Wednesday, January 29, 2014

የዘንድሮ ጥምቀት በሎስ አንጀለስ

Read in PDF
የዘንድሮ የጥምቀት በዓል በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅነት የተካሄደ ሲሆን አዳዲስ እና እንግዳ ነገሮች ተከስተዋል። የሎስ አንጀለስ የጥምቀት በዓልን በመላው ዓለም የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ሁሉ ልዩ የሚያደርገው የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት አይደለም። በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ትላልቅ የወንጌል ሰዎች በመፈራረቅ የእግዚአሔርን መንግሥት ምሥጢር የሚገልጡበት በመደማመጥና በአንድነት መፈሳዊ ዝማሬዎች እንደ ውሃ የሚፈሱበት፣ የእግዚአብሔር ክብር በግልጥ የሚታይበት በዓል ነው። ጥምቀት መከበር ካለበት እንደ ሎስ አንጀለስ ነው። በካልፎርኒያ አካባቢ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የፕሮቴስታንት እምነት አባላት ሳይቀሩ ወንጌልን ለመስማት ከሩቅ የሚመጡበት ነው። ወንጌል በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ ሲሰበክ በታሪክ አይታወቅም ሊቃነ ጳጳሳት ሊቃውንትና ካህናት ሰባክያን ጭምር ቁጭ ብለው ወንጌል የሚማሩበት ጊዜ ቢኖር የሎስ አንጀለስ ጥምቀት ነው። ሕዝቡ የዓመት ቀለቡን እንደሚሰበስብ ገበሬ መንፈሳዊ እና መለኮታዊ ምሥጢራትን ሰብስቦ ወደ ቤቱ የሚገባበት ጉባኤ ነው። ጥምቀት በሎስ አንጀለስ ከባሕላዊ እሴትነቱ ይልቅ የመዳን ምሥጢር በሰፊው የሚገለጥበት የደከመው በርትቶ የተጠራጠረው አምኖ ያላወቀው ንስሐ ገብቶ የተጣላው ታርቆ የሚመለስበት ልዩ በዓል ነው። የታደለም ሚስት ወይም ባል ሊያገኝ ይችላል።
  ይህን በዓል መንፈሳዊ ውበት እንዲጎናጸፍ ያደረጉት ግን ታሪክ የማይረሳቸው የቅድስት ማርያም እና የድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ናቸው የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን ሁሉም ባይሆኑም የክርስቶስን ምሥጢር የተረዱና በእግዚአብሔር የተደሰቱ ናቸው። ካሊፎርኒያዎቹ  በእግዚአብሔር ሥራ የሚደነቁ በወንጌል ጉዳይ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ጤነኛ ኢትዮጵያውያን ናቸው።

Tuesday, January 28, 2014

ሰራተኞችን በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር አባ እስጢፋኖስና ሰራተኞቻቸው የጀመሩት ቢዝነስ በፓትርያርኩ ደብዳቤ ተስተጓጎለ

