለው ጥያቄ ግን መነሣት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይሁንና የነቢያቱ ጥያቄ በክርስቶስ መምጣት ተመልሷል፡፡ ታዲያ እኛ መልስ የተገኘበትን ጾም ደግመን መጾማችን ለምን ይሆን? በተመለሰው የነቢያት ጥያቄ ላይ ሌላ ጥያቄ ለማንሣት ነው ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖረን ይሆን?

Monday, November 18, 2013

መናፍቁ ማነው?


አንዳንድ ጊዜ ስም አለቦታው ይወድቃል፡፡ አለቦታቸው ወድቀው ከሚገኙ ስሞች መካከል “መናፍቅ” የሚለው ስያሜ አንዱ ነው፡፡ በሚያምኑት ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ምክንያት መናፍቃን የሆኑ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ያላቸውን ሰዎች መናፍቃን ማለታቸው እየተለመደ መጥቷል፡፡ እንዲህ የሚያደርጉትን መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉውን መልካም መልካሙን ክፉ ለሚሉ፡ ጨለማውን ብርሃን ብርሃኑንም ጨለማ ለሚያደርጉ፡ ጣፋጩን መራራ መራራውንም ጣፋጭ ለሚያደርጉ ወዮላቸው!” ይላል (ትንቢተ ኢሳይያስ 5፡20)፡፡ ይህን ብዙ ጊዜ አለቦታው ወድቆ የሚገኘውን ስም ወደቦታው መመለስ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡

“መናፍቅ” የሚለው ቃል “… የሚጠራጠር፣ የሚያጠራጥር፣ ጠርጣሪ፣ አጠራጣሪ፣ ሃይማኖቱ ሕጹጽ የሆነ፣ ምሉእና ፍጹም ትክክል ይደለ፣ መንፈቁን አምኖ መንፈቁን የሚክድ” የሚል ፍቺ እንዳለው የኪዳነ ወልድ መዝገበ ቃላት ይናገራል (ገጽ 646)፡፡ ፍቺው እንደሚያስገነዝበን እግዚአብሔር በገለጠው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ላይ የሚጠራጠርንና የሚያጠራጥርን ሰው ነው መናፍቅ ብለን መጥራት የምንችለው፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ በአብዛኛው እግዚአብሔር የገለጠውን እውነት ሳይሸራርፍ የተቀበለውና ለዚያ ጥብቅና የቆመው፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር እውነት ላይ ሰዎች የጨመሩትን የስሕተት ትምህርት ስሕተት ነው የሚለው ሰው ነው መናፍቅ እየተባለ ያለው፡፡ ይህም የሚያሳየው “መናፍቅ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ሳይሆን ሰው በመሰለው መንገድ ‘እኔ ልክ ነኝ ሌላው ግን ተሳስቷል’ ሲል እያነሣ ለሌላው የሚቀጽለው የስድብ ስም ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ይህ ቃል የአንድን ሰው መናፍቅነት በተገቢው መንገድ በማረጋገጥ የሚቀጸል ሳይሆን በጠሉት ሁሉ ላይ ቀድመው የሚለጥፉት ክፉ ስም ሆኗልና ወደ ተገቢው ስፍራ መመለስ ይገባዋል፡፡

Monday, November 11, 2013

በብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ 37ኛ መደበኛ ጉባኤውን አጠናቀቀ

  • ብጹእ አቡነ ዮሴፍን ከምክትል ጸሐፊነት አንሥቷል

በመጀመሪያው የስብሰባ ቀን በዳላስ ያልተሳካው ቀሲስ መልዓኩ ባወቀን ከጸሐፊነት የማውረድ ጅማሬ በዚህ ጉባኤ ተፈጽሟል። አስቀድሞ በእጩነት ተይዞ የነበረውን ዲያቆን አንዱዓለም ግማዊን በቀሲስ መልአኩ ቦታ ተክቷል። በእለቱ እንዲናገር እድል የተሰጠው ዲ/ አንዷለም "አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ሲኖዶስ ሥር ይገኛሉ እነርሱን ለመከላከል ጠንክሬ እሠራለሁ» በተለይም አዳዲስ የሚከፈቱ አብያተ ክርስቲያናት በጸረ ማርያሞች የተሞሉ ናቸው ብሏል።