F አቡነ እስጢፋኖስን ይቃወማሉ የተባሉ አስተዳዳሪዎችን በዝውውር ስም ከደረጃ ዝቅ ለማድረግ የታሰበው እቅድ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት በተጻፈ ደብዳቤ ታደገ፡፡
F  አቡነ እስጢፋኖስ በኩርፊያ ወደ ጅማ ሄደዋል፡፡
F እስከ ዛሬ ሐራን በመሰሉ ስውር ብሎጎቹ ብቻ ‹‹መዋቅራዊ ነውጥ›› ብሎ የሰየመውን የትርምስ እስትራቴጂ ሲደግፍ የቆየው ማኅበረ ቅዱሳን ከደረሰበት ኪሳራ ለመውጣት በመደበኛ ድረ ገጹ እቅዱ እንዲጸድቅ ቅስቀሳውን ቀጥሏል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥልጣን ቆንጥጦ ለመያዝ ካለው ጽኑ ፍላጎት አንጻር በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተግባራዊ ለማድረግ የቋመጠለትንና ሥልጣኑን በሙሉ ከካህናት ነጥቆ ለማኅበሩ ደጋፊ እና አባል ምእመናን የሚሰጠውንና ካህናቱ እንደ ግል ድርጅት ሰራተኛ በቤተክርስቲያናቸው አንዳችም የጎላ ድርሻ ተግባር (ከመቀደስ ከማወደስ ውጪ) እንዳይኖራቸው የሚያደርገውን ‹‹መዋቅራዊ ነውጥ›› በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኙ አስተዳዳሪዎች ልዩ ልዩ ሰራተኞችና ካህናት በመቃወማቸው ምክንያት በተነሳው ተቃውሞ ዕቅዱ አካሄዱን ያልጠበቀ ሕግ አርቃቂው ክፍልም በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ ያላገኛና ቤተክርስቲያኒቱን ለአንድ ነጋዴ ማኅበር አሳልፎ የሚሰጥ በመሆኑ ታግዶ በሊቃውንት ሁሉን ያማከለና ከቤተክርስቲያኗ ሕጎችና መመሪያዎች ጋር የተዛመደ ጥናት እንዲቀርብ በቋሚ ሲኖዶስ መመሪያ ከተሰጠ በኋላ የእቅዱ መክሸፍ ያሳሰባቸው አቡነ እስጢፋኖስና የማኅበሩ ስውር አንቀሳቃሾች በፓትርያርኩ እና በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ላይ ግፊት ለማድረግ የተለያዩ ስብሰባዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በሰሜን አሜሪካ ያለው ሲኖዶስ ደጋፊ አስተዳዳሪዎችና ምክትል ሊቃነ መናብርቶቻቸውን አስቀድመው ወደ ጠቅላይ ቤተክህነቱ ቢልኩም አንዳች ጠብ ያለ ነገር አላገኙም በዚህ መዋቅራዊ ለውጥ ዋና አስተባባሪ የአፍሪካ ኅብረቱ የሕንጻ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የነበረውና ቤተክርስቲያን ውስጥ ከቀድሞዋ ሒሳብ ሹም ወ/ሮ ምንጭቱ ጋር በመሴሰን ተይዞ የተባረረው  ሙሰኛውና ጎሰኛው  ጌታቸው ደግፌ፤ ወጂ መድኃኔ ዓለም አለቃ ፤ በቅርቡ ከእስልምና ሃይማኖት ተመልሶ በአንድ ዓመት የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ  ሰበካ ጉባዔ ምክትል ሊቀ መንበር የሆነውና ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ በሥርዓተ ቁርባን ላይ ጭምር ከህናትን የሚሳደበው አቶ አበበ ይማም የሚቻላቸውን ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም፡፡ ማኅበሩ በአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ስም ያደራጃቸውንና ዩኒፎርም በማልበስ ለዓላመው ማስፈጸሚያነት የሚገለገልባቸውን ስውር አባላት ወደ መንበረ ፓትርያርኩ በመላክ አንዳች ውጤት ጠብቆ ነበር፡፡ ይሁንና በሀገረ ስብከቱ ካሉ ሰንበት ትምህርት ቤት ያልተወከሉና ማኅበሩ አባል የሆኑ ጥቂት ወጣቶችም የተሰጣቸውን የአቡነ እስጢፋኖስን ሥልጣን የማስቀጠል እና የማኅበሩን መዋቅር የማጸደቅ ተግባር በብቃት መወጣት ባለመቻላቸው አቡነ እስጢፋኖስ ተስፋ ወደ መቁረጡ አዘንብለዋል፡፡

Sunday, January 26, 2014

የግንቦት 15ቱ ውግዘት መነሻ፣ ሂደት፣ ፍጻሜና ቀጣዩ ሲገመገም ክፍል 16

Read in PDF

የግንቦት 15/2004 ዓ.ም «ውግዘት»ን በተመለከተ ኑፋቄ ተብለው በተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የተላለፈውን ሕገወጥ ውግዘት በተመከለተ በአዋልድ መጻሕፍትና በልማዳዊ ትምህርት ሲመዘኑ ኑፋቄ ተብለው የተወገዙትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶች ከዚህ በፊት በ15 ክፍሎች ማቅረባችን የሚታወስ ነው፡፡ በ“የእውነት ቃል አገልግሎት” ላይ የቀረቡትንና ኑፋቄ የተባሉትን ነጥቦችን መመልከት እንቀጥላለንና ይከተሉን፡፡ 16ኛው ክፍል ይኸው፣

“ሐ. በዓለመ ሙታን የሚገኙ ነፍሳትን መጥራት በእግዚአብሔር ቃል በእጅጉ የተወገዘ የባዕድ አምልኮ ድርጊት ነው” በማለት በአጸደ ነፍስ የሚማልዱ ቅዱሳንን ይተቻል፡፡ መጽሐፈ ሰዓታት በመቅደሱ ሚዛን ገጽ 33፡፡”

ከሊቃውንት ጉባኤ የማይጠበቅ ትልቅ ስሕተት! ለእውነት ሳይሆን ለተረት የቆመ መከላከያ! እውነትን ለሐሰት የሰዋ ትልቅ ድፍረት! ለሃይማኖት ዋና መሰረት የሆኑትን ብሉያትና ሐዲሳት ወደጎን ብሎ ልማደ አሕዛብን መከተል! የስህተት ትምህርትን በመደገፍ መጽሐፍ ቅዱስን ኑፋቄ ያደረገ አሳፋሪ ምላሽ! ለአምልኮተ እግዚአብሔር ደንታ ቢስ የሆነና ለአምልኮተ ባዕድ መስፋፋት ቀኝ እጁን የሰጠ ዳኝነት! 

Thursday, January 23, 2014

ለቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች እቆረቆራለሁ የሚለው ማኅበረ ቅዱሳን ሊቃነ ጳጳሳቱን በስድብና ስም በማጥፋት ዘመቻው ቀጥሎበታል፡፡

አበረ ከምስራቅ ኢትዮጵያ
ስሟን ቄስ ይጥራውና በቅርቡ የተከፈተችውን አንዲት የሐራ ተዋህዶ  እህት የሆነች የማቅ አዲስ ብሎግ  ሰሞኑን ስጎበኛት እስከ አሁን ያወጣቻቸው ጽሑፎች ከሐራ ተዋህዶ የተወሰዱ ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡ አንድ በሐራ ያልተጻፈ አዲስ ጽሑፍ ግን አነበብኩኝ እርሱም የማህበረ ቅዱሳን ራስ ምታት የሆነው የምስራቁ የሐገራችን ክፍል እጅግ በሚደንቅና በእግዚአብሔር አጋዥነት የማህበሩ ህዋስ ከእያንዳንዱ የቤተክርስቲያን መዋቅር ተነቃቅሎ በመውጣቱ ለመጨረሻ ግዜ ያገለግለኛል ብሎ ያስቀመጠውን ጥይት እየተኮሰ እንደሆነ ከዚህችው ብሎግ ላይ ለማንበብ ችያለሁ፡፡ ማህበሩ በእውነት መከራከርና ማሸነፍ ሲያቅተው በመጨረሻ የሚያደርገው ስድብና ስም ማጥፋት እንደሆነ ከዚህ በፊት ሲያሳይ ከነበረው ባህርዩ መረዳት ይቻላል፡፡ ሲሳደብና ስም ሲያጠፋ ደግሞ ማንንም አይፈራም፤ ማንንም አያከብርም፤ ከልምድ አቡነ ጳውሎስንም ከዚህ በፊት ሲሳደብ ሰምተነዋል፡፡

በምስራቅ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከዛሬ 19 አመት በፊት በድሬደዋ፣ በሐረር፣ በጅጅጋና በአሰበ ተፈሪ በቤተ ክርስቲያን በተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎት ስር ይሳተፉ በነበሩ ወጣቶች ላይ የፈጸማቸው ግፎች ቀን ቆጥረው በራሱ ላይ መጥተዉበት፣ ለረጅም አመታት ተደላድዬ ሁሉን አሸንፌ ተቆጣጥሬዋለሁ ካለው የተለያየ የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ተጠራርጎ በመውጣቱ፣ ከዚህ በፊት ሲያደርግ የነበረውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በማህበራትና በግለሰቦች እንዲሁም በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ የመጨረሻ ዱላውን በምእራብ ሐረርጌና ድሬደዋ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዕንባቆም  ላይ አዙሮአል፡፡