 በሁለተኛው ቀን የታየው ቅዱስ ፓትርያርኩ ለኦክላንድ መካነ ሰላም ኢየሱስ፣ እንዲሁም በ ዋሽንግተን ዲሲ ለብጹእ አቡነ ሳሙኤል የጻፏውቸው ደብዳቤዎችና አዲስ የተገዛው የቅዱስነታቸው ቤት ጉዳይ ነው። ቅዱስ ፓትርያርኩ ለኦክላንድ ኢየሱስ እውቅና የሰጡበት ደብዳቤ፣ እንዲሁም ለብጹእ አቡነ ሳሙኤል ለፍርድ ቤት የጻፉት ምሥክርነት ጉባኤው እንዲሽራቸው ተጠይቆ በዶ/ አባ ገ/ ሥላሴ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ዶ/ አባ ገብረ ሥላሴ ፓትርያርኩ በሌሉበት የፓትርያርኩን ውሳኔ መሻር ሕገ ወጥነት ነው ብለው ተከራክረዋል። ብጹእ አቡነ መልከ ጼዴቅ ለኦክላንድ ኢየሱስ በፓትርያርኩ የተሰጠውን እውቅና ሲቃወሙ መቆየታቸው ይታወሳል።ከቤተ ክርስቲያኑ ተውክሎ የመጣው ግለ ሰብ ለምን አቡነ መለከ ጼዴቅን ትታችሁ ወደ ፓትርያርኩ ሄዳችሁ ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄ አቡነ መልከ ጼዴቅ አውግዘው ስላባረሩን ሌላ አባት ፍለጋ ሄድን እንጂ እራሰቸውን ባለማክበር አይደለም ብሏል። ለምን ይቅርታ አትጠይቁም ? ለሚለው ጥያቄ ይቅርታ መጠየቅ አይከብደንም ነገር ግን የተበደልን እኛ ነን ቀርበን እንነጋገርና በደል ከተገኘብን እናደርገዋለን የበደሉን እርሳቸው ሆነው ከተገኙ ደግሞ ይቅርታ ይጠይቁናል በማለት መልሷል። ሽማግሌዎች ነገሩን ከፍጻሜ እንዲያደርሱ ውሳኔ ተላልፏል። በተመሳሳይ መልኩ ብጹእ አቡነ ሳሙኤል እራሳቸው ካቋቋሙት ከዲሲ ቅዱስ ገብርኤል በዶ/ ነጋ መባረራቸውን በመቃወም ክስ መሥርተዋል። ዶ/ ነጋ አቡነ ሳሙኤል የገብርኤል ቤ/ክር ኀላፊ አለመሆናቸውን የሚገለጥ ደብዳቤ ከአቡነ መልከ ጼዴቅ ለፍርድ ቤት በማጻፉ ቅዱስ ፓትርያርኩ ደግሞ የአቡነ መልከ ጼዴቅን ደብዳቤ የሚሽር ሌላ ደብዳቤ ለፍርድ ቤት ጽፈው ነበር። ይህ ደብዳቤ ነው ጉባኤው እንዲሽረው ታስቦ የነበረው። ይህም በዶክተር አባ ገ/ ሥላሴ ታጋይነት ሳይሆን ቀርቷል። በአባ ጽጌ ደገፋው የቀረበው ሪፖርት ፓትርያርኩ እኛ ሳናውቅ ከአትላንታ ወደ ዲሲ ለምን ተወሰዱ ? የማያገባቸው ሰዎች ቤቱን ሊያዝዙበት አይችሉም የሚል ሐሳብ ያለው ነበር። ፓትርያርኩ እየታመሙ ስለሆነ ባስቸኳይ እረፍት እንዲያገኙና ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ ሲባል በቤተ ሰባቸው አማካኝነት በክብር ወደ ቤታቸው ገብተዋል። ይህም የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስቆጣ መሆን የለበትም የሚል ምላሽ ተሰጥቶበታል።

Friday, November 8, 2013

በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ በኮሎምቦስ ኦሀዮ በሚገኘው መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