Monday, January 20, 2014

“ተአምረ ወመንክረ ገብረ መድኃኒነ በቃና ዘገሊላ” መድኃኒታችን በቃና ዘገሊላ ተአምርንና ድንቅን አደረገ

በየዓመቱ ጥር 12 ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ወር በገባ በ12 በዓለ ሚካኤል ነው ተብሎ ስለተወሰደ፣ በተጨማሪም ለጥምቀት በዓል ጥር 10 የወጣው የሚካኤል ታቦት ወደቦታው የሚመለሰው በ12 ስለሆነ በዓሉ የሚካኤል በዓል የሚመስላቸውም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ከዚህ ባሻገር በዓሉ ጌታ ውሃውን ወደወይን የለወጠበትና ክብሩን የገለጸበት ቢሆንም የጌታን ሳይሆን የማርያም አማላጅነት የታየበት ነው በማለት ተአምር ሰሪውን ጌታ ሳይሆን የማርያምን አማላጅነት ማጉላት የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በዓሉ ጌታችንና መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከተጠመቀና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ከተመሰከረለት በኋላ ያደረገውና ክብሩን የገለጸበት የመጀመሪያው ተአምር ነው፡፡

በቃና ዘገሊላ በተደረገው በመጀመሪያው ተአምር ምን ሆነ? በቃና ዘገሊላው ሰርግ ላይ የኢየሱስ እናት በዚያ እንደ ነበረችና ኢየሱስና ደቀመዛሙርቱ ጋር ወደ ሰርጉ እንደታደሙ ዮሐ. 1፥1-2 ይናገራል፡፡ የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም ስትል ለጌታ ነገረችው፡፡ እርሱም “አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት።”   ይህ አነጋገር የአክብሮትም የአርኅቆትም አነጋገር ነው፡፡ ልብ እንበል እናቱን “አንቺ ሴት” በማለት አክብሮ የጠራት ቢሆንም “እናቴ ሆይ” በማለት ፈንታ የሩቅን ሰው እንደሚያናግር “አንቺ ሴት” በማለቱ ደግሞ የሩቅ ሰው አድርጎ ነው ያናገራት፡፡ “አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” ሲል የተናገረውም፥ በውስጡ “ምን አድርግ ትይኛለሽ?” የሚል መልእክት አዝሏል፡፡ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” የሚለው ምክንያትም መልእክቱ ያዘለውን ሐሳብ ይበልጥ ያጎላል፡፡ ሆኖም ምላሹ አዎንታዊ በመሆኑ “እናቱም ለአገልጋዮቹ፦ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው።” ኢየሱስም በዚያ የነበሩትን ስድስት የድንጋይ ጋኖች በውሃ እንዲሞሉአቸው አዘዘና ሞሉአቸው፡፡ ከዚያ ለአሳዳሪው ቀድታችሁ ስጡት አለ፡፡ “አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ። ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።”

Thursday, January 16, 2014

ድርብ ታቦት

Read in PDF

ድርብ ታቦት ምንድን ነው?

 ታቦት ማለት ጽላት የሚቀመጥበት ሳጥን ማለት ነው ጥሬ ትርጉሙ ማደሪያ የሚል ነው የጽላት ማደሪያ ስለሆነ ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል። መጽሐፍ ቅዱስ ታቦት የሚለው ምን ዓይነት እንደሆነ ዘጸ. 25፥10-22 የተጻፈውን መረጃ በማድረግ ምስሉን ጨምር እናሳያችሁ። ከላይ በጠቀስነው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ታቦት ከግራር እንጨት የሚሠራና በወርቅ የተለበጠ ትልቅ እቃ ነው።


https://encrypted-tbn2.gstatic.com/images?q=tbn:ANd9GcTvmdt3aS0Csf25IwthLWECPgM04BLebfRA3CFFlEspjZ6EyxUIeA
1. ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣
  ቁመቱ አንድ ክንድ ተኩል፣
  ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል ነው።
  ታቦቱ አንድ ብቻ ነው

2. በውስጥና በውጭ በወርቅ የተለበጠ፣
   ዙሪያውን የወርቅ አክሊል ያለው፣
   አራት እግሮች ያሉት
   አራት ቀለበቶች ያሉት
   ሁለት መሎጊያዎች(መሸከሚያዎች)ያሉት ነው።

Wednesday, January 15, 2014

ግልጽ አደጋ በሎስ አንጀለስ አብያተ ክርስቲያናት

ምንጭ፦ www.ethiofreedom.com

ተከባብረውና አብረው በመስራት ብዙ አገልግሎት በሎስ አንጀለስ አካባቢ ላለው ምዕመን በመስጠታቸው የሚታወቁት ሁለቱ የድንግል እና ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት ጥሩ ወዳልሆነ ግጭት ውስጥ እየገቡ እንደሆነ የሚጠቁም መልእክት። በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት የሚገለገሉ ምዕመናን የክፍፍልን እና የጥልን ሀሰብ እምቢ ሊሉ ይገባል።

ሙሉውን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ 

Monday, January 13, 2014

‹‹ተሐድሶ በቤተ ክርስቲያናችን የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው››


ምንጭ፡- ተሐድሶ ብሎግ

እግዚአብሔር ፍጥረታቱን በተሐድሶ በሕይወት የሚያኖር አምላክ ነው፡፡ ተሐድሶ እግዚአብሔር ከምሕረቱ የተነሣ፣ ከጥንተ ተፈጥሮው የሳተውን ወደ ፈቃዱ የሚመልስበት፣ በሕይወት የሚያኖርበት፣ ከጥፋት የሚያድንበት የበጎነቱ ሥራ ነው፡፡

        በእግዚአብሔር የመታደስ ዕድል ከሚሰጣቸው መካከል አንዷ በምድር ያለችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን በክቡር የክርስቶስ ደም የተዋጀች፣ የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጥ የሕይወት ልክ የተሰጣት፣ የሕያው አምላክ፣ የጻድቅነቱ የቅድስናውና የክብሩ መገለጫ እንደራሴው ናት፡፡

        ቤተ ክርስቲያን ከጌታ ከተሰጣት የእምነትና የሕይወት መንገድ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ስትስት ወደ ራሱና ወደ ፈቃዱ ሊመልሳት ከፍቅሩ የተነሣ የመታደስን ዕድል ይሰጣታል፡፡

        ይህን ሰማያዊ የመታደስ በረከት እንዲያገኙ በአምላክ ልብ ቀድሞውኑ ከታሰቡት አብያተ ክርስቲያናትም መካከል አንዷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ በዓለም ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ቀድሞ ለተሐድሶ የአምላኳ ጥሪ የደረሳት ናት፡፡ የእግዚአብሔርን ጥሪ የተቀበሉ አገልጋዮቿና ምእመናን በቅዱስ ቃሉና በቅዱስ መንፈሱ ራሳቸውን እየመረመሩ በንስሓ ወደ እግዚአብሔር በመመለስ የሕይወት መታደስን አግኝተዋል፡፡ እስከ ዘመናችንም ድረስ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመታደስ ሂደት ላይ ናት፡፡

Friday, January 10, 2014

በምዕራብ ሐረርጌ አሰበ ተፈሪ ቅድስት ልደታ ለማርያምና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን የመጨረሻ ምሽጉን (ቶራቦራን) ለቀቀ