በብፁዕ ወቅደስ አቡነ መርቆርዮስ የሚመራው ስደተኛው ቅዱስ ሲኖድስ 37ኛውን መደበኛ ጉባኤ ምክንያት በማድረግ ጥቅምት 27/ 2006 ዓ.ም በኮሎምቦስ ኦሀዮ በሚገኘው መዴኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እየተካሄደ ነው።  ቅዱስ ፓትሪያርኩ በህመም ምክንያት በስብሰባው ላይ ያልተገኙ ሲሆን የሲኖዶሱን ምክትል ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍን ጨምሮ በርካታ ካህናትም አልተገኙም።  ምንጮቻችን እንደጠቆሙን በስብሰባው ላይ ካልተገኙት የሲኖዶሱ ሰባክያንና ካህናት መካከል  ሰባኬ ውንጌል አባ ወልደ ትንሳኤ፥ አባ ሃብተ ማርያም፥ ቀሲስ መልአኩ ባወቀ፥ ቀሲስ ጌታቸው፥ ቀሲስ እንዳልካቸው፣ መምህር ተከስተ ጫኔ እና ቀሲስ አንዱዓለም ይገኙበታል።

በስብሰባው ላይ ከተከናወኑና ከደረሱን ዜናዎች መካከል፦
  • የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጸሐፊ  ቀሲስ መላኩ በዲያቆን አንዱአለም ግማዊ እንዲተካ ተደርጓል።  ምክንያቱ ምን እንደሆነ የደረሰን መረጃ የለም
  • ዲያቆን አንዱአለም መምህር ተከስተ ጫኔን  ለስዕል አይሰገድም ይላል በማለት እንዲወገዝለት ክስ አቅርቧል። የደረሰን መረጃ እንደጠቆመው ዲያቆን አንዱዓለም  ክሱን በልቅሶ በማጀብ ከማቅረብ በተረፈ መረጃ ተጠይቆ ግን ለማቅረብ አልቻለም።  ሆኖም ግን ብጹዕ አቡነ ዮሐንስ፤ ብጹዕ አቡነ መልከጼዴቅ፤ እና ሌሎችም አባቶች  መምህር ተከስተ ላይ የአስተምህሮ እንከን አይተውበት እንደማያውቁ መስክረዋል።  የአንዱዓለም ክስ በዳላስ በቅርቡ ከተከፈተው የፈለገ ህይወት ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። የኢየሱስን ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶሱ ስር ለማካተት ውይይት የነበረ ሲሆን ዲያቆን አንዱዓለም ግን ቤተ ክርስቲያኑ በሲኖዶሱ ስር የሚካተት ከሆነ የዳላስ ሚካኤልን ከስደተኛው ሲኖዶስ ስር ሊያስወጣው እንደሚችል ፎክሯል።  

ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎችን እንደደረሱን እናቀርባለን።


Thursday, November 7, 2013

ማኅበረ ቅዱሳንንና አባ እስጢፋኖስን ምን አፋቀራቸው


ማኅበረ ቅዱሳን በቤተክርስቲያን ስም የሚነግድ ስብስብ እንጂ ለቤተክርስቲያን የሚያስብ አለመሆኑን ከዚህ ቀደም በማስረጃ ላይ ተመሥርተው በቀረቡ የተለያዩ ጽሑፎች ተመልክቷል፡፡ ዛሬም ቢሆን ማኅበሩ ጥቅሙ እስካልተነካበት ወይም እስከ ተጠበቀለት ድረስ ዐመፅን ጽድቅ፣ ጽድቅን ዐመፅ፣ እውነትን ሐሰት ሐሰትን እውነት፣ ሌባውን ታማኝ ታማኙን ሌባ ከማለት አይመለስም፤ ይህን በተግባር እያስመሰከረም ነው፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ አባ እስጢፋ በተለይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጰስ ሆነው ከተሾሙ በኋላ እያደረሱ ያለውን አስተዳደራዊ በደልና እያስፋፉ ያለውን ሙስና ከመኮነን ይልቅ በማበረታታቱ ሥራ መጠመዱ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ማኅበሩ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ከእርሳቸው ጋር በፍቅር የወደቀበት የፍቅር ጊዜው በመሆኑ ነው፡፡