በምሥራቅ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ግፍ በቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ ሲፈጽም የኖረው ማኅበረ ቅዱሳን በአሁን ጊዜ በምሥራቅ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ወሳኝ ወሳኝ የሆኑ ምሽጎቹን እያጣ ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ በምዕራብ ሐረርጌ አሰበ ተፈሪ ከፍተኛ ምሽግ አድርጎት የነበረው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሀገረ ስብከቱ ሲሆን፣ በተለይ አሁን ያሉት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ብርሃናት ከሃሊ በቃሉ ከመጡ በኋላ በሀገረ ስብከቱ የነበረውን ቦታና ተሰሚነት በሙሉ አጥቶ ምሽጉን ነቅሎ ወጥቷል፡፡ ከፍተኛ ምሽጉ አድርጓቸው የነበሩት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ,  በተጨማሪም ስብከተ ወንጌልና የሰንበት ትምህርት ቤት ሲሆኑ፣ ከዚህ በፊት እንደ ገለጽነው የስብከተ ወንጌል ክፍሉን አጥቷል፡፡ የሰበካ ጉባኤውን መዋቅር በከፍተኛ የምእመናን ትብብር የሀገረ ስብከቱ ጥንካሬና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጰጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆም ቆራጥ አመራር ለማህበረ ካህናቱና ለምእመናኑ እድል በመስጠቱ ሥልጣኑን ላለማጣት በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ቢፍጨረጨርም፣ በታላቅ ምት ስልጣኑን አስረክቦ በታሪክ ከ20 ዓመት በኋላ ማህበረ ካህናቱና ማህበረ ምእመናኑ የሰበካ ጉባኤ አመራር ቦታን ሊቆጣጠሩ ችለዋል፡፡

በደረሰበት ከፍተኛ ምት አፈግፍጎ የነበረው ማህበረ ቅዱሳን አባላቱን በከፍተኛ ሁኔታ ያመርትበት የነበረውን ምሽጉን ፈለገ ቅዱሳን ብሎ በሰየመው ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ አድርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከዚሁ ምሽጉ እየተነሳ የሰበካ ጉባኤውንም ሆነ ስብከተ ወንጌሉን ምርጫ ያውክ የነበረው ይሄው የፈሪሳዊያን ጥርቅም ማህበር፣ ወሳኝና ልክ እንደ ቢላደን ምሽግ ቶራ ቦራ ይመካበት የነበረው ምሽጉ ሰንበት ትምህርት ቤት አዲስ በተመረጠው ሰበካ ጉባኤና የሀገረ ስብከቱ ቆራጥ አመራር ተመቶ ሊለቅ ችሎአል፡፡

Wednesday, January 8, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሌሎች ሠራተኞች የደረሰበትን ሽንፈት ለማወራረድ ቅጥረኞቹን ሊሰበስብ ነው

የአባ እስጢፋ የልጆች አባትነት በሕይወት እያሉ በዲኤንኤ ምርመራ እንዲረጋገጥ ይጠይቃሉ

ማኅበረ ቅዱሳን ከአባ እስጢፋ ጋር ተመሳጥሮ ያረቀቀውና በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት የሚገኙ አስተዳዳሪዎች ጸሐፊዎችና ሌሎች ሠራተኞች መቃወማቸውንና በትግላቸውም ሕጉን ለማርቀቅ ሊቃውንት ያሉበት ሌላ ሕግ አርቃቂ ኮሚቴ እንዲሰየም ማድረጋቸውን ለመቃወምና ሕጉ እንዲጸድቅ ለማድረግ ካህናቱን በመቃወም የድጋፍ መግለጫ ስብሰባዎችን እያደረጃ መሆኑ ተሰማ፡፡ የማኅበሩ “ስውር” ብሎግ ሐራ እንደዘገበችው የድጋፍ መግለጫ ስብሰባው በሦስት ምዕራፍ የተከፈለ ሲሆን ለማቅ ያደሩና በገንዘብ የተገዙ አንዳንድ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ የአብነት መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤያት ሊቃነ መናብርትና ምእመናን በሁለተኛው ምዕራፍ፣ ሰንበት /ቤቶች ደግሞ በሦስተኛው ምዕራፍ የፊታችን አርብ ለስብሰባ እንደሚወጡ ዘግቧል፡፡ ይሁን እንጂ እንደከዚህ ቀደሙ የጠቀሳቸውን ሰዎች ሳይሆን ለስብሰባ የገዛቸውን ዩኒፎርም አልብሶ እንዳያመጣ የብዙዎች ጥርጣሬ አለ፡፡ የልደት በዓልንም በቤተ ክርስቲያኑ ባሰማራቸው ሰላዮቹ በኩል ለአርቡ ረብሻ እንዲዶልቱበት ማድረጉን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

ማቅ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉና በአባልነት የመለመላቸው እንዲሁም ቅጥረኞቹ ያደረጋቸውን የደኅንነት አባላት ጭምር ለዚህ ወሳኝ ተግባር ያሰማራ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በአቡነ ጳውሎስ ጊዜ እንኳን ማኅበረ ቅዱሳን በአንድ የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ የደገሰውን ድግስ አንበላም በማለት ፊት ለፊት እየተናገሩ ከአዳራሹ የወጡትን አንዳንድ አባቶችን ሚሊቴሪ በለበሱና ጠብመንጃ በያዙ የማቅ አባላትና ቅጥረኞች ይዞ ማስደብደቡ ማቅ በደኅንነት አባላት ውስጥ ምልምሎች እንዳሉት ማመላከቻ ሆኖ አልፏል፡፡ አሁንም በዚህ ግርግር ለመፍጠር ባሰበበት የአርቡ ስብሰባ እነዚህን በመንግስት መዋቅር ውስጥ በሚገኙና በመለመላቸው የደኅንነት አባላቱና ቅጥረኞቹ አማካይነት ሥራውን ለመሥራት እንዳሰበ እየተነገረ ነው፡፡

Monday, January 6, 2014

መንፈሳዊ መልእክት


እንኳን ለበዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!
“እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።”
(ሉቃ. 2፥10-11)
ጌታችንና አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በተወለደባት በዚያች ሌሊት መንጋቸውን ይጠብቁ ለነበሩ እረኞች የጌታ መልአክ የተናገረው የምሥራች ነው፡፡ የምሥራቹ በጊዜው ለእረኞቹ የተነገረ ቢሆንም መልእክቱ ግን በእረኞቹ ብቻ የሚወሰንና እነርሱን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ የምሥራቹ “ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች” ተብሏልና ለሰው ዘር ሁሉ የሆነ ታላቅ ደስታና የምሥራች ነው፡፡ የጌታ መወለድ ታላቅ ደስታና የምሥራች የሆነበት ዋናው ምክንያት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ኢየሱስ የዓለም መድኀኒት፣ እንዲሁም ይመጣል ተብሎ በነቢያት ትንቢት የተነገረለት መሲሕ (ክርስቶስ)መሆኑ ነው፡፡

ዛሬ የልደቱን መታሰቢያ የምንዘክረው መድኀኒት ክርስቶስ በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ከዛሬ 2006 ዓመት በፊት ተወልዷል፡፡ ልደቱን ስናስብ በዋናነት ማተኮር ያለብን ግን በተወለደ ጊዜ የሆነውን ያለፈውን ድርጊት ብቻ ሳይሆን የተወለደበትን ዓላማ ጭምር ሊሆን ይገባዋል፡፡ የተወለደው መድኀኒት ክርስቶስ ነው፡፡ እንዲህም ስንል መድኀኒትነቱ፦ በኃጢአት በሽታ ለታመምንና በሥጋ ሞት ከዚህ ዓለም ሳንለይ መድኀኒቱን  ካላገኘን ዘላለማዊ ሞት ለሚጠብቀን ለእኛ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ  የሚበልጥ ምን ደስታና የምሥራች አለ?