እርግጥ ቤተክህነት ውስጥ በጥቅም የሚለካ እንጂ እውነተኛም ዘላቂም የሚባል ፍቅር እንደሌለ ከማንም ስውር አይደለም፡፡ አባ እስጢፋኖስና ማቅ በፍቅር እፍ ያሉትም ማቅ አገር ያወቀውንና ፀሐይ የሞቀውን የአባ እስጢፋኖስን ገበና ሊሸፍን፣ እርሳቸውም በበኩላቸው ማቅ ዘወትር የሚያልመውን ቤተክርስቲያንን የመቆጣጠር ህልሙን በማሳካቱ ሂደት ሊረዱትና በቤተክርስቲያን ውስጥ ጥቅሙ እንዲከበርለት ሊያደርጉለት “በዓይን ቋንቋ” ዓይነት ስለተግባቡ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በቤተክህነት ታሪክ ባልተለመደ መልኩ የማቅ ሰዎች ካህናቱን አሰልጣኞች ሆነው የተሰየሙበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ከዚህ ባለፈም ማቅ ቤተክርስቲያንን እንዳሻው ለማድረግ እንዲያመቸው “የለውጥ አመራር መዋቅር፣ አደረጃጀትና ዝርዝር አሠራር ጥናት” ወዘተርፈ በሚሉ ከንግግር ባላለፉ መደለያዎች እርሱ ቤተክርስቲያኒቱን በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ በቁጥጥሩ ስር የሚያውልበትን በር ወለል አድርገው ከፍተውለታል፡፡ ከዚህ የተነሣ ማቅ ለአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ካህናት በለውጥ ስም መተዳደሪያ ደንብ እስከማርቀቅና በየአድባራቱ እንዲሠራጭ እስከማድረግ ያደረገ ሲሆን፣ ይህም የብዙዎችን ቁጣ በከፍተኛ ደረጃ መቀስቀሱ ታውቋል፡፡

Sunday, November 3, 2013

በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ማኅበረ ቅዱሳን እንዲፈርስ የቀረበው ሐሣብ ማቅን አሸብሮ “እንሠዋለታለን” ባሉ ጳጳሳት ትግል ለጊዜው መቀልበሱ ታወቀ
የዘንድሮው የጥቅምት ሲኖዶስ ስብሰባ ጥር 21/2006 ተጠናቀቀ፡፡ የስብሰባው አንዱ መነጋገሪያ የነበረው ከ32ኛው የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ጀምሮ እያነጋገረ የነበረው የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ ሲሆን፣ በስብሰባው ሁለተኛ ቀን ውሎ ፓትርያርክ ማትያስ “እስካሁን ከየአቅጣጫው የሚሰማውና የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያን ከሚጠቅመው ይልቅ የሚጎዳው ነገር እየበዛ መጥቷልና መፍረስ አለበት፡፡ ስለዚህ ይህ ጉባኤ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ አንድ ውሳኔ ማሳለፍ ይኖርበታል” የሚል ሐሳብ አቅርበው የነበረ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ይህን ያልተጠበቀ የፓትርያርኩን ሐሳብ የሠሙ የማቅ ደጋፊ የሆኑ አንዳንድ ጳጳሳት የፓትርያርኩን ሐሳብ በመቃወም ማኅበረ ቅዱሳን ሊፈርስ አይገባውም ሲሉ መከራከራቸውም ተደምጧል፡፡ ከእነዚህም መካከል አባ ቀውስጦስ “ማቅ በፍጹም አይፈርስም እንሠዋለን” ማለታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ ለነገሩ አባ ቀውስጦስ በማቅ ግፊት የቤተክርስቲያን ልጆች ሳይጠየቁ እንዲወገዙ በተደረገበት የግንቦት 15ቱ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ “ካልተወገዙ ለሃይማኖቴ እሠዋለሁ” ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አሁንም “ስለማቅ እሠዋለሁ” ማለታቸው መሥዋዕትነትን ዝቅ አድርገው የሚመለከቱ “አባት” መሆናቸውን ያስመሰከረ ክስተት ሆኗል፡፡