Saturday, January 4, 2014

የማቅ የለውጥ መዋቅር በአዲስ አበባ ሀገረስብከት አስተዳዳሪዎችና ሌሎች አገልጋዮች ትግል መቀልበሱ የተበሠረበት ስብሰባ ዝርዝር እነሆ


·        አባ እስጢፋኖስ እስከ ልደት ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስነት እንዲወርዱ ተጠየቀ
·        የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች ታላቁን ሊቅ አቡነ መርሐ ክርስቶስን ተሐድሶ ያሉ ደፋሮች ናቸው!
·        በማቅ የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ ውድቅ ሆኖ በሊቃውንት ሌላ ሕግ እንዲዘጋጅ ተብሏል
·        የማቅ አባላት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሕንጻ እንዲለቁ ተጠየቀ
·        “ማቅ የስም አባል እንጂ የቤተክርስቲያን አካል” አይደለም ተባለ
·        ማቅ “እንደ ክብሪት ከጐን ወጥቶ እሳት የሚለኩስ ማህበር ነው፡፡”

ማኅበረ ቅዱሳን ያረቀቀውና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ባለ በሌለ ኀይሉ ሲንቀሳቀስበት የቆየው የለውጥ መዋቅር በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳዳሪዎችና ሌሎች አገልጋዮች የተደራጀ ትግል መቀልበሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለተሰብሳቢዎቹ እንዳስታወቁት ባለፈው ቀርበው አቤቱታቸውን ባሰሙ ማግሥት ቋሚ ሲኖዶስ ተሰብብስቦ ማኅበረ ቅዱሳን ያረቀቀው የለውጥ መዋቅር ውድቅ እንዲደረግና የማኅበሩ አባላት ቀርቶ ከማኅበሩ ጋር ምንም ንክኪ የሌላቸው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ አባቶችና ምሁራን በድምሩ 9 አባላቱ ያሉበት ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ የተሠየመ መሆኑን አብሥረዋል፡፡ አክለውም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብቻ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያኗ በአጠቃላይ የሚሠራ ህግ ነው መውጣት ያለበት ብለዋል፡፡ ለተሠየሙት አባላትም ከጠቅላይ ቤተክህነት ደብዳቤ የደረሳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ ብሥራት በተሰማበት ዕለት በፓትርያርኩና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፊት ቀርበው አስተያየት እንዲሰጡ የተደረጉት የካህናቱ ተወካዮች ያለአንዳች መሸማቀቅና ያለፍርሀት በመረጃ ላይ የተመሠረቱ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል፡፡

Thursday, January 2, 2014

ሰበር ዜና፦ የማቅ የለውጥ መዋቅር በአዲስ አበባ ሀገረስብከት አስተዳዳሪዎችና ሌሎች አገልጋዮች ትግል ተቀለበሰ፤

አባ እስጢፋኖስ እስከ ልደት ከሀገረስብከቱ ሊቀጳጳስነት እንዲወርዱ ተጠየቀ

ማኅበረ ቅዱሳን ያረቀቀውና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ባለ በሌለ ኀይሉ ሲንቀሳቀስበት የቆየው የለውጥ መዋቅር በአዲስ አበባ ሀገረስብከት አስተዳዳሪዎችና ሌሎች አገልጋዮች የተደራጀ ትግል መቀልበሱ ተሰማ፡፡ በዛሬው ዕለት (23/4/2006ዓ.ም) ፓትርያርኩና ስምንት ያህል ጳጳሳት በተገኙበት ወደ 300 የሚጠጉ የደብር አስተዳዳሪዎችና ልዩ ልዩ አገልጋዮች ቀርበው ቀደም ሲል ያቀረቡት አቤቱታተቸው የት እንደደረሰ በጠየቁበት ስብሰባ ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደገለጹት፣ ማኅበረ ቅዱሳን ያረቀቀው የለውጥ መዋቅር ውድቅ እንዲደረግና የማኅበሩ አባላት ቀርቶ ከማኅበሩ ጋር ምንም ንክኪ የሌላቸው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ አባቶችና ምሁራን በድምሩ 9 አባላቱ ያሉበት ኮሚቴ በቋሚ ሲኖዶስ ተሠይሟል ብለዋል፡፡ አክለውም ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብቻ ሳይሆን ለቤተክርስቲያኗ በአጠቃላይ የሚሠራ ህግ ነው መውጣት ያለበት ብለዋል፡፡ ለተሠየሙት አባላትም ከጠቅላይ ቤተክህነት ደብዳቤ የደረሳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